ትሩፋን
ኀዳር ፳፮፤፳፻፲፰ ዓመተ ምሕረት
ቅዱሱ መጽሐፍ ትሩፋን ከጦርነት፣ ከስደት፣ ከምርኮ የተረፉትን ሰዎች እንደሚያመልክት ይነግረናል፡፡ “ትሩፍ” ጥሬ ቃሉ “የቀረ፣ የተረፈ፣ ቀሪ፣ ትርፍ” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ (መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ ገጽ ፱፻፫) ናቡከደነፆር እስራኤልን ወደ ባቢሎን ማርኮ ከወሰዳቸው ከሰባ ዘመን በኋላ በባቢሎን የቀሩት ከተማረኩት ሽማግሎች ትሩፋን ይባላሉ። በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ከኢየሩሳሌም ተማርከው ሰባ ዘመን በፋርስ በባቢሎን የሚኖሩ የእስራኤል ሕዝብ ትሩፋነ ባቢሎን እንደሆኑም መጽሐፍ ያስረዳናል። (ዕዝራ ፪፥፩)
በተለያዩ ዘመናት በአንድም በሌላ ምክንያት በሰዎች፣ በጎሳ፣ በማኅበረሰብ ዘንድ እንዲሁም በሀገራት መካከል በሚከሰት ጦርነት እልቂት አልያም የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ የተነሣ የብዙዎች ሕይወት ይጠፋል፤ ታሪክ ለዚህ ቀደምት ምስክር እንደሆነ የምናውቀው እውነት ነው፡፡ የጦርነት ወሬ ደግሞ ለእኛ አዲስ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ እራሱ ጌታ በወንጌል ሲናገር ‹‹ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፤ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል›› እንዳለው ምድር ላይ እነዚህ ሁሉ መከራዎች እየተከሰቱ እንደሆነ ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ (ማቴ.፳፬፥፮-፯)
ታዲያ የጦርነት አስከፊ ገጽታው እንጂ መልካም ጎኑ ምን አልባት እርሱ ባወቅና በፈቀደ ጠላትን ከሀገር የማስወጣቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህም አብዛኛዎቻችን ጦርነትን በውዴታ ሳይሆን በግዴታ የምንቀበለው ነው፡፡ ከሁሉም አስከፊው ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን፣ ዘመድ አዝማዳቸውንና ወዳጆቻቸውን የሚያጡ ትሩፋን የሚገጥማቸው ሥቃይና ጉዳት ነው፡፡ በአንድ በኩል ከአሰቃቂ ግድያ አልያም ከሞት መትረፍ ቢያስደስትም በሌላ በኩል ግን የሚወዱትን ማጣት እጅግ አስከፊ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የሞት ሞት የሆነው የነፍስ ሞት አሰቃቂ ነው፡፡
ሰዎች ሞትን እንፈራለን፤ የሥጋ ሞት አስጨናቂ እንደሆነ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ኢትፍርህዎ ለሞት፤ ፍርህዋ ለኃጢአት፤ ሞትን አትፍሩ፤ ኃጢአትን እንጂ›› ይለናል፡፡ ሊያስጨንቀን የሚገባው በኃጢአት ምክንያት የሚመጣብንን የነፍሳችን ሞት እንጂ የሥጋ ሞት ሊሆን እንደማይገባ በዚህ ቃል እንረዳለን፡፡ ‹‹አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ›› በሚለው አምላካዊ ቃል ሥጋዊ ሞት አይቀሬ በመሆኑም ምንም ለማንቀይረው ነገር መጨነቁ ጥቅም የለውም፡፡ (ዘፍ.፫፥፲፱)
የነፍስ እንጂ የሥጋ ጦርነት ትሩፋን ባንሆን እጅጉን ይመረጣል፡፡ ቃሉን ተረድተው፣ በሕጉ ኖረው ትእዛዙን የጠበቁ ጻድቃን ሁሉ በነፍሳቸው አትርፈው ከዚህ ዓለም ድካምና ዕረፍት በክብር እንደተለዩ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክር ናቸው፡፡ (ገድለ ቅዱሳን) አብነት መሆናቸውን ደግሞ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ሁላችን ማወቅ አለብን፡፡ እውነት ስለሆነው አንድ ጌታና አንዲት እውነተኛ ሃይማኖት ሲሉ መከራን በመቀበል በቀናው መንገድ ተጉዘው መልካም ፍሬን ያፈሩ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት የነፍስ አትራፊዎች/ትሩፋን/ ናቸው፡፡
የልባችን መሻት የሁላችንም ምኞት መሆን ያለበት ይህ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በመንፈስ ውጊያ ለማሸነፍ የሚያስችለንን ስንቃችንን ደግሞ ማከማቸት አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት፣ እኛ ግን እየተጨነቅን ያለነው በጊዜያዊ ችግርና ወቅታዊ የእርስ በርስ ጦርነት ላለመሞት ነው፡፡ የሥጋዊ ሞትን ፈርተን በምንዘናጋበት ጊዜ ግን ነፍሳችንን እንደ አንበሳ ነጥቀው ሊጥሏት ይችላሉና ይህንን እንፍራ!
ነፍስ ዘለዓለማዊ ስትሆን ሥጋ ግን ጊዜያዊ ነው፤ አላፊ ጠፊ የሆኑ ምድራዊ ነገሮችን ለሟሟላት በሚል በምድር ለመኖር ስንሻ ከሁለት ያጣም የመሆን ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለ ሥጋዊ ሞት ስናስብ መንፈሳዊ ዝለት ያጋጥመናል፤ በዚህም ጊዜ ነፍሳችን ትጎዳለች፤ ታድፋለች፤ ትመነምናለች፡፡
ሰው ጦርነትን ፈርቶ ሊሸሽ ይችላል፤ መሰደደም ሆነ መደበቅም አይከፋም፤ ግን ግልጽ የሆነውን አስከፊ ሁኔታና እየተካሄደ ያለውን ጦርነትም ይሁን እልቂት ማስቆም ካልተቻለ ሃይማኖታችን በሚፈቅድልን ተገቢ መንገድ ድምጻችንን ማሰማቱና መልእክት ማስተላለፍ እንጂ የጠላት ወገን ከሆኑ አካላት ጋር ግብ ግብ መፍጠር አልያም ጦርነት ውስጥ መግባት አላስፈላጊ ነው፡፡ ጠላት ፊት ለፊት መጥቶ ሊገለን ቢፈልግ እንኳን “ማኅተባችንን አንበጥስም” ብለን አንገታችንን ለሰይፍ ሰውነታችንን ለሞት አሳልፈን መስጠት ሰማዕትነት ነው፤ የክብር ሞትም ያሰጠናል፡፡
በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተለይም በዕረፍት በዓሏ በየወሩ ፳፩ ቀን የሚነበበው መልክአ ማርያም ‹‹ኃጥአን ከታላቅ የደስታ አደባባይ በተሰደዱ ጊዜ ምርኮ እሆንሽ ዘንድ ከእነርሱ ለይተሽ አስቀሪኝ›› ይለናል፡፡ (መልክአ ማርያም) ይህ ድንቅ ጸሎት የሚያመለክተን ከጦርነት ምርኮኝነት ለማምለጥ ማቀድ ሳይሆን ከኃጥአን ጎራ ላለመቆጠር መሻት እንዳለብን እንዲያውም የፍቅር ምርኮ መሆን እንደሚገባ ነው፡፡
ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን የአምላክ እናት የተለመነው ይህ መማጸኛ ለሁላችን እንደሚሆን እናምናለን፡፡ የነፍሳችንን ጥፋት የማይፈልገው አምላካችን አንዲያ ልጁን አሳልፎ ሰጥቶ ያዳነን ክብርት በሆነች እናቱ ድንግል ማርያም ነውና ታማልደን፣ ትለምንልን እና ትራዳን ዘንድ መማጸን የተገባን ነን፡፡ ከጠላት ሰይጣን የመንፈስ ውጊያ እንድታተርፈን፣ ምርኮዎቿ እንድታደርገንን እንለምናት፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!
