ቤተ ክርስቲያንን ጠብቋት

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

አባ ዘሚካኤል

ቅድሚያ ለቤተ ክርስቲያን እንቁም! ምን እንደምትልም እንጠብቃት (እንስማት)!

“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” (የሐዋ.20፥28)፡፡

 

ፓትርያርክ ለመሾም:-

  • ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
  • የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
  • አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!

 

ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ፡ ’አሁንም ራሳችሁን ጠብቁ’ የግእዙ ትርጓሜ ሲል’፣ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ’ለራሳችሁ ተጠንቀቁ’ ይላል፡፡

 

ቅዱስ ሉቃስ እንደጻፈው፣ የቅዱስ ጳውሎስን የማስጠንቀቂያ ምክር በጊዜው የመንጋው ጠባቂ ለሆኑት አባቶች መጀመሪያ “ራሳችሁን ጠብቁ’ ነው ያላቸው፡፡ በመሆኑም ይህን የቅዱስ ጳውሎስ ምክር የተረዱ አባቶቻችን ከሁሉ በፊት  ራሳቸውን በመልካም መንገድ ማቆምን ቅድሚያ ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን ከእምነት ለመለየት ከሚፈታተኗቸው:-በሥጋዊ ድካም ከሚመጡ ይሁን በሌሎች ውጫዊ ምክንያቶች ከሚነሡ እኩያት አሳቦችና ተግባራት ራሳቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ከሌላ ስለሚመጣው ፈተና ምክንያት ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል ”ወአነ አአምር ከመ ይመጽኡ እምድህሬየ ተኩላት መሰጥ እለ ኢይምህክዋ ለመርዔት፤ ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” (ማቴ፣ 7: 15) ይላል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ዋናው ነገር ሐሰተኛ መምህራን ሊያሳስቱ የሚሞክሩት ምእመናንን ብቻ አይደለም ታላላቆችንም ነው እንጂ፤ ከዚህ በፊት ከታየው ልምድ ለቤተ ክርስቲያን የጠቀሙ በመምሰል አባቶችን ወደ አላሰቡት ስህተት የሚጥሉ አሉ፣ ሰይጣን እንኳን ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ሊፈታተን ቀርቦ የለምን? ከላይ በተመሳሳይ ”ከኔ በኋላ ለምእመናን የማያዝኑ ሰውን እየነጣጠቁ ወደ ገሃነም የሚያወርዱ ሐሰተኞች መምህራን እንዲነሡ አውቃለሁ” ተብሏልና፡፡  ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳ ነገር ለምሳሌ፣ መከፋፈል እንዲፈጠር ሊያደርግ የሚችል ምክንያት እንዳይገኝ በየግል መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ቀጥሎም ጳጳሳትን በቡድን ማለትም ሲኖዶሱን ’ራሳችሁን ጠብቁ’ ማለት በመካከል የሚፈጠር አለመግባባት እና ሌላም ምክንያት እንዳይለያያችሁ ቀድማችሁ ጥንቃቄ አድርጉ ሲል ነው፡፡ በመከፋፈል ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተከፈተ በር፣ ከተከፈተ በኋላ እንኳን መልሶ ለመዝጋት ይቅርና የበሩን መዝጊያውን ለማግኘት የሚቸግር ይሆናል፡፡ ካለፈው የመከፋፈል ልምድ እንደ ተረዳነው፣ በሁለት መከፈል ሳይበቃ መዘዙ ወደ ብዙ ትንሽ ክፍፍል ጭምር ማምራቱን  መዳኘትና መግታት ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ይህ ሁኔታ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል አምላክ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በጸሎት እንጠይቀው፡፡

 

“ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናንን ሁሉ ጠብቁ፡፡ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳተ፣ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማችሁ እናንት ዕቀቡ ጠብቁ” ብሎአል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሹመት ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ማንም ሰው ደግም ይሥራ ክፉ፣ የሚሾመው ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡” ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ፣ በወርቀ ደሙ የዋጃትን የምእመናንን አንድነት ትጠብቋት ዘንድ የሾማችሁ፡፡” አባቶች የሚጠብቁት የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑትን ምእመናንን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ስንል የምእመናን አንድነት በመሆኑ፣ ከአባቶች ጠብቆት ውስጥ ምእመናንን ከመከፋፈል፣ ከኑፋቄ፣ ወዘተ በሽታ መከላከል ዋናው ተግባር ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ምእመናን በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ፣ በውጭ እና ከዚህም ከዚያም የሌለ በሚል ተከፋፍለን በመለያየት ተውጠን ከርመናል፡፡ እግዚአብሔር ሲኖዶሱን” ወኵሎ መራዕየ፣ ምእመናን ሁሉ ጠብቁ” በማለቱ ሁሉም ምእመናን ከመሰናከል የሚድኑበት፣ ከፋፋዮች ምክንያት የሚያጡበት፣ መናፍቃን የሚያፍሩበት፣ አንድነትን የሚያመጣ ቁርጥ ውሳኔ የሚሻበት ወቅት ነውና መንጋው በመከፋፈል ከመጥፋት አባቶች እንዲታደጉት ጊዜው ግድ ይላል፡፡

 

የመንጋው ጠባቂዎች የተባሉት ቅዱስ ሲኖዶስ በዋናነት ሲሆን ከሊቃነ ጳጳሳት ቀጥሎ በቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች በተዋረድም ሀገረ ስብከት፣ ወረዳ ቤተ ክህነትና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉትን ሲሆን፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር መንጋ የተባሉት መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ምእመናንን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ ከነዚህም ዋና ውሳኔ ሰጭው የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

 

ቅዱስ ሲኖዶስ የፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት መሪው መንፈስ ቅዱስ የሆነ ዐቢይ ጉባኤና የቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ በማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚወሰነው ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ይሆናል፡፡ ፓትርያርኩ ተጠሪነታቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔ ሊለውጡ አይችሉም፡፡ፓትርያርኩንም መርጦ የሚሾመው ይኸው ጉባኤ ነውና፡፡ ሁሉም ክርስቲያን በእኩል መረዳት ያለበት የሲኖዶስ አባላት ሲመረጡ እንደ ሕግ እግዚአብሔር መሆኑንና እግዚአብሔር ሳይፈቅድ ጳጳስ መሆን እንደማይቻል ነው፡፡ ሁለተኛም የተሰጣቸው ሓላፊነት ከእግዚአብሔር እንደመሆኑና የዘወትርም ሥራቸው በመሆኑ፣ ሁልጊዜም መንጋውን በመጠበቅ ለቤተ ክርስቲያን ስጋት የሆነውን ጉዳዮች በመለየት ጥንቃቄ ያደርጋሉ ብለን ማመን ይኖርብናል፡፡

 

እኛ ምእመናንም ደግሞ ማሰብ ያለብን አይነተኛ ነገር አለ፣ ይህም ለመንጋው ጠባቂዎች በትክክል ታዛዣቸው ነን? በጎቻቸው ነን ወይ?  ብለን እራሳችንን መመርመር አለብን፡፡ ለንባብ የበቃ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንኳን እንደሚታየው ትኩረት ሳይሰጠው ከመታለፉ አልፎ እንደውም ማጣጣል ሲደረግበት ነው የሚስተዋለው፡፡ በመሆኑም አንዳንድ ጊዜ አባቶቻችንን እንድንጠራጠር የሚያደርጉንን ወሬዎችን በመስማት ወሳኞቹ እኛ ሳንሆን አስቀድመን መሆን አለበት ብለን ወስነን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚወስነው ጋር እንዳንጋጭ ከወዲሁ፣

 

  1. ከማን መስማት እንዲገባን መመርመር የለብንም ይሆን?

  2. አስቀድመን ለመወሰንስ እኛ ማን ነን?

  3. የቅዱስ ሲኖዶስ ከሳሽ መሆን ይጠቅመን ይሆን?

  4. የቅዱስ ሲኖዶስ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው ካልን መንፈስ ቅዱስ አይጠብቃቸውምን?

  5. ቤተ ክርስቲያን የሾመቻቸው ሊቃውንት ከሃምሳ በላይ ሊቃነ ጳጳሳት አንድ ላይ ሆነው መክረው የሚወስኑት ውሳኔ ሳንቀበል በአንድ ሚዲያ ላይ አሰማምሮ ወይም አጣጥሎ በተጻፈ ጽሑፍ የምንረበሽ እና የምንፈተን ከሆን ስህተቱ የማን ይሆን?

  6. መረጃዎችን ማወቅ ጥሩ ሲሆን፣ ነገር ግን ከእምነት አንጻር የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የማጣጣል ሁኔታ የመልካም ይሆን?

 

የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሣትና ቀድሞ ሰው ካለው ልምድ እንዲሁም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ጋር መቆም እንዴት ይኖርብን ይሆን? ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም እስከ አሁን ከተለያዩ ጽሑፎች እንዳነበብነው፣ ከተለያዩ አስተያቶች እንደ ሰማነው፣ በጣም የሚገርመው መቼም፣ ምንም ሊጣጣሙ የማይችሉ አሳቦች ከተለያዩ ጽንፈኞች ሲቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ባንድ ወገን መጀመሪያ እርቁ ይቅደም በሚል በሚገባ መረጃ አሳማኝ ነገር ሲቀርብልን በሌላ ወገን የእርቁ አካላት የተባሉ ጨርሶ የእርቅ አሳብ እንዳልተነሣ ሁሉ እንደገና ለእርቁ መፈጸም እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሁኔታ አደረጉ ወይም ለአዲስ መለያየት መንገድ ይከፍታል የሚያሰኝ መረጃ ተቀናብሮ የቀረበ ስናይ እንዴት ይሆን ይህ አሳብ የሚታረቀው? መቼ ይሆን እርቁ የሚፈጸመው? የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ሁላችንንም ግድ አይለን ይሆን? በዚህ የተዘበራረቀ ሁኔታ አባቶችስ የምርጫውን ጉዳዩ እስከ መቼ ሊያቆዩት ይችሉ ይሆን? በዚህ ሁኔታ ላይ ባለድርሻ አካላት ሳያምኑበትና በወቅቱ ለቤተ ክርስቲያን ይጠቅማታል ብለው ባልወሰኑት የኛ ማጉረምረም ምን ጽድቅ ይፈጽም ይሆን? ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያንን የሚጎዳት አባላቶቿ ከአባቶች መንፈሳዊ እልባትና ከቅዱሳት መንፈሳውያን መጻሕፍት ምክር ይልቅ በዓለማውያን ፍልስፍና ስንደገፍ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ”እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም። መንፈሳዊውን ነገር ከመንፈሳዊው ነገር ጋር አስተያይተን መንፈስ በሚያስተምረን ቃል ይህን ደግሞ እንናገራለን እንጂ የሰው ጥበብ በሚያስተምረን ቃል አይደለም። ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፤ በመንፈስም የሚመረመር ስለ ሆነ ሊያውቀው አይችልም። መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም። እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው? እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን” (1 ቆሮ 2: 13-16) ይለናል።

 

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይጠቅማል ያሉትን ከምርጫው ጋር የተያያዙ የተለያዩ አሳቦች ሲያቀርቡ ተስተውለዋል፡፡ ግብአቱ መልካም ነው፣ በተለይ ሚዲያዎችን የሚከታተሉ ምእመናን፣ የሚጻፉ አሳቦችን ሁሉ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በላይ በማድረግ የማየቱን ጉዳይ ነው፡፡ መረዳት ያለብን ፍሬ አሳብ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሚዲያ እንደተጻፈ ሊያውቁም ላያውቁም ይችላሉ፣ በግድም የማወቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ብፁዓን አበው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሥራቸውን መሥራት አለባቸው እንጂ ተቀባይነትን ለማግኘት ሁል ጊዜ ወደ ሚዲያ መቅረብ አለባቸው አንልም፡፡ በየሚዲያዎች ሁሉም እንደፈቃዱ የጻፈውን ሁሉ ለማስፈጸም ደፋ ቀና ማለት አለባቸውም ልንል አይገባም፡፡ ከማንም ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ጊዜውን በዋጀ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያንን መምራት ስላለባቸው ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡ በአባቶች ውሳኔ ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ የሚወሰነውን ሁሉ በእውነት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በአግባቡ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ሁሉም እንዲህ ቢያረግ ማለትም ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ቢገዛ ቤተ ክርስቲያን አንድነትዋ ይጠበቃል፣ መለያየት አይኖርም፣ አንድነታችን ይጸናል፣ ከፋፋይ ያፍራል፣ ይልቁንም ሰይጣን ይመታል፣ በመስቀሉ እውነተኛ ፍቅር ይቀጠቀጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሚለየንን ሰይጣን ይቀጥቅጥልን!!!

 

በመሆኑም ቅዱስ ሉቃስ” ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሯቸው (የሐዋ. ሥራ.4፥32)” እንዲል፤ በአንድ ሲኖዶስ ውሳኔ ማዘዝና መታዘዝ ስንተዳደር ነው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ፍቅርና አንድነት የሚመጣው እንጂ በየቦታው ለራሳችን እንደ ራሳችን አሳብ መምህር ካቆምን እንናገራለን እንጂ በሕይወታችን ዘመን እርቅና አንድነትን ሳናያት ልናልፍ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን ዘመን የቤተ ክርስቲያንን አንድነቷን ያሳየን!!! ሳናይ አይውሰደን ብለን መመኘትና መጸለይ ይገባናል፡፡

 

ባጠቃላይም የአሁኑ ወቅታዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ፣ የፓትርያርክ ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም እንደሚለው፣ በዓለም ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ሁሉ በጉዳዩ ያገባቸዋል፤ (ይህንን ስንል ተመሳስለው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች በመምሰል የኑፋቄና የጸብ መንገድ ሁል ጊዜ የሚምሱትን ሳይጨምር መሆኑን መገንዘብ ያሻል)፡፡  ነገር ግን በፓትርያርክ ምርጫ እያንዳንዱ ሰው ድርሻው እስከምንድነው? የዚህ ጥያቄ ምክንያት፣ ምእመናን በተለይ በውጭ አገር ያሉ የተለያየ ሚድያ ስለሚከታተሉ፤ ሚዲያዎቹ በአንድ በኩል የቤተ ክርስቲያኗን ጥቅም የሚፈልጉ ሲሆኑ፣ ሌሎቹ  የፖለቲካ፣ የተሐድሶ ወዘተ ዓላማና ጥቅም ያላቸው ከወዲሁ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት የራሳቸውን ግምት በመስጠት ምእመናንን የሚያንጽ ወይም የሚረብሽ አሳብ ስለሚበትኑ፤ ከዚህ የተነሣ አንዳንድ ግለሰቦች በራሳቸው ፓትርያርክ የመረጡ ያህል እከሌ ይሁን እስከ ማለት የደረሱ አሉ፡፡ በመሆኑም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አንጻር የፓትርያርክ ምርጫ ሥርዓትን በመረዳት:-

 

  • ሁሉም ድርሻው እስከምን እንደሆነ ይወቅ!
  • የሲመቱ ሂደት ምንም ይሁን ምን የተዋሕዶ ምእመናንን ሊከፋፍል በሚችል መንገድ ለሚሠሩ በር አንክፈት!
  • አንድነታችን የበለጠ እንዲጸና እንጸልይ!
  • በተለያየ ቤተ ክርስቲያንን በማይወክሉ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ነገሮች ሁሉ እንደ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ሊታዩ አይችሉምና በጥንቃቄ መረጃዎችን እንይ
  • ምእመናንን ሊከፋፍል የሚችሉ ወሬዎች እየተለቀቁ ስለሆነ በጥንቃቄ እንከታተል
  • ሚዲያዎችም ጥንቃቄ ቢያደርጉ በጎ ሚያሰኝ ነው፣ ምእመናንን በመከፋፈል የሚገኝ ጽድቅ የለምና፡፡
  • እግዚአብሔር ከፈቀደው በቀር ማንም ሊመረጥ አይችልምና ከወዲሁ ተረብሸን የወደፊቱ ክርስትናችን ፍቅር የጎደለው እንዳይሆን እንጠንቀቅ
  • ሊመርጡ /ሊወስኑ/ ለሚችሉ ባላደራዎች ፈንታውን እንስጥ እንጂ በማንወስነው ጉዳይ አስቀድመን አንፈርጅ
  • ይልቁንም ሁሉን ማድረግ ለሚቻለው እግዚአብሔር አደራ እንስጥ፡፡

 

በዚህ በቃ ይበለን! ከዚህ በላይ በመከፋፈልና በመለያት እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አያሳየን!!!

 

ወስብሐት ለእግዚአበሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመሰቀሉ ክቡር አሜን!!!

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ 31ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጧት 3 ሰዓት ላይ በተካሄደው ጸሎት ተከፈተ፡፡

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


ጉባኤው ከዛሬ ጥቅምት 6 ቀን ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ጥቅምት 11 ቀን ድረስ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አማካኝነት አምስት አባላት ያሉበት አርቃቂ ኮሚቴ የተሰየመ ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቢ መንበረ ፓትርያርክ የጉባኤው መክፈቻ ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በዚሁ ቃለ ቡራኬያቸው “በዚህ ጉባኤ የታደማችሁ አባቶቼ ወንድሞቼ እንኳን ለዚህ ቀን አደረሳችሁ፡፡” ካሉ በኋላ  “ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ ቅዱሳን ያሰኘቻቸው ልጆቿ አያሌ ናቸው፡፡ ቅድስናናን የሚያሰጠው የቤተ ክርስቲያናችን ትውፊት ጠብቀን በቤተ ክርስቲያናችን ሊሠራ የሚገባውን ወስነን እንሠራለን” ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በ2005 ዓ.ም. ለመፈጸም ያሰበቻቸውን የዕቅድ ሪፓርት በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ፊሊጶስ የቀረበ ሲሆን ብፁዕነታቸው “በልዑል እግዚአብሔር አባታዊ ፈቃድ ከሐምሌ ወር 2003 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ወጥተን ወርደን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እድገትና ልማት፣ በሕዝባችን ሰላምና አንድነት፣ ሠርተን የሥራችንን የሥራ ክንውኖችና ውጤቶች እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነን ለመገምገም ያበቃንንና የሰበሰበንን አምላክ ደግመን ደጋግመን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ በብፁዕ ሥራ አስኪያጅ ጋባዥነትም በአቶ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ የ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ ክንውን አጠቃላይ ሪፓርት ቀርቧል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ በሪፓርታቸው፡- “ቅርሶችን በዓለም ዐቀፍ ምዝገባ ሰነድ ለማስያዝና የደመራ መስቀል በዓላችንን በዮኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ እንዲሁም የቅዱስ ያሬድ ዜማንና ሥርዐቱን ፊደላትና አኀዞችን የጥምቀት በዓልንም በቀጣይ ለማስመዝገብ ጥናቱ ተፈጽሟል” ብለዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን አማካኝነት በ2004 ዓ.ም. የተሠራውን አስመልክቶ ሲናገሩ “በተቀናጀ የገጠር ልማት 26,864,687.00/ በመመደብ 923,254 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዐሥር ፕሮጀክቶችን በተለያዩ ክልሎች ዘርግቶ ሠርቷል፡፡ ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ፣ በተቀናጀ የገጠር ልማት፣ በውኃ አቅርቦትና ንጽሕና አጠባበቅ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን በመከላከል፣ በገዳማት ልማት፣ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ክብካቤና ድጋፍ 26 ፕሮጀክቶን ዘርግቶ በ120,955,270.00 ብር በጀት ተግባራዊ አድርጓል” ብለዋል፡፡ ከሻይ እረፍት መልስ “ግጭት፣ የግጭት መንስኤና አፈታት” በሚል ርዕስ በልማት ኮሚሽን የስደተኞች ጉዳይ ሓላፊ አቶ ይልቃል ሽፈራው አማካኝነት ቀርቦ በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አማካኝነት ጉባኤው ተወያይቷል፡፡

 

ከምሳ ሰዓት በፊት የነበረው መርሐ ግብርም 6 ሰዓት ከሃያ ላይ በጸሎት ተዘግቷል፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ

ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤውን ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው ሀርመኒ ሆቴል አካሂዷል፡፡ በጉባኤው ላይ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የሲዳማ ጌዲኦ ቡርጂና አማሮ ልዩ ልዩ ወረዳዎች  ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ዶክተር አባ ኀይለ ማርያም መልሴ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ጨምሮ ከአብያተ ክርስቲያናት የተወከሉና የማኅበሩ አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በአሁኑ ጊዜ በትርጉም፣ በኅትመትና በስርጭት ሥራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ያስታወሱት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ይልማ ጌታሁን “በዘመናችን እየጨመረ የመጣውን የቅዱሳት መጽሐፍት ፍላጎት ስንመለከት ጥረታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር እንዳለብን ይታመናል፡፡ ይህንን ተግባር ደግሞ በተገቢው መንገድ ለማከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሓላፊነታቸውን ባግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ ማኅበሩ በያዝነው ዓመት በሰባት ዋና ዋና ዘርፎች ሊሠራቸው ያሰባቸውን ዕቅዶች በሪፖርታቸው ያካተቱት  ዋና ጸሐፊው፥ በአባላት ምዝገባና በቅስቀሳ ዘርፍ ሁሉንም ክርስቲያን ለማሳተፍ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳና ምዝገባ ለማከናወን እንዳቀደ አስታውቀዋል፡፡

 

በኢትዮጵያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የወንጌላውያን ኅብረትና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአባልነት ተካተዋል፡፡

Dn. mulugeta

በአባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላሙ ውይይት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

ጥቅምት 2 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


Dn. mulugetaየማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራርና የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤያት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ በአስተዳደርና በተወሰኑ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን አተረጓጎም ልዩነት ምክንያት ለሁለት አሠርት ዓመታት ተለያይተው በቆዩ አባቶች መካከል የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት እስከ መጨረሻው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ “የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳ በአገር ውስጥና በውጪ አገር በሚገኙ አባቶች መካከል የተጀመረው ውይይት ከሁሉም ጉዳዮች በፊት ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራና እንዲፈጸም የማኅበሩ ፍላጎት መሆኑን ለማስታወቅና እንደ ጥያቄም ለማቅረብ ነው፡፡” በማለት መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ስለተካሄደው ስብሰባ መግለጫ የሰጡት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኀይለ ማርያም ናቸው፡፡

 

ዋና ጸሐፊው ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ “የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ሌሎቹም ምእመናን የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተግተው መጸለይ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የሰላሙንና የዕርቁን ሁኔታ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን ከማድረግ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱም አንድነቷ ተመልሶ የምትሠራበት ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ ማኅበሩ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመፈጸም ዝግጁ ነው፡፡ ስለሆነም የማኅበሩ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መምህራን ጭምር የማኅበሩን አቋም የማስታወቅ ሓላፊነት አለባቸው፡፡” ብለዋል፡፡

 

እርቁ እንዴት ይሁን? እንዴት ይፈጸም የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጣቸው በሁለቱም ቦታዎች በሚገኙ አባቶችና በአስታሪቂ ሽማግሌዎች መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት መተው እንደሚገባ ያስታወቁት ዲ/ን ሙሉጌታ የተጀመረው እርቅ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግና እግዚአብሔርንም በጸሎት እንዲማጸን አሳስበዋል፡፡

 

ዋና ጸሐፊው በማጠቃለያ መልእክታቸው፡- “ፍቅር ሰላምና አንድነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ስምረት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፡፡ ሁል ጊዜ ለፍቅር ለመግባባትና አብሮ ለመሥራት በሰላም ለመኖር ሁሉም መጣር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የሚያደናቅፍ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ አንድነትን የሚጠላ ፍቅርን የሚጠላ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ለዚህ ጉዳይ መትጋት ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡

እነሆ ክረምት አለፈ

 

ጥቅምት 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“እነሆ ክረምት አለፈ ዝናሙም አልፎ ሄደ አበባው በምድር ላይ ታየ የመከር ጊዜ ደረሰ የቁርዬውም ድምጽ ተሰማ በለሱ ጎመራ ወይኖቹም አበቡ” መኀ.2፥11-13

 

ከዚህ ቀድሞ እንደተመለከትነው ክረምት ወርኀ ማይ/ውኃ/ ወርኀ ልምላሜ ወንዞች የሚሞሉበት ደመናና ጉም የሚሳብበት ሰማይ በደመና ተሸፍኖ የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚያስተምርበት በመብረቅ በነጎድጓድ ድምጽ ታጅቦ ኀይለ እግዚአብሔርን የሚያስረዳበት መሆኑን ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ግን መግቦቱን ጨርሶ እነሆ ክረምት አለፈ ጊዜውንም በክረምት ከሚታየው ልምላሜ ቀጥሎ ለሚመጡ ለአበባና ለፍሬ አስረክቦ ከልምላሜ ቀጥለው የምናያቸው አበባና ፍሬ የሚያስተምሩት ቁም ነገር አለና፡፡

 

ከአበቦች ምን እንማራለን?

አበቦች ውብና ማራኪ አስደሳች ከመሆናቸው የተነሣ የሰው ልጅ በሙሉ አበቦችን ይፈልጋል ምድርም በአበቦች አጊጣ ተሸልማ ስትታይ ክረምት ከለበሰችው ልምላሜ ይበልጥ ታስደስታለች፡፡ “አሰርገዎ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ አሰርገዋ በሥነ ጽጌያት” ሰማይን በከዋክብት አስጌጠው ምድርንም በአበቦች ደምግባት ሸለማት” ብሎ ቅዱስ ያሬድ ዘምሯል፡፡ ከዚህ የምንረዳው አምላካችን የሁሉ ጌጥ መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፈ ኪዳን “ሠርጎ ዓለም ሣራሪሃ ለምድር ወኩሎ ተከለ ለሠርጎ ዓለም፡፡” የዓለም ጌጥ ምድርን የፈጠራት ሁሉንም ለዓለም ጌጥ ፈጠረ” ተብሎ ተጽፏል፡፡ በሜትር የማይለካ ሰማይን በከዋክብት፣ በፀሐይ፣ በጨረቃ ስፋቷ በዐይነ ገመድ የማይመጠን ምድር በአበባ ማስጌጥ ከቻለ ለሦስት ክንድ ከስንዝር የሆነ የሰውን ልጅ ማልበስ ማስጌጥ መሸለም ለምን አይችልም? ይችላል እንጂ፡፡ ታዲያ ከላይ የተመለከትናቸው ሁሉ የሚናገሩት የእግዚአብሔርን ከሓሊነት ነው፡፡ አፍ ሳይኖራቸው ይናገራሉ፤ አንደበትም ሳይኖራቸው ይመሰክራሉ፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ጌታችን ሲያስተምር እንዲህ አለ “ወበእንተ አራዝኒ ምንተኑ ትሄልዩ ርዕዩ ጽጌያተ ገዳም ዘከመ ይልህቁ ኢይፈትሉ ወኢይጸምው ወባህቱ እብለክሙ ከመ ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ በኩሉ ክብሩ ከመ አሐዱ እምዕሉ” ማቴ.6፥28፡፡

 

ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ! እንዴት እንደሚያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ! አይደክሙም አይፈትሉም ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞን ስንኳን በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” ብሎ አበቦች ከእግዚአብሔር አግኝተው ነው ጌጥን ውበትን ተጎናጽፈው የሚኖሩት ለእነዚህ አበቦች ውበትን መውደድን የሰጠ እግዚአብሔር ለእኛም ይሰጠናል ብሎ ማመን የሚገባ መሆኑን በመግለጽ ሰው ምን እለብሳለሁ በምን አጌጣለሁ ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ እግዚአብሔር በተፈጥሮ ውብ አድርጎ የፈጠረው እንደሆነ በማሰብ የጎደለው ሁሉ ከእግዚአብሔር የሚገኝ እንጂ በጭንቀት በመወጠርና በማማረር እንደማይገኝ ይልቁንም አበቦችን እንዲህ ያስጌጠ አምላክ ለእያንዳንዳችን የሚያስፈልገንን ሁሉ መስጠት የሚችል መሆኑን ማወቅ የተሻለ ነው፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል እንጂ መጨነቅ ሊሆን እንደማይገባም ያስተምረናል አበቦች ይህን ውበት ያገኙት በመጨነቅ አይደለም ሰውስ ከአበባ እንዴት ያንሳል?

 

በትክክል ሰው አበባን ይመስላል አበባ ያብባል በመልካም መዓዛው ከሰው ጀምሮ እስከ ጥቃቅን ፍጥረታት ድረስ ይማርካል ከአበባ ላይ መስፈር የሚፈልጉት ንቦች ብቻ አይደሉም ትንኞችና ዝንቦችም ጭምር እንጂ፡፡ ንቦች ማር ይሠሩበታል ዝንቦችና ትንኞች ደግሞ ቆሻሻቸውን ያራግፉበታል፡፡ ከዚህ በኋላ አበባው ይጠወልጋል ይረግፋል የሚከቡት ንቦችም ሆኑ ትንኞችና ዝንቦች አይፈልጉትም፡፡ አበባ በጊዜ ማራኪና አስደሳች ቢሆን ሲደርቅ ግን የሚፈልገው የለም የሚረግጠው እንጂ፡፡ አበባ ሲደርቅ አበባ መሆኑ እንኳን ይዘነጋል፡፡ በዚያን ጊዜ ወዳጁ ሁሉ ይርቀዋል ያን ጊዜ ወዳጅ የሚሆነው መደፋት አሊያም እሳት ብቻ ነው፡፡

 

ሰውም በእውነቱ ይህን ይመስላል ሲወለድ እናት አባት ዘመድ አዝማድ ወዳጅ በመወለዱ ይደሰታል፡፡ ሲያድግ አንተ ልጅ የማነህ አቡሽዬ የሚለው የሚስመው የሚከበው ይበዛል ሁሉም ምነው እንደዚህ ልጅ በሆንኩኝ አይ ልጅነት እያለ ይመኛል፡፡ ልጁ ካደገ በኋላ ግን እንደ አበባው ደረቅ እያለ የሚያስከፋ የሚያሳዝን፣ የሚያሰቃይም ሕይወቱ አላዋቂ አጫጅ እንደ አጨደው የፈረስ ሳር  ምስቅልቅል ያለ ሀዘንና መከራ የከበቡት ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን አበባውን ዝንቦች ትንኞች እንዲሁም ማር መሥራት የሚችሉ ንቦች እንደሚከቡት ሰውንም እንደመአር የሚጣፍጥ መልካም ሥራ እንዲሠራ የሚረዱት መላእክት ይከቡታል ይረዱታል፤ ይላላኩታል በአንጻሩ ደግሞ እንደ ቆሻሻ የኀጢአትን ክምር የሚጭኑበት አጋንንት እንደ ትንኝና ዝንብ ከበው ኅሊናውን በክፉ ሐሳብ ያቆሽሹታል፡፡ በመላእክት ተከቦና ታጅቦ መልካም ሥራ ሲሠራ እግዚአብሔርንም ሰውንም ራሱንም መላእክትንም ያስደስታል፡፡ በፍቅሩም አሕዛብን ይማርካል፡፡ በሌላ መልኩ አጋንንት እንደዝንቦችና ትንኞች በላዩ ላይ ሰፍረው የኀጢአት ቆሻሻቸው መጣያ አድርገውት ክፉ እየሠራ ሲታይ እግዚአብሔርንም መላእክትንም ሰውንም ያሳዝናል አበባው ደርቆ ሲወድቅ እንደሚያስጠላ እርሱም ያንን ይመስላል፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ነው ኢሳይያስ እንዲህ ብሎ ያስተማረው “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው፡፡ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው፡፡ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል” ኢሳ.40፥6-8 የሰው ልጅ ሕይወቱ እንዲህ እንደ ሣር ጠፊ እንደ አበባም ረጋፊ ከሆነ በዚህ ጊዜው ንስሐ መግባት ሥጋውን በልቶ ደሙን መጠጣት፤ ስርቆትን፣ ዝሙትን፣ ሐሰትን፣ ትዕቢትን፣ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ቂምን፣ በቀልን፣ ሥጋዊና ሰይጣናዊ ቅናትን አስወግዶ ወደ ፈጣሪው መቅረብ ይገባዋል፡፡ አበባ ዕድሜው አጭር ነው፡፡ ሰውም እንደዚያው ስለሆነ ሰው ሞትን መቅደም አለበት እንጂ ንስሐ ሳይገባ በሞት መቀደም የለበትም፡፡ ሰው በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ሞትን ማሰብ መቻል ይገባዋል፡፡ “አብድ ውእቱ ዘይሄሊ ካልአ ዘእንበለ መቃብሩ ወርስቱ” እርስቱ ከሆነው ከሞትና ከመቃብር ሌላ የሚያስብ ሰነፍ ነው” እንዲል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ

 

በሌላ መልኩ አበባን ስንመለከተው የሚወድቀው፣ የሚረግፈው ፍሬ ለማስገኘት ነው፡፡ አበባ ሲኖር በመአዛው ሰውን ያስደስታል፡፡ ሲረግፍም በፍሬው ይጠቅማል፡፡ ሰው ሲኖርም ሲሞትም ፈጣሪውን የሚያስደስት መሆን አለበት እንጂ ያለፍሬ ንስሐ መሞት የለበትም፡፡ “ግብሩኬ እንከ ፍሬ ሰናየ ዘይደልወክሙ ለንስሐ” ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ማቴ.3፥8

 

“እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ይቆረጣል፡፡ ወደ እሳትም ይጣላል ማቴ.3፥10 ተብሏልና፡፡ ሰውም መልካም ፍሬን አፍርቶ፣ ንስሐ ገብቶ፣ ተዘጋጅቶ፣ የሰማይ ቤቱን ሠርቶ፣ መንግሥተ ሰማያትን ሽቶ፣ ራሱን በንስሐ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ፣ ሰውቶ፣ ከእግዚአብሔር ተጠግቶ፣ መኖር አለበት፡፡ በጭፈራ በስካር የተሰጠውን ጊዜ ማቃጠል ራስንና እግዚአብሔርን መበደል ከቃለ እግዚአብሔር መኮብለል በኀጢአት ገደል መውደቅ በዚህም እንደታላቅ ሰው መመጻደቅ አይገባም፡፡ ጊዜ መሣሪያ እንጂ መቀለጃ አይደለም፡፡ መጽደቂያ እንጂ መኮነኛ፣ መነሻ እንጂ መውደቂያ፣ መሣሪያ እንጂ መክሰሪያ፣ ሊሆን አልተሰጠም፡፡ ታዲያ በዚህ እንደ አበባ በተሰጠን ጊዜ መጠቀም ድርሻችን ነው፡፡ ስለ አበባ ይህን ያክል በጥቂቱ ካልን፡-

 

ከፍሬስ የምንማረው ምንድር ነው?

አበባው ሲያልፍ ፍሬው ይተካል፡፡ ስለፍሬው ለመነጋገር ከዛፎች መነሣቱ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ የአበቦችም የፍሬዎችም ተሸካሚ ወይም አስገኝ ዛፎች ስለሆኑ ያለ ዛፍ ፍሬን ማሰብ ከባል በፊት ልጅ እንደማለት ነውና፡፡ ዕፅዋት፣ አዝርዕት አትክልት ሲያፈሩ በአንድ መንገድ ብቻ አያፈሩም በራሳቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩ አሉ፤ በሥራቸው የሚያፈሩ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምሳሌነት ያላቸው አስተማሪዎች ናቸው በራሳቸው የሚያፈሩት በራሳቸው ጥረው ግረው የሚኖሩ ሰዎች  አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት ሚስት አግብተው፣ ልጅ ወልደው፣ በሐብታቸው ነግደው፣ በንብረታቸው ተጠቅመው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡

 

በሥራቸው የሚያፈሩት ሎሌዎቻቸውን ሠራተኞቻቸውን አዝዘው ልከው የሚኖሩ ሰዎች አምሳል ናቸው ይህ ሰሙ ነው ወርቁ ግን “አንዱ መቶ አንዱ ስልሣ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ” ማቴ.13፥8-10፡፡

 

በራሳቸው የሚያፈሩት የባለመቶ ክብር አምሳል ናቸው፡፡ በጎናቸው የሚያፈሩት የባለ ሥልሳ ክብር በሥራቸው የሚያፈሩት የባለ ሠላሳ ክብር አምሳል ናቸው፡፡

 

ከነዚህም አዝርዕት፣ ዕፅዋት፣ አትክልት ወገን በራሳቸው በጎናቸው በጫፋቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ አሉ፡፡ በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ አሉ እነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

 

በራሳቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ወፍ ጠርጥሮት፣ ጠላት ለቅሞት የሚቀሩ በዚህ ዓለም ብዙ ትሩፋት፣ ብዙ ምግባር ሠርተው ይዩልን፣ ይሰሙልን፣ ይወቁልን ብለው በከንቱ ውዳሴ ተጎድተው በወዲያኛው ዓለም ሳይጠቀሙ የሚቀሩ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡

 

በሥራቸው አፍርተው ፍሬያቸውን ከወፍ ከጠላት ሰውረው የሚያስቀሩ በዚህ ዓለም ሲኖሩ ብዙ ትሩፋት ምግባር ሰርተው አብልተው አላበላንም፣ አጠጥተው አላጠጣንም፣ አልብሰው አላለበስንም እያሉ ክብራቸውን ሸሽገው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙት አምሳል ናቸው፡፡

 

ዳግመኛም ከአንድ መሬት በቅለው የሚበሉ የማይበሉ፣ የሚጣፍጡ የማይጣፍጡ፣ ሬትና መርዝ፣ ወይንና ትርንጎ ይገኛሉ፡፡ ሬትና መርዝ የኀጥአን፣ ወይንና ትረንጎ የጻድቃን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ከአንድ መሬት በቅለው በመጣፈጥና በመምረር እንዲለዩ ጻድቃንና ኀጥአንም ከአንድ ከአዳም ከአራቱ ባሕርያት ተፈጥረው በምግባርና በሃይማኖት፣ በክህደትና በኀጢአት፣ በክፋትና በበጎነት ተለይተው ሲኖሩ ጻድቃን ወደ ጎተራው መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ፡፡ ኀጥአን ግን አይገቡም፡፡ ወደ ገሃነመ እሳት ይወርዳሉ እንጂ፡፡ “ፍሬያቸው ሐሞት ነው፡፡ ዘለዓለም መራራ ነው” እንዲል ዘዳ.32፥33፡፡

 

እነዚህ አዝርዕት፣ አትክልት፣ ዕፅዋት በየዘራቸው ይበቅላሉ እንጂ ያለ ዘራቸው አይበቅሉም፡፡ ፍሬም አይሰጡም፡፡ እንደዚሁም ጻድቃንና ኀጥአንም ያለ ዘራቸው ያለ ቤታቸው አይበቅሉም፡፡

 

“ወእምፍሬሆሙ ተአምርዎሙ እስመ ዕፅ ሠናይ ፍሬ ሰናየ ይፈሪ ወዕኩይሰ ዕፅ ፍሬ እኩየ ይፈሪ” ማቴ.7፥16-18


“ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያደርጋል”

 

ከአዝርዕት ከአትክልት ክረምት ለምልመው በጋ የሚደርቁ ክረምት ደርቀው በበጋ የሚለመልሙ አሉ፡፡ በክረምት ለምልመው በበጋ የሚደርቁት በዚህ ዓለም ሳሉ በልተው፣ ጠጥተው፣ ለብሰው፣ ሞግሰው በዚያኛው ዓለም የማይጠቀሙት ናቸው፡፡ እንደነዌ ያሉ ሉቃ.16፥25

 

ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመለሙት በዚህ ዓለም ሲኖሩ ተርበው ታርዘው ጎስቁለው በወዲያኛው ዓለም የሚጠቀሙ ሰዎች አምሳል ናቸው፡፡ እንደ አልዓዛር እንደ ኢዮብ ያሉ ናቸው፡፡ ኢዮ.2፥1፣ ሉቃ.16፥19 ስለዚህ እኛም የሰው ልጆች መራራ ሳይሆን ጣፋጭ፣ ጠላት የሚለቅመው ሳይሆን፣ ከጠላት የሚሰውረውን ፍሬ፣ ክረምት ለምለሞ በጋ የሚደርውን ሳይሆን ክረምት ደርቀው በጋ የሚለመልሙትን መሆን አለብን፡፡

 

እግዚአብሔር በቸርነቱ በምሕረቱ ይርዳን፡፡

ይቆየን

የቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ ረቂቅ ይመከርበት!

መስከረም 30 ቀን 2005

ሰበካ ጉባኤ በካህናትና በምእመናን ኅብረት ላይ የቆመ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ሥርዐት ነው፡፡ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ባሉት መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በየደረጃው አመራር ይሰጣል፣

 

ዕቅድ ያወጣል፣ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ጉባኤው ቤተ ክርስቲያናችን ከመሬት ስሪት ተነሥታ በሕዝብ ባለቤትነት ላይ የተመሠረተችበትና ሕጋዊ ሰውነት ያገኘችበትም የሕግ አካል ነው፡፡

 

በየደረጃው በሚያወጣቸው ዕቅዶች፣ በሚሰጣቸው አመራርና በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎቹ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቃል፡፡ አገልግሎቷንም የተሟላ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር እንዲደራጁ በማድረግ ችሎታቸውን ተጠቅሞ ኑሮአቸውን ያሻሽላል፡፡ ምእመናንን ለማብዛትና በመንፈሳዊ ዕውቀት ጎልምሰው በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡

 

እነዚህን ዓላማዎቹን ከማስፈጸም አኳያ ጾታ ካህናትና ጾታ ምእመናን /ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ሊቃውንት፣ ወጣቶች/ በምልዐት የተወከሉበትም በመሆኑ አሳታፊ ነው፡፡

 

ይሁንና በአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ደረጃ የምእመናን ንቃተ ሕሊና እየዳበረ ቢሆንም ተሳትፎው በሚፈለገው ደረጃ እያደገ አይደለም፡፡ ሰበካ ጉባኤ በወረዳ ቤተ ክህነትና በመንበረ ጵጵስና አካባቢ የተረሳም ይመስላል፡፡ በየዓመቱ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቢካሔድም፤ በጉባኤውም አልፎ አልፎ ሥልጠናዎች መስጠታቸው ቢበረታቱም ወደ መሬት የማይወርዱ ወደ ተግባር የማይለወጡ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

 

ዘንድሮም ከጥቅምት 6-11 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ሠላሳ አንደኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይካሔዳል፡፡ እናም ተገቢ /የካህናት፣ የወጣቶችና የምእመናን/ የውክልና ተሳትፎው እንዲጠበቅ፣ ከተለመደው ሪፖርታዊ መግለጫ በዘለለ ቁም ነገራዊ አጀንዳ ተኮር ቢሆን፤ አጀንዳዎቹ በወቅታዊና ዘላቂ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ፣ አወያይና አሳታፊ ሊሆኑ ይገባል እንላለን፡፡

 

ከሪፖርት አቀራረብ ጋር በተያያዘም የአህጉረ ስብከት ሪፖርት በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ተጠቃሎ ቢቀርብና የቁጥጥር አገልግሎት ሪፖርት ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ከማስፈን አኳያ ራሱን ችሎና ለብቻው ተለይቶ ቢቀርብና ተገቢ የሆነ ውይይትም ሊደረግበት ይገባል፡፡

 

በዘንድሮው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው ማሻሻያ ረቂቅ፣ ተቋማዊ ማሻሻያ (Structural Reform)፣ በዕርቀ ሰላሙ እውንነት ላይ፣ በፓትርያርክ ምርጫ አፈጻጸም ሥርዐት ላይ አተኩሮ እንዲወያይና የውሳኔ አሳብ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያሳልፍ ቢደረግ፤ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ዕረፍት በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይና በቀጣይነት ሊደረጉ የሚገባቸውን የሚጠቁም ሰነድ በዐቃቤ መንበሩ የሚመራው ኮሚቴ አዘጋጅቶ የጉባኤው ተሳታፊ እንዲወያይበት ሊደረግ ይገባል፡፡ ጉባኤው ዕቅድና በጀት መትከል ቢጀምር፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥልትን አቅጣጫ ቢበይን ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን እናምናለን፡፡

 

ሌላው ቢቀር እንኳን የቃለ ዓዋዲው ማሻሻያዎች ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ሠላሳ አንደኛ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንዲመክሩበትና እንዲያዳብሩት ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

 

ይህን ስንል የቃለ ዓዋዲው መሻሻል የአሁኑንና የቀጣዩን ዘመን የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ ርምጃ ለማስቀጠል የላቀ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡

 

በዚህ መልኩ የቃለ ዓዋዲው መሻሻል ተግባራዊ መሆን ለመዋቅር ማሻሻያችን መርሕ ይሆናል፤ የሕግ አውጪውን፣ ሕግ አስፈጻሚውንና የሕግ ተርጓሚውን ተግባር፣ ሥልጣንና ሓላፊነት በመለየት፡-

 

  • ተጠያቂነትና ግልጽነት እንዲሰፍን፣
  • የቤተ ክርስቲያናችን ሀብት /የሰው ኀይል፣ የገንዘብና ንብረት/ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል፣
  • ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊነት ምሳሌያዊ የሆነችና ሞራላዊ የበላይነት ያላት ተቋም እንድትሆን /በብኩንነት፣ ምዝበራና ዘረፋ ላይ/ ያስችላታል፡፡

 

በዓለም አቀፍም ደረጃ /በውጭው ዓለም/ ላለችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም የበለጠ የመስፋፋትና የአንድነት በርን ይከፍታል እንላለን፡፡

 

ስለዚህ የዘንድሮ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቃለ ዓዋዲው ማሻሻያ ላይ ለመምከር ባለቤትም፣ ባለሥልጣንም ነውና ይመለከተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ ከዚህም የተለየ፣ ከዚህም የበለጠ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በቃለ ዐዋዲው ማሻሻያዎች ላይ ይምከር! ማሻሻያዎቹን ያዳብር! እንላለን፡፡

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 2  ከጥቅምት 1-15 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ዘመነ ጽጌ

ginbote 26 035

በ44ቱ የሀገር ውስጥ ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤ ይደረጋል

መስከረም 28 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

 

ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥ አገልግሎቱን ለማፋጠን ባቋቋማቸው 44 ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂድ ተገለጸ፡፡

ginbote 26 035የሀገር ውስጥ ማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ማደራጃና ማስተባበሪያ ዋና ክፍል ሓላፊና ምክትል ዋና ጸሓፊ ዲ/ን አንዱአምላክ ይበልጣል እንደገለጹት ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ከጥቅምት 15 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤ በዚህ ወቅት እንዲደረግ ምክንያቱ የማኅበሩ ቀጣይ የ4 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ በማኅበሩ 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማጽደቅ ስለነበረበት መሆኑን ገልጸው ማእከላቱም የቀጣይ 4 ዓመት ዕቅዳቸው በስልታዊ ዕቅድ መሠረት የሚያዘጋጁ ሲሆን የ2005 ዕቅዳቸውም በጉባኤው የሚጸድቅ በመሆኑ ነው፡፡

 

ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ኅዳር መባቻ ድረስ በሚደረገው ጉባኤም በየማእከላቱ ከዋናው ማእከል ተወካይ ልዑክ የሚገኝ ሲሆን በጉባኤውም የ2004 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸምና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ይገመገማል የተለያየ አጀንዳም ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን ጉባኤውም የ2005 ዓ.ም. ዕቅድ በማጽደቅና የአገልግሎት ጊዜያቸውን የፈጸሙ የማእከላት የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

 

በጠቅላላ ጉባኤውም የማእከላቱ አባላት፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች፣ የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ተወካዮች፣ የምእመናን ተወካዮች፣ የወረዳ ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያዎች ተወካዮች ይሳተፋሉ፡፡

 

በዚህ የማእከላት ጠቅላላ ጉባኤ እያንዳንዱ ማእከል ለ2 ቀናት የሚቆይ ጉባኤ የሚያደርግ መሆኑን የገለጹት ዲ/ን አንዱ አምላክ ይበልጣል ከማእከላቱ ጠቅላላ ጉባኤ በመቀጠልም በማእከላቱ ስር የሚገኙ ወረዳ ማእከላት ጠቅላላ ጉባኤያቸው የሚያከናውኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በሀገር ውስጥ ብቻ 44 ማእከላት፣ 333 ወረዳ ማእከላት 183 ግንኙነት ጣቢያዎችና 325 የግቢ ጉባኤያትን ያዋቀረ መሆኑ ይታወቃል፡፡

meskel 1

መስቀል (ለሕፃናት)

መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም


ቢኒያም ፍቅረ ማርያም


meskel 1እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ፡፡ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በአዲስ ደብተር፣ በአዲስ እስክርቢቶ፣ በአዲስ ልብስ … ስትማሩ ምን ተሰማችሁ? በጣም ያስደስታል አይደል? ይህ ሁሉ የሆነው እግዚአብሔር አዲስ ዘመን አዲስ ዓመት ስለሰጠን ነው፡፡ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓልም የእግዚአብሔር ሥጦታ ነው፡፡

 

የዘወትር ጸሎት በሚጸለይበት ጊዜ ስለመስቀል እንዲህ የሚል አልሰማችሁም “…መስቀል ኀይላችን ነው፤ ኀይላችን መስቀል ነው፤ የሚያጸናን መስቀል ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፡፡ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን፡፡ ያመንነው እኛ በመስቀሉ እንድናለን፡፡ ድነናልም፡፡ …” እያልን የምንጸልየው እኛ በጉልበታችን፣ በእውቀታችን ባለን ነገር ሁሉ እንዳንመካ፤ ነገር ግን በመስቀሉ እንድንመካ ነው፡፡

 

በመስቀል እንመካለን ምክንያቱም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ማለትም ከአባታችን አዳም ከእናታችን ሔዋን ጀምሮ እስከ አሁን ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስን እንደ ደካማ በመስቀል ተሰቅሎ /ተቸንክሮ/ ድል ስላደረገው፤ አዳምና ሔዋንን ከሲዖል እስራት ነፃ ስላደረጋቸው ነው፡፡ ለእኛም መስቀሉ መመኪያችን ሆኖ ዲያብሎስ መስቀሉን ሲያይ ይሸሸናልና ነው፡፡

 

ልጆች መስከረም 17 የምናከብረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት አይሁድ መስቀሉ የታመሙትን እንደሚፈውስ፣ የሞቱትን እንደሚያስነሣ ባወቁ ጊዜ በክፉ ቅናት ተነሣሥተው በመስቀሉ ክብር እንዳይገኝ ቆፍረው ቀብረውት፣ ቆሻሻ መጣያም አድርገውት ስለነበር እግዚአብሔርም መስቀሉ ተቀብሮ እንዲቀር ስላልፈለገ ንግሥት እሌኒን አስነሥቶ አባ መቃርስ እና አባ ኪራኮስ በሚባሉ አባቶች መሪነት በቦታው በደረሱ ጊዜ ቦታው ከቆሻሻው ክምር የተነሣ ተራራ ሆኖ ስለነበር ትክክለኛው ቦታ የት እንደሆነ ማወቅ አልቻሉም፡፡

 

ንግሥት እሌኒም ወደ እግዚአብሔር በመጸለይዋ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦላት ደመራ እንድትደምር በዚያም ላይ እጣን እንድትጨምር ስለነገራት አገልጋዮቿን ወታደሮቿን ጠርታ በአካባቢው ደመራ እንዲተክሉ፣ እንዲያቀጣጥሉ፣ እጣንም እንዲጨምሩበት ነገረቻቸው፡፡ በተባሉትም መሠረት አድርገው ጢሱ  ወደሰማይ ከወጣ በኋላ በእግዚአብሔር ኀይል ተመልሶ መስቀሉ ወደ ተቀበረበት ተራራ አመለከተ፡፡ በዚህ ጊዜ ንግሥት እሌኒ እና አገልጋዮቿ ደስ አላቸው፡፡

 

ከስድስት ወራት ቁፋሮ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም የታመሙትን ሲፈውስ ሙት ሲያስነሣ በማየታቸው ከሁለቱ መስቀሎች ለመለየት ችለዋል፡፡ ዲያብሎስ በአይሁድ ላይ አድሮ መስቀሉን ቢደብቅም በእግዚአብሔር ኀይል ሊገኝ ችሏል፡፡ ልጆች መስቀላችሁን አትደብቁ እሺ! ቸር ሰንብቱ፡፡

ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ዕርቅና ሰላም መሠረት ናቸው

መስከረም 22 ቀን 2005 ዓ.ም.


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የተለያዩ ፈተናዎች የተፈራረቁባት ሲሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ የእግዚአብሔር ማደሪያ ነችና የመጣውን የፈተና ጎርፍና ነፋስ ሁሉ ተቋቁማ አሁን ላለንበት ዘመን ደርሳለች፡፡ የዐላውያን ገዢዎችን ሰይፍ ከውስጥም ከውጭም የነበሩ መናፍቃንን ቅሰጣ ተሻግራ እስከአሁን የሐዋርያትን፣ የቅዱሳን ሊቃውንትን የአትናቴዎስን የቄርሎስን ሃይማኖት ይዛ ተገኝታለች፡፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የሚመጡባትን ፈተናዎች የምታደንቅ፣ በዚያም ተስፋ የምትቆርጥ አይደለችም፡፡ ሁል ጊዜም ቢሆን የገሃነም ደጆች የሚሰብቁት ግልጽና ስውር ጦር እንዳለ ስለምታውቅ ከሚመጣው ፈተና ሁሉ አሸንፋ ትወጣ ዘንድ ወደ አምላኳ ትለምናለች እንጂ፡፡

 

በዚህ ባለንበትም ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ካጋጠሟት ከባድ ፈተናዎች አንዱ ለሃያ ዓመታት ያህል የቆየው የአባቶች መለያየት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ታሪኮች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እንግዳ ነገር ባይሆኑም የሚያስከትሉት ጉዳት ግን ቀላል የማይባል ነው፡፡ በማወቅም ባለማወቅም ከውስጥ ወይም ከውጪ በሆኑ ምክንያቶች እንዲህ ያሉ መለያየቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ዋናው ነጥብ ግን ከርስትና በሃይማኖት ምክንያት ካልሆነ በቀር ለመለያየት፣ መንጋን ለመበተን ወይም ለመከፋፈል የሚያበቃ ሥነ ኅሊና /ሞራል/ የሚሰጥ ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሃይማኖታችን ተስፋ እንድናደርግ የሚነግረንን የእግዚአብሔር ጸጋ ሁሉ መንግሥቱንም ማግኘት የሚቻለው የዕርቅና ሰላም ሕይወት ሲኖረን ነው፡፡ ጌታችን “እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” እንዳለ የሕጉ ሁሉ ፍጻሜ ነው፡፡ /ዮሐ.15፥12/ እርስ በእርስ ብቻም ሳይሆን ብንችል ከሁሉም ጋር በሰላም እንድንኖር ታዘናል፡፡ ያለሰላምና ፍቅር ቤተ ክርብስቲያንን ማነጽ ማጽናትም አይቻልም፡፡

 

በ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን ያጋጠማት መከፋፈል ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሞግዚት አስተዳደር ነጻ ወጥተን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በተመሠረተው መንበረ ፓትርያርክ ጥንካሬ እና አሠራር ላይ ጥያቄም የሚያስነሣ ሆኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የውጪና የሀገር ውስጥ የአገልግሎት እንቅስቃሴዎችም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሱ፣ የስደተኛው፣ የገለልተኛው ወዘተ እየተባለች ሁሉም እንደፈቃዱ የሚኖርባት ሆና ቆይታለች፡፡

 

እነዚህ ነገሮች ዕረፍት የነሧቸው የተለያዩ ወገኖችም በአባቶች መካከል ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹ እልባት አግኝተው ቤተ ክርስቲያኒቱ ወደቀድሞው አንድነቷ ሳትመለስ በሂደት ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዐረፉ፡፡ የእርሳቸው ዕረፍትን ተከትሎም ችግሮቹ የበለጠ እንዳይወሳሰቡና መቋጫ ሳያገኙ ወደባሰ ቀውስ፣ አለመረጋጋትና ማባሪያ ወደሌለው መወጋገዝ እንዳይገባ እስከቀጣዩ ፓትርያርክ ሢመት ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ከመቼው ጊዜ በላቀ ሁኔታ እንዲቀጥል ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ ሁሉም ወገን ግፊት እያደረገ ነው፡፡

 

አገልግሎቱን አጠናክሮ የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ነገር ሁሉ ማየት ዋነኛ ግቡ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ጉዳይ በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ መለያየቱ በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን በተጨባጭ ያየው ማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቤተሰቦች ጉዳዩ አንገብጋቢ መሆኑን ይረዳል፡፡

 

በዚህ መለያየት ውስጥ ዓላማቸውን ለመፈጸም ይጥሩ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ ለመንሰራፋትም ይውተረተሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አገልግሎታችንም በሚፈለገው ደረጃ በፍጥነት ሄዷል ማለት አይቻልም፡፡ በርካታ ምእመናን በመናፍቃን ተወስደዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚፈለገውንም ያህል ሀገራዊ አስተዋጽኦ ስታደርግ ቆይታለች ለማለት አያስደፍርም፡፡

 

ሌሎች ምክንያቶችም እንዳሉ ሆነው ይኸው በአባቶች መካከል ያለው መለያየትም ከላይ ለዘረዘርናቸው ውስንነቶች የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ መንበረ ፓትርያርክና ቅዱስ ሲኖዶስ ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ቁጥጥር ተላቀው ያገኙትን መንፈሳዊ ሥልጣንና መንበር በተሻለ አሠራር ወደላቀ የአገልግሎት አቅም የሚያደርሱበትን ሁነኛ ጊዜዎች በእነዚህ መለያየቶች ምክንያት አባክነዋል ማለት ይቻላል፡፡ የተሻለ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት ማሳየት ሲቻል ወደ ኋላ ለመመለሱ አስተዋጾኦ አድርጓል፡፡ ይህ በሁሉም ልብ ያለ ሐዘን እንዲቀረፍ አባቶች ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም በቀላሉ ተፈቶ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ ሳንችል መዘግየታችን ትውልዳችንንም የሚያስወቅስ ሆኗል፡፡

 

ይሁን እንጂ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ ተጀምሮ የነበረው የዕርቅና ሰላም ሂደት አሁን እልባት እንዲሰጠው የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ መግባታችንን ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ማኅበራችን የዕርቅና ሰላሙ ጉዳይ አስተዳደራዊ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን የክርስቲያናዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር ጉዳይ መሆኑ እንዲታሰብበት ይሻል፡፡ ስለዚህ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድና ችግሩን ለመፍታት በሚያሳምን ደረጃ መንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ ጉዳዩም ክብደት እንዲሰጠው ይፈልጋል፡፡ የምናገለግላት ቤተ ክርስቲያን በየምክንያቱ እየተለያየች ባለብዙ መዋቅር ስትሆን ማየት የማይታገሱት ነገር ነው፡፡ የዕርቅና የሰላም ሂደቶቹም ውጤት በግልጽ እየቀረቡ ሕዝበ ክርስቲያኑም ግፊት እንዲየደርግባቸው ይሻል፡፡

 

ለዚህም በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቁ ለመንጋውም እንዲጠነቀቁ አደራ የተሰጣቸው ብፁዓን አባቶች ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ዕርቅና ሰላምን በቤተ ክርስቲያን አስፍኖ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለአገልግሎት የሚመች ስልታዊ አካሄድ አሠራርና አደረጃጀት እንዲሰፍን መፍቀድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንንም ከእግዚአብሔር የሆነውን አደራ ከመጠበቅ አንጻር፣ ለአገልግሎቱ ስኬት ከማምጣት፣ ምእመናን በአገልግሎቱ ረክተው እንዲጸኑ ከማድረግ፣ በታሪክ ውስጥ ተጠያቂ ካለመሆን አንጻር ሁሉ ሓላፊነትን ሊወጡ ይገባል፡፡

 

ሁሉም የክርስቲያን ወገን ቢሆን ሊረዳው የሚገባው የሰበሰበችን ቤተ ክርስቲያን እጅግ ታሪካዊ ባዕለጸጋና አኩሪ መሆኗን ነው፡፡ የሊቃውንቱ የቅዱስ ያሬድ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ የእነ አቡነ ተክለሃይማኖት የእነ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ልንረዳ ይገባል፡፡ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባታል፡፡ ስለዚህ ክብርና አንድነቷን ዕርቅና ሰላምን በማስፈን ልናጸና ይገባል፡፡ ላለብን ችግር መፍትሔ የሚሰጠውም ፈጣሪ መሆኑን በማመን ብፁዓን አባቶችን በጸሎት መርዳት ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት በጥብቅ እንደምንፈልገውም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መግለጽ ግፊትም ማድረግ ይገባናል፡፡ ለሚፈለገው አንድነት ደግሞ መሠረቱ ዕርቅና ሰላም ነው፡፡

 

ቤተ ክህነቱም እግዚአብሔር ያለፈውን ይቅር እንዲለን፣ ከሚመጣውም እንዲጠብቀን ስለ አንድነታችን በጸሎት ሊተጋ ይገባል፡፡ ያለፈው መልካም ያልሆነው ነገር ሁሉ ሊረሳ፣ በጎው ደግሞ ሊወሳ ይገባል፡፡ በጎ ፈቃድና ሰላምን መውደድ ከሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነው የተረዳነው ነውና ሁሉም ወገን ያንኑ እንዲያጸና መምከር ይጠበቅበታል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳንም በበኩሉ ከዚህ ቀደም ይዞት የቆየውን ይህንኑ አቋም አሁንም ለማስተጋባት የተገደደው ከችግሩ ወቅታዊነትና ከጊዜው አንገብጋቢነት የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ከምንም ዓይነት መዘዝ በጸዳ ሁኔታ፣ ቀኖናዊና ሃይማኖታዊ መሠረቶች ተጠብቀው ዕርቅና ሰላምን የማስፈን እንቅስቃሴው በሚያሳምን ደረጃ ሊኬድበት ይገባል፡፡ የአባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ጥረት ሊመሰገን እንደሚገባው ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ውጤት እስከሚገኝ ለሂደቱ አስፈላጊውን ሁሉ አስተዋጽኦ ሊያበረክት መዘጋጀቱን ለሁሉም ወገን ሊገልጽ ይወዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 20ኛ ዓመት ቁጥር 5 2005 ዓ.ም.