ለካህናት የዐቅም ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

በደሴ ከተማ ቤተ ክህነት፤ በማኅረ ቅዱሳን ደሴ ማእከልና ደሴ ወረዳ ማእከል አስተባባሪነት ሚያዚያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ደሴ ከተማ ለሚገኙ ከሰባ በላይ ለሚደርሱ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የአንድ ቀን ስልጠና ተሰጠ፡፡

ስልጠናው የተዘጋጀበትን ዓላማ የደሴ ከተማ ቤተ ከህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር ቆሞስ አባ ለይኩን ወንድይፍራው ሲገልጹ በከተማው ከዐሥር በላይ አብያተ ክርስቲያናት እና በርካታ ካህናት ስለሚገኙ በዞን ከተማነቱም ለምዕራብ ወሎ እና ለሌሎችም አጎራባች አካባቢዎች መጋቢ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የካህናትን አቅም በሥልጠና ማገዝ እያጋጠሙን ባሉት ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ መወያየት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መርሐ ግብሩ እንደተዘጋጀ ገልጸዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው ሥልጠና ትምህርተ ኖሎት፤ የካህናት ሚና ከቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች እና ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በሚል ርእስ ቤተ ክርስቲያን ከውጭ እና ከውስጥ እያገጠሟት ባሉ ፈተናዎች እና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም የካህናት ድርሻ ምን መሆን አለበት በሚሉት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት በንስሓ ልጆች አያያዝ ዙሪያ እያጋጠሟቸው ስላሉ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው፣ ዐሥራት አለመክፈል በቤተ ክርስቲያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት፣ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ አሁን ያለበት ደረጃ፣ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች እያጋጠማቸው ስላሉ ፈተናዎች እና ሌሎችም ቤተ ክርስቲያንን ከውጭና ከውስጥ እያጋጠሟት ስላሉ ፈተናዎች እና መፍትሔዎቻቸው በማንሳት የጉባኤው ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

ለአብነት ተማሪዎች የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከደሴ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን ደሴ ማእከል የቅዱሳት መካናት ማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል አስተባባሪነት በሰሜን ወሎ ደላንታ እና መሀል ሳይንት ለሚገኙ የአብነት ተማሪዎች የአልባሳት ድጋፍ ተደረገ፡፡

በነዚህ ወረዳዎች ብዛት ያላቸው የአብነት ተማሪዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የሆነውን የአልባሳት ችግር ለመቅረፍ ከማእከሉ አባላት፣ ከግቢ ጉባኤያት እና ከምእመናን አልባሳትን በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጉን ማእከሉ ገልጿል፡፡

ማእከሉ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የአብነት መምህራንና ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ለመቅረፍ ጊዜያዊ እና ቋሚ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ ትምህርት፣ በጤና አጠባበቅ እና በአልባሳት ከሚደረጉ ድጋፎች በተጨማሪ ለዘጠኝ (9) የአብነት መምህራን ለእያንዳንዳቸው ብር 200.00 ወርሃዊ ድጎማ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለአንድ የአብነት ት/ቤትም ቋሚ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ማእከሉ ገልጿል፡፡

 

በሊቢያ ለተሠዉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የመታሰቢያ ጉባኤ ተካሄደ

ግንቦት 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ(ከጎንደር ማእከል)

በሊቢያ ለተሠዉ 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በጎንደር ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ለ3 ቀናት የቆየ የመታሰቢያ ጉባኤ ተካሄደ፡፡

ጉባኤውን ያዘጋጁት የጎንደር ከተማ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ በማኅበረ ቅዱሳን የጎንደር ማእከል እና የጎንደር ከተማ የጥምር መንፈሳዊ ማኅበራት በጋራ በመተባበር ሲሆን፤ ከሚያዚያ 24 – 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉባኤው ተካሂዷል፡፡

ጉባኤው የተጀመረው ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከ7፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፤ ለሦሰት ቀናት በቆየው ጉባኤ በሰባኪያነ ወንጌል ትምህርት፤ ሰማዕታቱን የሚዘክሩ መነባንብ፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ፤ ከምእመናን ለቀረቡ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተ ክረስቲያን መልስ፤ መዝሙር በጎንደር ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት እና በተጋባዥ መዘምራን፤ የጧፍ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በተያያዘ ዜና የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በሊቢያ ለተሠዉት 30 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የከተማው ምእመናን በተገኙበት ሚያዚያ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በርዕሰ አድባራት አደባባይ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎላቸዋል፡፡ በዕለቱም 30 ሻማዎች በርተዋል፡፡

001sinoddd

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

001sinoddd

ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በጸሎት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲካሔድ ቆይቶ ዛሬ ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ተጠናቅቆ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ላይ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡

ከሁለቱ አንዱ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ የሚውለው የርክበ ካህናት ጉባኤ ነው፡፡

በመሆኑም የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶአል፡፡

በመቀጠልም ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባን በጸሎትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ ሰንብቶአል፡፡ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችንም አስተላልፎአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለዐራት ቀናት ያህል ባካሄደው ቀኖናዊ ጉባኤ፡-

-ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፣

-ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፣

-ከሀገር ውጭ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት መጠበቅ የሚያስችሉትን ርእሰ ጉዳዮች በማንሣት በስፋትና በጥልቀት አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1.ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በጉባኤ መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ የሀገራችን ዕድገትንና የሰላም አስፈላጊነት በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

2.ምልአተ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ መግለጫ ሪፖርት አዳምጦ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡

3.ምንም ጥፋትና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሽባሪዎች ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

4.እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በሊቢያ የተሠውት 21 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በሁሉቱም አብያተ ክርስቲያኖች ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለሆነ፣ የሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

5.በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም እርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ኃላፊነቱን ወስዶ በንቃትና በትጋት እንዲሠራ ጉባኤው ወስኖአል፡፡

6.ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አምስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኗን ቅዱስ ሲኖዶስ አውስቶ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት እንድትተጋ ጉባኤው መልእክቱን አስተላልፏል፡፡

7.ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት ተጭኖአት ከቆየ የድህነት አረንቋ በተጨማሪ የእርስ በእርስ ግጭት ጥሎባት ባለፈ ጠባሳ ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም በተገኘው ሰላም ምክንያት ባሳለፍናቸው ዓመታት እየታዩ ያሉ የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላምን ጠቃሚነት ከምንም ጊዜ በላይ መገንዘብ የተቻለበት ስለሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ሰላሙንና አንድነቱን አጽነቶ በመያዝ ሀገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ጥቃት ነቅቶ እንዲጠበቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ያሳስባል፤

8.ሀገራችን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የካፒታል እጥረት እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ሠርቶ የመበልፀግ ግንዛቤ ማነስ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማናቸውም መመዘኛ ከሌላው የተሻለች እንደሆነች የታወቀ ስለሆነ፤ ወጣቶች ልጆቻችን ወደ ሰው ሀገር እየኮበለሉ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ በሀገራቸው ሠርተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ኅብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በሰፊው እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል፤

9.ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን ችግሮች ቁልፍ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ልማትን በማጠናከርና ዕድገትን በማረጋገጥ ድህነትን ማስወገድ ስለሆነ ሕዝባችን ይህን ከልብ ተቀብሎ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እኩል ለማሰለፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርቦሽ ለማሳካት በርትቶ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

10.በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያ ክርስቲያናት በየቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ሁሉ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎአል፡፡

11.በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የእርቀ ሰላም ድርድር ለሀገራችን ልማትና ለሕዝባችን አንድነት የሚሰጠው ጥቅም የማይናቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችን በር ለሰላምና ለእርቅ ክፍት መሆኑን ምልዓተ ጉባኤው ገልጿል፡፡

12.ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

001jimaa

የጅማ ማእከል የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እንደሚያካሄድ ገለጸ

ሚያዝ 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

በጅማ ማእከል

001jimaaበማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል ሁለተኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊሙ ኮሳ ወረዳ ቤተ ክህነት በምትገኘው ጥንታዊና ታሪካዊ በሆነችው ኮሳ ቅደስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንደሚያካሄድ ገለጸ፡፡

የኮሳ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከጅማ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የትኬቱ ዋጋ ምሳን ጨምሮ 150፡00 ብር መሆኑን ማእከሉ ገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የወንጌል ትምህርት በተጋባዥ መምህራን፤ ያሬዳዊ ወረብ እና ቅኔ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ምክረ አበው /ከምእመናን ለሚጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥበት/፤ ያሬዳዊ ዝማሬ በማእከሉ መዘምራን፤ በተጋባዥ ዘማርያንና በአጥቢያው ሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ይቀርባል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፤ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች፤ የሊሙ ሰቃ፤ የሊሙ ኮሳ፤ የአጋሮና ቀርሳ እንዲሁም የጅማ ከተማ ምእመናን በመርሐ ግብሩ ላይ ይሳተፈሉ ሲል ማእከሉ አስታወቋል፡፡

ጥያቄ ለመጠየቅ ለሚፈልጉ ምእመናን በሚከተለው የኢሜል አድራሻ መላክ እንደሚችሉ ማእከሉ አሳስቧል፡፡

jimmamkhh2@gmail.com ወይም aynisha5@gmail.com

001deb

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ያስገነባው መንበረ ጵጵስና እና ጽ/ቤት ተመረቀ

ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

001deb002deb

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባው ለመንበረ ጵጵስና እና ለጽ/ቤት አገልግሎት የሚውል ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሚያዝያ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡

በሀገረ ስብከቱ የተገነባውን ሕንፃ ለመመረቅ ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎች ከአዲስ አበባ ወደ በደብረ ብርሃን ሲመጡ በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የሃያ ዘጠኝ ወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የዞኑ እና የከተማው የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ እንዲሁም የደብረ ብርሃን ከተማ ምእመናን አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

003deb004deb

ቅዱስነታቸው ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ሕንፃውን ከመረቁ በኋላ አገልግሎት የሚሰጡትን ክፍሎች በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤፍሬምና በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እየተመሩ ጎብኝተዋል፡፡

በዐፄ ዘርዓያዕቆብ ደባባይ በተከናወነው መርሐ ግብር ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት በደብረ ብርሃን ከተማ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሚያስደስቱ ናቸው፡፡ ከመንበረ ጵጰስናው ግንባታ በተጨማሪ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ደባባይ እየተገነባ የሚገኘው ባለ 5 ፎቅ ሕንፃም ሀገረ ስብከቱ ለሚያከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ተጨማሪ ሀብት የሚያስገኝ በመሆኑ ሌሎችም አህጉረ ስብከቶች ከዚህ ልማት ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አባ ዘውዱ በየነ ባቀረቡት ሪፖርት በሀገረ ስብከቱ 29 ወረዳ ቤተ ክህነት፤ 2000 አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ የገለጹ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ360 በላይ አብያተ ክርስቲያናት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ በኋላ እንደታነጹ አብራርተዋል፡፡

006deb005deb

ለካህናት ሥልጠና በመስጠት፤ የሰበካ ጉባኤ ክፍያን በማሳደግና በማሰባሰብ፤ ስብከተ ወንጌል በማስፋፋት፤ መምህራንን በማፍራትና በመመደብ፤ በአረንጓዴ ልማት፤ በደብረ ብርሃን ሥላሴ ሰባት መምህራንን በመመደብ በአብነት ትምህርት በርካታ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት፤ የካህናት ደዝን በማሳደግ ሀገረ ስብከቱ አገልግሎቱን በማፋጠን ላይ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በንግድ ማእከላት አካባቢ በመሆኑና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ባለማስቻሉ ሌላ ባለ ሁለት ፎቅ መንበረ ጵጵስና እና ጽ/ቤትን አጠቃሎ የያዘ ሕንፃ በመገንባት ለዛሬው ምረቃ መብቃቱን ያብራሩት ሥራ አስኪያጁ ባለ አምስት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ በሪፖርታቸው ከተዳሰሱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል ተጀምሮ፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ወረብ፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ መዝሙር፤ በደብረ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ቅኔ ቀርቧል፡፡

010de009deb

100sinodoss

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎት ተጀመረ

ሚያዝያ 27 ቀን 2007ዓ.ም

100sinodossበዓመት ሁለት ጊዜ የሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ዛሬ ሚያዝያ 27 ቀን 2007ዓ.ም. ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ተጀመረ፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕትነት በመጽሐፈ ስንክሳር

ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ አመ ዕሥራ ወሠሉሱ ለሚያዝያ በዛቲ ዕለተ ኮነ ፍጻሜ ስምዑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ዐቢይ ወክቡር ዘተሰምየ ፀሐየ ወኮከበ ጽባሕ፡፡

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ፡፡

የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው፡፡ ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል፡፡ ከቀጰዶቅያ አገር ነው፡፡ የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍልስጥዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ፡፡

ሃያ ዓመትም በሆነው ጊዜ የአባቱን ሹመት ሊቀበል ወደ ንጉሥ ዱድያኖስ ዘንድ ሔደ፡፡ ንጉሡም ጣዖትን እንዲአመልኩ ሰዎችን ሁሉ ሲያስገድዳቸው አገኘው፡፡

ይህንንም አይቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እጅግ አዘነ በእርሱ ዘንድ ያለውን ገንዘቡን ሁሉ ለድኆች፣ ለምስኪኖች ሰጠ ባሮቹንም ነፃ አወጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላ በንጉሥ ፊት ቁሞ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ፡፡ ንጉሡም አባበለው ብዙ ቃል ኪዳንም ገባለት እርሱ ግን አልተቀበለውም፡፡

ለመስማት እንኳ የሚያስጨንቅ ሥቃይን አሠቃየው ጌታችን ግን ያጸናዋል ቍስሉንም ያድነዋል ሦስት ጊዜም እንደሚሞት እርሱም እንደሚአስነሣው በአራተኛውም የምስክርን አክሊልን እንደሚቀበል ነገረው፡፡ ቃል ኪዳንም ሰጠው ስሙ በዓለሙ ሁሉ የተገለጠ ይሆን ዘንድ በተጋድሎና መከራ በመቀበልም ጽኑዕ በሆነ ሥቃይም ሰባት ዓመት እንደሚኖር መላእክትም እንደሚአገለግሉት ነገረው፡፡

ንጉሡም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለመታዘዙና ባለመመለሱ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም አትናስዮስ የሚባል ታላቅ ሥራየኛ አመጣ፡፡ እርሱም መርዝን ቀምሞ በጽዋ መልቶ አስማት ደግሞ እንዲጠጣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው፡፡ ወዲያውኑ የሚሞት መስሎት ነበር፡፡ ቅዱሱም ያንን ጽዋ ጠጣው ምንም ጉዳት አልደረሰበትም፡፡

ያ መሠርይም በክብር ባለቤት በጌታ በኢየሱስ አምኖ በሰማዕትነት ሞተ፡፡ ከእርሱም ጋር ሌሎች ብዙዎች ሰዎች በሰማዕትነት ሙተው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ ቁጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ሰባት መቶ ነፍስ ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም በዱድያኖስና በሰባ ነገሥታት ፊት በቆመ ጊዜ በዚያም የተቀመጡባቸው የዕንጨት ወንበሮች ነበሩ፡፡ ቅዱሱንም እሊህን የተቀመጥንባቸውን ወንበሮች እንዲበቅሉ እንዲአብቡና እንዲአፈሩ ታደርጋቸው ዘንድ ከአንተ እንሻለን አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ ጸለየ እንዳሉትም አደረጋቸው ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው ቍጥር የሌላቸው ብዙ አሕዛብ በጌታችን አመኑ፡፡

ከዚህም በኋላ ቅዱሱን ወስደው በጐድጓዳ ብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት፡፡ አቃጥለው አሳርረውም ሥጋውንና ዐጥንቱን ፈጭተው አመድ አድርገው ከረጅም ተራራ ላይ በተኑት፡፡ ጌታችንም ነፍሱን ወደ ሥጋው መልሷት ደግሞ አስነሣው፡፡ ወደ ነገሥታቱም ተመልሶ በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ስም ሰበከ፡፡ ቍጥር የሌላቸው አሕዛብ አይተው አደነቁ በጌታችንም አምነው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡

ነገሥታቱም ደግመው ሙታኖችን ብታሥነሣ አምላክህ ዕውነተኛ አምላክ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በእርሱም እናምናለን አሉት፡፡ ቅዱሱም ጸለየ ከጒድጓድም ውስጥ ወንዶችና ሴቶችን ጐልማሶችንም አስነሣላቸው እነዚያም በክብር ባለቤት በጌታችን ስም አስተማሩ የገሀነምንም ወሬ ተናገሩ ጥምቀትንም ተቀብለው ተመልሰው ዐረፉ፡፡

ከሀድያን ነገሥታት ግን ሙታንን ያስነሣህ አይደለም የረቀቁ ሰይጣናትን አሳየህ እንጂ ብለው ተከራከሩ፡፡ ከዚያም ከጭንቀታቸው ብዛት የተነሣ ከአንዲት ድኃ ሴት ዘንድ አስጠበቁት እርሷም እንጀራ ልትለምንለት ወጣች የእግዚአብሔርም መልአክ በላዩ ከበጎ ነገር ሁሉ የተመላ ማዕድን አቀረበለት፡፡ የዚያች መበለትም የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍን አበቀለ ታላቅ ዛፍም ሆነ፡፡

ያቺም መበለት በተመለሰች ጊዜ የቤቷ ምሰሶ ቅርንጫፍ አብቅሎ ታላቅ ዛፍ እንደሆነ ስለ ማዕዱም ይህን ታላቅ ምልክት አይታ የክርስቲያኖች አምላክ ሰው ተመስሎ ወደ እኔ መጣ አለች፡፡ ቅዱስም እኔ አምላክ አይደለሁም፡፡ የአምላክ ባሪያ ነኝ እንጂ አላት፡፡ እርሷም እንዲህ ብላ ለመነችው የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ቸርነትህ እንድትደርሰኝ እለምንሃለሁ፡፡ ዕውር ደንቆሮ ዲዳ ጐባጣ የሆነ ልጅ አለኝና ታድንልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡ ስለ ጌታችን እምነትም አስተማራትና በመስቀል ምልክት አማተበው ያን ጊዜም አየ፡፡ ቅዱሱም በሌላ ጊዜ እንዲሰማ እንዲናገርና እንዲሔድ እንዲአገለግለኝም እኔ እሻለሁ አላት፡፡

በዚያን ጊዜ ንጉሡ በአገሩ ሜዳ ውስጥ ሲዘዋወር ያቺን ዛፍ አይቶ አደነቀ ስለ እርሷም ጠየቀ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእርሷ ዘንድ የተቀመጠባት የዚያች መበለት የቤቷ ምሰሶ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ንጉሡም ተቆጣ ቅዱሱንም ከዚያ ወስዶ አስገረፈው በመንኰራኵርም አበራዩት ሙቶም ከከተማ ውጭ ጣሉት ጌታም ከሞት አስነሣው ወደ ነገሥታቱም ተመለከተ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ ስለ ሕይወቱም አደነቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ይሸነግለው ዘንድ ጀመረ በመንግሥቱ ላይም ሁለተኛ ያደርገው ዘንድ ቃል ገባለት ቅዱስ ጊዮርጊስም እየዘበተበት ነገ በጥዋት ለአማልክቶችህ መሥዋዕትን አቀርባለሁ አንተም ሕዝቡ እንዲሰበሰቡ እዘዝ እኔ ስሠዋ እንዲአዩ አለው፡፡ ንጉሡም ዕውነት የሚሠዋ መስሎት ደስ አለው ወደ ቤተ መንግሥቱም እልፍኝ አስገብቶ አሳደረው፡፡

ለጸሎትም ተነሣ የዳዊትንም መዝሙር አነበበ የዱድያኖስ ሚስቱ እለስክንድርያ ንግሥት ሰምታ ቃሉ ደስ አሰኛት የሚያነበውንም ይተረጒምላት ዘንድ ለመናቸው፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ሰው እስከሆነበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ ሊያስረዳትና ሊያስገነዝባት ጀመረ፡፡ ትምህርቱም በልቡዋ ተቀርጾ በክብር ባለቤት በጌታችን አመነች፡፡

በማግሥቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአማልክት ሲሠዋ ለማየት ሰው ሁሉ እንዲሰበሰብ ዐዋጅ ነጋሪ ዞረ የቤቷን ምሰሶ ያበቀለላት ያቺ መበለት ሰምታ ዕውነት መስሏት እጅግ እያዘነች ልጅዋን ተሸክማ እያለቀሰችም ወጣች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስም በአያት ጊዜ ፈገግ አለ ልጅሽን በምድር ላይ አኑሪው አላት፡፡ ከዚያም ልጅዋን ጠርቶ ወደ አጵሎን ሒድ ወደእኔም ይመጣ ዘንድ በክብር ባለቤት በጌታዬ ኢየሱስ ስም እዘዘው አለው፡፡ ያን ጊዜ ያ ልጅ ድኖ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳዘዘው ወደ ጣዖቱ ቦታ ሒዶ አዘዘው፡፡ በጣዖቱ ያደረ ያ ርኵስ መንፈስም ከማደሪያው ወጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አለት መጥቶ እኔ ሰውን ሁሉ የማስት እንጂ አምላክ አይደለሁም ብሎ በሕዝቡ ሁሉ ፊት አመነ፡፡ ቅዱሱም ትውጠው ዘንድ ምድርን አዘዛትና ወዲያውኑ ዋጠችው ጣዖታቱንም ከአገልጋዮቻቸው ጋራ አጠፋቸው ንጉሡም ከወገኖቹ ጋር ዐፈረ፡፡

ብስጭትና ቁጣንም እንደተመላ ወደ ንግሥት ሚስቱ ዘንድ ገባ፡፡ እርሷም አምላካቸው ጽኑዕና ኃያል ነውና ክርስቲያኖችን አትጣላቸው አላልኩህምን አለችው፡፡ ይህንንም ከእርስዋ ሰምቶ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጣ ወደ ክብር ባለቤት ክርስቶስ እምነት የከበረ ጊዮርጊስ እንደአስገባት አወቀ፡፡

ከዚህም በኋላ ከከተማ ውጭ እንዲጐትቷትና በመጋዝም እንዲሰነጥቋት አዘዘ፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለች፡፡

በዚያም ጊዜ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሥራ ነገሥታቱ ሁሉም ደነገጡ ኀፍረት ደግሞ እንዳይጨምርባቸው ከእርሱም እንዲአርፍ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ እንዲጽፍ ንጉሥ ዱድያኖስን መከሩት፡፡

ያን ጊዜም የክቡር ጊዮርጊስን ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ፡፡ ድል አድራጊ ጊዮርጊስም እጅግ ደስ አለው፡፡ እሳት ከሰማይ አውርዶ ሰባውን ነገሥት ያቃጥላቸው ዘንድ መከራውም ከክርስቲያን ወገን ጸጥ ይል ዘንድ ጌታችንን ለመነው፡፡ ወዲያው እሳት ወርዶ ከሠራዊታቸው ጋር ሰባውን ነገሥታት አቃጠላቸው፡፡

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተገልጾ ብዙ ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ በምድር መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ እኔ ኃጢአቱን ሁሉ እደመስሳለሁ በመከራም ውስጥ ሁኖ በባሕርም ሆነ በየብስ ወይም በደዌ በስምህ የሚለምነኝን እኔ ፈጥኜ ከመከራው አድነዋለሁ፡፡ ይህንንም ጌታችን ተናግሮ በክብር ወደ ሰማይ ወጣ፡፡

ከዚህ በኋላ ራሱን ዘንበል አድርጎ በሰይፍ ቆረጡት በመንግሥተ ሰማያት አክሊላትን ተቀበለ፡፡ ከአገልጋዮቹም የቀሩት ሥጋውን ወስደው በልብስ ጠቀለሉት ወደሀገሩ ልዳም ወሰዱት፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሠርተው በውስጥዋ አኖሩት ከእርሱም ቍጥር የሌላቸው ብዙዎች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ጊዮርጊስም በረከቱ ረድኤቱ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ከሥጋና ከነፍስ መከራ ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን፡፡

ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 20

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

ስለ ሰማዕታት፤ ስለ አማንያን፤ ስለ ከሃድያን

ቍ.744፡- ብፁዕ ኤጲስ ቆጶስ ያዕቆብና ቅዱስ እስጢፋኖስ በእኛ ዘንድ የከበሩ እንደሆኑ ሰማዕታት በእናንተ ዘንድ የከበሩ ይሁኑ፡፡ እነዚህም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ትሩፋታቸውም የማይገኝ ነው፡፡

ቍ.747፡- ሰማዕታትም እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው ግን እኔም በሰማይ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው እነዚህ ናቸው፡፡/ማቴ.10፤32/ በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ አሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡

ቍ.748፡- ሰማዕታትን ከሚረዱዋቸው ወገን አንዱ መከራ ቢያገኘው ብፁዕ ነው፡፡ እርሱ የሰማዕታት ተባባሪያቸው ነውና፡፡ በመከራዎቹም ክርስቶስን መስለው እኛንም ከካህናት ብዙ መከራ አገኘን፡፡ ከእነርሱም ዘንድ ደስ እያለን ወጣን፡፡ ስለመድኃኒታችን ስለ ክርስቶስ መከራን እንቀበል ዘንድ አድሎናልና፡፡ /የሐዋ. 5፤41/ እናንተም እንደዚህ መከራ በተቀበላችሁ ጊዜ ደስ ይበላችሁ፡፡ እናንተ በፍርድ ቀን ትመሰግናላችሁና፡፡

ቍ.749፡- ስለሃይማኖት የሚያሳድዷቸውን ስለጌታችን ትእዛዝ ከአገር ወደ አገር የሚሸሹትን ተቀበሏቸው፤ አሳርፏቸውም፤ ጥቀሟቸውም፤ እንደ ሰማዕታትም አድርጋችሁ አክብሯቸው፡፡ በተቀበላችኋቸውም ጊዜ እናንተ ደስ ይበላችሁ፡፡ ጌታ ክርስቶስ ስለ እኔ ባሳደዷችሁ ጊዜ እናንተ ብፁዓን ናችሁ፤ ፈጽሞ ደስ ይበላችሁ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና፡፡ እንደዚሁም ከእናንተ አስቀድመው የነበሩ ነቢያትን አሳደዷቸው፡፡ እኔን ካሳደዱ ግን ዳግመኛ እናንተን ያሳድዷችኋል፡፡ ከዚች አገር ቢያሳድዷችሁ ወደ ሌላይቱ አገር ሂዱ ብሏልና፡፡ /ማቴ. 5፤11-12፣ ማቴ. 10፤23/

ቍ.750፡- ዳግመኛም እንዲህ አለ፤ በዚህ ዓለም መከራና ኀዘን ያገኛችኋል፡፡ ወደ አደባባይ ያገቧችኋል፡፡ ለእናንተ ምስክር ሊሆንላችሁ ስለ እኔ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ያደርሷችኋል፡፡ እስከ መጨረሻው የታገሠ እርሱ ይድናል፡፡ ለክርስቶስ እንዳልሆነ የሚክድ ከእግዚአብሔርም ይልቅ ፈጽሞ ራሱን የወደደ ሰው ግን ይቅርታን አያገኝም፡፡ የእግዚአብሔር ጠላት የሰዎች ወዳጅ ሊሆን ወድዷልና፡፡ ስለተባረከችውም መንግሥት ፈንታ የዘለዓለም እሳትን ወድዷልና፡፡ /ማቴ. 10፤17-23/ ስለእርሱም ጌታችን በሰው ፊት የካደኝን ስሜንም የለወጠውን እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት እክደዋለሁ፡፡ እለውጠዋለሁም አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤8-9/

ቍ.751፡- እንደዚህም ለእኛ ለደቀ መዛሙርቱ ከእኔ ይልቅ አባቱንና እናቱን ወይም ወንድ ልጁንና ሴት ልጁን የሚወድ እኔን አይመስለኝም፡፡ የሞቱንም መከራ ተሸክሞ ያልተከተለኝ እኔን አይመስለኝም አለ፡፡ ሰውነቱን የሚወድ ይጣላት፤ ሰውነቱን የጣላ ግን በእኔ ዘንድ ያገኛታል፡፡ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱን ካጣ ምን ይጠቅመዋል? ሰው ለነፍሱ ቤዛ ምን በሰጠ ነበር፡፡ /ማቴ. 10፤37-39፣ ማቴ. 16፤22-27/ ዳግመኛም ሥጋችሁን የሚገድሉትን ሰዎች አትፍሯቸው፡፡ ነፍሳችሁን ግን መግደል አይቻላቸውም፡፡ ነፍስና ሥጋን አንድ አድርጎ በገሃነም እሳት መቅጣት የሚቻለውን ፍሩት እንጂ አለ፡፡ /ሉቃ. 12፤4-5፣ ማቴ. 10፤28/

ቍ.754፡- ብንጨነቅም ኃላፊውን ዘመን ስለመፍራት ሃይማኖታችንን አንለውጥ፡፡ አንዱስ እንኳ አለኝታውን ቢክድ ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለጥቂትም ዘመን ከሚሆነው ሞት የተነሣ ቢፈራ ድኅነት በሌለበት በጸና ደዌ ነገ ቢያዝ ከዚች ሕይወት የተለየ ይሆናል፡፡ የወዲያውንም ዓለም ያጣል፡፡ ልቅሶ፤ ጥርስ ማፋጨት ባለበት በጨለማ ውስጥ ለዘለዓሙ ይኖራል፡፡ /ማቴ. 8፤13/

ቍ.755 እና 756፡- ያልተጠመቀ ሰውም ልቡ አይዘን፡፡ ስለ ክርስቶስ የተቀበለው መከራ የተመረጠ ጥምቀት ይሆንለታልና፡፡ የሞቱን ምሳሌ በተቀበለ ጊዜ በጌታ አምሳል ሞቷልና፡፡ ሁለት ልብ አይሁን፡፡ እነርሱ ቢገድሉት እርሱም ቢገደል ይጸድቃልና፤ በደሙ ብቻ ተጠምቋልና፡፡

ቍ.761፡- በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ደማቸውን ላፈሰሱ ሁሉ ባረፉበት ቀን መታሰቢያቸውን ያድርጉላቸው፡፡

ቍ.765:- በሰማዕታት በዓል የሚሰበሰቡትን ሰዎች የሚንቃቸው ሰው ትዕቢትን የተመላ ነውና የተወገዘ /የተለየ/ ይሁን፡፡

ቍ.766፡- ምእመናን የክርስቶስን ሰማዕታት ትተው ዓላውያን ሰማዕታ ወደሚሏቸው ቦታ መሄድ አይገባቸውም፡፡ ስለ ክርስቶስ ፍቅር መጋደላችን እንዴት መሆን እንደሚገባው እነሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጻፈ፤ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንዲህ አለ፤ የክርስቶስን ፍቅር ማን ያስተወናል? መከራ ነውን፤ እስራት ነውን፤ ስደት ነውን ረሃብ ነውን፤ መራቆት ነውን መጣላት ነውን፤ ሰይፍ ነውን፤ ስለአንተ ዘወትር ይገደላሉና እንደሚታረዱም በጎች ን ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ የወደደን በመውደዳችን እኛ ድል እንነሳለን፤ እኔም ሊለየኝ የሚችል እንደሌለ አምናለሁ፡፡ ሞት ቢሆን፤ ሕይትም ቢሆን፤ መላእክት ቢሆኑ፤ አለቆችም ቢሆኑ፤ አሁን ያለውም ይመጣም ዘንድ ያለው ሥራ ሁሉ ቢሆን ኃይለኞችም ቢሆኑ፤ ላይኛውም ቢሆን፤ ታችኛውም ቢሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየኝ አይችልም፡፡ /ሮሜ. 8፤35-39/

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? (ሮሜ 8፡35)

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

መጽሐፍ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ የሚነግረንን የሰውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ስንመለከት ጎልተው የሚወጡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ታላቅ በጎ ሃሳብና ልዩ አባታዊ ቸርነት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጆች ለዚህ አምላካዊ ጥሪና ቸርነት የሚሰጡት የአጸፌታ መልስ ነው፡፡ የሰዎች አጸፌታዊ መልስም ሁለት ዓይነት ነው፡፡ ይህም ጥቂቶቹ ለአምላካቸው በጎ ምላሽ ሲሰጡ ቀሪዎቹ (በታሪክ ሲታይ ብዙዎቹ) ለአምላካቸው መታዘዝን እምቢ ማለታቸውንና ማመጻቸውን ነው፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ የሚያሳየን ከመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ የዲያብሎስን የጎዮንሽ ክፉ ምክር ሰምተው በአምላካቸው ላይ ሲያምጹ፣ ከዚያም የተነሣ ከጸጋ ተራቁተው በራሳቸው ላይ ተደራራቢ ዕዳ በደል ማምጣታቸውን ነው፡፡ ከዚያም ዐመጽ የተጀመረው የሰው ሕይወት እየቀጠለ ክፉው ቃየን የራሱን ወንድም አቤልን በግፍ ደሙን ሲያፈስሰውና ሲገድለው እናያለን፡፡

በሰው ልጆች የመጀመሪያ ጥፋትና ዐመጽ የመጣውን ዕዳና በደል፣ አጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የወደቀውን ብዙ ጉዳትና ጥፋት ለማስወገድና ሰውን ወደ ሕይወትና ክብር ለመመለስ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን ፍለጋ ልዩ በሆነ አመጣጥ አካላዊ ቃል ሰው ሆኖ ወደ ፈጠራቸው የሰው ልጆች ባሕርያችንን ባሕርዩ አድርጎ ሲገለጥ ደግሞ በደስታ እንደ መቀበል ፋንታ አሁንም ብዙዎች ተቃወሙት፡፡ ነገሩ ድንገት የደረሰባቸውና ያልጠበቁት እንዳይሆንባቸው እግዚአብሔር ከገነት ሲባረሩ ጀምሮ በትንቢት፣ በራዕይ፣ በተምሳሌትና በመሳሰለው ሁሉ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንደሚመጣ ደግሞ ደጋግሞ ሲናገር ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ትንቢትና ሱባኤ የተነገራቸው አይሁድ ለማመን የመጀመሪያዎቹ ሊሆኑ ሲገባቸው የእግዚአብሔርን እውነትና ልዩ ጸጋ ለመቀበል አልፈለጉም፡፡ ቅዱስ ወንጌል ውስተ እሊአሁ መጽአ ወእሊአሁሰ ኢተወክፍዎ – የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም በማለት ይህን አሳዛኝ እውነታ ይነግረናል፡፡ ዮሐ. 1፡12

እውነትን የሚቃወሙ አይሁድ ተቃውሟቸውና ጥላቻቸው እያደገ ሄዶ ጫፍ ሲደርስም ምንም እንኳ እርሱ በፈቃዱ ወዶ ቢያደርገውም እነርሱ ግን እናጠፋዋለን መስሏቸው በመስቀል ሰቀሉት፡፡ በመቃብር ለማስቀረትና ከዚያ ወዲያ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ነገር እንዳይነገርና ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ በማሰብ መቃብሩን ጥቂት ሰዎች ብቻቸውን ሊያንከባልሉት የማይችሉት ታላቅ ደንጊያ ገጥመው ዘጉት፡፡ ይህም አልበቃቸው ብሎ ከሮማውያን ወታደሮች እንዲመደቡ አድርገው ዙሪያውን እንዲጠብቁ አደረጓቸው፡፡ በገዢው ማኅተምም አተሙት፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ ጥረትና ጥበቃ ሥግው ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩን ክፈቱልኝ ደንጊያውን አንሡልኝ ሳይል መቃብሩ እንደ ታተመ ሞትን ድል አድርጎ ከመነሣት አላገደውም፡፡ ቅዱሳን መላእክት ወደ መቃብሩ የሄዱትን ቅዱሳት አንስት ምንተ ተኃሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምውታን ተንሥአ ኢሀሎ ዝየሰ – ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቷል እንጂ በዚህ የለም? በማለት የሞትንና የመቃብርን ይዞ የማስቀረትና የማፍረስ የማበስበስ ኃይል ድል አድርጐ መነሣቱን የምሥራች አበሠራቸው፡፡ ሉቃ. 24፡5 ሞትንና የክፋ ኃይልን ሁሉ ድል አድርጎ ለተነሣው ለመድኃኒታችንና ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን!

እርሱ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ መከራ የተቀበለውና የሞተው፣ ወደ መቃብር የወረደው እርሱ አሁን ሕያው ሆኖ መነሣቱን በመካከላቸው እየተገኘ የተወጋ ጎኑን፣ የተቸነከሩ እጆቹንና እግሮቹን በማሳየት የተነሣው ያው እርሱ መሆኑን ደጋግሞ አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ እነርሱ ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ይህን የሞትን በክርስቶስ ትንሣኤ መወገድና በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወት፣ ልጅነት፣ መንግሥተ ሰማያት በእርሱ ዘንድ የተዘጋጀ መሆኑን እንዲመሰክሩ መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁብሎ ላካቸው፤ ። የሐዋ. 1፡8

መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን የሕይወትን ቃል እንዲሰብኩ ወደ ዓለም ሲልካቸው ምን እንደሚጠብቃቸው ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፣ . . . እያለ አስቀድሞ ደግሞ ደጋግሞ እውነታውን ነግሯቸዋል፣ አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ማቴ. 10፡28 እንዲሁም እነርሱን የሚያሳድዷቸው እምነት አያስፈልግም ወይም በእግዚአብሔር መኖር አናምንም የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ ይልቁንም እግዚአብሔርን ያገለገሉና ለእርሱ የቀኑ የሚመስላቸው ሃይማኖተኞች ነን ባይ የሆኑ ሰዎችም እንደሚሆኑ እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬያችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጧችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው በማለት በሚገባ አስቀድሞ አስጠንቅቋቸዋል፣ አስተምሯቸዋል፡፡ ዮሐ. 16፡1-3 እምነት የለኝም ከሚለው ባላነሰ በተሳሳተ እምነት ውስጥ ያሉም እውነተኛ ክርስቲያኖችን በጽኑ ጭካኔ ሲጨፈጭፉ ኖረዋል፡፡ ማንም ሰው የመሰለውን ማመን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ችግር የሚሆነው ሌላውን ሰው ግድ እኔ የማምነውን ካላመንክ በስተቀር በዚህች ምድር ላይ የመኖር መብት የለህም ሲል ነው፡፡ በምድራችን ላይ ብዙ ግፍ ሲፈጸም የኖረውና አሁንም እየተፈጸመ ያለው ከዚህ የተሳሳተ እምነትና አስተሳሰብ የተነሣ ነው፡- እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የሰጠውን ነጻነትና መብት በመጋፋት ሰዎችን በማስተማርና በሳመንና ሳይሆን በኃይልና በጉልበት በማስገደድ የራስን እምነት በሌላው ላይ መጫን፡፡ ይህም ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ በእግዚአብሔር እናምናለን የሚሉት ብቻ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር መኖር አናምንም፣ ሃይማኖት የለንም የሚሉትም (ይህም በራሱ እምነት ስለሆነ) ሌሎችን እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ብዙ ግፍ ሲያደርሱ ኖረዋል፣ ዛሬም ያው ሁኔታ መልኩንና ቅርጹን ቢቀይር እንጂ ጨርሶ አልቀረም፡፡

እንግዲህ የክርስቶስ ተከታዮች (ክርስቲያኖች) ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመናቱ የየጊዜውን መስቀል ሲሸከሙና ከመስቀሉ በኋላ የሚገኘውን አክሊል ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ በዘመናት የሚኖሩ ክርስቲያኖች የሚሸከሙት መስቀል አንድ ዓይነት አይደለም፤ ለዚህ ነው ጌታችን መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ ያለው፡፡ ማቴ. 16፡24 መስቀሉን ማለቱ ለእርሱ የተዘጋጀለትን መከራ ማለቱ ነው፡፡ በክርስትና የመጀመሪያው ምስክር የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ ለአይሁድ የኢየሱስ ክርስቶስን እውነተኛ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ እነርሱ (አይሁድ) እንቀበላቸዋለን በሚሏቸው የብሉያት መጻሕፍት ሁሉ የተነገረውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መድኃኒት (መሢሕ) መሆኑን፣ እነርሱም ኢየሱስን መስቀላቸው ታላቅ ጥፋት መሆኑን ሲነግራቸው ተከራክረው መርታት ስላልቻሉ በደንጊያ ወግረው ገደሉት፡፡ . . . ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት። ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በሚሉት በአንድ ጎበዝ እግር አጠገብ አኖሩ። እስጢፋኖስም፡- ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም፡- ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር። የሐዋ. 7፡57-60 ስለ ክርስቶስ እየመሰከሩ ይህን እውነትና ሕይወት በሚቃወሙ በክፉዎች እጅ መገደልና ሰማዕትነትን መቀበል አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡ በክርስቶስ መከራና መስቀል የተጀመረው የክርስትና ጉዞም በሕይወት መዝገብ ላይ በደም ቀለም መጻፍ ጀመረ፡፡

በመቀጠልም ከሐዋርያት መካከል ቅዱስ ያዕቆብ በሄሮድስ እጅ በሠይፍ በመገደል ሰማዕት ሆነ፡፡ በዚያም ዘመን ንጉሡ ሄሮድስ መከራ ያጸናባቸው ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ በአንዳንዶቹ ላይ እጁን ጫነባቸው። የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። የሐዋ. 12፡1-2 ከዚያ በኋላ ክርስቲያኖችን መግደልና ማሰቃየት እየሰፋና ተቋማዊ መልክ እየያዘ ሄዶ በተለይ በሮማ ግዛት ግዛት ክርስትና በዐዋጅ ሕገ ወጥ ሃይማኖት ነው ተባለ፡፡ በፋርስ ግዛትም እንዲሁ ክርስትና በመንግሥት በይፋ የሚሳደድ ሆነ፡፡ ኔሮን ቄሣር የሮም ከተማ ነዋሪ ክርስቲያኖችን በመግደሉ ሂደት እንዲተባበረውና እንዲደግፈው በማሰብ የከተማን የተወሰነ ክፍል ካቃጠለ በኋላ ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው አለ፡፡ ከዚያም ክርስቲኖያችን ያገኛቸው ሁሉ እንደ ሀገር ጠላት በመቁጠር ገደላቸው፡፡ በዚህም ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው የብዙ ብዙ የሆኑ የክርስቲያኖች ደም ፈሰሰ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም አንዱ በስቅላት ሌላው በምትረተ ሠይፍ ሞቱ፡፡ አንዳንዶቹ የሮም ቄሣሮች ደግሞ ክርስቲያኖችን ማታ ማታ ሰቅለው በእሳት እያነደዱ እንደ ሻማ እንደ መብራት እስኪጠቀሙባቸው ደረሱ፡፡

በዚያን ዘመን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለው ሕይወታቸውን ለሰማዕትነት የሰጡትን ቅዱሳን አባቶችና እናቶች እንዲሁም ሕጻናት ቁጥራቸውን ቀርቶ ግምታቸውን እንኳ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ ይህን ለመረዳት አንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ ያለውን ብቻ ጠቅሰን እንለፍ፡፡ በዚያን ዘመን ብዙ ሰዎችን በአንድ ጊዜ በቀላሉ ለመግደል የሚያስችሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት በግብጽ እና በሦርያ የነበሩ ክርስቲያኖች የሚገድሏቸው ወታደሮች እጃቸው ከመግደል እየደከመና ሠይፋቸው በደም እየታለለ እነርሱም እስኪያርፉና መሣሪያቸውን እስኪወለውሉ ድረስ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት ለመገደል ለብዙ ቀናት ወረፋዎችን ይጠብቁ ነበር ይሏል፡፡

መንገድ ላይ እንደ ወደቀውና በድንጋይ ላይ እንደ በቀለው ዘር የጊዜውን መከራ ፈርተውና የዚህን ዓለም ሕይወት ወድደው ክርስቶስን የካዱ ቢኖሩም ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ግን በየጊዜው የሚሆነውን መከራ በጽናት ተቀብለው ለሃይማኖታቸው ለክርስቶስ መስክረዋል፡፡ ሲኖሩም ኑሯቸው ሁሉ የሰማዕትነት ሞትን በመጠበቅ ነበር፡፡ ክርስቲያኖችን ከማሳደድ የተመለሰውና ታላቅ ሐዋርያ የሆነው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ያለው ለዚህ ነው፡-

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼያለሁ። ሮሜ 8፡36-39

እግዚአብሔርም ምእመናን መከራውን በጽናት እንዲቀበሉ በቅዱስ ቃሉ፣ አጽናኝና አበረታች መላእክትን በመላክና በተለያዩ መንገዶች ሥቃዩን ያሥታግሣቸውና ያበረታቸው ነበር፡፡ ለአብነትም በሮማውያን ቄሣሮች በእነ ኔሮንና ድምጥያኖስ ዘመን ይደርስ የነበረውን መከራ በራእየ ዮሐንስ ላይ በታናሽ እስያ የነበሩትን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ በማለት ያበረታታቸው ነበር፡-

በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል። . . . ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም። ራ. 2፡8-11

ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ ሴቶችም መከራውን በጽናት ይቀበሉ ነበር፡፡ አንዲት ነፍሰ ጡር የነበረች እናት ሃይማኖቷ ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ብቻ ታስራ ሳለ በሮማውያን ሕግ ነፍሰ ጡሮች አይገደሉ ስለ ነበር ምነው በውስጤ ያለው ጽንስ ቶሎ ተወልዶልኝ ለሃይማኖቴ መስክሬ በሞትኩ ብላ ጸለየች፡፡ ልትወልድ ስትል ምጡ ሲያስጨንቃት ከጠባቂዎቹ ወታደሮች መካከል አንዱ ባያት ጊዜ ምነው ቶሎ ብዬ ለክርስቶስ መስክሬ በሞትኩ ስትይ አልነበር? ተፈጥሯዊ የሆነው ምጥ ይህን ያህል ካስጨነቀሽ ከእኛ እጅ የምትቀበዪውን መከራማ እንዴት አድርገሽ ትችይዋለሽ? አላት፡፡ እርሷም ይህን (ምጡን) የምቀበለው ብቻዬን ነው፤ ስለ ክርስቶስ የምቀበለውን መከራ ግን የምቀበለው ብቻዬን ሳይሆን ከክርስቶስ ጋር ነው፣ እንዲያውም መከራውን የሚቀበለው ራሱ ነው አለችው፡፡ አዎ፣ ስለ ክርስቶስ ያልተከፈለ ዋጋ የለም፤ ለእርሱ የማይከፈል ውድ ዋጋም የለም!

አሁንም ክፉዎች የመዳንን መንገድና እውነትን አንቀበልም ማለታቸው ሳያንስ ሌሎችንም እንደ እኛ ካልሆናችሁ በማለት ለማስገደድና የራሳቸውን አስተሳሰብና እምነት በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታጥቀው ክርስቶስን አንክድም የሚሉ ክርስቲያኖችን አንገታቸውን እንደ ከብት አጋድመው በሠይፍ እያረዱ ይገኛሉ፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ የሚጠራው ቡድን ከወር በፊት 21 ግብጻውያን ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ክርስቶስን አንክድም በማለታቸው ብቻ አንገታቸውን አርደው ገድለዋቸዋል፡፡ በሶሪያና በኢራቅ በየጊዜው ብዙ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ ይገደላሉ፣ ይሠቃያሉ፤ የቀሩትም ሀገር ለቀው ይሄዳሉ፡፡

ሰሞኑንም ይኸው ራሱን እስላማዊ መንግሥት – Islamic State (IS) ብሎ በሚጠራው ቡድን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ታምነው የክርስትና ሃይማኖታቸውን አንክድም በማለታቸው ምክንያት የተወሰኑት በጥይት ተደብድበው፣ ሌሎቹ ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ በሠይፍ ታርደው የተገደሉትን ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንን ስናስብ መከራቸውና ስቃያቸው ይሰማናል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ለእመ አሐዱ አካል ሐመ የሐምም ምስሌሁ ኩሉ ነፍስትነ – አንድም አካል ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ እንደሚለው የእነርሱ ጭንቀትና ስቃይ የእኛም ጭንቀትና ስቃይ ነውና። 1 ቆሮ. 12፡26-27 እነርሱስ አንድ ጊዜ ተቀብለውት ሄደዋል፣ ለእኛ ግን በየጊዜው የማይረሳና ባስታወሱት ቁጥር ውስጥን የሚያደማ የማይሽር የሕሊና ቁስል ነው፡፡ እነዚህ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የተቀበሉት መከራና ግፍ የሁላችንም መከራና ግፍ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ የሚቀበሉት መከራና የሚጋደሉት ተጋድሎ የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፡፡ ጌታችን የኋላውን ቅዱስ ጳውሎስ የቀደመውን ሳውል በሚያስደንቅ ሁኔታ ሲጠራው ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? አለው፡፡ እርሱም ጌታ ሆይ ማን ነህ? ባለው ጊዜ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ የሐዋ. 9፡3-5 ጌታችን የክርስቲያኖችን ስደትና መከራ የራሱ አድርጎ ለምን ታሳድደኛለህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ አለው እንጂ ለምን ታሳድዳቸዋለህ? አላለውም፡፡ ስለሆነም እነዚህ ወንድሞቻችን ስለ ሃይማኖታቸው የተጋደሉት ተጋድሎና የተቀበሉት መከራ የክርስቶስ የመከራው አካል ነው፤ የሰውነት የአካል ክፍሎች የሚሠሩት ሥራ የራስ ሥራ አካል ነውና፡፡

ይህ የወንድሞቻችን መከራና የግፍ ሞት ሁለት ገጽታ ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል የገዳዮቻቸውን ጭካኔና አረመኔነት ስንመለከተውና የወንድሞቻችንን ስቃይ ስናስበው በእጅጉ ይዘገንናል፤ ማንኛውንም ሰው የሆነን ሁሉ ይነካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመዳን መንገድ ስለ ሆነችው ስለ ክርስትና እምነታቸው ሲሉ በእግዚአብሔር ኃይል ጨክነው ለክርስቶስ መስክረው መሞታቸውንና እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናታቸውን ስናስበው ደግሞ ልዩ የሆነ ደስታ ይፈጥራል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥቂት ቀናት በፊት በግብጽ 21 ክርስቲያኖች እምነታቸውን እንደ መሰከሩ ሁሉ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ 30 እውነተኛ መስካሪዎችን አገኘች፡፡ እነዚህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍሬዎች ናቸውና! እንኳን ወላጆቻቸውንና ከዚህ ሞታቸው አስቀድሞ ያውቋቸው የነበሩት ሰዎች ይቅርና አገዳደላቸውን የሚያሳየውንና አይ ኤስ የለቀቀውን ምስል ወድምፅ የተመለከተን ማንኛውንም ሰው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወንድሞቻችን በቅድስት ሥላሴ ስላላቸው እምነት፣ ስለ ክርስቶስ አምላክነትና መድኃኒትነት፣ በአጠቃላይ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ስለ ሆነችውና ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለ ተሰጠችው አንዲት ሃይማኖት መስክረው መሞታቸው እያሳዘነ የሚያስደስት፣ እያስለቀሰ እልል የሚያሰኝ ነው፡፡ በቀድሞ ዘመን ክርስቲያኖች ለሃይማኖታቸው መስክረው ወደሚገደሉባቸው ቦታዎች ሲወሰዱ እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን፣ ሚስቶች ባሎቻቸውን፣ ወዳጅም ወዳጁን አይዞህ፣ በርታ፣ ጽና፣ ምስክርነትህን ፈጽም፣ የምትሄደው ወደ ክርስቶስ ነው እያሉ አንዱ ሌላውን ያበረታታ ነበር፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ሰው እንደ መሆናቸው ማዘን ባይቀርም የእነዚህ እውነተኛ ክርስቲያን ወላጆች ቤተሰቦች በመሆናቸው ሊደሰቱና እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ለሁሉ የሚገኝ
ጸጋና ክብር አይደለምና!

መከራው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ጎዳት? ወይስ ጠቀማት?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዘመነ ሰማዕታት በገጠማት በዚያ ሁሉ መከራ እየደከመች ሄደች ወይስ እየጠነከረች? የምእመናን ቁጥርስ እያነሰ ሄደ ወይስ እየበዛ? ታሪክ እንደሚያስረዳን በክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤው የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመከራው እየበዛችና እየጠነከረች ሄደች እንጂ ጠላቶቿ እንዳሰቡት እየደከመችና እየጠፋች አልሄደችም፡፡ ይልቁንም አሳዶጆቿና ገዳዮቿ የነበሩት ቄሣሮች እነ ኔሮን፣ እነ ድምጥያኖስ፣ እነ ትራጃን፣ እነ ዳክዮስ፣ እነ ቫሌንቲኖስ፣ እነ ጋሌሪዮስ፣ እነ መክስምያኖስ፣ እነ ድዮቅልጥያኖስ፣ እነ ሉቅያኖስና መሰሎቻቸው ሞተው የት እንደ ወደቁ መቃብራቸው እንኳ የማይታወቅ ሲሆን እነርሱ የገደሏቸውና ያሰቃዩዋቸው ክርስቲያኖች ግን ስማቸው በዓለም ይታወቃል፣ መቃብራቸውንና ዐጽማቸው ያረፉባቸውን ቤተ ክርስቲያኖች ምእመናን በታላቅ ክብርና ፍቅር ይሰለሟቸዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ያልተጠቀሱትን ገዳዮቻቸውን ግን በመልካም እንኳ የሚያነሳቸው የለም፣ በግፍ የሞቱትን ቅዱሳን ክርስቲያኖች ግን የክርስቲያኑ ዓለም ብቻ ሳይሆን ቅን ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ የሚያከብራቸው ናቸው፡፡

ክርስትና በዓለም የተስፋፋው በአፍና በመጽሐፍ በሚደረገው ስብከት ብቻ አልነበረም፤ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ዓይናቸው እያየ ሞትን ሲንቁትና ፊት ለፊት ሲጋፈጡት በማየትም ነበር እንጂ፡፡ እንደ ሌላው ሰው ሁሉ ሰውነታቸው ሕማምና መከራ የሚሰማውና ስቃይን የማይወድ፣ ለአካላቸው መለዋወጫ፣ ለሕይወታቸውም ምትክ የሌላቸው ሲሆን እንዲህ ሞትን የሚንቁትና ደስ እያላቸው የሚሞቱት በትምህርታቸው እንደሚሉት አምላካቸው በእውነት ሞትን በትንሣኤው ድል ያደረገው በመሆኑና ከዚህ ዓለም ሕይወት በኋላ እርግጠኛ የሆነ ሌላ ሕይወት ቢኖር ነው እያሉ አሕዛብ ከክርስቲያኖች የምስክርነት ዐውድ ሕያው ወንጌልን ይማሩ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሣ ክርስቲያኖቹን እንዲገድሉ ከተመደቡት ወታደሮች መካከል እንኳ ሳይቀር በክርስቲያኖች ጽናትና በስቃያቸው ጊዜ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ከሚሠራቸው የተለያዩ ገቢረ ተአምራት የተነሣ እኔም በእነዚህ ሰዎች አምላክ አምኛለሁ እያሉ በደማቸው እየተጠመቁ ሰማዕታት የሆኑ ብዙዎች አሉ፡፡

ለአብነትም በአርብኣ ሐራ ሰማዕታት የተፈጸመውን ብቻ እናስታውስ፡፡ የሮማ የምሥራቁ ክፍለ ግዛት ገዢ በነበረው በሉቅያኖስ ባለ ሥልጣናት ለጣዖታት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ሲታዘዙ እምቢ በማለታቸው በከተማው ውስጥ በነበረ አንድ በረዷማ የውኃ ኩሬ ላይ የጣሏቸው አርባ ክርስቲያን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ከዚያ ከተጣሉበት በረዷማ ኩሬ ፊት ለፊት ደግሞ ለመታጠቢያነት ተስማሚና ምቹ የሆነ የፍል ውኃ መታጠቢያ ነበር፡፡ ከአርባው መካከል አንደኛው ከቅዝቃዜው ጽናት የተነሣ አውጡኝ አለና ወዲያውኑ እየሮጠ በሙቅ ውኃው መታጠቢያ ለመታጠብ ሄደ፡፡ ወዲያውኑ እንደ ገባም ሰውነቱ ብስክስክ ብሎ ሞተ፡፡ የእነዚያን ተጋዳይ ወታደሮች ሥቃያቸውን ሲከታተሉ ከነበሩት አስፈጻሚ ወታደሮች መካከል አንደኛው ራሱን በፍል ውኃው እያሞቀ ይህን እንግዳ ነገር እየተመለከተ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜም መላእክት ከሰማያት ወርደው ለአርባው ተጋዳዮች አክሊል ሲያቀዳጇቸው የአንደኛው አክሊል ግን ተንጠልጥሎ በአየር ላይ ሲቀር ተመለከተ፡፡ ያን ጊዜ ያ ወታደር በወጣው ሰው ቦታ ገብቶ በክርስቶስ ታምኖ ወዲያውኑ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለ፡፡ (ቅዱስ ባስልዮስ፣ ስለ አርብኣ ሐራ ሰማዕታት፣ ትምህርት፣ ትምህርት 19)

በተለይም ደግሞ በጣም ብዙ ክርስቲያኖችን በመግደልና በማሰቃየት ወደር ያልነበረውን አርያኖስ የተባለውን የግብጽ ገዢ ፍጻሜ ማስታወሱ ለዚህ ሕያው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አርያኖስ በሮማ ግዛት ውስጥ ክርስቲያኖችን በማሰቃየትና በእነርሱ ላይ ይፈጽም በነበረው በጭካኔው ወደር የለሽ ነበር፡፡ አንድ ቀንም የእርሱ አጫዋች (አዝማሪ) የነበረው ፈልሞን በፊቱ ቆሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን መሆኑ መሰከረ፡፡ ያን ጊዜ አርያኖስ ፊልሞንን እና አብላዮስ የተባለውን ጓደኛውን በፍላጻ እንዲነድፏቸው አዘዘ፡፡ አንዲት ፍላጻም ወደ አርያኖስ ተመልሳ ዓይኑን አወጣችው፣ የፍላጻው ሕማምም እጅግ አሠቃየው፡፡ በጣም እየተሠቃየ ሳለ ከክርስቲያኖቹ አንዱ ከሰማዕታቱ ደም ወስደህ ብትቀባው ትድን ነበር አለው፡፡ እርሱም ይህን ያህል እየጠላኋቸውና እያሰቃየኋቸው ይምሩኛልን? ቢላቸው አዎ፣ በክርስትና ጠላትን መውደድና ለጠላት መጸለይ እንጂ መበቀል የለም አሉት፡፡ እንደ ነገሩት ከሰማዕታቱ ደም ወስዶ ቁስሉን ሲቀባው ወዲያውኑ ተፈወሰ፡፡ ከዚያ በኋላ እርሱም በክርስቲያኖች አምላክ አምኖ ጣዖታቱን ሰባብሮ ክርስቲያኖችን ምሕረት የሌለው ሥቃይ ስላሠቃያቸው ታላቅ ጸጸት ተጸጸተ፡፡ ከዚያም ስለ ክርስቶስ መስክሮ በሌላ ገዢ ተገድሎ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ (ስንክሳር መጋት 7 እና 8)

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ ሞትን ድል ማድረጉና የሞትን ኃይልና አስፈሪነት ማጥፋቱ ለሰዎች ከተገለጠበትና ለዓለምም ከሚገለጥበት አንደኛው መንገድ ይህ የክርስቶስ አካላትና ተከታዮች (ክርስቲያኖች) መከራንና ሞትን በጽናት መቀበላቸው፣ ሞትን መናቃቸውና ፊት ለፊት መጋፈጣቸው ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምኑ ወይም ስለሚመጣው ሕይወት በሃይማኖታቸው ቁርጠኛ ያልሆኑ ሰዎች እንደ ጦር የሚፈሩትን ሞት፣ እንዲሁም ሌት ተቀን የሚጨነቁለትን የዚህን ዓለም ሕይወት በክርስቶስ ትንሣኤ ያመኑ ክርስቲያን ሰማዕታት ሲንቁትና ፊት ለፊት ሳይፈሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሲጋፈጡት ሲያዩ ብዙዎች ከሞት በላይና ባሻገር ስላለው ሕይወትና እውነት በሰማዕታት ጽናትና ብርታት አማካይነት ተምረዋል፡፡ ከአሕዛብ ወገን፣ ሰማዕታቱን ይገድሉና ያሠቃዩ ከነበሩት ከወታደሮችም ሳይቀር በዚሁ ተስበው ለሰማዕትነት የበቁት በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡

እንደዚሁም ደግሞ ክርስቶስ ሞትን ድል ባያደርገው ኖሮ ሰማዕታትም ሞትን መጋፈጥና መናቅ ባልቻሉ ነበር፡፡ የእነርሱ ተጋድሏቸው፣ መከራቸውና ድል አድራጊነታቸው የመስቀሉ ድል፣ የትንሣኤው ኃይል ቀጣይ አካልና ሕያው ምስክር ነው፡፡ የእነርሱ ጽናትና ተጋድሎ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደረገው መሆኑን በተግባር የሚመሰክሩ ምስክሮች ናቸው፤ ምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፣ ስለዚህም ነፍሴ ፈለገቻቸው እንደ ተባለ፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት ሰማዕታት – ምስክሮች፣ መስካሪዎች የተባሉትም ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 118፡129

ስለሆነም መከራ መስቀል ክርስትና የተመሠረተበት፣ ያደገበትና የኖረበት ሕይወት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ክርስትናን የሚያዳክመው መከራ ሳይሆን ምንነቱን አለመረዳትና ቁሳውይነት፣ ቅምጥልነትና ሥጋውይነት ናቸው፡፡ ሰማዕትነትማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሞትን ያህል ከባድ ነገር ስለ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ሞትን ባሸነፈው በትንሣኤው ኃይል የናቁትንና ለብዙዎች ኢአማንያን በክርስቶስ ማመንና ሰማዕት እስከ መሆን መድረስ ምክንያት የሆኑ ብዙ መንፈሳዊ ጀግኖችን ያፈራችበት ነው፡፡ ለዚህ ነው በሁለተኛው መቶ ዓመት ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ ላይ የነበረው የክርስትና መብት ተሟጋቾችና ጠበቆች መካከል አንዱ የሆነው የሰሜን አፍሪካው የቅርጣግናው ሊቅ ጠርጠሉስ ስለ ክርስትና እምነት ንጹሕነትና እውነተኛነት ለአሳዳጆችና ለመከራ ዳራጊዎች በጻፈው የጥብቅና መጽሐፍ ላይ እንዲህ ሲል የገለጸው፡-

“አሠቃዩን፣ ግደሉን፣ ንቀፉን፣ ኰንኑን፣ አቃጥሉን፣፤ የእናንተ ክፋት፣ ግፍና ጭካኔ የእኛ ንጽሕና ማረጋገጫ ነው፡፡ እናንተ በወገራችሁንና በቆረጣችሁን መጠን ቁጥራችን እልፍ እየሆነ ይሄዳል፤ ደመ ሰማዕታት የክርስቲያኖች ዘር ነው፡፡ – Torture us, condemn us, crucify us, destroy us! Your wickedness is the proof of our innocence. . . . The more we are hewn down by you, the more numerous do we become. The blood of the martyrs is the seed of the Church. Apologeticus, Chapter 50)

አዎ፣ ምንም ያልበደሏቸውንና አንዳችም መከላከያ የሌላቸውን ወንድሞቻችንን በክርስትና ሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ በግፍ መግደላቸው ሁለት እውነታዎችን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከእነዚህም አንደኛው እውነተኛ ክርስቲያኖች ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅርና ጽናት፣ እንዲሁም እውነተኛነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የገዳዮቹ እምነታቸው ከመሠረቱ ስህተትና ውሸት መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም እውነትን የያዘ ሰው ያ አምነዋለሁ የሚለውን እውነት በማስረዳት ማሳመን ይገባዋል እንጂ እውነትን በግድ መጫን አይቻልም፡፡ ስለሆነም ገዳዮቹ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው ሌላውን ሰው ሊያሳምን የማይችል ደካማና ሐሰት ስለሆነ በኃይልና በመሣሪያ ኃይል ካልሀነ በስተቀር የሰውን አእምሮ ማሳመን የማይችል መሆኑን ራሳቸው ቀርጸው ያሠራጩት ምስልና ድምፅ ይመሰክርባቸዋል፡፡ በዚህም በአንድ በኩል እግዚአብሔርን አምነውና መስክረው የሞቱትን የወንድሞቻችንን አሟሟትና ማንነት እንድናውቅ ስላደረጉን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የራሳቸውን የገዳዮቹን የእምነት አስተሳሰብ ባዶነትና ሐሰትነቱ ከጥንትም የታወቀ ቢሆንም አሁን ደግሞ ከራሳቸው ንግግርና ድርጊት እንዲጋለጥ ያደረገውን ምስል ወድምፅ በማሠራጨታቸው እናመሰግናቸዋለን፡፡ እንደ ገደሏቸው ሳይነግሩን የሆነ ቦታ ጥለዋቸው ብቻ ቢሆን ኖሮ ዓለም ይህን ሁሉ ትምህርት ከየት ያገኝ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዓመት ማብቂያ ገደማ በተፈጸመው የክርስቲያኖች ጭፍጨፋ ስለ ክርስቶስ መስክረው የሞቱ ቅዱሳን ሰማዕታት ነፍሳቸው እንዲህ ብላ ወደ እግዚአብሔር ፍትሕን ጠይቃ ነበር፡- “አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። በታላቅ ድምፅም እየጮኹ፡- ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፣ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም? ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።” በዚህ ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው መልስ “እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው” የሚል ነበር። ራእ. 6፡9-11 እስከዚያው ድረስ ግን “ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፡፡”

እግዚአብሔር ክርስቲያኖችን በግፍ በገደሏቸው ላይ ፍርድን በቶሎ ያልሰጠበት ዋና ምክንያት እንደ እነዚያ ያሉና ስለ ክርስቶስ መስክረው የሚሞቱ በየዘመኑ የሚነሡ ሰማዕታት መኖራቸውን እርሱ በአምላክነቱ ስለሚያውቅ ይህ የሰማዕትነት ዕድል እንዳይቀርባቸው ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለክርስቶስ እየመሠከሩ የሚሞቱ አሉና እርሱ የሚያውቃቸው እነዚያ ሰዎች ለዚህ ክብር ሳይበቁ እንዳይቀሩ የፍርድ ጊዜውን እርሱ ባወቀ አቆይቶታል፡፡ ግፍ ፈጻሚዎችን ቀድሞ በአንደኛው መቶ ዓመት ላይ አጥፍቷቸው ቢሆን ኖሮ ከዚያ በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ወደፊትም እንዲሁ እርሱ የሚያውቃቸው ሰማዕታት ይህን የሰማዕትነት አክሊል አያገኙም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም እነዚህን የመሰሉ ጌጦቿን አታገኝም ነበር፡፡ ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ጌጦች ናቸውና፤ በከመ ከዋክብት ያሠረግውዎ ለሰማይ በሥኖሙ ከማሁ ሰማዕትኒ ያሠረግውዋ ለቤተ ክርስቲያን በገድሎሙ – ከዋክብት ሰማይን በውበታቸው እንደሚያስውቡት ሰማዕታትም በገድላቸው ቤተ ክርስቲያንን ያስጌጧታል እንዳለ ቅዱስ ያሬድ፡፡ (ጾመ ድጓ ዘቴዎቅሪጦስ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕትነትን መቀበል ሕይወቷ ነው፡፡ በዮዲት ጉዲት ዘመን፣ በግራኝ አህመድ ዘመን፣ በሱስንዮስ ዘመን ቁጥራቸውን እግዚአብሔር ብቻ የሚያውቃቸው ብዙ ክርስቲያኖች በሰማዕትነት መስክረው ዐርፈዋል፡፡ በሙሶለኒ ፋሽስት ወረራ ዘመንም እንዲሁ የደብረ ሊባኖስ፣ የዝቋላ፣ የማኅበረ ሥላሴ፣ እንዲሁም የሌሎች የብዙ ገዳማት መነኰሳትና ባሕታውያን ስለ ሃይማኖታቸው በግፍ ተጨፍጨው በሰማዕትነት ሞተዋል፡፡ ገዳማቱ ግን አሁንም አሉ፣ መነኰሳትና ባሕታውያንም፣ ምአመናንም እንዲሁ አሉ፡፡ ክፉ ያደረጉት ተጎዱ እንጂ ክፉው የደረሰባቸውን አልጎዷቸውም፡፡ እውነተኛ ጉዳት ማለት በጊዜው ጊዜ አይቀር የነበረውን የሥጋ ሞት በሰው እጅ መቀበል ሳይሆን መልካም ሊሠሩበት በተሰጣቸው ጊዜና አእምሮ በሰዎች ላይ ግፍና ጭካኔ ፈጽሞ ከእግዚአብሔር መለየትና ሊቀር ይችል የነበረውን ሞተ ነፍስ በፈቃድ በራስ ላይ ማምጣት ነውና፡፡

ስለሆነም እንዲህ ለሚያደርጉ ክፉዎች ሰዎች ልናዝንላቸውና ልንጸልይላቸው ይገባል፡፡ ጌታችን እንዲህ ብሎ አስተምሮናልና፡

ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።ማቴ. 5፡43-48

አዎ፣ ክርስትና የሚጠሉንን የምንጠላበትና ክፉ ያደረጉብንን በዚያው በክፋት መንገድ አጸፋ የምንመልስበት ሳይሆን ስለ ክፉ አድራጊዎቹ ጥፋት ከልብ የምናዝንበትና የጥፋታቸውን ምንነት ተረድተው ወደ አእምሯቸው ይመለሱ ዘንድ እግዚአብሔርን የምንለምንበት ሕይወት ነው፡፡ ክርስትና ድንጋይ ለወረወረብን መልሰን የምንወረውርበት፣ ጉድጓድ በማሰብን ላይ ሌላ ጉድጓድ የምንቆፍርበት አይደለም፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰቀሉትና ያ አልበቃቸው ብሎ ተጠማሁ ባለ ጊዜ እንኳ መራራ ሐሞትን በአፉ ላደረጉለት ለክፉዎች አይሁድ እንኳ አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁም ይቅር በላቸው ብሎ እንደ ጸለየላቸው እኛም ለክፉ አድራጊዎችና ለጠላቶቻችን የምንጸልይበት ሕይወት ነው፡፡ አለዘበለዚያ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ልንሆን አንችልም፡፡ ክፉዎች ክፉ በመሆናቸው በእነርሱ ክፋት ተገፋፍቶ ወይም እልክ ውስጥ ገብቶ እነርሱ በሄዱበት የክፋት መንገድ መሄድ ገና ከጅምሩ መሸነፍና ድል መነሣት ነውና፡፡ ምክንያቱም የክፉ ሰው ድርጊቱና ዓላማው ሌላውንም እንደ እርሱ ክፉ ማድረግና ወደ እርሱ የክፋት አስተሳሰብና ድርጊት እንዲሳብ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ አስተሳሰብና ድርጊት እንደ ክፉዎቹ ሰዎች አስተሳሰብና ድርጊት ከሆነ ብርሃን ወደ ጨለማ፣ ጨው ወደ አልጫ ተለወጠ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገና ሲጀመር መሸነፍ ነው፤ ክፉው መልካሙን አጠፋው ማለት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉሲል በአጽንዖት የሚያስጠነቅቀን፡፡ ሮሜ 12፡21 በክፉ መሸነፍ ማለት ወደ ክፋ መሳብና ክፉዎቹ እንደሚያደርጉት ለማድረግ መነሣት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ክፉውን በመልካም አሸንፉ እንጂ ካለ በኋላ ቀጥሎ በክፉ አትሸነፉ አለ እንጂ “በክፉ አታሸንፉ” አላለም፡፡ ምክንያቱም ክፉን በመልካም ብቻ እንጂ በክፉ
ማሸነፍ አይቻልምና፡፡ ክፉ መሆን ከጀመረ ግን በክፉ ተሸንፏል ማለት ነው፡፡ ሰው በክፉዎች ምክንያት እርሱም የሚከፋ ከሆነ ከጅምሩ ተሸንፏል ማለት ነውና፡፡ ፡፡

ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱበት ለነበሩት አይሁድ ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ ጸለየላቸው እንጂ አጥፋቸው አላለም፡፡ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስም ጸሎት እንዲሁ በከንቱ አልቀረም፡፡ እርሱን ሲወግሩ የነበሩትን ሰዎች ሲያስተባብርና ልብሳቸውን ሲጠብቅ የነበረው ሳውል የተባለው ኃይለኛ ጸረ ክርስቲያን ወጣት (የኋላው ቅዱስ ጳውሎስ) የእግዚአብሔር ቸርነት ልቡን እንዲነካውና ወደ ክርስትና እንዲመለስ ታላቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህንንም አንድ ሊቅ የቅዱስ እስጢፋኖስ ጸሎት ለቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስን አስገኘላት ብሏል፡፡ በየዘመናቱ የነበሩ ክርስቲያኖች ሁሉ መከራ በሚያደርሱባቸው ላይ እንዲሁ ስህተታቸውን የሚገነዘብ ልቡና እንዲሰጣቸውና ወደ እውነት እንዲመለሱ ጸለዩላቸው እንጂ በክፉው መንገድ እንበቀላቸው ብለው አልተነሡም፡፡ በዘመነ ዲዮቅልጥያኖስ ታላላቅ የቤተ መንግሥት ተወላጆችና መኳንንት ከነበሩት ወገን ሰማዕትነትን የተቀበሉት እነ ቅዱስ ቴዎድሮስ፣ ቅዱስ ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ዮስጦስ፣ ቅዱስ አቦሊ፣ ቅዱስ ፊቅጦር . . . በጦር ሜዳ ጀግንነታቸውና አርበኝነታቸው የታወቁ ኃያላን ነበሩ፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቲያኖችን ማሰቃየት ሲጀምር በመጀመሪያ ያደረጉት ነገር ትጥቃቸውን መፍታትና ስለ ክርስቶስ መክራ ለመቀበል በመዘጋጀት ወደ ፊቱ ቀርበው ሃይማኖታቸውን መመስከር ነበር፡፡ የእነርሱ ታማኝ ሠራዊትና ወዳጆች ከነበሩት ብዙዎች ስለ እነርሱ በመቆጨትና በመቆርቆር ዲዮቅልጥያኖስን ወግተን እናጥፋውና እናንተ ግዙን ሲሏቸው አልተቀበሏቸውም፡፡ እነዚህ ሰማዕታት መጀመሪያ ያደረጉት ነገር በዘመኑ የነበራቸውን አርበኝነት፣ ኃያልነት፣ የወገንና የሠራዊት ድጋፍ ሁሉ ትተው ስለ ክርስቶስ መስክሮ ለመሞት ብቻቸውን መቅረብ ነበር፡፡ ክርስትና በሠይፍ የተመሠረተና ለመስፋፋትም ሠይፍ የሚያስፈል
ገው አይደለምና፡፡ ሠይፍን የሚያነሱማ እነርሱው ራሳቸው በሠይፍ እንደሚጠፉ ባለቤቱ አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ማቴ. 26፡52 ታሪክም ይህንኑ እውነታ ያስተምረናል፡፡

ክርስትና በዚህ ዓለም የድሎትና የቅንጦት ኑሮ የሚመኙበትና የሚኖሩበት ሳይሆን ክርስቶስ በዚህ ዓለም የመስቀል ሞት ስለ እኛ በፈቃዱ እንደ ተቀበለና እንደ ተነሣ ክርስቲያኖችም በዚህ ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ በትዕግሥት በጥብዐት በመቀበል በትንሣኤው ኃይል ድል የሚያደርጉበት ነው፡፡ ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት ተብሏልና፡፡ 1 ጢሞ. 5፡6

እነዚህን ወንድሞቻችንን ወደ እግዚአብሔር ፈጥነው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አልጎዷቸውም፡፡ ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለዩዋት እንጂ አልገደሏትም፤ ነፍስን ለመግደል ማንም አይችልምና፡፡ ይህ የሥጋና የነፍስ መለያየት (ሞተ ሥጋ) ደግሞ በሕማምም ሆነ በዕድሜ ብዛት መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ከዚያ ቀድመው ለክርስቶስ መስክረው ወደ አምላካቸውና መድኃኒታቸው እንዲሄዱ አደረጓቸው እንጂ አንዳችም አልጎዷቸውም፡፡ ራሱ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንዲህ ብሏልና፡- ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ዮሐ. 11፡25-26 ለክርስቶስ መስክሮ መሞት ደግሞ ለአንድ ክርስቲያን እጅግ ታላቅ ጸጋና መታደል ነው፤ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ተብሏልና፡፡ ማቴ. 10፡32

ቅድስናን (ሰማዕትነትን) እውቅና መስጠትን በተመለከተ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የሆኑትን ቅዱሳን ናቸው ስትል ቅድስናቸውን እውቅና የመስጠት ጉዳይ እንጂ ቅዱሳን የማድረግ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህም ማለት እነዚያን ሰዎች ቅዱሳን የሚያደርጋቸው እግዚአብሔር ባሳየው የሕይወት መንገድ መጓዛቸውና እርሱን ደስ ያሰኙ መሆናቸው እንጂ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ናቸው ብላ በምትሰጠው ውሳኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅድስናቸውን የማወቅ ውሳኔ የሚመጣው ከሰዎቹ ቅድስና እንጂ የሰዎቹ ቅድስና ከቤተ ክርስቲያን ውሳኔ የሚመጣ አይደለም ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያውቃቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የሆኑ ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ዓለም ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሁሉንም ሊያውቃቸው መቸም መች አይችልም፡፡ ምክንያቱም በየበረሓው ወድቀው ከእኩያት ፍትወታትና ከክፉ መናፍስት ጋር ተጋድለው እግዚአብሔርን አገልግለው ያለፉና እንኳን ቅድስናቸው መኖራቸው እንኳ ከእግዚአብሔር በቀር በሰዎች ያልታወቀ ብዙ ቅዱሳን ነበሩና፣ ዛሬም ይኖራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወበኀቤዬሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ እኄልቆሙ እምኆጻ ይበዝኁ – አቤቱ ወዳጆችህ በእኔ ዘንድ እጅግ ብዙዎች ናቸው፣ ብቆጥራቸውም ከአሸዋ ይልቅ በዙ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ መዝ. 138፡17-18

እንደዚሁም በዚህ ዓለም ሲኖሩ ኃጢአተኞች መስለው፣ እብድ መስለው፣ የውሻ አስከሬን እስከ መጎተትና አመንዝራ እስከ መምሰል ደርሰው፣ ሰው እንኳን ቅድስናቸውን ሊያውቀው ይቅርና ጥሩ ሰዎች እንኳ አድርጐ የማይመለከታቸው ብዙ ቅዱሳን እንደ ነበሩ ዜና አበውና መጽሐፈ ገነት፣ እንዲሁም ስንክሳርና የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ድርሳናት ይነግሩናል፡፡ ከሰማዕታት መካከልም ታላላቅ ተጋድሎ የተጋደሉና ብዙ ዓይነት ጸዋትወ መከራ የተቀበሉ፣ ብዙ ጊዜ ሞተው የተነሡና እግዚአብሔር ብዙ ተአምራት ያደረገላቸው ብዙ ሰማዕታት አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሚታወቁት ግን በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም በሰዎች ዘንድ አለመታወቃቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ክብራቸውን በእኛ ዘንድ ከታወቁት ሰማዕታት ያነሰ አያደርገውም፤ የክብራቸው መሠረት በእኛ ዘንድ መታወቅ አለመታወቃቸው፣ በዓል ያላቸውና የሚታሰቡ መሆን አለመሆናቸው አይደለምና፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ ሊቅ ሲያስረዳ በሰማይ ባሉ ከዋክብት መስሎ አስረድቷል፡፡ በሰማይ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑና ቁጥራቸው ይህን ያህል ተብሎ የማይታወቁ ከዋክብት አሉ፡፡ ለእኛ የሚያበሩልንና መኖራቸውን የምናውቃቸው ካሉት ከዋክብት እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ብቻ እንደ ሆኑ ከቅዱሳንም እኛ የምናውቃቸው ለአርአያና ለትምህርት ይሆኑን ዘንድ በጣም ጥቂቶቹን ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከመራቃቸው የተነሣ ለእኛ በጣም ጥቃቅን መስለው የሚታዩንና ከነመኖራቸው የማናውቃቸው ትሪሊዮን ጊዜ ትሪሊዮንና ከዚም በላይ በቁጥር ሊገለጽ የማይቻል የሆኑ ከዋክብት እንዳሉ ሁሉ በቅዱሳንም እንዲሁ ነው፡፡ ለእኛ የሚታዩትና የምናውቃቸውም ሆኑ የማይታዩት የማናውቃቸው ከዋክብት የጋራ መገለጫቸው በሰማይ ያሉ ሰማያውያን መሆናቸው እንደ ሆነ ሁሉ የቅዱሳን የጋራ መገለጫቸው ሁሉም ሰማያውያንና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበሩ መሆናቸው ነው፡፡

በእግዚአብሔር ቸርነት የሚገኝ ቅድስና ከሚገኝበት መንገድ አንዱ ሰማዕትነት ነው፡፡ ሰማዕታትም የሰማዕትነት አክሊል የሚቀዳጁት ሰማዕታት ናቸው ተብሎ ሲወሰንላቸው ወይም ዐዋጅ ሲታወጅላቸው ሳይሆን ለአምላካቸው ያላቸውን ጽኑ ፍቅርና ታማኝነት መከራውንና ሞቱን ሳይፈሩ ምስክርነታቸውን በሰጡና ከዚያም የሞትን ጽዋ በጽናት በተቀበሉ ጊዜ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመዋቅሯ ሰማዕት ብላ እውቅና የምትሰጠው ከእነርሱ ከበረከታቸው ለመሳተፍና ለምስክርነታቸው ዕውቅና ለመስጠትና ለማክበር ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ለሰማዕትነታቸው ዕውቅና የመስጠት አለመስጠቱ ጉዳይ እነርሱ በሚያገኙት ጸጋና በሚሆኑት ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ስለሆነ ብዙም የሚያጣድፍ ጉዳይ አለመሆኑንና ረጋ ብሎ አስተውሎ ቢደረግ የሚያመልጥ ነገር አለመኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ መንፈስ ማድረጉ መልካም ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ ከእነዚህ ሰማዕታት የሚከተሉት ነገሮች እንማራለን፡-

1.ክርስትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ዘመን አንሥቶ በየዘመናቱ ዓይነቱና ስፋቱ ይለያይ እንጂ ጉዞው በመስቀል ላይ ማለትም በመከራ ላይ መሆኑን፣

2.ክርስትናን ከምድረ ገጽ ለማጥፋትና በዓለም ላይ የአረመኔ ሥርዓት ለመመሥረት አይ ኤስ እና መሰሎቹ የተለያዩ ቡድኖች ክርስቲያኖቹን በመግደልና አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በማቃጠልና በማፍረስ ላይ መሆናቸውን፣

3.ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው አደጋ ችላ ሊባል የሚገባው ሳይሆን እያንዳንዱ ክርስቲያን በንቃት ሊከታተለው የሚገባ መሆኑንና ሕሊናዊና መንፈሳዊ ዝግጅት፣ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ የልብ ጸሎት የሚያስፈልግ መሆኑን፣ እና

4.በመጨረሻም እነዚህ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ለክርስቶስ ታምነው ሞትን በጽናት መቀበላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ጽኑ ፍቅር አጽንተን በመከራም እንኳ ቢሆን ጸንተን እንድንቆም የሚያስተምር ሕያው ወንጌል መሆኑን ነው፡፡ እነርሱ በሠይፍ ለመታረድና በጥይት ተደብድበው እስከሚገደሉ ድረስ ለሃይማኖታቸው ከጸኑ እኛ ከዚያ ደረጃ ባልደረሱ ተራና ጥቃቅን ሰበቦችና ምክንያቶች ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳንክድና በእርሱ ካለን ሕይወት እንዳንለይ፣ በክርስቶስ ያለንን እውነተኛ ኦርቶዶክሳዊና ሐዋርያዊ እምነት እስ መጨረሻው አጽንተን እንድንጠብቅ የወንድሞቻችን ደም ሕያው ሆኖ ከፊታችን እየጮኸ ያስተምረናል፡፡

እኛም እንደ ወንድሞቻችን መኑ ያኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ሕማምኑ ምንዳቤኑ ተሰዶኑ ረሐብኑ ዕርቃንኑ መጥባሕትኑ ጻዕርኑ -ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ልንልና በዚህ ሕይወት ልንኖር ይገባናል፡፡ ሮሜ 8፡35

እግዚአብሔር አምላክ ከእርሱ አንድነትና የአባትነት ፍቅር ከሚለይ ነገር ሁሉ ይጠብቀን፣

እኛንም ፈቃዱ ቢሆን እንደ ወንድሞቻችን በጽናት እንድንቆምና ለአክሊለ ሰማዕት እንድንበቃ ያድርሰን፣ አሜን፡፡