niqodimos_

ኒቆዲሞስ/ለሕፃናት/

መጋቢት 21 2004ዓ.ም

በቴዎድሮስ እሸቱ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? መልካም ይኸው ዘወረደ ብለን በመጀመሪያው ሳምንት የጀመርነው ጾም ዛሬ ኒቆዲሞስ ላይ ደርሷል፡፡ ኒቆዲሞስ የ7ኛው ሳምንት መጠሪያ ነው፡፡

niqodimos_

ልጆች የአይሁድ መምህር የሆነ አንድ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ነበር፡፡ ይህ የአይሁድ መምህር ማታ ማታ እየመጣ ከክርስቶስ እግር ስር ቁጭ ብሎ ትምህርት ይማር ነበር፡፡ ልጆች ማታ ማታ እየመጣ የሚማረው ለምን መሰላችሁ፡፡

 

አንደኛ የአይሁድ መምህር ስለሆነ ሲማር እንዳያዩት ነው፡፡ ሲማር ካዩት ገና ሳይማር ነው እንዴ የሚያስተምረን እንዳይሉት፡፡ ሁለተኛ አይሁድ ክርስቶስን ያመነና የተከተለ ከሀገራችን /ከምኲራባችን/ ይባረራል ብለው ስለነበር እንዳይባረር ፈርቶ ሦስተኛ ደግሞ ሌሊት ሲማሩ ምንም የሚረብሽና ዐሳብን የሚሰርቅ ነገር ስለሌለ ትምህርት በደንብ ይበገባል ብሎ በማሰብ ነው፡፡ እናንተስ በሌሊት ትምህርታችሁን የምታጠኑት እንዲገባችሁ አይደል ልጆች? በሌሊት ዐሳባችሁ አይበተንም፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ማታ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ስለ ጥምቀት አስተማረው፡፡ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊወርስ አይችልም” አለው፡፡ ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ ካረጀ በኋላ እንዴት ድጋሚ ሊወለድ ይችላል” ብሎ ጠየቀ ክርስቶስ ዳግም ልደት ማለት ሰው በጥምቀት የሚያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት እንደሆነ ሰው ተጠምቆ የእግዚአብሔር ልጅ ካልሆነ መንግሥተ ሰማያትን እንደማይወርስ አስተማረው፡፡ ኒቆዲሞስም ስለ ጥምቀት በሚገባ ተረዳ፡፡

አያችሁ ልጆች እንግዲህ በዚህ ሳምንት ከሚነገረው ታሪክ በርካታ ቁም ነገሮችን እናገኛለን ለምሳሌ እኛ ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል ቀን ከሌሊት ሳንል ሁል ጊዜ መማር እንዳለብን፤ ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጠይቀን መረዳት እንዳለብን ነው፡፡ እንደዚህ በማድረግ ስለ እምነታችን በቂ እውቀት ልንጨብጥ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ለዛሬ አበቃሁ ደህና ሰንብቱ፡፡

የዐብይ ጾም ስብከት /ክፍል 6/

መጋቢት 20/2004 ዓ.ም.

በአያሌው ዘኢየሱስ

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

 

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ውስጥ የምናነበው ወንጌል የሚያሳስበን ስለ በጎና ታማኝ አገልጋይ የተነገረውን ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ የወንጌል ንባብ ውስጥ ጌታ በምሳሌ አድርጎ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ሰዎች እንደ ሥራቸው እንደሚዳኙ በሰፊው አስተምሯል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ አንድ ጌታ ለሦስት ባሮቹ ለእያንዳንዳቸው እንደ አቅማቸው ለአንዱ አምስት መክሊት፣ ለአንዱ ሁለት መክሊትና ለሌላው ደግሞ አንድ መክሊት ከሰጣቸው በኋላ ነግዱና አትርፉ በማለት እርሱ ወደ ሌላ አገር መሄዱ ተገልጦአል፡፡ በዚህም መሠረት አምስት መክሊት የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በተሰጠው አምስት መክሊት ቆላ ወርዶ ደጋ ወጥቶ ከነገደ በኋላ አምስት ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ አኖረ፡፡ ሁለት መክሊቶችን የተቀበለው ሁለተኛው ባሪያም በተሰጡት አምስት መክሊቶች ከነገደ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አስቀመጠ፡፡ ሦስተኛው ባሪያ ግን ከእነዚህ ሁለት ባሪያዎች በተለየ ሳይወጣና ሳይወርድ፣ ሳይደክምና ሳያተርፍ በአቅሙ መጠን በተሰጠው አንድ መክሊት ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ ወስዶ ጉድጓድ በመቆፈር ቀበረው፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ለእነዚህ ሦስት ባሪያዎች በመጠን የተለያዩ መክሊቶችን ሰጥቶ ወደ ሩቅ አገር ሄዶ የነበረው ጌታቸው ወደ እነርሱ ተመልሶ መጣ፡፡ ከዚያም እያንዳንዳቸው በየተራ ወደ እርሱ እያስገባ በተሰጧቸው መከሊቶች ምን እንደሠሩ ይጠይቃቸውም ይቆጣጠራቸውም ጀመር፡፡ በዚህ መሠረት አምስት መክሊቶችን የተቀበለው የመጀመሪያው ባሪያ በጌታው ፊት ቀርቦ በተሰጡት አምስት መክሊቶች ሌሎች ተጨማሪ መክሊቶችን በማትረፍ በድምሩ አሥር መክሊቶችን ለጌታው አስረከበ፡፡ ሁለተኛውም እንዲሁ በተሰጡት ሁለት መክሊቶች ሌሎች ሁለት መክሊቶችን አትርፎ አሁን በእጁ ላይ ያሉትን አራት መክሊቶች ለጌታው አስረከበ፡፡ በዚህ ጊዜ የእነዚህ ሁለት ባሪያዎች ጌታ በእነርሱ ደስ በመሰኘት ለሁለቱም አንተ መልካም፣ በጎና ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ ስለምሾምህ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ በማለት ወደ መንግሥቱ አስገባቸው፡፡

ምንም ሥራ ሳይሠራና ሳያተርፍ የተሰጠውን አንድ መክሊት ጉድጓድ ውስጥ የቀበረው ሦስተኛው ባሪያ ግን ባዶ እጁን መቅረቡ ሳያንሰው በድፍረት ጌታ ሆይ፡- ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ስለማውቅና ስለ ፈራሁ መክሊትህን ጉድጓድ ቆፍሬ በመቅበር አቆይቼልሃለሁና እነሆ ተረከበኝ የሚል መልስ ሰጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ስለ ተቆጣ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፤በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ሰው መሆኔን ታውቃለህን? ካወቅህ ደግሞ ገንዘቤን ለሚነግዱበት ወይም ለሚለውጡ ሰዎች በመስጠት እነርሱ እንዲያተርፉበት ማድረግና እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ ከእነርሱ መቀበል እንድችል ማድረግ ትችል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሳታደርግ ጭራሹኑ በድፍረት እነዚህን በእውነት ላይ ያልተመሠረቱ ክፉ ቃላትን ስለ ተናገርህ ቅጣት ይገባሃል በማለት ለወታደሮቹ፡- ያለውን መክሊት ውሰዱና አሥር መክሊት ላተረፈው ጨምሩለት፤ ላለው ይሰጠዋል ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ ስለዚህ የማይጠቅመውን ባሪያ ወደ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ውጪ አውጡት በማለት አዘዛቸው፡፡

ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ሳለ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን ቃል በቃል ወይም በሰምና ወርቅ ወይም በምሳሌ አስተምሮአቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት እርሱ ይህን ትምህርት ያስተማረው በምሳሌ ነው፡፡ ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ያስተምር የነበረው አስቀድሞ በነቢዩ ዳዊት «አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ፡፡» (መዝ 77፥2) ተብሎ የተነገረውን የትንቢት ቃል ለመፈጸምና ቃሉን የሚሰሙት ተማሪዎቹ የሚማሩት ትምህርት ሳይገባቸው እየተጠራጠሩ ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ ለማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ብቻ ከሰባት በማያንሱ ምሳሌዎች ስለምትመጣው መንግሥቱ በስፋት አስተምሯል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌልን ቃል በዚህ ዓለም ላይ ሲዘራ ዘሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ በተሠማሩ ሰዎች ልብ ውስጥ በተለያዩ ምሳሌዎች አማካኝነት ይዘራ ነበር፡፡ ይህ በመሆኑም ጌታ ቃሉን ለገበሬዎች በዘርና በእንክርዳድ እንዲሁም በሰናፍጭ ቅንጣት፣ ለእናቶች በእርሾ፣ ለነጋዴዎች በመዝገብና በዕንቁ፣ ለዓሣ አጥማጆች በመረብ. . . ወዘተ እየመሰለ በምሳሌ ያስተምራቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በአሥሩ ቆነጃጅት፣ በሰርግ ቤት፣ በበግና በፍየል. . . ወዘተ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለ መንግሥቱ በስፋት በምሳሌ አስተምሯል፡፡ ጌታ ይሁን ያደርግ የነበረው ትምህርቱ ለተማሪዎቹ እንዲብራራላቸውና ግልጽ እንዲሆንላቸው ነበር፡፡

በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ሰንበት ውስጥ የምናነበው ንባብ፣ የምንሰበከው ስብከትና የምንዘምረው መዝሙር የሚነግረንም ስለ አንድ በጎናና ታማኝ ባሪያ በምሳሌ የተነገረውን ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የወንጌል ቃል መሠረት «ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው» ተብሎ የተጠቀሰው ሰው በዳግም ምጽአቱ ወደዚህ ምድር ተመልሶ ከመምጣቱ በፊት ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰውን ቅን ፈራጅ አምላካችን በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በምሳሌው ውስጥ የተጠቀሱት ባሪያዎች የሚወክሉት ምዕመናንን ወይም እኛን ነው፡፡ መክሊት የተባለው በጎ የሚያሰኘው በጎና መልካም ሥራ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች የሚመሰሉት ሥራን ከሃይማኖት ጋር አስተባብረው የያዙትን ጻድቃን ሲሆን መክሊቱን ጉድጓድ በመቆፈር የቀበረው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ደግሞ ምግባርና ሃይማኖት የሌላቸው የኃጢአተኛ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት በመካከላችን ተገኝቶ ስለ መንግሥተ የምትናገረውን ወንጌል ከሰበከልን በኋላ ለእያንዳንዳችን አንድ፣ ሁለትና አምስት መክሊቶችን በመስጠት ለፍርድ እስከምመጣ ደረስ ነግዳችሁና አትርፋችሁ ጠብቁኝ ብሎን በዕርገቱ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ  ሄዷል፡፡ በመሆኑም ሁላችንም ከእግዚአብሔር የተለያዩ መክሊቶችን ተቀብለናል፤ እንድንነግድባቸውና እንድናተርፍባቸው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- «ለአንዱ ጥበብን መነገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፤ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፤ለአንዱም ትንቢትን መናገር፤ለአንዱም መናፍስትን መለየት፤ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፤ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል፡፡» 1ኛ ቆሮ.12፥8-11፡፡

እግዚአብሔር ለልጆቹ የሰጣቸው መክሊት ይህ ብቻ አይደለም፤ለአንዱ መስበክ ለሌላው የማስተማር ለሌላው የመቀደስ ለሌላው የመዘመር ለሌላው የመባረክ ለሌላው የማገልገል. . . ወዘተ መክሊቶችን ወይም ስጦታዎችን ሰጥቶአል፡፡ በፍርድ ቀን ሁሉም ሰው የሚፈረድበት በተሰጠው መክሊት ትርፍ መሠረት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚሰጠው አንድ መክሊት ብቻ አይደለም፡፡ ሁለት ወይም ሦስት ወይም ከዚያ በላይ መክሊቶች ሊሰጡት ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌ አድርገን ብንወስድ ለመጥምቀ መለኮት የተሰጡት መክሊቶች ብዙ ናቸው፤ በብሕትውና መኖር፣ ማጥመቅ፣ ነቢይነት፣ ንስሓ ተቀባይ ካህን፣ ስብከት፣ የሰዎችን ልብ ለጌታ የተስተካከለ መንገድ አድርጎ ማዘጋጀት፣ . . .፡፡ ዮሐንስ በተሰጡት በእነዚህ ሀብቶቹ ወይም መክሊቶቹ የብዙዎችን ልብ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ እጅግ ስላተረፈ ጌታ ስለ እርሱ «ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤. . .» (ማቴ.11፥11) በማለት መስክሮለታል፡፡

ይህን ስብከት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚናገረውን የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ስብከት ሳዘጋጅ ከሦስት ቀናት በፊት በሞት የተለዩንን በጎና ታማኝ አገልጋይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ መንፈሳዊ ሕይወት እያሰብሁ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለእኚህ ታላቅ አባት ብዙ መክሊቶችን ስለ ሰጧቸው በእነዚህ መክሊቶች ብዙ ሰዎችን ለእግዚአብሔር አፍርተውለታል፡፡ ይህን በማስመልከት ስለ እርሳቸው የአገልግሎት ዘመናት በሚናገር መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ተብሎ የተጻፉትን ቃላት አንብቤያለሁ፡- «ከምንም ነገር በላይ ቅዱስነታቸው ታታሪ ሰባኪ፣ እጅግ ጎበዝ መምህር፣ ጥበበኛ ጸሐፊ፣ ተሰጥኦ ያላቸው ገጣሚ፣ መናኝ መነኩሴ፣ የዋህ ባሕታዊ፣ የሚያነቃቁ ጳጳስ፣ ታላቅ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በስብከቶቻቸው ያነሣሡና በታላላቅ ሥራዎቻቸው የሚመሩ ብሩህ ኮከብ ናቸው፡፡» መክሊት ተቀብሎ በተቀበለው መክሊት ሌሎች መክሊቶችን የሚያተርፍ ሰው በፍርድ ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ «መልካም፤ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙም እሾምሃለሁ፤ወደ ጌታህ ደስታ ግባ. . .» ይባላል፡፡ መክሊቱን መሬት ቆፍሮ የሚቀብረው አገልጋይ ግን በውጪ ባለው ጨለማ ውስጥ ተጥሎ በዚያ በልቅሶና ጥርስ በማፋጨት እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ዛሬ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉም አንድ ከሆነው ከእግዚአብሔር መንፈስ የተለያዩ ስጦታዎችን ወይም መክሊቶችን ተቀብሏል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም መክሊቱን ቆፍሮ ስለ ቀበረ ለእግዚአብሔር ምንም ሊያተርፍ አልቻለም፡፡ በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ የተሰጠውን መክሊት ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራበት ወይም ሳይነግድበት ወይም ሳያተርፍበት በመሬት ውስጥ ቆፍሮ በማስቀመጡና ጌታው ሲመጣ በማስረከቡ በዚህ ዘመን ከምንገኝ ሰዎች እጅጉን ይሻላል ብዬ አስባለሁ፤እኛ መክሊቶቻችንን ጠብቀን በማቆየት ለእግዚአብሔር ማስረከብ እንኳ አልቻልንምና፡፡ ዛሬ የተቀበለ ሁሉ ቀብሯል ወይም ጥሏል፡፡ አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ በተሰጠው የመቀደስ መክሊት መቀደስ ሲገባው የሚዘፍን ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡ አንድ የመዘመር መክሊት የተሰጠው አገልጋይ ለእግዚአብሔር መዘመር ሲገባው ሰዎችን የሚያማ ወይም የሚሳደብ ከሆነ መክሊቱን ጥሏል፡፡   ትክክለኛውን የወንጌል ትምህርት እንዲያስተምርና ሰዎችን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስገባ የማስተማር መክሊት ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለ ሰው በዚህ መክሊቱ የኑፋቄ ስብከት በመስበክ የዋህ የሆኑ ሰዎችን ወደ ሲዖል ለመምራት የሚያስተምርበት ከሆነ መክሊቱን ሙሉ ለሙሉ ጥሎታል ወይም አጥፍቶታል እንጂ አልቀበረውም፡፡ በተሰጠው የመባረክ መክሊት ወይም ሥልጣን ምዕመናንን መባረክና ኃጢአታቸውን መናዘዝ ሲገባው ለጥንቆላ ሥራ ተቀምጦ እፈርዳለሁ የሚል ከሆነ መክሊት የተባለ ክህነቱን አቃሎአታል አጥፍቷታልም እንጂ አልቀበራትም፡፡ በእግዚአብሔር መድረክ ላይ ወንጌልን መናገር ሲገባው ተራ ወሬ ወይም ፖለቲካ የሚደሰኩር ከሆነ ይህ ሰው መክሊቱን ጥሏል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ፡፡ ለዚህ ነው በዚህ ዘመን ውሰጥ ያለን ሰዎች መክሊቱን ከቀበረው ሰው የምናንስ ክፉና ሃኬተኛ ሰዎች ነን እንጂ ከእርሱ የምንሻልበት ምንም ዓይነት ነገር የለንም የምንለው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ በወንጌል እንደ ተነገረለት ለጻድቃን ሊፈርድላቸውና በኃጥአተኞች ላይ ሊፈርድባቸው ይመጣል፡፡ ከፍርዱ በፊት ሁላችንንም በሰጠን መክሊቶች መጠን ይቆጣጠረናል፡፡ አንድ መክሊት የተሰጠው ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ሁለት የተሰጠው ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያም በላይ የሆኑ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ አምስት የተቀበልነው ደግሞ አምስትና ከዚያም የሚበልጡ መክሊቶችን ማትረፍ ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ እኛ ያተረፍነው ምንድር ነው? በዕርቅ ፋንታ ጠብን የምናባብስ ስለሆንን በመክሊታችን ሰዎችን አጉድለናል እንጂ ማትረፍ አልቻልንም፡፡ በመመረቅ ፋንታ የምናረገም ከሆንን መክሊታችንን ጥለናል፡፡ በመጸለይ ፋንታ ለመደባደብ የምንጋበዝ ከሆንንም የተሰጠንን መክሊት አጥፍተናል፡፡ ታዲያ የገብርኄርን ሰንበት ዛሬ ስናከብር አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ እያንዳንዳችንን ታተርፉበት ዘንድ የሰጠኋችሁን መክሊት እስከነ ትርፉ አስረክቡኝ ቢለን ምንድር ነው የምናስረክበው? የምንሰጠውስ መልስ ምንስ የሚል መልስ ነው?

በወንጌል ላይ የተጠቀሰው ያ ሃኬተኛ ባሪያ መክሊቱን መቅበሩ ሳያንሰው  ለጌታው የሰጠው ክፉ መልስ ለከፍተኛ ቅጣት ዳርጎታል፡፡ እርሱ ለጌታው «ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፡፡» የሚል መልስ ነበር የሰጠው፡፡ በዘመናችን ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ከዚህ ባሪያ ጋር የሚመሳሰል ጠባይ አላቸው፤ እነርሱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምንም ነገር ሳያውቁ የእግዚአብሔርን ጠባይና እውቀት በእነርሱ የእውቀት ሚዛን ላይ ይሰፍራሉና፡፡ አንድ ሰው በጠና ሕመም ከታመመ ወይም ከልጆቹ አንዱ በሞት ቢለየው ወይም ንብረቱን በእሳት ቃጠሎ ቢያጣ ይህን አደጋ ያደረሰበት እግዚአብሔር እንደ ሆነ አድርጎ ለእርሱ በእርሱ ላይ ለእርሱ የማይገባ ቃላትን የሚሰነዝር ሰው አለ፡፡ ከዚህ አንጻር እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ሕልውና ላይ በመምጣት «እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ይህ ሕመም ወይም አደጋ በእኔ ላይ አይደርስም ነበር፡፡» ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ «እግዚአብሔር እንደዚህ የጨከነብኝ ምን አድርጌው ነው;» እያሉ እግዚአብሔርን እንደ ሃኬተኛው ባሪያ ጨካኝ የሚያደርጉት ሰዎች አሉ፡፡ እግዚአብሔርን «የለህም» ወይም «ጨካኝ» ማለት ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨለማ የሚያስገባ ክፉ መልስ ነው፡፡ ሰዎች ሁለት ጊዜ ሳያስቡና አንድ ጊዜ ሳያውቁ በቸልተኝነት በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝሩአቸው ቃላት ከባድ ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

የጻድቁ የኢዮብ ሚስት እርሷ በእግዚአብሔር ላይ በልቧ ስትሰነዝራቸው የነበሩትን ቃላት ባሏም እንደ እርሷ ይሰነዝራቸው ዘንድ «እግዚአብሔርን ስደበውና ሙት» በማለት በእርሱ ላይ ልታነሣሣው ሞክራ ነበር፡፡ ሊነቀፍ ወይም ሊወገዝ ወይም ሊኮነን የሚገባው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ መዓቱ የራቀና ምሕረቱ የበዛ አምላክ ነው እንጂ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ያልዘራነውን የጽድቅ ፍሬ እንድንዘራና እንድናጭድ፤ያልበተንነውንም መልካም ዘር በመበተን በፍርድ ቀን ምርቱን እንድንሰበስብ የሚፈልግ ጌታ ነው፡፡ እኛ ሠላሳ፣ ስድሳና መቶ ፍሬ በማፍራት የእነዚህ ፍሬዎችን ምርት በመሰብሰብ ሰማያዊ መንግሥቱን እንድንወርስ ስለሚፈልግ «ጨካኝ» አምላክ አይደለም፡፡ እርሱ ለሚያምኑትና ለሚታመኑት ሁሉ የሚታመን ታማኝ ጌታ ነው እንጂ የሚያምኑትን የሚክድ «ጨካኝ» ፈጣሪ አይደለም፡፡ ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበስብ ሰው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም፤ ጨካኝ፣ ከሀዲና የማይታመንም ሰው ነው፡፡

ዛሬ እግዚአብሔር በጎና ታማኝ አገልጋይ አጥቶአል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታመን አገልጋይ አጥታለች፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ «ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም፡፡» (መዝ 13፡3) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ዘመን አገልጋዮች ነው፡፡ ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለቤተ ክርስቲያን ታማኝ ሊሆን አልቻለም፡፡ በጥቂቱ ታምኖ በብዙ ላይ ሊሾም የሚችል ሰው ስለ ጠፋ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ያለህ እያለ ነው፤ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ፡፡ አገልጋዩም ሆነ ምዕመኑ በአንድነት ተባብሮ ከዳተኛ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቃሉ የሚገኝ ሰው ማግኘት ተቸግራለች፡፡ ሁሉም የተሰለፈው የቤተ ክርስቲያንን ሙዳይ በመቦጥቦጥ የግል ብልጽግናውን ለማዳበር እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምዕመናን መዳንና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ሲል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አገልጋዮችን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሾማቸውና የሚሾማቸው ግን ራሳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያንንና መንጋውን ከጥፋት እንዲጠብቁ ነው፤ ሐዋ.20፥28፡፡ ለመጠበቅ ተሾሞ የሚያጠፋ ጠባቂ ዕድል ፈንታውና ዕጣ ተርታው ትሉ በማያንቀላፋበትና እሳቱ በማይጠፋበት ዘላለማዊ ሲዖል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ አገልጋይ ቅጣቱ ዘላለማዊ መሆኑን ከወዲሁ ሊያውቅ ይገባዋል፡፡ እርሱ ጌታው በዳግም ምጽአቱ እስከሚገለጥ ድረስ መንጋውን በመመገብ፣ ውኃ በማጠጣትና በማሳረፍ ፋንታ ለራሱ ብቻ የሚበላና የሚጠግብ፤ የሚጠጣና የሚሰክር፤የሚያርፍና ዘና የሚል ከሆነ ጌታው ባላሰባት ሰዓት ተገልጦ ከሁለት ይሰነጥቀዋል፤ዕድሉንም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ባለበት ጨለማ ውስጥ ያደርግበታል፤ ማቴ. 24፥45-51፡፡ ዛሬ ጌታ አይመጣም ወይም ይዘገያል ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተለያያ መልኩ የሚዘርፍና እግዚአብሔርን የሚያሳዝን አገልጋይም ሆነ ተገልጋይ ከዚህ ጠባዩ ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ የተቀበለው ለዚህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በጥፊ የተመታላት፣ ርኩስ ምራቅ የተቀበለላት፣ የሾህ አክሊል የተቀዳጀላት፣ የተንገላታላትና ሞተላት ለዚህች ቤተ ክርስቲያንና ለዚህ ምዕመን ነውና አገልጋዮች በጎና ታማኞች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከእኛ ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡

ይቆየን፡፡

በጎውን ሁሉ ለእኛ ያደረገና የሚያደርግ እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤አሜን፡፡

የአስቦት ገዳም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡

መጋቢት 20 ቀን 2004 ዓ.ም

በኢዮብ ሥዩም


በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት የማገኘው የአሰቦት ቅድስት ሥላሴና የአባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም ደን በአሁኑ ጊዜ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጠ፡፡

 

ያነጋገርናቸው የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለ ማርያም እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም የካቲት 20/2004 በገዳሙ ጥብቅ ደን ላይ የተነሣው እሳት ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፡፡ እሳቱን አስነስተውታል ተብለው በሚጠረጠሩ ግለሰቦች ዳግሞ እንዳይነሣ ማስተማመኛ ባይኖርም ለአሁኑ ምንም ዓይነት የእሳት ሥጋት የለም ብለዋል፡፡

በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በሞባይል ስልክ የጽሑፍ መልእክት “የአሰቦት ሥላሴ አካባቢ ደን በድጋሚ ተቃጠለ ምን ይሻለናል” በሚል ርእስ እየተሰራጨ ያለው መልእክትም ሐሰት እንደሆነና ገዳሙን እንደማይመለከትም አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

 

በገዳሙ ይዞታ የነበረውና በእሳት አደጋ የወደመውን ደን መልሶ ወደነበረበት ለመመለስና ገዳማውያኑን ለመርዳት በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ያደነቁት አስተዳዳሪው በተለያየ ቦታ ያሉ ምእመናን ለገዳሙ እርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

የጽሑፍ መልእክቶችን መሰራጨት ተከትሎ ያነጋገርናቸው ምእመናንም እንደነዚህ ዓይነት የአሉባልታ ወሬዎችና ያልተጣሩ መረጃዎች በገዳማት ላይ እየተከሠቱ ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ ናቸው ብለዋል፡፡

 

በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአባ ሳሙኤል ዘወገግ የተመሠረተው የአሰቦት ገዳም በተደጋጋሚ እየደረሰበት ያለውን ችግር ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ ማኅበረ ቅዱሳን ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥናት እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ቃጠሎ መጥፋቱ ተገለጠ፡፡

መጋቢት 20/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  • ገዳሙ አሁንም ድጋፍን ይሻል፡፡

የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ተከስቶ የነበረው ቃጠሎ መጥፋቱን የገዳሙ አበምኔት አባ ኢሳይያስ  ገለጹ፡፡ ገዳሙም ተጨማሪ ርዳታና ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል፡፡

ረቡዕ ጠዋት መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም የቅዱሳን ከተማ በሚባለው የመናንያን መናኸሪያ ጭስ ይታይ የነበር ሲሆን፣ በምእመናን፣ በፌደራል ፓሊስና በኦሮሚያ ፓሊስ አባላት ጥረት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ በቦታው የነበሩት ምእመናን ገልጸውልናል፡፡ ሁለቱ ቀናት ረቡዕና ሐሙስ በተደረገው ርብርብ በገዳሙ አንደኛው አቅጣጫ ያለው የእሳቱ መንስኤ ለዘለቄታው ሊጠፋ እንደቻለ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያስረዳል፡፡ በቅዱሳን ከተማ ያለውን እሳት የማጥፋት ጥረት ከጠዋቱ 12፡00 የጀመረ ሲሆን ወደ 9፡30 አካባቢ ሙሉ ለሙሉ ሊጠፋ ችሏል፡፡

 

እሳቱን ለማጥፋት ጥረት በሚደረግበት ጊዜ፣ አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ አባልና አንድ ምእመን እሳቱ ላይ በመውደቃቸው ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ወዲያውኑ ወደ ሕክምና እንደተወሰዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የፖሊስ አባሉ አደጋ እጁ ላይ ሲደርስበት ከቢሾፍቱ የመጣው ምእመን እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡

 

በተያያዘም የገዳሙን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተወካዮችና ከመስተዳድር አካላት ጋር በገደሙ አጠቃላይ ችግሮች ዙሪያ በስፋት መነጋገራቸውን አባ ኢሳይያስ ተናግረዋል፡፡

 

የመንገድና የውሃ ችግር በገዳሙ ላይ ጎልተው የሚታዩ ፈተናዎች መሆናቸውንና ይህንንም ለመፍታት የሁሉም ርብርብ እንደሚጠይቅ ያሳሰቡት አበምኔቱ ገዳሙ ያለውን የምግብ ፍጆታ በቃጠሎው ለተሳተፉ ምእመናን በማዋሉ ሊሟጠጥ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ለመነኮሳቱ የሚሆን ቀለብ ባለመኖሩና ጊዜያዊ ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አማካይነት ከበጎ አድራጊ ምእመናን ያገኘውን የበሶ፣ የስኳርና የውኃ ልገሳ በትላንትናው ዕለት ወደ ገዳሙ በመውሰድ ለሚመለከታቸው አባቶች አስረክቧል፡፡

 

በቢሾፍቱ የማኅበረ ቅዱሳን ማእከል አባላት፣ በቢሾፍቱ ደብረ መዊእ ቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያንም ገዳሙ ያለበትን ጊዜያዊ የውኃ ችግር ለመቅረፍ እንዲቻል ምእመናንን በማስተባበር ብዛት ያላቸው የውኃ ጀሪካኖችን በመሰብሰብ ውኃ በመሙላት ወደ ገዳሙ በማመላለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በጎ አድራጊ ምእመናን ገንዘብ በማሰባሰብ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ጥራጥሬና እህል በመግዛት ወደ ገዳሙ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

 

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት፣ የፌደራል ፓሊስ፣ የኦሮሚያ ፓሊስ፣ የአየር ኀይል፣ ማኅበራትና ምእመናን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍቅር አስገድዷቸው ከሩቅም፣ ከቅርብም ወደ ገዳሙ በመገስገስ ቃጠሎውን ለማጥፋት ላደረጉት ከፍተኛ ርብርብ አበምኔቱ ምስጋናቸውን በራሳቸውና በማኅበረ መነኮሳቱ ስም አቅርበዋል፡፡

004

«በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ ?» መጽሐፍ ታተመ

መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

004ከዓመታት በፊት ፓስተር እንደነበሩ በሚነገርላቸው ግለሰብ ተዘጋጅተው በጀርመን ሀገር ለታተሙት የቅሰጣ መጻሕፍት ምላሽ የሰጠ መጽሐፍ መታተሙ ታወቀ፡፡ ገዳሙ ደምሳሽ በተባሉትና በአሁኑ ወቅት በጀርመን ቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በተሾሙ ግለሰብ ተዘጋጅተው ለታተሙት ሦስት መጻሕፍት ምላሽ የሰጡት መምህር ኅሩይ ኤርምያስ የተባሉ  በዚያው በጀርመን የሚኖሩ ሊቅ ሲኾኑ፤ የመጽሐፋቸው ርእስ «መጻሕፍትን መርምሩ በእልቅና ካባ ፓስተር መቅደስ ገባ ?» የሚል እንደኾነ ከቦታው የደረሰን ሪፖርት ያስረዳል፡፡ መጽሐፉ 219 ገጾች ያሉት ሲኾን አዘጋጁ በመጽሐፉ መግቢያ እንደገለጹት መልስ የሰጡባቸው መጻሕፍት “የመናፍቃን ሰፊ የቅሰጣ ማስፈጸሚያ ወጥመዶች አካል፤ በውጭ ሳይኾን በውስጥ ተጠምደው ምእመናንን በገዛ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው አደባባይ የሚያጠምዱ ናቸው ” ብለዋል፡፡ አክለውም መልስ የሰጡባቸው  መጻሕፍት «ቤተ ክርስቲያንን ይሳደባሉ፣ ይተቻሉ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያንቋሽሻሉ» ካሉ በኋላ የእሳቸው መልስ የኑፋቄ መጻሕፍቱን ደራሲ ተደራሽ ያደረገ ቢመስልም ዋና «ዓላማው መላው ምእመናን ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁና የተሳሳተ ትምህርት ሰርጎ እንዳይገባ ማንቃትና ማዘጋጀት ነው» ብለዋል፡፡ በመጻሕፍቱ ይዘትና በአዘጋጁ ወቅታዊ አስተምሕሮ በመደናገር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መፍትሔ እንድትሰጣቸው ከአካባቢው አስተዳደር ጀምሮ እስከ ሊቃውንት ጉባኤና ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ አቤት ሲሉ የቆዩት ምእመናን በመምህር ኅሩይ መጽሐፍ መጽናናታቸውንና መደሰታቸውን ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

መልስ የተሰጠባቸውን መጻሕፍት አዘጋጅ አስመልክቶ ከአካባቢው ምእመናን በደረሰን አቤቱታ መሠረት፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከትን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስንና በቤተ ክርስቲያኗ የሀገረ ጀርመን ሊቀ ካህናት የኾኑትን ሊቀ ካህናት ዶክተር መርዐዊ ተበጀን በማነጋገር ሰፋ ያለ ዘገባ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በኅዳር ወር፣ ቅጽ 19፣ ቁጥር 236 እትማችን ሰፋ ያለ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ አንባብያን ጉዳዩን ከስሩ ይረዱት ዘንድ በወቅቱ የታተመውን ዘገባ ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡፡

–   –     –    –     –    –     –    –    –   –

•    በጀርመን አገር በሚገኙ አብያተ ከርስቲያናት የሚፈፀሙ ሃይማኖታዊ ሕፀፆች እና በደሎች ተገቢው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የምእመናን ሕብረት ጠየቀ

በጀርመን አገር በኑፋቄ ትምሕርታቸው የሚታወቁት እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ አስተዳዳሪ የሆኑት የ«ቀሲስ» ገዳሙ ደምሳሽ እና ከአንድ መቶ ሥልሳ ሺሕ ዩሮ በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገንዘብ ለግል ጥቅም ባዋሉ ግለሰብ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ መእመናን ጠየቁ፡፡

 

በጀርመን አገር የሚገኘው የምእመናን ኅብረት ይህንኑ በማስመልከት ሰሞኑን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ለጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ እና ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሰራጨው ደብዳቤ ከቤተ ከርስቲያኒቱ ሥርዐትና ደንብ ውጪ የተፈጸመው በደል ተጣርቶ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡

 

ኅብረቱ ባሰራጨው ደብዳቤ እንዳመለከተው የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማገልገል ላይ ያሉት «ቀሲስ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም በመናፍቃን የእምነት ድርጅት ውስጥ በሰባኪነት አገልግሎታቸው በተጨማሪ፤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ ሦስት የኑፋቄ መጻሕፍትን አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፡፡ በቅርቡም አራተኛ መጽሐፍ አዘጋጅተው ያሳተሙ ሲሆን ሌሎች ኑፋቄ አዘል ሦስት መጻሕፍት በማዘጋጀት ላይ እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

 

መጻሐፍቶቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዶግማ ውጪ የሆኑ መልእክት የሚያስተላልፉ መሆናቸውን የጠቀሰው ይህ ደብዳቤ ከዚህ ውጪ የተለያዩ የኑፋቄ ትምህርቶችን በማስተማር እና በካሴት በማሳተም ምእመናንን እያሳቱ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

 

ባለፈው ዓመት ብቻ በግልጽ የታወቁ አምስት የቪዝባደን ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያገለግሉ እና ከእርሳቸው እግር ሥር የማይጠፉ የነበሩ ምእምናን እና የሰበካ ጉባኤው አባላት ወደ ሌላ እምነት ተቋም ሔደው እንዲጠመቁ ማድጋቸውን ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ለፃፏቸው መጻሕፍት እና የኑፋቄ ትምህርቶችን ሳያስተካክሉ እና እርማት ሳይሰጡ እንዲሁም የፀፀት ምላሽ ሳይሰጡ በ1997 ዓ.ም የአስተርዩ ማርያም በዓል ዕለት በጀርመን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ በሆኑት ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ አማካኝነት «ቀሲስ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተመልሰዋል» የሚል ማደናገሪያ መልእክት መተላለፉ እንዳሳዘነው ኅብረቱ በጻፈው ማመልከቻ ጠቅሷል፡፡

 

እኚሁ ግለሰብ ቀደም ሲል በኅቡዕ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ያለምንም ፍራቻ በግላጭ ስለሚዘሩት ኑፋቄ ጀርመን ሀገር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በመጠቆም አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም አስተዳደሩ ለጥያቄው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ነገሩን ወደ ጎን በመተው እና በማለባበስ ላይ መሆኑን ደብዳቤው ጠቅሷል፡፡ ግለሰቡ በተለያዩ አድባራት እየተገፉ ትምህርት እንዲያስተምሩ ከዚህም አልፎ ለሚያደርጉት ተፃራሪ ድርጊት አስተዳደሩ ድጋፍ እየሰጡ እንደሚገኝ በቅሬታ ደብዳቤው ገልጧል፡፡

 

ይህ ድርጊት በርካታ ምእመናንን ያሳዘነ እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲርቅ ምክንያት እየሆነ ስለሆነ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት መፍትሔ እንዲሰጡ የምእመናን ኅብረቱ በአፅንኦት አሳስቧል፡፡

 

ኅብረቱ ባቀረበው አቤቱታ በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከመቶ ሠላሳ ሺሕ ዩሮ በላይ ገንዘብ አጥፍተው በሊቀ ጳጳሱ የታገዱት ካህን ጉዳይ ተጣርቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንደትወስድ ጠይቀዋል፡፡

 

«በሃይማኖታችን እና በመላው ምእመናን ላይ የተቃጣውን ከባድ የእምነት ፈተና ለመቋቋም እንድንችል ጉዳዩን በጥልቀት መርምራችሁ ተገቢውን ውሳኔ በአፋጣኝ እንድትሰጡበት በልዑል እግዚአብሔር ስም እንማፀናለን» ሲል የምእመናን ኅብረቱ ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ባሠራጨው የአቤቱታ ደብዳቤ አመልክቷል፡፡

 

ጉዳዩ የሚመለከታቸው በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ ሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ በአቤቱታው ላይ ተጠይቀው  በሰጡት ምላሽ፤ «ቀሲሰ» ገዳሙ ከአሁን ቀደም የሌላ እምነት ተከታይ ቢሆኑም ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመመለሳቸው በክህነታቸው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

«ቅዱስ ቤተ ክርስትያን ወደ እርሷ የመጡትን ትቀበላለች፣ አታገልም፡፡ የቀሲስ ገዳሙም ጉዳይ ይኸው ነው፡፡ ሊቃነ ጳጳሳትም አቡነ ዮሴፍ እና አቡነ እንጦንስ በፈቀዱት መሠረት አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ ነው፡፡» ያሉት ሓላፊው፤ አሳተሙት ስለተባለው የኑፋቄ መጻሕፍት እና ትምህርት በሊቃውንት ጉባኤ ተመርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሒደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከሁለት ዓመት በፊት ሚያዝያ ጊዮርጊስ የንግስ ዕለት የሰሜን አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ «ቀሲስ» ገዳሙ በዓውደ ምሕረት ላይ ባስተማሩትን ትምህርት በመደሰት «መጋቢ ሐዲስ» የሚል ሹመት መስጠታቸውንም ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

 

ሓላፊው እንዳሉት የቀሲስ ገዳሙን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በአገልግሎት እንዲቀጥሉ የሚቃወሙ በርካታ ምእመናን እንዳሉ ሁሉ የሚደግፏቸውም የዛን ያህል የበዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የሚመጣውን ቅሬታ አጣርቶ ውሳኔ ለመስጠት በሚደረገው ሒደት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትክክለኛ አካሔድ በመከተል ውሳኔውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

 

በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እና የምእመናን ኅብረቱ ውሳኔ እንዲሰጥበት በየጠየቀው በሙኒክ ቅዱስ ቤተ ጊዮርጊስ ቤተ ከርስቲያን ገንዘብ ምዝበራ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ «ይህ ጉዳይ በሀገሪቱ ፍ/ቤት በሕግ የተያዘ በመሆኑ ምንም የምለው ነገር የለኝም፤ በተፈፀመው ወንጀል ግን አዝኛለሁ» ብለዋል፡፡ ድርጊቱ እንዴት እና መቼ እንደተፈፀመ እንዲሁም ማን እንደፈፀመው ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ውሳኔ ሲያገኝ በይፋ እንደሚገለጽም አስረድተዋል፡፡

 

«በጥምቀት አንድ ነን» በሚል ከአሁን ቀደም ከሌሎች የእምነት ተቋማት ጋር ስለፈረሙት ጉዳይ ማስተካከያ ስለመሰጠቱ እና ስለአለመሰጠቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ የቆየ በመሆኑ መነሳት እንደሌለበት ቿቅሰው፣ ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው መፈራረማቸው ዛሬም ስሕተት ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

 

«በመፈራረማችን ያጣነውም ያገኘነውም ነገር የለም፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሥራች ከመሆናችን አንፃር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር እንጂ ከዛ ውጪ የተደረገ ስምምነት አይደለም» ያሉት ሓላፊው፤ «በዚህ በኩል ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አካል ‘ትክክል አላደረክም’ ያለኝ የለም» ብለዋል፡፡

 

«በመፈራረሜ የፈፀምኩት ስሕተት ባለመኖሩ አልፀፀትም ይቅርታም አልጠይቅም፣  የምፀፀተው ስፈራረም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ባለመጠየቄ ነው፤ እንዲህ ሰዎችን የሚያሳዝን መሆኑን አላወኩም፡፡ ፈቃድ ብጠይቅ ትልቅ ቁም ነገር ነበረው» ሲሉ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

 

የመገናኛ አውታሮች በሰፉበት፣ ዘመኑን ዋጁ በሚባልበት በዚህ ወቅት ከዓለም ተገልለን ብቻችንን ከመሆን እንዲህ ያለ ኅብረት መፍጠር ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸውም ሓላፊው አስረድተዋል፡፡

በምእመናኑ ኅብረት ጥያቄ እና በሊቀ ካህናት ዶ/ር መርአዊ ተበጀ ምላሽ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው የሰሜን ምእራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ በጀርመን የሚነሱ የምእመናን ጥያቄዎችን ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

ከቀሲስ ገዳሙ ጉዳይ የጠራ መረጃ ስላልተገኘ እስካሁን በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት እርምጃ ለመውሰድ ያስቸገረ መሆኑን ጠቅሰው ጉዳዮቹ ተጣርተው በቅርቡ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል፡፡

 

የተፃፉት የኑፋቄ መጻሕፍት ላይ ወደ ፮ የሚሆኑ ነጥቦችን አውጥተው ማብራሪያ እንዲሰጡ በጠየቋቸው ጊዜ «ቀሲሱ» ‘አማርኛ ችግር ስላለብኝ ነው’ ማለታቸውን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው መጻሕፍቶቹ በሊቃውንት ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ በተቋቋመው የሃይማኖት ጉዳይ አጣሪ ኮሚቴ ተመርምረው ስሕተት እንዳለባቸው ከታመነ ቤተ ክርስቲያኒቱ እርምጃ እንደምትወስድ ተናግረዋል፡፡ ወደ ጀርመን ተመልሰው ከሌሎች ካህናት ጋር ስለ ጉዳዩ በመወያየት ተጨማሪ የማጣራት ሥራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

 

የኑፋቄ ትምህርት ለሚያስተምሩ ግለሰብ እንዴት መጋቢ ሐዲስ የሚል ማዕረግ ሰጡ) የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፤ «ቀደም ሲል በሌላ እምነት እስከ ፓስትርነት ደረጃ የደረሰ ማዕረግ እንደነበረው ባለማወቄ እና በትምህርቱም ምእመናንን ጥሩ እውቀት ማስጨበጡን በመገንዘብ ይህንኑ ማዕረግ በቃል ሰጥቼዋለሁ፡፡ በጽሑፍ ያረጋገጥኩበት እና እውቅና የሰጠሁበት ሁኔታ ግን የለም» ብለዋል፡፡ ያ ማዕረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና እንደሌለው፣ ባለማወቅ በቃል የተፈፀመ ስሕተት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

 

የተፃፈው መጽሐፍ እንግሊዝ ሀገር ለሚገኙ ሊቃውንት ሰጥተው ስሕተቱ እየተነቀሰ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፤ ከአሁን ቀደም ‘አቡነ ዮሴፍ ፈቅደው አገልግሎት እንዲሰጥ አደረጉ’ የተባለውን እና ማን አለቃ አድርጎ እንደሾማቸው በማጣራት ወደ ጀርመን ተመልሰው ከካህናቱ ጋር የመወያየት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

 

ብፁዕነታቸው በሙኒክ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ስለተፈፀመው ምዝበራ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከ19 ዓመት በላይ በዛው ቤተ ክርስቲያን በሓላፊነት ሲያገለግሉ በነበሩ ቄስ መስፍን ድርጊቱ መፈፀሙን ጠቅሰው፤ ጉዳዩ በሀገሪቱ ፍ/ቤት ለመከሰስ በአቃቢ ሕግ እየተመረመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

እዛ ያሉት ሰበካ ጉባኤ እና ምእመናን ባደረጉት የኦዲት ምርመራ በሰነድ ብቻ 166 ሺሕ ዩሮ መጉደሉን እንዳረጋገጡ ጠቅሰው፤ ከሰነድ ውጪ ያለ ደረሰኝ ከምእመናን የገባ በርካታ ገንዘብም ይጎድላል የሚል እምነት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

 

የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ብፁዕነታቸው ቿቅሰው፤ ይህን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ ለፈፀሙት ተግባር ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሱን ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ለመውሰድ እንድትችል አህጉረ ስብከቱ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር በጥምቀት አንድ ስለመሆኗ ስለተፈረመው ሰነድ ጉዳይ በሰጡት ቃል ፍርርሙ እርሳቸው ወደዛ ሀገር ከመሔዳቸው 2 ዓመት ቀድሞ የተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፍርርሙ ለአንድ ግለሰብ ለጥቅም ሲባል የተፈፀመ እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና የሰጠችው አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

እስካሁን ከፊርማ ያለፈ በተግባር የተፈፀመ ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ያመለከቱት ብፁዕነታቸው፤ ጉዳዩን ከምእምናን በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት ለቅዱስነታቸው ጭምር ማሳወቃቸውን አስረድተዋል፡፡

 

በአጠቃላይ የምእመናን ኅብረትም ሆነ ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ወዳጆች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎና መርምሮ ተገቢውን እርማት ለመስጠት ጥረቱ እንደሚቀጥል ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡

 

በወቅቱ የደቡብ፣ ደቡብ ምእራብ እና ደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ሐምሌ 2 ቀን 2003 ዓ.ም «ለሚመለከተው ሁሉ» በሚል በጻፉት ደብዳቤ «ቀሲስ ገዳሙ ደምሳሽ በመባል የሚጠሩት ግለሰብ በፍራንክፈርት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ክብረ በዓል ላይ ታቦተ ሕጉ በቆመበትና ማኅበረ ምእመናን በተሰበሰቡበት ከስሕተቴ ተመልሻለሁ ሀገር ቤት ሔጄ ንስሐ ገብቻለሁ በማለት ለሕዝቡ በአስታወቁበት ወቅት ከስሕተት መመለስዋና ንስሐ መግባትዎ መልካም ነው ሆኖም ግን ቤተ ክርስቲያን መጠቀም የሚችሉት እንደማንኛውም ማኅበረ ምእመናን ነው ከማለት በስተቀር በቤተ ክርስቲያን ክህነት አገልግሎት ተመድበው እንዲሠሩ በቃልም ሆነ በጽሐፍ ያስተላለፍኩት ምንም ዓይት ትዕዛዝ የሌለ መሆኑን እገልፃለሁኝ» ሲሉ ገልጸዋል፡፡

 

ከዚህ በፊት እንዳልነው አሁንም ጉዳዩን እየተከታተልን የምንዘግብ መኾኑን እንገልጻለን፡፡

 

ምንጭ፡- /ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ 19ኛ ዓመት ቁ.236  ኅዳር 2004 ዓ.ም./

ክርስቲያናዊ ሕይወት

መጋቢት 19/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

  • “ለማኅበረ ቅዱሳን አማርኛ መካነ ድር ዝግጅት ክፍል፡፡ መንፈሳዊ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ እባካችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝን ምክር ለግሱኝ?”

ውብ አንተ


የተከበርክ ወንድማችን ውብ አንተ ክርስቲያናዊ ሕይወትህ እንዲበረታ መንፈሳዊ ምክር ፈልገህ ስለጻፍክልን እናመሰግናለን፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወት ይህ ነው ወይም ያ ነው ብሎ ቁርጥ ያለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ጊዜና ቦታ ይገድበናል፡፡

 

ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት የሚመልሰኝ ምክር እፈልጋለሁ የሚለውን ዐሳብህን ብቻ ነጥሎ ማየት አሁን ያለህበትን የሕይወት ደረጃ ብናውቀው ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም ጥምቀተ ክርስትናን ተቀብለህ በክርስቶስ ክርስቲያን እንደተባልክ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም እንደ ክርስቲያን መኖር ያለብህን ሕይወት ስላልኖርክ በውስጥህ የሚወቅስህ ነገር አለ፡፡ ይህ ወቃሽ ኅሊና በልቡናህ ስለተሳለ እግዚአብሔርን አመስግነው፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የሚጸጸት፣ የሚጨነቅ የሚተክዝ ልቡና ያለው ሰው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ያልተለየው ነው፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲመሰክር እንዲህ አለ “…መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይናገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” ሮሜ.8፥26-27

መንፈስ ቅዱስ አካሉ አንድ ሲሆን ጸጋው ብዙ ነው፡፡ ጸጋው የማይመረመር ረቂቅና ምሉዕ  ስለሆነ በጎ ችሎታዎች ሁሉ ከእሱ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሰማዕታትን ለእውነትና ምሥክርነት የሚያዘጋጅ፣ ሐዋርያትን ለስብከት የሚያሰማራ መነኮሳትን በገዳም የሚያጸና ተነሳሕያንን ለንስሐ የሚያነሣሣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ከእኛ ጋር ሲሆን ለጸሎት እንነሣለን ለምጽዋት እጆቻችንን እንዘረጋለን ለምሥጋና አፋችንን እንከፍታለን፡፡ ለአምልኮ ወደ ቅድስናው ቦታ እንገሰግሳለን፡፡

 

ይህ በመሆኑ ኀጢአት ስንሠራ ከቤተ መቅደስ ስንለይ ከቃለ እግዚአብሔር ስንርቅ የምንጨነቀው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሲሆን ብቻ ነው፡፡

 

ክርሰቲያናዊ ሕይወት በጣም ጥልቅና ሰፊ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወት ተመክረን ከምንሰማው ተጽፎልን ከምናነበው ይልቅ በሕይወታችን የምንቀምሰው በሒደት የምንማረው ሕይወት ነው፡፡ ሒደት ደግሞ መውደቅና መነሣት፣ ማዘንና መደሰትን ማልቀስና መሳቅ፣ ማጣትና ማግኘትን ይመለከታል፡፡ ክርስትና ስናገኝ የምንደሰትበት ስናጣ የምናዝንበት ስንወድቅ ተስፋ የምንቆርጥበት ሕይወት አይደለም፡፡ ክርስትና በትናንቱ ጥንካሬያችን የምንኩራራበት የትዝታ ሕይወት ሳይሆን አሁን የምንኖርበት ቤት የምንጓዝበት ጎዳና ነው፡፡

ክርስትና ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ቁጥር 38 የተጻፈውን እንመልከት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ ሲያስተምር በርካታ ሰዎች ልባቸው ተነክቷል፡፡ በትምህርቱም ተመስጠው ወደ 3ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች አምነዋል፡፡ እነዚህ ያመኑትን ሰዎች በሕይወታቸው የፈጸሙት በርካታ ቁም ነገር ነበር፡፡

1. የሚያስተምረውን ትምህርት በሚገባ አደመጡት ስለሆነም ልባቸው ተነካ፡፡

አሁንም ቃለ እግዚአብሔርን ለመማር ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ ቅዱሳት መጻሕፍት ስናነብ መዝሙር ስናዳምጥ በማስተዋል መሆን አለበት፡፡ ሳናቋርጥ ሁል ጊዜ ቃለ እግዚአብሔርን በማስተዋል የምናዳምጥ ከሆነ አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ ልባችንን ይከፍታል፡፡ በመቀጠልም ወደ እውነተኛው የሕይወት አቅጣጫ ይመራናል፡፡ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ይመራችኋል” /ዮሐ.16፥13/ ብሎ ሐዋርያው እንደጻፈልን እውነት ወደ ሆነው ክርስቶስ ያደርሰናል፡፡

 

2. ምን እናድርግ? አሉ፡፡

ሰው የሚማረውን ከተረዳው በኋላ ቀጣዩ ጥያቄ ምን ላድርግ? ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ሊያሳድድ ወደ ደማስቆ ሲሔድ በመንገድ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት የሚያደርገው ሥራ እግዚአብሔርን ስላሳዘነው የመውጊያውን ጦር ብትቃወመው ለአንተ ይብስብሃል አለው፡፡ የምቃወምህ አንተ ማን ነህ? ብሎ ጥያቄውን አቀረበ የምታሳድደኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለው ታዲያ ምን እንዳደርግ ትወዳለህ” ብሎ ተናገረ፡፡ የምታደርገውን በከተማ የምታገኘው ሰው ይነግርሃል ብሎ አምላካችን ፈቃዱን ገለጠለት፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ ቅዱስ ጳውሎስ ሕይወቱ ተለውጦ እግዚአብሔርን እያገለገለ ኖረ፡፡ /ሐዋ.9፥1/

 

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ሐዋርያው ፊልጶስን ክርስቲያን እንዳልሆን የሚከለክለኝ ነገር ምንድን ነው?” /ሐዋ.8፥36/ ብሎታል፡፡

 

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጸ ንባቦች የሚያስረዱት እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ሰዎችን ሲያስተምር ከልባቸው የተነኩ ሰዎች የመጀመሪያው ግብረ መልሳቸው “ምን ላድርግ?” የሚል ነው፡፡

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እነዚህን አዲስ አማንያን “ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁም ይሠረያል” አላቸው፡፡ ስለዚህ ስረየተ ኀጢአትን ለማግኘት ንስሐ መግባት ያስፈልጋል፡፡

 

3. በጸሎት በረቱ

በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑት ምእመናን ንስሐ ገብተው ከተጠመቁ በኋላ በጸሎት ይተጉ ጀመር፡፡ ያላቸውን ሀብት ሸጠው በአንድነትና በኅብረት በጥሩ ልብ ይተጉ ነበር፡፡ ይላል እነዚህ ሁሉ ሒደቶች ለክርስትና ሕይወታችን ጥሩ የሆኑ ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

ወደ ክርስትና ሕይወት ለመመለስ እና በዚሁም ለመጽናት የአባቶቻችንን ሕይወት የሚያብራሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ይጠቅማል የእግዚአብሔርን ቃል የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው፡፡” /ዕብ.13፥7/ እንዳለው ሐዋርያው የቅዱሳን ሐዋርያትን፣ ሰማእታትን ጻድቃንን ሕይወት ስንመለከት በሃይማኖት እንበረታለን፡፡

 

ጠያቂያችን ውብ አንተ፡፡ ዋናው እና ትልቁ ነገር አንተ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ያለህ የልብ ፍላጎት ነው፡፡ ፍላጎትህ ስሜታዊ ሳይሆን ልባዊ ከሆነ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ያስተምርሃል፡፡ ስለዚህ ሳታቋርጥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ ቅዳሴውን አስቀድስ ቃለ እግዚአብሔርን ተማር መዝሙርን አዳምጥ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ ሊቃውንት አባቶችን ቅረባቸው ቅዱሳት መካናትን ተሳለም፡፡ የበለጠ ፍቅሩ እያደረብህ ጣእሙ እየገባህ ሕይወቱ እየናፈቀህ ይሔዳል፡፡ ሁሉም የሚሆነው በፈቃደ እግዚአብሔር ስለሆነ በሃይማኖት እንድትጸና አምላክህን በጸሎት ጠይቀው፡፡

 

እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔ ተማሩ በነፍሳችሁ ዕረፍት ታገኛላችሁ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” /ማቴ.11፥28-30/

 

ወስብሐት ለእግዚብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር፡፡

በዝቋላ ገዳም ደን ላይ ለደረሰው የእሳት አደጋ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ፡፡

መጋቢት 18/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን አብርሃም አንዳርጌ

•    እሳቱ መጥፋቱ የተገለጠ ሲሆን የእሳት አደጋን ለመከላከል የሚያስችል ቋሚ ጥናትም ተጀምሯል፡፡


በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ምሥራቃዊ ክፍል መቃጠሉን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ የሚገኙ ምእመናን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ፡፡

 

ቃጠሎውን ተከትሎ ከአካባቢው በአቅራቢያው ከሚገኙ ከተማዎች ምእመናን ወደ ቦታው በመሔድ እሳቱን ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በቦታው በመገኘት ቡራኬ ሰጥተው ምእመናን የሚያከናውኑትን ሥራ አበረታተዋል፡፡ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም የተመራ ልዑክ ሰኞ ቃጠሎው እንደተሰማ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በቦታው በመገኘት ጊዜያዊ የውኃ፣ የዳቦና የገንዘብ ድጋፍ ለገዳሙ እንዲደረግ በማስተባበር እሳቱን የማጥፋቱን ሥራ ለማከናወን ተችሏል፡፡

 

ባጠቃላይ በገዳሙ ላይ ለደረሰው ጉዳትና ለዘለቄታው መፍትሔ ጥናት ለማድረግ ከ171,860 ብር በላይ የሚጠጋ ገንዘብና ቁሳቁስ በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት ከአሜሪካ ማዕከል፣ ከአሜሪካ ማኅበረ ባለወልድ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነትና ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበ ሲሆን ከ85 ሺ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ጊዜያዊ የምግብና የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በቀረውና ወደፊትም ለቋሚ ፕሮጀክቶች ጥናት በሚሰበሰበው ገቢ በዝቋላና በአሰቦት ገዳማት ዘላቂ የመከላከልና የልማት ሥራ ለማከናወን የጥናት ሥራዎቹ መጀመራቸው ታውቋል፡፡

 

በወቅቱ ለተፈጠረው ችግር በሶ፣ ስኳር፣ ከ2000 ሊትር በላይ ውኃ፣ 16 ገጀራና 15 ዶማ ጨምሮ ሌሎች እርዳታዎችን በመሰብሰብ እንዲሁም ከ20 ኩንታል ጤፍ ጋር ለገዳሙ ገቢ ተደርጓል፡፡ ይህም በገዳሙ ውስጥ ለተፈጠረው የምግብ እጥረት መፍትሔ እንደሚሰጠው ታምኖበታል፡፡

 

እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት የማኅበረ ቅዱሳን አባላትን ጨምሮ በናዝሬት ማአከል አስተባባሪነት ሰባት አውቶብስ የአዳማ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የደብረ ዘይት አየር ኀይል አባላት የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የፌደራል ልዩ ኀይል፣ የአዲስ አበባ፣ አድማ፣ ደብረ ዘይት፣ ሞጆና አካባቢው ምእመናን ቦታው ድረስ በመገኘት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡

 

በዚህም እሳቱን በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለ ሲሆን ባጠቃላይ በገዳሙ ላይ ዘላቂ ልማት እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ዘላቂ የመከላከልና የልማት ሥራዎችን ለመጀመር በትናንትናው ዕለት አምስት ባለሙያዎች የያዘ የጥናት ቡድን ወደ ዝቋላ ገዳም የላከ ሲሆን ከገዳማውኑ ጋር በመወያየት በሚወሰነው አቅጣጫ መሠረት ሥራው ይጀመራል፡

 

በዚሁ አጋጣሚ ዘላቂ አደጋን የመከላከልና የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የምትፈልጉ ሁሉ የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናትና አብነት ትምህርት ቤቶች መርጃና ማቋቋሚያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ፣ የአካውንት ቁጥር 01730604664000፣ በመጠቀም የምትችሉ መሆኑነ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

ጸሎት

መጋቢት 18/2004 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ጸሎት ጸለየ፡- ለመነ፣ ጠየቀ አማለደ፣ ማለደ ካለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ነው፡፡ ጸሎት ማለት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እግዚአብሔርን ማመስገን መለመን፣ መጠየቅ፣ መማለድ፣ መማፀን ነው፡፡ “ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር፡፡” አባታችን አዳምም ከመላእክት ተምሮ በየሰዓቱ ይጸልይ ያመሰግን ነበር፡፡ ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ አዳም በመጣ ጊዜ ጸሎት እያደረገ ስለነበር ዲያብሎስን ድል ነሥቶታል ሔዋንን ግን ሥራ ፈትታ እግሯን ዘርግታ ስለአገኛት ድል ነስቷታል፡፡

ጸሎት ሰማእታት ከነደደ እሳት፣ ከተሳለ ስለት፣ ከአላውያን መኳንንት፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ከዲያብሎስ ተንኮል እና ሽንገላ ዲያብሎስ በእነርሱ ላይ ከአጠመደው አሽከላ የዳኑበት ጋሻ ነው፡፡ ኤፌ.6፥10 21 ጸሎት፣ ሰው አሳቡን ለእግዚአብሔር የሚገልጥበት እግዚአብሔርም የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው፡፡

የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁ ምቱ ይከፈትላችኋል” የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው ማቴ.7፥7

ጸሎት፡- በሦስት ክፍል ይከፈላል

  1. ጸሎተ አኰቴት

  2. ጸሎተ ምህላ

  3. ጸሎተ አስተብቊዖት

  1. ጸሎተ አኰቴት፡- ማለት እግዚአብሔርን ከሁሉም አስቀድሞ ስለተደረገልን ነገር በማመስገን የሚጀመር ጸሎት ነው ይህም ዓይነት ጸሎት የቅዱስ ባስልዮስን የምስጋና ጸሎት የመሰለ ነው፡፡

“ነአኲቶ ለገባሬ ሠናያት ላዕሌነ እግዚአብሔር መሐሪ”

“ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ ይቅርባይ እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን” ይልና ምክንኀያቱን ሲገልጥ ጠብቆናልና፥ አቅርቦናልና፥ ወደ እርሱም ተቀብሎናልና፥ እስከዚችም ሰዓት አድርሶናልና” ይላል፡፡ /ሥርዐተ ቅዳሴ/ ይህ ጸሎት የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኰቴት/ ይባላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን የምስጋና ጸሎት ለፊልጵስዮስ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው “ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” ይላል፡፡ ፊል.4፥6 ዳግመኛም “ስለእናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመስግነዋለሁ” 1ቆሮ.1፥4 ብሎ ከመለመን አስቀድሞ እግዚአብሔርን ማመስገን አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፡፡ በዚህ መሠረት ሰው የተደረገለትን በጎ ነገር ሁሉ በማሰብ ፈጣሪውን ማመስገን ከማመስገንም ቀጥሎ የሚያስፈልገውን ከፈጣሪው መለመን አስፈላጊ ነው፡፡

ከቅዱስ ጳውሎስ የምንማረው ለእኛ ስለተደረገልን ብቻ ማመስገንን አይደለም፤ ሌሎች ስለተደረገላቸውም ማመስገን ተገቢ መሆኑን እንጂ፡፡ “ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ሲል ለወገኖቹ ስለተደረገላቸው በጎ ነገር በደስታ ማመስገኑ ነው፡፡ ክርስትና ማለት ለእኔ ብቻ ማለት ሳይሆን ለሌሎችም መኖር፣ ለሌሎች በተደረገው የእግዚአብሔር ስጦታም ደስ መሰኘት ነው፡፡ ይህን የምስጋና ጸሎት /ጸሎተ አኮቴት/ ብዙ አባቶች፣ እናቶች ተጠቅመውበታል፡፡ ለምሳሌም ያህል ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን መመልከት እንችላለን፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ እግዚአብሔር ያደረገላትን በጎ ነገር ስትመሰክር “እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ በጎበኘን ጊዜ እንዲህ አደረገልኝ” ብላለች፡፡ ሉቃ.1፥25 እግዚአብሔር ጎበኘኝ ብላ ቸርነቱን አደረገለኝም በማለት የተደረገላትን መልካም ስጦታ ዮሐንስን መጽነሷን ገልጣ አመስግናለች፡፡ ዘካርያስም እንዲሁ አመስግኗል፡፡ “ያን ጊዜም አፉ ተከፈተ አንደበቱም ተናገረ እግዚአብሔርንም አመሰገነ” ሉቃ.1፥65 “ከዚህ ጊዜ ያደረስከኝ፥ ከደዌ የፈወስከኝ፥ ዮሐንስን የሰጠኸኝ ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል በመቀጠልም ይቅር ያለን ለወገኖቹም ድኅነትን ያደረገ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን ከባሪያው ከዳዊት ቤት የምንድንበትን ቀንድ አስነሣልን፡፡” ሉቃ.1፥68 በዘካርያስ ጸሎት ውስጥ ምስጋናውን አስቀድሞ ትንቢቱን አስከትሎ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምስጋናውና ትንቢቱ አምላክ ለእኛ ያደረገው የቤዛነቱን ሥራ በመግለጥ ሲያመሰግን እንመለከታለን፡፡

2. ጸሎተ ምህላ፡- ጸሎተ ምህላ ስለፈውሰ ሕሙማን …… ስለ ሀገርና ስለነገሥታት ስለ ጳጳሳት፣ ካህናት ዲያቆናት፣ ምዕመናን ሕይወት ቸነፈር፣ ጦርነት፣ ረሀብ፣ ድርቅ ወይም ሌላ አስጊ ነገር በሆነ ጊዜ በብዛት፣ በማኅበር የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡ የምህላ ጸሎት ሲጸለይ በእስራኤል ላይ ቸነፈር በተነሣ ጊዜ አሮን በሽተኞን ባንድ ወገን ጤነኞችን ባንድ ወገን አድርጎ የክህነት ልብሱን ለብሶ ማዕጠንተ ወርቁን ይዞ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን አስበህ የወገኖችህን ኀጢአት ይቅር በል”  እንደጸለየላቸው ነው፡፡ ዘኁ.16፥46-50

ዛሬም ካህናት ከጠቀስናቸው አስጊ ነገሮች ማንኛውም በሀገር ላይ ቢመጣ ወደ ሀገር እንዳይገባ ገብቶ ቢሆን ከፍ ያለ ጉዳት እንዳያመጣ የክህነት ልብስ ለብሰው ማዕጠንቱ ይዘው ሥዕለ ማርያም፣ መስቀል አቅርበው ማኅበረ ክርስቲያንን ሰብስበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን “ስለእኛ ከድንግል ማርያም መወለድህን ስለእኛ መሠቀል መሞትህን አስበህ የህዝብን ኀጢአት ይቅር በል ከመዓት ወደ ምሕረት ተመለሰ” እያሉ በምህላ ይጸልያሉ፡፡

የምህላ ጸሎት መአትን መቅሰፍትን ይመልሳል ጦርን፣ ቸነፈርን ያስታግሳል መሠረቱም፡፡
“ጾም ለዩ ምህላ ስበኩ” ያለው ቃል ነው፡፡ ይህ ጸሎት በሰላም ጊዜ ሰላሙ ዘላቂ እንዲሆን በጦርነት ጊዜ ለመከላከያነት ዋና መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አጥብቀን ልንከተለው ይገባል፡፡

የምህላ ጸሎት ነገሠታት ከዙፋናቸው ወርደው ወንድ ሙሽራ ሴት ሙሽራ ከጫጉላቸው፣ ከመጋረጃቸው ለምግብ የደረሱ ልጆች ከምግብ ለምግብ ያልደረሱ ከጡት ተከልክለው ሕዝብ ሁሉ ምንጣፍ ለብሰው አመድ ነስንሰው የሚጸልዩት ከፍተኛ ጸሎት ነው ኢዩ.2፥12-18፣ ዮና.3፥5

3.    ጸሎተ አስብቊዖት

ይህ ጸሎት አንድ ሰው ስለሚፈልገው ነገር ቦታ ለይቶ ሱባኤ ገብቶ የሚጸልየው ጸሎት ነው፡፡ ይህ ጸሎት በተለይ ጣዕመ ጸጋን በቀመሱ በተባሕትዎ፣ በምናኔ በገዳም በሚኖሩ አበው ዘንድ የተለመደና የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ወጣንያን እግዚአብሔርን ጠይቀው አድርግ አታድርግ የሚል መልስን አይጠብቁም፡፡ ፍጹማን አባቶች ግን እግዚአብሔር ጠይቀው አድርግ ወይም አታድርግ የሚል ፈቃደ እግዚአብሔርን ሳይቀበሉ የሚያደርጉት ነገር የለምና ቦታ፣ ጊዜ ወስነው ፈቃደ እግዚአብሔር ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ጸሎተ አስተብቊዖት ይባላል፡፡ ይህም ማለት መላልሶ ደጋግሞ ያለ ዕረፍት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚደረግ ጸሎት ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቁ መቃርስ ዓለምን ዞሮ ለመጎብኘት ለተከታታይ አምስት ዓመታት እግዚአብሔርን ከለመነ በኋላ እየዞረ መካነ ቅዱሳንን እንዲጎበኝ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አግኝቷል በዚህም ከእርሱ ከገድል በትሩፋት የሚበልጡ መናንያን በማግኘቱ መነኮሳትማ እነርሱ እንጂ እኔ ምንድን ነኝ? እያለ ራሱን እየወቀሰ እንደተመለሰ በመጽሐፈ መነኮሳት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን “መስተበቊዕ” የሚባል የጸሎት ክፍል፡፡ አለ ይህ ጸሎት በካህናት አባቶቻችን ስለሙታን፣ ስለሕያዋን፣ ስለነገሠታት፣ ስለ ጳጳሳት ስለ ንዑሰ ክርስቲያን፣ ስለ ምእመናን መባዕ ስለሚያቀርቡ ስለነጋድያን፣ ስለዝናም ስለ ወንዞች የሚጸለይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጸሎት ክፍል ነው፡፡

ጠቅላላውን በቤተ ክርስቲያን የሚጸልዩ ጸሎታት ጸሎተ ፍትሐት፣ ጸሎተ ተክሊል፣ ጸሎተ ህሙማን፣ ጸሎተ ቅዳሴ፣ ጸሎተ ሰዓታት፣ የግል ጸሎት፣ የማኅበር ጸሎት እነዚህ ሁሉ ከላይ ከዘረዘርዓቸው ሦስቱ የጸሎት ክፍሎች አይወጡም፡፡ ከጸሎተ አኰቴት ከጸሎተ ምህላ፣ ከጸሎተ አስተበቊዖት ይመደባሉ፡፡ እነዚህን ጸሎታት በሰቂለ ኅሊና በአንቃዕድዎ /ዐይንን ወደ እግዚአብሔር በማንሳት/ መጸለይ ታላቅ ዋጋ የሚያሰጥ ከሰይጣን ወጥመድ የሚታደግ ሕይወትን የሚስተካከል ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቅ አጋንንትን የሚያርቅ ኀይለ እግዚአብሔርን ለሚጸልየው የሚያስታጥቅ መላእክትን የሚያስመስል ነው፡፡

እኛም ሰውነታችን ከበደል ልቡናችን ከቂም ከበቀል እንዲሁም ከተንኮል ንጹሕ አድርገን ብንጸልይ እንጠቀማለን ጸሎታችን ተሰሚ ልመናችንና ጩኸታችን ግዳጅ ፈጻሚ ይሆናል፡፡ የአባቶቻችን ጸሎት የተቀበለ እግዚአብሔር አምላካችን ጸሎታችንን ይቀበለናል፡፡

ይቆየን

በቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ላይ ያተኮረ መድረክ ሊዘጋጅ ነው፡፡

መጋቢት 17/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር አዘጋጅነት መጋቢት 29 ቀን 2004 ዓ.ም በቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ላይ ያተኮረ የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል እንዳስታወቀው በዚህ የጥናት ጉባኤ የቅዱስ ያሬድ የዜማ አስተምህሮ ክፍል የሆነው የምዕራፍ ሚናና፣ አጠቃቀም በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ታውቋል፡፡

ጥናቱን የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ ትምህርትና የመምህራን ሙያ ልማት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ውቤ ካሣዬ ሲሆኑ ጥናቱን በመምራትና በማወያየት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዳሚ መምህር በዶ/ር ሥርግው ገላው እንደሚሳተፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

በመርሐ ግብሩም በዘመናችን እየታየ ባለው የዜማ ችግር ላይ መፍትሔ ጠቋሚ የሚሆኑ ሀሳቦች በማንሣት፣ የሚታዩትን ችግሮች የችግሮቹንም ምንነት በመለየት ለዜማችን መሠረታዊ ችግር የሆኑትን በመፈተሽ፣ በመፍትሔው ላይ የጋራ መግባባትን መፍጠር የሚያስችል መሆኑን ከጥናትና ምርምር ማእከሉ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

 

በጉባኤው ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆችና፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ዘማርያንና ሰባኪያን እንዲሁም ከሙያው ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚካሔድ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ላይ ምእመናን እንዲገኙ የምርምር ማእከሉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡