እግረ ኅሊና

ሰኔ ፲፱፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ጉባኤ ዘርግተው በዐውድ ምሕረት ላይ በተመስጦ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምሩ የሰሚው በጎ ፈቃድና እዝነ ልቡና ከእነርሱ ጋር እንደሆነ በማመን ነው፡፡ የሕይወት ማዕድ ተዘጋጅቶ ሲቀርብም ታዳሚው ሊቋደስ የተገባ በመሆኑ በጆሮአችንም ሆነ በእዝነ ልቡናችን ሰምቶ መቀበል ድርሻችን ነው፡፡

አልፎ አልፎ ግን በአንድም ይሁን በሌላ አንዳንድ ውስጣዊ አልያም ውጫዊ እክሎች በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በሌሎች መርሐ ግብራት ላይ የሚደረገውን ሥርዓተ ጸሎት፣ የሚሰበከውንና የሚሰጠውን ትምህርት ደግሞም የሚዘመረውን ዝማሬ ማድመጥም ሆነ መከታተል ሊያዳግተን ይችላል፡፡ አባቶቻችን “በእግረ ኅሊናችሁም ጭምር ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት አለባችሁ” ሲሉ የሚደመጡት ለዚህ ነው፡፡ አለበለዚያ ሰውነታችን እንጂ የተገኘው እኛ ግን በድን እንደሆነ ሰው የተቀመጥን እንደሆንንም ያስረዱናል፡፡ ወይንም ደግሞ በዚያ ስፍራ የተገኘው አካላችን ይሁን እንጂ ሐሳባችንም አእምሮአችንም በእግረ ሕሊና ወደ ሌላ ቦታ ተጉዞ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ሌላ የሥጋዊና የምድራዊ የሆነ ሐሳብን ስናወጣና ስናወርድ ሰማያዊ የሆነው መብልና መጠጥ ያመልጠናል፡፡

አእምሮአችን ሙሉ በሙሉ ነጻ ሆኖ፣ ኅሊናችን በአንድ ሐሳብ ተሰብስቦ እና ትረኩረት ሰጥተን ማድመጥና መከታተል ካልቻልን በመንፈሳዊ ሕይወታችን እንጎዳለን፡፡ ከምንም በላይ ለሕይወታችን የሚያስፈልገውን ሕብስተ ሕይወት የምናገኘው በእግዚአብሔር ቤት ነውና በተለይም ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ ትኩረታችን በሙሉ መሆን ያለበት አምላካችንን በጸሎት ከማናገርና ቃሉን ከመማር ጋር ነው፡፡

እንዲያውም ሊቃውንቱ የረቀቀውንና የገዘፈውን ቃል ለመረዳት ማስተዋልም ጭምር እንደሚያስፈልግ ይነገሩናል፡፡ “ታዲያ ይህን በተመስጦ ማዳመጥና መረዳት ለማምጣት ምን ማድረግ ይቻላል?” ከተባለ መልሱ አስቀድሞ ችግሮቹን መለየትና መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራትንም ማከናወን ይሆናል፡፡

በአብዛኛው ጊዜ የሐሳብ መበታተን፣ የአእምሮ መታወክና የስሜት መረበሽ የሚከሰተው በቤት ውስጥና ባለንበት ስፍራ ከሚነሡ ውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ኩነቶች የተነሣ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመምጣታችን በፊት ከቤተ ሰብ፣ ከጎረቤት፣ ወይም ከወዳጅ ዘመድ ጋር በተፈጠረ ችግር፣ በኑሮአችን ውስጥ የዕለት ጉርሻችንን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገንን የገንዘብ መጠን ለሟሟላት ሲያቅተን፣ በሕመምና በሥነ ልቡና ሥቃይ ምክንያት ትኩረት ልናጣ እንችላለን፡፡ በእርግጥ ይህ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ቢሆንም በዚያች ሰዓት ተጨንቀን መፍትሔ ማግኘት እንደማንችል ራሳችንን በማሳመን ተስፋ ወደ ሆነው የእግዚአብሔር ቃል ትኩረታችን መልሰን ብናዳምጥ የተሻለ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን መፍትሔም ሳናገኝ ከቤተ ክርስቲያንም ማዕድ ሳንቋደስ ቀርተን አጉል እንሆናለን፡፡

እንደዚህ ዓይነት እክሎችን ለመፍታት ሌላው መፍትሔ ምክረ ካህን ነው፡፡ ንስሓ አባት ያለን አባታችንን በማማከር ከተቻለ ችግር ከተፈጠረባቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት መልካም ነው፡፡ ንስሓ አባት የሌለን ደግሞ ቶሎ በመያዝ ማማከር ይገባል፡፡ የገንዘብ ወይም ሌላ መሠረታዊ ነገሮች ጉድለታችንንም ቢሆን የሚሞላልን አምላካችን እንደሆነ ማመን ይገባናል፡፡ ለፍጥረታቱ ሁሉን የሚመግብ እርሱ ነውና በጸሎት ማሳሰብ፣ እርሱ የፈቀደውን ሥራ እንዲሰጠን መለመን፣ በስእለትም መጠየቅ ይጠበቅብናል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን በሥጋዊ ድሎት፣ ምኞትና ፈቃድ ተውጠን፣ አእምሮአችንን በእንደነዚያ ዓይነት እኩይ ሐሳቦች መወጠር ወደ ጥፋትና ኃጢአት የሚመራ በመሆኑ በቶሎ ልንታረም ይገባል፡፡ አልባሌ በሆነ ነገር ተስበን፣ በዓለማዊ እይታና በፍትወተ ኃጢአት ተይዘን ቤተ ክርስቲያን የምንገኝ ከሆነ አእምሮአችንም ሆነ ልቡናችን በክፋት የሚታወር ይሆናል፡፡ በትኩረት ማጣታችንና በእግረ ኅሊናችን እኩይ ስፍራ መገኘታችን ብቻም ሳይሆን ከቀናው መንገድ መውታጣችን በዚህ ጊዜ እርግጥ ነው፡፡

እናም ከእኛ የሚጠበቀው ይህ ችግር መሆኑን ተረድተንንና ዐውቀን በመቀበል መፍትሔ ለመፈለግ መፋጠን መሆን አለበት፡፡ “እንደ ማንኛውም ሰው ደካማ ስለሆንኩ ነው እንዲህ ላስብ የቻልኩትና ምንም ማለት አይደለም” እያልን ግን ሰበብ የምንፈጥር ከሆነ ከእውነተኛው ጎዳና ወጥተን በጥፋት መንገድ እየተጓዝን ነውና መለስ እንበል፡፡

አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሌሎች አያዩንም ብሎ በማሰባቸው በውስጣቸው ብዙ ነገር ያስባሉ፡፡ በተለይም ቤተ ክርስቲያን በሚሳተፉበት ጊዜ ምን ማግኘት እንዳለባቸው ባለማወቅም ሆነ ባለመረዳት አልያም በግዴለሽነት፣ አንዳንድ ጊዜም በንቀት በማይሆን ሐሳብ ውስጥ ይዋዥቃሉ፡፡ ልብን ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ግን ምንም እንደማይሰወረው እንደሚያውቅ ግን ረስተውት ይሆን? ወይስ አላወቁም ይሆን? ይህ ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ነው፡፡ (መዝ.፯፥፱)

አንዳንዶች ደግሞ በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ቤተ ክርስቲያን ወይም ስፍራ በመገኘታቸው የተነሣ በመላመዳቸው የተነሣ ከልባቸው ሆነው ማዳመጥንም ሆነ መከታተል ሲሰለቹ ይስተዋላሉ፡፡ ይህ እንዲያውም የአብዛኛው ሰው ወቅታዊ ችግር ሆኗል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያደርግ ርጉም ይሁን” ይላልና (ኤር.፵፰፥፲) እጅግ ልንጠነቀቅ በእግረ ኅሊናችን ጭምር በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን፣ ትኩረት ሰጥተን በሙሉ ልባችን ልንታደም ይገባል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!