ክርስቲያናዊ ሕይወት
መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ
-
“ለማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ መካነ ድር ዝግጅት ክፍል፡፡ መንፈሳዊ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ እባካችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝን ምክር ለግሱኝ?”
ውብ አንተ
የተከበርክ ወንድማችን ውብ አንተ ክርስቲያናዊ ሕይወትህ እንዲበረታ መንፈሳዊ ምክር ፈልገህ ስለጻፍክልን እናመሰግናለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ይህ ነው ወይም ያ ነው ብሎ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜና ቦታ ይገድበናል፡፡
ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝ ምክር እፈልጋለሁ የሚለውን ዐሳብህን ብቻ ነጥሎ ማየት አሁን ያለህበትን የሕይወት ደረጃ ብናውቀው ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብለህ በክርስቶስ ክርስቲያን እንደተባልክ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም እንደ ክርስቲያን መኖር ያለብህን ሕይወት ስላልኖርክ በውስጥህ የሚወቅስህ ነገር አለ፡፡ ይህ ወቃሽ ኅሊና በልቡናህ ስለተሳለ እግዚአብሔርን አመስግነው፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የሚጸጸት፣ የሚጨነቅ የሚተክዝ ልቡና ያለው ሰው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያልተለየው ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲመሰክር እንዲህ አለ “…መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይናገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” ሮሜ.8፥26-27