ውጤታማ ለመሆን በውይይት ማመን

መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም


የአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ ፓትርያርኩ ዐርፈው መንበረ ፕትርክናው ባዶ መኾኑ ከተረጋገጠበት ዕለት ጀምሮ መንበሩን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይበቃል ያለውን አካል የመሾም፤ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የማስቀጠል ሓላፊነት የተጣለበት ቅዱስ ሲኖዶስ አምስት ዋና ዋና ተግባራትን ፈጽሟል፡፡

 

የመጀመሪያው ፓትርያርኩ ማረፋቸው እንደተሰማና እንደተረጋገጠ በፓትርያርኩ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የሰበሰበቻቸውን ሀብታት በአግባቡ እንዲጠብቁ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ፓትርያርኩ ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ዐርፈው በዕለቱ ወደ 7፡30 አካባቢ ይኖሩበትና በቢሮነት ይገለገሉባቸው የነበሩትን ቤቶች አሽጓል፡፡ ሁለተኛው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት መንበረ ፕትርክናውን የሚጠብቅ፤ ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ ሲኖዶሱን በበላይነት የሚመራ፣ /ህየንተ ፓትርያርክ/ ኾኖ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር የሚመራ ዐቃቤ መንበር መምረጥነው፡፡ በዚሁም ነሐሴ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ከያዙት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስና በተጨማሪ ዐቃቤ መንበር ኾነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡

 

ሦስተኛው /በይፋ የተገለጠ ነገር ባይኖርም/ ከወቅቱ ቋሚ ሲኖዶስ ጋር ቀጣዩ ፓትርያርክ ከመመረጡ በፊት ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራት የቤተ ክርስቲያኗን ሁሉን ዐቀፍ አስተዳደራዊ ፈርጆች አጥንቶ የሚታረመውን አርሞ የሌለውን አዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉባኤ የሚያቀርብ ሰባት አባላት ያሉት የሊቃነ ጳጳሳት ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ መምረጡ ነው፡፡ ዐራተኛው የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት ለክብራቸውም በሚገባ መልኩ እንዲፈጸም ማድረጉ ነው፡፡ አምስተኛው እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኗ መልካም መሪ ይሰጥ ዘንድ የጸሎት ዐዋጅ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማወጅ ነው፡፡

 

ከላይ ያየናቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ ተግባራት አፈጻጸማቸው በይፋ የታየ መግለጫም የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ ምን እየሠራ እንዳለ እየተሰጠ ያለ መግለጫ የለም፡፡ ይህ ጽሑፍ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አመራረጥ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሊሔድበት የሚገባውን መስመር በአጭሩና በመጠኑ ይጠቁማል፡፡

 

1. መቅደም ያለበትን ማስቀደም፡- ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ጥሩ ተጓዘች፣ በአንጻሩም ቢኾን ኢኮኖሚዋ አደገ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት የሚገሠግሠው ምእመን ቁጥር ጨመረ ቢባልም ሒደቱን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተ፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለዘመናት አስከብረው ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ አድርገው ያቆዩዋት ዕሴቶቿን ክፉኛ ሲገዳደር የቆየ አንድ መሠረታዊ ችግር አለ፡፡ ይኸውም የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ እንዲከፋፈል ያደረገና በአባቶች መካከል የተከሠተ የመለያየት ችግር ነው፡፡ ይህ ልዩነት ለሃያ ዓመታት ምእመኑን ሲያደናግር የኖረ፣ በሁለቱ ጎራ ያሉ አባቶችም እርስ በርስ ተወጋግዘው ቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ አልባ እንድትመስል አድርጎ ያቆየ፣ ለብዙ ሥጋውያን ሰዎች ዓላማ ማስፈጸሚያነትም ሲያገለግል የኖረ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በዚያ መጠላለፍና አልሸነፍ ባይነት – ስትናጥበት ከቆየችበት ችግር የምትላቀቅበት መልካም አጋጣሚ ላይ ትገኛለች፡፡ በመኾኑም ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራ ዘንድ የተሰየመው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ለሃያ ዓመት የዘለቀ ልዩነት አጥብቦ ቤተ ክርስቲያኗን ወደ ቀደመ የአንድነት ጉዞዋ መመለስ አለበት፡፡ ይህን ሲያደርግም የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊያጤን ይገባል፡፡

 

ሀ. የችግሩን መንሥኤ ከመሠረቱ ማጥናት፡- ከላይ የገለጽነው የመከፋፈል ችግር የብዙ ትንንሽ ችግሮች ውጤት ነው፡፡ ዝርዝራቸውን ትተን መገለጫቸውን ብናይ ፖለቲካዊ ዓላማ፣ ሀብት የማካበት ዓላማ፣ የግል ክብርና ምቾት ፍለጋ ዓላማና ቤተ ክርስቲያኗን በኑፋቄ የማወክል ዓላማ ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች በየግላቸው ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት መጠናቸው ቢለያይም በሁለቱም ጎራዎች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ልዩነቱን በመጠቀም ዓላማዎቻቸውን ሲያሳኩና ለማሳካት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በመኾኑም በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች ቤተ ክርስቲያኗ የምትናፍቀውን ሰላም አስፍነው በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር ደገኛ ተግባር ለመፈጸም፤ የችግሩን ምንጮች አጥንተው በመለየት እነዚህን አካላት በምክርም በተግሣጽም ማረም ወይም መለየት ይገባቸዋል፡፡

 

ለ. የዕርቁን አስፈጻሚዎች በጥንቃቄ መምረጥ፡- በአባቶች መለያየት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ ከተከፈለችበት ጊዜ አንሥቶ በኦፊሴል ያልተገለጹትን ጨምሮ ሁለቱንም አካላት በመወከል በሚቀመጡ አባቶች አማካኝነት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ድካሞቹ ሁሉ ውጤት አላመጡም፡፡ ለዚህ ከሚሰጡት ምክንያቶች አንዱ የሚወከሉት አባቶች ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ በኩል የማስፈጸም ብቃት ማነስ ወይም ለማስፈጸም ጠንክሮ አለመሥራት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መካከል የሚከሠትን ችግር ለመፍታት ምድራዊ ጥበብና ቀመር ቦታ የላቸውም፡፡ «እንዲህ ቢባል እንዲህ በሉ» የሚለው ቅደመ ውትወታም አያስፈልግም፡፡ «እንዲህ ብል እከሌ ምን ይላል?» ወይም «የምናገረውን እከሌን ልጠይቅ» የሚሉት ደካማ አስተሳሰቦችም ሊኖሩ አይገባም፡፡በመኾኑም በቀጣይ ይህንን ሁሉም የሚናፍቀውን አንድነት እውን ለማድረግ ከሁለቱም ወገን የሚመረጡት አባቶች እውነትንና አንድነትን በማስቀደም ራሳቸውን ኾነው የሚወያዩ መኾን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በሁለቱም በኩል ያሉት አባቶች ይወክሏቸው ዘንድ በሚመርጧቸው ሰዎች  ብቃት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

 

ሐ.  የዕርቅ ውይይቱ በሁሉም አካላት በኩል እንዲጀመር ማድረግ፡- ይህ ችግር እንዲፈታ በማድረግ ሥልጣንና ሓላፊነት ያላቸው በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች እንደ ኾኑ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሃያ ዓመታት መሠረታዊው የአባቶች ልዩነት ያቆሰላቸው በርካታ አካላት በሁለቱም በኩል በየደረጃው አሉ፡፡ እነሱም በሁለቱም በኩል ያሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን አባቶች በዕርቅ ከተዋሐዱ እነዚህ አካላት አሻፈረኝ ብለው እንደተለያዩ ይቀራሉ ባይባልም የእነሱም መወያየት ዕርቁን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ የአባቶችን መዋሐድ የማይፈልጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችንም ለመለየት ያግዛል፡፡

 

2.    በቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ላይ በጥብዓትና በግልጽ መወያየት መጀመር፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ችግር ገዝፎ ይታይ የነበረው በኢትዮጵያና በአሜሪካ አብያተ ክህነት መካከል ብቻ አልነበረም፡፡ እዚህ አዲስ አበባም በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክህነቱ አስተዳደርና በቅዱስ ሲኖዶሱ አመራር ላይም ችግሮች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹ ገዝፈው የቤተ ክርስቲያኗን ምልዐት እስከ ማወክና ምእመኑን ወደ ቀቢጸ ተስፋ እስከ መክተትም ደርሰው ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የማይስማሟት ዘረኝነት፣ ሙስናና አድሎአዊነት በይፋ ታይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና አገልግሎት የሚጠበቀውን ያህል ዘመናዊ አልሆነም፡፡ አህጉረ ስብከት በልማት አገልግሎት መጓዝ ያለባቸውን ያህል አልተጓዙም፡፡ ለዚህ ሁሉ በብዙዎች እንደ ምክንያት ይጠቀስ የነበረው የቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተዳደርና የአመራር ችግር ነው፡፡ አከራካሪ ነው፡፡ የኾነው ኾኖ አሁን ይህ ምክንያት በዜማነት የሚነሣበት ጊዜ አልፏል፡፡ ለሃያ ዓመታት በምክንያትነት ሲነሡ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርክ የሉም፡፡ እንደ ሥራቸው ወደሚከፍላቸው አምላክ ሔደዋል፡፡ ስለዚህ የሲኖዶሱ አባላት ሌላ ምክንያት ፈጥሮ የሚቀጥሉትን ሃያ ዓመታትም ተመሳሳይ ዜማ ሲያዜሙ ላለመኖር በመንበረ ፕትርክናው ስለሚያስቀምጡት አባትና ስለሚቀመጥበት አግባብ እንዲሁም ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ አስተዳደራዊ መልክእ መወያየትና ቀጥተኛ መስመር ማስቀመጥ አለባቸው፡፡

 

3.    ችግሮችን አጥንተው ለውሳኔ የሚያቀርቡ ልዩ ልዩ ጉባኤያትን ማቋቋም፡- ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር በበላይነት የሚመራ፣ በባለሞያዎች ተጠንቶ በሚቀርብለት መሠረታዊ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ነው፡፡ ይህ እንዲኾን ደግሞ አስፈላጊውን አቅጣጫ ለአስፈጻሚው አካል መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ ማድረግ ያለበት የቤቱን መሠረታዊ ችግሮች ሙያዊ በኾነ መንገድ አጥንተው ከነመፍትሔ ሐሳባቸው  የሚያቀርቡ የባለሞያዎች ቡድኖችን ማቋቋም ነው፡፡ ቡድኖቹም በተወሰነላቸው ጊዜ የቤተ ክርስቲያኗን መሠረታዊ ችግሮች ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋር እንዲያቀርቡለት መመሪያና ትእዛዝ መስጠት፣ ለሥራቸው ቅልጥፍናም አስፈላጊው ሎጂስቲክስ እንዲሟላላቸው ማድረግ  ይጠበቅበታል፡፡ የቀደመ አገልግሎቷን ለማስቀጠል 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ሙያዊና አስተዳደርንና አሠራርን መከተል ይጠበቅባታል፡፡ ለዚያ ደግሞ አሁን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ኖርበታል፡፡ አሁን በሚታየው ሁኔታ ሦስት የባለሙያዎች ቡድኖች እንዲቋቋሙ ግድ ይላል፡፡ እነዚህም የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ጥናት ቡድን፣ የሰው ኃይል ጥናት ቡድንና የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና አሠራር ጥናት ቡድን ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች በየተሰጧቸው አርእስት ያሉትን ጉዳዮች ፈትሸው ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የመፍትሔ ሐሳቦችንና የአሠራር መንገዶችን አጥንተው ያቀርባሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በሚቀርቡለት ሰነዶች ዙሪያ ተወያይቶ ይወስናል፡፡

4.    ጣልቃ ገብነትን በጥንቃቄ መከታተል፡- የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች የሚመነጩት ከውስጥም ከውጭም ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲነሡ የቆዩትና በመነሣት ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ሙሉ በሙሉ በውስጧ ባሉ አካላት /ምእመናን፣ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣/ ድካም ብቻ የመጡ አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ዐውቃም ይሁን ሳታውቅ በገቡባት ባዕዳን እጆች የተነሣ  ችግር ላይ ስትወድቅ ቆይታለች፡፡ እነዚህ የባዕዳን እጆች አሁንም በቤተ ክህነታችን አሠራር ድርሻ እንዲኖራቸው መፈቀድ የለበትም፡፡ ስለዚህ አሁን ሁሉም ዐይኑን አፍጥጦ እንዲኾን የሚጠብቀው ሒደት ከየትኛውም ውጫዊ አካል ተፅዕኖ በጸዳ መልኩ እንዲኾን ሓላፊነት ያለበት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኗ በመስቀለኛ መንገድ ላይ በቆመችበት ሰዓት ወደደጉ የመምራት ሓላፊነት ያለባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛ ድርሻ አለባቸው፡፡ እነሱ ከየትኛውም ጫና ነጻ በኾነ መልኩ እንዲመሩ ደግሞ የሚመለከተን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችን በምንችለው ሁሉ ልናግዛቸው ያስፈልጋል፡፡

 

5. በቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ ጉዞ ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት በየደረጃው እንዲወያዩ ቢደረግ፡- ወቅቱ ሁሉም የቤተ ክርሰቲያኗ አካላት ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ ጉዞ ስለ መሪዎቿና አመራር ሥልታቸው፣ ስለ አገልግሎቷና አገልጋዮቿ ብቃት በስፋት መወያየት ያለባቸው ጊዜ ነው፡፡ በዘርፉ ምሁራን በቃልም በመጻፍም እንደሚገለጠው ዘመናዊ አመራር የጋርዮሽ ተግባር ነው፡፡ ይህ አባባል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ተግባራዊነቱ ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም አካላት እየተወያዩ ለቤተ ክርስቲያኗ ይበጃሉ የሚባሉ ሐሳቦችን ወደ ዋናው ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲልኩ ሲኾን ነው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ ለውይይቱና ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መቃናትና ቀጥተኛነት እሱ የሚመራቸው አካላት /የቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወዘተ/ በየመልኩ እንዲወያዩ አቅጣጫ መስጠት አለበት፡፡ እነዚህ አካላትም የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት ግብዣ በመቀበል ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

 

ስናጠቃልል፡- በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ የምዕራፉ ወሳኝነትም ቤተ ክርስቲያኗ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድታ ወደ ፊት የምትራመድበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ በጥንቃቄ መራመድ ያለባት ጊዜ ላይ በመኾኗ ነው፡፡ ጥንቃቄው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ለመምራት እግዚአብሔር መርጦ ያስቀመጣቸው አባቶች ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የወለደቻቸው ልጆቿ ሁሉ ለእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ መልካም ጉዞ በሚችሉት ሁሉ መወያየት ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ሁሉ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ይሰምር ዘንድ ደግሞ የእኔ ሐሳብ ብቻ ተቀባይ ይሁን ከሚል መገዳደር ርቆ ሁሉንም በፍቅር ማድረግና የፍቅር አምላክ የመሠረተልንን ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ልንኖርባት ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተ መሥርቶም ያጸና አምላክ ደጉን ሁሉ ያድርግልን፡፡

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን