eresha be 3

የበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የልማት ሥራ ተጎበኘ

ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

eresha be 3በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል ሥራ አሥፈጻሚ አባላትን ያቀፈ የልዑካን ቡድን በበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን እየተከናወነ የሚገኘውን የልማት ሥራ ለመመልከትና ከደብሩ አስተዳደር አካላት ጋር ለመወያየት ኅዳር 23 ቀን 2005 ዓ.ም. ጉብኝት አካሄደ፡፡

 

የአዲስ አበባ ማእከል ከበኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ ጋር ባደረገው የውል ሥምምነትeresha be 2 መሠረት በባለሙያ አስጠንቶ ዘመናዊ የግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተያዘው እቅድ መሠረት እሰካሁን ከተከናወኑት ውስጥ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኑ ይዞታ በሆነው 3 ሄክታር መሬት ላይ የተዘራው የጤፍ እርሻ የሚገኝበትን መቃኘት የመጀመሪያው የጉብኝቱ አካል ነበር፡፡

 

የጤፉ እርሻ ለዓይን ይማርካል፡፡ ከ250 አስከ 300 ካሬ ሜትር የሚሆነው ከሌላው ማሳ ለየት ባለ ሁኔታ በቁመትም፤ ሆነ በያዘው የፍሬ መጠን ከፍተኛነት ይለያል፡፡ ለአጨዳ የደረሰ በሚመስል መልኩ ወደ ቢጫነት አዘንብሏል፡፡ ቀሪውም ባማረ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል፡፡ ከፍተኛ ክትትል እንደተደረገበትም ያመለክታል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ገብረ አማኑኤል ቦታው ጠፍ የነበረና የከብቶች መዋያ ሆኖ መቆየቱንና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከማኅበረ ቅዱሳን አዲስ አበባ ማዕከል ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በባለሙያ ተጠንቶና ታርሶ ፍሬ ለማየት እንደበቁ የገለጹ ሲሆን ወደፊትም ተደጋግፎ የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደተዘጋጁ በጉብኝቱ ላይ ተናግረዋል፡፡

 

“በእርሻ ሥራው ላይ የደብሩ ካህናት የንስሐ ልጆቻቸውን በማስተባበር፤ ለዘር የሚሆን ጤፍ በማቅረብ፤ በጉልጓሎና ዘር በሚዘራበት ውቅት ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በማሰማራት፤ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በመማር ላይ የሚገኙ ከ200 በላይ የአብነት ተማሪዎች፤ የደብሩ አስተዳደር፤ ካህናትና ዲያቆናት ተሳትፈውበታል፡፡ ምርቱም በመማር ላይ ለሚገኙት የአብነት ተማሪዎች የምግብ ፍጆታነት ይውላል” በማለት የገለጹት ደግሞ የቀድሞው የቤተ ክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ከፍያለው አየለ ናቸው፡፡

 

eresha be“የግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብሮችን ለመጠቀም ጥረት አድርገናል፡፡ ለማስተማር የፈለግነው የአካባቢው አርሶ አደሮችና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን በጎ ተሞክሮዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ ነው፡፡ በበሬ ብቻ ሳይሆን በትራክተር እንዲታረስም አድርገናል፡፡ ከ3 ሄክታር መሬቱ ላይ ከ250 እሰከ 300 ካሬ ሜትሩ ለሙከራ ምርጥ ዘር ተጠቅመናል፡፡ የትኛው የተሻለ እንደሆነ ለሁሉም ለማሳየት የቻልንበት ነው፡፡ ገና ሳይታጨድ ልዩነቱም ጎልቶ ይታያል፡፡ በሚቀጥለው አመትም ጤፍ በመሥመር መዝራትን ተግባራዊ የምናደርግበት ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ምእመናን የቤተ ክርስቲያናችንን ተሞክሮ ተመልክተው እነሱም እንዲጠቀሙበት ለማስተማር ነው፡፡” በማለት ወይዘሪት መቅደስ አለሙ በአዲስ አበባ ማእከል የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ክፍል ሰብሳቢ በጉብኝቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

 

በቀጣይነት የተካሄደው አብነት ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ሁኔታ ለመቃኘት የተደረገ ጉብኝት ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱ በ3 መምህራን ከ200 በላይ ተማሪዎችን በማቀፍ የአቋቋም፤ የቅኔ፤ እንዲሁም የቅዳሴ ትምህርቶች የሚሰጥበት ተቋም ነው፡፡

 

በሁለት አዳራሾች ውስጥ መኝታቸውን ያደረጉት የአብነት ተማሪዎቹ የመኝታቸው ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው፤ አልጋቸው በርብራብ እንጨትeresha be 4 የተዘጋጁ ናቸው፤ የሳር ፍራሽና ካርቱን አንጥፈውበታል፡፡ አንዱን ከአንዱ ለመለየት በማዳበሪያ ተከፋፍሏል፤ በአንዱ አዳራሽ ውስጥ አዳራቸውን የሚያደርጉት ተማሪዎች ብዛት ከአንድ መቶ ይበልጣል፡፡ አዳራሹ ውስጥ እሳት ቢነሣ ወይም በሽታ ቢገባ የሚተርፍ ያለ አይመስልም፡፡ አንድ የማብሰያ ክፍል ሲኖር ሁሉንም ማስተናገድ ስለማይችል የተወሰኑት ተማሪዎች ውጪ ሜዳው ላይ ምግባቸውን ለማብሰል ይገደዳሉ፡፡

 

የቤተ ክተርስቲያኑ አስተዳደር ጉባኤ ያለውን ችግር በመረዳት ለሰንዳፋ በኬ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከል፤ በቅደም ተከተልም ለአዲስ አበባና ለዋናው ማእከል የችግሩ አሳሳቢነት በማሳወቅ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱ መሠረት የአብነት ትምህርት ቤቱን ለማደራጀትና ለማጠናከር ፤ ተማሪዎቹም ተምረው የነገዎቹ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሆኑ ለማስልቻል ጥረት በመደረግ ላይ  ይገኛል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ከፍተኛ በጀት በመመደብ የአብነት ትምህርት ቤቱን ዘመናዊ ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ግንባታውንም በዚህ ዓመት ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በጉብኝቱ ላይ ተገልጧል፡፡

 

በመጨረሻም በጋራ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሁሉም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ገብረ አማኑኤል ጥሪያቸውን ያስተላለፉ ሲሆን በልማት ሥራው ላይ ለተሣተፉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የሰንዳፋ ወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎች፤ የደብሩ አስተዳደር፤ ካህናትና ዲያቆናት፤ የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት፤ የማኅበረ ቅዱሳን የሰንዳፋ ማእከል ሓላፊዎችና አባላት፤ ጥሪ የተደረገላቸው የአጥቢያው ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

በኬ ደብረ ምሕረት ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1860ዎቹ ውስጥ እንደ ተተከለ ይነገራል፡፡

mkmesfin1

የማዕረግ ተመራቂው የወርቅ ሜዳልያውን ለማኅበሩ አበረከተ

29/03/2005ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ደብረ ዘይት በሚገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንስሳት ህክምናና ግብርና ኮሌጅ በ2004 ዓ.ም. የተመረቀው ዶክተር መስፍን ማሞ በአጠቃላይ ውጤት (GPA) 3.98  እጅግ በጣም ከፍተኛ ማዕረግ በማምጣት ተመርቋል፡፡ ኮሌጁም ላስመዘገበው ውጤት Outstanding Student Of The Year 2012 College Of Veternary & Agriculture በማለት ኮሌጁ በበላይነት ላጠናቀቁ ተማሪዎች የሚሰጠውን የወርቅ ሜዳልያ ሽልማት አበርክቶለታል፡፡

mkmesfin1

ዶክተር መስፍን ማሞ ይህንን ሽልማት በመያዝ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል በመምጣት “በትምህርቴ ባስመዘገብኩት ውጤት ያገኘሁት ሽልማት ነው፡፡ ለኔ አይገባኝም፡፡” በማለት ለማኅበሩ እንደሚሰጥ አሳወቀ፡፡

 

በርክክቡ ላይ ከኮሌጁ የተሸለመውን  የወርቅ ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን  ለምን መሥጠት እንደፈለገ ዶክተር መስፍን ማሞ ሲገልጽ “ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ በሀገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም ከፍተኛ አገልግሎት እያበረከተ ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በማስተዋወቅና ምዕመናንን በማስተማር እያበረከተ ላለው ጥረት ከፍተኛ አክብሮት አለኝ፡፡ በግቢ ጉባኤ አማካይነት በሥነ ምግባር የታነጸና የዓላማ ሠው እንድሆን ማኅበሩ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልኛልና ያለኝን ታላቅ አክብሮት ለመግለጽ ስል ይህንን ከኮሌጁ የተሸለምኩትን የወርቅ ሜዳልያ ሰጥቻለሁ” ብሏል፡፡

mkmesfin2የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ ዲያቆን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም የወርቅ ሜዳልያውን በተረከቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት  “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በግቢ ጉባኤያት ቆይታቸው በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተሸለሙትን ሜዳልያ ለማኅበሩ ሲያበረክቱ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

 

ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ከመደበኛው ትምህርታቸው ውጪ ጊዜያቸውን በፕሮግራምና  በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ለውጤት መብቃት እንደሚችሉ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው፡፡ ሽልማቱ ለማኅበራችን እንዲሁም ለቤተ ክርስቲናችን ታላቅ ኩራት ነው፡፡” በማለት የገለጹ ሲሆን ዶክተር መስፍን ማሞ ላደረጉት አርአያነት ያለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

ከዚህ ቀደም ከጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁት ዲያቆን ዶክተር እንግዳ አበበ የተሸለሙትን የወርቅ ሜዳልያ ለማኅበረ ቅዱሳን በሥጦታ እንዳበረከቱ ይታወቃል፡፡

nebabe 2 1

የንባብ ባሕልን ለማሳደግ ውይይት ተካሄደ

ኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


የንባብ ባሕልን በማሳደግ በመረጃና በእውቀት የበለጸገ ማኅበረሰብ እንፍጠር በሚል ርዕስ የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከልnebabe 2 1 ያዘጋጀው የውይይት መድረክ  ኅዳር 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ስዓት ላይ በማኅበሩ ሕንፃ ላይ ተካሄደ፡፡

 

ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ በመርሐ ግብሩ ላይ ለተገኙት እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን የውይይት መድረኩ የተዘጋጀበትን ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹም “በሀገራችን ብሎም በቤተ ክርስቲያናችን በጣም በአሳሳቢ ሁኔታ እየቀነሰ የመጣውን የንባብ ባሕል ለማሳደግ እንዲቻል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው፡፡ የማያነብ ትውልድ አዲስ ነገር መፍጠር አይችልም፤ አዲስ ነገርንም ለመቀበል ያስቸግረዋል፡፡ የንባብ ባሕላችን ምን ላይ እንደሚገኝ፤ ያጋጠሙ ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሔዎች ላይ ለመወያትና እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን በእውቀትና በመረጃ ከማነፅና ከመቅረፅ አንጻር ሊኖራት የሚገባት ሚና ምን መሆን እንዳለበት ለማመላከት ነው፡፡” ብለዋል፡፡

 

nebabe 3የውይይት መድረኩ በአቶ ወንድወሰን አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል መምህር የተመራ ሲሆን ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ለውይይት መድረኩ መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ጽሑፍም “ሥነ ፍጥረት የሚነበብ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ለፍጥረቱ የሰጠው ትልቁ ሥጦታ  ነው፡፡” በማለት የጥናት ጽሑፋቸውን በመጀመር በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጻሕፍት የተነገሩትን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል” በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ፀኑ፤ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስብ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው” መዝ.86፤6 “በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም አፌ አዟልና” (ኢሳይያስ 34፤16) በማለት ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ከቅዱሳን አበው መካከል “ቅዱሳት መጻሕፍትን አለማወቅ የስህተት ሁሉ ምንጭ ነው” በማለት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከተናገረው በመነሣት የቅዱሳት መጻሕፍት ጠቀሜታን  አብራርተዋል፡፡

 

መጻሕፍትን የማንበብ ፋይዳን አስመልክቶም ተጠቃሽ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች አንሥተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፤ መጻሕፍት በዘመናት ሂደት የተከማቹ የሰው ልጆች የእውቀት መዛግብት የሚተላለፍባቸው መንገዶች መሆናቸው፤ መጻሕፍት ጓደኛ ስለመሆናቸው፤ መጻሕፍት የመንፈስ ምግቦች መሆናቸው፤ መጻሕፍት አንድን ርዕሰ ጉዳይ ወጥና ምሉዕ በሆነ ሁኔታ ለመዳሰስ ያስችላሉ፤ መጻሕፍት ተጠቃሽ /Quatable/ ናቸው፤ መጻሕፍት በተሳሳተ መንገድ መጥቀስም መጠቀስም ባያስቀሩም ስህተቶችን ይቀንሳሉ፤ መጻሕፍት ትውልድን ይሻገራሉ በማለት የመጻሕፍትን ፋይዳ በዝርዝር ዳስሰዋል፡፡

 

ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የንባብ ልምድ በኢትዮጵያ አስመልክቶ ባቀረቡት ትንተናም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናቶች በጥልቀት ያለመሠራታቸውና አንድ ጥናት አቶ አለም እሸቱ የተባሉ ተመራማሪ  ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በጥናታቸውም መሠረት በ220 ሰዎች ላይ ለናሙና ያህል በቀረበ መጠይቅ ለምን መጻሕፍትን እንደማያነቡ በሰጡት ምላሽ “ላይኔ ስለምፈራ አላነብም፤ ሳነብ አይገባኝም፤ ምክንያቱን አላውቅም፤ የአውሮፓ እግር ኳስ እያለ እንዴት አነባለሁ፤ ትላልቅ መጻሕፍትን ሳይ ተስፋ ያስቆርጡኛል፤ ከቤተሰብ አልለመድኩም፤ ሴት ልጅ ቤት ውሰጥ ቁጭ ብላ ቤተሰብን ማገዝ እንጂ ለማንበብ አይፈቀድላትም ፤. . . የሚሉ ምላሾችን መስጠታቸው ንባብ በኢትዮጵያ ውስጥ አለማደጉን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

በጥናታቸው ማጠቃለያም የንባብ ባሕልን ለማሳደግ መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውንም ጠቁመዋል፡፡ የንባብ ፍላጎት እንዲኖር ማድረግ፤ ከሕፃንነት ጀምሮ የማንበብ ፍቅርና ልምድ እንዲኖር ማድረግ፤ የመጻሕፍት ስብስብና ክምችት መፍጠር እንደ መፍትሔ ካቀረቧቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

 

nebabe 2 2ጥናቱ ከቀረበ በኋላም በንባብ ባሕል ላይ ያተኮረ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የዩኒቨርስቲ ምሁራንና ተማሪዎች እንዲሁም ተሳታፊዎች አስተያየቶቻቸውንና የመፍትሔ አሳቦቻቸውን አቅርበዋል፡፡ በአብዛኛው ከተጠቀሱት ውስጥም የንባብ ባሕላችንን ለማሳደግ በዋነኛነት ቤተሰብና ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ሓላፊነት እንዳለባቸው ፤ ልጆች ከሕፃንነት ጀምሮ ንባብን ባሕል አድርገው እንዲያድጉ ከፍተኛ ሥራ መሠራት እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን አንባቢ ትውልድን ለመፍጥር በሚያደርገው አገልግሎት ውስጥ መጻሕፍትን የማሰባሰብ፤ ቤተ መጻሕፍቱን በዘመናዊ መልክ የማደራጀት ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝና  በአሁኑ ወቅት ቤተ መጻሕፍቱ ከሁለት ሺህ የማይበልጡ መጻሕፍትን ብቻ አሰባስቦ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፤ በዐራት ዓመታት ውስጥም የመጻሕፍቱን ቁጥር ሃምሳ ሺህ ለማድረስ መታቀዱን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር ዲያቆን ዮሐንስ አድገ የገለጹ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ምሁራንና ምእመናን አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

 

በውይይቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ እንዲሁም ተማሪዎችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለማሳካት የገዳማት ድርሻ!!

  • የወርቃማው ዘመን ወርቃማ ደራሲ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የገድል መጽሐፍ  ይመረቃል

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ጥንታውያን ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለማጠናከር ላለፉት 10 ዓመታት ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ከምዕመናን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡

 

ማኅበሩ ይህንን አገልግሎት አጠናክሮ ለመቀጠል ከ50 ጥንታውያን ገዳማት የተውጣጡ አበምኔቶች በተገኙበት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮ ለማሳካት ገዳማት ያላቸው ድርሻ ”  በሚል መሪ ቃል ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል በተቀናጀ ልማት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡

 

እርስዎም በዕለቱ ተገኝተው የመርሐ ግብሩ ተሳታፊ በመሆን የአባቶችን ቡራኬ በመቀበል ድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ በአክብሮት ተጋብዘዋል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

አድራሻ ፡- ስድስት ኪሎ ከምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ከፍ ብሎ በኢትዮጵያ ስብሰባ ማዕከል
አዘጋጅ ፡-የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል