Archive for year: 2019
ምስክርነት
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፰ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸው ቃል «በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፤ በሰማርያ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቼ ትሆኑኛላችሁ» የሚል ነው፡፡
ይሁዳ ኢየሩሳሌምን የሚያጠቃልል ግዛት ነው፤በኢየሩሳሌም የጌታችን ተአምር የተፈጸመበት፤ ብዙ ሰው ስለ እርሱ የሰማበትም ከተማ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ይልቅ በይሁዳ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁም የሚሰሙም ዝቅተኛ ናቸው፡፡ ሌላው ሰማርያ ነው፤ ሳምራውያን ከአይሁድ ጋር በሥርዓት አይተባበሩም፤ በመጽሐፍ ቁጥርም፤ በባህልም፤ በቤተ መቅደስም አይገናኙም፤ አንዱ አንዱን ይጸየፈዋል፡፡
እኛስ በሕይወታችን ውስጥ ለሃይማኖታችን እየመሰከርን ነው? ከሐዋርያት ሥራ እንደምናነበው ቅዱስ እስጢፋኖስ መከራ በተቀበለ ጊዜና በክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ላይ ሰይፍ በተመዘዘ ጊዜ ሁሉም ከኢየሩሳሌም እየወጡ ተጉዘዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን፤ ቤታቸውንና ሀገራቸውን ትተው ወደ አሕዛብ ሀገር ሄዱ፤ በሔዱበት ቦታ ግን ወንጌል ተሰበከች፤ እነርሱ በሥጋ ቢጎዱ ቤተ ክርስቲያን ግን ተጠቅማለች ፡፡ የእኛ ወገኖች ቻይና፤ ዓረብ፤ አውሮፓና አፍሪካ ገብተዋል፤ ኢትዮጵያዊ ዘር ምናልባት ያልገባበት አንታርቲካ ብቻ ሊሆን ይችላል፤ እነርሱ በሄዱበት ሁሉ ወንጌል አስተማሩ የሚል መጽሐፍ ተጽፎልናል? ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ወንጌል ተሰበከ ሳይሆን የሚሰማው ተጣሉ፤ተበጣበጡ፤ይተማማሉ ይቀናናሉ የሚል ነው፤ ይህ ነው ወንጌል? ወንጌል የሰላም፤ የፍቅርና የደኅንነት ምንጭ ነው፤የብጥብጥ፤ የጦርነት ፤የጭቅጭቅ ግን አይደለም፡፡
ከሐዋርያት ዕጣ ፈንታ በገዛ እጁ በጠፋው በይሁዳ ምትክ ሰው ለመተካት ሐዋርያት ዕጣ ሲጣጣሉ «ከእኛ ጋር አብረው ከነበሩት ከእነዚህ ሰዎች አንዱ የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል» ብለዋል፤ በሐዋርያት ሥራ ፩፥፳፪፡፡ ሁለቱን ሰዎች ዕጣ የምንጥለው ለምንድን ነው? ለሚለው የሰጡት መልስ «ከሁለቱ አንዱ ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር እንዲሆን» የሚል ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወለደ፤ አስተማረ፤ ተያዘ፤ ተገረፈ፤ ተሰቀለ፤ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ የሚለው ቃል የትንሣኤው ምስክር ነው፡፡
እኛስ የማን ምስክር ነን? ብዙዎቻችን ጥሩ የፊልም ተዋናዮች ነን፤ ስለ እነርሱ ተናገሩ ብንባል የምንናገረውን ስለ ቅዱስ ጳውሎስ ተርኩ ብንባል አንተርክም፡፡ ስለ አንድ ዘፋኝ የምንናገረውን ያህል ስለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፤ ስለ ቅዱስ ያሬድ ተናገሩ ብንባል አንናገርም፤ የፊልም ተዋናዮቹንና የዘፋኞቹን ፎቶ ደረታችን ላይ ለጥፈን እየተንጠባረርን የምንሄደውን ያህል የቅዱሳንን ሥዕል በቤታችን ለመስቀል እናፍራለን፡፡ ታዲያ የማን ምስክሮች ነን? ዛሬ ኢትዮጵያውያንን በየቦታው እያጨቃጨቀን ያለው ስለ ምግብ ነው? ይበላል ወይስ አይበላም፤ ያገድፋል ወይስ አያገድፍም፤ የማያገድፍ ነገር በዚህ ምድር ላይ መተው ብቻ ነው፡፡
የሁላችንም ምስክርነት የትንሣኤው መሆን አለበት፤ ለምን የትንሣኤው የሚለውን መረጡ? ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ መነሣቱንና በሞት ላይ፤ በዲያብሎስ ላይ ኀይል እንዳለው፤ የተረዳነው በትንሣኤው ስለሆነ ነው፡፡ የትንሣኤው ምስክር ነው ወይስ ነገ የምንቃጠለውን ቃጠሎ ዛሬ እየመሰከርን ነው?‹‹እነሆ ቀን እንደ እሳት እየነደደ ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሚል.፬፥፩፡፡
ምስክሮቼ ትሆናላችሁ የሚለው ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ለሐዋርያት ነው፤ በኋላ ግን ሃይማኖታቸውን የገለጡ፤ ያስፋፉ፤ የመሰከሩ፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአሕዛብ የሰበኩ ሁሉ ምስክሮች ተብለዋል፡፡ ጌታም በወንጌል፤ «በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን ግን እኔም በሰማያት በአለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ» ብሏል፤ ማቴ. ፲፥፴፪፡፡ ዛሬ ስለ ምስክሮች ስንሰማ በአእምሮአችን የሚመጡት እነዚህ ስለ እምነት ብለው በፈቃዳቸው መከራን መቀበል የቻሉ ምስክሮች ናቸው፡፡
ከትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና ታሪካዊ አመጣጣቸው
ዲያቆን ተመስገን ዘገየ
ከትንሣኤ ሌሊት ፩ ሰዓት ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ያለው ሳምንት የፉሲካ ምሥጢር የተገለጠበት፤ ከግብፅ ወደ ምድረርስት ከሲኦል ወደ ገነት መሻገርን የሚያመላክት ሳምንት ነው። ለፉሲካ የሚታረደውም በግ ፉሲካ ይባላል (ዘዳ. ፲፮÷፪:፭÷፮)፤ ፉሲካ ማለት ደግሞ ማለፍ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትም ሳምንት የፉሲካ ሳምንት ነበር፤ (ሉቃ. ፳፪፥፲፬-፲፮፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፰-፵)።
እርሱም ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን ፉሲካችን ክርስቶስ ተባለ፤ ብሉይ ደግሞ የሐዲስ አምሳል ነው። ይኸውም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ ባሕረ ኤርትራን ካሻገራቸው በኋላ ወደ ምድረ ርስት፤ ነፍሳት ደግሞ በክርስቶስ መሪነት ከሲኦል ወደ ገነት መግባታቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕለቱም ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ በትረ ሙሴ የመስቀል ምሳሌ፤ግብፅ የሲኦል፤ የገሃነመ እሳት፤ የፈርዖን የዲያብሎስ፤ ሠራዊቱ የሠራዊተ ዲያብሎስ፤ እስራኤል የምእመናንና ባሕረ ኤርትራ የባሕረ ሲኦል ምሳሌ ነው፡፡
ሰኞ– ማዕዶት (ፀአተ ሲኦል)
ማዕዶት የቃሉ ትርጓሜ መሻገር ሲሆን፤ በዚህ ቀን ቤተ ክርስቲያን ነፍሳት በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከሐሳር ወደ ክብር፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት መሻገራቸውንና ፉሲካችን ክርስቶስ መሆኑን ታስባለች።
ማክሰኞ– ቶማስ
ቅዱስ ቶማስ በጦር የተወጋ ጎኑን፤ በቀኖት የተቸነከረው እጁንና እግሩን ካላየሁ አላምንም በማለቱ ክርስቶስም «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፤እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን» ብሎታል። ቶማስም «ጌታዬ አምላኬም»፤ ብሎ በመለሰ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስም «ስለ አየኸኝ አመንህን? ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓንስ ናቸው» አለው (ዮሐ ፳፥፳፯-፳፱)፤ ቶማስ የጌታን ፍቅር ተገንዝቦ ትንሣኤውን ስላመነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለቱን ቶማስ ብላ ታስበዋለች።
ዲዲሞስ የተባለ ከአሥራ አንዱ ደቀ መዛሙር አንዱ ቶማስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ባላቸው ጊዜ ከእርሳቸው ጋራ አልነበረም»። ከ፲፪ቱ ሐዋርያት አንዱ (ማቴ. ፲፥፪-፫) ቶማስ በአራማይክ ዲዲሞስ በግሪክ መንታ ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፳፥፳፬)፡፡ ቶማስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በፋርስና በሕንድ ወንጌልን እንዳስተማረ ይነገራል። ለቶማስ ጎኑን እንዲዳስስ የፈቀደው ለሌሎችም ቅዱሳን ሐዋርያት የተቸነከረውን እጅና እግሩን ያሳየው ካህናት ሥጋውና ደሙን እንዲፈትቱ ነው፤ ዮሐንስም በእጃችን ዳሰስነው ብሏል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፴፱)፡፡
ለማርያም መግደላዊት ግን የተነሣ ዕለት አትንኪኝ ማለቱ ለሴቶች ሥጋውን ደሙን መፈተት አልተፈቀደም ሲል ነው ብለው ሊቃውንት ያትታሉ፤ «አትንኪኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጅና፡- ወደ አባቴ÷ ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬ÷ ወደ አምላካችሁም አርጋለሁ አለ ብለሽ ንገሪአቸው» አላት፤ (ዮሐ. ፳፥፲፯)። ገቦ መለኮቱን የዳሰሰች እጁ በሕይወት ትኖራለች፤ በሕንድ ሀገር ከታቦት ጋር በመንበር ላይ ትኖራለች። በየዓመቱ በእመቤታችን በዓል በአስተርእዮ ሊያጥኑ ሲገቡ የሚሾመውን ወጥታ ቀኝ እጁን ትይዘዋለች፤ ዓመት አገልግሎ ያርፋል።
ረቡዕ –አልዓዛር
አልዓዛር ክርስቶስ ያስነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም ነው፤ የስሙም ትርጓሜ እግዚአብሔር ረድቷል ማለት ነው፤ (ዮሐ. ፲፩፥፯-፵፰)፤ አልዓዛር የሞተው መጋቢት ፲፯ ነበር፡፡ እህቶቹም ክርስቶስ እንዲመጣ መልእክት ልከውበት ነበር፤ ክርስቶስ ግን በ፬ኛው ቀን ማለትም መጋቢት ፳ መጥቶ ከሞት አስነሥቶታል፤(ዮሐ.፲፩፥፵፬)፡፡ ፋሲካውንም በወዳጁ በአልዓዛር ቤት ያከብር ዘንድ ከቀደ መዛሙርቱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አስቀድሞ ላከ፤ ከዚያም በአልዓዛር ቤት ሆኖ የሐዲስ ኪዳንን ሥርዓት ምሥጢረ ቁርባንን ሰርቶ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው፤ አልዓዛር ከተነሣ በኋላ በሐዋርያት ኤጲስ ቆጶስነት ተሸሞ ፵ ዓመት አገልግሎ ግንቦት ፳፯ ቀን ዐርፏል (ስንክሳር ግንቦት ፳፯)፡፡
አዳም ሐሙስ
አዳም የመጀመሪያ ሰውና የሰው ሁሉ አባት ነው፤ በ፮ኛው ቀን የተፈጠረ የሰው ሁሉ ምንጭ ስለሆነ የሰው ዘር ሁሉ ከእርሱ ተገኝቷል፡፡ በዚህ ዕለት ለአዳም የተሰጠው የተስፋ ቃል ስለመፈጸሙ፤ (ዘፍ. ፫÷፲፭) አዳም ከነልጆቹ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻ ስለመውጣቱ ይታሰብበታል፡፡ ክርስቶስ በተነሳበት በአምስተኛው ቀን ሐሙስ አዳም ይባላል፤ ጌታችን አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት እንደነበር በቀሌምንጦስ ተጽፏል፡፡
አዳምና ሔዋን በገነት ፯ ዓመት ከቆዩ በኋላ ትእዛዙን በመተላለፋቸው ከኤደን ገነት አስወጣቸው (ኩፋ.፬፥፲፮፤ዘፍ.፫፥፳፫) «ብዙ ተባዙ» ያለው ቃል እንዳይቀር በምድር ላይ ወርደው ልጆችን ወለዱ ይላል፡፡ የተወለዱትም ልጆችም በቁጥር ፷ እንደሆኑ (፩መቃ. ፳፰፥፮) የተወለዱት ልጆች ደጎችና ክፉዎች እንደ ነበሩ በአቤልና በቃየል ታውቋል፤ (ዘፍ. ፬፥፰)፤ አዳም በዚህ ዓለም ፱፻፴ ዓመት ኑሮ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ፵፻፭፻፸ ሚያዚያ ፮ ዐርፏል፡፡
ዐርብ– ቤተ ክርስቲያን
ዐርብ የእግዚአብሔር ቅድስት ማደሪያ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ተሰይማለች፤ ይህም ሁሉም ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመባት ዕለት በመሆኗ ነው፤ ዕለተ ዐርብ፤ የሥራ መከተቻ፤ ምዕራብና መግቢያ በሚሉት ስያሜዎችም ትጠራለች፡፡
በዕለቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ያደረገውን ተአምር በመስቀሉ ድኅነትን እንዳሳየ፤ በቀራንዮ የሕንጻዋ መሠረት እንደተተከለላትና ሥጋ መለኮት እንደተቆረሰላት፤ ልጆቿን ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የምትወልድበት ማየ ገቦ እንደፈሰሰላት ተገልጾባታል፤(ኤፍ.፪፥፲፱፤ራዕ.፩፥፮-፰)፡፡
ቅዳሜ– ቅዱሳት አንስት
ቅዳሜ ቅዱሳት አንስት ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ስያሜ በስቅለት ዕለት በልቅሶና በዋይታ የሸኙትን፤(ሉቃ. ፳፫፥፳፯) በዕለተ ትንሣኤ ሽቱና አበባ ይዘው ወደ መቃብር የገሰገሱትን፤ ከሁሉም ቀድሞ ጌታችን በዕለተ ሰንበት ተነሥቶ ለተገለጸላቸው ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜንም መታሰቢያ ለማድረግ ነው፤«ከሳንምንቱ በመጀመሪያዩቱ ቀን ያዘጋጁትን ሽቶ ይዘው እጅግ ማልደው ወደ መቃብሩ ሄዱ፤ሌሎች ሴቶችም አብረዋቸው ነበሩ (ሉቃ. ፳፬ ፥ ፩ )፡፡
እሑድ– ዳግም ትንሣኤ
«ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና÷«ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፤ ማቴ.፳፥፲፱፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተሰውሮ ከሰነበተ በኋላ በዕለተ እሑድ በዝግ ቤት እንዳሉ ዳግም ተገለጸላቸው፤ስለዚህም ዳግም ትንሣኤ ተባለ፡፡
(ምንጭ:-መዝሙረ ማኅሌት ወቅዳሴ፤ ሥርዓተ አምልኮ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ፤ ምዕ. ፳፥፳፬)
ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ሉቃ. ፳፬፥፭
ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ
በኦሪት ዘፀአት ፲፪፥፳፩-፳፰ እንደተጻፈው ይህ ዕለት በብሉይ ኪዳን ፋሲካ በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጉሙም መሻገር ማለት ነው፤ ይህም ሕዝበ እሥራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት የተሸጋገሩበት ዕለት ነው፤ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ትንሣኤ ይባላል፡፡ በዓለ ትንሣኤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ ነጻነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከኀሳር ወደ ክብር የተሸጋገርንበት ዕለት በመሆኑ ትንሣኤ እንለዋለን፤ ቅዱስ ሉቃ. ፳፬፥፭ የጻፈውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ስለ በዓለ ትንሣኤ ጥቂት ዐበይት ነገሮችን እንመልከት፡፡
ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ይህንን ጥያቄ የጠየቀው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ሲሆን ጥያቄው የቀረበላቸው ደግሞ በማለዳ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር የሄዱት ቅዱሳት አንስት ነበሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት ውለው ባደረበት አድረው የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ያዩት ቅዱሳት እናቶች የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በተባለች በዕለተ እሑድ በማለዳ የመቃብሩን ጠባቂዎችና የሌሊቱን ጨለማ ሳይፈሩ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ገሰገሡ፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ይህንን ጥያቄ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ አቀረበላቸው፤ ቅዱሳት አንስት የመልአኩን ጥያቄ እንደሰሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ የተናገረውን ቃል አስታወሱ፡፡ ከዚያም ቅዱሳት አንስት ወደ ሐዋርያት ሄደው ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ተናገሩ፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤውን አበሠሩ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን በግልጽ ተረዱ፡፡ የተሰቀለውን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ሕማሙንና ትንሣኤውን፤ በአባቱ ዕሪና በልዕልና መቀመጡን ዞረው አስተምረዋል፡፡
በዓለ ትንሣኤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፤ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ተስፋ አበውና ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሞ በትንሣኤው የሞት ሥልጣን በመሻሩ የቤተ ክርስቲያን አበው በዓለ ትንሣኤን «የበዓላት በኵር» በማለት ይጠሩታል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞት አሳዛኝ ታሪክ ሳይኾን ሕያው እውነት ነው፤ የዓለም መድኃኒት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሐዋርያት ስብከት፤ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው፡፡ ስለዚህም ዘወትር በጸሎተ ቅዳሴያችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሞታችንን፤ ከእርሱ ጋር መነሣታችንንና ሕያው መሆናችንን እንገልጻለን፤ ሕማሙንና ሞቱን፤ ትንሣኤውን፤ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እንሰብካለን፡፡ በበዓለ ትንሣኤ በዕለተ ስቅለት የነበረው የኀዘን ዜማ በታላቅ የደስታ ዜማ ይተካል፤ በዚህ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ነጭ ልብስ ለብሳ የደስታ ዝማሬ ታሰማለች፡፡
ከነቢያት ወገን ታላቁ ነቢይ ኤልያስ እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕም በእግዚአብሔር ኃይል ሙታንን እንዳስነሡ ይታወቃል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፰ ቍጥር ፲፬ ታሪኳ የተጻፈው የምኵራብ አለቃ የነበረችው ልጅ፤ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ ቍጥር ፲፪ ታሪኩ የተጻፈው ናይን በምትባል ሥፍራ የነበችው የድሃዪቱ ልጅ እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ታሪኩ የሚነበበው አልአዛር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በለየበት ሰዓት ቍጥራቸው ከስድስት መቶ የሚያንስ ከአምስት መቶ የሚበልጥ ሰዎች ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዳግመኛ ሞተዋል፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ግን ከሁሉ ይለያል፤ እርሱ ከሙታን ለመነሣት አሥነሽ አላስፈለገውም፣ ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይሞት፤ በማይለወጥ ሥጋ በመነሣቱ እንደሌሎች ዳግመኛ ሞትና ትንሣኤ የለበትም፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በቀዳማዊ ቆሮንቶስ ምዕራፍ ፲፭ ቍጥር ፳፫ እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ(በማይሞትና በማይበሰብስ ሥጋ) በሞቱ ሞትን ድል ነሥቶ፤ የሞት መውጊያን አሸንፎ፤ ሲኦልን በዝብዞ ከሙታን በመነሣቱ የትንሣኤያችን በኵር(መሪ) ተብሏል፡፡ ዳግመኛም ይህ ሐዋርያ በቆላስይስ መልእክቱ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፲፰ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «የሙታን በኵር» በማለት ጠርቶታል፡፡
የድኅነታችን አለኝታ የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማሙና በሞቱ የዲያብሎስን ቁራኝነት በማጥፋት አጋንንትን ድል የመንሣትን ኃይል ሰጥቶናል፡፡ ከጥንት ዠምሮ የሰውን ነፍስ የሚጎዳ የዲያብሎስን ሥልጣን ያጠፋ ዘንድ ፤ የፈጠረውን ዓለም ያድን ዘንድ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ፈቃድ፤ በአባቱ ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት በሥጋው ሞቶ በመለኮቱ ሕያው ሆነ፡፡ የሞት አበጋዝን ዲያብሎስን ኃይል ያጠፋ ዘንድ የማይሞተው የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሞተ፤ ሕይወት መድኃኒት በምትሆን ሞቱ ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ሙታንን ያድን ዘንድ እርሱ የሕያው አምላክ ልጅ ሞተ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለው እርሱ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሌሊት አደረ፡፡ ያን ጊዜ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባታችን በአዳም በደል ተግዘው ወደ ሲኦል የወረዱት ነፍሳት በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻ አወጥቷቸዋል፡፡ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱና ለንጹሐን ሐዋርያቱ እንደተናገረው በሦስተኛው ዕለት በሥልጣኑ ከሙታን ተነሥቷል፤ በዚህም ሙስና መቃብርን(በመቃብር ውስጥ መፍረስ መበስበስን) አጥፍቶልናል፤ ዳግመኛ ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ በመነሣቱ ለትንሣኤያችን በኵር ኾኖልናል፤ ቆላ. ፩ ፥ ፲፰፡፡ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን ገልጦልናል፤ ከሞት ወደ ሕይወት መልሶናል፤ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ለሰውነታችን ትንሣኤን፤ ለነፍሳችን ሕይወትን ሰጥቶናል፤ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ቍጥር ፳፭ እንዳስተማረን እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነው፤ እርሱ የሕይወታችን መገኛ ነው፡፡
በዓለ ትንሣኤን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን ማስተዋል ይገባናል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ አጠገብ ለተገኙት ሴቶች እንደነገራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋን መካከል እንጂ በሙታን መካከል አይገኝም፡፡ አባታችን አዳም የማይገባውን አምላክነት ሽቶ ዕፀ በለስን በመብላቱ ሞተ ሕሊና፤ ሞተ ሥጋ እንዲሁም ሞተ ነፍስ አግኝቶታል፡፡ ዳግመኛም በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ነበር፡፡ ሞተ ሕሊና በኃጢአት መኖር ነው፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፩ «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችኹ» በማለት እንደጻፈው በኃጢአት መኖር ሞት ነው፤ ዳግመኛም ሐዋርያው እንዳስተማረን የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው፤ ሞተ ሥጋ የሥጋ ከነፍስ መለየት ነው፤ ሞተ ነፍስ ደግሞ የነፍስ ከጸጋ እግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በአንጻሩ ትንሣኤም በሦስት ወገን ይታያል፤ ትንሣኤ ሕሊና(ልቡና) በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ፤ ትንሣኤ ዘሥጋ እንደወለተ ኢያኢሮስ፤ እንደአልአዛር ከሞት መነሣት በኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት መነሣት ነው፤ ትንሣኤ ነፍስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በቀኝ መቆም ነው፡፡
ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ ርቆ ስለኃጢአታችን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ከእርሱም ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ሞትን ድል አድራጊው የሕይወት ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር የሚሆነው እኛም ከእርሱ ጋር መኖር የምንችለው ለኃጢአታችን ሥርየት በቀራንዮ አደባባይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን ሕያዋን ስንሆን ነው፡፡ ፋሲካን መፈሰክ የሚገባን የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ በተሠዋው በእግዚአብሔር በግ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንጂ በእንስሳት ሥጋና ደም ሊሆን አይገባም፡፡ ለትንሣኤ በዓል ሊያስጨንቀን የሚገባው በገንዘባችን የምንገበየው ምድራዊ መብል መጠጡ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ የተሰጠን ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን አለመቀበላችን ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤ ሕያው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ይገኝ ዘንድ በትንሣኤ ልቡና ሕያዋን የምንሆንበት መንፈሳዊ በዓል ነው፤ ስለዚህም በዓለ ትንሣኤን ስናከበር በትንሣኤ ሕሊና ሕያዋን ሆነን ቅዱስ ቍርባን መቀበል ይገባናል፡፡
ተስፋ ትንሣኤን የምናምን ክርስቲያኖች ዘመናችን ሳይፈጸም የምሕረትና የፍቅር እጆቹን ዘርግቶ ወደሚጠራን ሕያው አምላክ በንስሐ እንቅረብ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅር የተሰጠንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ ያንጊዜ ትንሣኤ ልቡና እናገኛለን፤ ያን ጊዜ በምሕረቱና በፍቅሩ በትንሣኤ ዘጉባኤ በክብር ተነሥተን በቀኙ እንቆማለን፤ የሰው ዐይን ያላየውን፤ ጀሮ ያልሰማውን፤ የሰው ልብ ያላሰበውን ዓለም ሳይፈጠር ለወዳጆቹ ያዘጋጀውን ተድላ ነፍስ የሚገኝበትን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡
ለመንግሥቱ ጥንት ወይንም ፍጻሜ የሌለው የሕያው አምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት በምትሆን ሞቱ የእኛን ሞት ወደ ሕይወት ለውጦ ቅድስት ትንሣኤውን ገልጦልናል፤ ብርሃነ ትንሣኤውን አሳይቶናል፡፡ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መልሕቅ በሚባል መጽሐፉ «በትንሣኤውም የትንሣኤያችንንም ተስፋ ምሥጢር እንናገራለን» በማለት እንደተናገረው ዳግመኛም በኒቅያ የተሰበሰቡ አበው «የሙታንን መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን» በማለት በቀኖና ሃይማኖት እንደጻፉልን ክርስቲያኖች በመቃብር ያሉ፤ በተለያየ አሟሟት የሞቱ ሙታን ሁሉ የሚነሡበት ትንሣኤ ሙታን መኖሩን እናምናለን፡፡
ሕያው አምላካችን ሕያዋን ሆነን እንኖር ዘንድ በመስቀሉ ወደ ሰማያዊ አባቱ አቅርቦናል፤ በእርሱና በእኛ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶልናል፤ በቅድስት ትንሣኤው ትንሣኤ ልቡና የንስሐ በር ከፍቶልናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማኅየዊት በምትሆን ሞቱ የገነት ደጅን ከፍቶልናል፤ ፍሬዋንም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጥቶናል፤ ስለዚህም ሕያዋን እንሆን ዘንድ ወደ ሕይወት መድኃኒት ቀርበን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ በሕይወታችን ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ እንዳይሠለጥንብን፤ ትንሣኤ ሕሊና ትንሣኤ ነፍስን እናገኝ ዘንድ የትንሣኤን በዓል በሕያውነት ጸንተን እንኖር ዘንድ ምግባር ትሩፋት በመሥራት እናክብር፡፡
የትንሣኤን በዓል ስናከበር ጽኑ ድቀትን፤ ኀፍረትንና ውርደትን አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፤ በጭፈራና በዳንኪራ፤ በጣፋጭ መብልና መጠጥ ሰውነትን ማድከምና ልዩ ልዩ ኅብረ ኃጢአት ከመሥራት እንራቅ፤ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በኃጢአት በፍዳ እንዳንያዝ እንንቃ፡፡ በኃጢአት የተነሣ ተስፋ ትንሣኤ እንዳናጣ ዛሬ በንስሐ እንታጠብ፤ ትንሣኤ ሕሊና እናገኝ ዘንድ እንፍጠን፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ እጥፍ ዋጋ የምናገኝበትን ለሌሎች በጎ ማድረግን፤ ለድሆች ማካፈልን፤ ሕሙማን መጎብኘትን ገንዘብ እናድርግ፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ቸርነቱ ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ይሁን፤ የአባቶቻችን ጥርጥር የሌለባት የቀናች ሃይማኖታቸው፤ ድል የማትነሣ ተጋድሏቸው የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ያብቃን፤ አሜን፡፡
የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት
በተክለ አብ
በጲላጦስ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፤ ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ መከራን ተቀበለ፤ ጲላጦስ በ፫ ሰዓት ይሰቅል ዘንድ ሲፈርድበትም፤ ‹‹መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ›› (ዮሐ.፲፱፥፲፯) የራስ ቅል ስፍራ ቀራንዮ-ጎልጎታ አዳም ዐጽም የተቀበረበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ የመስቀሉንም እንጨት በዚያ በምድር መካከል አይሁዶች ተከሉት፡፡ የአዳም አጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም ወደ መርከብ እንደታቦት አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል፡፡ ጌታችንም ከአዳም የራስ ቅል በላይ ሊያድነው መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁዶችም የቀራንዮን ዳገት እየገረፉ ከወደ ጫፍ አደረሱት፤ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው ዐይኖቹ እያዩ እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዐርብ ቀትር ፮ ሰዓት ላይም ተሰቀለ፡፡
ጌታችን የተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ በሰማይ መካከል በሆነ ጊዜ የጥላ መታየት በሚጠፋበት፤ ወደ ሰው ተረከዝም በሚገባበት ነበር፡፤ ከ፮ ሰዓት ጀምሮ እስከ ፱ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፤ጨረቃ፤ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር፤ ‹‹ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ምድርም ሁሉ እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ›› ማር.፲፭፥፴፫፡፡
በ፱ ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ ፫ት በምድር ፬ት ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ፤ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ፡፡ ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፤ፍያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት(መንግሥት) ሆኖ ታየው፤እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል፤ በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል፡፡ መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤አብርሃምን፤ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው፡፡ ‹‹በጌታችን ኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፤ የእናቱም እኅት፤ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፤መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር›› (ዮሐ.፲፱፥፳፭) ‹‹እነርሱም ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜም ነበሩ›› (ማር.፲፭፥፵)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው የአደራ ቃላት አንዱ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ መሰጠቷ ነው፤ ለወዳጁ ዮሐንስ ከስጦታ ሁሉ ስጦታ የሆነች እናቱን እናት ትሁንህ ብሎ ሰጠው፤‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ በኋላ ወደ ቤቱ ወስዷት ፲፭ ዓመት ኖራለች፤ በዚህም የዮሐንስ ቤት በአቢዳራ ቤት ተመስላለች፤እመቤታችንም የሚያጽናናትን ወዳጁ ዮሐንስን ሰጥቷታል፡፡ የእመቤታችን ለዮሐንስ መሰጠት ቀድሞ በሙሴ አንጻር ጽላቷ ለሕዝቡ ሁሉ እንደተሰጠች፤በዮሐንስ አንጻርም እመቤታችን ለሁላችን ለምእመናን ተሰጥታናለች፡፡
፱ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፤(ማር.፲፭፥፴፬)፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ፤›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ ኤልያስን ይጣራል እያሉ አሙት፤ ክህደትንም ተናገሩ፤ ያንጊዜ አንዱ ወታደር ሮጦ ሆምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና በሰፍነግ መልቶ በሂሶጽም አድርጎ በአፉ ውስጥ ጨመረለት፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ሁሉ ተፈጸመ አለ፤ (ማር. ፲፭፥፴፯)፤ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ የሁለቱ ወንበዴዎች፤ ፈያታይ ዘየማንንና ፈያታይ ዘጸጋምን አብረው አወረዷቸው፤ ከጌታችን ዘንድ ቢቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ ሌላው ግን የተመሰለው ምሳሌ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው፤ የፋሲካውን በግ ‹‹አጥንቱን ከእርሱ አትስበሩ›› የተባለው አሁን ተፈጸመ፤(በዘፀ.፲፪፥፲)፡፡ ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው እንዲል ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል፡፡ ለንጊኖስ ጥንተ ታሪኩ አንድ ዐይኑ የጠፋ ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደ ጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው፡፡ አመሻሹ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኘቱ፤ስለምን ከመሢሑ ሞት አልተባበርክም አሉት? እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዐይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜ ዐይኑ በራለት፤ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ለ ቅርጽ ሆኖ በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆነ፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ቀድተው በዓለም ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው የጌታችን ደም የነጠበበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ያለው (ሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ከጌታ ጎን የፈሰሰው ውኃ ደግሞ ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው ማየ ገቦ ይሆናል፡፡
ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፤ ይህ ቅዳሜ ጌታችን ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ እኛም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ስለምናሳልፈው ነው፡፡ ቄጠማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤው ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሰሩታል፤ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፤ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ተሰበከና ታወጀ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡
በዚህች ቅድስት ቅዳሜ፤ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ፤ በዚህች ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ጌታችን የተቀበረበትም ስፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፤ ዮሴፍ ከኒቆዲሞስ ጋር ሆኖ ጌታችንን እንደፍጡር በሐዘንና በልቅሶ ሲገንዙት የጌታችን ዐይኖች ተገለጡ ‹‹እንደፍጡር ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው›› አላቸው፡፡
ሰሙነ ሕማማት (ከዕለተ ሰኑይ እስከ ቀዳሚት ሰንበት)
በመምህር ቸርነት አበበ
መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
መግቢያ
ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ የሰው ልጅ ቢያጠፋ፣ ቢበድል፣ ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳን የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነው አምላክ የጠፋውን ሊፈልግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ላጣው ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኀጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ኾነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡
ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?
‹ሰሙን› – ‹‹ሰመነ ስምንት (ሳምንት) አደረገ›› ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ‹ሕማም (ሕማማት)› – ‹ሐመ ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ይህም የሰውን ዘር ዂሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኀጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡
በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት፣ ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይፈጸምም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምፅ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መኾናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡ Read more
ሆሣዕና በአርያም
በወልደ አማኑኤል
ሆሣዕና በአርያም ማለት በሰማይ ያለ መድኃኒት ነው፡፡ ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ዕለት ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ስለሆነ የክብረ በዓሉ ምስጋና በዋዜማው ይጀመራል፡፡ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ካህናቱ ‹‹በእምርት ዕለት በዓልነ፣ በታወቀ የበዓላችን ቀን ከበሮ ምቱ›› በማለት የዋዜማውን ምስጋና ይጀምራሉ፡፡ የዋዜማው የምስጋና ቀለም እጅግ ሰፊ ስለሆነ በዚህ መዘርዘር አይቻልምና ከዋዜማው ፍጻሜ በኋላ ያለውን ሥርዓት እንመልከት፡፡
በሌሊተ ሆሣዕና ማኅሌት ከመቆሙ በፊት በካህኑ ተባርኮ በሰሙነ ሕማማት ሲነበብ፤ ሲተረጎም የሚሰነብተው ግብረ ሕማማት የተባለው መጽሐፍ ሲነበብ ነው፡፡ ‹‹ስቡሕ ወውዱስ ዘሣረረ ኩሎ ዓለመ››፣ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ፍጹም የተመሰገነ ነው፡፡ የምስጋናዎች ሁሉ ርእስ የዕለቱ የማኅሌቱ ምሥጋና በካህናት በሊቃውንት ይፈጸማል፡፡
ከዐብይ ጾም መግቢያ ጀምሮ በዝምታ የሰነበቱት ከበሮና ጸናጽል የምስጋናው ባለ ድርሻዎች ናቸው፡፡ በዚህ የተጀመረው ማኅሌት ሌሊቱን ሙሉ አድሮ መዝሙር በሚባለው ምስጋና በኩል አድርጎ ሰላም በተባለ የምስጋና ማሳረጊያ ይጠናቀቃል፡፡
ሥርዓተ ዑደት ዘሆሣዕና
ሥርዓተ ማኅሌቱ ተፈጽሞ፤ ሥርዓተ ቅዳሴው ከመጀመሩ በፊት እስከዚያ ሰዓት ከነበረው ሥርዓት ለየት ያለ ነው፡፡ ይሔውም ሊቃውንቱ የዕለት ድጓ እየቃኙ፣ እየመሩና እየተመሩ፣ ዲያቆኑ ከመዝሙረ ዳዊት የዕለቱን በዓል የተመለከተ ምስባክ በዜማ እያሳመረ፣ ካህናቱም በዓሉን የተመለከተ የዕለቱ ተረኛ ካህን በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፡፩-፲፫ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል በሚያነብበት ወቅት በአራቱም መዓዘን ቤተ መቅደሱን አንድ ጊዜ ይዞሩታል፡፡
ለምሳሌ ከምዕራቡ ወደ ምሥራቅ ባለው በር ፊት ለፊት በመቆም መምህሩ ‹‹አርእዩነ ፍኖቶ ወንሑር ቤቶ፣ ወደ ቤቱም እንገባ ዘንድ መንገዱን አሳዩን፤››የሚለውን ድጓ ይቃኛሉ፡፡ ካህናቱ እየተከተሉ ያዜማሉ ዲያቆኑ ‹‹ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘየይድር ውስተ ጽዮን፤ በጽዮን የሚገለጥ እግዚአብሔርን አመስግኑ›› እያለ የዕለቱ ተረኛ ካህን ያዜማል፡፡ በዚህ ዐይነት መልክ በአራቱም መዓዝነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ዑደቱ ይፈጸማል፡፡
ሥርዓተ ቅዳሴ ዘሆሣዕና
በዕለተ ሆሣዕና አሁንም የቅዳሴው አገባብ ሥርዓት ከሌሎች ዕለታት ለየት ያለ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ዲያቆናቱ ኅብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋዕ ይዘው በምዕራብ በር በኩል ይቆማል፡፡ ሠራኢው ዲያቆን በዜማ አሰምቶ ‹‹አርኅው ኖኃተ መኳንንት፣ አለቆች ደጆችን /በሮችን/ ክፈቱ›› ይላል፡፡ ካህኑም በመንጦላዕት ውስጥ ሆኖ ‹‹መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት››፣ ይህን የክብር ንጉሥ የኃያላን አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ ብሎ ይመልሳል፡፡ ዲያቆኑ ሦስት ጊዜ የክፈቱልኝ ጥያቄያዊ ዜማውን ካዜመ በኋላ ‹‹ይባእ ንጉሠ ስብሐት›› የክብር ንጉሥ ይግባ ብሎ ፈቅዶለት ይገባል፤መዝ. ፳፫፥፯፡፡
ይህንንም አበው እንደሚከተለው ያመሰጥሩታል፤ አንደኛ ቅዱስ ገብርኤልና ወላዲተ አምላክ በምሥጢረ ብስራት ጊዜ የተነጋገሩት እንደሆነና በመጨረሻም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ››፣ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ ብላ መቀበሏን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ፈያታዊ ዘየማንና መልአኩ ኪሩብ በማእከለ ገነት የተነጋገሩትን በድርጊት ለማሳየት መሆኑን ያስተምራሉ፡፡ ዋናው ምሥጢር ግን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሊገባ ሲል ብዙዎቹ እንዳይገባ ቢፈልጉም ከፊሎቹ ግን እንዲገባ መፍቀዳቸውን ያሳያል፡፡እንደተለመደው ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ ‹‹እግዚአ ሕያዋን›› /የሕያዋን ጌታ/ የተሰኘው ጸሎት በካህናት ተደርሶ ለምእመናን ሥርዓተ ፍትሐት ይደረግላቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ሥርዓተ ፍትሐት ስለማይደረግ፤ በሰሙነ ሕማማት የማይከናወኑ ምሥጢራት በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናል፡፡
ምእመናኑ ተባርኮ የተሰጣቸውን የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ወደ እየቤታቸው ያመራሉ፡፡ የዘንባባው ምሥጢር የተጀመረው በታላቁ አባት በአብርሃም ነው፤ ኩፋ. ፲፫፥፳፩፡፡ ይህን የአባታቸውን ሥርዓት አብነት አድርገው እስራኤል የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ፣ ዮዲት ድል ባደረገች ወቅት ዘንባባ እየያዙ እግዚአብሔርን አመስግነውበታል፡፡ ጌታችን በዕለተ ሆሳሣና ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባም ሽማግሌዎችና ሕፃናት የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እንደተቀበሉት እናነባለን፡፡‹‹ኢትዮጵያዊያን ምእመናንም ክርስቶስ የሰላም ነጻነት የድኅነት አምላክ መሆኑን ለመመስከር ዘንባባውን ይዘው ወደ ቤታቸው ይገባሉ››፤በእጃቸውም እንደ ቀለበት ያስሩታል፡፡
ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም ያደረሰን አምላክ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን!
‹‹ወአንትሙሰ ተዐቀቡ፤ ወግበሩ ተዝከረ ሕማማቲሁ፤ እናንተስ ተጠበቁ፤ የሕማሙን መታሰቢያ አድርጉ››፤/ትእዛዝ ፴፩/
በወልደ አማኑኤል
ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ የጌታችን የምሥጢረ ሕማማቱን ነገር መንፈስ ቅዱስ ሲገልጽለት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማታችንንም ተሸከመ››ማቴ. ፰፥፲፯/ኢሳ ፶፫፥፬/ ሲል ተናገረ፤ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ስለኛ ድኅነት በፍቃዱ ሕማማተ መስቀልን በትዕግስት በመሸከም መከራ መስቀሉ ስለተፈጸመበት፤ እኛም መከራ መስቀሉን የምናስብበት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ተባለ፤ ኢሳ. ፶፫፥፬፡፡
ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም የነበረው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንዑስ፤ በማዕከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትንና በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ታዲያ ሰሙነ ሕማማትን ጌታችን ለሰው ዘር በሙሉ ያደረገው ትድግና ቅዱሳን መጻሕፍት በየበኩላቸው ቢዘረዝሩትም ቸርነቱ፤ ርህራሄውና በጠቅላላው በአምላካዊ ጥበቡ የሰራቸው ዕፁብ ድንቅ የሆኑ ሥራዎች ጸሐፊ፣ አንባቢና ሰሚ ሊደርስባቸውና ዝርዝራቸውን ሊከተላቸው ሲፈልግ፤ ገና በሀሳቡ ውጥን ላይ ድካም እንዲሰማውና ፍጡርነቱ ፈጣሪን እንዳይመረምር ያስገድደዋል፡፡
መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር በቃሉ ብቻ ዳን በማለት ሊያድነው ሲቻለው የሰውን ባሕርይ ባሕሪዩ አድርጎ በፈቃዱ ሰው የሆነበትን፤ ሰውም ከሆነ በኋላ የተቀበላቸው ልዩ ልዩ መከራ የተቀበለበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሰሙነ ሕማማት በቤተ ክርስቲያናችን የሚደረጉ ሥርዓቶች በጥቂቱ እንመልከት፡-
ሥርዓተ ሰሙነ ሕማማት
ሰሙነ ሕማማትን የምናከብረው አባቶች ሐዋርያት የጌታን ጾም ለብቻው እንድናስበው እንዳደረጉን ሁሉ የጌታ ሕማማትም እንዲሁ በተለየ ለብቻው እንድናስበው የሰሩልን ሥርዓት ነው፡፡ ታዲያ ይህን ሳምንት ሊቃወንተ ቤተ ክርስቲያን ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተ ኩነኔ (፶፻፭፻ ዘመን) እና የጌታችን ሕማም መከራ እንግልት የሚታሰቡበት ነው ብለው ያስቡታል፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሁለት ነገሮች ምክንያት በማድረግ በሰሙነ ሕማማት የሚተገበሩ ሥርዓቶች አሉ፤ እነርሱም፡-
ጥቁር ልብስ መልበስ
በሰሙነ ሕማማት ወቅት በተለይ በዕለተ ዐርብ ካህናቱ ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ የኃዘንና የመከራ መገለጫ በመሆኑ በዚህ ወቅትም የጌታን ኃዘን መከራ ለማሰብና ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ ጥቁር ልብስ ባይገኝ ደግሞ የተገኘውን ልብስ ገልብጠው ይለብሱታል፡፡
በጸሎተ ሐሙስ ቃጭሉ ተቀይሮ ጸናጽል ይሆናል
በጸሎተ ሐሙስ በቅዳሴው ወቅት ቃጭሉ ተለውጦ ጸናጽል ይሆናል፤ ምክንያቱም በዘመነ ኦሪት የነበሩ አበው ጸሎታቸው ፍጽም ሥርዓት እንዳላሰጣቸው ለማጠይቅ ነው፡፡ ከቃጭል የጸናጽሉ ድምጽ ከርቀት እንደማይሰማ ሁሉ የአበው ጩኸት አናሳ መሆኑን ለማጠየቅ፤ የይሁዳን ግብር ለመግለጥና ይሁዳ ጌታን ለማስያዝ በድብቅ ያደባ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡
እርስ በእርሳችን አንሳሳምም፤ መስቀል አንሳለምም
እርስ በእርሳችን አለመሳሳማችን ይሁዳ በመሳም አሳልፎ መስጠቱን ለማሰብና ለማስረዳት ሲሆን መስቀልን ያለመሳለማችን ምክንያቱ ደግሞ፤ መስቀል በዘመነ ኦሪት የኃጥአን መቅጫ እንጂ የሰላም ምልክት እንዳልነበረ ለማጠየቅ ነው፡፡ መጽሐፍትም በመስቀሉ ስለምን አደረገ እንዲሉ መስቀል አዳኝ የሆነ ጌታ ከተሰቀለ በኋላ መሆኑን እንድናስብ ነው፡፡
አብዝተን መጾም አለብን
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አብዝተን እንድንጾምና እንድንፀልይ ያዙናል፤ ለምሳሌ በሰሙነ ሕማማት የሚችል በሁለት ቀን ውኃና ጨው ያለበት ምግብ እየተመገበ እንዲጾም ሲያዙን ያልቻለ ግን ፲፫ ሰዓት እየጾመ እየጸለየ ውኃንና ጨው የበዛበት ምግብ እንዲመገብ አዘዋል፡፡
ለሙታን ፍትሐት አይደረግም
በሰሙነ ሕማማት ወቅት ለሞቱ ሰዎች ፍትሐት አይደረግላቸውም፤ ዓመተ ፍዳና ዓመተ ኩነኔን የምናስብበት ወቅት በመሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ የነበሩ ሰዎች ፍትሐት እንደማይደረግላቸው ለማጠየቅ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን ተስፋ ላለውና ለአማኝ እንጂ ለማያምን ትንሣኤ ዘለክብር፤ ለማይነሣ ቢሆን ፍትሐት አይደረግለትም፡፡
በወይራ ቅጠል ጥብጠባ ይደረጋል
በዕለተ ዐርብ ሥርዓቱን ከፈጸምን በኋላ ወደ ካህናት አባቶቻችን እየሔድን በወይራ ዝንጣፊ ጥብጠባ ተደርጎልን ቀኖና እንቀበላለን፤ በዚህ ወቅት የምንቀበለው ቀኖና የሰሙነ ሕማማትን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ወይራ ጽኑ በመሆኑ የጌታ መከራ ጽኑ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡
ሕጽበተ እግር ይደረጋል
በጸሎተ ሐሙስ በካህናት አባቶችን የሚፈጸም እግር የማጠብ ሥርዓት ይፈጸማል፤ በዚህም መነሻ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር እንዳጠበና እርሱን አብነት ስላደረግን ነው፡፡
በዚህ ወቅት በዋነኝነት ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጽሐፍ ይነበባል
የሰሙነ ሕማማት ሥርዓተ ጸሎትና አገልግሎት ሁኔታ ከቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ አምልኮት ጋር የተያያዘ ቢሆንም አሁን ያለውን ሥርዓት የያዘ ግብረ ሕማማት የተሰኘው መጻሕፍ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ የዋለው ከጌታ ልደት በኋላ በ፲፬ተኛው ምእት ዓመት ነው፡፡ ከ፲፫፻፵ እስከ ፲፬፻፹ ዓ.ም የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሰላማ ብርሃነ ዐዜብ ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ እንደተረጎሙት፤ ቀደም ሲል በግዕዝ ብቻ ታትሞ በነበረው የግብረ ሕማማት መጽሐፍ ውስጥ ተገልጧል፡፡
የመጽሐፉ ስያሜም ከጥንት ስሙ ጀምሮ ግብረ ሕማማት እንደሚባል በመጽሐፍ ውስጥ በብዙ ክፍል ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ይህም ቀዳማዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ከጥንት ፍጥረት ከባሕርይ አባቱ አብ፤ ከባሕርይ ሕይወቱ መንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ በረቂቅ ጥበቡ ዓለማትንና ፍጥረታትን ሁሉ በየወገኑ ፈጥሮ እንደባሕርያቸው በቸርነቱ እየመገበና እየጠበቀ ሲገዛ ይኖራል፡፡ አካላዊ ቃል ወልድ በተለየ አካሉ ዓለምን ከፈጠረበት በሚበልጥ ጥበብ ሰው ሆኖ፤ ሥጋን ለብሶ፤ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፤ አዳምን ከነዘሩ እንደገና በአዲስ ተፈጥሮ ወደ ቀደመ ክብሩና ቦታው እንደመለሰው ያመለክታል፤ ፪ኛ ቆሮ. ፭፥፲፯/ ዕራ.፳፩፥፭/ ኢሳ. ፵፫፥፲፱/፡፡