የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – የመጨረሻ ክፍል
የጽድቅ ሥራ እና የኀጢአት ተግባር በአንድ ልብ አመንጪነት ይፈጸማሉ፡፡ ልዩነቱ ጻድቃን ልቡናቸውን መልካም ነገርን ሲያሳስቡት፤ ኃጥኣን ደግሞ ለክፉ ነገር ማዋላችን ነው፡፡ “ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፤ ክፉ ሰው ግን ከክፉ ልቡ መዝብ ክፉ ነገርን ያወጣል፤” እንዲል (ማቴ. ፲፪፥፴፭)፡፡ በዚህ ዓለም እግዚአብሔርን የሚያስረሱን ሥጋውያን ተግባራት ብዙ ቢኾኑም፣ በአንጻሩ ደግሞ ፈቃደ ሥጋችንን በማሸነፍ ሕግጋቱን ጠብቀን ለመኖር የምንችልባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ጣዖት በሚመለክበት አካባቢ ቤተ ክርስቲያን እናገኛለን፤ ዓለማዊ ጫጫታ በሚበዛበት ቦታ ቅዳሴ እንሰማለን፡፡ እንግዲህ ለሥጋችን ነጻነት፣ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅመንን መምረጥ የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ስለኾነም “እሺ ብትሉ፣ ለእኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ” እንደ ተባልነው (ኢሳ. ፩፥፲፱) እንደ ዝሙት ያሉ አስነዋሪ ተግባራትን ከሚያስፈጽመን ሰይጣን ሸሽተን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ልንከተል ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ መላው ምእመናን በተለይ እሳታዊ ባሕርይ የሚበረታብን ወጣቶች በምድር በልዩ ልዩ ደዌያት እንዳንያዝ፣ በሰማይም በገሃነመ እሳት እንዳንጣል ከዝሙት ሥራ ዂሉ ራሳችንን በመጠበቅ በተቀደሰው ጋብቻ ልንወሰን ያስፈልገናል፡፡ ከዝሙት ኀጢአት ነጻ ለመኾንም ፈሪሃ እግዚአብሔርን ገንዘብ ማድረግ፤ ሥጋን በጸሎት፣ በጾምና በስግደት እንደዚሁም በሥራ ማድከም፤ በስሜት አለመነዳት፤ ራስን ከስሜታዊነት መጠበቅ፤ ከዚህም ባሻገር ሞተ ወልደ እግዚአብሔርንና የቅዱሳንን ተጋድሎ ማስታወስ ዋነኛ መፍትሔዎች ናቸው፡፡