የመስቀል ኃይልና ቅርጾች በሚል ርዕስ የነገረ ቤተክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው

ጥናታዊ ጽሑፉ የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ አምስት ኪሎ ቅድስተ ማርያም አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው አዳራሽ ይካሔዳል፡፡

“የመስቀሉ ኃይልና ቅርጾች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ላይም ቁጥራቸው ከ350-400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በጉባኤው ላይም ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ ክህነት የመመሪያ ሓላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ከሌሎች ማኅበራት የተወጣጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

በጉባኤው ላይ በሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍም የመስቀል ኃይልና ቅርጾችን በተመለከተ ግንዛቤ ከመፍጠርም በተጨማሪ አጠቃላይ ስለ መስቀል ገናናነት በማስረዳት ትውልዱ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በዕለቱ የሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍ ርዕስን አስመልክቶ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሁሉም ምዕመናን መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጉባኤው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 ይቆያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መንፈሳዊ ኮሌጆችና “ደቀ መዛሙርቱ” ምን እና ምን ናቸው?

ኅዳር 21 ቀን 2008 ዓ.ም

ክፍል አምስት

የተሐድሶ መረብ አድማስና የትኩረት አቅጣጫዎች በሚል ባለፉት ሁለት ዕትሞች ስለ አዲስ አበባ፣ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ፣ ስለ ምዕራብና ደቡብ ኢትዮጵያ የተሐድሶ መናፍቃን አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ መንፈሳዊ ኮሌጆችን መሠረት ያደረገውን የተሐድሶ መናፍቃንን ዒላማ ከብዙው በጥቂቱ፣ ከረጅሙ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ተሐድሶ መናፍቃን ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንት የማድረግ ዕቅዳቸውን ዕውን ለማድረግ ትኩረት ካደረጉባቸው ተቋማት መካከል የመጀመሪያዎቹና ግንባር ቀደሞቹ የመንፈሳዊ ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት€ ናቸው፡፡ እስካሁን በማኅበር ደረጃ የሚንቀሳቀሱት ከሃያ አምስት በላይ የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅቶች ቀላል የማይባሉ አባሎቻቸው በመንፈሳዊ ኮሌጆች ተምረው ያለፉ፣ ይሠሩ የነበሩ ወይም በመሥራት ላይ የሚገኙ እንዲሁም የሚማሩ ናቸው፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ የሚታየው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ከተማሪዎች ምልመላ እና ተማሪዎቹ ወደ ኮሌጆቹ ሲገቡ ከሚደረግላቸው ቅበላ ጀምሮ የሚሠራ ነው፡፡ የገንዘብ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ደቀ መዛሙርት ደግሞ በድጋፍ ስም ይቀርቧቸዋል፡፡ መጻሕፍትንና ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በመዋዋስ ስም ግንኙነት በመፍጠር ኦርቶዶክሳዊ ተማሪዎችን ወደ ቡድናቸው ያስገባሉ፡፡

ከተለያዩ መንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ €œደቀ መዛሙርት€ ኅቡዕ ቡድን መሥርተው በቤተ ክርስቲያን ላይ ሰፋ ያለ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ ቡድኑ ዓላማውን ለማሳካት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተወካይ በማስቀመጥ ሥራውን ይሠራል። ይህ ስውር ቡድን በመጨረሻ ላይ ለማሣካት ዓላማ አድርጌ ተነሣኋቸው የሚላቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በራሳቸው መንገድና የኑፋቄ አቅጣጫ በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ ካስቀመጣቸው የማስመሰያ ግቦች፡-

ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቃል በምልዓት እንዲኖርባቸው ማድረግ፣

በሥነ መለኮት ትምህርት ገንቢ ዕውቀት ያላቸውን አገልጋዮች በማደራጀት የወንጌልን እን ቅስቃሴ ማስፋፋት፣

 በቤተ ክርስቲያኒቷ ውስጥ ከስንዴ ጋር አብረው የገቡትን ትምህርቶችና መጻሕፍት (አስተምህሮዎች) ማስወገድ፣

 ቤተ ክርስቲያን ምንም ከማይጠቅም ወግ፣ ልማድ እና በብልሃት ከተፈጠሩ ተረታዊ ትምህርቶች ተለይታ እውነት የሆነው ክርስቶስ እንዲሰበክ ማድረግ፣

 የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት በክርስቶስ ጥላ ሥር ተሰብስበው እንዲያመልኩና በአንድ እንዲተባበሩ ማድረግ፣

 ወንጌል በእያንዳንዱ ቤት አንኳኩቶ በመግባት መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ፣

 ወጥና ተከታታይ ትምህርትን በማዘጋጀት ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን በማነቃቃት ለዓለም ብርሃን የሆነውን የጌታን ቃል ለሁሉም እንደየአቅማቸውና እንደየደረጃቸው ማዳረስ፣

 በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት መሥራት፣

 የወንጌልን ተልእኮና ለውጥ ሊያፋጥን በሚቻል መልኩ የተለያዩ ተቋማትን ማእከል በማድረግ መንቀሳቀስ፣

 የቤተ ክርስቲያን ለውጥና ዕድገት የሚሹትን ሁሉ ማደራጀት፣

 በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እራሱን የቻለ ማኅበር ማቋቋም የሚሉ ናቸው፡፡ (ምንጭ፡- የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ገጽ ፺፬)

እነዚህን እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች በመደርደር €œቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ድረስ ዘመናትን የፈጀችው ወንጌልን ስትሰብክ ሳይሆን ስለ ቅዱሳን ስታስተምር ነው፤ አሁን መስበክ ያለብን ክርስቶስን ነው€ የሚለውን ተሐድሶ መናፍቃን ያራምዱት የነበረውን የፕሮቴስታንት አስተምሮ ይዞ የተነሣ ነው። ለቅዱሳን የማስተማር ጸጋ ስለሰጣቸው ስለ ክርስቶስ ማስተማር መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል ቤተ ክርስቲያን ጉልላቷ ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ሳታስተምር የዋለችበት ዕለት ያለ ለማስመሰል መሞከራቸው ስሕተት ነው፡፡ ዓላማዬን ያሳኩልኛል ብሎ ካሰማራቸው ሰዎች ሲገልጽ ደግሞ እንዲህ ብሏል፡፡ ሥራውን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ሆኖ የለውጥ መሪ የሚሆኑ በእምነትና በዕውቀት የታመነባቸው የነገረ መለኮት ተማሪዎች፣ ልዩ ልዩ መምህራን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ምእመናን፣ ልዩ ልዩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ይህ ሲባል በመንፈሳዊ ለውጥ የሚሠሩትን አካላትም ያካትታል፡፡

ቡድኑ በዋነኝነት በመንፈሳዊ ተቋማት ያሉና ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎችን ቢያማክልም በግላቸውና በማኅበር ተጀራጅተው ከሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ጋር አብሮ ይሠራል። ይህ ማኅበር ዓላማውን ለማሳካት የምንፍቅናውን መርዝ ለመርጨት ያሰበባቸው ቦታዎች መንፈሳዊ ኮሌጆች ብቻ ሳይሆኑ፤ የካህናት ማሠልጠኛ ሥፍራዎች፣ ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ የቤተ ክህነት መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት እና ማኅበራት ናቸው፡፡

ለእንቅስቃሴው አስተዋጽኦ ያደረጉ ሁኔታዎች

በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ ያለው የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታዩ ከኮሌጆቹ አስተዳደራዊ መዋቅርና አሠራር እንዲሁም ከተማሪዎች ክትትል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

፩.አስተዳደራዊ ችግሮች

መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ የሚከሠቱት የአብዛኛዎቹ ችግሮች መነሻቸው አስተዳደራዊ ችግር ነው፡፡ ይህ የሁሉም ችግሮች ምንጭ ነው፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጆች አስቀድመው አስተዳደራዊውን ችግር ቢፈቱ ሌሎችን በቀላሉ መፍታት ይችላሉ፡፡ ከገንዘብ አያያዝ፣ ከተማሪዎች ጋር ባለው መልካም ግንኙነት፣ ከመምህራን ቅጥር እና ከአስተዳደር ሓላፊዎች ምደባ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ይታያሉ፡፡ እነዚህ አስተዳደራዊ ችግሮች ተቋሙ ዋና ጉዳዩ የሆኑት ደቀ መዛሙርትን ዘንግቶ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲጠመድ ያደርጉታል፡፡ ተሐድሶ መናፍቃኑ ደግሞ ይህንን ክፍተት በደንብ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አስተዳደራዊውን ችግር ሃይማኖታዊ አስመስሎ ከማቅረብ ጀምሮ በየጊዜው ለአስተዳደሩ የቤት ሥራ የሆኑ ጉዳዮችን በመብት ስም እያነሡ እነርሱ የውስጥ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ይተጋሉ፡፡

፪.የገንዘብ እጥረትና የአጠቃቀም ችግር

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደ አንድ ችግር የሚነሣው የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያን ከማንኛውም አካል በላይ የሆነ ሀብት አላት፡፡ ይህም ሀብት የልጆቿ ዕውቀት፣ ጉልበትና ገንዘብ ነው፡፡ ይህንን በአግባቡ አቀናጅቶ የሚያሠራ መዋቅር፣ አሠራርና ስልት ባለመዘርጋቱ ግን ብዙ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጥባቸው ጠፍቶ ሲዘጉ ይታያሉ፡፡ ከተማ ላይ አብያተ ክርስቲያናት በሚልዮንና ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅሱ፣ እያንዳንዳቸው ከአንድ መቶ በላይ አገልጋዮች ሲኖሯቸው በገጠር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በአንጻሩ ዕጣንና ጧፍ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን የሚከፍት አንድ ካህን አጥተው ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማእከላዊ የሆነ የገንዘብ አያያዝ ባለመኖሩ የተከሠተ ችግር ነው፡፡

የዚህ ችግር ውጤትም በአጥቢያዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ተቋማትም የሚታይ ነው፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጆች በዚህ ከሚፈተኑት የቤተ ክርስቲያን ተቋማት መካከል ናቸው፡፡ ኮሌጆቹ እንደ ተቋም ለአገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለማሟላት የገንዘብ እጥረት ያጋጥማቸዋል፡፡ ይህ ክፍተት ደግሞ በእርዳታ ስም መናፍቃኑ ወደ ተቋማቱ እንዲገቡ በር ከፈተላቸው፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚማሩ ደቀ መዛሙርትም ወደ ሌላ እምነት እንዲገቡና የተሐድሶ መናፍቃኑን ጎራ እነዲቀላቀሉ ከሚያደርጓቸው ችግሮች አንዱ የገንዘብ እጥረት ነው፡፡

፫.የምልመላ መስፈርት

ተማሪዎች ወደ ኮሌጆች የሚገቡት ከዚህ በፊት የነበራቸው ሰብእና (ማንነትና ምንነት) ተጠንቶና ታውቆ ሳይሆን ሀገረ ስብከት ላይ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጆች ለመላክ ሓላፊነት ካላቸው አካላት ጋር ባላቸው ቅርበት ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ብዙ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ፣ ትልቅ አቅም ያላቸው ሰዎች እየቀሩ በጓደኝነት፣ በዝምድና፣ አለፍ ሲልም በጥቅማ ጥቅም ወደ ኮሌጆች የሚገቡት ተማሪዎች በርካታ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ኮሌጆች የሚገቡ ሰዎች ደግሞ ዐዋቂ ቢሆኑ እንጂ ክርስቲያን መሆን አይችሉም፡፡ ዐዋቂነትና መራቀቅ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ አይደለም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን በንባብ ላይ ከሚራቀቀው ዐዋቂ ይልቅ፣ እየተንተባተበ ወልድ ዋሕድ ብሎ የሚመሰክር ኦርቶዶክሳዊ ደቀ መዝሙር ያስፈልጋታል፡፡

በተጨማሪም ወደ ኮሌጆች የሚገቡበት የትምህርት መስፈርት ተመሳሳይ ባለመሆኑ በክፍል ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ለአንዳንዶቹ የሚጠጥርባቸው ለሌሎቹ ደግሞ የሚመጥናቸው አልሆን ይላል፡፡ ለምሳሌ በኮሌጆች ውስጥ በመደበኛው ዲፕሎማ መርሐ ግብር ከዐሥረኛ ክፍል ጀምሮ እስከ ዲግሪ ድረስ፣ ከፊደል ተማሪ እስከ መጻሕፍት መምህራን ድረስ አንድ ላይ በአንድ ክፍል የሚማሩበት ዕድል አለ፡፡ ባለዲግሪው በእንግሊዝኛ የሚሰጡ ትምህርቶች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖረው ሲችል፣ ዐሥረኛ ክፍል የጨረሰው ከትምህርቱ በላይ ፈታኝ የሚሆንበት እንግሊዝኛ ቋንቋ ማጥናቱ ይሆናል፡፡ ወደ ግእዝ ቋንቋ ስንመጣም ችግሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ የቅኔ እና የመጻሕፍት መምህራን ግእዝን ካልቆጠረው ጋር አብረው ይማራሉ፡፡

፬.የትምህርት አሰጣጥ

ኮሌጆች ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት አብዛኛው ዕውቀት ተኮር እንጂ ምግባር ተኮር አይደለም፡፡ የትምህርት አሰጣጡም ተማሪዎች ጉዳዩን ዐውቀውት ማስተማር እንዲችሉ ማድረግን እንጂ እንዲኖሩት ማድረግን ዓላማው ያደረገ አይደለም፡፡ የነገረ መለኮት ምሩቅ ከሌሎች ሰዎች የሚለየው በዕውቀቱ እንጂ በሕይወቱ እንዲሆን የተሠራው ሥራ አናሳነው፤ ወይም የለም፡፡ ይህ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለግለሰቡ ሕይወት አንዳች ረብ የሌለው መጻሕፍትን ይዞ እንደማይጠቀምባቸው ቤተ መጻሕፍት መሆን ነው፡፡

ትምህርቱም በመምህራን እውነተኛነት፣ ታማኝነትና ክርስትና ላይ የተመሠረተ እንጂ የኮሌጆቹ አስተዳደሮች ስለሚሰጠው ትምህርት የሚያደርጉት ክትትል የለም፡፡ ኮሌጆቹ አንድ መምህር ክፍል መግባት ወይም አለመግባቱን፣ ገብቶ የሚያስተምረው የትምህርት ይዘት ኦርቶዶክሳዊ ዶግማና ቀኖናን የተከተለ መሆን አለመሆኑን የሚቆጠ ጣጠሩበት ሥርዓት የላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ ማስተማር መንፈሳዊ አገልግሎት ሳይሆን የገንዘብ ማግኛ ሥራ አድርገው የሚቆጥሩ ብዙ መምህራን እንዲኖሩ የሚያደርግና ያደረገ አሠራር መፍጠር ችሏል፡፡

፭.የተማሪ አያያዝ

ኮሌጆች ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን አሟልተው በመደበኛው የቀን መርሐ ግብር የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ባላቸው ትርፍ ጊዜ የት እንደሚሔዱ፣ ምን እንደሚሠሩ፣ ከማን ጋር እንደሚውሉ ወዘተ የሚደረገው ቁጥጥር በጣም የላላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ትምህርት የማይሰጥባቸውን ዕለታት ተማሪዎች መገኘት ከማይገባቸው አልባሌ ቦታዎች ጀምሮ ወደ መናፍቃን አዳራሽ ሳይቀር ይሔዳሉ፡፡ ለምሳሌ በከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲማሩ ከነበሩ የተወሰኑ ተማሪዎች መካከል እሑድ ከዐራት ሰዓት ጀምሮ የሚሔዱበት የመናፍቃን አዳራሽ አለ፡፡ ሰፊ እረፍት ሲኖራቸው ደግሞ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ በአሸናፊ መኮንን ሰብሳቢነት በኮሌጁ ውስጥ ስለሚሠሩት የኑፋቄ ሥራ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ የተለያዩ የመናፍቃን መጻሕፍትን በኮሌጁ ውስጥ በነጻ ያድላሉ፣ “የአሸናፊ መኮንንን መጻሕፍት ያላነበበ ተማሪ የነገረ መለኮት ተማሪ አይባልም” የተባለ እስከሚመስል ድረስ በነፍስ ወከፍ ለሚከተሏቸው ሰዎች ሁሉ ይታደላል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የኮሌጆቹ አስተዳደሮች የሚያስተምሯቸው ሰዎች ሕይወት ገዷቸው የሚሠሩት ሥራ እንደሌለ ነው፡፡

፮.ከወጡ በኋላ ያለው ክትትል ማነስ

ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ከሦስቱም መንፈሳዊ ኮሌጆች ልጆችን ታስመርቃለች፡፡ ነገር ግን በኮሌጆች ውስጥ ቆይተው መውጣታቸውን እንጂ በትክክል የሚገባቸውን ነገር (ዕውቀትን ከሥነ ምግባር አስተባብረው) ይዘው መውጣታቸውን፣ ከወጡም በኋላ በተመደቡበት ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያን የምትፈልግባቸውን ያህል እየሠሩ መሆኑን፣ የሚያስተምሩት ትምህርት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት የተከተለ መሆኑን የምታውቅበት ሥርዓት አልዘረጋችም፡፡ እስካሁን ስንት ደቀ መዛሙርት ተመረቁ? ከተመረቁት ውስጥ ስንቶች በአገልግሎት ላይ አሉ?፣ ስንቶች በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በምግባራቸው ቀንተው እያገለገሉ ነው? ስንቶች አገልግሎት አቁመዋል? ስንቶችስ ወደ ሌላ እምነት ገብተዋል? ወደ ሌላ እምነት እንዲገቡ ያደረጋቸው ገፊ ምክንያት ምንድን ነው? አሁን ያሉበት አቋም ምን ይመስላል? የሚሉት ጉዳዮች ለኮሌጆችም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች መሆን አልቻሉም፡፡ ይህ ክፍተት እነሱን መሣሪያ አድርገው ለመጠቀም ሌት ከቀን ለሚተጉት መናፍቃን ጥሩ ዕድል ሆኗ ቸው ውጭ ሆነው ለሚሠሩት የጥፋት ሥራ የውስጥ ዐርበኛ ሆነው የሚያገለግሏቸው ኦርቶ-ጴንጤ€ የኮሌጅ ምሩቃን ሰባኪ፣ የስብከተ ወንጌል ሓላፊና የደብር አስተዳዳሪ ሆነው እንዲቀመጡ አድጓል፡፡

፯.የትኩረት ማነስ

በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ በዓላማና በረቀቀ ዘዴ እየተሠራ ያለውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን ካለመቀበል ጀምሮ እንቅስቃሴውን ለማስቆም የተሠሩ ሥራዎች አለመኖራቸው ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተሐድሶ ማኅበረ ቅዱሳን የፈጠረው የመወደጃ ፍረጃ€ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የተሸረበ ሥውር ሴራ መሆኑን አልተረዱትም፣ ወይም ሊረዱት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ይህ አቋም ሁለት ዓይነት ትርጉም ይኖረዋል፡፡ አንደኛው በአስተዳደር ሓላፊነት ላይ ካሉት አካላት ውስጥ ተሐድሶን የሚደግፉ፣ የውስጥ ዐርበኛ ሆነው የሚሠሩና በዓላማ የተሰማሩ ሰዎች አሉ ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ትኩረት የማይሰጡ፣ ክርስትናን በጊዜያዊ ነገር የሚለውጡ፣ የሚነገራቸውን ነገር ላለመስማት ጆሯቸውን የደፈኑ እና ምን እየተሠራ እንደሆነ እንኳን መረጃው የሌላቸው ሰዎች በሓላፊነት ላይ እንደተቀመጡ የሚያስገነዝብ ነው፡፡

እንቅስቃሴው በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጉዳት

፩.ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ችግር

አንድ መናፍቅ ምንም ትምህርት የሌለውን ክርስቲያን ከማታለል ይልቅ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቀ ሰባኪን ማሳመን ይቀለዋል፡፡ ለዚህም ነው በተሐድሶ መናፍቃን ማኅበራት ውስጥ ከምእመኑ ይልቅ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ከተመረቁት ደቀ መዛሙርት መካከል የሚበዙት መናፍቅ የሆኑት፡፡ ብዙ ተመራቂዎች እንደሚናገሩት ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቀ ሰው የመጀመሪያ የምስጋና ጸሎቱ €œአቤቱ መናፍቅ ሳልሆን እንድወጣ ስላደረግኸኝ አመሰግንሀለሁ የሚል ነው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ምሩቅና መናፍቅ አቻ ለአቻ የሚነገሩ ቃላት ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ንግግሮች መንፈሳዊ ኮሌጆችና €œደቀ መዛሙርቱ€ ምን እና ምን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ እንድንጠይቅ ያስገድዱናል፡፡

ለብዙ የተሐድሶ መናፍቃን መፈጠር፣ ለብዙ ምእመናን ከአገልግሎት መውጣትና ከሃይማኖት መራቅ የዋናውን ድርሻ የሚወስዱት እነዚሁ €œደቀ መዛሙርት€ ናቸው፡፡ ሃይማኖቱን በመተውም ቅድሚያውን የሚይዘውም ያልተማረው ኅብረተሰብ ሳይሆን እነዚሁ ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያቱ መጀመሪያ የነበራቸው የትምህርት መሠረት ወይም የትምህርት አሰጣጡ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመናፍቃኑ የመጀመሪያ €œጥቅሶች€ (ማሳያዎች ማለታችን ነው) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት ሳይሆኑ ከእነዚህ መንፈሳዊ ኮሌጆች አፈንግጠው የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ የደቀ መዛሙርቱ በሃይማኖትና በምግባር መውጣት የቤተ ክርስቲያን ችግር ተደርጎ ተወስዶ ለብዙ ምእመናን ከመንገዳቸው ለመውጣት ምክንያት ሆኗል፡፡

፪.ሁሉንም እንዲጠሉ ማድረግ

ከመንፈሳዊ ኮሌጆች ተመርቀው የወጡ በቃልም በሕይወትም የሚያስተምሩ፣ ሃይማኖትና ምግባር እንደ ድርና ማግ አስተባብረው የያዙ የቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ በገጠር ያለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲጠናከር አምሳና መቶ ኪሎ ሜትር በእግራቸው እየሔዱ፣ ወጣቶችን እየሰበሰቡና እያስተማሩ ሌት ከቀን የሚደክሙ ደቀ መዛሙርት አሉ፡፡ እንደእነዚህ ያሉ ደቀ መዛሙርት ያሉትን ያህል ደግሞ፣ ከርሳቸው እስከሞላ ድረስ ለሌላው መዳን አለመዳን ግድ የሌላቸው የቤተ ክርስቲያን የብብት እሳት የሆኑም አሉ፡፡ በሥጋና በመንፈስ መግባ ያሳደገቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ከጠላቷ ከአርዮስ ጋር ወግነው ሊያፈርሷት የሚሯሯጡ የእናት ጡት ነካሾች በቁጥር እየበዙ መሔዳቸው ምእመናን እውነተኞችን አገልጋዮች እንዲጠራጠሩ፣ ከመጥፎዎቹ ጋር አብረው ደምረው እንዲጠሉ በር እየከፈተ ነው፡፡

፫.የሰውና የገንዘብ ኪሳራ

የቤተ ክርስቲያን ገንዘቧ ሰው እንጂ ብርና ወርቅ አይደለም፡፡ በመምህራን እግር ተተክተው መንጋውን እንዲጠብቁ ለብዙ ዓመታት የደከመችባቸው ልጆቿን ከማጣት በላይ ለቤተ ክርስቲያን ሌላ ኪሳራ የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያጣችው ልጆቿን ብቻ አይደለም፤ ለእነዚህ ሰዎች ያባከነችውን ገንዘብ፣ የሰው ኃይልና ጊዜ ጭምር እንጂ፡፡ ከመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚመረቁ እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት ከመድረኩ ርቀው የቢሮ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ይህም ለቤተ ክርስቲያን ሁለት መንታ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ አንደኛው ቤተ ክርስቲያን ስትለፋባቸው የኖረቻቸው ልጆቿ ዓላማዋን ሳያሣኩላት መቅረታቸው ሲሆን፤ ሁለተኛውና አሳዛኙ ደግሞ ሌሎች የተሐድሶ አቀንቃኞች ቦታውን እንዲይዙት ማድረጉ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ቦታውን መያዛቸው ብቻ ሳይሆን እውነተኞቹ ከመድረኩ ስለጠፉ እነርሱ እውነተኛ መስለው መታየታቸው የበለጠ ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳት ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ተሰሚነት ያለው የሚናገር፣ የሚጽፍ ወይም የሚዘምር ሰው ስለሆነ ነው፡፡

የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በሁሉም ኮሌጆች ያለ መሆኑን ከየኮሌጆቹ በተለያዩ ጊዜያት የተባረሩ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች፣ ምክርና ተግሣጽ ተሰጥቷቸው የቀጠሉ ተማሪዎች ማስረጃዎች ናቸው፡፡ እንቅስቃሴው በሦስቱም መንፈሳዊ ኮሌጆች ያለ ነው፡፡ በየኮሌጆቹ ማሳያዎችን በመጥቀስ ጉዳዮችን ማብራራት ተገቢ ይሆናልና ወደዚያ እንለፍ፡፡

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አዲስ አበባ መሆኑና መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ መሠረት አድርጎ የሚሠራውን የውጪውን የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅትም ትኩረት የሳበ በመሆኑ ብዙ እንቅስቃሴዎች ይደረጉበታል፡፡ ከውጪ እስከ አገር ውስጥ መረባቸውን የዘረጉ የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅ ቶች ሰፋ ያለ መሠረት ለመጣል ሲሞክሩ ነበር፣ አሁንም እየሠሩ ነው፡፡ እንቅስቃሴው በአብዛኛው የቀን መደበኛ ተማሪዎችን ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከኮሌጁ ተመርቀው በተሐድሶ መናፍቃን መረብ ውስጥ ያሉ ደቀ መዛሙርት€ አሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በትምህርት ላይ ያሉ ወደ መናፍቃን አዳራሽ የሚሔዱ፣ ከአሸናፊ መኮንን ጋር የሚማሩ ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ ፳፻ወ፮ ዓ.ም ላይ ቁጥራቸው ዐሥር የሚደርሱ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚነቅፍና የክህደት ትምህርት ሲያሠራጩ በኮሌጁ ደቀ መዛሙርት መረጃ ቀርቦባቸዋል፡፡ ጉዳያቸውም ለኮሌጁ ቀርቦ እየታየ ሲሆን፤ የድምጽና የሰው ማስረጃ የቀረበባቸው የኑፋቄ ትምህርቶቻቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡

፩.አማላጃችን ኢየሱስ ነው እንጂ ሌላ አማላጅ የለም፤

፪.በጸጋው አንዴ ድነናል፣ ስለዚህ ሥራ ለምስክርነት ነው እንጂ ለመዳናችን ምንም አያስፈልግም፤

፫.ኅብስቱ መታሰቢያ ነው እንጂ፣ ሕይወት የሚሰጥ አማናዊ የጌታ ሥጋና ደም አይደለም፤

፬.ለፍጡር አድኅነኒ አይባልም፣ ማርያም አታድንም፤

፭.በጸሎት ቤት ስለ ድንግል ማርያም ክብር ትምህርት ሲሰጥ “ተረታ ተረትህን ተውና ውረድ” ብሎ መቃወም፤

፮.ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ መላእክት እያልን ወንጌልን አንሸቃቅጥ፤

፯.ጻድቃን ሰማዕታት፣ መላእክት አያማልዱም፣ አያድኑም፣ አያስፈልጉም፣ አንድ ጌታ አለን፤

፰.ለቅዱሳን ስግደት አይገባም፣ የአምልኮ እንጂ የጸጋ የሚባል ስግደት የለም፤

፱.ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን አትሰብክም፣ የምትሰብከው ፍጡራንን ነው፤

፲.ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምባቸው መጻሕፍት በሙሉ ኮተቶች ናቸው፤

፲፩.እኛ የሐዲስ ኪዳን ልጆች ነን የአንድምታ መጻሕፍት አያስፈልጉንም፤

፲፪.በሐዲስ ኪዳን ካህን አያስፈልግም፣ ሊቀ ካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፣ ንስሐም መናገር ያለብን ለጌታ ብቻ ነው፤

፲፫.በጳጳሳት፣ በመነኮሳት፣ በቀሳውስት፣ በዲያቆናት እንዲሁም ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በሚያስተምሩትና በሚማሩት፣ በሚጾሙትና በሚያስቀድሱት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ላይ ጸያፍ ስድብና ዘለፋ መናገር፡፡ ከሚናገሯቸው የስድብ ቃላት ውስጥ፡- ግብዞች፣ በጨለማ የሚኖሩ፣ ዶማዎች፣ ደንቆሮዎች፣ ያልበራላቸው፣ የጌታ ጠላቶች፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡

፲፬.ታቦት ጆሮ ስለሌለው አይሰማም፣ ስለዚህ አያስፈልግም ፣

፲፭.ሕዝቡን ለብዙ ሺሕ ዘመናት ለጣዖት ስናሰግደው ኖረናል፣

፲፮.አሁን ካለንበት የጨለማ ጫካ መውጣት አለብን፣

፲፯.ቤተ ክርስቲያን፡- ዘረኝነትንና ጽንፈኝነትን ታስፋፋለች፣ የተወሰነ ጎሳ ናት፣

፲፰.አንደኛ ዓመት ተማሪዎችን ሲያገኟቸው €œቲዮሎጂ መማር ከፈለግህ የበላኸውን መትፋት አለብህ€፣ ወዘተ በማለት መዝለፍና ክፉ ምክር መምከር የሚሉት ናቸው፡፡

ይህ የሚያሳየው ከዚህ ኮሌጅ ተመርቀው የተሐድሶ መናፍቃኑን ጎራ የተቀላቀሉት ሰዎች ኮሌጁን በሚፈልጉት መልኩ ለመቅረፅ ሰፋ ያለ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ነው፡፡ ይህም ፍሬ ኮሌጁ በእነዚህ ደቀ መዛሙርት ላይ እንደሆነው በየጊዜው እያጠራ ካልሔደ ችግሩን ውስብስብ እና ከባድ ያደርገዋል፡፡

ሌላኛው ኮሌጅ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች “ብዙ ሰዎችን ያፈራንበት ቤታችን ነው ብለው በድፍረት የሚናገሩለት” ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ነው፡፡ ተሐድሶዎችና መናፍቃኑ ከዚህ ኮሌጅ ተመርቆ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ መገኘት የተአምር ያህል የሚቆጠር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እነርሱም ከዚህ ኮሌጅ የተመረቀ መሆኑን ያረጋገጡትን ሰው በልበ ሙሉነት ይቀበላሉ፡፡ በኮሌጁ የኑፋቄው ጠንሳሽ መሠረት ስብሐት ለአብ ነው፡፡ የእርሱን ፈለግ ተከትለው ብዙ ጥፋት ያደረሱት ደግሞ በ፳፻ወ፬ ዓ.ም ተወግዘው የተለዩት ጽጌ ሥጦታውና ግርማ በቀለ ናቸው፡፡ ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ የተከሉት እሾህ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እያደማ ይኖራል፡፡ ከዚህ ኮሌጅ ተመርቀው አንዳንዴ ፕሮቴስታንት፣ ሌላ ጊዜ ሙስሊም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኦርቶዶክስ ሆነው የሚተውኑ ደቀ መዛሙርት€ አሉ፡፡

ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በተሐድሶ መናፍቃን ብዙ ተጽእኖ የደረሰበት ኮሌጅ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት በኮሌጁ እንደ ሐሰተኛ የሚቆጠሩትና አንገታቸውን ደፍተው የሚሔዱት የነበሩት ኦርቶዶክሳውያን ነበሩ፡፡ ይህ የሆነው በሓላፊነት ላይ የነበሩት መሪዎች ድጋፍ የሚሰጡት ከትክክለኞቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይልቅ ለተሐድሶ መናፍቃኑ ስለ ነበር ነው፡፡ ይህ የሆነውም እንቅስቃሴውን የሚደግፉ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ስለሚያግዟቸው ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ ለውጦች እየታዩበት ነው፡፡ የዚህ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተሐድሶ ጠንሳሽ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የመቀሌ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ የነበረ ሰው ነው፡፡ አዳዲስ ተማሪዎች ሲገቡ አጥምደው ወደ ቡድናቸው ያስገቡ ነበር፡፡ በ፳፻ወ፮ ዓ.ም ያለውና በዛብህ የሚባሉ ቀንደኛ የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኞች ከዚህ ኮሌጅ ኑፋቄያቸው ተደር ሶበት ተባረዋል፡፡

የተሐድሶ መናፍቃን ተላላኪ የሆኑት የኮሌጁ ተማሪዎች በዕረፍት ሰዓታቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተው በአሸናፊ መኮንን አስተባባሪነት ይሰበሰባሉ፡፡ ለቡድናቸው አባላት መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአሸናፊ መኮንን መጻሕፍት እና ሌሎችም ተሐድሶዎች የጻፏቸው መጻሕፍት ይታደላሉ፡፡ ፳፻ወ፯ ዓ.ም ላይ በኮሌጁ ተማሪዎች በተደረገ የመረጃ ማጠናቀር የተደረሰበት በኮሌጁ ከሚማሩት ተማሪዎች ውስጥ ሃምሳ በመቶ ያህሉ ተሐድሶዎችና የተሐድሶ መናፍቃን ደጋፊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የኮሌጁ ተማሪዎች ግንባር ቀደም የተሐድሶ አንቀሳቃሾች ናቸው፡፡

ስለ መንፈሳዊ ኮሌጆች ስንናገር መንፈሳዊ ኮሌጆች በእምነት የጸኑ፣ በምግባር የቀኑ ደቀ መዛሙርትን አላፈሩም ማለታችን አለመሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከተመሠረቱበት ዓላማ አንጻር የምርቱን ያህል ግርዱም እየበዛ ማስቸገሩን ለማሳየት አቅርበናል፡፡ እንኳን ትልቅ ተቋም አንድ ግለሰብም የወለዳቸው ልጆች ሁሉ መልካሞች፣ ያስተማራቸው ተማሪዎች ሁሉ ዐዋቂዎች ወይም መንፈሳውያን እንደማይሆኑለት ይታወቃል፡፡ ይህ የነበረ፣ ያለና የሚቀጥል እውነት ነው፡፡ ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩት ሐዋርያት መካከል ይሁዳ በስንዴ መካከል የበቀለ እንክርዳድ ነበር፤ በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ እግር ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩት ደቀ መዛሙርት መካከልም አርዮስ በቅሏል፡፡

ነገር ግን በመንፈሳዊ ኮሌጆች ውስጥ እየታየ ያለው ንጹሕና የተቀላቀለ ስንዴ አስገብቶ እንክርዳድ የማምረቱ ጉዳይ እየጨመረ መምጣቱን አህጉረ ስብከትም እየገለጡ ነው፡፡ እዚህ ላይ ለማስገንዘብ የምንፈልገውም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አቅሟን የምታጠናክርባቸው፣ ተተኪ ሊቃውንትን የምታፈራባቸው መንፈሳዊ ካሌጆች፤ የተሐድሶ መናፍቃን መፈልፈያ ለማድረግ በዓላማ ሌት ከቀን እየተሠራ ያለውን ተግባር ምን ያህል አውቀነዋል በሚል እንጂ፤ በየኮሌጆቹ ውስጥ ሆነው አቅማቸው በፈቀደ፣ ይህን ሥውር ደባና ዘመቻ ለማጋለጥ የሚተጉ ደቀ መዛሙርት የሉም ለማለት አይደለም፡፡፡ ሆኖም ግን ተፅዕኖውና ዘመቻው ከእነሱ አቅም በላይ ስለሆነ፤ በመዋቅሩ ደረጃ ችግሩን ለመቅረፍ መሠራት የሚኖርባቸውን ተግባራት ለማመላከትና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ በየኮሌጆቹ የሚገኙ ደቀ መዛሙርትም በፅናት ሆነው የተሐድሶ መናፍቃን ዓላማ ግቡን እንዳይመታ ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ ለማሳሰብ ነው፡፡

እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት እኩይ ተግባራቸውን ስለገለጡባቸው ተሐድሶ መናፍቃንም ተነካን በሚል የዋሃንን አስተባብረው ለመጮህ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ደግመን እንጠይቃለን መንፈሳዊ ኮሌጆችና €œደቀ መዛሙርት ምን እና ምን ናቸው?€ ይህንን የምንለው ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ተቀርፈው ኦርቶዶክሳውያን ደቀ መዛሙርት እንዲበዙና ወጥተውም በተማሩት ሙያ እንዲያገለግሉ የሚያ ደርግ ሥራ መሥራት እንደሚገባን ለማመልከት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የኢቢኤስ የቴሌቪዥን ሥርጭርቱ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገለጸ

ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ዝግጅቱን በኦን ላይን፣ በስልክ እና በአሜሪካ የማኅበረሰብ ቴሌቪዥኖች ማሠራጨቱን ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት /EBS/ አማካይነት የሚያቀርበው ሳምንታዊ የአንድ ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የተቋረጠበትም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጠቀሰው ማሠራጫ ጣቢያ አማካይነት በቤተ ክርስቲያኗ ስም ትምህርት የሚያስተላልፉትን አካላት ማንነትና ዓላማ አጣርቶ መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጥ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሚሠራጩ መርሐ ግብራት እንዲቆሙ በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ታቅፎ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ በመሆኑ የተጻፈው ደብዳቤ ይመለከተዋል ብሎ ባያምንም፤ አባቶች በጣቢያው አማካይነት የሚተላለፉትን መርሐ ግብራት ይዘትና ዓላማ በአግባቡ አጣርተው መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጡ ሥርጭቱን ማቆሙን መርጧል፡፡

በአስቸኳይ አገልግሎቱን ለመጀመር በሚችልበት ሁኔታም ከቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካላት ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በሀገር ውስጥና በተለይ በአረብ ሀገራት መርሐ ግብሩን በቀጥታ በኢቢኤስ ማሠራጫ ጣቢያ ሲከታተሉ የነበሩ ምእምናን በትእግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ፤ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ እስከሚጀምር ድረስ http://onlinetv.eotc.tv/ በስልክ አሜሪካ ለሚገኙ ምእመናን በ605-475-81-72፣ ካናዳ (604)-670-96-98፣ አውሮፓ (ጀርመን 0699-432-98-11፣ እንግሊዝ(ዩኬ) 033-0332-63-60 መከታተል እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

እኛም ሁኔታውን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ከኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደሚጀምር የኅትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ም/ክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ገለጹ፡፡

በNilesat, OBS /Oromiya broadcast Service/ ለሠላሳ ደቂቃ ዘወትር እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ረቡዕ ከጠዋቱ 12፡30-1፡00 ሰዓት የሚሠራጨው መርሐ ግብር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን ጠብቆ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲያውቁ እና ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ከእምነታቸው ለወጡ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩን ምክትል ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል በርካታ መጻሕፍት ታትመው እየወጡ በመሆናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የአፋን አሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ይህንን ለመከላከል ምእመናን ለማስተማር፣ እምነታቸውን ጠብቀው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ ምእመናንን የሚያንጹ በርካታ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን፣ የጸሎት መጻሕፍትንና መጽሔት በማሳተም፣ በኦሮምኛ ድረ ገጽ ጭምር ሲያሠራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም Dangaa Lubbuu/ የነፍስ ምግብ/ የተሰኘ መጽሔት በማሳተም ለምእመናን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡

በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉ መርሐ ግብሮችን በካናዳ ለማዳረስ በስልክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋፋት የሚያስተላልፋቸውን ዝግጅቶች በስልክ አማካይነት በካናዳ ለሚገኙ ምእመናን ማሠራጨት ጀመረ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ምእመናን ስለእምነታቸውና ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲያውቁ፣ በሃይማኖት እንዲጸኑ መረጃ በመስጠትና በማስተማር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚያሰራጫቸውን መርሐ ግብሮች በሰሜን አሜሪካ፣ በጀርመን እና በእንግሊዝ /UK/ በስልክ አማካይነት በማዳረስ ላይ ነው፡፡

ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ብቻ ሳይወሰን ቁጥሩን ወደ ዐራት በማሳደግ በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉት ዝግጅቶችን በቅርቡ በስልክ አማካይነት በካናዳ ማሠራጨቱን ቀጥሏል፡፡

በካናዳ የሚገኙ ምእመናን የስልክ አገልግሎቱን (604) 670 9698 በመደወል በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉም መረጃው ያመለክታል፡፡

sami.02.07

የጥቅምት 2008 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎት ተጀመረ

ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም

sami.02.07በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ተጀመረ፡፡

ምልዓተ ጉባኤው አስፈላጊና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

ስንክሳር፡- መስከረም ስድስት

መስከረም 6 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነብይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ዐረፈ፡፡

ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ፣ እሊህም ኦዝያን፣ ኢዮአታም፤ አካዝ፤ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው፡፡

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ እነሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል፡፡ እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወለወዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች፡፡

ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚያስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መስዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ፡፡

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በእግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ፡፡

በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰናክሬም ሠፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ አርበኞችን ገደለ፡፡ የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሱ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ፡፡

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ አንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው፡፡

ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ፣ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ፡፡ ይህን ከነገረው በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነብዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ፣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ፣ ዕንባህንም አየሁ፡፡ እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው፡፡

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለመመለሳቸው ትንቢት ተናገረ፡፡ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ፡፡

ክብር ይግባውና ስለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ፣ እንዲህም አለ፡፡ እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ፣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም፡፡

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በምናሴ ላይ ትንቢት ተናገረ፣ ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው፣ ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ፡፡

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል፡፡ እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና ጌታችን ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከሁላችን ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 23-25፡፡ 

ስንክሳር፡- መስከረም አምስት

መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም አምስት በዚች ቀን የከበረች ሶፊያ ከሁለት ልጆቿ አክሶስና በርናባ ከሚባሉት ጋር በሰማዕትንት ሞተች፡፡

ይችም ቅደስት አስቀድማ አረማዊ ነበረች፣ ወላጆቿም ጣዖታትን የሚያመልኩ ናቸው፡፡ እርሷም በልቧ አስተዋለች፣ መረመረችም፣ የወላጆቿ ሃይማኖት ከንቱ እንደሆነ ተረዳች፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ መኖፌ ኤጲስ ቆጶስ ሔዳ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ታመነች፡፡ እንዲህም አለችው፤ በሕያው አምላክህ አምኛለሁና አጥምቀኝ እርሱም ሃይማኖትን፣ የቤተ ክርስቲያንም ሕግ አስተማራት፡፡ ከዚህም በኋላ ከልጆቿ ጋር በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡

ከዚህም በኋላ የሀገር ሰዎች ለአማልእክት መስገድን ትታ ክርስቲያን እንደሆነች በገዢው በክላድያኖስ ዘንድ ወነጀሏት፡፡ ገዢውም ወደ እርሱ አስቀርቦ መረመራት፡፡ እርሷም ክብር ይግባውና በክርስቶስ አመነች እንጂ አልካደችም፣ ከልጆቿም ጋር ብዙ ሥቃይን አሠቃያት፡፡

በሥቃይም ውስጥ ላሉ ልጆቿ ታስታግሳቸውና ታጽናናቸው ነበር፣ እንዲህም ትላቸው ነበር፡፡ ልጆቼ ጠንክሩ፣ ጨክኑ የአንጌቤንዋን እመቤት ሶፍያን እመስላታለሁ፤ እናንተም ጲስጢስ፤ አላጲስ አጋጲስ የተባሉ ልጆቿን ምሰሉ፣ እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱላት፣ እናት ሆይ እኛ ፍለጋሽን እንከተላለንና ስለእኛ አትፈሪ ይህንንም በሚባባሉ ጊዜ ከእናታቸው ጋር ተሳሳሙ፡፡

ገዢውም ሲሳሳሙ አይቶ ደናግል ልጆቿ እንዲፈሩ እናታቸውን በጅራፍ ይገርፏት ዘንድ አዘዘ፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዶ እናታቸውን ከግርፋት ሲሠውራት አዩ፡፡

ዝንጉዎችም ይገርፏት ዘንድ ባራቆቷት ጊዜ በዚያን ሰዓት እንዲህ በማለት ትጮህ ነበር፡፡ ዓለሙን ሁሉ በፈጠረ በእውነተኛ አምላክ በእግዚአብሔር የማምን ክርስቲያናዊት ነኝ፣ ያን ጊዜም ገዢው ምላሷን ከሥሩ እንዲቆርጡ አዘዘ፡፡ እርሷ ግን መጮህንና መናገርን አላቋረጠችም፡፡

ከዚህም በኋላ ገዢው ወደ እሥር ቤት እንዲወስዷት አዘዘ፤ ትሸነግላትም ዘንድ ሚስቱን ወደእርሰዋ ላከ፡፡ እርሰዋ ግን ምንም አልመለሰችላትም፡፡ ራሷንም በሰይፍ ይቆርጧት ዘንድ አዘዘ፤ የድል አክሊልም ተቀበለች፡፡ አንዲት ሴትም መጥታ ሥጋዋን በጭልታ ወሰደች፣ ወደ ቤቷም አስገብታ በፊቷ መብራትን አኖረች፡፡

ከዚህም በኋላ ልጆቿን ጠርቶ እሺ ይሉት ዘንድ አስፈራራቸው፣ እምቢ ባሉትም ጊዜ እያከታተለ ራሳቸውን አስቆረጠ፣ ምሥክርነታቸውንና ተጋድሏቸውንም ፈጸሙ፡፡ ከመቃብራቸውም በሽታውንና ደዌውን ሁሉ የሚፈውሱ ብዙ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ደግ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ የቅዱሳት ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወደ ቁስጥንጥንያ አፍልሶ ወሰደ፡፡

የሶፍያንና የልጆቿን ዜና ከመስማቱ በፊት ታላላቅና ሰፊ የሆኑ ቤቶች እንዲሠሩ በላይዋም ይቺ ቤት የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ናት ብለው ጽሑፍ እንዲቀርጹበት አዘዘ፡፡ እነርሱም ንጉሡ እንዳዘዘ ወደ ማታ ሲሆን ይጽፋሉ፣ የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ ያንን ደምስሶ ይቺ ቤት የሶፍያ ናት ብሎ ይጽፋል፡፡ የሕንፃውም ባለሙያዎች የሚያደርጉትን አጡ፣ መጻፋቸውንም ተዉ፡፡

በአንዲት ቀንም የንጉሥ ልጅ ብቻውን ሲጫወት መልአክ ተገለጸለትና የዚች ቤት ስሟ ማነው አለው፡፡ ሕፃኑም አላወቅሁም አለው፣ መልአኩም ሁለተኛ እንዲህ አለው አባትህን የሶፍያ ቤት ብለህ ሰይማት ብለህ ንገረው ሕፃኑም ተመልሼ እስክመጣ ትጠብቀኛለህን አለው፣ መልአኩ አዎን እጠብቅሃለሁ አለው፡፡

አባቱም ይህን ሰምቶ መልአክ እንደሆነ ዐወቀ፡፡ ሕፃኑንም በመጠበቅ ምክንያት ያ መልአክ ከዚያች ቦታ እንዳይሄድ ብሎ ንጉሡ ልጁን ገደለው፡፡ መልአኩም ሕፃኑን እየጠበቀ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡

የዚያች ቤተ ክርስቲያም ርዝመቷ ሰባት መቶ ዘጠኝ ክንድ ሆነ፣ አግድመቷም ሦስት መቶ ሰባት ክንድ፣ ምሰሶዎቿም ዐራት መቶ፣ ጠረጴዛዎቿም ስምንት፣ የሚያበሩ ዕንቁቿ ዐራት ናቸው፣ ከአጎበሩ በላይ የተቀረጹ ኪሩቤልም በየሁለት ክንፎቻቸው የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ታቦት ይጋርዳሉ፡፡

ሥጋቸው በውስጡ ያለበትን የቅድስት ሶፍያንና የልጆቿን ሳጥን በታላቅ ምስጋናና ክብር ወደዚያ አስገብተው አኖሩ፡፡

በድኖቻቸውን የሰበሰበች ያቺንም ሴት ከእርሳቸው ጋር ቀበሯት፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ከመስከረም እስከ የካቲት፣ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማሳተሚያ ደርጅት፣ 1994 ዓ.ም፣ ገጽ 20-21፡፡

01awropa

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥንና የሬድዮ ሥርጭት በአውሮፓ በስልከ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም

01awropaማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን እንዲሁም በሬድዮ አያሰራጨ የሚገኘውን መንፈሳዊ መርሐ ግብር በአውሮፓም ምእመናን ባሉበት ሆነው በቀላሉ በስልክ ሥርጭቱን መከታተል እንዲችሉ ማድረጉን የአውሮፓ ማእከል አስታወቀ፡፡

በዚህም መሠረት በጀርመን የሚገኙ ምእመናን በ0699-432-98-11 ፣በእንግሊዝ /UK/ 033-032-63-60 በመደወል  መከታተል እንደሚችሉ ከማእከሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በሰሜን አሜሪካም በተመሳሳይ ሁኔታ የቴሌቪዥንና የስልክ አገልግሎት መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥርጭት በስልክ የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ

ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘጋጀ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጨው መርሐ ግብር በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን በቀላሉ በተመቻቸው ጊዜ ስልክ ደውለው የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ምእመናን 605-475-8172 ስልክ ቁጥር በመጠቀም በተመቻቸው ጊዜ መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉ በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎቱ የሚሠራው በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሲሆን በቅርቡ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲኖር ማኅበረ ቅዱሳን በመሥራት ላይ ይገኛል::