333 (2)

ስትተባበሩ ሁሉንም ታሸንፋላችሁ /ለሕፃናት/

የካቲት 8/2004 ዓ.ም.

በቴዎድሮስ እሸቱ

ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ ከዚህ በታች ያለውን ተረት በደንብ አንብቡ በርካታ ቁም ነገሮችን ታገኙበታላችሁ መልካም ንባብ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን በአንድ ሀገር የሚኖር ሰው ነበር ይህ ሰው ዘጠኝ ልጆች ሲኖሩት ሁሉም እርስ በራሳቸው የማይዋደዱ የማይስማሙ ነበሩ333 (2) ሁሉም አባታቸው የሚያወርሳቸውን የራሳቸውን ድርሻ ይዘው ለብቻቸው መኖር ይፈልጉ ነበር፡፡ ከዚያም አንድ ቀን አባታቸው በጠና ታሞ አልጋ ላይ ተኛ ልጆቹንም ጠራቸውና አንድ ትእዛዝ አዘዛቸው ትእዛዙም “ሁላችሁም ሒዱና ለየራሳችሁ አንድ አንድ ጭራሮ ይዛችሁ ኑ” የሚል ነበር፡፡ ከዚያም ልጆቹ ወደውጪ ሔደው ለየራሳቸው አንድ አንድ ጭራሮ ይዘው ተመለሱ፡፡

 

አባታቸውም ታላቁን ልጅ ጠርቶ የያዝከውን ጭራሮ ስበረው አለው ታላቁ ልጅም ጭራሮዋን ቀሽ አድርጎ ሰበራት እንዲህ እንዲህ እያሉ ሁሉም ልጆች የየራሳቸውን ጭራሮዎች ሰበሯቸው፡፡ ከዚያም አባትየው ትልቁን ልጅ ጠራውና የሁሉንም ወንድሞችህን ጭራሮ ሰብስብ አለው፡፡ታላቁ ልጅም የሁሉንም ጭራሮ ተቀብሎ ሰብስቦ ያዘ አባትየውም በል አሁን የያዝካቸውን ጭራሮ አንድ ላይ ስበራቸው አለው፡፡

22ታላቁ ልጅም ቢሞክር ቢሞክር ቢታገል ጭራሮዎቹን ሊሰብራቸው አልቻለም ሁሉም ልጆች ቢሞክሩ አንድ ላይ የተሰበሰቡትን ጭራሮዎች ሊሰብሯቸው አልቻሉም ከዚያም አባትየው ልጆቹ ወደእርሱ እንዲጠጉ በምልክት ጠራቸውና እንዲህ ብሎ ነገራቸው፡፡

ልጆቼ በመጀመሪያ ሁላችሁም የያዛችኋቸውን ጭራሮዎች በቀላል ሰበራችኋቸው በኋላ ግን333 (1) አንድ ላይ ሲሰበሰቡ ከእናንተ ውስጥ ማናችሁም ልትሰብሩ አልቻላችሁም፡፡ እናንተም የምትለያዩ ከሆነ አንድ ላይ የማትሆኑ ከሆነ ጠላት በቀላሉ ያጠፋችኋል ሌባ ይዘርፋችኋል፤ ጠንካራና ጎበዝ ልትሆኑ አትችሉም፡፡ አንድ ላይ ከሆናችሁ ግን ማንም አይደፍራችሁም፡፡ አሁን እኔ ልሞት ነው የማወርሳችሁን ሀብት በጋራ ተጠቀሙበት በመካከላችሁ መለያየት እንዳይኖር አደራ አላቸው፡፡ ከዚያም ትንሽ ቆይቶ ሞተ እነሱም ከዚያች ዕለት በኋላ ሳይጣሉ እርስ በእርስ በመዋደድ በፍቅር አንድ ላይ መኖር ጀመሩ ተባብረው ስለሚሠሩም ሀብታምና ጠንካሮች መሆን ቻሉ፡፡

ልጆቼ እነዚህ ወንድማማቾች ባይተባበሩ ኖሮ ጠንካሮች መሆን አይችሉም ጠላትም በቀላሉ ያጠቃቸዋል፡፡ እናንተም ከጓደኞቻችሁ በመጠየቅ ለጓደኞቻችሁ የምታውቁትን በማስረዳት ልትተባበሩ ይገባል በትብብር ስታጠኑ የሚከብዳችሁ ሁሉ ይቀላችኋል፡፡

IMG_0038

ምክረ አበው በሐዊረ ሕይወት

  • “ሐዊረ ሕይወት ከመንፈሳዊ ጉዞዎች ሊጠበቁ የሚገባቸውን ተግባራት የሚያመለክት ነው”

የካቲት 5/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

IMG_0038ማኅበረ ቅዱሳንን ከአባላቱ ውጭ ካሉ ምእመናን ጋር የሚያገኘው መድረክ እንደሆነ ይታመናል ሐዊረ ሕይወት መንፈሳዊ ጉዞ፡፡ ከ4 ሺሕ ምእመናን በላይ ይሳተፉበታል ተብሎ ለሚጠበቀው የዘንድሮው ጉዞ ከማንኛውም ጊዜ በላይ በተቀናጀና በተደራጃ መንገድ ዝግጁቱን ለማሳካት ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ የሚያስተባብር አገልጋይም ተመድቧል፡፡ በአገር ቤት ያሉትን ምእመናን ብቻ ሳይሆን ባሕር አቋርጠው ሰማይን ጠቅሰው ለሚመጡ ምእመናን ሁኔታዎች ተደላድለውላቸዋል፡፡ የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ከወትሮው በምን ይለያል? የሚሉ እና ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዲመልሱልን የጉዞውን መርሐ ግብር የሚያስተባብሩትን ዲያቆን ሙሉዓለም ካሳን የመካነ ድራችን እንግዳ አድርገናቸዋል ተከታተሉን፡፡

መካነ ድር፡- እስኪ አጠር አጠር ካሉ ጥያቄዎች ልጀምርና ጉዞው መቼ ይደርጋል? ስንት ቀንስ ይፈጃል?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ይከናወናል፡፡ መርሐ ግብሩም ደርሶ መልስ ነው፡፡

 

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ወደየት ነው የሚደረገው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ጉዞው በደብረ ብርሃን መስመር ወደ በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይደረጋል፡፡

 

መካነ ድር፡– በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም የተመረጠበት ልዩ ምክንያት አለ?

 

ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- ባለፈው ዓመት ከተመለከትነው ልምድ በመነሣት የዚህን ዓመት ጉዞ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህ ዓመት በርካታ ቁጥር ያላቸው ምእመናን ይዘን እንጓዛለን፡፡ በመሆኑም እስከ 4000 ምእመናን እንደሚጓዙ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ይህን በርካታ ቁጥር ሊያስተናግድ /ሊቀበል/ የሚችል የተመቸ መልክዐ ምድር ያስፈልጋል፡፡ በአንጻሩም አቅመ ደካማ ሰዎች በጉዞው መሳተፍ ቢፈልጉ ደርሰው በጊዜ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተለየ መልኩ ደግሞ በተመረጠው ደብር አካባቢ ካሉት አድባራትና ገዳማት በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጥንታዊነቷና በታሪካዊነቷ በውስጧ ከያዘቻቸው የአብነት መምህራንና ደቀመዛሙርት ቀዳሚ በመሆኗ መርጠናታል፡፡

 

መካነ ድር፡- ሐዊረ ሕይወት ማለት ምን ማለት ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ሐዊረ ሕይወት የሚሉ ሁለቱ ቃላት ከግእዝ ቋንቋ የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሙሉ ትርጉማቸውም የሕይወት ጉዞ ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በዓለማችን የሚከናወኑ የተለያዩ የጉዞ ዓይነቶች አሉ አንድ ሰው ለመዝናናትም ይሁን ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ደግሞ አገር ለማየት ይጓዛል፡፡ ያ ጉዞ ሥጋዊና ምድራዊ ጉዞ ነው፡፡ መንፈሳዊ ጉዞ ቀድሞ በብሉያት እንደተፈጸመው በዘመነ ሐዲስም አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘው እሱን አብነት አድርገን እንጓዛለን፡፡ በዓላትን ለማክበር ቅዱሳት መካናትን ለመሳለም ከቦታውም በረከት ለማግኘት እንሔዳለን፡፡ ይህ ጉዞ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት ጉዞ ስለሆነ ሐዊረ ሕይወት /የሕይወት ጉዞ/ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ጉዞ ዝግጅትና ዓላማስ ምን ይመስላል?

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- ስለ ዝግጅቱ ከመናገሬ በፊት ስለጉዞው ዓላማ ከመናገር ብጀምር ይሻላል፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት “ስም ግብርን ይገልጠዋል” ተብሎ እንደተጻፈው ጉዞው ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓላማን ይዞ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው በመሆኑም በሥራ ቦታ በመኖሪያ አካባቢ ባለው ውጣ ውረድ ሁከተ ኅሊና ያጋጥማል፡፡ በተለያየ ምክንያት የተጨነቀና የዛለ አእምሮ በእንደዚህ ዐይነት ጉዞ ይታደሳል፡፡ ቃለ እግዚአብሔር ሲነገርም በተከተተ ልቡና ማዳመጥ ያመቻል፡፡ በእንደዚህ ዐይነት ቦታና ሁኔታ የሚነገር ቃለ እግዚአብሔር ወደ ውስጥ ዘልቆ ይገባል የንስሐ ፍሬንም ያፈራል፡፡ ከቦታውም በረከት ያስገኛል፡፡ በዚያውም በተለያየ አጋጣሚ የእግዚአብሔር ቃል ይሰበካል፡፡ በተለየ አጋጣሚ  የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ለማጠንከር ለመንፈሳዊ ዓላማ ታስቦ የተዘጋጀ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው፡፡ በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ጉዞ ምን ተግባራት እንደሚጠበቁና ጉዞውን ለሚያዘጋጀው ተቋም የሚያስፈልገውን ሥርዐት ለማመልከትም ያግዛል ተጓዦች በአካል በአእምሮ በነፍስ ተዘጋጅተው በቅዱስ ቦታ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ያስተምራል፡፡ የጉዞው ዓላማ ሥጋዊ ጥቅምና ቁሳዊ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ የተዘጋጀ መርሐ ግብር አይደለም ዋናውና ተቀዳሚ ዓላማችን መንፈሳዊ ትርፍ እንጂ ሥጋዊ ትርፍ አይደለም፡፡

 

ዝግጅቱን በተመለከተ ጉዞው የተሳካ እንዲሆን አባቶች በጸሎት እንዲያስቡን አሳስበናል፡፡ የጉዞውን ትኬት በአካል በስልክ በአጭር የስልክ መልእክትና በኢ-ሜል ለማግኘት መረጃ ለሚጠይቁ ምእመናን ተፈላጊውን መረጃ ለመስጠት የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ተመድቧል፡፡ በጉዞው የሚሳተፉት አዲስ አበባ የሚገኙ ምእመናን ብቻ አይደሉም ከክፍለ ሀገርና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ተጓዦች ስለሚኖሩ በጉዞው መርሐ ግብር እንዴት መሳተፍ እንደሚችሉ ከወዲሁ ግንዛቤ በመስጠት ላይ እንገኛለን፡፡

መካነ ድር፡– የጉዞ ቲኬቶችን የት ማግኘት ይቻላል?

 

ዲ/ን ሙሉ ዓለም፡- በአዲስ አበባ ያሉ ምእመናን 5 ኪሎ ሸዋ ዳቦ ፊትለፊት በማኅበረ ቅዱሳን ሐመርና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ማከፋፈያ ሱቅ፣ እሳት አደጋ ፊት ለፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ በቂርቆስ የገበያ አዳራሽ ብሎክ A ቁጥር 230፣ ጎፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ ኮልፌ አጠና ተራ እፎይታ ገበያ ፊት ለፊት ሳሪስ ማከፋፈያ አዲሱ ሰፈር፣ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥር፣ አምስት ኪሎ በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ ሥር ንዋየ ቅዱሳት መሸጫ፣ ዓለም ፀሐይ ድልድይ ፊት ለፊት፣ ኪዳነ ምሕረት ከፍተኛ ክሊኒክ፣ መርካቶ ኬኔዲ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ እቴነሽ የሕንጻ መሣሪያ ቁጥር 107ና ኮስሪሞ ላንድ አውቶብስ ተራ ትልቁ መናኸሪያ ፊት ለፊት ማግኘት ይቻላል፡፡

 

ከክፍለ ሀገር ለሚመጡ ተጓዦች በየርእሰ ከተማቸው ባለው የማኅበረ ቅዱሳን ማእካላት ጽ/ቤት ቲኬቶች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከውጭ ሀገር መምጣት ለሚፈልጉ ምእመናንም http://www.hawirehiywet.somee.com መመዝገብ ይችላሉ፡፡ የውጭ ሀገር ተመዝጋቢዎች ስለ ጉዞው ትኬት ክፍያ በተመለከተ በኢ-ሜይል መልእክት መለዋወጥ ይቻላል፡፡

 

መካነ ድር፡- በጉዞው የሚቀርቡ መርሐ ግብሮች ምንድን ናቸው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም እንደደረሰን ጸሎተ ቅዳሴውን እናደርሳለን፡፡ ከቅዳሴ ውጭ በቤተ ክርስቲያኑ ካህናት ሊቃውንትና ደቀ መዛሙርት ጋር በመሆን የጋራ ጸሎት እናደርሳለን በመቀጠል በማኅበርና በግል የተጋበዙ ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀርባሉ፡፡ በገና ደርዳሪዎችም የበገና መዝሙር ያሰማሉ ከዚያም በሊቃውንት አባቶቻችን ትምሕርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ በመጨረሻም ትምህርት ያከናወኑ፣ ምሥጢር ያደላደሉ፣ በእድሜ የበሰሉ በመከራ የተፈተኑ አባቶቻችን የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ምክረ አበው በምእመናን በጣም የሚወደድና የሚናፈቅ መርሐ ግብር በመሆኑ ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር የምእመናን ጥያቄ ይመለሳል፡፡ ሕይወታቸውም ይስተካከል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በተዘጋጀው የጉዞ ትኬት ላይ እንደተገለጠው ምእመናን ጥያቄያቸውን በስልክ፣ በኢ-ሜይል በአጭር የሞባይል መልእክት በተለይም በአካል በመቅረብ ጥያቄአቸውን ማቅረብ ይችላሉ፡፡

 

መካነ ድር፡- ከተጓዦች የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- በጉዞው ሊደረጉ ስለሚገባቸው ዝግጅቶች ከሞላ ጎደል በትኬቶች ላይ ተገልጠዋል፡፡ ሆኖም ለማስታወስና ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ማስታወስ እንወዳለን፡፡ የመጀመሪያው የጊዜ አጠቃቀማችን ሥርዓታዊ መሆን አለበት፡፡ ከአዲስ አበባ የምንነሣበት ሰዓት ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ ነው፡፡ ከዚህ የጊዜ ገደብ ቀድመንም አንነሣም ዘግይተንም አንጓዝም ስለዚህ በተቻለ መጠን ተጓዞች ሰዓት አክብረው እንዲገኙ እናሳስባለን፡፡ ሁለተኛው ማንኛውም ዐይነት ጽሑፍ ያላቸውን ቲሸርቶች ለብሶ መምጣት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተረፈ አለባበሳችን ክርስቲያናዊ መሆን አለበት፡፡ በመጨረሻም አስተባባሪዎች የሚነግሩንን እየሰማን ምንም ዐይነት መጠባበቅ ሳይኖር በተመደብንበት መኪና በተሰጠን ሰዓት መገኘት ከተጓዦቻችን ይጠበቃል፡፡

 

መካነ ድር፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት ካለፈው ዓመት ሐዊረ ሕይወት በምን ይለያል?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- የዘንድሮው ሐዊረ ሕይወት በርካታ አዲስ ነገሮችን ይዟል በእውነት ለመናገር የአሁኑ ሐዊረ ሕይወት የተደራጃና የተጠናከረ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ለመርሐ ግብሩ ስኬት ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡ ሰፊ የዝግጅት ጊዜ መኖሩ በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን ያመቻል ሌላም ባለፈው ዓመት ለመርሐ ግብሩ ሲባል ዝግጅቱ ቀደም ተብሎ ተጀምሯል፡፡  ሌላው ባለፈው ዓመት ባደረግነው ጉዞ የተሰጡን አስተየየቶች ነበሩ፡፡ እነዚያ አስተየየቶች በአሁኑ ጉዞ ተስተካክለውና ታርመው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ለምክረ አበው የሰጠነው ጊዜ ሰፊ መሆኑም በራሱ አንድ አዲስ ነገር ነው ከሁሉም በላይ የምእመናን ቁጥር በ1ሺሕ ጨምሯል፡፡ ባለፈው ዓመት 3000 የሚሆኑ ተጓዦች ነበሩ አሁን ግን የምእመናን ቁጥር በ1000 ልዩነት 4000 ይሆናል፡፡ የምዝገባው አተገባበርም ቢሆን የተሳለጠና የተመቻቸ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከጅማ፣ ከመቀሌ ከአፋርና ከናዝሬት የመጡ ተጓዦች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከእሩቅ ሀገር ለሚመጡ ምእመናን የአዳር መርሐ ግብር አዘጋጅተናል በአጠቃላይ ጉዞው እስኪጠናቀቅ ድረስ ራሱን የቻለ ጽ/ቤት፣ መደበኛ አገልጋይ፣ መኖሩ፡፡ ትምህርቶች በብሉቱዝና በሲዲ ወጪውን የሚሸፍንልን ካገኘን ለማሠራጨት መዘጋጀታቸው አዲስ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች የዚህን ዓመት ሐዊረ ሕይወት ልዩ ያደርጉታል፡፡

 

መካነ ድር፡- የመነሻ ቦታው የት ነው?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡– ከአዲስ አበባ ለሚነሡ ምእመናን 5ኪሎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ በማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ምእመናን ደግሞ ባሉበት ርእሰ ከተማ በማኅበረ ቅዱሳን ማእከላት ጽ/ቤት መነሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስ የምፈልገው ጉዳይ ከአዲስ አበባ ዙሪያ የሚመጡ ምእመናን በዋዜማው መጥተው ማደር አይጠበቅባቸውም፡፡ ከቦታው ቅርበት የተነሣ በዕለቱ ቀደም ብለው ቢነሡ መጋቢት 2 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት መድረስ ይችላሉ፡፡ ከጅማ፣ ከመቀሌ፣ ከአፋርና ራቅ ካለ ቦታ የሚመጡ ምእመናን ግን መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ.ም አዲስ አበባ መግባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለእነዚህ እንግዶቻችንም በማኅበረ ቅዱሳን ሕንፃ መኝታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

 

መካነ ድር፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እግዚአብሔር አምላክ ሥራችንን እንዲያከናውንልን ምእመናን በጸሎታቸው እንዲያስቡን ቀዳሚው መልእክቴ ነው፡፡ ሌላው መልእክት ይህ ጉዞ ለሥጋዊ ጥቅምና ለትርፍ የተዘጋጀ የጉዞ መርሐ ግብር አይደለም፡፡ 4000 ሰዎችን የሚያስጠልል ድንኳን፣ 4000 ወንበርና 4000 ሳህን ጀኔሬተርና ሞንታርቦ ከአዲስ አበባ ጭነን ነው የምንሔደው የሕክምና ቡድኖች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከእኛ ጋር ይጓዛሉ፡፡ ስለዚህ ከትራንስፓርት ውጭ ከ100,000 ብር በላይ ወጭ ይጠይቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና እና ዶግማ የጠበቁ ትምህርቶች በሲዲ ለማሠራጨትም አቅደናል እነዚህን ሁሉ ወጭዎች ለመሸፈን ማስታወቂያ በማሠራትም ይሁን በተለያየ ዘዴ ጉዞውን እንድንደግፍ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

 

መካነ ድር፡– ስለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው፡፡

 

ዲ/ን ሙሉዓለም፡- እኔም ተገቢውን መረጃ በተገቢው ሰዓት እንዳደርስ እድሉን ስለሰጣችሁን በእግዚአብሔር ስም አመሰግናለሁ፡፡

በርናባስ ረድእ /ለሕፃናት/

የካቲት 3/2004 ዓ.ም.
በቴዎድሮስ እሸቱ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ዛሬ ከ12ቱ አርድእት አንዱ ስለሆነው ስለ ቅዱስ በርናባስ ታሪክ በአጭሩ እጽፍላችኋለሁ፡፡

በርናባስ ማለት የስሙ ትርጉም ወልደ ፍስሐ የደስታ ልጅ ማለት ነው የተወለደው ቆጵሮስ በሚባል አገር ነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአረገ በኋላ ሀብት ንብረቱን በመሸጥ ለሐዋርያት ሰጥቶአቸዋል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ክርስትና ዓለም ሲጠራ ከሐዋርያት ጋር ያስተዋወቀው እርሱ ነው፡፡ ከቅዱስ ጳውሎስም ጋር በመሆን በልጥራን ያስተምሩ በነበረበት ወቅት አንድ ሕመምተኛ ፈወሱ፡፡ በዚህ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪ አማልክት በሰው አምሳል ወደ እኛ ወረዱ ኑ መስዋእት እንሠዋላቸው ብለው ላም ይጎትቱ ጀመር፡፡ እነ ቅዱስ በርናባስም እኛ እንደ እናንተ የምንምት ሰዎች ነን ተው ብለው ከለከሏቸው የዚያ ሀገር ሰዎችም ስማቸውን ቀይረው ቅዱስ በርናባስን ድያ ጳውሎስን ሄርሜን ብለው ሰይመዋቸዋል፡፡

ቅዱስ በርናባስም እንዲህ ከሀገር ሀገር እየተዘዋወረ ሲያስተምር ኖሮ ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመጎብኘት ቅዱስ ማርቆስን አስከትሎ ወደ ቆጵሮስ በመመለስ ማስተማር ጀመረ፡፡ ከቆጵሮስ በተጨማሪም ሶርያንና ዲልቅያን ጨምሮ ሲያስተምር አሕዛብ /የማያምኑ/ ጠልተው፤ ተመቅኝተው በድንጋይ በመውገር ነፍሱን ከሥጋው ከለዩ በኋላ ከእሳት ጣሉት፡፡ እሳቱ ግን ሥጋውን ሳያቃጥለው ቅዱስ ማርቆስ አንሥቶ ቀብሮታል፡፡

የገዳማውያኑ ጸሎትና አንድምታው /በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ/!!

በገብረእግዚአብሔር ኪደ

የካቲት 3/2004 ዓ.ም

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ በአባቱ ክብር ሲመጣ ለሁሉም እንደሥራው ያስረክባል” /ማቴ.16፡27/ ብሎ ሲናገር እኔም ንግግሩን ስሰማ የድል አክሊልን ከሚቀዳጁ ቅዱሳን ወገን ስላልሆንኩኝ ተብረከረክኩ፡፡ ይህን ፍርሐቴንና ጭንቀቴን ሌሎች ሰዎችም እንደሚጋሩኝ አስባለሁ፡፡ ይህን ሁሉ በልቡ እያሰበ የማይደነግጥ ማን ነው? የማይንቀጠቀጠውስ ማን ነው? ከነነዌ ሰዎች በላይ ማቅን የማይለብስና አብዝቶ የማይጾምስ ማን ነው? ምክንያቱም ይኸን ሁሉ  የምናደርገው ስለ አንዲት ከተማ መገለባበጥ ተጨንቀን ሳይሆን ዘለዓለማዊውን ቅጣትና ትሉ የማያንቀላፋ እሳቱም የማይጠፋውን ነበልባል ለማለፍ ነው፡፡

በየበረሀውና በየገዳማቱ የሚኖሩት አበው ወእማት ይኸንን ቃል ከሌላው ሰው በበለጠ አኳኋን ስለ ገባቸው እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ፤ አደንቃቸውማለሁ፡፡ ምክንያቱም እራታቸውን ከቀማመሱ በኋላ፣ እንደውም እራታቸውን ሳይሆን ምሳቸውን ከተመገቡ በኋላ (ምክንያቱም አብዝተው የሚጾሙና የሚያዝኑ ስለሆነ እራት የሚባል ነገር አያውቁም በዜማ አምላካቸውን ያመሰግኑና መዝሙር ይዘምራሉ፡፡ እናንተም መዝሙሩን መስማት ከፈለጋችሁ ላስታውሳችሁ እና ደጋግማችሁ ዘምሩት፡፡ መዝሙሩ እንዲህ ይላል፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን፣ ሥጋ ለባሽን ሁሉ የምትመግብ ቡሩክ እግዚአብሔር ሆይ! መልካሙ ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን፡፡ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ይገባኻል! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህም የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ የተመላን አድርገን፡፡”

ይህ ዝማሬ በተለይም የመጨረሻው ስንኝ አንክሮ የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም መብል በባሕርይው የድካምና የመወፈር ስሜትን የሚያመጣ ቢሆንም በመነኰሳቱ ዘንድ ግን በነፍስ ላይ ሲያበራና ነገረ ምጽአትን ሲያሳስብ እንመለከተዋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች እስራኤል ሰማያዊው መና ከተመገቡ በኋላ ምን እንዳገኛቸው ተምረዋል፡፡ እንዲህ እንደተባለ፡- “የተወደደውን ጥጋብ አቀናጣው፤ ሰባ፤ ወፈረ፤ ሰፋ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ ዳግመኛም ሙሴ፡- “በበላህና በጠገብህም ጊዜ… እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ” እንዲል /ዘዳ.6፡11-12/፡፡

እስኤላውያን የተወደደውን ምግብ ከበሉ በኋላ አሳፋሪ ነገርን ለማድረግ ጀመሩ፡፡

እናንተስ ይኼን የመሰለ ነገር በእናንተ ዘንድ እንዳይሆን ትገነዘባላችሁን? ምንም እንኳን ለድንጋይ፣ ወይም ለወርቅ ምስል በግ ወይም ከብት ባትሠዉም የራሳችሁን ነፍስ ስለሠዋችሁ መዳናችሁን እንዴት እንደምታጥዋት እና እንዴት ያለ ቁጣ እንደሚደርስባችሁ ተመልከቱ፡፡ እነዚህን መነኰሳት ስንመለከት ይኼን የመሰለ ውድቀት በእነርሱ እንዳይደርስ በመፍራት ምግባቸውን ከተመገቡ በኋላና በጊዜ ጾማቸው መካከል ሁሉ ስለዚያች አስፈሪ ቀን እና ስለ አስጨናቂው የፍርድ ወንበር ያስባሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ መነኰሳት እንኳን በጾም ሌሊቱን ሁሉ በመሬት ላይ ተኝተው እንቅልፍን በማጣት በንቃትና ማቅን በመልበስ እልፍ ጊዜ እየደጋገሙ ስለዚያች ቀን በማሰብ የሚተጉ ከሆነ የምግብ ክምር በጠረጴዛችን ላይ ከምረን ስንጀምርም ስንጨርስም የማንጸልይ ትሩፋተ ሥጋ ትሩፋተ ነፍስ የሌለን እኛስ ይኼን የምናደርገው መቼ ይሆን?

ስለዚህ ምግበ ሥጋ ብቻ በምግብ ጠረጴዛች እንዳንከምር ይኼን የመሰለ ጣዕመ ዝማሬ እና ትርጕሙን እንናገር፡፡ ከዚያ በኋላ ጥቅሙን እየተመለከትን በማዕዳችን ዙርያ እንድናመሰግን እና ለሆድ ብቻ ብለን የምናደርገውን ሩጫ በማስወገድ የመላእክትን ሥርዓት ወደ ቤታችን እናስገባ፡፡ ከመብላታችሁ በኋላ መልካም እንዲሆንላችሁ ይኸን ታደርጉ ዘንድ ይገባችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ብያንስ እንኳን ለምነግራችሁ ቃል ፈቃደኞች ስላልሆናችሁ ይኸንን ጣዕመ ዝማሬ አድምጡና ከዛሬ ጀምራችሁ ከማዕዳችሁ በፊትም ይሁን በኋላ ምስጋናን ተለማመዱ፡፡
“ብሩክ እግዚአብሔር ሆይ!” ነው ያሉት፡፡ እነዚህ መነኰሳት የሐዋርያትን ትእዛዝ ሲፈጽሙ እንመለከታቸዋለን፡፡ ሐዋርያት እንዲህ ብለው ነበርና፡- “እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት” /ቈላ.3፡17/፡፡

ሲቀጥሉ ደግሞ የእግዚአብሔር መግቦት ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለሁል ጊዜ እንደሆነ ሲናገሩ፡- “ከታናሽነታችን ጀምረህ የምትመግበን” ነው ያሉት፡፡ ይኼን ትእዛዝ ደግሞ፡- “እግዚአብሔር ምግባችሁን ይሰጣችኋልና አትጨነቁ” ማለት ነው፡፡ እናንተ ከአንድ ንጉሥ ጋር እየኖራችሁ ንጉሡ ምግባችሁን ሁሉ ከግምጃ ቤት እያወጣ የሚሰጣችሁ ከሆነ በጭራሽ ስለምትበሉት ነገር አታስቡም፤ ምግብ እንደሚሰጣችሁ ተስፋችሁን ሁሉ በንጉሡ ላይ ጥላችሁታልና፡፡ እንግዲያስ ከዝናብም በላይ በእናንተ ላይ እነዚህን ነገሮች ሊያዘንም የሚችለውን እግዚአብሔር በበለጠ አኳኋን ተስፋ እያደረጋችሁ ስለ አንዳች ነገር ልትጨናነቁ አይገባችሁም፡፡ አዎ! እነዚህ መነኰሳት ራሳቸውንና በእግራቸው ለሚተኩት ደቀመዛሙርቶቻቸው ያስተምሩ ዘንድ ይኼን መዝሙር ደጋግመው ይዘምራሉ፡፡

ከዚህ በኋላ እነዚህ መነኰሳት ለራሳቸው ብቻ ያመሰግናሉ እንዳይባል፡- “ሥጋ ለባሽንም ሁሉ የምትመግብ” ይላሉ፡፡ ስለዚህ በዓለም ሕዝብ ፈንታ እነርሱ ያመሰግናሉ፤ እንደ ዓለም ሁሉ አባቶች እግዚአብሔርን ይባርካሉ፤ ጽኑ ፍቅረ ቢጽን /የወንድም ፍቅርን/ ይለማመዳሉ፡፡ ወንድሞቻቸውን እግዚአብሔር ስለመገበላቸው ያመሰግናሉ እንጂ አይጠሉም፡፡

እንግዲህ በቀደሙትና በእነዚህ የምስጋናቸው ቃል እንዴት አመስጋኝነትን፣ እንደገለጹና ዓለማዊ ምቾትን እንዳራቁ ተመለከታችሁን? እግዚአብሔር ሥጋ ለባሹን ሁሉ የሚመግብ አምላክ ከሆነ የሚያመሰግኑትን ደግሞ የበለጠ ይመግባቸዋል፤ በዓለም ኑሮ ለተወጠሩት እንኳን የሚመግብ ከሆነ ከዓለማዊ ምኞት ራሳቸውን ላራቁ ደግሞ ይበልጥ ይመግባቸዋል፡፡

ይኼን ግልጽ ያደርግ ዘንድ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “ከብዙ ድንቢጦች እናንተ አትበልጡምን?” /ሉቃ.12፡7/፡፡ በዚህም እምነታችንን በሀብትና በምድር ፍሬ እንዳንጥል አስጠንቅቆናል፡፡ ምክንያቱም ምግባችንን የሚሰጡን እነዚህ ሳይሆኑ እግዚአብሔር ነውና /ዘዳ.8፡3፣ ማቴ.4፡4/፡፡…

ተሐራምያኑ ልመናቸውን ይቀጥሉና አምላካቸውን፡- “ልባችንን በደስታና በሐሴት ሙላልን” ይሉታል፡፡ ይህን ማለታቸውስ ምን ማለት ነው? በዚህ ዓለም ደስታ ይሆን? በፍጹም! ይኸን የለመኑ ቢሆን ኖሮ ራሳቸውን በየፍርኩታው፣ በየገደሉ፣ በየበረኻው ማቅ ለብሰው ባልተመላለሱ ነበር፡፡ ስለዚህ እየለመኑት ያለው ደስታና ሐሴት ከዚህች ዓለም ደስታ ጋር ምንም ዓይነት ኅብረት የሌለው ይልቁንም የመላእክትን ሐሴት የሆነውና ሰማያዊውን ደስታ ነው፡፡

አጠያየቃቸውን እንኳን ተመልክተን ከሆነ ቀለል ባለ አገላለጽ “ስጠን” ሳይሆን “ሙላልን”፤ “እኛን” ሳይሆን “ልባችንን” ነው የሚሉት፡፡ የልብ ሐሴት ማለት የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑት ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም የመሳሰሉ ናቸውና /ገላ.5፡22/፡፡

ስለዚህ ኀጢአት ሐዘንን ስለምታመጣ ያለዚህም ደስታ ስለማይገኝ በዚሁ ደስታ አማካኝነት ጽድቅን እየለመኑ ነው ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው፡- “እግዚአብሔር ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጐ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” ይላል /2ቆሮ.9፡8/፡፡ እነዚህ መነኰሳት በዚህች አጭር ምስጋናቸው “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” የሚለውን የወንጌሉን ቃል እንደ ተገበሩትና እነዚህን ሁሉ ለመንፈስ ፍሬ እንዴት እንደ ፈለጓቸው ተመልከቱ፡፡ ምክንያቱም፡- “በጐው ሥራችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ ልብ በሉ! “ሥራችንን እንፈጽም ዘንድ፣ በጐ ምግባርን እንሠራ ዘንድ” ብቻ ሳይሆን “ይበዛልን ዘንድ” ነው እያሉ ያሉት፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ዘንድ ትንሽዋን ፈቃድ ሲፈልግብን እነዚህ መነኰሳት ግን ከዚህም በላይ የሆነ መታዘዝን ነው ያሳያት፡፡ ይህ አባባል የመልካም ባሮች እና ራሳቸውን የሚገዙ የጠንቃቃ ሰዎች መገለጫ ነው፡፡

በመቀጠል ይኸን መልካም ሥራ የሚሠሩት በራሳቸው አቅም እንዳልሆነ እና ደካማነታቸውን ለመግለጽ፡- “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከርሱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ገር ክብርና ጌትነት ለአንተ ይሁን አሜን” ይላሉ፡፡ በምስጋና የጀመሩት ልመናቸው በምስጋና ያሳርጉታል፡፡

ከዚህ በኋላ አዲስ ምስጋና የጀመሩ ቢመስሉም ያንኑ ምስጋናቸውን ተከትሎ የሚመጣ ተጨማሪ ሐሳብ ይቀጥላሉ፡፡ ይኼም ቅዱስ ጳውሎስ መልእክቶቹን ሲጀምር፡- “እንደ አባታችንና እንደ አምላካችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ፡፡ ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን አሜን” ገላ.4፥5 ብሎ በምስጋና ጀምሮ ተመልሶ ወደ መጀመርያው ሐሳብ እንደሚመለስ የመሰለ ነው፡፡ በሌላ ቦታም ቅዱስ ጳውሎስ ፡- “በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን” ሲል ቃሉን ፈሞ ሳይሆን እንደገና እንደጀመረ /ሮሜ.1፡25/፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን መነኰሳት ጸሎታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደገና ጀመሩ ብለን የምንወቅሳቸው አይደለንም፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያቱ በምስጋና ጀምረው በምስጋና ጨርሰው ዳግመኛ መልእክታቸውን እንደሚቀጥሉ ሁሉ እነዚህ መነኰሳትም ይኼን በመሰለ መንገድ ምስጋናቸውን ይጀምራሉ፡፡

ስለዚህ፡- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ንጉሥ እገዚአብሔር ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! ደስ ታሰኘን ዘንድ ምግባችንን ሰጥተኸናልና” ይላሉ፡፡

ምስጋናን ማቅረብ ያለብን ስለ ትልልቅ ጉዳዮቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ጥቃቅኑም ጭምር መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መነኰሳት የተባሕትዎን ኑሮ የሚንቁትን ሁሉ ያሳፍሩ ዘንድ ስለ ጥቃቅኑም ጭምር ያመሰግናሉ፡፡ እነዚህ መነኰሳት መናፍቃን እንደሚያወሩት  ማለትም የእግዚአብሔርን ፍጥረት ከመጥላት ወይም ጋብቻን ከማንቋሸሽ አንጻር ሳይሆን ቁጥብነትን፣ ራስን መግዛት ይለማመዱ ዘንድ ይኼን ያደርጋሉ፡፡

ምስጋናቸው ደግሞ እግዚአብሔር ከዚህ አስቀድሞ በሰጣቸው ሁሉ የተገደበ ሳይሆን ፡- “በመንፈስ ቅዱስ ሙላን” እያሉ ወደ ሰማያዊ መሻት እንደሚወጡና ያንን ሕይወት እንደሚናፍቁ ልብ በሉ፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔር ካልረዳው በስተቀር ማንም ሰው ታላለቅ ሥራዎችን መሥራት አይችልም፤ ቢሠራ እንኳን ታላላቅ መሆን ያለባቸውን ያህል ታላላቅ አይሆኑም፡፡

ስለዚህ፡-“ በጐ ሥራችን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይበዛልን ዘንድ” እንዳሉ ሁሉ አሁንም “በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ በቅዱስ መንፈስህ ሙላን” ይላሉ፡፡

እንግዲህ ስለአሁኑ ዓለም ኑሮዋቸው ጸሎት ሳይሆን ምስጋናን ብቻ እንዳቀረቡና ከመንፈስ ቅዱስ ለሚሆነው ነገር ግን ጸሎትም ምስጋናም እንዳቀረቡ ተገነዘባችሁን? ጌታም ያስተማረው ይኼንኑ ነበር፡- “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፤ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” እንዲል /ማቴ.6፡33/፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በእነዚህ መነኰሳት ዘንድ ያለውን ከፍተኛ መልካምነት ልብ በሉ፡፡ ምክንያቱም ሲጸልዩ፡- “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ስትከፍለው እንዳናፍርና በፊትህ የተገባን ሆነን እንገኝ ዘንድ” ነው የሚሉት፡፡ እንዲህ ማለታቸውም ነበር፡- “በብዙዎች ዘንድ የሚደርስብን ማንኛውም የሚያሳፍር ነገር አያስጨንቀንም፤ ሰዎች በእኛ ላይ የወደዱትን ሁሉ ቢናገሩ፣ ቢስቁብን፣ ቢታበይቡን ለእኛ ቁብም አይሰጠንም፡፡ የእኛ ጭንቀትና ናፍቆት በፊትህ የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ ብቻ ነው፡፡” በዚሁ ጸሎታቸውም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ደግሞም መንግሥቱን ለሚያወርሳቸው ያዘጋጀውን መልካሙን ሁሉ እና የእሳቱን ባሕር በሚገባ አስቀምጠውታል፡፡

ሲጸልዩም፡- “እንዳንቀጣ” ሳይሆን “በአንተ ፊት የምናፍር ሆነን እንዳንገኝ” ነው ያሉት፡፡ ይኸውም እኛ ሁላችን ከገሃነም አስፈሪነት ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት መቆምን እንድንፈራ ሲያስተምሩን ነው፡፡

ታድያ እነዚህ መጻተኞች፣ ስደተኞች፣ የበረሀው ከዚያም በላይ ደግሞ የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች የሆኑት እነዚህ መነኰሳት ምን ያህል እንደጠቀሙን ተመለከታችሁን? እኛ በዚህ ምድር ሐሳብ ስንፏቀቅ እነርሱ ግን በተቃራኒው ከዚህ ዓለም ተቃራኒ በመቆም የመንግሥተ ሰማያት ዜጐች ሆነዋል፡፡

ዝማሬአቸውን ከጨረሱ በኋላ ስለ ኃጢአታቸው በማዘንና በማያቋርጥ የእንባ ጅረት ካለቀሱ በኋላ ለቀጣዩ ቀን ራሳቸውን እንደ አዲስ ይዘጋጁ ዘንድ ትንሽ ዕረፍት ይወስዳሉ፡፡ እንደገና ተነሥተውም ሲያመሰግኑ ደግሞም መዝሙረ ዳዊታቸውን እየደገሙ ሌሊትን ቀን ያደርጉታል፡፡
የሚደንቀው ነገር ደግሞ ወንዶች ብቻ ሳይሆኑ የተፈጥሮ ደካማነታቸውን በትጋት በማሸነፍ ይኼን ራስን የመካድ ኑሮ የሚፈጽሙት ሴት መነኰሳየያትም ናቸው፡፡

እንግዲያስ እኛም ወንዶች ስንሆን የእነዚህን ሴት መነኰሳይያትን ትጋት እየተመለከትን በራሳችን የምናፍር እንሁን፡፡ እንደ ጥላ ከሚያልፉት፣ እንደ ሕልም ከሚረሱትና እንደ ጢስ ከሚተጉት ከዚህኛው ዓለም ጉዳዮች ጋር እንታሠር፡፡ ብዙዎቻችን በዚሁ ድንዛዜ ተይዘን ዕድሜአችን ያልቃልና፡፡

የአብዛኞቻችን የዕድሜአችን የመጀመርያው አጋማሽ በዚሁ ስንፍና የተሞሉ ናቸው፡፡ ወደ ሁለተኛው የዕድሜአችን አጋማሽ ከገባን በኋላም ትንሽ ደስታን አጣጥመን መልሰን በርኩሰት፣ በድካምና በሌሎች የማይረቡ ነገሮችን እንታነቃለን፡፡

ስለዚህ ሌባ የማይሰርቃቸውንና ዘላለማውያን የሆኑትን /የማያልፉትን/ ሀብታት እንዲሁም ማርጀት (ሽምግልና) የሌለበትን ሕይወት ትሹ ዘንድ እማልዳችኋለሁ፡፡

አንድ ሰው በከተማ ውስጥ ሆኖም እንደ እነዚህ መነኰሳት ራስን መግዛት መለማመድ ይችላል፡፡ አዎ! ሚስት አግብቶ፣ በቤትና በኑሮ ጉዳዮች የተጠመደ ሰው እንኳን መጸለይ፣ መጾምና ስለ ኃጢአቱ ማልቀስ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ከሐዋርያት የተማሩትም ምንም እንኳ በከተማ ቢኖሩ በበረሃ የሚኖሩትን ሰዎች ንጽሕናና ቅድስና ይዘው ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ እንደ አቂላና ጵርስቅላ ብዙ ሠራተኞች የነበሯቸውም እንዲሁ አድርገዋል፡፡

ነቢያቱም እንዲሁ ሚስትና ቤት ነበራቸው እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ሊቀ ነቢያት ሙሴ፡፡ እነርሱ ከበጎ ምግባርና ትሩፋት የተነሣ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡

እንግዲያስ እኛም እነዚህን ሁሉ እየመሰልናቸው እግዚአብሔርን ያለማቋረጥ እናመስግን፤ በጊዜውም ያለጊዜውም በመዝሙር እንቀኝለት፤ ትዕግሥትንና መልካም ምግባርን ሁሉ ገንዘብ እናድርግ፡፡ በገዳማውያኑ የተለመደውን ራስን የመግዛት የሕይወት ልምምድ ወደ ምንኖርበት የከተማ ሕይወት በማምጣት በእግዚአብሔር ፊት የተገባን ሆነን እንገኝ፡፡ ብርሃናችንም በሰው ፊት ይብራ፡፡ ሊመጣ ያለውን በጎ ስጦታ ሁሉ እንውረስ፡፡

ይህንን ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱና ሰውን በመውደዱ ያድለን፡፡ ምስጋና ክብርና ለእርሱ በእርሱ ለአብ ሕይወትን ከሚሰጥ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን!!!

የድርሳንና የገድል ልዩነት ምንድን ነው?

ጥር 30/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ጊዜ ድርሳንና ገድል ሲባል እሰማለሁ፡፡ እኔም የድርሳንና የገድል ልዩነት ብዙ ጊዜ አይገባኝም፤ እባካችሁ የድርሳንና የገድልን አንድነትና ልዩነት አስረዱኝ”

ገብረ እግዚአብሔር
ከዲላ

ውድ ጠያቂያችን በእርግጥ እርስዎ እንዳሉት ድርሳንና ገድል በቤተ ክርስቲያን የማይነሡበት ጊዜ የለም፡፡ “የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው” ዕብ.13፥7 እንደተባለው በሃይማኖትና በምግባር ለመጠንከር ገድለ ቅዱሳንን የያዙ መጻሕፍትን እናነባለን፤ እንጸልይባቸዋለን፡፡ የቅዱሳን መላእክትንም ጠባቂነት፣ የሊቃውንትን ተግሣጽ ትርጓሜና ምክር የዕለተ ሰንበትን ክብር እና የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነት ሥራ የሚናገሩ ድርሳናትን ሁል ጊዜ እናነባለን እናደርሳለን፡፡

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለው መጽሐፋቸው “ድርሳን” የሚለውን ቃል እንዲህ ብለው ይፈቱታል “ድርሳን በቁሙ “የተደረሰ፣ የተጣፈ፣ ቃለ ነገር፣ ሰፊ ንባብ፣ ረዥም ስብከት፣ ትርጓሜ፣ አፈታት፣ ጉሥዐተ ልብ፣ መዝሙር፣ ምሥጢሩ የሚያጠግብ፣ ቃሉ የተሳካ፣ ጣዕመ ቃሉና ኃይለ ቃሉ ደስ የሚያሰኝ ልብ የሚነካ” ማለት ነው፡፡

ድርሳን ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ተራዳኢነት ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ክብርና ጸጋ፣ ስለ ዕለተ ሰንበት ክብርና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚናገሩ /የሚያትቱ/ መጻሕፍት ማለታችን ነው፡፡

እስከ 2000 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ወደ 138 የሚሆኑ በድርሳን ስያሜ የሚጠሩ መጻሕፍት እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 11ዱ የመላእክት ድርሳናት ሲሆኑ  የ11ዱ መላእክት ስምም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቅዱስ ሩፋኤል፣ ቅዱስ ራጉኤል፣ ቅዱስ ዑራኤል፣ ቅዱስ አፍኒን፣ ቅዱስ ፋኑኤል፣ ቅዱስ ሳቁኤል፣ ቅዱስ ሱርያል፣ ቅዱስ ሱራፌልና ቅዱስ ኪሩቤል ናቸው፡፡

የመላእክትድርሳናት በአብዛኛው ተመሳሳይነት ባሕርይ አላቸው፡፡ የውስጥ ይዞታቸውም በ5 ይከፈላል፡፡ እነሱም መቅድም፣ ድርሳን፣ ተአምራት፣ አርኬና መልክእ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ድርሳን የምንለው የባለ ድርሳኑን መልአክ ግብር በፈጣሪው ዘንድ ያለውን ሞገስ የሠራቸውን ተአምራት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እያጣቀሰ የሚያብራራ ክፍል ነው፡፡ በአጠቃላይ ድርሳንን በ4 መክፈል ይቻላል፡፡

  1. ድርሳነ መላእክት የሚባለው ድርሳነ ሚካኤል ድርሳነ ገብርኤልን የመሳሰሉትን ነው፡፡
  2. ድርሳነ ሰንበት ስለ ዕለተ ሰንበት ክብር የሚያብራራ መጽሐፍ ድርሳነ መስቀል ደግሞ የመስቀሉን ታሪክና አመጣጥ ይተርካል፡፡
  3. ድርሳነ ሊቃውንት ደግሞ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን የሚባለው ነው፡፡ ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ድርሳን ዘቅዱስ ቄርሎስንም ያጠቃልላል፡፡
  4. ድርሳነ ማኅየዊና ድርሳነ መድኀኔ ዓለም የመሳሰሉት ድርሳናት የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያዘክሩ ድርሳናት ናቸው፡፡

 

ገድል፡- “በቁሙ ትግል ፈተና ውጊያ ሰልፍ ድልና አክሊል እስ    ኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም የሚሠሩት ሥራ የሚቀበሉት መከራ ማለት ነው” ሲሉ ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት ፍቺያቸው አስቀምጠውታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ገድል ማለት ጻድቃንና ሰማዕታት በሕይወት ዘመናቸው እያሉ የሠሩትን ሥራ የሚናገር መጽሐፍ እንደሆነ አብራርተዋል /ደስታ ተክለ ወልድ 2036፣ አለቃ ኪዳለ ወልድ ክፍሌ 301/ የገድል መጻሕፍት ጻድቃን፣ ሰማዕታት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትእዛዘ እግዚአብሔር እንዲከበር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ከአላውያን ነገሥታት፣ ከቢጽ ሐሳውያን፣ ከጠላት ዲያብሎስና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያወሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸው በኑሮአቸው እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳዩን የሕይወታቸው መስተዋቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ገድል ስንል የቅዱሳን ታሪክ፣ ተአምራት፣ ቃል ኪዳንና መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ይህ እንዲህ ይሆናል ይቻላል ተብሎ የተነገረው ቃል በእውነት የሚኖር በቃልና በሥራም የሚገለጥ እንደሆነ የምናየው በቅዱሳን ገድል ነው፡፡ /ማቴ.10፥37፣ ሉቃ.14፥27፣ 1ቆሮ.11፥26-28/

ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው /2ቆሮ.11፥23-22 ዕብ.11፥32-40/ ራሱ የሐዋርያት ሥራ የምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያትን ግብር /ሥራ/ ገድልና ዜና የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳንም መጽሐፈ ጦቢት መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ሶስና፣ የመሳሰሉት በሰዎቹ ኑሮ የተገለጠውን የእምነታቸውን ፍሬ የሚያሳዩ የገድል መጻሕፍት ናቸው፡፡

ገድላት በ3 ይከፍላሉ እነሱም፡-

  1. ገድለ ሰማዕታት፡- ለምሳሌ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ገድለ ፋሲለደስ፣ ገድለ ኢየሉጣ
  2. ገድለ ሐዋርያት፡- በአንድነት የተሰበሰቡ የሐዋርያት አገልግሎት ተአምራት መከራ የያዙ መጽሐፍት
  3. ገድለ ጻድቃን፡- ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስና የመሳሰሉትን ነው፡፡

ውድ ጠያቂያችን ምላሹን ለማጠቃለል ድርሳን ሲባል የመላእክትን ግብር በፈጣሪያቸው ዘንድ ያላቸውን ሞገስና የሠሯቸውን ገቢረ ተአምራት እየዘረዘሩ የሚናገሩ፣ ስለ ዕለተ ሰንበትና ቅዱስ መስቀል ክብር የሚያስረዱ ድርሳነ ሰንበትንና የድርሳነ መስቀል፣ የመጻሕፍት ትርጓሜ ምክርና ተግሣጽ እንዲሁም ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት የመሰከሩበት የሊቃውንት መጻሕፍት፣ በመጨረሻም የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያስታውሱ እንደእነ ድርሳነ ማኅየዊ ያሉት መጻሕፍት በድርሳን ሥር ይጠቃለላሉ፡፡

ገድል ደግሞ ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ጥበብ የቅዱሳንን መከራ ተጋድሎ፣ ተአምራትና ቃል ኪዳን የያዙ የቤተ ክርስቲያን ሕያውነት የሚገለጥባቸው መጻሕፍትናቸው፡፡ ድርሳናትም ሆኑ ገድላት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የማይጋጩ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያብራሩ የሚተረጉሙና የሚተነትኑ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሰፋ የለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ሐመረ ተዋሕዶ 1999፥61፣ ሐመር ጥር/የካቲት 2000፥27 አዋልድ መጻሕፍት ማኅበረ ቅዱሳን፣ ሜጋ ማተሚያ ቤት 1995፣ የኢዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትናንት ዛሬና ነገ፣ ብራና ማተሚያ ቤት፣ ማኅበረ ቅዱሳን፣ 1995፥16 የሚሉ መጻሕፍትና መጽሔቶችን ቢያነኳቸው መልካም ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በመላእክት ተራዳኢነት በቅዱሳን ጸሎት ሁላችንንም ይጠብቀን፡፡

ራስን የመግዛት ጥበብ


ጥር 29/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆ “ፍልስፍና ማለት ጥበብን ማፍቀር ማለት ነው፤ ጥበብ ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህም ፍልስፍና ማለት እግዚአብሔርን ማፍቀር ማለት ነው”ብሎ ያስተምራል፡፡ እኛም በበኩላችን እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ሰውም በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ስለሆነ ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ እንላለን፡፡ አንድ ጸሐፊ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር፡- “እግዚአብሔር ሰውን ከፍቅር አፈር አበጀው፡፡ ስለዚህም ሰው ፍቅር የሚገዛው ፍጥረት ሆነ፤ ስለዚህም ሰው ፍቅር ሲያጣ እንደ በድን ሬሳ ሲቆጠር በፍቅር ውስጥ ካለ ሕያው ነው፡፡ ሕይወቱም እግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔርም ፍቅር ነው፡፡” ስለዚህም ክርስቲያናዊ ፍልስፍና ፍቅርን መሠረት ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ለፍልስፍና ትምህርታችን መንደርደሪያ የሚሆነን ፍቅር የሆነውን ተፈጥሮአችንን በሚገባ ማወቃችንና መረዳታችን ነው፡፡

ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረውን ሰውን ትንሹ ዓለም ይለዋል፡፡ እንዲህም ያለበት ምክንያት ሰማያዊና ምድራዊ ተፈጥሮ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ ረቂቅ በሆነችው የነፍስ ተፈጥሮው በኩል ረቂቃን ከሆኑ መናፍስት ጋር አኗኗሩን ሲያደርግ፤ ግዙፍ በሆነችው ሥጋዊ ተፈጥሮው በኩል ደግሞ በምድር ፍጥረታት ላይ ገዢ ሆኖ ጠቅሟቸውም ተጠቅሞባቸውም ይኖራል፡፡ ስለዚህም ነው ሰው በሁለት ዓለማት እኩል የሚኖር ፍጥረት ነው መባሉ፡፡ ወይም ሰው የሁለት አካላት ውሕደት ውጤት ነው፡፡ ነፍስ የራሱዋ የሆነ አካል ያላት ስትሆን በዚህ ተፈጥሮዋ መላእክትን ትመስላቸዋለች፣ እንደ ምግባሩዋ ከቅዱሳን ወይም ከርኩሳን መናፍስት ጋር ኅብረትን ትፈጥራለች፡፡ በነፍስ ሕያው ሆና የምትኖር ሥጋችንም ከዚህ ዓለም ጋር ተመጋግባና ተግባብታ ለመኖር የሚረዳት የራሱዋ የሆነ አካላዊ ተፈጥሮ ያላት ናት፡፡ መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ለመንፈሳዊያንና(በእርሱ ዘንድ ረቂቃን አይደሉም) ለምድራዊያን ፍጥረታት ሕይወትን ሰጥቶ እንደሚያኖራቸው እንዲሁ ነፍስም ለሥጋ ሕይወትን ሰጥታ ታኖራታለች፡፡ በዚህም ተፈጥሮአችን አምላክን እንመስለዋለን፡፡ “ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ የራሱን መልክ እንዲሥል እንዲሁ እግዚአብሔር ነፍስና ሥጋን በማዋሐድ የራሱን መልክ በመሳል ሰው አድርጎ ፈጠረው፡፡”(ቅዱስ ኤፍሬም)

 

ነፍስ ከሥጋ ተፈጥሮአዋ ሳትለይ ከመንፈሳዊያን ፍጥረታት ጋር ኅብረትን መፍጠር ይቻላታል፡፡ ሥጋም ከነፍስ ሳትለይ ነፍስ ሕይወት ሆኗት ለራሷ ሕልውና ጠቃሚ የሆኑትን ተግባራት በምድር ላይ ታከናውናለች፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ አድርጎ ሰውን ከፈጠረው በኋላ የሕይወት እስትንፋስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን በአፍንጫው እፍ አለበት፡፡ (አክሲማሮስ ገጽ.156) መንፈስ ቅዱስም ለነፍሳችን እውነተኛ እውቀትን በመግለጥ፤ ነፍስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሥጋዋን እንድትመራት ይረዳታል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዲህ አድርጎ ፈጠረው፡፡ ስለዚህም ሰው ማለት ሥጋው ለነፍሱ፣ ነፍሱም ለመንፈስ ቅዱስ የሚገዙለት ፍጥረት ማለት ነው፡፡

 

አንድ ሰው ይልቁኑ አንድ ክርስቲያን ይህ ሰብአዊ ተዋቅሮውን ካወቀ እግዚአብሔር እርሱን ለምን ዓላማ እንደፈጠረው ይረዳል፡፡ ስለዚህም ነው የትምህርት መጀመሪያው ራስን ማወቅ ነው ብለው ቅዱሳን አባቶች ማስተማራቸው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም “ማንነትህን የማታውቅ ከሆነ የፈጣሪህን ቃል መስማት እንዴት ይቻልሃል?”ሲል፣ ቅዱስ ባሲልዮስ ዘቂሳርያ ደግሞ “ከትምህርቶች ሁሉ የሚልቀው ትምህርት ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ከአወቀ እግዚአብሔርን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ከአወቀ ደግሞ እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል” ብሎ ያስተማረው፡፡ ራስን ማወቅ የመንፈሳዊ ሕይወታችን መሠረት ነው፡፡

 

ቅዱሳን አባቶቻችን ራስን የማወቅ ጥበብን በሦስት የእውቀት እርከኖች ከፋፍለው ያስቀምጡታል፡፡ የመጀመሪያው እርከን ማንነትን መረዳት ነው፡፡ ይህ እርከን ተፈጥሮአዊ መዋቅርን የመረዳት እርከን (carnal stage) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ያም ማለት የራስን ተፈጥሮዊ ጠባይ ማወቅ ማለት ነው፡፡ ሰው ራሱን ካወቀ ራሱን ለመግዛትና እንደ ፈጠሪው ፈቃድ ለመመላለስ መሠረት ይጥላል፡፡ ራሳችንን ካወቅን በኋላ የሚቀጥለው የእውቀት እርከን መንፈሳዊያኑንና ምድራዊያኑን የስሜት ሕዋሳቶቻችንን ተጠቅመን አካባቢያችንን መረዳት ነው፡፡ በዚህ እርከን ውስጥ ስንገኝ በዙሪያችን ያሉትን ረቂቃን መናፍስትንና ግዙፋን ፍጥረታትን ወደ መረዳትና ከእነርሱ ጋር ግንኙትን ወደ መጀመር እንመጣለን፡፡ ይህም የለብዎ እርከን(sensual stage) ይባላል፡፡  ሦስተኛውና የመጨረሻው እርከን መንፈሳዊያን ሆነን የምንመላለስበት እርከን ሲሆን መንፈሳዊ እርከን ተብሎ ይታወቃል (spiritual stage)፡፡ ይህ የቅዱሳን መላእክትንና የአጋንንትን ንግግር የምንለይበትና በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የምንመላለስበት የእውቀት ወይም የቅድስና እርከን ነው፡፡ ይህን እርከን ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል ራሱ ግን በማንም አይመረመርም፡፡ እንዲያስተምረው የጌታን ልብ ማን አውቆት ነው እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን”በማለት ይተነትነዋል፡፡(1ቆሮ.2፡15-16)

 

አንድ ሰው መንፈሳዊ ነው የምንለውም እነዚህ የእውቀት እርከኖችን አልፎ የመንፈስ ቅዱስን መልእክት ማዳመጥና መለየት ወደሚችልበት እርከን ሲሸጋገር ነው፡፡ ይህን ለማስረዳት ቅዱሳን “በክርስቶስ ያመነ አንድ ሰው አውቃለሁ፤ ዘመኑ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት ነው፤ ነገር ግን በሥጋው ይሁን በነፍሱ እንጃ፤ እግዚአብሔር ያውቃል ያ ሰው እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ነጥቀው ወሰዱት” (2ቆሮ.12፡2) ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ይጠቀማሉ፡፡ እንደ ቅዱሳኑ አስተምህሮ ሦስቱ ሰማያት የተባሉት ቅዱሱ ያለፈባፋቸውን ሁለቱን የእውቀት እርከኖችንና በስተመጨረሻ የደረሰበትን የእርሱን የእውቀት ከፍታን ነው፡፡ በዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ የሚገኝ ቅዱስ በዚህ ምድር ሳለ የትንሣኤን ሕይወት ጣዕም መቅመስ ይጀምራል፡፡ ይህም ማለት  ከአምላክ ጋር፣ ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር ለመነጋገር የበቃ ይሆናል፣ የአጋንንትንም ምክርና አሳብ ይለያል፣ በሰው ልቡና የሚመላለሰውን ክፉም ይሁን በጎ አሳብ ማወቅና መረዳት ይችላል፣ መጪውን ያውቃል፡፡ እነኝህን ሁሉ ግን የምናገኘው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ነው፡፡

 

ነፍስ ለሥጋ ብርሃኗ እንደሆነች ለነፍስም ብርሃኗ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ረቂቁንና መንፈሳዊውን ዓለም መረዳት አይቻለንም፡፡ በዚህም ላይ ጨምረን ነፍሳችንን ከኃጢአት ንጹሕ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ ያለበለዚያ እውር ድንብራቸውን እንደሚመላለሱ ወገኖች እንሆናለን፡፡ ይህን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው” ብሎ ይገልጸዋል፡፡ (ዮሐ.5፥25) ወንድሜ ሆይ በዚህ ቦታ ሙታን ያላቸው ነፍሳቸው የተለየቻቸውንና ወደ መቃብር የወረዱትን ወገኖችን ነውን ? ስለሰማያዊው አኗኗራቸው ፈጽመው የማያቁትን አይደለምን ? ይህ ኃይለ ቃል ምን አልባት ግልጽ ላይሆን ይችላል፤ በማቴዎስ ወንጌል ላይ ጌታችን እርሱን ለሚከተል ደቀመዝሙር የተናገረውን እስቲ እናስተውለው፤ “ኢየሱስም፡- ተከተለኝ ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው”(ማቴ.8፥22) ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚህ በቁም ሳሉ ሙታን እንደሆኑ አሳወቀው፡፡ የሞተ ሰው በዚህ ዓለም ምን ይፈጸም ምን አንዳች የሚያውቀው እንደሌለ እንዲሁ እነዚህም ወገኖችም ለሰማያዊው ዓለም እንደምውት ናቸውና ስለሰማያዊ አኗኗራቸው የሚያቁት አንዳች ነገር የላቸውም፡፡ ነገር ግን ሕያዋን እንደተባሉት በሁለቱም ዓለማት ታውረው ይኖሩ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሙታን አላቸው እንጂ በሥጋማ መሰሎቻቸውን ሊቀብሩ ተፍ ተፍ እያሉ እኮ ነው!

 

ቅዱሳን “አካሔዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አደረጉ” ሲባልም ምድራዊ አኗኗራቸውን ትተው ከረቂቃኑ ፍጥረታት ጋር ኖሩ ማለት እኮ አይደለም፡፡ ሄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ ሲባል አኗኗሩን ከምድራዊው አኗኗር ለየ ማለት ሳይሆን ሁለቱንም ዓለማት በአግባቡ ኖረባቸው ሲለን ነው፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ቤተሰብ መሥርቶ ልጆችንም ወልዶ ይኖር ነበር፡፡ በኋላም አምላኩ ወደ ብሔረ ሕያዋን ወሰደው፡፡ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ የተባለለት ቅዱስ ነው፡፡ በምድራዊ ሕይወቱም በቅድስና ተመላለሰ፡፡ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሕያዋን የተባሉ ቅዱሳን ናቸው (ማቴ.22፥31-32)፡፡ ይህም የሚያሳየው በረቂቁም በግዙፉም ዓለም እኩል ሕያዋን ሆነው ይኖሩ እንደነበር ነው፡፡

 

በእዚህ የእውቀት እርከን ውስጥ ያሉ ቅዱሳን ሕይወት ምን እንደሚመስል ሶርያዊ ቅዱስ ዮሴፍ (ባለራእይው ዮሴፍም ይባላል) እንዲህ ይገልጸዋል፡- “መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምንረዳው አእምሮአችን ፍጹም ብሩህ በሆነ የማስተዋል ብርሃን ሲሞላ ነው፡፡ በዚያ ጊዜ በልባችን ጠፈር ላይ የሰንፔር ድንጋይን የመሰለ ሰማይ ተዘርግቶ ከልባችን ጠፈር ልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት ያሉዋቸው ብርሃናት (እውቀቶች) ሲፍለቀለቁ ይታየናል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ማራኪ የሆኑ ብርሃናት በልቡናችን የሚፍለቀለቁት ሥላሴ በልቡናችን ውስጥ የባሕርይ የሆነውን ብርሃን ሲያበራልን ነው፡፡ በሥላሴ ብርሃን እገዛ የሚኖረን እውቀት ፍጥረታዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀውና እንድንረዳው የሚያደርገን ሲሆን ከዚህ አልፈን መንፈሳዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀው ያበቃናል፡፡ በመቀጠልም ስለ እግዚአብሔር ቅን ፍርድና መግቦት ወደ ማወቅ እንመጣለን፡፡

 

በዚህ መልክ ከፍ ከፍ በማለት ከክርስቶስ የክብሩ ብርሃን ተካፋዮች ለመሆን እንበቃለን፡፡ ከዚህ ቅዱስና ግሩም ከሆነው እይታ ስንደርስ እጅግ ውብ አድርጎ በፈጠራቸው ዓለማት በእጅጉ እንደነቃለን፡፡ ከእነርሱ የምናገኘው ማስተዋል እጅግ ታላቅ ነው፡፡ በዚህ ድንቅ በሆነ የእውቀት ከፍታ ውስጥ ስንገኝ ስለ ሁለቱ ዓለማት ያለን እውቀት እንደ ጅረት ውኃ ከአንደበታችን ሞልቶ ይፈሳል፡፡ የሚመጣውን ዓለም በዚህ ዓለም ሳለን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ እጅግ ውብ የሆነውን የመላእክትን ማስተዋል ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ ደስታቸውን፣ ምስጋናቸውን፣ ክብራቸውን፣ ዝማሬአቸውንና ቅኔአቸውን እንሰማለን፡፡ መላእክትን ከእነ ማእረጋቸውና ከእነ ክብራቸው እንመለከታቸዋለን፣ እርስ በእርሳቸው  ያላቸውንም አንድነት እንረዳለን፣ ቅዱሳን ነፍሳትን ለመመልከት እንበቃለን፣ ገነትን ማየት፣ ከሕይወት ዛፍ መመገብን (መላእክት የሚመግቡትን የፍቅር ማዕድ ማለቱ ነው)፣ ከቅዱሳን ነፍሳትና መላእክት ጋር መነጋገርና ከዚህም ባለፈ ልዩ ልዩ በረከቶችን ለማግኘት የበቃህ እንሆናለን፡፡” ወደዚህ የቅድስና ወይም የእውቀት ከፍታ ለመወጣጣት ግን አስቀድመን እንደጻፍንላችሁ የራስን ማንነትን ማወቅ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

 

ከላይ ነፍሳችን በሁለቱም ዓለማት አኩል ተሳትፎ እንዳላት ተመለክተናል፡፡ ይህች ረቂቅ የሆነች ተፈጥሮአችን ሥራዎቹዋን የምታጠናቅርበት አካል አላት፡፡ ይህን ረቂቅ አካል እኛ አእምሮ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ይህች ነፍስ ሁለት ወገን የሆኑ የስሜት ሕዋሳት ሲኖሩዋት አንደኛው ወገን ረቂቁን ዓለም የምናስተውልበት ሲሆን ሁለተኛው ወገን ግን ግዙፉዋን ዓለም የምንረዳበት ነው፡፡ ነፍስ ረቂቁን ዓለም እና ግዙፉን ዓለም በምትረዳባቸው የስሜት ሕዋሳት በኩል መረጃዎችን ረቂቅ ወደሆነው የአእምሮዋ ክፍል ታስገባለች፡፡ አእምሮም በስሜት ሕዋሳቱ በኩል ያገኛቸውን  ጠቃሚ መረጃዎች ወደ ውስጠኛው የአእምሮ ክፍሉ አስገብቶ ያኖራቸዋል፡፡

 

እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ አእምሮአችን ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ አንደኛው ልዩ ልዩ አሳቦችን የሚያኖርበት ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል እንለዋለን፡፡ ሌላኛው ክፍል ደግሞ አእምሮአችን በላይኛው የአእምሮ ክፍላችን ከሚመላለሱት ዐሳቦች ይጠቅሙኛል ያላቸውን ዐሳቦች የሚያኖርበት ክፍል ነው፡፡ አንድ ዐሳብ ወደ ታችኛው የአእምሮ ክፍላችን ከመግባቱ በፊት በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ረዘም ያሉ ሒደቶችን ያሳልፋል፡፡ እነዚህ ሒደቶች አንድን ሰው ከስህተት ጠብቀው በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ መልካም ሆኖ እንዲመላለስ ይረዱታል፡፡

 

ሰው ሁለት ወገን ከሆኑት የስሜት ሕዋሳቱ ከመንፈሳዊው ዓለምና ከግዙፉ ዓለም መረጃን ወደ ላይኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባል፡፡ አእምሮም ለሁለቱ አካላት ማለትም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅም መስለው ወደ ታዩት ይሳባል ወይም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እነርሱ ያዘነብላል፡፡ ይህ ዝንባሌ አጥብቆ መሻት(passion) ይባላል፡፡ አእምሮአችን በአንድ ነገር በመሳቡ ብቻ ዐሳቡን ወደ ተግባር ይመልሰዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ በካሜራ ምስልን እንደምናስቀር እንዲሁ ለበለጠ መረዳት የተሳበበትን ነገር ምስል በውስጡ ያስቀረዋል፡፡ ይህ ምስልን በልቡና ውስጥ ማስቀመጥ “ምናብ” (imagination) ተብሎ እንጠራዋለን፡፡ በምናብ መልክ በአእምሮአችን ውስጥ ያስቀመጠውን ዐሳብ አእምሮአችን ደግሞ ደጋግሞ ጠቀሜታውንና ጉዳቱን እንዲሁም እውነተኝነቱን ይመረምራል፤ ያሰላስለዋል፡፡ በዚህም አንድ አቋምን ወደ መያዝ ይመጣል፡፡ ይህ ወደ አንዱ ማድላት አቋም (opinion) ይባላል፡፡ ከዚህም በኋላ አእምሮአችን ዐሳቡ ለሰብእናችን የሚጠቅም ሆኖ ሲያገኘው ሊተገብረው ፍላጎት ያድርበታል፡፡ ይህ ፍላጎቱ ፈቃድ (will) ይባላል፡፡ በመጨረሻም ወደ ትግበራ ይመጣል፡፡

 

አእምሮአችን ወደ ተግባር ሊመልሰው የመረጠውንም ዐሳብ ለአተገባበር  እንዲመች ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል ያስገባዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እግዚአብሔር ወደ ተግባር ለማምጣት በፈቀድነው ፈቃዳችን የሚፈርድብን ወይም የሚባርከን፡፡ ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳኗ ታቦት መቅደስ ለመሥራት አሰበ፡፡ ዐስቦም አልቀረም ወደ ተግባር ለመግባት ነቢዩ ናታንን አማከረው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ዳዊት ቤቱን እንዲሠራለት ፈቃዱ አልነበረም፤ ቢሆንም ቅን ስለሆነው ዐሳቡ እግዚአብሔር ባረከው እንዲህም አለው “እግዚአብሔር ቤት እንደምትሠራለት ይነግርሃል፤ እሠራለታለሁ ብለሃልና፡፡ ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፤ መንግሥቱንም አዘጋጃለሁ፡፡ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል ዙፋኑን ለዘለዓለም አጸናለሁ” ብሎ ባረከው፡፡ (2ሳሙ.7፡) ይህ ከእርሱ ወገን ክርስቶስ እንዲወለድ የሚያሳይ ዘለዓለማዊ በረከት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጁ ሰሎሞን ለዘለዓለም ነግሦ አላየነውምና፡፡ ለዘለዓለም በዳዊት ዙፋን ላይ የነገሠው ከዳዊት ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ (ሉቃ.1፡31) ክፉን ዐሳብ ዐስቦ እርሱን ለመተግበር ፈቃዱ ያለው ሰው ምንም እንኳ ድንጊቱን በተግባር አይፈጽመው እንጂ ልክ ድርጊቱን እንደፈጸመው ተደርጎ ይፈረድበታል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ አመነዝሮአል” ብሎ አስተማረን፡፡(ማቴ.5፡28)

 

ከላይ የዘረዘርናቸውን ሒደቶች የሚፈጸሙት በኅሊናችን መሣሪያነት ነው፡፡ ኅሊናችን ውስጥ እውነትን ከሐሰት የምንለይበት ሚዛን አለ፡፡ እርሱም እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በኅሊናችን ያኖረው ሕጉ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “… አሕዛብ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ … ኅሊናቸው ሲመሰክርላቸው ኅሊናቸው እርስ በእርስ ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግን ሥራ ያሳያሉ፡፡”(ሮሜ.2፡15) ብሎናል፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ወገን የስሜት ሕዋሳቶቻችን ወደ አእምሮአችን የሚገቡ ዐሳቦች ሁሉ እኛን በደለኞች አያሰኙንም፡፡ ነገር ግን እነርሱን በአእምሮአችን ውስጥ አልምተን ወደ መተግበር ፈቃድ ስንመጣ ፍርዱ የዛን ሰዓት በእኛ ላይ ይፈጸማል፡፡

 

ዲያብሎስ ክፉ ዐሳቦችን ከእኛ የመነጩ አድርጎ በአእምሮአችን ውስጥ ሊዘራብን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ስጋት ሊፈጠርብን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የመነጨውን ክፉ ዐሳብ በጽኑ በመቃወም የእግዚአብሔር ወገን ከሆኑት ቅዱሳን መላእክት ጋር ልንወግን ይገባናል፡፡ ይህን ትምህርት የምንቋቸው ባሕታዊው ዮሐንስ የሚባለው ሶርያዊ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የጻፈልንን ድንቅ የሆነ ጽሑፍ በመመልከት ይሆናል ፡፡ እንዲህ ይለናል፡- “በልቡናህ የሚመላለሱትን ዐሳቦችን በጥንቃቄ ተከታተላቸው፡፡ ክፉ ዐሳብ በልቡናህ ዘልቆ ቢገባ አትረበሽ ይህ ዐሳብ ከአእምሮህ የመነጨ እንዳልሆነ ከአእምሮህ በላይ ያለውን የሚውቅ ጌታህ ይረዳዋል፡፡ እርሱ የሚመለከተው ጥልቅ ከሆነው የአእምሮህ ክፍል በመነጨ ክፉ ዐሳብ ደስተኛ የሆንክ እንደሆነ ነው፡፡ የሚጠሉ ክፉ ዐሳቦች በላይኛው የአእምሮህ ክፍል ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡

 

ቢሆንም እግዚአብሔር የሚመረምረው የተጠሉ ክፉ ዐሳቦችን ለይቶ ማስወገድ የሚችለውን ጥልቁን የአእምሮአችንን ክፍል ነው፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል በሚመላለሱት በተጠሉ ክፉ ዐሳቦች የተነሣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ አይፈርድብንም፡፡ ነገር ግን ከጥልቁ  የአእምሮአችን ክፍል የሚመነጩ የተጠሉ ዐሳቦች ስውር በሆኑ እጆቹ የማስወገድ ችሎታው ካለው  እእምሮ ክፍል የሚመነጩ ከሆኑ ግን ፍርድ ይጠብቀናል፡፡ ከጥልቁ የአእምሮችን ክፍል አመንጭተን ለምናመላልሳቸው ክፉ ዐሳቦች እግዚአብሔር በእኛ ላይ ከመፍረድ አይመለስም፡፡ በላይኛው የአእምሮአችን ክፍል የሚመላለሰው ዐሳብም ወደ ውስጠኛው የአእምሮአችን ክፍል እንዳይገባ መከላከል ስንችል ወደ ውስጥ እንዲገባ ከፈቅድንለት እግዚአብሔር ፍርዱን ከዚህ የተነሣ ይሰጣል፡፡ እንዳውም ክፉ ዐሳብ በውስጥህ ጎጆውን ቢሠራና ብዙ ቀንም በአእምሮህ ቢሰነብት፣ ከእዛም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ቢገባ፣ ነገር ግን ውስጠኛው የአእምሮው ክፍል ያለማቋረጥ ላለመቀበል የሚሟገተውና ከአንተም ትእዛዝ የማይወጣ ከሆነ፣ አትረበሽ ይህ ክፉ የሆነው አሳብ ተነቅሎ መወገዱ አይቀርም፡፡ በዚህም ከእግዚአበሔር ዘንድ የምትቀበለው አንዳች ፍርድ የለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ከጥልቁ አእምሮህ የመነጨው መልካሙ ዐስተሳሰብህ ከእግዚአብሔር አምላክህ ዘንድ ታላቅ ዋጋን ያሰጥሃል፡፡ ክፉ ዐስተሳሰብን የሚቃወም የለመደ አእምሮንም ገንዘብህ ታደርጋለህ፡፡”

 

እንግዲህ እግዚአብሔር አምላክ እንዴት እጹብና ድንቅ አድርጎ እንደፈጠረን እናስተውል፡፡ ነገሮችን በአግባቡ እንድናከናውን እግዚአብሔር በአእምሮአችን ውስጥ ልዩ የሆነ ሥርዐትን ዘርግቶልናል፡፡ በእነዚህም የአእምሮ ሥርዐታት አምላክንና ሰውን ሳንበድል ፍቅርን አንግሠናት በዚህ ዓለም በአግባቡ ያለስህተት መመላለስን በሚመጣው ዓለም ከቅዱሳን ጋር የርስቱ ወራሾች ለመሆን እንበቃለን፡፡ እግዚአብሔር ይህን በመረዳት ወደ ተግባር መልሰነው ለመመላለስ ማስተዋል ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

የነነዌ ጦም (ለሕፃናት)

ጥር 29/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ተባለ ሰው መጥቶ “ተነሥተህ ወደ ነነዌ ከተማ ሒድ፤  ሕዝቡ ኀጢአት ስለሠሩ ልቀጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ሔደህ ካስተማርካቸው እና እነሱም ከጥፋታቸው ከተመለሱ እምራቸዋለሁ፡፡” አለው ዮናስ ግን ወደ እነርሱ ሔዶ እግዚአብሔር የነገረውን ቢነግራቸው ይጎዱኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን መልእክት ላይናገር ወስኖ ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ለመሸሽ ፈለገ፡፡  እግዚአብሔር እርሱን ፈልጎ እንደማያገኘውም አሰበ፡፡ ነገር ግን ማንም ከእግዚአብሔር መሸሽ አይችልም፡፡ ዮናስ ግን ይህን አላወቀም ነበር፡፡

ዮናስ በመርከቧ ላይ ሳለ ከባድ አውሎ ነፋስ ተነሣ፡፡ የመርከቧ ተሳፋሪዎች በሙሉ ተጨነቁ  መርከቧ ከተገለበጠች እንዳይሞቱ አሰቡና እግዚአብሔር እንዲረዳቸው ጸለዩ፡፡ ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ሸሽቶ መምጣቱን አሰበ እሱን ወደ ውኃው ቢወረውሩት አውሎ ንፋሱ እንደሚቆም ነገራቸው፡፡ ሰዎቹ በጣም አዘኑ ነገር ግን መርከቧ እንዳትሰምጥባቸው ዮናስን ወደ ባሕሩ ወረወሩት፡፡ ዮናስ በውኃው ውስጥ እንዲሞት ግን እግዚአብሔር አልተወውም፡፡ ዮናስን ሳይጎዳው እንዲውጠው ዓሣ አንበሪ ላከ፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ ዓሣ አንበሪው እየዋኘ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጥቶ ዮናስን ተፋው፡፡ ከተፋው በኋላ እግዚአብሔር ዮናስ ወደ ነነዌ ሔዶ እንዲያስተምራቸው በድጋሚ ነገረው፡፡ ዮናስም ወደ ነነዌ ሔደ እግዚአብሔር የነገረውን ነገራቸው፡፡ ሰዎቹም ሰሙት፡፡ በነነዌ የነገሠው ንጉሥ የዮናስን ትምህርት በሰማ ጊዜ ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፡፡ ሕፃን፣ ሽማግሌ ሳይሉ እንስሳትም ሳይቀሩ ለሦስት ቀን እንዲጦሙ እና እንዲጸልዩ አዘዘ፡፡ ሕዝቡም ሁሉም ሦስት ቀን ጦሙ ጸለዩ፡፡ እግዚአብሔርም ሕዝቡ በጥፋታቸው ስለተጸጸቱ እና ስለጦሙ ከጥፋት አዳናቸው፡፡

ከታሪኩ የምንረዳው፡-

  1. ጦም እና ጸሎት ሊደርስብን ከሚችለው መከራ እና ችግር እንደሚያድን
  2. እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ እንዳለ እና በየትም ቦታ ብንሆን የምንሠራውን ሉ እንደሚመለከተን ያስረዳል፡፡

 

የነነዌ ሰዎች የንስሐ ምስክሮች

በዲ/ን በረከት አዝመራው

የነነዌ ጾም ከሰባቱ የቤተክርስቲያን አጽዋማት አንዱና የዐቢይ ጾም ማዘጋጃ ደወል ነው፡፡ ይህ የነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ በቤተክርስቲያናችን በጣም ታላቅ ዋጋ ያለውና የራሱ መዝሙር የሚዘመርለት፣ ቅዳሴ የሚቀደስበት ታላቅ መታሰቢያ ያለው ታሪክ ነው፡፡ ራሱ ጌታችንም የነነዌ ሰዎችን የንስሐ ታሪክ በመጥቀስ አይሁድን ገስጾበታል፤ በፍርድ ቀንም በዚያ ትውልድ ዘንድ እንደሚፈርዱበት ተናግሯል፡፡ ይህም የሆነበት የነነዌ ሰዎች ደስ የሚያሰኝ የንስሐ ታሪክ ስላላቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስደሳች የንስሐ ታሪክ በጾመ ነነዌ ከሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባት አንጻር ለመመርመር እንሞከራለን፡፡

 

ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት እንደሆነ ሁሉ ንስሐ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡  በዚህ ከእግዚአብሔር ሊለዩ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች ባለቡት ዓለም እስካለን ድረስ ሕይወታችን ሁሉ የንስሐ ጊዜ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም ጊዜ በተለየ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስባቸው የጾም ወቅቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ታላቁና ዋነኛው ዐቢይ ጾም ነው፡፡

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በዐቢይ ጾም ከእያንዳንዱ ምእመን ልቦና የንስሐ ፍሬን ትፈልጋለች፤ ያለትንሣኤ ልቦና /ንስሐ/ የክርስቶስን ትንሣኤ በእውነትና በደስታ ማክበር አይቻልምና፡፡ ለመሆኑ ከንስሐ የሚያሰናክሉን ነገሮች ምን ምን ናቸው? የነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለዚህ ምን ያስተምረናል?

1.    ቅንጦትን መውደድ

ምንም እንኳን በደፈናው ገንዘብ የኃጢአት ምንጭ ነው ባንልም እንደ ወንጌል ትእዛዝ በክርስቲያናዊ መንገድ ካልተያዘ ግን እግዚአብሔርን ሊያስረሳና የኃጢአት ማስፈጸሚያና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜም ገንዘብና ባለጸግነት ከእግዚአብሔር በመለየታችን ያጣነውን ሰላምና ደስታ ለማግኘት ተስፋ የምንጥልበት ጣኦት ሆኖ ሊቀየር ይችላል፡፡ በሀብታችን በምናገኘው ጊዜያዊ ደስታና ሰላም ዘላለማዊውንና ፍጹምን የእግዚአብሔር ስጦታ መፈለግ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን መናፈቅ ልናቆም እንችላለን፡፡ በዚህ መልኩ ብልጽግና ከንስሐ የሚያሰናክል ወጥመድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር ሀብት እንኳ ቢሰጠን ለተቸገረ በመመጽወት፣ ልጆቻችን በክርስቲያናዊ መንገድ በማሳደግ፣ የቤተክርስቲያንን አገልግሎት በማፋጠን የእውነተኛ ደስታና የጽድቅ መንገድ እንድናደርገው እንጂ እግዚአብሔርን የተጠማች ነፍሳችንን ጥሪዋን በማደናቀፍና ጩኸቷን በማፈን በሥጋ ድሎት ውስጥ የምንደበቅበት መሣሪያ እንድናደረገው አይደለም፡፡ ለ«ታላቂቷ ከተማ» ነነዌም የጥፋት መንገድ የሆናት በብልጽገናዋና በታላቅነቷ እግዚአብሔርን ረስታ የኃጢአት ከተማ መሆኗ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ገንዘብ ለዮናስ ከእግዚአብሔር የመከለያ መሣሪያ ሲሆን እናገኘዋልን፡፡ «. ..  ከእግዚአብሔርም ፊት ኮብልሎ ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ዋጋ ሰጥቶ ወደ እርሷ /ወደ መርከቧ/ ገባ» እንዲል /ዮና፤1-3/፡፡

በዚህ ሰዓት ለዮናስ ገንዘብ ባይኖረው ይሻል ነበር፡፡ እኛም ቢሆን ከንስሐ የሚመልስ፣ ለኃጢአት መሣሪያ የሚሆን ሀብት ከሚኖረን በድኅነት ብንኖር ይሻለናል፡፡ ምንም እንኳ በቤተክርስቲያናችን ትውፊት ዐቢይ ጾም አብዝተን የምንጸልይበት፣ በጾም በስግደትና በምጽዋት ልናሳልፈው የሚገባ ወቅት ቢሆንም ፤ አሁን አሁን ግን ገንዘብ ማግበስበሻ እየሆነ እንደሆነ እናያለን፡፡ በመሠረቱ በጾም ወቅት ከሆዳችን የምንቀንሰው ገንዘብ እንድናጠራቅመው ሳይሆን እንድንመጸወተው የሚገባ ነው፡፡ ለማጠራቀምማ የማያምኑ ሰዎችስ ምግብ ይቀንሱ የለ? ለዚህ ነው በነነዌ ጾም በመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት «አሁንም እናንተ ባለ ጠጎች ስለሚደርስባችሁ ጭንቅ ዋይ ዋይ እያላችሁ አልቅሱ፡፡ ሀብታችሁ ተበላሽቷል፣ ልብሳችሁም በብል ተበልቷ፡፡ ወርቃችሁም ብራችሁም ዝጓል፤ ዝገቱም ምስክር ይሆንባችኋል፤ ሥጋችሁንም እንደ እሳት ይበላል፡፡ ለኋለኛው ቀን መዝገብን አከማችታችኋል፡፡ እነሆ እርሻሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፣የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ጸባዖት ጆሮ ገብቷል፡፡ በምድር ላይ ተቀማጥላችኋል፤ በሴሰኝነትም ኖራችኋል፤ ለእርድ ቀን እንደሚወፍር ልባችሁን አወፍራችኋል፡፡» በማለት አስፈሪ ተግሳጽ የሚያስተላልፈው፡፡ ስለዚህ በዐቢይ ጾም አብዝተን የምንመጸውትበት፣ ከእግዚአብሔር የሆነውን ስጦታ የምንፈልግበት፣ የንስሐ ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡

2.    ለኃጢአት ሌላ ተጠያቂ መፈለግ

ሌላው ከንስሐ ሲያርቀን የሚገኘው ምክንያት በሰዎች መፍረድ ነው፡፡ በሰዎች የሚፈርድ ሰው ራሱን የሚያጸድቅ ነው፡፡ ራሱን ያጸደቀ ደግሞ ንስሐ መግባትና ከኃጢአት መመለስ ዳገት ይሆንበታል፡፡ ከነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ ውስጥ ለንስሐ በጣም አስቸጋሪ የነበረው ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ መርከበኞቹና የነነዌ ሰዎች በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ዮናስ ግን ከታሪኩ መጀመሪያ እስከ መጨረሻዋ ጊዜ ድረስ በእግዚአብሔር ያጉረመርም ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከእግዚአብሔር መኮብለሉና የነነዌ ሰዎችን ድኅነት መቃወሙን እንደ  ስህተት እንጂ እንደራሱ ስህተት አለመቁጠሩ ነው፡፡  ለዚህ ነበር ከእግዚአብሔር ኮብልሎ ሲሔድ እንኳ ምንም ዓይነት ጭንቀት ሳይሰማው «በከባድ እንቅልፍ» ተኝቶ የነበረው /ዮና.1-5/፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ኃጢአት እግዚአብሔርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም በራሳቸው ከመፍረድ ይልቅ በሰዎች መፍረድ ይጀምራሉ፤ ወይም የኃጢአታቸው ምክንያት እግዚአብሔርን አድርገው ይገኛሉ፡፡ ነቢዩ ዮናስ የራሱን ክብር ፈላጊነት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ምሕረት የኃጢአቱ ምክንያት ማድረጉ የሚያስገርም ነው፡፡ ይህም ለብዙ ጊዜ ከንስሐ እንዳዘገየው ከታሪኩ እንማራለን፡፡ በተቃራኒው ለንስሐ ቅርብ የሆኑት መርከበኞች በዮናስ ላይ ለመፍረድ ምን ያህል እንደተጨነቁ ስናይ ቀድሞውኑ በዮናስ አለመታዘዝ ምክንያትም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ንስሐ ሊመልሳቸው የፈለገ ይህን አይቶ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

በጾመ ነነዌ የመጀመሪያው ቀን /ሰኞ/ የሚነበበው የቅዱስ ጳዉሎስ መልእክትም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው፡- «ስለዚህ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፣ የምታመካኘው የለህም በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኮንናለህና፡፡ አንተም ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና፡፡ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደሆነ እናውቃለንና፡፡ . . . ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ስታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን? ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቁጣ ቀን ቁጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ»/ሮሜ.2-1-5/፡፡ በተቃራኒው ግን በሰው ላይ ከመፍረድ በራሳቸው ላይ መፍረድን የሚመርጡ ሰዎች ለንስሐ ቅርብ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ የሚነበበው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም የሚያብራራው ይህንኑ ነው/1ቆሮ.4-1/፡፡

3.    የእግዚአብሔርን ተግሳጽ አለመቀበል

በነነዌ ሰዎች የንስሐ ታሪክ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ሰዎችን ሲገስጽ እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ዮናስን በማዕበል፣ ወደባሕር እንዲወረወር በማድረግ፣ አሳ አንበሪ እንዲውጠው በማድረግ እግዚአብሔር ወደ ትክክለኛ መንገዱ ሊመልሰው ቢጥርም በዚህ ሁሉ ሊመለስ አልቻለም፤ ከአሳ አንበሪ አፍ ወጥቶ ሔዶ ቢሰብክም እግዚአብሔር ይቅር ሲላቸው ግን በእግዚአብሔር ላይ ማጉረምረም ጀምሯልና፡፡ ድሮም ቢሆን በፍርሃት እንጂ ስህተቱን ተቀብሎ አልነበረም ወደ ነነዌ ሔዶ የሰበከው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ነፋስ፣ አሳ አንበሪ፣ ትል፣ ፀሐይ/ እንዴት እንደሚታዘዙለት እርሱ ግን ታላቅ ነቢይ ሲሆን አልታዘዝም ማለቱን በማሳየትም ገስጾታል፡፡ በመጨረሻም ለንስሐ በቅቷል፡፡ መርከበኞቹም በመርከባቸው ላይ የተነሣው ማዕበል ተግሳጽ ሆኗቸው ወደ ንስሐ ተመልሰዋል፡፡ ከዘላለም ሕይወት እንዳንለይ አጥብቆ የሚፈልገው እግዚአብሔር ልዩ ልዩ መከራዎችንም በማምጣት ወደ ንስሐ እንድንመለስ ያደርጋል፡፡ ለዚህ ተግሳጽ ግን በትክክለኛ ወይም በተሳሳተ መንገድ መልስ ልንሰጥ እንችላለን፡፡ ካወቅንባቸውና ከተጠቀምንባቸው ችግሮችና መከራዎች ወደንስሐ የሚመሩ መንገዶች ናቸው፡፡ የነነዌ ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡ በነነዌ ጾም በቅዳሴ የሚነበቡት የሚከተሉት ምንባባትም በአጽንኦት የሚገልጹት ይህንኑ ነው፡፡

 

ምስባክ:- «ማዕበልህና ሞገድህ ሁሉ በላዬ አለፈ፡፡
እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዛል በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል
የእኔ ስዕለት ለሕይወቴ አምላክ ነው፡፡»
/መዝ.41-7-8/

መልእክት:- «. .  . ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል. . .» /ሐዋ.14-22/፡፡

 

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አሳዛኙ ነገር ሰው ካለፈ ሕይወቱ አለመማሩ ነው፡፡ በነቢዩ በዮናስ ታሪክም የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ እግዚአብሔር የተሳፈረበትን መርከብ ካናወጠ፣ ዮናስ በአሳ አንበሪ እንዲዋጥ ካደረገ በኋላ እንኳ እግዚአብሔር በነነዌ ሰዎች ላይ ያሳየው ምሕረት ዮናስ ሞትን እስኪመኝ ድረስ እንዲያዝንና በእግዚአብሔር ላይ እንዲያጉረመርም አድርጎታልና፡፡ በእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ተግሳጻት ከእግዚአብሔር ዘንድ ቢመጣም ከኃጢአት ባለመመለስ ከዮናስ ያልተለየ መልስ ነው የምንሰጠው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ራሳችንን የምናይበት፣ በሕይወታችን ያደረጋቸውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የምንመረምርበት፣ በውስጣችን ያደፈጡትን አውሬዎች የምናድንበት የተረጋጋና ሰፋ ያለ ጊዜ ስለሌለን ነው፡፡ ይህን አጥብቃ የተረዳችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በልዩ ልዩ መንገድ የሚጠራንን የእግዚአብሔር ድምፅ የምናዳምጥበት፣ በመልካም ምክንያቶች የተሸፈኑ ነገር ግን መልካም ያልሆኑና መልካም ልንሠራበት የምንችለውን የሕይወት ጊዜዎችን የሚያቃጥሉ ከንቱ ምኞቶቻችን፣ የማይጨበጡና የማይደረስባቸው «ክፉ ተስፋዎቻችን» ሁሉ የምንመረምርበት፣ መልካሟንና እውነተኛዋን ነገር ግን አስቸጋሪዋንና ጠባቧን የሕይወት መንገዳችን አጉልተን «የምናስምርበት» ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥታናለች፤ ይህም ዐቢይ ጾም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበትም የዚህን አስቸጋሪና አወናባጅ ዓለም በድል የተወጡ ሰዎች የሚያዩትን የዘለዓለማዊን ሕይወት «ቀብድ» የትንሣኤውን ብርሃን እናያለን፡፡ ዐቢይ ጾምን እንደሚገባ ያላሳለፈ ክርስቲያን ግን የትንሣኤን ድግስ በልቶ ሆዱን ይሞላ እንደሆነ እንጂ የትንሣኤን ታላቅ ደስታ መቅመስ አይችልም፡፡ ስለዚህም ዐቢይ ጾም ለክርስቲያን ታላቅ ስጦታ መሆኑን ልናውቅ ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለጾም በጻፉት መጽሐፋቸው «በዐቢይ ጾም ሕይወቱን ያልቀየረ ክርስቲያን በሌሎች አጽዋማት ይቀይራል ማለት ይከብዳል» በማለት የጻፉት፡፡

4.    ክፉ እኔነት

በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከብዙ የዮናስ ስህተቶች ጀርባ የነበረውና ንስሐውን ያዘገየበት ታላቁ መሰናከል ክፉ እኔነት ነው፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የነነዌ ሰዎችን ድኀነት ሳይሆን የራሱን ክብር እንዲመለከት ያደረገው በዮናስ ሕይወት ውስጥ በጥልቅ የተተከለ ክፉ እኔነቱ ነው፡፡ በዚያ ሁሉ ታሪክ ውስጥ በርግጥም ዮናስ ስለራሱ እንጂ ስለሰዎች ሲያስብ አልታየም፡፡ ነቢዩ ዮናስ «እኔ ሐሰተኛ ነቢይ ከምባል የነነዌ ሰዎች መጥፋት ይሻላል»«የዮናስ አምላክ ቃሉን ይቀይራል ከምባል የነነዌ ሰዎች ይጥፉ» ብሎ ያስብ እንጂ እግዚአብሔር ግን አላለም፡፡ አመድና ትቢያ የሆነው የሰው ልጅ ስለክብሩ ሲጨነቅ ክብር የባሕሪዩ የሆነ ሩህሩህ አምላክ ግን ማንም እንዲጠፋ አልፈቀደም፡፡

በርግጥ የነነዌ ሰዎች በመዳናቸው የዮናስም የእግዚአብሔርም ቃለ አልታበለም፡፡ ዮናስ «ነነዌ በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች» ብሎ ሰበከ፡፡ አመጸኛዋ ነነዌ ግን በቁጣ እሳት ከመጥፋቷ በፊት በንስሐ ራሷን አዋረደች፡፡ በዚያን ጊዜ ነነዌ በንስሐ አዲስ ፍጥረት የሆነች፣ እግዚአብሔር የሚያጠፋት ሳትሆን የሚወዳት ሌላ ነነዌ ሆነች፡፡ ዮናስ ሆይ በንስሐ የታደሰችው ነነዌ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ እንደማያጠፋስ ለምን አላሰብክም? ታላቁ የእግዚአብሔር ነቢይ ሆይ ንስሐ የገባችዋን ነነዌን ማጥፋት አምላክህን አያስነቅፈውምን? በነቢዩ በዮናስ ውስጥ ያለው እኔነቱ በርግጥም እግዚአብሔርንም፣ የነነዌ ሰዎችንም እንዳያስብ መጋረጃ ሆኖበት ነበር፡፡

በነቢዩ በዮናስ ሕይወት ውስጥ ክፉ እኔነቱ በዚህ መልክ ቢገለጥም፣ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ግን በተለያየ መንገድ ሊገለጥ ይችላል፡፡ አንዳንዶቻችን «እኔ ቅዱስ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ተጠናውቶናል፡፡ ኃጢአታችን ለንስሐ አባታችንና ለጓደኞቻችን ስንናገር እንኳ «ኃጢአትን የመናገር ቅድስና» እንጂ ኃጢአተኝነታችን አይሰማንም፡፡ «እኔ ርኩስ ነኝ» ስንልም ራስን በፈቃድ ኃጢአተኛ የማድረግ «ቅድስና» እንጂ ልባዊ የሆነ ንስሐ አይሰማንም፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ «እኔ አዋቂ ነኝ» የማለት ክፉ እኔነት ይዞናል፡፡ «እኔ እኮ ምንም አላውቅም» ብለን ስንናገር እንኳን በልባችን ራስን ዝቅ ማድረግን «እያስተማርን» ነው በፍቅር ከተሰባሰቡ መንፈሳውያን ወንድሞችና እኅቶች መካከል እንኳን «ወርቃማ መንፈሳዊ ምክሮችን» ለመለገስ እንጂ መች ፍቅርን ‘ከታናናሾቻችን’ ለመማር እንቀመጣለንና፡፡ በዚህም በባዶነታችን እንኖራለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን «ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች መድኃኒት አያስፈልጋቸውም» ብሏል፡፡ ሕመምተኞች መሆናችን አውቀን በንስሐ ብንቀርብ መድኃንኒት ይሆነናል፤ ራሳችንን አጽድቀንና «ቅዱስ ነኝ» ብለን በውሸት የጤንነት ስሜት መድኃኒት መፈለግ ከተውን ግን ከነኃጢአታችን እንሞታለን፡፡ ጌታችን ለእውራን ብርሃን፣ ዕውቀት ለሌላቸው ሰማያዊ ጥበብን የሚሰጥ ራሱ የእግዚአብሔር ጥበብ መሆኑ እውነት ነው፤ ነገር ግን ራሳችን በአዋቂዎች ተራ ከመደብን መምህር አልፎን ይሔዳል፡፡ ጌታ አለማወቃቸውን ያወቁትን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ጥበብን የሚፈልጉትን ሲያስተምር እንጂ «ምሁራንን» ሊያስተምር አልመጣምና፡፡ በኃጢአት መኖር እንደ ሀሞት መሮት፣ እንደጨለማ ከብዶት ከልቡ የሚጮኽን ተነሣሒ ለመቀደስ፣ እግዚአብሔር የዕውቀት ምንጭ የሕሊና ብርሃን መሆኑን አውቀው ከጥልቅ ከልቦናቸው ዕውቀትን የሚፈልጉትን ለማስተማር መጥቷልና እንደዚሁ ካልሆንን ከዚህ ጸጋ ዕድል ፈንታ አይኖረንም፡፡

ይህን ሁሉ የሕይወታችን ውጥንቅጥ እንመረምርበት ዘንድ ታላቁ የቤተክርስቲያን ስጦታ ዐቢይ ጾም እነሆ፡፡

የእውነተኛ ንስሐ ውጤቶች በነነዌ ሰዎች ታሪክ

1.    የዘላለም ሕይወት ተስፋ

ነነዌ የጥፋት ፍርድ ከተፈረደባት በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጣት ከተማ ናት፡፡ በሌላ አነጋገር ነነዌ ሞታ የተነሣች ከተማ ናት ማለት ይቻላል፡፡ ነቢዩ ዮናስም ወደ ባሕር ከተጣለ፣ በአሳ አንበሪ ሆድ ውስጥ ካደረ በኋላ የመኖር ተስፋ የተሰጠው ሰው ነው፡፡ መርከበኞችም መርከባቸው በማዕበል ከተመታች በኋላ፣ ማዕበሉ ካሸነፋቸው በኋላ በእግዚአብሔር ምሕረት ሌላ የመኖር ተስፋ የተሰጣቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የነነዌ ታሪክ የተስፋ ታሪክ ነው፡፡

ንስሐም በኃጢአት ከሞቱ በኋላ እንደገና የመኖር ተስፋ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የዘለዓለም ሕይወትን ተስፋ ማድረግ ይከብዳቸዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ በንስሐ አለመኖራቸው ነው፡፡ ሰው ያላየውን ነገር እንዴት ይናፍቃል? የማያውቀውን ነገርስ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? በንስሐ የሚኖር ሰው ግን የዘለዓለም ሕይወት ቀብድ የሆነ ትንሣኤ ልቦናን ይነሣልና የዘለዓለም ሕይወትን በተስፋ ይናፈቃሉ፡፡ ዐቢይ ጾምንም በንስሐና ራስን በመመርመር ያሳለፈ ሰው በትንሣኤው ትንሣኤን ይቀምሳልና ዘለዓለማዊውን ትንሣኤ በተሰፋ ይናፍቃል፡፡

በነነዌ ጾም የሚነበቡ የቅዳሴ ምንባባትም ይህን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፡-

«. . .  ትዕግሥትም ፈተናን፣ ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን በመከራችን ደግሞ እንመካለን፡፡ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም፡፡» /ሮሜ.5-4-5/፡፡

«እናንተ ግን፣ ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን  ጠብቁ፡፡» /ይሁዳ.1-20/፡፡

2.    በእግዚአብሔር ዘንድ መከበር

በንስሐ የተመለሰችው ነነዌ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ ከብራለች፡፡ የነነዌ ሰዎች ንስሐ በማይገቡ ዘንድ በትውልዱ ሁሉ ምስክር ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቅዷል፡፡ «የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፣ እነሆም «ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ» እንዲል /ሉቃ.11-32/፡፡ የነቢዩ የዮናስ ታሪክም እንደዚሁ ነው፡፡ የንስሐ ሰባኪ የሆነው ራሱም ከብዙ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኋላ በንስሐ የተመለሰው ዮናስ የክርስቶስ ምልክት እንዲሆን እግዚአብሔር መፍቀዱ እግዚአብሔር ለተነሳሕያን የሚሰውን ክብር ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን በዚህ ምድር ያለን ሰዎች የተነሣሕያንን ክብር ባናውቅም በሰማይ ያሉ መላእክት ግን በአንድ ኃጢአተኛ ንስሐ መግባት ታላቅ ደስታ ማድረጋቸው የንስሐን ክብር ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው ለንስሐ የተዘጋጀ ልብን በማየት እግዚአብሔር አስቀድሞ ነነዌን «ታላቂቷ ከተማ» ብሎ የጠራት /ዮናስ.1-2/፡፡ ተነሣሕያን የእግዚአብሔር ይቅርታና ፍቅር የሚገለጥባቸው ሰዎች ናቸውና በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ዘንድ የከበሩ ሰዎች ናቸው፡፡

3.    የእግዚአብሔርን ኃይል ማየት

በነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔር ኃያልነት በግልጥ ተገልጧል፡፡ የእግዚአብሔር ኃያልነትም በትዕግሥቱ፣ በፍቅሩ፣ ፍጥረትን በመግዛቱ፣ ለሰው ልጆች በሰጠው ድንቅ ነፃነት ወዘተ ተገልጧል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንዲትም ነፍስ ሳትጠፋ ሁሉም ይድኑ ዘንድ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግሥቱ ኃያልነት እንዴት ድንቅ ነው! የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያስተምር ዘንድ ነቢይ የሆነው ዮናስ እንኳ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ትቶ ሲኮበልል በሔደበት ሁሉ እየተከተለ በተለያየ መንገድ ወደ መንገዱ እንዲመለስ ይሠራ ነበር፡፡ ምናልባትም ሰው ዮናስን ይህን ያህል አይታገሰውም፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን ‘የመምከር’ ዕድል ቢሰጠን «ጌታ ሆይ አንተ ሁሉን ማድረግ ትችላለህ፤ ከነዚህ ድንጋዮት እንኳ ለአብርሃም ልጆች ማስነሣት ትችላለህ፡፡ ለምን ዮናስን ትለምነዋለህ? ተወው ሌላ ነቢይ ወደ ነነዌ ላክ፡፡ ዮናስን ርግፍ አድርገህ ተወው ከነነዌ ሰዎች የራሱን ክብር አስቀድሟልና፡፡» እንል ይሆናል፡፡ በባሕሪዩ ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ግን ዮናስ በንስሐ ይመለስ ዘንድ ጠብቆታል፤ በመጨረሻም ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ነቢይ አድርጎታል፡፡

በነነዌ ታሪክ የእግዚአብሔር የፍቅሩ ታላቅነትም ተገልጧል፡፡ የእስራኤል አምላክ ይባል እንጂ ከአሕዛብ መካከል ለንስሐ የተዘጋጀ ሕዝብ ሲያይ ነቢዩን ልኮ ሕዝቡ አድርጓቸዋል፡፡ ቀና ልብ ያላቸው፣ ዮናስ ሲተኛ እንኳ ለማያውቁት አምላክ ሲጸልዩ የነበሩትን መርከበኞችንም በዮናስ  ምክንያት እንዲያውቁት አድርጓል፡፡ በርግጥም እግዚአብሔር ወደርሱ የምታይን ነፍስ፣ እርሱን የተጠማችን ልቦና አይተዋትም፡፡

በነነዌ ሰዎች ታሪክ የታየው ሌላው የእግዚአብሔር ኃይል በፍጥረቱ ላይ ያለው ሥልጣን ነው፡፡ ግዕዛን የሌላቸው ፍጥረታት /ፀሐይ፣ ማዕበል፣ ትል፣ ዛፍ፣ አሳ አንበሪ. . . / የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያለምንም ተቃውሞ ሲፈጽሙ እናያለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ታላቅ ስጦታ ‘ነፃነትን’ እናደንቃለን፡፡ ፍጥረታት የሚታዘዙለት ኃይል እግዚአብሔር በነፃነት የፈጠረው የሰው ልጅ ፈቃዱን ሲጥስ ይመለስ ዘንድ በሚታዘዙት ፍጥረታት፣ በነቢያት. . . ይናገራል እንጂ ልቦናን በኃይሉ ቀይሮ እንደፈቃዱ እንዲኖር አያደርግም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መቀየር የፈለገን ልብ መቀየር የሚችል የሁሉ ፈጣሪ መሆኑን ፍጥረታቱን በማዘዝ አሳይቷል፡፡

ከዚህ ታሪክ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገሮችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በንስሐ የምንኖር ከሆነ ወደዚህ ሕይወት እንደርስ ዘንድ እግዚአብሔር የታገሰባቸውን ያለፉትን የኃጢአት ዘመናት አስተውለን የእግዚአብሔርን የትዕግሥቱን ብርታት በሕይወታችን እናውቃለን፡፡ ከዚህ በኋላ ስለ እግዚአብሔር ታጋሽነት ሰዎች ሊነግሩን አያስፈልግም፤ በሕይወታችን አይተነዋልና፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ወደ እርሱ እንመለስ ዘንድ በሕይወታችን ውስጥ የሠራውን የፍቅሩን ብርታትም እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ምድር ላይ ከቢሊዮኖች መካከል አንድ ብንሆንም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በንስሐ መመለሳችን ሁሌ በእግዚአብሔር ሕሊና ውስጥ ሲታሰብ የኖረ፣ በሰማያት ካሉ ቅዱሳን ይልቅ የአንድ ኃጢአተኛ መመለስ ለሰማያትና ለእግዚአብሔር ደስታ የሚሰጥ መሆኑን ስናውቅ በርግጥም እግዚአብሔር እንዴት ሰውን ወዳጅ ነው? ነፍሳችንስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል የምትወደድ ናት? እንላለን፡፡

ከዚህ ሌላ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ሁሉን የማድረግ ሥልጣን በመታዘዝ እንዳሳዩ ሁሉ በንስሐ የተመለሰ ኃጢአተኛም የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት የሚታይበት ይሆናል፡፡ በኃጢአት የኖረን፣ አያሌ ዘመናትን በዲያብሎስ ምክር በጠማማ መንገድ የኖረን ልቦና መቀየር ከኃያሉ ከእግዚአብሔር በቀር ለማን ይቻለዋል? ኃጢአተኛን ‘ቅዱስ’ ማድረግ የእግዚአብሔር የብቻው የኃያልነቱ ውጤት ነውና፡፡ ለዚህ ነው ‘ተነሳሕያን’ ሰማዕታት ናቸው የሚባለው፤ የእግዚአብሔርን ሥራ በሕይወታቸው ይመሰክራሉና፡፡ ጥንታውያን ክርስቲያኖች በደማቸው የእግዚአብሔርን ክብር መስክረው ከሆነ ለዚህ ትውልድ ደግሞ «የንስሐ» ሰማዕትነት ቀርቶለታል፡፡

በአጠቃላይ ከነነዌ ሰዎች ታሪክ ስለንስሐ ብዙ እንማራለን፡፡ ለዚህም ነው ከብዙ የንስሐ ታሪኮች መርጣ ቅድስት ቤተክርስቲያን በተለየ ክብር የምታስበው፡፡ ለዚህም ነው ለታላቁ የንስሐ ወቅት ለዐቢይ ጾም ማዘጋጃ መግቢያ ያደረገችው፡፡ እኛም ከዚህ ታሪክ ተምረን፣ የተማረነውንም በንስሐ ወቅታችን /በአሁኑ ጾም/ በተግባር ልናውለው ይገባል፡፡ ለዚህም የተነሳሕያን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጾመ ነነዌ!!

ጥር 25/2004 ዓ.ም.

በገብረእግዚአብሔር ኪደ

ነነዌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸው በስፋት ከተጻፈላቸው የሜሶፖታምያ ከተሞች አንዷ ናት፡፡ ብዙ የሥነ መለኲት ምሁራን ከዛሬዋ የሞሱል ከተማ በተቃራኒ ከባግዳድ ሰሜን ምዕራብ 350 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንደ ነበረች ይስማማሉ፡፡ ምንም እንኳን በ4000 ቅ.ል.ክ. ገደማ በናምሩድ በኩል ብትቆረቆርም /ዘፍ.10፡11-12/ የአሦራውያን ዋና ከተማ የሆነችው ግን በ1400 ቅ.ል.ክ. ነው /2ነገ.19፡36/፡፡ በከተማዋ በጣም ታዋቂ የነበረው የጣዖት ቤተ መቅደስ የአስታሮት ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡
በዚህች ከተማ የሚኖሩት ሰዎች የሚሠሩት ክፋትና ኃጢአት እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ጽዋው ሞልቶ መጥፊያቸው ስለ ደረሰ ለፍጥረቱ ርኅራኄ ያለው እግዚአብሔር ግን ንስሐ ይገቡ ዘንድ ነብዩ ዮናስን ልኮላቸዋል፡፡ ይህ ነብይ ከአሕዛብ ወደ አሕዛብ የተላከ ነብይ ነው፡፡ አላላኩም  አንድ ነብይ ወደ እስራኤላውያን ተልኮ እንደሚያደርገው ለመገሰጽ ሳይሆን ወደ ንስሐ ይጠራቸው ዘንድ ነበር፡፡ ነገር ግን ነብዩ ወደዚያች ከተማ እንዲሄድ በእግዚአብሔር ቢታዘዝም ወደ ተርሴስ ሲኮበልል እንመለከተዋለን፡፡ ቅዱስ ጄሮም ነብዩ ለምን እንዲህ እንዳደረገ ሲናገር፡- “ዮናስ አሕዛብን ከመጥላቱ የተነሣ ሳይሆን መዳን ከእስራኤል እየራቀ መሆኑን በትንቢት መነጽር ሲመለከት ወደ ነነዌ አልሄድም አለ፡፡ ይኸውም ሙሴ ይህን ሕዝብ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍህ ደምስሰኝ ያለው ዓይነት ነበር /ዘጸ.32፡31-32/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ስለ እነርሱ እርሱ ቢረገም እንደሚመርጥ እንደሰማነው” ብሏል /ሮሜ.9፡3/፡፡ በእርግጥም በዘመነ ሐዲስ አሕዛብ በክርስቶስ አምነው ሲጠመቁ እስራኤል ግን መጻሕፍትን ብቻ ይዘው ቀርተዋል፤ እስራኤል ነብያትን ብቻ ይዘው ሲቀሩ አሕዛብ ግን የነብያቱን የትንቢት ፍጻሜ ይዘዋል /ማቴ.12፡42/፡፡
ልብና ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ አምላክ ግን ዮናስ ላለመታዘዝ ብሎ እንዳላደረገው ስላወቀ በልዩ ጥበቡ ሲወስደው እናያለን፡፡ አስቀድሞ ታላቅ ነፋስን በመርከቢቱ ላይ አመጣ፤ ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አሰናዳ፤ ቀጥሎም ዓሣው በየብስ እንዲተፋው አደረገ፡፡
ዮናስ ወደዚያች ከተማ ከደረሰ በኋላ ግን ምንም እንኳን የሦስት ቀን መንገድ ዙሮ መስበክ ቢጠበቅበትም የአንድ ቀን መንገድ ያህል ወደ ከተማይቱ ውስጥ ሊገባ ጀመረ፤ ጮኾም በሦስት ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች አለ። የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ለጾም አዋጅ ነገሩ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ። ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ ደረሰ፤ እርሱም ከዙፋኑ ተነሥቶ መጐናጸፊያውን አወለቀ ማቅም ለበሰ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።  አዋጅም አስነገረ፥ በነነዌም ውስጥ የንጉሡንና የመኳንንቱን ትእዛዝ አሳወጀ፥ እንዲህም አለ፡- “ሰዎችና እንስሶች ላሞችና በጎች አንዳችን አይቅመሱ፤ አይሰማሩም ውኃንም አይጠጡ፤ ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ። እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” ሰው ወዳጁ ጌታም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፤ ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም። በእርግጥም እግዚአብሔርን የሚፈራ ልቡና የትምህርት ጋጋታ አያስፈልገውም፤ የቀናት ብዛት አያስፈልገውም፡፡
እኛ ክርስቲያኖችም ይህን በማዘከር “ንስሐ ብንገባ እንደ ነነዌ ሰዎች ከተቃጣው ማንኛውም መቅሰፍት እንድናለን” በማለት በየዓመቱ ከዓብይ ጾም መግቢያ ሁለት ሳምንት አስቀድማ ካለችው ሰኞ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ድረስ “ጾመ ነነዌ” በማለት እንጾማታለን፡፡ ዘንድሮም ዓብይ ጾም የካቲት 12 ስለሚገባ የአሁኑ ሰኞ ጥር 28 እስከ ረቡዕ ጥር 30 እንጾማታለን፡፡
እግዚአብሔር የመረጠውን ዓይነት ጾም እንድንጾም ከተቃጣው ማንኛውም ዓይነት ፈተናም እንድናመልጥ ሰውን በመውደድ ሰው የሆነው ክርስቶስ ይርዳን አሜን!!
0015

ተዋሕዶ ያለ ጥርጥር ታላቅ ምስጢር /1ኛጢሞ 3፥16/

ጥር 23/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሁለት ዓመት የዕሥር ጊዜውን ጨርሶ ከሮም ከተማ ከወጣ በኋላ ጥቂት የአገልግሎት ጊዜ ሲያገኝ በ66 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የጢሞቴዎስ መልእክት ጽፏል፡፡

0015“እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል” እንደሚባለው  በግብር በቃል በሐሳብ ሥነ ፍጥረትን ከፈጠረበት አምላካዊ ጥበቡ ይልቅ ሰው በወደቀ ጊዜ ከወደቀበት የተነሣበት የአምላክ ሰው መሆን ምስጢር ታላቅ በመሆኑ ይኸ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ተብሎ ተጽፏል፡፡ “በሥጋ የተገለጠ በመንፈስ የጸደቀ ለመላእክት የታየ በአሕዛብ የተሰበከ በዓለም የታመነ በክብር ያረገ” ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወሰኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ታላቅ ነው፡፡

አዳም የ30 ዘመን ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በገነት 7 ዓመት ከኖረ በኋላ በምክረ ከይሲ ተታልሎ ልጅነቱን ቢያጣም ኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃደ ሥጋን በጾም ድል ነሥቶ ሰው በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር አስተምሮ ስስትን ድል አደረገ፡፡ የአዳም እግሮች ወደ ዕፀ በለስ ተጉዘው በእጁ ቆርጦ ቢበላ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ ተጉዞ እጆቹና እግሮቹን ተቸንክሮ ተሰቅሎ አዳነው፡፡ አዳም ከጸጋ ልብሱ ቢራቆት ኢየሱስ ክርስቶስም የብርሃን ልብሱ እንዲመለስለት እርቃኑን ሆኖ ተሰቀለ፡፡ ይህ ሁሉ የማዳን ሥራው በሥጋ በመገለጡ የተደረገ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ የአዳምን ሞት ወሰዶ የእሱን ሕይወት ሰጥቶ የመቃብርን ኀይል ሽሮ ሞትን ድል አድርጎ እኛን ያዳነበት ጥበቡ ያለጥርጥር ታላቅ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ምስጢሩ ታላቅ መሆኑን ቅዱስ አትናቴዎስ ሲያስረዳ “ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት መረዳት /ማወቅ/ የልብሱን ጠርዝ ብቻ እንደማወቅ ነው፡፡ ስለ ምስጢረ መለኮት የበለጠ በመረመርኩ ቁጥር የበለጠ ምስጢር ይሆንብኛል” ይላል፡፡ እውነትም የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት መመርመር የአምላክ ሰው የመሆንን ምስጢር መረዳት ለሰው አእምሮ የረቀቀ ነው፡፡

አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ አዳምን እና ልጆቹን ያዳነበት ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ በመሆኑ በቸርነቱ ያዳነንን አምላክ ከማመስገን በቀር ምን ልንል እንችላለን?

በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ትምህርታችን አምላክ ሰው ሆኖ አዳምንና ልጆቹን አዳናቸው ብለን እናስተምራለን አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ ስንል በምስጢረ ተዋሕዶ ነው፡፡ በ431 ዓ.ም በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ከክህደቱ ለመመለስ 200 የሚሆኑ ሊቃውንት ሲሰበሰቡ የሊቃውንቱ አፈ ጉባኤ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ ተዋሕዶ የሚለውን ቃል አጉልቶ ተጠቅሞበታል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ኦርቶዶክስ ከሚለው ቃል ጋር ተዋሕዶ የሚለው ቃል የበለጠ መታወቅ ጀምሯል፡፡

አምላክ ሰው ሆነ ስንል መለኮት ወደ ሥጋነት ሥጋም ወደ መለኮትነት ተለወጠ ማለታችን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ /ሐውልት/ ሆናለች /ዘፍ.19፥26/፡፡ በቃና ዘገሊላም በገቢረ ተአምር ውኃው ወደ ወይን ጠጅ ተለውጧል /ዮሐ.2፥1/፡፡ የሎጥ ሚስት የጨው ሐውልት እንደሆነችው፤ ማየ ቃናም ፍጹም የወይን ጠጅ እንደሆነው አምላክ ሰው ሆነ ስንል አምላክነቱን ለውጦ ፍጹም ሰው ብቻ ሆነ ማለታችን አይደለም፡፡ እንዲሁም አምላክ ተለውጦ ሰው ቢሆንማ ኖሮ የእሩቅ ብእሲ ደም ድኅነትን ሊያሰጥ ስለማይችል በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነውን ፍጹም ድኅነት ከንቱ ያደርግብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ እንደማይለወጥ በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል /ሚል.3፥6/፡፡ በመሆኑም አምላካችን ሰው የሆነበት ምስጢር ቃል /መለኮት/ በሥጋ ሥጋም በቃል ሳይለወጥ ሳይጠፋፉ መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡

“ቃል ሥጋ ሆነ…. በእኛም ላይ አደረ” /ዮሐ.1፥1-14/ የሚለው ገጸንባብ መጽሐፍ በማኅደር ውኃ በማድጋ እንዲያድር መለኮት በሥጋ ላይ አደረበት ማለት አይደለም፡፡ “የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም በተወለደው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ አደረበትና የጸጋ አምላክ አደረገው እንጂ ሥጋን አልተዋሐደም” ብሎ ንስጥሮስ ያስተማረው  የኅድረት /ማደር/ ትምህርት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የተወገዘ ክህደት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” /ማቴ.3፥17/ አለ እንጂ “የልጄ ማደሪያ የሆነውን እርሱን ስሙት አላለም”፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ነቢዩ ሲያስረዳ “…ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ…” /ኢሳ. 9፥6/ ብሏል፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነው እያለች ታስተምራለች፡፡

አምላክ ሰው የሆነው መለኮትና ሥጋ ተቀላቅለው ነው አንልም፡፡ መቀላቀል /ቱሳሔ/ መደባለቅንና ከሁለቱም የተለየ ማእከላዊ ነገር መፍጠርን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ውኃና ወተት ሲቀላቀሉ ስም ማእከላዊ መልክ ማእከላዊና ጣእም ማእከላዊን ያመጣሉ፡፡ ስም ማእከላዊ ውኃ ከወተት ጋር ቢቀላቀል ፈጽሞ ውኃ ፈጽሞም ወተት ባለመሆኑ አንጀራሮ የተባለ ሌላ ስም ይሰጠዋል፡፡ መልክ ማእከላዊ ስንልም ውኃው እንደወተቱ ባለመንጣቱ እንደ ውኃውም ባለመጥቆሩ መካከለኛ የሆነ መልክ ይይዛል፡፡ ጣእም ማእከላዊ ውኃውም ወተቱም የቀደመ ጣእማቸውን ለቀው እንደ ውኃ ባለመገረም/ባለመክበድ/ እንደ ወተቱ ባለመጣም ማእከላዊ የሆነ ጣእም ያመጣል፡፡ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢር ግን ሥጋ የሥጋን ባሕርይ ሳይለቅ መለኮትም የመለኮትነትን ባሕርይ ሳይለቅ በተአቅቦ /በመጠባበቅ/ ባለመጠፋፋት ነው፡፡ መለኮትና ሥጋ ሳይቀላቀሉ ሥጋ የመለኮትን ባሕርይ የራሱ አድርጎ መለኮትም የሥጋን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጎ በተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡

አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል ልብስ በልብስ ላይ እንደሚደረብ መለኮትና ሥጋ እንደዚሁ በትድምርት /በመደራረብ/ ሰው ሆነ ማለት አይደለም፡፡ በቆሎና ስንዴ ቢቀላቀሉ ይህ በቆሎ ነው ይህ ስንዴ ነው ብለን እንደምንለያቸው የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ በመለያየት /በቡአዴ/ ከቶ አልሆነም፡፡

ማኅተመ አበው ቅዱስ ቄርሎስ ምስጢረ ተዋሕዶን ባስተማረበት ትምህርቱ አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰው አምላክ ሆነ ስንል በተዋሕዶ እንደሆነ በምሳሌ ገልጦ አስተምሯል፡፡ ተዋሕዶውም ነቢዩ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በጎቹን ሲጠብቅ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥል ሐመልማሉም በነበልባሉ ሳይጠፋ እንዳልተጠፋፉት መለኮት ሥጋን ሳያቀልጠው መለኮትም በሥጋ ሳይጠፋ በተዋሕዶ አንድ ሆነ እንላለን፡፡ በእሳት ውስጥ የገባ ብረትም የባሕርዩ ያልነበረውን ብሩህነት በእሳቱ ያገኛል፤ ቀድሞ አይፋጅ የነበረው ብረት ይፋጃል፡፡ አካል ያልነበረው እሳትም በብረቱ ሆኖ ቅርጽ ይኖረዋል፡፡ አይጨበጥ የነበረው እሳት ይጨበጣል፤ አይዳሰስ የነበረው እሳት ይዳሰሳል፡፡ አንጥረኛው በጉጠት ብረቱን ይዞ ፍህም የሆነውን ብረት ይቀጠቅጠዋል፡፡ ብረቱ ሲደበደብ የተመታው እሳቱ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ብረቱ ነው አይባልም፡፡ እሳትና ብረት በተዋሕዶ አንድ ስለሆኑ ብረቱ ሲመታ እሳቱ አለ፤ እሳቱ ሲመታም ብረቱ አለ፡፡ እሳቱ ሲፋጅም /ቢያቃጥልም/ ብረቱ አለ፡፡የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶም በዚህ መልክ ስለሆነ መለኮት ሥጋን በመዋሐዱ መከራን ተቀብሎ ሞቶ አዳነን ብለን እናምናለን፡፡

በዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ዐይነ ስውሩን ሰው አምላካችን ሊያድነው በፈቀደ ጊዜ ምራቁን ወደመሬት እንትፍ ብሎ በጭቃ ዐይኑን ቀብቶ አድኖታል /ዮሐ.9፥1/ ምራቅ ብቻውን ዐይንን በማብራት ተአምር መሥራት የማይችል የሥጋ ገንዘብ ነበረ፡፡ መለኮት ብቻውንም ምራቅ ማውጣት አፈር ማራስ አይስማማውም ሥጋ ከመለኮት ጋር ተዋሕዷልና በምራቁ ዕውርን አበርቷል፡፡ ገቢረ ተአምራቱም የተከናወነው በሥጋ ብቻ ነው ወይም በመለኮት ብቻ ነው አይባልም፡፡

ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ ሰው በመሆኑ በባሕርዩ ተዋራጅነት የለውም በላይ በሰማያት ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተምሮ መከራን ተቀብሎ ፍጹም ድኅነትን ሰጥቶናል፡፡ በሥጋ ተርቧል፣ ተጠምቷል አንቀላፍቷል፡፡ አምላክ ነውና ሙት አንሥቷል ድውይ ፈውሷል፡፡ በመሆኑም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆነ የምንለው በተዋሕዶ ነው፡፡ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ በመሆኑ የሥጋንም የመለኮትንም ሥራ ባለመለያየት ባለመነጣጠል ሠራ በቅዱስ መጽሐፍ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ፡፡” /ሐዋ.26፥28/ ተብሎ መጻፉ መለኮት በባሕርዩ ሥጋ ደም ኖሮት አይደለም፡፡ ይህ የሐዋርያው ቃል መለኮት የሥጋን ባሕርይ ባሕርዩ አደረገ ደሙን አፈሰሰ ሥጋውን ቆረሰ ብለን ለምናስተምረው የተዋሕዶ ትምህርት የታመነ ምስክር ነው፡፡ እግዚአብሔር “በገዛ ደሙ” ቤተ ክርስቲያንን የዋጃት በተዋሕዶ ሰው በመሆን ነውና በእውነት ይህ ምስጢር ታላቅ ነው፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ስለምስጢረ ሥጋዌ እንዲህ ይላል” ሐዋርያ ሊሆን የተጠራ የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ጳውሎስ በነቢያቱ አፍ በቅዱሳት መጻሕፍት አስቀድሞ ስለልጁ የተናገረ በሰብአዊ ሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ በአብና በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ዐሳየ ዳግመኛም ነቢዩ እንባቆም እንዲህ አለ፤ እግዚአብሔር ከቴማን ቅዱሱም ከፋራን ተራራ ይመጣል፡፡ ፋራን በጣዕዋ /በጥጃ/ ይተረጎማል ጣዕዋ በንጽሕት ድንግል ይተረጎማል፡፡ ክብሩ ሰማያትን  ከድኗል፡፡ ይህም በመለኮት ኀይል ከአባቱ ጋር እኩል ትክክል በመባል ይተረጎማል፡፡ ምስጋናውም ምድርን ሞልቷል ይህም በአጽናፈ ዓለም በተሰበከው ገቢረ ተአምራት ይተረጎማል በምድር ሁሉ ነገራቸው ወጣ፡፡ እስከ አጽናፈ ዓለም ንግግራቸው ደረሰ፤ ተብሎ በነቢዩ እንደተነገረ፤ ዳግመኛ በነቢይ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው ተብሎ እንደተነገረ፤ ዳግመኛም ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ፤ ጌታ እግዚአብሐር ተገለጠልን፤ እንደገና በኪሩቤል የሚቀመጥ ተገለጠ፤ ተብሎ እንደተነገረ ያለሥጋዌ እግዚአብሔርን ያየ ማነው? ሙሴን “ፊቴን ዐየቶ በሕይወት የሚቆይ የለም” እንዳለው ነው” ይላል፡፡ /ሮሜ.1፥33፣ ዕብ.1፥1፣ ዕን.3፥3፣ መዝ.18፥4፣ መዝ.117፥26-27፣ መዝ.79፥1፣ ዘፀ.33፥1/ (መጽሐፈ ምስጢር 2000፥82 በአማኑኤል ማተሚያ ቤት ኀይለ ማርያም ላቀው /መ/ር/ እንደተረጎመው)

ተዋሕዶ ከሚጠት /ከመመለስ/፣ ከውላጤ /ከመለወጥ/፣ ከቱሳሔ /ከመቀላቀል/፣ ከትድምርት /ከመደረብ/ ከቡዐዴ /ከመቀራረብ/ በራቀና በተለየ ሁኔታ አምላክ ሰው የሆነበት ምስጢር ነው፡፡ መለኮትና ሥጋ አንዱ አንዱን ሳያጠፋው፣ ሳይለውጠው፣ ያለ መለያየት፣ ያለመከፋፈል ያለ መጠፋፋት ያለ መቀላቀል በተዐቅቦ /በመጠባበቅ/ የተዋሐዱበት አምላክ ሰው የሆነበት ይህ ምስጢር ድንቅ ነው፡፡

ቅዱስ ቄርሎስ የተዋሕዶን ምስጢር በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል “የሚረዳህስ ከሆነ የትስብእትና /የሥጋ/ የመለኮትን ተዋሕዶ በእኛ ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ መስለን እንነግርሀለን፤ እኛ በነፍስና በሥጋ የተፈጠርን ነንና፤ አንዱን የሥጋ አንዱን የነፍስ ብለን ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አናደርገውም፤ ሰው ከሁለት አንድ በመሆኑ አንድ ነው እንጂ፡፡ ከሁለቱም ባሕርያት አንድ በመሆኑ ሁለት ሰው አይባልም፡፡ በነፍስ በሥጋ የተፈጠረው ሰው አንድ ነው እንጂ፡፡ ይህንንስ ካወቅን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተዋሕዶ በፊት እርስ በርሳቸው አንድ ካልነበሩ ከተዋሕዶ በኋላም ከማይለያዩ ከሁለት ባሕርያት አንድ እንደሆነ እናውቃለን” /ሃይማኖተ አበው ዘቄርሎስ.78፥19/

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ በምድር ላይ በመገለጡ ከባሕርዩ የጎደለበት ነገር የለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በላይ በሰማያት በመላእክት እየተመሰገነ በምድር ዞሮ አስተማረ፤ መከራ ተቀበለ ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ አስተምህሮ ምስክር የሚሆነን የቅዱሳን መላእክትና የቅዱስ ያሬድ የምስጋና ቃል ነው፡፡መላእክቱ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” አሉ /ሉቃ.2፥14/፡፡ ቅዱስ ያሬድም “ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ ጌታቸው በብብትሽ /በክንድሽ/ ተቀምጦ እንደ ሕፃን ጡትሽን ሲጠባ መላእክት ባዩት ጊዜ በአርያም ፈለጉትና በዚህ ዓለም እንደ ቀድሞው ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አገኙት” ብሎ አመስጥሮታል፡፡ ፀሐይ ባለችበት ሆና ምድርን እንደምታሞቅ እርሱም በዙፋኑ ተቀምጦ /ዓለምን እየገዛ/ በምድር በሥጋ ማርያም ተገለጠ፡፡ ሥጋን ተዋሕዶ ዞሮ አስተማረ” /አንቀጸ ብርሃን ዘቅዱስ ያሬድ/

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ እኛን ያዳነበት ጥበቡ በልባችን ስናስበው በአንደበታችን ስንናገረው ምስጢሩ ድንቅ በመሆኑ ሐዋርያው ይህ ምስጢር ያለጥርጥር ታላቅ ነው ይላል፡፡ ነቢዩ ሙሴም የእግዚአብሔር ሥራ ግሩም በመሆኑ አምነን ከመቀበል ውጭ መርምረን መድረስ ስለማንችል “ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው” ዘዳ.29፥29 እንድንል ያስታውሰናል፡፡

ሎቱ ስብሐት ለዘበስብሐተ አቡሁ ይሴባሕ ወሎቱ ቅድሳት ለዘበቅድሳተ መንፈሱ ይትቄደስ ለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን፡፡በአባቱ ምስጋና ለሚመሰገን ለእርሱ ምስጋና ይገባል፡፡ በመንፈሱ ቅድስና ለሚቀደስ ለእርሱ ምስጋና ይገባል ለዘለዓለሙ አሜን፡፡