በመተከል ሀገረ ስብከት ግልገል በለስ 8620 አዳዲስ አማንያን ተጠመቁ

ሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር ተጠማቂያኑ፡፡

02gilgel 2በመተከል ሀገረ ስብከት በግልገል በለስ ማእከል ሥር በሚገኙ 3 ወረዳዎች 8620 አዳዲስ አማንያንን ሚያዝያ 15 እና 16 ቀን 2008 ዓ.ም መጠመቃቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ገለጸ፡፡

በማንዱራ፣ ድባጤ እና ዳንጉ ወረዳዎች የሚገኙት እነዚህ አዳዲስ አማንያን በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት ከሀገረ ስብከቱ፣ ከወረዳ ቤተ ክህነቶች እና ከግልገል በለስ ማእከል ጋር በመተባበር የቅድሰት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲማሩ መቆየታቸውን ከማኅበሩ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ፍቅር እንዳላቸው የገለጹት ተጠማቂያኑ እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር በማለት ሲናፍቁት የነበረው ጊዜ በመድረሱና ፍላጎታቸው በመሳካቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የመረጃው ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡

ሆሳዕና

ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም

በመምህር ኃለ ማርያም ላቀው

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፡፡ መዝ.117፡25-26 የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኟትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ /ሉቃ.22፤18/ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ /ጸበርት/ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፡፡ እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ ዘካ.9፡9፤ ማቴ.21፡4፤ ማር.11፡1-10፤ሉቃ.19፡28-40፤ ዮሐ.12፤15፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን /ሉቃ.2፡13/ እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ /ዮሐ.14፡27/ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ አሞጽ4፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም፡፡ ኢሳ.66፡2፤ መዝ.50፡17፡፡

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ ሜኖሶታ ሁለት ከተሞች የኦሮምኛ ቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመረ

ሚያዚያ 11 ቀን 2008 ዓ.ም

ከአሜሪካ ማእከል

ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ ሜኖሶታ ውስጥ በሚገኙ በሚኖፖሊስ እና በቅዱስ ጳውሎስ /Minneapolis & Saint Paul/ ሁለት ከተሞች ከሚያዚያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሥርጭቱን ማስተላለፍ መጀመሩን የአሜሪካ ማእከል ገለጸ፡፡

የቴሌቪዥን ሥርጭቱ በየሳምንቱ እሑድ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት /Sunday at 4:00 PM USA Central time/ በቻናል 75 የሚተላለፍ ሲሆን ምእመናን መርሐ ግብሩን እንዲከታተሉ ማእከሉ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአሜሪካ የሜኖፖሊስ ማእከል ሚያዚያ 8 እና 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጉባኤ ማካሔዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

01admaa

አዳማ ማእከል የሐዊረ ሕይወት አካሔደ

መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

ከአዳማ ማእከል

01admaaበማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ለ4ኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በመቂ ግራዋ ጃዌ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም አካሔደ፡፡

መርሐ ግብሩ በደብሩ ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን በማእከሉ መዝምራንና በቀሲስ ምንዳየ ብርሃኑ መዝሙር ቀርቦ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት ዓላማ(ተልዕኮ) ያለው ክርስቲያን€ በሚል ርዕስ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በምክረ አበው መርሐ ግብር ከምእመናን የተሰበሰቡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርጎ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ የምእመናንና የሊቃውንት ድርሻ፤ ገድላትና ድርሳናት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ያላቸው አገልግሎት፤ ሉላዊነትን እንዴት መቋቋም ይቻላል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ያደረገችው አስተዋጽኦ፣ . . . አስመለክቶ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ መልስ ተሰጥቶባቸው የጠዋት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በተከናወነው ቀጣይ መርሐ ግብር በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ጌታ ሆይ አድነኝ ብሎ ጮኸ€ በሚል ርዕስ የወንጌል ትምህርት፣ በመቂ ግራዋ ጃዌ አቡነ ገብረ መንፈስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተከታታይ ቀርበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በግንባታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከምእመናን የ27 ሺሕ(27000) ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡