ቅድስት አፎምያና ባሕራን

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሰኔ ፲፩፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁልን? በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ ታውጀው ከሚጾሙ አጽዋማት አንዱ የሆነው ጾመ ሐዋርያት የሚጾምበት ወቅት ላይ ነንና ይህን ጾም እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? አባቶቻችንን ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ከተቀበሉ በኋላ ወደ አገልግሎት ከመሄዳቸው በፊት ጾምን ጾመዋል፤ ይህን ጾም ምእመናን በየዓመቱ በዓለ ኀምሳ ከተከበረ ማግስት ጀምሮ እስከ ሐምሌ አምስት ቀን ድረስ እንጾመዋለን፤ ልጆች! እንግዲህ እኛም እንደ አቅማችን ይህንን ጾም መጾም ይገባናል፤ በዘመናዊ ትምህርታችሁም ከፈተና በፊት በርትታችሁ በማጥናት ፈተናውን በደንብ መሥራት ይገባችኋል፤ መልካም! ለዛሬ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት እንማራለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ተልከው እኛን የሚጠብቁን ናቸው፤ መልካም ስንሠራ ችግር በገጠመን ጊዜ በጸሎት ስንማጸናቸው ፈጥነው በመምጣት ከዚያ መከራ ያወጡናል፤ ከእግዚአብሔር አማልደው ምሕረትን ያሰጡናል፡፡ ከቅዱሳን መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሚካኤል ከመከራ ካዳናቸው መካከል ሁለቱን ታሪክ አንሥተን ለዛሬ እንማራለን፡፡

ባሕራን

አምላካችን እግዚአብሔርን የሚያመልኩ፣ የሚፈሩ መልካም ምግባር የነበራቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ በተለይ ደግሞ ባሕራን የቅዱስ ሚካኤልን በዓል አብልጦ ያከብር ነበር፡፡ ከጎረቤታቸው የነበረው ሰው ግን በጣም ክፉና እግዚአብሔርን የማያውቅ፣ ለሰዎችም የማይራራ በመሆኑ ይህን ደግ ሰው ይጠላውና ያቃልለው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀንም ደጉ ሰው ታመመ፤ የዕረፍት ቀኑ በደረሰ ጊዜ ሚስቱን የቅዱስ ሚካኤልን በዓል ታደርግ ዘንድ አዘዛትና ዐረፈ (ሞተ)፤ እርሷም በዚያን ጊዜ ፀንሳ ነበርና እጅጉን አዘነች፤ የመውለጃዋ ቀንም እንደደረሰም በመጨነቋ ቅዱስ ሚካኤልን ተማጸነችው፤ በዚህን ጊዜ ብርሃን በቤቷ በራ፡፡ እርሱም ስለረዳት በሰላም ውብ የሆነ ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም ልጁን እንዲህ ብሎ ባረከው፤ “ርኅራኄ የሌለው የዚህን ባለጸጋ ገንዘብ፣ ሀብት፣ ጥሪቱንም ሁሉ ሕፃኑ እንዲወርስ እግዚአብሔር አዝዟል፤”

በዚህ ጊዜ ሀብታሙ ሰው በቤቱ አልጋ ላይ ሆና ሳለ ጌታ ጆሮውን ከፈተለትና መልአኩ ያለውን ነገር ሰማ፤ እጅግም አዘነ፤ ልጁንም የሚገድልበት መንገድ መፈለግ ጀመረ፤ የልጁ እናት ብቻዋን ያለ አባት ልጁን ለማሳደግ መቸገሯን ተመለከተና “ልጁን እኔ ላሳድገው ስጪኝ” አላት፤ እርሷም በጣም ቸግሯት ስለነበር “ልጄ ከሚራብ አሳድገው” አለችው፤ በጣም የሚገርመው ይህ ክፉ ሰው ልጆች ሊያሳድገው ሳይሆን ሊገድለው ፈለገና ትልቅ ሳጥን አዘጋጀቶ ከውስጡ ከቶ ማንም ሳያየው ወደ ባሕር ውስጥ ጨመረው፤ የልጁ እናት ግን ሁል ጊዜም በጸሎት ቅዱስ ሚካኤልን “ልጆችን ጠብቅልኝ” እያለች ትጸልይ ነበር፡፡

ታዲያ ያ ክፉ ሰው ሕፃኑን ወደ ባሕር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል ሕፃኑ ምንም ሳይሆን ሳጥኑን በባሕሩ ላይ እያንሳፈፈ ወደ መሬት (ወደ ወደብ) አደረሰው፤ በዚያ አገር በወንዙ ዳርቻ የነበረ ደግ ሰው ያንን ሳጥን አገኘው፤ ሲከፍተው በጣም የሚያምር ትንሽዬ ልጅ በሳጥኑ ውስጥ ተኝቶ ተመለከተ፤ ከዚያም አውጥቶ በእንክብካቤ አሳደገው፤ ስሙንም “ባሕራን” አለው፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከዓመት በኋላ ሕፃኑን ወደ ባሕር የጣለው ክፉ ሰው ወደዚያ አገር መጣ፤ መሸበትና ማደሪያ ሲያጣ ከዚያ እንዲያሳድሩት ጠየቃቸው፤ ገብቶ መብላትና መጠጣት ጀመረ፤ ባሕራንን ያሳደገው ሰው “ባሕራን” ብሎ ሲጣራ ያ ሰውዬ ባሕራን በሚለው ስም በጣም ተገርሞ “እንዴት ያለ ስም ነው?” አለ፤ ለምን ባሕራን ብሎ እንደሰየመው ሲጠይቀው ታሪኩን ነገረው፤ በሕፃንነቱ ከባሕር አግኝቶ እንዳሳደገው ሲነግረው ሰውየው ደነገጠ! ለካስ እንዲሞት ከባሕር የጣለው ሕፃን አልሞተም፤ በጣም ተናደደ፤ አሁንም እንዴት አድርጎ እንደሚገለው ተንኮል ማሰብ ጀመረ፤ ከዚያም ለሰውየው “ይህን ልጅህን ልላከው፤ ከቤተ ዕቃ ረስቼ መጣው” አለው፤ ሰውየውም “እሺ ላከው” አለው፤ ‹‹ይህ ልጅ ሲመጣ ገድላችሁ ቅበሩት›› የሚል ደብዳቤ ጽፎ በማሸግ ባሕራንን አድርስ አለው፡፡

ባሕራን በታማኝነት ያንን ደብዳቤ ይዞ ሲጓዝ ቅዱስ ሚካኤል በሰው አምሳል በፈረስ ላይ ተቀምጦ ከመንገድ አገኘው፤ ‹‹ወዴት ነው ምትሄደው?›› ሲለውም ‹‹ይህንን ደብዳቤ አንዳደርስ ተልኬ ነው›› አለው፡፡ ‹‹ስጠኝ ልየው›› ሲለው ‹‹አይ የአደራ ደብዳቤ ነው አልሰጥህም›› አለ፡፡ ከዚያም ቅዱስ ሚካኤል ‹‹ እሺ ከፍ አድርገህ አሳየኝ›› አለው፤ ባሕራን ደብዳቤውን (ወረቀቱን) ከፍ አድርጎ ሲያሳየው ቅዱስ ሚካኤል እፍ አለበት፤ ‹‹ይህ ልጅ ሲመጣ ገድላችሁ ቅበሩት›› የሚለው ደብዳቤውም እንዲህ ተብሎ ተቀየረ ‹‹ ይህ ልጅ ሲመጣ ልጄን አጋቡትና ንብረቴን በሙሉ ይውረስ›› የሚል ሆነ፤ ይደንቃል! ቅዱስ ሚካኤል የባሕራንን የሞቱን ደብዳቤ በደስታ ቀየረለት፤ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራሉ፤ ያድናቸውማል፡።›› ተብሎ እንደተጻፈው ቅዱስ ሚካኤል ባሕራንን ከታዘዘበት ሞት አዳነው፡፡ (መዝ.፴፫፥፯)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ባሕራን ወደ ተላከበት ቦታ እዚያ እንደደረሰ ደብዳቤውን ሲሰጣቸው የሰውየው ቤተሰቦች አነበቡና ልጃቸውን አጋቡት፤ ብዙ ደስታ ተደረገ፤ የሰውየውንም ንብረት አወረሱት፡፡ ከብዙ ቀናት በኋላ ያ ክፉ ሰው ከሄደበት ሲመለሰ በቤቱ ደስታ ሲደረግ ሰማ፤ አገልጋዩን ጠርቶ፤ ‹‹ምንድን ነው የምሰማው ግርግር፣ ደስታ?›› ብሎ ጠየቀው አገልጋዩም እንዲህ አለው፤ ‹‹አንተ በላከው ደብዳቤ መሠረት ለላከው ልጅ ልጅህን አጋባናት፤ ንብረትህንም አወረስነው›› አሉት፡። ይህንን ሲሰማ ከፈረሱ ላይ ደንግጦ ወደቀ፤ ሞተም፡፡

አያችሁ ልጆች! በሰው ላይ ተንኮል የሚያስብ ራሱ ይጎዳል፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ መልካም የሚያደርግ ደግሞ ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ተልከው በመምጣት ከመከራ ያድኑታል፡፡ ታዲያ ባሕራን በተሰጠው ገንዘብ ቤተ ክርስቲያን አሠራበት፤ ለችግረኞች ረዳበት፤ በደስታም መኖር ጀመረ፡፡
ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታማኝነትን፣ ታዛዥነትን፣ እግዚአብሔርን ማክበር ሕጉን መጠበቅ እንዳለብን፣ ክፉ የሚያደርጉ ሰዎች ክፋታቸው ራሱ እንደሚቀጣቸው፤ ሰዎችን ማታለል እንደ ሌለብን፤ እንማራለን፡፡

ቅድስት አፎምያ

አፎምያ እና አስተራኒቆስ የተባሉ በጣም መልካም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለችግረኛ ሰዎች የሚያበሉ፣ ቅዱስ ሚካኤልን የሚወዱ ሰዎች ነበሩ፤ ይጾማሉ፤ ይጸልያሉ…. ትእዛዙን ይጠብቃሉ፡፡ ታዲያ አስተራኒቆስ የተባለው ታመመ፤ ለሚስቱ ለአፎምያ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አሠርቶ በቤት እንድታስቀምጠው ሰጣት፤ እርሱም በሰላም ዐረፈ፤ ከዚህ በኋላ አፎምያ በጾም በጸሎት ጸናች፤ ካላት ከንብረቷ ለችግረኞች ማብላት፣ ማጠጣት ጀመረች፡፡

መልካም ሥራዎችን አብዝታ ስትሠራ ሰይጣን በዚህ ቀና፤ ሊፈትናት ይህንን መልካም ሥራ ሊያሰናክላት ተነሣ፤ በመጀመሪያ ቀን መነኩሴ መስሎ መጣና ‹‹ለምንድን ነው በጾም ራስሽን የምትጎጂው? ለምንስ ገንዘብሽን ለሰው ትሰጫለሽ? ደግሞም ብቻሽን አትሁኚ፤ ሌላ ባል አግቢ›› አላት፡፡ በዚህን ጊዜ አፎምያ ‹‹አንተ መነኩሴ አይደለህ እንዴት መልካም ሥራን አትሥሪ ብለህ ትመክረኛለህ?›› አለችው፤ አፈረና ‹‹እኔ ለአንቺ ብዬ ነው›› አላት፤ ከዚያም ሄደ፡፡

በሌላ ጊዜ ደገግሞ ‹‹ሚካኤል ነኝ አንቺ ጋር ተልኬ ነው›› ብሎ መጣ፤ እርሷም ቤቷ ያለው አስተራኒቆስ አሠርቶ የሰጣት ‹‹የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ መስቀል ይዟል፤ ይህ የመጣው ግን ባዶ እጁን ነው›› ብላ ተጠራጠረችና ከቤቷ ገብታ የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ይዛ ወጣች፤ ሰይጣኑ ሥዕሉን ሲመለከት ብን ብሎ ጠፋ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሰይጣን ተፈጥሮው እንደ መልአክ ስለሆነ የተለያየ ነገር እየመሰለ ይለዋወጣልኋ እንደ ሰው፣ እንደ አውሬ፣ እንደ መልአክ እየተለዋወጠ ሰዎችን ያሳስታል፤ ሁለት ጊዜ መጥቶ አፎምያን ሊያታልላት ሞከረ፤ እርሷ ግን መንፈሳዊት፣ መልካም ደግ ሴት ስለነበረች አልቻላትም፤ በመጨረሻ ተናዶ ሊይዛት ዘሎ ሲመጣ አፎምያ ‹‹ቅዱስ ሚካኤል ድረስልኝ›› ብላ ተጣራች፤ ቅዱስ ሚካኤልም ፈጥኖ መጣና አዳናት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ሰይጣንን እርግጥ አደረገውና ሁለተኛ የእርሱ ስም በሚጠራበት ቦታ እንዳይደርስ አናዘዘው፡፡
ልጆች! ለእነዚህ ሁለት ሰዎች የተደረገው ተአምር የሚዘከርበትና የሚከበርበት ሰኔ ዐሥራ ሁለት ቀን በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያናት በድምቀት ይከበራል፡፡ እናንተም የዚህን የከበረ የሊቀ መላእክትን በዓልን ከቤተሰቦቻችሁ ጋር በመሆን እንድታከብሩ እናሳስባችኋለን፡፡

መልካም ልጆች! ታሪኩን እንደወደዳችሁትና እንደተረዳችሁት ተስፋ እያደረግን ለአሁኑ በዚህ እንለያችኋለን፡፡ ሁል ጊዜም እንደምንነግራችሁ በዘመናዊ ትምህርታችሁ በርትታችሁ መማር አትዘንጉ፤ ለወላጅ መታዘዝን፣ ለሰዎች መልካም ማድረግን እንዳትረሱ፤ በሰንበት ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመሄድ መንፈሳዊ ትምህርትንም ተማሩ፡፡ ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!