በዓለ ጥምቀት
ጥር፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
በጥር ዐሥራ ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ በዮርዳኖስ ወንዝ ውኃ ተጠመቀ።
ይችህም ዕለት በዮናኒ ቋንቋ ኤጲፋንያ ትባላለች፤ ትርጓሜውም “መለኮት የተገለጠበት ማለት ነው።” ልዩ የሆነች የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦባታልና አብ ከሰማይ ሆኖ “የምወደው በርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” እያለ ሲመሰክር ወልድም በዮርዳኖስ ወንዝ ቁሞ ሳለ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል በወልድ ራስ ላይ ሲቀመጥ ይህ አጥማቂው ዮሐንስ እንደመሰከረ።
እንዲህ ሲል “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከውኃ በወጣ ጊዜ ወዲያውኑ ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በጌታችን ራስ ላይ ተቀመጠ፤ ከሰማይም እንዲህ የሚል ቃል መጣ፤ “ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ነው፤ እርሱንም ስሙት።”
በዚች ዕለት ጌታችን ራሱን ገልጦአልና ከዚህ በፊት ሠላሳ ዓመት ያህል ራሱን አልገለጠም ነበር፤ ግን በዚች ዕለት ለእስራኤል ልጆች ራሱን ገለጠ፤ “እነሆ የእግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ” ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ እንደገለጠው የከበረ ወንጌል ምስክር ሆነ።
“እኔ አላውቀውም ነበር፤ ነገር ግን እስራኤል ያውቁት ዘንድ በውኃ ላጠምቅ ስለዚህ መጣሁ” አለ። በዚህም በዓል የእግዚአብሔር ልጅ የክርስቶስ የጌትነቱ ክብር ተገልጧል፤ እርሱም የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት ለማስወገድ የሚሰዋ የእግዚአብሔር አማናዊ በግ ነው።
ስለዚህም ይህ በዓል በክርስቲያን ወገኖች ሁሉ ዘንድ የከበረና ከፍ ከፍ ያለ ሆነ በርሱም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ በአከበረው ውኃ ይነጹበታል፤ የተቀበሉትንም ንጽሕና ጠብቀው ቢኖሩ በውስጡ የኃጢአታቸውን ሥርየት ያገኛሉ።
ስለዚህም ከክፉ ነገር ሁሉ ተጠብቀን የፈጣሪያችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነቱን ብዛት ልናመሰግን ይገባናል፤ እርሱ ስለ እኛ ሰው ሆኖ ከኃጢአታችን አድኖናልና።
ለእርሱም ከቸር አባቱ ሕይወት ከሆነ መንፈስ ቅዱስም ጋር ክብር ምስጋና ስግደትም ይሁን፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!
መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጥር፣ ፲፩
