ሥርዓተ አምልኮ

በዓላት ከማንኛውም ቀናት የበለጠ አምላካችን እግዚአብሔርን የምናመሰገንባቸውና የምናወድስባቸው፣ የተቀደሱትን ዕለታት በማሰብና በመዘከር በዝማሬ፣ በሽብሻቦና በእልልታ የምናከብርባቸው ናቸው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው የሚወጡባቸውና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚባርኩባቸው ስለሆኑም በክብርና በድምቀት ይከበራሉ፡፡   

“ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” (ሥርዓተ ቅዳሴ)

ምሥራቅ የቃሉ ፍቺ “የፀሐይ መውጫ” ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፮፻፹) በሥርዓተ ቅዳሴ ላይ ዲያቆኑ “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” በማለት በዜማ ለምእመናኑ ያውጃል፤ በእርግጥ በቅዳሴ ጊዜ በመካከል የሚያነቃቁና የአለንበትን ቦታ እንድናስተውል የሚያደርጉ ሌሎች ዐዋጆች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል “እለ ትነብሩ ተንሥኡ፤ የተቀመጣችሁ ተነሡ” የሚለው ነው፡፡ በቅዳሴ ጊዜ ከታመመ ከአረጋዊ በቀር ማን ማንም አይቀመጥም፡፡ ሰው እያስቀደሰ እየጸለየ ልቡናው ሌላ ቦታ ይሆንበታል፤ ይባዝናል፤ ያለበትን ትቶ በሌላ ዓለም ይባዝናል፡፡ አንዳንዴ ጸሎት እየጸለይን ሐሳባችን ሊበታተን ይችላል፡፡ ከየት ጀምረን የት እንዳቆምንም ይጠፋብናል፤ መጀመራችን እንጂ እንዴት እንደጨረስነውም ሳናውቀው ጨርሰን እናገኘዋለን፤ ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ “የተቀመጣችሁ ተነሡ” ማለቱ “የቆማችሁ በማን ፊት እንደሆነ አስታውሉ” ሲል ነው፡፡

እንዲሁም “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ሲባል ምን ማለት ነው? ዲያቆኑስ ምን እንድናደርግ ነው ያዘዘን? የሚለውን በመቀጠል እናያልን።

ጾመ ፍልሰታ

አምላክን የወለደች እመቤታችን ድንግል ማርያም ከዕረፍቷ በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው፤ እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው፡፡

ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር ዐሥራ ስድተኛ ቀን ተድላ ደስታ ወደአለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ፡፡ የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ዘንድ ተቀምጦ አየው፡፡ የንጽሕት እናቱንም ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፤ እነርሱም ”የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል‘ አሏት፡፡ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡…

ጥምቀት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትሆን፣ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደው መንግሥተ ሰማያት እንዲገቡ  እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመሆን በጥር ዐሥራ አንድ ቀን ተጠምቋልና ይህችን የተከበረች ቀን ሕዝበ ክርስቲያን ያከብር ዘንድ ይገባል፡፡

ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሊጠብቁ ይገባል!

ማኅበረ ምእመናን የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ  ብዙ ቢሆኑም እንኳን አንድ ልብና አንድ ሐሳብ ሆነው እንዲጸልዩ፣ እንዲሰግዱ፣ እንዲያመሰግኑ፣ እንዲያስቀድሱ፣ እንዲቆርቡ እንዲሁም እንዲዘምሩ ለማድረግ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ካህናት ሲቀድሱ ምእመናን በኅበረት ተሰጥኦ ይቀበላሉ፤ በጋራ ሆነው ይጸልያሉ፤ በዓላትን በአንድነት ያከብራሉ፤ በሰንበት ጽዋ ማኅበር በአንድነት ያዘጋጃሉ፤ ቅዱሳንን በጋር ይዘክራሉ፡፡

ነገር ግን ይህን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚጻረሩ ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በድፍረት ሲገቡ መመልከት ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ለምሳሌ የቅዳሴ ሥርዓትን አቋርጦ  መግባትና መውጣት፣ በትምህርተ ወንጌልም፣ በቅዳሴ እንዲሁም በሌሎች የጸሎት ሰዓታት ላይ ማውራት፣ ሥርዓት የሌለው አልባሳት በተለይም ሴቶቸ (አጭር እና ሰውነትን የሚያሳይ ልብስ) መልበስ…

በዓለ ሢመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ‹ሚካኤል ሥዩም በዲበ ኃይላት፤ በኃይላት ላይ የተሾምክ ሚካኤል› ሲል ያመሰገነው ቅዱስ ሚካኤል በኃይላት መላእክት ላይ የተሾመ ሊቀ መላእክት እንደመሆኑ በዓለ ሢመቱ ኅዳር ፲፪ ቀን በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡

«ስለ ሰላም ጸልዩ» (ሥርዓተ ቅዳሴ)

ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ እጅጉን ከሚያስፈልገን ነገር ዋነኛው ሰላም ነው፡፡ ያለ ሰላም መኖር አይቻልንም፡፡ ሰላም የተረበሹትን ያረጋጋል፤ ያዘኑትን ያጽናናል፤ ጦርነትን ወደ ዕርቅ ይለውጣል፡፡

ባሕረ ሀሳብ

የእስክንድርያ ዐሥራ ሁለተኛ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ ባሕረ ሀሳብን ሲደርሰው የቤተ ክርስቲያን ዕውቀት ያልነበረው በግብርና ሥራ የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ ሆኖም ለዘመናት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሥርዓት የተመራችበትን የዘመን አቆጣጣር በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ሊደርሰው ችሏል፤ ታሪኩም እንዲህ ነበር፡፡

‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮)

በዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት በእለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በቤተ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ ይህን ባለመውደዱም የገመድ ጅራፍ ካበጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)

‹‹እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፫፥፩)

                                                                                                 ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ 

ጸናጽል ድምፁ መልካም የሆነ የምስጋና መሳርያ በመሆኑ ከቀደሙት ሌዋውያን አሁን እስካሉት የሐዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ መዘምራን ፣ ከቀደመው የሙሴ ድንኳን ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነው የምንቆመው መሳርያ ነው፡፡ ምስጋናችንም ሆነ መዝሙራችን ያለከበሮና ጸናጽል ምን ውበት ሊኖረው ይችላል ብለን እንጀምራለን? አንጀምረውም፡፡ የሊቃውንቱ መዳፍ ያለ ጸናጽል አይንቀሳቀስም፣ ቅኔ ማኅሌቱም ያለ ከበሮ አይደምቅም ፤ እንደ ጾመ ኢየሱስ ያለ ቀን ካልገጠመው በስተቀር ቅኔ ማኅሌት ከነዚህ  ነገሮች አይለይም፤ ይገርማል! ዳሩ ግን አንድም ቀን ቢሆን በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ለሥጋውና ለደሙ ክብር በሚደረገው አገልግሎት ተሳትፈው አይተናቸው አናውቅም፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ አገልግሎታቸው ከውጭ ብቻ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ የባዶ ሕይወት ተምሳሌት አድርጎ ተጠቅሞበታል፤ “የሰውን ሁሉ ልሳን ባውቅ፣ በመላእክትም ቋንቋ ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ነሐስ፤ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ነኝ” (፩ቆሮ ፲፫÷፩) ይላል፡፡ ይህን ስመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ መቅደሱ ያደገች ነፍሴን አሰብኩና እስራኤል ሲማረኩ “ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን” ብለው እንደተናገሩ እኔም ለተማረከችውና ባዶዋን ለቀረችው ጽዮን ሰውነቴ አለቀስኩላት፤ ከኔ በቀር ጽዮን ሰውነቴ ባለተስፋ ምድር መሆኗን ማን ያውቅላታል? የተገባላትንስ ቃል ኪዳን ከኔ በቀር ማን ያውቅላታል?

ስለዚህ ደጋግሜ በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሆኜ ምርር ብየ አለቀስኩላት፤ ደግሜ ደጋግሜም እንዲህ አልኳት፤ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደ ሚንሿሿም  ጸናጽል ነሽ አልኳት፡፡ እስኪ አስቡት! ያለኔ ማኅሌቱ አይጀመር፣ ዝማሬው አይደምቅ ፣ የሊቃውንቱ ጉሮሮ አይከፈት፣ ሽብሻቧቸው አያምርበት ፣ እጃቸው ያለኔ አይንቀሳቀስ፣ ቅኔው አይጸፋ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! ምኑ ነው ያለኔ የሚያምረው፤ በየትኛው አገልግሎት ነው እኔ የማልገባው፤ የትኛውስ ሊቅ ነው ያለኔ በእግዚአብሔር ምስጋና ላይ የተገኘው ፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ እኔ ለዚች ቤተ መቅደስ አገልግሎት አስፈልጋለሁ ፡፡

ያለበለዚያማ ማኅሌቱ ምን ውበት ሊኖረው፤ ማንስ ነው እኔ በሌለሁበት ያለ እንቅልፍ የሚያገለግለው፤ ከከበሮው ተስማምቶ በሚወጣው መልካሙ ድምፄ ብዙዎቹ ይመሰጣሉ፣ የድምፄን ውበት በውስጠኛው ጆሯቸው እየሰሙ እንዲህ አሳምሮ የፈጠረኝን “ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑ” እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ የድምፄን መልካምነት ብቻ እየተመለከቱ ወይ መታደል ብለው ያደንቃሉ፤ እኔ እስከማዜም ድረስ በጉጉት ይጠባባቃሉ ፤ሰው ሲዳር፤  ሲሞትም ሆነ ሲሾም ያለኔ ምኑ ያምራል፤ አምጡት፣ አምጡት ይባላል፡፡

ይህን ሁሉ ክብሬን አየሁና በሰዎች መካከል በኩራት ተቀምጨ ሳለሁ ከዕለታት አንድ ቀን የሥጋየን መጋረጃ ግልጥ አደረግሁና ነፍሴን ተመለከትኋት፤ ትጮኻለች! አዳመጥኳት፤ ላደርገው የሚገባኝን እንኳን ያለደረግሁ፤ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፡፡ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ እያለች ታንጎራጉራለች፡፡

የሚጎሰመው ነጋሪት፣ የሚመታው ከበሮ፣ የሚንሿሿው ጸናጽል ለራሳቸው ምን ተጠቅመዋል? ከነሱ በኋላ እየተነሣ ስንት ትውልድ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሰ፣ ከተስፋው  የደረሰ፤ ሌላው በነሱ ተጠቅሞ አድማሳትን በቅድስናው ሲያካልል፣ መላእክትን ሲያክል፤ እነሱ ግን አሁንም ምድራውያን ናቸው፡፡ በዚህኛው ትውልድም አልተለወጡም፤ ጌታ እስኪመጣ ከዚህ ዓይነት ሕይወት የሚወጡም አይመስሉም፤

እኔም እንደነሱ ነኝ! ቃሉን እሰብካለሁ፣ ዝማሬውን እዘምራለሁ፣መወድሱን እቀኛለሁ፣ሰዓታቱን አቆማለሁ፤ ኪዳኑን አደርሳለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከዳር አንብቤአለሁ፡፡ ዳሩ ግን መች እኖርበታለሁ ፤ ሰዎቹ ከአፌ የሚወጣውን ቃሉን እየሰሙ የሕይወቴ ነጸብራቅ እየመሰላቸው ይገረማሉ፤ እንደኔ ለመሆን ይቀናሉ፤ እኔ ግን ሳላስበው እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡  እጮኻለሁ እንጅ  ለምን እንደምጮኽ እንኳን አላውቅም፤ በምጮኸው ጩኸት ከቶ አልለወጥም፤ ከኔ በኋላ እየተነሱ ብዙዎቹ ከምሥራቅና ከምዕራብ እየመጡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብተዋል ፤ ከኔ በኋላ ቃሉን የሰሙት በቃሉ ተለውጠው ንስሓ ገብተዋል፡፡ እኔ ግን ዛሬም ሳያውቅ እንደሚጮሕ ነሐስ፣ ሳይወድ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡

የምጮኸው ገብቶኝ ቢሆንኮ ከኔ የሚቀድም ማንም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ሕይወት የሌለኝ ቆርቆሮ ነኝ፤ ድምፄ መልካም ነው፣ ትጋቴ ግሩም ነው፡፡ ከምስጋናው ጋር መስማማቴ፣ በሁሉም እጅ መግባቴ መልካም ነበር፤ ሆኖም ፍቅር የለኝምና ምን ይሆናል፡፡  ሥጋየን ለሰማይ አዕዋፍ ብሰጥ ፣ያለኝንም ለድሆች ባካፍል ፣ የድሆች አባት ብባል ፣አጥንቴም እስኪታይ ብጾም ብጸልይ ፍቅር ግን ከሌለኝ ያው እንደሚጮኸው ነሐስ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል መሆኔ አይደለ? ሥጋውን ደሙን ካልተቀበልኩ የኔ መጮኽ ምን ሊጠቅም ! ለካ ለሥጋውና ለደሙ የሚያስፈልገው በበጎ ዝምታ ዝም ያላለው እንደኔ የሚንሿሿው ጸናጽል አይደለም ብላ ነፍሴ ስታለቅስ እኔንም አስለቀሰችኝ ፡፡

ኦ!አምላኬ ጸናጽልነቴን ለውጥልኝ፣ነሐስነቴን አርቅልኝ!