ተስፋ መቁረጥ የኅሊና ሞት!
ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ታኅሣሥ ፲፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ኅሊና የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ “የአፍአ፣ የውስጥ ሕዋስ፣ ረቂቅ፣ ውሳጣዊ፣ ተነሣሽ፣ ተንቀሣቃሽ” በማለት ይገልጡታል፤ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ ፬፻፸፯)
ኅሊና ጥሩና በጎውን፣ ትክክልና ስሕተቱን የሚለይ የአእምሮ ክፍል ነው፤ የራስ መመዘኛ፣ ክፉና በጎውን መለያ፣ የግላዊ ሂስ ማቀነባበሪያ፣ የነፍስ ክፍል በማለትም ይተነትኑታል፡፡ ኅሊና በጎውንና ክፉውን የምንለይበት መልካም ስንሠራ ሰላም፣ መረጋጋት እንዲሰማን፣ ስንበድልና ሕግ ስንተላለፍ ወቀሳን የሚያደርስብን ነው ፤ ‹‹..እነርሱም ይህንን ሲሰሙ ኅሊናቸው ወቀሳቸውና ከሽማግሌዎች ጀምሮ እስከ ኋለኛዎቹ አንድ አንድ እያሉ ወጡ ….›› (ዮሐ.፰፥፱) አበው ኅሊናን ‹‹እግዚአብሔር በሰው ልጅ ውስጥ ያስቀመጠው እውነተኛ ዳኛ ነው›› በማለትም ይገልጡታል፡፡ ዛሬ በዚህ መልእክታችን ማስገንዘብ የፈለግነው ስለ ኅሊና ምንነት በጥልቀት መመልከት ሳይሆን ተስፋ መቁረጥ ስለሚያመጣብን የኅሊና ሞት ነው፡፡
ተስፋ ለክርስቲያኖች ሕያው ነው፤ ግዑዝ አይደለም ወይም ቁስ አይደለም ሕይወት ያለው ነው እንጂ፤ ‹‹…በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፣ ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍረንም›› (ሮሜ ፭፥፲፭) ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጠው፤ ተስፋ የእምነታችን ምንጭ ነው፤ የተስፋ ምንጭ ወይም መገኛው ደግሞ የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፤ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእከቱ ‹‹…የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይሙላባችሁ…›› (ሮሜ ፲፭፥፲፫) በማለት ገልጾልናል፡፡
ሰው ምግብ ሳይመገብ፣ ውኃም ሳይጠጣ ለተወሰነ ጊዜ መቆየት ይችላል፤ አየርም አጥሮት እንዲሁ ለደቂቃዎችም ቢሆን በሕይወት የመኖር ዕድል አለው፤ ተስፋ ከቆረጠ ግን ለሰከንድ መኖር አይችልም፡፡ በዚህ ምድር ላይ እየተቸገርን፣ በፈተና ወጀብ ታጅበንም፣ እየተሰደድንም እየኖርን ያለነው ነገን ከዛሬ የተሻለ ሆኖ እናገኘዋለን በሚል ተስፋ ነው፤ ተስፋ ባይኖረን ከትናንት አልፈን ዛሬን ባላየናት፣ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን ባልናፈቅናት ነበር፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ በላከለት አባታዊ ምክሩ የኅሊናን መሞት ምን ያህል ለጥፋት እንደሚዳርግ እንዲህ ይገልጠዋል፤ ‹‹…እምነትና በጎ ኅሊና ይኑርህ፤ አንዳንዶች ኅሊናን ጥለው መርከብ ያለ መሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና›› (፩ኛ ጢሞ.፩፥፲፱) መርከብ ያለመሪ በባሕር ላይ ቢጓዝ ዕጣ ፈንታው ከጥልቁ ሰጥሞ መጥፋት ነው፡፡
ሰዎች በተስፋ ከመቁረጥ የተነሣ ኅሊናቸውን ሲጥሉ፣ ማገናዘብ ሲያቁሞ፣ ሰብእናቸውን አጥተው፣ ከሕገ እግዚአብሔርም ወጠተው እንደሚጠፋ እንስሳት ሆነው በራሳቸው ላይ በሚወስዱት ያልተገባ እርምጃ፣ በምድር ኑሮአቸው ጨልሞ፣ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወታቸውም ዕጣ ፈንታቸው ከዲያብሎስና ሠራዊቱ ጋር እሳቱ ከማይጠፋ ትሉ ከማያቀላፋ ዘለዓለማዊ እሳት ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ በእምነት ነገር መጥፋት ነው፡፡ እምነት ከሌለ ተስፋ አይኖረውም፤ ተስፋ ከሌለው፣ በጎ ኅሊና አይኖረውም፤ ከጽድቅ ሳይሆን ከበደል፣ ከሕይወት ሳይሆን ከሞት ያደርሳል፡፡
ከጨለማው ባሻገር ብርሃን፣ ከአቀበቱ ጀርባ ለምለም ሜዳ፣ ከኀዘን ባሻገር ደስታ፣ ከወጀብና ከአውሎ ነፋስ በኋላ ጸጥታና መረጋጋት፣ ከትንሣኤ በኋላ ሕይወት እንዳለ የሚያምን ክርስቲያን፣ የሚገጥመውን ፈተና፣ መከራና ስደት፣ ማጣት፣ መገፋትን በአኮቴት ተቀብሎ፣ ነገን እያለመ በትዕግሥት ይጠብቃል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርን አምነው የሚያደርጓት ተሰፋ እንደማይጨበጥ ደመና (ጉም) አልያም ርቆ እንደተሰቀለ ዳቦ ሳይሆን፣ የሚፈጸም፣ እውነት የሆነ ነው፡፡ በእርሱ ዘንድ ያለን ተስፋ ምኞትና ናፍቆት ብቻ ሳይሆን አለኝታና መተማመን የሚገኝበት ነውና። ነቢዩ ዕንባቆም በመከራ ጊዜ እንኳን ቢሆን ጸንቶ መገኘት እንደሚገባ እንዲህ በማለት የገለጸው ለዚህም ነው፤ ‹‹….ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥር ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ በጎችም ከበረት ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጣ ውስጥ ባይገኙ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለው፡፡›› (ዕን.፫፥፲፯)
በእግዚአብሔር ላይ እምነታቸው የጸና፣ ተስፋቸው የለመለሙ፣ ኅሊናቸው ሳይሞትባቸው የፈለጉትን አግኝተዋል፤ ከገቡበት ስምጥ፣ ከሰጠሙበት አዘቅት፣ ወጥተዋል፤ ከከበባቸው ጨለማ፣ ከወረደባቸው የመከራ ዶፍ፣ በመንገዳቸው የገጠማቸው ጉድባ ተሻግረዋል፤ በጉዟቸው የተጋረጠውን ወጀብ ተስፋን ይዘው፣ ከኅሊና ሞት አምልጠው ካሰቡበት ደርሰዋል፤ የሻቱትን አግኝተዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ እንደተጻፈ፤ ‹‹የሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህ›› (መዝ.፻፵፬፥፲፭)፤ ‹‹…በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም…፡፡›› (፪ኛ ቆሮ.፬፥፰)
እስራኤላውያን በግብጽ ከነበሩበት የሰቆቃ፣ የባርነት ሕይወት እግዚአብሔር በሊቀ ነቢያት መሪነት አውጥቷቸው ወደ ተስፋይቱ አገር ከነዓን ይጓዙ በነበረበጽት ጊዜ በኤርትራ ባሕር በፊሀሒሮት በሚባል ሥፍራ በነበሩበት ጊዜ ልበ ደንዳናው ፈርዖን፣ ማርኮ ዳግመኛ በባርነት ሕዝቡን ለመገዛት በማሰብ ሠራዊቱን አስከትሎ መጣ፤ እስራኤላውያን ከፊታቸው የኤርትራ ባሕር ተጋረጠ፤ ከኋላቸው የፈርዖን ሠራዊት ተከተለ፤ እምነታቸው ላልቶ በግብጻውያን ያደረገውን ድንቅ ሥራውን ረስተው ተስፋ ቆረጡ፤ ‹‹…በበረሃ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላል…›› እስከማለት ደረሱ፤ ሊቀ ነቢያት ሙሴ እምነቱ የጸና፣ በእግዚአብሔር ያለው ተስፋው የታመነ ነበርና አንደበቱን ሞልቶ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ ‹‹…አትፍሩ! ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያን ለዘለዓለም አታይዋቸውምና ቁሙ፤ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርገውን እግዚአብሔርን ማዳን እዩ፡፡›› (ዘጸ.፲፬፥፲፫)
ሊቃውንት ሲያስተምሩ በእግዚአብሔር ለታመነው ለሊቀ ነቢያት ሙሴ በኤርትራ ባሕር መሐል የመጓዢያ ለምለም መስክ በእምነት መነጽር ይታየው ነበር፤ በእግዚአብሔር የሚታመን በድቅድቅ ጨለማ መሐል ብርሃን፣ ከከበቡት ተራሮች ባሻገር ለምለም መስክ ይታየዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ በሚታወቀው የመከራ ዘመን ክርስቲያኖች አምልኮታቸውን በነጻነት መፈጸም፣ በዓላቸውን በደስታ በአደባባይ ማክበር ባልቻሉበት የጭንቅ ወቅት ተስፋ ሳይቆርጡ በግበበ ምድር (በካታኮም) መልእክታትን በኮድ (በምሥጢር) በመጻፍ በሰው ሰውኛ አይቻልም የተባለውን የመከራ ዘመን አልፈው፤ ለተከታይ ትውልድ ደማቸው ዘር፣ አጽማቸው አጥር (ከለላ)፣ ሆኖ ጠፉ ሲባል እየበዙ፣ ሞቱ ሲባል እየተኩ ክርስትናን አስቀጥለዋል፡፡
ክርስትና በደስታ ጊዜ የሚያምኑት ብቻ ሳይሆን በመከራ ጊዜ በሕይወት የሚገልጡት ነው፤ ታዲያ ይህን ለማድረግ ከኅሊና ሞት መጠበቅ ያሻል፤ ከኅሊና ሞት ለመዳን ደግሞ እምነት፣ ተስፋና ፍቅርን መያዝ ግድ ይላል፡፡
በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ የሶርያው ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሰብስቦ ሰማርያን ከበባት፤ የሚገባም የሚወጣም ጠፋ፤ በሰማርያ ታላቅ ረኃብ ሆነ፤ ሰው የሚበላው ጠፍቶ የርግብ ኩስ እስኪመገቡ ደረሱ፤ ከዚያም የከፋ ነገርን አደረጉ! እግዚአብሔር ሕዝቡን ይታደግ ዘንድ በነቢዩ ኤልሳዕ አማካኝነት ረኀባቸው እንደሚወገድ መልእክት ለንጉሡ ተነገረው፤ ንጉሡ ኢዮራም ግን ከነበረው ረኃብ ጽናት የተነሣ ተስፋ ቆርጦ ነበርና ‹‹እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን..›› በማለት የተስፋ መቁረጥ እምነት መጉደል ያለበትን ንግግር ተናገር! (፪ኛ ነገ.፮፥፳፭)
ነቢዩ ኤልሳዕም ‹‹…እነሆ በዓይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያም አትቀምስም አለ…›› (፪ኛ ነገሥ. ፯፥፩-፮) ነቢዩ ኤልሳዕ እንደተናገረው ሆነ እግዚአብሔር ይችላል፤ በአራት ለምጻሞች አማካኝነት ሶርያውያንን አስደንብሮ ከከተማው በራፍ እንዲሸሽ አደረገ፤ ሕዝቡም ያጣውን መብል (እህል) ከከበቧቸው ጠላቶቻቸው ሰፈር አግንቶ ተመገቡ፡፡ ሶርያውያን የጦር ሰፈራቸውን ለቀው መሄዳቸውን የሰማው ንጉሥ ሊመለከት ሲወጣ ሕዝቡ ገፍትሮ ጣለው፤ ረግጠውትም ሞተ፤ የእግዚአብሔር ነቢይ ኤልሳዕ ‹‹…እነሆ በዓይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያም አትቀምስም …›› ብሎ እንደተናገረው እግዚአብሔር ለሕዝቡ ምግብን ሰጠ፤ ተመገቡም፤ ንጉሡም ተመለከተ፤ ግን አልተመገበውም፤ ምክንያም አስቀድሞ በኅሊናው ሞቷልና፡፡
አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ሁሉ ሲቆላለፉ ሊሆን የሚችለው የማይሆን መስሎ ይታየንና ከማስተዋል ማነስና፣ ከእምነት መጉደል የተነሣ እንዴት ይሆናል? በሚል ሥጋዌ አመለካከትና እሳቤ የተስፋ መቁረጥ ንግግር ከአንደበታችን ይደመጣል፤ የኅሊናን ሞት ቀድመን እንሞታለን፤ እግዚአብሔር ግን ይችላል፡፡ የእኛ ኃላፊነት በማንኛውም ነገር በምንችለው መጠን ያቅማችንን ማድረግ ከዚያም እንደ ካህኑ ዔሊ ‹‹…እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ደስ ያሰኘውን ያድርግ…›› ልንል ይገባል፡፡ (፩ኛ ሳሙ.፫፥፲፰) እግዚአብሔር በአራት ለምጻሞች፣ ሰዎች በናቋቸው፣ ከማኅበረሰቡ በተገለሉ ሰዎች አማካኝነት ጠላቶቻቸውን አሳዶ የሕዝቡን ታሪክ ለወጠው፤ በእግዚአብሔር ከታመንን ሁሉን ማድረግ ስለሚቻል በአንዳች ነገር ተስፋን አንቆርጥም፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
