የአዲስ አበባ ማእከል 500 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መመረቃቸውን ገለጸ።
በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ዋና ክፍል ቅዱስ ገብርኤል ማስተባበሪያ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ሲያስተምራቸው የነበሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በደብረ ጽጌ ፋንታ ቅድስት አርሴማ ወቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ማስመረቁን የማስተባበሪያው ኃላፊ አቶ ተሾመ ሙሉጌታ ገለጸዋል።
በዕለቱም ትምህርተ ወንጌል በመጋቤ ሐዲስ መምህር ጥላሁን ታዬ ፣መዝሙርና ወረብ በተመራቂ ተማሪዎች የቀረበ ሲሆን የደብሩ አስተዳዳሪና ካህናት ፣የማእከሉ ሰብሳቢና የማእከሉ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ሰብሳቢ ዲ/ን ኃይለ ማርያም መድኅን እንኳን አደረሳችሁ በማለት የማኅበሩን መልእክት ያስተላለፋ ሲሆን በመልእክታቸውም በብዙ ውጣ ውረድ አልፋችሁ ለዚህ ለምረቃ ዕለት በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ እያልን በቀጣይ ጉዟችሁ ቤተሰብን፣ ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን እንድታገለግሉ አደራ እንላለን በማለት ለተመራቂዎች አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች የዕውቅናና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለሁሉም የግቢ ጉባኤው ተመራቂዎች የአደራ መስቀል ተሰጥቷል።
ዘገባው በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ነው።
