‹‹እኔ ሰላማዊ ነኝ!›› (መዝ.፻፲፱፥፯)
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፳፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ሰላም “ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ ዕርቅ፣ ፍቅር፣ አንድነት” ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፰፻፷፮) አንድ ሰው ሰላም አለው ሲባል ጤነኛ እና ለሰዎች ፍቅር ያለው ኅብረትን አንድነትን የሚወድ ማለት ነው፡፡ ሰላም ለሰዎች ሁሉ አስፈላጊና መሠረታዊ ከሆኑ ነገሮችም አንዱ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ለማከናወን ቅድሚያ ሰላም መሆን አስፈላጊ ነው፤ በሕይወታችን ደስተኛ ሆነን ለመኖር፣ አእምሮአችንን ከጭንቀት ነጻ ለማድረግ፣ ለሰዎች መልካም ነገርን ለማሰብ እኛም ደስተኛ እና ጤነኛ ለመሆን ሰላማዊ መሆን አለብን፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ እንዲህ ይመክረናል፤ ‹‹…ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ…፡፡›› (ሮሜ ፲፪፥፲፰) ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር እኛ የሰላም ሰዎች ነገሮችን በትዕግሥት የምናልፍ፣ ለሰዎች መልካም የምናስብ ልንሆን ይገባል፡፡
ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው?! ለመግቢያ ያህል ሰላም ስለሚለው ኃይለ ቃል ገለጽን እንጂ ርእሰ ጉዳዩን የመረጥነው ስለ ሰላም ምንነት በስፋት ለማብራራት አይደለም፤ ሰላማዊ ሰው ስለመሆን እንጂ! በርእሳችን ላይ ‹‹እንዘ ሰላማዊ አነ፤ እኔ ሰላማዊ ነኝ›› የሚለውን ኃይለ ቃል የተናረው ልብ አምላክ ንጉሥ ዳዊት ነው፤ መተርጉማን አበው ነቢዩ ንጉሥ ዳዊት ይህንን ደስ የሚል ከመንፈስ ፍሬዎች መካከል አንዱ የሆነውን ቃል፤ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት›› (ገላ.፭፥፳፪) መናገሩ ለምን እንደሆነ ሲያመሠጥሩ ከሕይወት ታሪኩ ክፍል አንዱን ይተርካሉ፤ ነገሩ እንዲህ ነው!
ንጉሥ ዳዊት በነቢዩ ሳሙኤል አማካኝነት ተቀብቶ ከነገሠ በኋላ ጎልያድን በመግደሉ በሕዝቡ ዘንድ ባገኘው ከበሬታ ምክንያት ንጉሥ ሳኦል ሊገድለው ተነሣ፤ ብላቴናው ነቢይ ዳዊትም ከሳኦል ፊት ሸሽቶ ሄደ፤ በቀርሜሎስም ከባለሟሎቹ ጋር ተቀመጠ፡፡ በዚያም ናባል የሚባል ሰው ነበር፤ ሚስቱም አቢግያ ትባላለች ዳዊት በዚያ ስፈራ በመኖሩ የአካባቢውን ሰዎች ንብረት በሽፍቶች (በቀማኞች) እንዳይወሰድ ከለላም ሆነ፤ ዳዊትም የሚገባውን ግብር እንዲያገባ ለናባል መልእክተኞችን ላከ፤ ናባል ግን ከስጦታው ይልቅ ስድብንም ጨምሮ የእንቢታን ምላሽ ሰጠ፡፡ ንጉሥ ዳዊት በዚህ ተቆጥቶ ናባልና የእርሱ የሆኑትን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ወሰነ፤ ይህንን ነገር የናባል ሚስት አቢግያ ሰማች፤ ከዚያም የሚገባውን እጅ መንሻ ይዛ ወደ ንጉሥ ዳዊት ገሰገሰች፤ ከእግሩም ሥር በግንባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች፤ ሊወስድ የመጣውን ርምጃ (ቅጣት) እንዳይፈጽም እንዲህ አለችው ‹‹…ወደ ደም እንዳትገባ አጅህም ራስህን እንዳታድን የከለከለህ እግዚአብሔር ነው …›› (፩ኛ ሳሙ. ፳፭፥፳፮) እጅ መንሻውንም ሰጠች፤ ንጉሥ ዳዊትም የሰላም ሰው ነውና የአቢግያን የሰላም መልእክት ተቀብሎ ከጸብ ይልቅ ሰላምን፣ ከበቅል ይልቅ ይቅርታን መረጠ እንዲህም ሲል አመሰገነና ‹‹…ዛሬ እኔን ለመገናኘት አንቺን የሰደደ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ወደ ደም እንዳልሄድ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አእምሮሽ የተመሰገነ ይሁን አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ…›› አላት፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፳፭፥፳፮) የሰላም ሰው ንጉሥ ዳዊት ስለ መልካምነቱ፣ ስለ ይቅርታው በትዕቢት የተገዳደረው ናባል ግን ተቀሥፎ ሞተ፡፡
ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?! ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ዳዊት ለተበደለ ሊፈርድ የበደለን ሊቀጣ በእግዚአብሔር የተመረጠ የሕዝቡ መሪ ሆኖ ሳለ በትዕቢት የተገዳደረው ናባል ያስቆጣውን ልቡን ብልህና አስተዋይዋ አቢግያ በሰላማዊ ንግግሯ አበረደችው፡፡ ንጉሠ ዳዊት ሰላሙን ከይቅርታው አገኘው፤ የበቀል ጉዞውን በትዕግሥት ገታው፤ በአንድ ሰው ምክንያት ጉዳዩ የማይመለከታቸውን ከመቅጣት (ከማጥፋትና) ደስታውን ከሚነጥቅ፣ ዕረፍቱን ከሚነሣ፣ ፍቅርን ከሚያሳጣ፣ ጤናውን ከሚያቃውስ፣ ከጸጸት አዘቅት ከሚከት ከሰላም እጦት ራሱን ጠበቀ፡፡
ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው?! ሰላምን ፍለጋ ዘምረናል፤ ጸልየናል፤ እኛ ሰላማዊ ለመሆን ምን ያህል ጥረናል! “ሰላም አውለን” ብለን ከቤት ስንወጣ ሰላማዊ ለመሆን፣ ጥላቻን በፍቅር፣ በደልን በይቅርታ ለመለወጥ ምን ያህል ጥረናል?! ጤናችንን የሚያቃውስ፣ ፍቅራችንን የሚያደፈርስ፣ አንድነታችንን የሚበታትን ጥላቻን፤ ከልባችን አንግሠን፣ ሰላማችንን የሚያርቅ ሰብእናችንን የሚያጎድፍ፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት የሚለየንን ቂም አርግዘን ሰላምን እንዴት ማግኘት ይቻላል?! አምላካችን ጥላቻን በፍቅር፣ በደልን በይቅርታ ቀይሮ ሰላማችንን ሰጠን፤ ‹‹..ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላምን እሰጣችኋላሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም…›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፳፯)፤ ፈለጉን እንከተል እንመስለውም ዘንድ ‹‹ከእኔ ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና›› ብሎ ነገረን፤ በምግባራቸው ሊመስሉት የተከተሉት፣ መጠራታቸውን በመመረጥ መመረጣውን በመጽደቅ ያጸኑ ቅዱሳን አባቶቻችን የሰላምን ጥቅም በጥልቀት ተረድተው እኛም እንጠቀምበት ዘንድ እንዲህ ይመክሩናል!፤ ‹‹…በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ …፡፡›› (ሮሜ ፲፪፥፲፰)
ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?! ሰላም ከራሳችን ይጀምራል፡፡ እያንዳንዳችን ሰላማዊ ከሆንን ሰላማዊ ቤተሰብ ይኖረናል፤ ሰላማችን ከእኛም አልፎ ለጎረቤት፣ ከፍ ሲል ለከተማ ከዚያም ለአገርና ለዓለም ይተርፋል፤ ሰላም ከየትም አይገኝም፤ የሰላም መፍለቂያዋ ከቂም በቀል ከራቀ፣ ከጥላቻ ከጸዳ፣ ፍቅርን ካነገሠ፣ አንድነትን ከመረጠ ልባችን ነው፤ ለዚህም ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው ‹‹…አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና…›› በማለት የሚመክረን የሰላም መገኘዋ፣ የሕይወት መውጫ ከሆነ ልባችን ነውና፡፡ (ምሳ. ፬፥፳፫)
‹‹ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው ምላሱን ከክፉ፣ ከንፈሮቹንም ተንኮልን ከመናገር ይከልክል፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፤ መልካምንም ያድርግ፤ ሰላምን ይሻ ይከተላትም…፡፡›› (፩ኛ ጴጥ.፫፥፲፩፤መዝ.፴፫፥፲፬)
ውድ ክርስቲያኖች! የሰላም መገኛው የት ነው ?! ሰላምን ከፈለግናት ከራስ ወዳድነት እንለይ፤ ምክንያቱም ‹‹የዓለማችን ችግር ሁል ጊዜ ምንጩ ራስ ወዳድነት ነውና›› በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ ሁለት መነኮሳት ስለ ሰላም መደፍረስ፣ ስለጸብ መነሻ ምን እንደሆነ መጠያየቅ ጀመሩ፤ አንደኛው እንዲህ ሲል ጠየቀ! ‹‹ሰዎች ሰላማቸውን የሚያጡት፣ ፍቅራቸው የሚደፈርሰው በምን ምክንያት ነው?››! አንደኛው በምሳሌ ያስረዳው ዘንድ የያዘውን ዳዊት (የጸሎት) መጽሐፍ ተቀበለውና እንዲህ ያስረዳው ጀመር፤ ‹‹ይህ ዳዊት (የጸሎት መጽሐፍ) ያንተ ነው፤ እኔ ግን እነጥቅህና የእኔ ነው እልሃለው፤ አንተ ደግሞ የእኔ ነው ትላለህ፤ የዚህን ጊዜ በመካከላችን ጸብ ይጀመራል፤ ፍቅራችን ይጎረብጣል፤ ሰላማችን ይናጋል›› በማለት አስረዳው፤ በምሳሌም በተግባር ለማሳየት ብሎ የጓደኛውን ዳዊት (የጸሎት) መጽሐፍ ነጠቀውና ‹‹የእኔ ነው›› አለው፤ ያም የዋህ መነኩሴ ‹‹አይ የእኔ ነው፤ የአንተ አይደለም›› ማለት ሲገባው እርሱ ግን ‹‹እሺ የአንተ ነው፤ ውሰደው›› ብሎ የእራሱን የሆነ ዳዊት (የጸሎት መጽሐፍ) ተወለት! በመነኮሳት (በአባቶች) ዘንድ ፍቅር እንጂ ጸብ የለምና፤ የእኛ እንጂ የእኔ የሚባል ነገር የለምና! ሰላምን ከሌላ ሰው ከሩቅ ሳይሆን ከራሳቸን እንፈልጋት፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
