ጌታችን ፈዋሽ ውኃን አፈለቀ!
ሰኔ ፮፤፳፻፲፯ ዓመተ ምሕረት
ሰኔ ስምንት ቀን አምላክን የወለደች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የእመቤታችን ማርያም የታወቀችው በውኃ ምንጭ ዘንድ ያለች የቤተ ክርስቲያንዋ ቅዳሴ ነው::
እርሱም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሷ ጋር ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ ሲመለስ ያፈለቀው የተባረከ መታጠቢያ ነው::
ይህም እንዲህ ነው። ለጻድቁ ዮሴፍ የእግዝአብሔር መላክ ተገልጾለት ሕፃኑንና እናቱ ይዘህ ወደ ግብጽ አገር ሒድ አለው::
ዮሴፍም ነቅቶ ክብር ይግባውና ሕፃኑን እናቱን ሰሎሜን ይዞ ወደ ግብጽ አገር ሔዱ በዚያም ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ኖሩ::
ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ሁለተኛ ተገለጠለት ወደ እስራኤልም አገር ሕፃኑንና እናቱን ይዞ እንዲመለስ አዘዘው::
በሚመለስበት ጊዜ ወደ መዓልቃ ደረሱ። ከዚያም ወደ መጣርያ አገር ደረሱ። ይቺም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃ ያፈለቀባትና የመታጠቢያ ቦታ ናት። እርሷም እስከ ዛሬ አለች።
ሰዎችም ከአገር ሁሉ ከየነገዱ ሁሉ መጥተው አምላክን ወደ ወለደችና በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ወደ ጸናች ቅድስት ድንግል እመቤታችን ይለምናሉ። ከተባረከው የውኃ ምንጭ ታጥበው ከደዌያቸው ይድናሉ።
ለአምላካችን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት፣ አማላጅነት፣ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!
መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ