ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም.
ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ
የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የጎንደር መ/መ/መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከተሥአቱ ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡ጥምቀት ተጠምቀ ተጠመቀ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ጥምቀት ማለት በውሃ መጠመቅና በወራጅ ወንዝ በሐይቅ ውስጥ በምንጭ የሚፈጸም ነው:: በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ልዩ ነው::
በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው:: የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው:: እሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው:: ለኛ አርአያና አብነት ለመሆን በሰላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመሥክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡
በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢር አዳም የሰላሳ ዓመት፤ ሔዋን የአሥራ አምስት ዓመት ሰው ሁነው ተፈጥረው አዳም በአርባ ቀን ሄዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሰላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡
ወየአክል ሠላሳ ክረምቱ ለእግዚእ ኢየሱስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ሠላሳ ዓመት ሁኖት ነበር፡፡ ሉቃ ፫-፳፫ በሰላሳ ዓመት የመጠመቁ ምስጢር ይህ ሲሆን እኛ ዛሬ ወንዶች በአርባ ቀን ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምሥጢር ግን አዳም በአርባ ቀኑ ሄዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ ልጅነትን አግኝተው ሁለተኛ የተወለዱበትን ምሥጢር የያዘና የጠበቀ ምሥጢረጥምቀትና ሥርዓተ ጥምቀት ነው፡፡ ኩፋ ፬-፱
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደእንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ አይደለም ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ ያስቆጠረውን የዘመን ሱባዔ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጅ፡፡ የተነገረውን ትንቢት የተመሰለውን ምሳሌ እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፡፡
ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምኀበ ዮሐንስ ማቴ ፫-፲፫ ማር፩-፱ ሉቃ ፫-፳፩ ዮሐ ፩-፴፪ ለጌታ ሰላሳ ዓመት ሲመላው ለዮሐንስ መንፈቅ ሲተርፈው ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ አብ በደመና ሁኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ብሎ ሲመሠክር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ታወቋል፡፡
ያን ጊዜ ጌታ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ መጣ አለ፡፡ ምነው አገልጋይ ወደጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደአገልጋዩ ይሄዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? ቢሉ ጌታ መምጣቱ ለትሕትና ነው እንጅ ለልዕልና አይደለምና ዳግመኛም ለአብነት ነው ጌታ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ዛሬ ነገሥታት መኳንንት ካህናትን ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሂዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን ነው፡፡
ያውስ ቢሆን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ ትንቢቱን ምሳሌውን ለመፈጸም ትንቢት ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ አቤቱ ውሃዎች አንተን አይተው ሸሹ ተብሎ ተነግሯል መዝ ፸፮-፲፮፣ ፻፲፫-፫
ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ(ምንጩ) አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች ወርዶ ይገናኛል ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ)ምንጩ አንድ እንደሆነ የሰውም መገኛው (ምንጩ)አንድ አዳም ነውና ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቍልፈት ተለያይተዋል ከታች በወደብ እንዲገናኝ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ሁነዋልና ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃልከ ወሚመርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ አለው፡፡ምሳሌውን ታያለህና ሑር ዕድዎ ለዮርዳኖስ፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድአለው፡፡ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዲቅ ኅብስተ አኮቴት ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታልና፡፡ አብርሃም የምእመን ዮርዳኖስ የጥምቀት መልከ ጼዴቅ የካህናት፡፡ ኅብስተ አኰቴት ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነውና ያን ለመፈጸም ዘፍ ፲፬-፲፫-፳፬፡፡
ዳግመኛም ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ ነገ ካልዕ ፭ ፰-፲፱ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነውና ያን ለመፈጸም ነው፡፡ ዳግመኛም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደምድረ ርስት ሲሄዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲሄዱ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሽህ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡
ዛሬም ታቦታቱን ወደጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሽህ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈ አምላካዊ ትዕዛዝ መሆኑ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል “ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሽህ ክንድ ይሁን በዚህ መንገድ በፊት አልሄዳችሁበትምና የምትሁዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደታቦቱ አትቅረቡ ብለው አዘዙ” ኢያ፫-፩–፲፯፡፡
ዛሬ ሌዋውያን ካህናትና ሊቃውንት በዝማሬ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዕልልታና ሆታ ታቦታቱን አጅበው ወደጥምቀተ ባሕር ለሚወርዱ ታቦታት በመጽሐፈ ኢያሱ ምዕራፍ ሦስት ቁጥር ሦስት ላይ የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸውና ለበዓለ ጥምቀቱ መነሻ አምላካዊ ሕግና ሥርዓት ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደዮርዳኖስ መጥቶ በዮሐንስ እጅ መጠመቁም በዘመነ ወንጌል ክርስቶስ ከተጠመቀበት ሠላሳ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ በየዓመቱ ጥር አሥራ አንድ ቀን ለሚከበረው በዓለ ጥምቀት አምላካዊ ታሪካዊ ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ክርስቲያናዊ ሕግና ሥርዓት ያለው በዓል ስለሆነ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሲከበር የሚኖርታላቅ በዓል መሆኑን ያስረዳል፡፡
ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቆርጡ መጥረቢያው ከውሃው ውስጥ ወደቀ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትዕምርተ መስቀል ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል እንደዚሁም ሁሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርም ተወልዶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በቀራንዮ በቅዱስ መስቀል ተሰቀሎ ከጎኑ ጥሩ ውሃና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀ አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው ነገ ካልዕ ፮-፩–፯፡፡
መጠመቁም ለሱ ክብር የሚጨመርለት ሁኖ አይደለም ዮርዳኖስን ብርህት ማሕጸን ለማድረግ እኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመሆን ነው እንጅ ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደእግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል እንዲል፡፡ ዮሐ ፫-፫ ማር፲፮-፲፮
እኛም ስንጠመቅ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ፡፡ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው እንዲል ማቴ ፳፰-፲፱ ኢዮብ ንዕማን ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡
ትንቢቱን አስቀድሞ በነቢያት አናግሯል ምሳለውንም አስመስሏል ሱባዔውንም አስቆጥሯል በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምስጢሩ ምንድን ነው ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው ፡፡ሲጨነቁ አይቶ አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ማለትም አዳም የዲያብሎስ ተገዥ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን የተገዥነታችሁን ስም ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር አላቸው ፡፡
እነሱም የሚቀልላቸው መስሏቸው ፈቀዱለት እነሱም አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ብሎ በወረቀት ብጽፈው ይጠፋብኛል ሲል በማይጠፋ በሁለት ዕብነ(ሩካም)በረድ ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶልናልእና በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ይህ ነው፡፡
ወዮሐንስሰ ዐበዮ እንዘ ይብል አንሰ እፈቅድ እምኃቤከ እጠመቅ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጅ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን ብሎ አይሆንም አለው ወአንተኑ ትመጽእ ኀቤየ አገልጋይ ወደጌታው ይሄዳል እንጅ ጌታ ወደአገልጋዩ ይሄዳልን አለው እናቱ ኤልሳቤጥ ምንትኑ አነ ከመ ትምጽኢ ኀቤየ እሙ ለእግዚእየ እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ ኤልሳቤጥ የጌታየ እናቱ እኔ ወደአንች እመጣለሁ እንጅ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናገረው ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤሎ ኅድግ ምዕረሰ ጌታም መልሶ አንድ ጊዜስ ተው አለው አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡
እስመ ከመዝ ተድላ ውእቱ ለነ ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነውና አንተ መጥምቀ መለኮት ተብለህ ክብርህ ይነገራልና እኔም በአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ ተብየ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራልና ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ጽድቀ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽምይገባናልና፡፡
ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታ እንዲጠመቅ ትንቢት ተነግሯልና ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት ዳግመኛም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ ለባሕርይ ልጁ ለኔ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ለነ ተድላ ደስታችን ነውና አብ በደመና ሁኖ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ብሎ ሲመሠክር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ይገለጣልና የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናልና ወእምዝ ኀደጎ ከዚህ በኋላ ተወው፡፡
ስመ አብ ብከ ወስመ ወልድ ለሊከ ወስመ መንፈስ ቅዱስ ህልው ውስቴትከ ባዕደ አጠምቅ በስምከ ወበስመ መኑ አጠምቅ ኪያከ አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ ቢለው ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ ብለህ አጥምቀኝ አለው ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደባሕር ወርደዋል፡፡
ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወጽአ እማይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውሃው ወጣ ጥምቀቱን በውሃ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ሊፈጸም ትንቢት ወእነዝሐክሙ በማይ ወትነጽሑ ተብሎ ተነግሯል ምሳሌ ውሃ ለሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለውሃ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለሁሉ የሚገባ ነው ያለጥምቀት ወደእግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና ውሃ መልክ ያሳያል መልክ ያለመልማል ጥምቀትም መልክዐ ነፍስ ያሳያል መልክዐ ነፍስ ያለመልማልና፡፡
ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ ሰማይ ተከፈተለት አሁን በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው እቃ እንዲታይ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ተገለጸ ሲል ነው ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡
ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ ከመ ርግብ ወነበረ ላዕሌሁ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ርግብ አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ሐጸማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና ፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢሆን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው፡፡ በተባለ ነበርና አሁንስ ርግብ አለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀ ከሌሊቱ በአሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች ርግቦች ከየቦታቸው አይወጡምና ርግብ አለመሆኑ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በዚህ ይታወቃል፡፡
መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውሃው ከወጣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው ከውሃው ሳለ ወርዶ ቢሆን ለቀድሶተ ማያት የወረደ ነው ባሉት ነበርና ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢሆን ለክብረ ዮሐንስ የወረደ ነው ባሉት ነበርና ረቦ ወርዷል ያሉ እንደሆነ አብ ምሉዕ ነው አንተም ምሉዕ ነህ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደሆነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ የአንተም ሕይወት ነኝ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፡፡ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል ምሥጢሩ ግን እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት አብነትለመሆን ነው፡፡
ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በሱ ህልው ሁኜ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው የሚል ቃል ከወደሰማይ ተሰማ፡፡ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጅ ሌላ ቃል አይደለም የሥላሴ ልብ ቃል እስትንፋስ አንድ ነውና አብ ልብ ወልድ ቃል መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመሆን አንድ አምላክ ነውና አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ፡ወለወልድ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው ሲል ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደተናገረው ነው፡፡
ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት በረከት ይክፈለን