ሰኔ15 ፣2003 ዓ.ም
ከእመቤት ፈለገ
በእስራኤል ሀገር ውስጥ አክዓብ የሚባል ንጉሥ ነበር፡፡ ንጉሡም በዓል የሚባል ጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን አሳዘነው፡፡ በዚሁ ሀገር ውስጥ የሚገኝ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የሚፈጽም ኤልያስ የሚባል ነቢይ ነበር፡፡ ንጉሡና ሕዝቦቹ እግዚአብሔርን እንዳስቀየሙት ባየ ጊዜ ዝናብ እንዳይዘንብ ጸለየ፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረም፡፡ ከብዙ ቀንም በኋላ በሦስተኛው ዓመት “አክዓብ ጋር ሂድ በምድር ላይም ዝናብ እሰጣለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ለኤልያስ ነገረው፡፡ በአገሪቱም ውስጥ ከፍተኛ ረሃብ ሆኖ ነበር፡፡
አብድዩ የሚባል እግዚአብሔርን የሚፈራ የንጉሡ አገልጋይ ነበር በመንገድ ሲሄድ ነቢዩ ኤልያስን አገኘው፡፡ አብድዮም ሮጠና የአክብሮት ስግደት ሰገደለት፡፡
ነቢዩ ኤልያስም “ሂድና ለጌታህ ኤልያስ እዚህ አለልህ” ብለህ ንገረው አለው፡፡ አብድዩም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ አክአብም ነብዩ ኤልያስን እንዳገኘው “አስራኤልን የምትበጠብጠው አንተ ነህ” አለው ይህንን ያለበትም ምክንያት ዝናብ ለረጅም ጊዜ ስላልነበረ ነው፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ዝናብ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ እስራኤልን ሲበጠብጧት የነበሩት ግን ሕዝቦቹና ንጉሡ ነበሩ ምክንያቱም እግዚአብሔርን ክደው ሌላ አምላክ /ጣዖት/ ማምለክ ጀምረው ነበር፡፡
ነቢዩ ኤልያስ አክአብን አራት መቶ ሃምሳ የጣዖቱን /የበአልን/ ነቢያትን እንዲጠራቸው ለንጉሡ ነገረውና በአንድ ላይ ተሰበሰቡ፡፡ ከዚያም ነቢዩ ኤልያስ እንዲህ አላቸው “ከእግዚአብሔር ነቢያት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነኝ፣ በእናንተ በኩል ግን አራት መቶ ሃምሳ ነቢያት አሉ፡፡ አንድ በሬ ውሰዱ አርዳችሁም በእንጨት ላይ አስቀምጡትና አምላካችሁን እየጠራችሁ ጸሎት አድርጉ እሳት አታንዱበት ከሰማይ አምላካችሁ እሳት አውርዶ ያዘጋጃችሁትን ነገር ከበላው እኔ በእናንተ አምላክ አምናለሁ፡፡ ይሄ ካልሆነና እኔ በአምላኬ በእግዚአብሔር ስም ጸልዬ ያዘጋጀሁትን እሳት ከሰማይ ወርዶ ከበላው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ አላቸው፡፡ ሁሉም ሰው ተስማማ፡፡
በአልን ያመልኩ የነበሩት 450 የሐሰት ነብያት ቀኑን ሙሉ ቢጸልዩ ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡
ነቢዩ ኤያልስ እሳት ከሰማይ ወርዶ እርሱ ያስቀመጠውን እንዲወስደው ብዙ ውሃ አደረገበት፡፡ ልጆች እንደምታውቁት ውሃ እሳትን ያጠፋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸሎት አደረገ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህንና እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ሆይ እባክህ ስማኝ ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ እንጨቱን፣ ድንጋዩን፣ ዐፈሩን፣ ፈጽማ በላች በጉድጓድ ውስጥ ያለውን ውሃ ላሰች፡፡
ሕዝብም ሁሉ ይህን ሲያይ በግንባራቸው ተደፍተው አምላከ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው አሉ፡፡
አያችሁ ልጆች እግዚአብሔር በጣም ኃያል አምላክ ነው፡፡ እኛም የእርሱ ትእዛዛት የምንፈጽም ከሆነ ለእኛም ጥሩ ነገሮችን ማድረግ እንድንችልኃይል ይሰጠናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር