በማኅበረ ቅዱሳን ወሊሶ ማእከል ያስተማራቸውን ዲያቆናት ማዕረገ ቅስና እንዲቀበሉ በማድረግ አስመረቀ
በማኅበረ ቅዱሳን ወሊሶማእከልያስተማራቸውንዲያቆናትማዕረገቅስናእንዲቀበሉበማድረግአስመረቀ
ግንቦት ፲፩/፳፻፲፰ ዓ.ም
በማኅበረ ቅዱሳን ወሊሶ ማእከል ላለፉት ሦስት ወራት በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር ከሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎች የተወጣጡ 17 ዲያቆናትን ሲያሠለጥን የቆየ ሲሆን ከሠልጣኞቹ መካከል 8 ደቀ መዛሙርት ማዕረገ ቅስና እንዲቀበሉ በማድረግ የተቀሩት ደግሞ ተጨማሪ የአቅም ማጎልበቻ ትምህርቶችን እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል።
ደቀ መዛሙርቱ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሸገር ሀገረ ስብከት በአጃምባ ደብረ ብርሃን አቡነ ተ/ሃይማኖት ቤተ ክርስተያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ፣ የሸገር አህጉረ ስብከት እና የምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ማዕረገ ቅስና ተቀብለዋል።
በማኅበረ ቅዱሳን የወሊሶ ማእከል ሰብሳቢ አቶ ንጉሤ አብዴቾ እንደተናገሩት የወሊሶ ማእከል በሀገረ ስብከቱ ያለውን የአገልጋይ እጥረት ለመፍታት ለመምህራን እና ለደቀ መዛሙርት ወርኃዊ ድጎማ በማድረግ ፣ ንዋያተ ቅዱሳትን ጨምሮ የመማርያ መጻሕፍትን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመደገፍ በርካታ ዲያቆናትን ማፍራት የተቻለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም በሀገረ ስብከቱ ሦስት ወረዳዎች በሚገኙ ሦስት አጥቢያዎች ከ85 በላይ ዲያቆናትን እያስተማረ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
የወሊሶ ማእከል በሀገረ ስብከቱ ስላለው የአገልጋይ እጥረት የዳሰሳ ጥናት በማድረግ መደበኛ አገልጋይ ከሌላቸው አጥቢያዎች አምስት ደቀ መዛሙርትን እንዲሁም አንድ ካህን ብቻ ካላቸው ሦስት ደቀ መዛሙርትን በመውሰድ የክህነት አገልግሎት እና የትምህርተ ሃይማኖት ኮርሶችን ሲወስዱ ከቆዩ በኋላ ማዕረገ ቅስና እንዲያገኙ መደረጉ ተገልጿል።
ተከታታይ ትምህርት በማስተማር ዲያቆናትን ከዲቁና ወደ ቅስና ያሳደገው ወሊሶ ማእከል ይህን እና ሌሎች አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ፈተናዎች እንደገጠሙትም ለማወቅ ተችሏል። በሀገረ ስብከቱ የአገልጋይ እጥረት ያለባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች ያሉባቸው፣ ከወረዳ ከተሞችም የራቁ በመሆናቸው በተፈለገው ጊዜ መድረስ እና መረጃ መሰብሰብ አለመቻሉ፣ ወደ ቅስና ገብተው ቤተ ክርስተያንን ማገልገል የሚችሉ ፍላጎት ያላቸው ደቀ መዛሙርትን ማግኘት አለመቻል እና የምልመላ መሥፈርቶችን የሚያሟሉ ደቀ መዛሙርት ቁጥር ማነስ ማእከሉ አገልግሎቱን በተፈለገው ደረጃ ለማዳረስ ፈተና ሆነው መቆየታቸው ተነግሯል።
አገልጋዮቹ ከዚህ ቀደም ለዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በዲቁና ሲያገለግሉ የነበረ እና የተዘጋጀውን የምልመላ መስፈርት ያሟሉ ስለሆነ ወደየ አካባቢያቸው ሲመለሱ የተሟላ የቅስና አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ባለፉት ሦስት ወራት በተሰጠው ሥልጠና የዋናው ማእከልን ድጋፍ ጨምሮ በአጠቃላይ የወሊሶ ማእከል ከአራት መቶ ሺ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከማእከሉ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
