“ሕያው ዜማከ ወሕያው ድርሳንከ” በሚል መሪ ቃል የዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብር እንደሚከናወን የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል አስታወቀ
ግንቦት ፲፪/፳፻፲፰ ዓ.ም
በማኅበረ ቅዱሳን የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል “ሕያው ዜማከ ወሕያው ድርሳንከ” በሚል መሪ ቃል የዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብር በዋናው ማእከል፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ማእከላት፣ በወረዳ ማእከላት እንዲሁም በግቢ ጉባኤያት እንደሚከናወን አስታውቋል።
ማኅበረ ቅዱሳን ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዝሙራትን፣ የዜማ መሣሪያዎችንና ኪነ ጥበባትን በተመለከተ የተለያዩ መርሐ ግብራትን፣ ዐውደ ጥናቶችን በማድረግ ሥርዐታቸው እንዲከበርና ምእመናን አገልግሎታቸውን እንዲረዱ ማድረግ ሲሆን አንዱ የዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብርን ማከናወን ነው በማለት የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል ገልጿል።
በዚህም መርሐ ግብሩ የሚከናወነው ዝክረ ቅዱስ ያሬድ ለኦርቶዶክሳዊ መዝሙር፣ ለመንፈሳዊ ኪነ ጥበብ፣ ለአስተምሮዋም መሠረት ስለሆነ የእርሱን ሕይወቱን፣ ሥራዎቹን በማውሳትና አርአያ እንዲሆን በማድረግ እንዲሁም ምእመናን እንዲያውቁትና ሥርዐቱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ መሆኑም ተገልጿል።
ቅዱስ ያሬድ የተሰወረበት ዕለት ግንቦት 11 ስለሆነ ሙሉ የግንቦት ወር በማእከላት፣ በወረዳ ማእከላትና በግቢ ጉባኤያት የተለያዩ ጉባኤ በማድረግ የሚከበር ሲሆን የዋናው ማእከልም ከአዲስ አበባ ማእከል ጋር በመሆን እንደሚያከብር ተጠቅሷል።
በማያያዝ እንደ ዋናው ማእከል የዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብር መከናወን ከተጀመረ ከ10 ዓመት በላይ እንደሆነው የገለጸው የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል አክሎም በዘንድሮው ዓመትም ሁለቴ የሚያከብር ሲሆን የመጀመሪያው የፊታችን እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጠዋት ከቅዳሴ በኋላ ከሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም እና ከሰዓት ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ ከጉለሌ አምባ ደብረ መድኃኒት ቅድስት ኪዳነ ምሕረትና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ጋር በመተባበር በዐውደ ምሕረት ይከበራል፤ ሁለተኛው ደግሞ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ላይ እንደያሚከብር ተገልጿል።
በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ያሉ ጥሪ የሚደረግላቸው መምህራን፣ ዘማሪያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች፣ የማኅበሩ አባላትና ምእመናን እንደሚገኙ የገለጸው የዜማና ኪነ ጥበባት ማእከል አያይዞም ሁሉም እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።
