Picture3

ማኅበረ ቅዱሳን ሐዋርያዊ አገልግሎት በአርሲ ሀገረ ስብከት አካሔደ

ታኅሣሥ 20/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሐዋርየዊ Picture3አገልግሎት በአርሲ ሀገረ ስብከት ከኅዳር 29/2004 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 10/2004 ዓ.ም ለ11 ተከታታይ ቀናት በተለየዩ ወረዳዎች አካሔደ፡፡ 27 አባላት የተሳተፉበት ሐዋርያዊ አገልግሎት በተመረጡ 6 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በአሰላ ከተማ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያፈራቻቸው የማኅበረ ቅዱሳን ሰባኪያነ ወንጌል አማካይነት በአውደ ምሕረት ላይ ለምእመናን ሰፋ ያለ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በማኅበሩ መዝሙር ክፍል አባላት አማካይነት ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩትን የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቀ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

በአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ማኅበረ ቅዱሳን በያዘው እቅድ መሠረት የሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎት እንዲካሔድ በመፍቀድና በመከታተል እንዲሁም አባታዊ ምክራቸውንና ቡራኬ በመለገስ፤ በጸሎት በማገዝ አገልግሎቱ የተሳካ እንዲሆን አባታዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ6ቱ ወረዳዎች ማለትም በአሳሳ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፤ በሳጉሬ ደብረ ገነት ልደታ ለማርያም፣ በበቆጂ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ በኢተያ ቅዱስ በዓለወልድ፤ በሁሩታ ደብረ መዊዕ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በአሰላ ደብረ መድኃኒት መድኀኔዓለም እና በዴራ ደብረ መድኀኒት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያናት በእያንዳንዳቸው ለ2 ቀናት /በበቆጂ አንድ ቀን ብቻ/ የቆየ የወንጌል ትምህርትና ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል፡፡ አገልግሎቱም ምዕመናን በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲቆሙ ከተለያዩ ኢ አማኒያን የኑፋቄ ትምህርት እንዲጠበቁ፤ ከእነሱም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትሻውን አገልግሎት እንዲያበረክቱ ፤ንስሐ ገብተው የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የመንግሥቱ ወራሾች ይሆኑ ዘንድ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ላይ ያተኮረ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም በሳጉሬ ቅድስት ሥላሴ፣ በአሰላ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በቅድስት ሥላሴ /ቤተ ሥላሴ/ ቤተ ክርስቲያናት ቅዳሜና እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ መምህራን ለምእመናን ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

በአገልግሎት ዙሪያ ያነጋገርናቸው ምእመናን በሰጡት አስተያየት እምነታቸውን ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም ከመናፍቃን Picture2የኑፋቄ ትምህርት ይጠበቁ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና መሠረት ያደረገ ትምህርት በቀጣይነት እንዲሰጥ፤ እንዳይቋረጥባቸው ተማጽነዋል፡፡ “በሕፃንነቴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እሰማቸው የነበሩ መዝሙራትን እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ እባካችሁ እኛንም ልጆቻችንም ከዳንኪራ ባልተናነሰ በስመ መዝሙር ከሚቀርቡና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ካልጠበቁ ጩኸቶች ታደጉን፡፡” ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ውዥንብር ውስጥ ይከታቸው የነበረው የያሬዳዊ ዜማ አቀራረብ የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል ያቀረበውን ከተመለከቱ በኋላ ትክክለኛውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቁትን ለመለየት እንደረዳቸውና ማኅበረ ቅዱሳን እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ “የማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን በሚዘምሩበት ወቅት በተለይ ሴቶች እኅቶቻችን ሲዘመሩ የሙሴ እኅት ማርያም እስራኤላውያን ባህረ ኤርትራን በተሻገሩበት ወቅት ከበሮ ይዛ እግዚአብሔርን ያመሰገኘችበት ዝማሬ አስታወሰኝ፡፡ ሰናይ እገሪሆሙ ለእለ ይእዜኑ ሰናየ ዜና /ኢሳ.52 እንዲል የምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮች አመጣጥ መልካም ነው፡፡ መልካም ዜና የሚናገሩ ናቸውና፡፡”በማለት በአገልግሎቱ በመደሰት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡በተጨማሪም ከየማዕከላቱ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በሐገረ ስብከቱ 27 ወረዳዎች ውስጥ 500 ቤተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በሁሉም ወረዳዎች በመንቀሳቀስ 15 የወረዳ ማእከላት 11 የግንኙነት ጣቢያዎችና 1 ልዩ ማእከል በማቋቋም ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የተካሔደው ሐዋርያዊ የአገልግሎት መርሐ ግብር ኅዳር 29/2004 ተጀመሮ በ6 ወረዳዎችና በአሰላ ከተማ አከናውኖ ታኅሣሥ 10/2004 ዓ.ም በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ሲሆን በአጠቃላይ ከ20000 በላይ ምእመናን በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ተከታትለዋል፡፡

St.Gebrieale 1

በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል

ታኅሣሥ 18/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
St.Gebrieale 1

ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም  አነሣሁ” አለና አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኀይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ  ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፡5-9)

 

ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ መልአክ ግርማ የአምላክን ግርማ ይመስላል፡፡ ይህን ለመረዳት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮቱ ለወንጌላዊው ዮሐንስ የተገለጠበትን መገለጥ መመልከት በቂ ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይ ስለተመለከተው የክርስቶስ ግርማ ሲናገር፡- “ከኋላዬም እንደ መለከት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ሰማሁ፡፡…የሰው ልጅ የሚመስልን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ልብስ የለበሰ ፣ ወገቡንም በወርቅ ዝናር የታጠቀ ነበር፡፡ ራሱና የራስ ጠጉሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡ እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙህ ውኃ ድምፅ ነበረ፡፡”… ባየሁትም ጊዜ ከእግሩ ሥር ወደቅሁ አንደ ሞተ ሰው ሆነሁ” አለ፡፡(ራእይ.1፡2-17) በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ቅዱስ ገብርኤል በግርማው አምላኩን እንደሚመስል አንረዳለን፡፡  የስሙም ትርጓሜ የሚያስዳው ይህን እውነታ ነው፡፡ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነውና፡፡

 
 
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች” አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ”(ዳን.10፡13) ብሎ በተናገረው ንግግሩ በመላእክት ላይ የተሾሙ ሌሎች አለቆች እንዳሉ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በቅዱሳን መላእክት ዘንድ ስላሉት ነገዶች ሲገልጽ “… በሰማይ ያለውን በምደር ያለውን የሚታየውንምና የማይታየውን መናብርትም ቢሆኑ አጋእዝትም ቢሆኑ መኳንንትም ቢሆኑ ቀደምትም ቢሆኑ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ” (ቈላ.1፡16)በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡ ከዚህ ተነሥተን መላእክት በተለያዩ  ዐበይት ነገዶች የተከፈሉና ለእያንዳንዱም ነገድ የራሱ የሆነ አለቃ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእነዚህ ዐበይት የመላእክት ነገዶች መካከል አንዱ በሆነው አርባብ (አጋእዝት ወይም ጌቶች) /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/ በሚባለው ዐቢይ ነገድ ላይ የተሾመ ሲሆን ከበታቹም የሚመራቸው ዐሥር ነገደ መላእክት አሉ፡፡
 
kulubi Gabriel
ቅዱሳን መላእክት በቅዱስ ሚካኤል ፊት አውራሪነት የሰው ልጆች ጠላት የሆነውን ዲያብሎስን ተዋግተው ድል ከመንሳታቸው አስቀድሞ ቅዱስ ገብርኤል እንደ አምላክ ሊመለክ የወደደውን ሳጥናኤልን በመቃወም“አይዞአችሁ ፈጣሪያችን ፈጥሮ አይጥለንምና አስክናገኘው፣ እስክናውቀው ድረስ በያለንበት እንቁም፡፡” (አክሲማሮስ ገጽ.35) በማለት መላእክት ያረጋጋ መልአክ ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በሰማያት የሳጥናኤል ትዕቢትና ውድቀት ምን እንደሚመስል ሲጽፍልን “አንተ በንጋት የሚወጣ አጥቢያ ኮከብ ሆይ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! ወደ  አሕዛብ መልእክትን የላክ አንተ ሆይ እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቀጠቀጥህ! አንተም በልብህ፡- ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደረጋለሁ፤… በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ ዛሬ ግን ወደ ሲኦል ትወድቃለህ፤ ወደ ምደር ጥልቅም ትወርዳለህ”(ኢሳ.14-16)በማለት ገለጠልን፡፡ ወደ ምድር የጣሉት በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት እነ ቅዱስ ገብርኤል ነበሩ፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ገብርኤል “እነሆ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ” እንዲሁም “ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም” አለ፡፡(ዳን.10፡13፣21)
 
ቅዱስ ገብርኤል በብሉይ ኪዳን በቅድስና ሕይወት ለተጋውና በገዢዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያደረበት ሰው(ዳን.5፡11)ተብሎ ለተመሰገነው ለነቢዩ ዳንኤል ማስተዋልንና ጥበብን የሰጠ መልአክ ነበር፡፡ ለዚህ ነቢይ እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን ከሰይጣንና ከሞት ባርነት ነጻ ሊያወጣቸው ሰው እንደሚሆንና ሰማይንና ምድርን አሳልፎ በቅዱሳን ላይ ነግሦ እንደሚኖር በምሳሌ ገልጾ ያስተማረው መልአክ ነው፡፡(ዳን.9፡21-22) አሁንም ነቢዩ ዳዊት “አቤቱ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ብፁዕ ነው፡፡ በልቅሶ ሸለቆ በወሰንኸቸው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና፡፡”(መዝ.83፡5-6)እንዳለው በቅድስና ሕይወት በመጽናታቸው ምክንያት ቅዱስ ገብርኤል መምህር የሆናቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ የእኛ እውቀት በሰማያት ከትመው ካሉት ቅዱሳን መላእክት እውቀት ጋር ሲነጻጸር እኛን እንደ ሕፃናት ያደርገናል፡፡ እኛ የእነርሱን እውቀት ገንዘባችን የምናደርገው በትንሣኤ ነው፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ “ዛሬ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፡፡ አሁን በከፊል ኋላ ግን እንደተገለጠልኝ መጠን ሁሉን አውቃለሁ”(1ቆሮ.13፡12)ብሎ አስተማረን፡፡ ስለዚህም እውቀታችን የተሟላ እንዲሆንና ሰይጣንን ለመቃወም እንድንበቃ የቅዱሳን መላእክት የእውቀት ድጋፍ በእጅጉ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ከእኛ ይልቅ ሳጥናኤልን የሚያውቁት እነርሱ ናቸውና፡፡ እንዲህም ስለሆነ ጌታችን በእውቀታቸው እኛን እንዲረዱን ለእያንዳንዳችን  ጠባቂ መልአክትን ሰጠን፡፡(ማቴ.18፡10፤ሉቃ.13፡6-9)
 
ቅዱስ ገብርኤል ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ለተጠሩት መንፈሳዊ እውቀቱን የሚያካፍላቸው መልአክ ብቻ አይደለም፤ ለእግዚአብሔር በመገዛታቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክም ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሁሉ ሲያስገዛለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ  አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም  የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም አወስዳቸዋለሁ፤ከእኔም የሚያመልጥ የለም የሚቃወመኝም የለም፡፡”(ኢሳ.10፡13-14) ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ ዱራ(አዱራን) በሚባል ስፍራ ላይ አቆመው፡፡ በግዛቱ በልዩ ልዩ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉትን ሹማምንቱንና ገዢዎችን ሰበሰባቸው፤ “የመለከትና የእንቢልታ የመሰንቆና የክራር የበገናና የዋሽንትን የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ወድቃችሁ ንጉሥ ናብከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፡፡ ወድቆም ለማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣል” ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን አዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ የመለከቱና የእንቢልታው እንዲህም የዘፈን ድምፅ በተሰማ ጊዜ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡
 
በባቢሎን አውራጃዎች ላይ የተሾሙ አዛርያ(ሲድራቅ)፣ አናንያና(ሚሳቅ) ሚሳኤል(አብደናጎ) ግን ንጉሥ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡ ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ነገሩት፤ ንጉሥም እጅግ ተቆጥቶ ወደ እርሱ አስጠራቸው፡፡ እርሱ ላቆመው ለወርቅ ምስል ያልሰገዱ እንደሆነ እጅና እግራቸውን ታስረው ወደ እቶን እሳቱ እንደሚጣሉ አስጠነቀቃቸው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅ ግን  “ናብከደነፆር ሆይ! በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አንፈልግም፡፡ ንጉሥ ሆይ! እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፣ ከሚነደውም ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፤ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልክትህን አንዳናመልክ፣ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” ብለው መለሱለት፡፡ የንጉሥ ናብከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእነ ማዕረግ ልብሳቸው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው ትእዛዝን አስተላለፈ፡፡ ትእዛዙ አስቸኳይ ነበርና እነርሱን ወደ እሳቱ የጣሏቸውም ኃያላን በእሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሞቱ፡፡ እንዲህ ሲሆን ሳለ ግን ሠልስቱ ደቂቅ ወደ አምላካቸው “በፍጹም ልባችን እናምንሃለን፣ እንፈራሃለን፣ አታሳፍረን እንጂ ገጸ ረድኤትህንም እንፈልጋለን፡፡” እያሉ ይጸልዩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታቸውን ተቀበለ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም እስራታቸውን ፈታ፤ እሳቱን እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠልስቱ ደቂቅም መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይክበር ስምህም ለዘለዓለም የተመሰገነና የከበረ ነው” በማለት አመሰገኑት፡፡
 
ንጉሥ ናብከደነፆርም ሠልስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ከእነርሱ ጋር የሰው መልክ ያለው ነገር ግን አምላክን የሚመስል መልአክ ተመለከተ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሊቀ ካህናቱን ቀያፋን ፊቱን ጸፍቶ አፉን ከፍቶ “ሕዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡምን”(ዮሐ.11፡49) ብሎ እንዳናገረው እንዲሁ ናብከደነፆርንም “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ እንዲናገር አደረገው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅን መልክ ያለው ያለው በኋላም መልአክ ብሎ የተናገረለት ቅዱስ ገብርኤልን ነበር፡፡ እርሱ ስለመሆኑ ለነቢዩ ዳንኤል በተገለጠበት ግርማ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡
ናብከደነፆርም ወደ እሳቱ እቶን በመቅረብ እነዚህ ብላቴኖችን “እናንተ የልዑል አምላክ ባሮች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው፡፡” እነርሱም ከእሳቱ ወጡ ሹማምንቱና መኳንንቱ፣ አማካሪዎችና የአገር ገዢዎች ሁሉ እሳቱ በእነዚህ ብላቴኖች ላይ አንዳች አቅም እንዳልነበረው፣ ከጠጉራቸው ቅንጣት አንዱን እንኳ እንዳላቃጠለው፣ ሰናፊናቸውም እንዳልተለወጠ፣ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው ተመለከቱ፡፡ ንጉሥ ናብከደነፆርም መልአኩን ልኮ ያዳናቸውን የእነዚህን ቅዱሳንን አምላክ አመሰገነ፡፡ በእነርሱ አምላክ ላይም የስድብን ቃል የሚናገር ሰው እንደሚገደልና ቤቱም የጉድፍ መጣያ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ፡፡ አዛርያ አናንያ ሚሳኤልም በንጉሡና በሹማምነቱ ዘንድ ሞገስ አገኙ በክብርም ከፍ ከፍ አሉ፡፡(ዳን.3 በሙሉ)
 
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን መንጎቹዋ የእምነትን ፍሬ ከእነዚህ ብላቴኖች ተምረው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑና የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት እንዲረዱ በታኅሣሥ 19 ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እምነት በድርጊት ሊታይ የሚገባው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምናለሁ የሚል ሁሉ ካመነበት ጊዜ አንስቶ ክርስቶስን መስሎ ለመኖር ሊተጋና መስሎ ሊመላለስ ይገባዋል፡፡ በሠልስቱ ደቂቅ  የታየው እምነት በአንድ ጀምበር የተገነባ እምነት ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ በአንድ እግዚአብሔር ታምነው በቅድስና ሕይወት በመመላለስ የመጣ እምነት ነው፡፡ እነዚህ ብላቴኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን የድል አክሊል ተስፋ አድርገዋልና አርባ ዘጠኝ ክንድ ያህል የነደደውን የእሳት እቶን አላስፈራቸውም፤ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸው ጽኑ እምነት በእሳት ተቃጥለው ለመሞት እንኳ አስጨከናቸው፡፡ እንዲህም ሆነው በመገኘታቸው በእምነታቸው እግዚአብሔርን ደስ አሰኙት፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ባለሟሉን ቅዱስ ገብርኤልን በመላክ ከእሳቱ እቶን ታደጋቸው፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ እምነት ሰዶማውያን ገዢዎች በተነሡባት በአሁኑዋ ዓለም በእኛ ክርስቲያኖች ላይ ሊታይ የሚገባው እምነት ነው፡፡ እነዚህ ገዢዎች ኢኮኖሚያዊ ጡንቻቸውን ታምነው፣ ነፍሳችን በእነርሱ እጅ የተያዘች መስሎአቸው፣ በእኛ ላይ ሰይጣናዊ ሕግጋትን ሊጭኑብን ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች የምድሪቱ ገዢዎች እኛን ለማስፈራራት ሲሉ በእኛ ላይ ያነደዱትን እሳት በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት እንደሚያጠፋልን በእግዚአብሔር ታምነን በእምነት ልንቃወማቸው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእነዚህ ከክፉ ሰዶማውያን ገዢዎች ጥፋት ምድራችንን ይታደጋት፤ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ጸሎት ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
Sebe

ሕንፃ ሰብእ ወይስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይቀድማል?

ታኅሣሥ 16/2004 ዓ.ም

ትርጉም፡- በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

Sebe

“የጌታን ቤት በወርቅ ወይም በብር ባለማስጌጣቸው ከጌታ ዘንድ በሰዎች ላይ የሚመጣ አንዳች ቅጣት የለም”


ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴ.14፥23 ያለውን ንባብ በተረጎመበት ድርሳኑ ከሰው የሚቀርብላቸው ከንቱ ውዳሴን ሽተው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስጌጡ የሚታዩ ነገር ግን እንደ አልዓዛር ከደጃቸው የወደቀውን ተርቦና ታርዞ አልባሽና አጉራሽ ሽቶ ያለውን ደሃ ገላምጠው የሚያልፉትን ሰዎች ይገሥፃል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን አንዳንድ ባለጠጎች ደሃ ወገናቸውን ዘንግተው ከእግዚአብሔር ዋጋ የሚያገኙ መስሎአቸው ቤተ ክርስቲያንን የወርቅና የብር ማከማቻና መመስገኛቸው አድርገዋት ነበር፡፡ ይህ ጥፋት በአሁኑ ጊዜ መልኩን ቀይሮ በሕንፃ ኮሚቴ ሰበብ ምዕመኑን ዘርፎ የራሳን ሀብት ማከማቸት በአደባባይ የሚሰማና የሚታይ ምሥጢር  እየሆነ ነው፡፡ እነዚህን በዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከተነሡት ጋር ስናነጻጽራቸው እነዚያ ከእነዚህ በጣም ተሸለው እናገኛቸዋል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እነዚያን እንዴት ብሎ እንደሚወቅሳቸው እንመልከትና በዚህ ዘመን የሚፈጸመው ዐይን ያወጣ ዘረፋ ምን ያህል አስከፊ ቅጣትን ሊያመጣ እንደሚችል እናስተውለው፡፡

… ሰው ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናትንንና ረዳት ያጡ ባልቴቶችን ከልብስ አራቁቶ በወርቅ የተለበጠ ጽዋ ለቤተ ክርስቲያን በማበርከቱ ብቻ የሚድን እንዳይመስለው ይጠንቀቅ፡፡ የጌታን ማዕድ ማክበር ከፈለግህ ስለእርሷ የተሠዋላትን ነፍስህን ከወርቅ ይልቅ ንጹሕ በማድረግ በእርሱ ፊት መባዕ አድርገህ አቅርባት፡፡ ነፍስህ በኃጢአት ረክሳና ጎስቁላ አንተ ለእርሱ የወርቅ ጽዋ በማግባትህ አንዳች የምታገኘው በረከት ያለ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህም በወርቅ የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትን መስጠት የእኛ ተቀዳሚ ተግባር አይሁን፡፡ ነገር ግን የምናደርገውን ሁሉ በቅንነት እናድርግ እንዲህ ከሆነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ዋጋ ታላቅ ይሆንልናል፡፡ ሥራችንን በቅንነት መሥራታችን ከወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረ ዋጋ አለው፤ እንዲህ በማድረጋችንም ከቅጣት እናመልጣለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን የወርቅና የብር ማምረቻ /ፋብሪካ/ ወይም ማከማቻ አይደለችም፡፡ ነገር ግን የመላእክት ጉባኤ እንጂ፡፡ ስለዚህም የነፍሳችንን ቅድስና እንያዝ አምላካችንም ከእኛ የሚፈልገው ይኼንኑ ነው፡፡ ስጦታችን ከነፍሳችን ይልቅ አይከብርም፡፡

 

 

ጌታችን ከሐዋርያት ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ሥጋውን በብር ዳሕል ደሙንም በወርቅ ጽዋ አድርጎ አልነበረም ያቀረበላቸው፡፡ ነገር ግን በማዕዱ የነበሩት ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ እጅግ የከበሩና ማዕዱም ታላቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማዕዱ ሲቀርብ ሐዋርያት በመንፈስ ነበሩና፡፡ ለጌታችን ቅዱስ ሥጋና ደም ተገቢውን ክብር መስጠት ትሻለህን? አስቀድመህ ደሃ ወገንህን አስበው፥ መግበው፥ አልብሰው፥ የሚገባውን ሁሉ አድርግለት፡፡ እንዲህ ስል ቅዱስ ሥጋውን አታክብረው ማለቴ አለመሆኑን ልትረዳኝ ይገባሃል፡፡ አንተ በዚህ ማዕድ ቅዱስ ሥጋውን በሐር ጨርቅ በመክደንህ ያከበርከው ይመስልሃል፡፡ ነገር ግን ይህን አካል /ቅዱስ ሥጋውን/ በሌላ መንገድ አራቁተኸዋል፤ ለብርድም አጋልጠኸዋል፡፡ጌታችን ኅብስቱን አንሥቶ “ይህ ሥጋዬ ነው” ሲለን “ስራብ አላበላችሁኝም ስጠማ አላጠጣችሁኝም” ያለው አካሉን አይደለምን? ስለዚህም ጌታችን “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁ ለእኔም አላደረጋችሁትም” በማለትም ጨምሮ አስተማረን፡፡

ድሆች ወገኖቻችን ለመኖር የሚያስችላቸውን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ሁሉ ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡ ይህን ማድረግ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ግዴታችን ነው፡፡ በዚህ መልክ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእኛ እንደሚሻው በመሆን ሕይወታችንን ቅዱስ በማድረግ ወደ ማዕዱ እንቅረብ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩን ሊያጥበው በቀረበ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “እግሬን በአንተ ልታጠብ አይገባኝም” በማለት ተከላክሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ የእርሱ መከላከል ከአክብሮት ይልቅ ታላቅ በረከትን ሊያሳጣው የሚችል መከላከል እንደሆነ አልተረዳም ነበር፡፡ ቢሆንም ከጌታ ዘንድ “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” የሚለውን ቃል ሲሰማ እርሱ ያሰበው ነገር ተገቢ እንዳልነበረ ተረዳ፡፡ እንዲሁ እኛም እንደታዘዝነው ለድሆች ወገኖቻችን ቸርነትን እናድርግ፤ እርሱን ማክበራችንም የሚረጋገጠው በፍቅረ ቢጽ እንጂ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን በማስጌጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በወርቅ ሳይሆን ከወርቅ ይልቅ ንጽሕት በሆነች ነፍስ ደስ ይሰኛልና፡፡ እንዲህ ስል ግን ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳታምጡ ማለቴ እንዳልሆነ ልትረዱኝ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ከስጦታዎቻችሁ በፊት ትእዛዙን መፈጸም ይቀድማል፡፡

በእርግጥ በተሰበረ ልብ ሆናችሁ ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ብታመጡ እርሱ አይባርካችሁም እያልኩ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ድሆችን ከረዳችሁ በኋላ ስጦታን ለእርሱ ብታቀርቡ ታላቅ ዋጋን ታገኛለችሁ፡፡  በዚያኛው ስጦታ አቅራቢው ብቻ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህኛው ግን ቸርነትን የተደረገለት ወገንም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንድም የወርቅና የብር ዕቃን ስጦታዎች ማድረጋችን ከሰዎች ምስጋናን ለማግኘት ብለን የፈጸምነው ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም ደሃ ወገንህ ተርቦና ተጠምቶ እንዲሁም ታርዞ አንተ እንዲህ ማድረግህ ከዚህ ውጪ ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ ደሃው ወገንህ በርሃብ እየማቀቀ አንተ የጌታን የማዕድ ጠረጴዛ በወርቅና በብር እቃዎች ብትሞላው ምንድን ነው ጥቅምህ? ነገር ግን አስቀድመህ ደሃውን አብላው አጠጣው እንዲሁም አልብሰው፡፡ በመቀጠል የጌታን ማዕድ (መንበሩን) በፈለግኸው መልክ በወርቅም ይሁን በብር አስጊጠው፡፡

ለድሃ ወገንህ ለጥሙ ጠብታ ታክል ቀዝቃዛ ውኃ እንኳ ሳትሰጠው የወርቅ ጽዋን ስጦታ አድርገህ ለእግዚአብሔር ታመጣለታለህን? እንዲህ ማድረግህ ጌታን ያስደስተዋልን? አካሉን የሚሸፍንበትን እራፊ ጨርቅ ለደሃ ወገንህ ነፍገኸው፣ መንበሩን በወርቅ ግምጃ ጨርቅ በማስጌጥህ ከጌታ ዘንድ የረባ ዋጋ አገኛለሁ ብለህ ታስባለህን? እንዲህ በማድረግ ጌታ አምላክህን በስጦታህ ልትሸነግለው ትፈልጋለህን? በዚህስ ድርጊትህ በአንተ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ አይነድምን? ወገንህ አካሉን የሚሸፍንበት እራፊ ጨርቅ አጥቶ በብርድ እየተጠበሰና በመንገድ ዳር ወድቆ የወገን ያለህ እያለ አንተ የቤተ ክርስቲያን ዐምዶች በወርቅ በመለበጥህ ጌታ በአንተ ደስ የሚለው ይመስልሃልን? ይህል ከባድ ኃጢአት አይደለምን?… ኦ እግዚኦ አድኅነነ እም ዘከመ ዝ ምግባር አኩይ!!

yesemayu_bm

የሰማዩ ቤተ መንግሥት (ለህጻናት)

15/04/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

 

በህንድ ሀገር ታከሻሊላ በተባለ ከተማ ጎንዶፓረስ የተባለ ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ስለ ነበረው የንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት ዝና እየሰማ እርሱም በሀገሩ ማሠራት ይፈልግ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ነጋዴዎች በየሀገሩ ሲጓዙ የታወቀ ግንበኛ  እንዲያመጡለት አዘዛቸው፡፡

 

ይህንን መልእክት ከሰሙት ነጋዴዎች መካከል አንዱ ፋርስ ወደሚባለው ሀገር ተጓዘ ከዚያም ያ ነጋዴ አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስን አገኘው፡፡ ነጋዴው ቶማስ ከኢየሩሳሌም እንደመጣ ሲሰማ የግንበኝነት ሙያ ይችል እንደሆነ ጠየቀው፤ ሐዋርያው ቶማስ ወደ ህንድ ሄዶ ማስተማር ይፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህም ይህንን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ለመሔድ “በኢየሩሳሌም ሳለሁ ህንፃ በመገንባት እኖር ነበር፡፡” አለው፡፡

ነጋዴውም በጣም ተደስቶ ቶማስን ወደ ህንድ ወሰደው፡፡ ንጉሡም የቶማስን ሙያ ሲሰማ በጣም ደስ አለው፡፡ ከዚያም ከከተማው አጠገብ ወደሚገኘው ሔዶ ቶማስን ወሰደውና በጫካ የተሞላውን ሜዳ እያሳየ ቤተ መንግሥቱ በዚያ ቦታ ላይ እንዲሠራ ነገረው፡፡ ቅዱስ ቶማስ የቤተ መንግሥቱን አሠራር ሲነግረው ንጉሡ ተሠርቶ እስከሚያየው ቸኮለ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ንጉሡ ለህንጻው መሥሪያ ብዙ ገንዘብ ለቅዱስ ቶማስ ይልክለት ጀመር፡፡

 

ቅዱስ ቶማስ ግን ገንዘቡን ሲያገኝ የሚሔደው ወደ ድሆች መንደር ነበር፡፡ በዚያም ለተራቡት ምግብ፣ ልብስ ለሌላቸው ልብስ፣ መጠለያ ቤት ለሌላቸው ደግሞ ቤት እየገዛ መስጠት ጀመረ፡፡ የታመሙትን እያዳነና እየስተማረ ይኖር ጀመረ፡፡

 

yesemayu_bm

 

ንጉሥ ጎንዶፓረስ ለሕንፃው መሥሪያ የመደበው ገንዘብ እና ጊዜ እንዳለቀ፣ ቤተ መንግሥቱን ሊጎበኝ መጣ፡፡ ወደ ቦታው ደርሶ ቢመለከት እንኳን ሕንፃው ሊሠራ ጫካው አልተነካም፡፡ ንጉሡም በዚያ የሚያልፍ መንገደኛ ጠርቶ ቶማስ የታለ? ሲል ጠየቀው፡፡

 

“ቶማስ በድሆች መንደር የተቸገሩትን እየረዳና እያስተማረ ይገኛል፡፡” ሲል መንገደኛው መለሰለት፡፡ “እርሱስ ጥሩ ግን የሰራልኝ ቤተ መንግሥት የታለ?” ብሎ መንገደኛውን ጠየቀው፡፡ መንገደኛውም “በድንጋይ የተሠራ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፤ ጌታዬ፤ ነገር ግን ሕዝብዎ በጣም እንደተደሰተ መመልከት ይችላሉ፡፡” አለው፡፡

 

በዚህ ጊዜ ንጉሡ ያ ሁሉ ገንዘብ እንደባከነበት መጠራጠር ጀመረ ወዲያው ወታደሮቹ ቶማስን ፈልገው እንዲያመጡ ላካቸው፡፡ ቅዱስ ቶማስ ተይዞ እንደመጣ “ቤተ መንግሥቴን ለምን አልሠራህልኝም ጫካው እንኳን መቼ ተነሣ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ቶማስም “በእርግጥ በምድር ላይ የድንጋይ ቤተ መንግሥት ላያዩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን በሰማይ ላይ ቤተ መንግሥት ሠርቼሎታለሁ፡፡” አለው፡፡

 

ያን ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ፤ ቶማስን እጅ እግሩን እንዲያሰቃዩት አዞ እስር ቤት አስገባው፡፡ በዚያች ሌሊት የንጉሡ ወንድም ልዑል ጋድ በድንገት ታሞ ሞተ፡፡ የጋድ ነፍስ በመላእክት ታጅባ ወደ ሰማያት ወጣች፡፡ የጋድን ነፍስ ካጀቧት መላእክት አንዱ ብዙ ቤተ መንግሥታትን እያሳያት “እንድትኖሪበት ደስ ያለሽን ምረጪ፡፡” አላት፡፡ የጋድ ነፍስም ከቤተ መንግሥታቱ ሁሉ የሚያምረውን መረጠች “ይህ ቤተ መንግሥት የአንቺ አይደለም፤ ቶማስ ለንጉሥ ጎንዶፓረስ የሠራለት ሰማያዊ ቤተ መንግሥት ነው፡፡”

 

ጋድ ሊቀብሩት በተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው ተነሣ፡፡ ከዚያም ያየውን ሁሉ ለንጉሡ እና ለተሰበሰቡት ሰዎች ነገራቸው፡፡

 

ንጉሡ ይህን ሲሰማ በቶማስ ላይ በሠራው ሁሉ አዘነ፣ ያሰበው ቤተ መንግሥት መሠራቱን ሲሰማ ቶማስን ከእስር ቤት አስመጣው፡፡ እራሱ እና ቤተሰቡም በክርስቶስ አምላክነት አምነው ተጠመቁ፡፡ ለቶማስም ያለውን ገንዘብ ሁሉ “ሌላም ቤተ መንግሥት ሥራልኝ” እያለ ይሰጠው ጀመር፡፡ የሀገሩ ሰዎችም እንደርሱ ያደርጉ ጀመር፡፡

 

የተቸገሩትን መርዳት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም ሥራ ነው፡፡ የተቸገሩ ሰዎችን የምንረዳ ከሆነ ደግሞ በምድር ላይ አይተነው የማናውቀውን እጅግ በጣም ያማረ ቤት ያሰጠናል፡፡

 

kidase

የምእመናን መሰባሰብ፤ የቅዳሴ ቀዳሚ ምስጢር

ታኅሣሥ 13/2004 ዓ.ም

በዲ/ን በረከት አዝመራው

ቅዳሴ የአንዲቷ ሰማያዊት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ገጽ እንደሆነ ሁሉ የምእመናን መሰባሰብ ደግሞ የቅዳሴ የመጀመሪያ መሠረት ነው፡፡ kidaseበመሰባሰብ የፈጸመው የቅዳሴ ሥርዓታችን አስቀድሞም በቅዱሳን መላእክት ዓለም የነበረና በምድር ባለች መቅደሱም በምእመናን መሰባሰብ የሚፈጸም ነው፡፡ “እኔ በመካከላቸው እሆናለሁ” ብሎ ደስ የሚያሰኝ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን የገባልን ጌታችን፣ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት” በማለት መሰባሰባችን ጸጋና ረድኤቱን እንድናገኝ ምክንያት መሆኑን ነግሮናል /ማቴ.18፥20/ በዚህ ርዕስም የጌታን ቃል በታላቅ ትጋት በፈጸመች ሰማያዊ ሥርዓቷን ከቅዱሳን መላእክት ዓለም ያገኘች፣ የምስጋና ሥርዓቷም በትውፊት ደርሶ ለቤተ ክርስቲየን መሠረት በሆነው በጠንታዊት /በሐዋርያት ዘመን/ ቤተ ክርስቲያን ለምእመናን መሰባሰብ ይሰጥ የነበረውን ትኩረትና ምስጢራዊ እይታ እንመለከታለን፡፡

 

የምእመናን መሰባሰብ በቅዳሴ ጥንታዊ ትውፊት

ተሰባስቦ እግዚአብሔርን ማመስገን መሥዋዕትን ማቅረብ አስቀድሞ በብሉይ ኪዳንም በምሳለ የቆየ ቢሆንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐዋርያት ጋር በቤተ አልዓዛር የአይሁድን ፋሲካ ሲያከብር የአማናዊው ቅዳሴ መሠረት ተጣለ /ሉቃ.22፥7/፡፡ የቤተ እስራኤል ጉባኤ መሠረት ይሆኑ ዘንድ ዐሠራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች የመረጠ እግዚአብሔር እስራኤል ዘነፍስ የተባሉ የምእመናን ጉባኤ የሆነች የቤተ ክርስቲያን መሠረቶች የሆኑ ሐዋርያትን ሰብስቦ በመንግሥተ ሰማያት ማዕድ ላይ አስቀመጣቸው /ሉቃ.22፥29-30/፡፡ በዚህም በሐዋርያት በኩል የቤተ ክርስቲያን አንድነት መመሠረቱን እንመለከታለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መምጣት /ጸጋውን ረድኤቱን በመቀበል/ የጌታን ምስጢር ሁሉ የተረዱት ሐዋርያት አባቶቻችንም የቅዳሴን ምስጢር ምእመናንን ሰብስበው በአንድነት የሚፈጽሙ ሆነዋል /የሐዋ.20፥2/፡፡
ይህ ሥርዓት በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በእርግጥም የጸና ሆኗል፡፡ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” የሚለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ “በመጀመሪያ ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ…” በማለት በእርሱ ዘመን የምእመናን መሰብሰብ ለዐበይት ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ቅድመ ሁኔታ እንደነበረ ይናገራል /1ቆሮ.11-18/፡፡ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” በማለቱም ይህ በሥርዓተ ቅዳሴ በቤተ ክርስቲያን የመሰባሰብ ምስጢር ከዚያ በኋላ ሥርዓቱን ጠብቆ በትውፊት የሚተላለፍ ሆኗል፡፡
የሐዋርያት ተከታዮች የሆኑ አበውም ይህን የሐዋርያት ትውፊት ተቀብለው በቀጥታ ለትውለድ አስተላልፈዋል፡፡ ይህንንም “ትምህርታችን ከቅዳሴ ጋር የተስማማ ቅዳሴያችንም ትምህርታችንን የሚያጸና ነው” ብለው አጽንተውታል፡፡ /St. Iranaeus, Against Heresies 4:18-5/ /ማቴ.18፥ 20/፡፡

በዚህ ዘመን ምእመናን ሁሉ በቅዳሴ ተገኝተው ሁሉም ሥጋወደሙ ተቀብለው ይሔዱ ነበር፡፡ የታመመ እንኳ ቢኖር ሔደው ያቀብሉት ነበር፡፡ ያለሕማምና ከባድ ችግር ቅዳሴ የቀረ ሰው ራሱን አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን እንደለየ ይቆጠር ነበር /fr.Alexander Schmemann, Eucharist, pp.24/፡፡

ሥርዓተ ቅዳሴ የሁሉም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃም ይህን ለማስፈጸም አመቺ ተደርጐ ይሠራ ነበር፡፡ ይህ ጥንታዊ የሕንፃ ቤተ ክርስትያን አሠራር ትውፊት አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን በግልጽ ያለ ነው፡፡ ቅዳሴ ወንዶች፤ ሴቶች፣ ሕፃናት ሁሉ ሊሳተፉት የሚገባ ምስጢር ባይሆን በቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ወንዶች፣ ሴቶች የሚቆሙበት ቦታ ለይቶ ማዘጋጀት ለምን ያስፈልግ ነበር? ይህ የሆነው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ የክርስቶስ አካል የሆነች የምእመናን አንድነት ማሳያ ስለሆነ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት ስንል ሁሉንም ምእመናን አቅፋ የያዘች መሆኗን እንደሚገልጽ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን የዚህ መገለጫ ከሆነ ሁሉን ሊይዝ ይገባዋልና፡፡

በቅዳሴ ጊዜ ስላለው የምእመናን ኅብረት /ስብስብ/ የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን እይታ ከዚህም የመጠቀ ነበር፡፡ በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የምእመናን ስብስብ ምድራውያንን ብቻ ሳይሆን ሰማያውያንንም ያጠቃለለ እንደሆነ ይታመን እንደነበር በምርምር በተገኙ ጥንታውያን ሥዕሎች ይታያል፡፡ በልባዊ እምነታቸው በጥልቀት ያለውን የእነርሱን እና የሰማያውያንን ኅብረት በሥዕል ያሳዩ ነበር፡፡ አንድ የነገረ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ ይህን ሲገልጹ “በብዙ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሥዕላቱ ከማኅበረ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚሳተፉ፣ የዚህን ምስጢር ትርጉም የሚናገሩ፣ ዘላለማዊ እንቅስቃሴውንና መስመሩን የሚያሟሉ እንደሆነ እንረዳለን” ይላሉ /Alexander schememann. The Euchrist pp.21/
ይህ ሥርዓት አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን ይታያል፤ ይጠበቃልም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ትውፊት መሠረትም ቅዱሳት ሥዕላት ቅድስትና መቅደሱን በሚለየው ግድግዳ ላይ ይሣላሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሌላ ምስክር አለን፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴአችን ይዘቱና አፈጻጸሙ እንደሚያመለክተን እያንዳንዱ የካህን ጸሎት እየንዳንዱ የዲያቆን ትእዛዝ በምእመናን መልስ /አሜን/ ይጸናል፤ ይፈጸማል፡፡ በመጽሐፈ ቅዳሴ የምናነበው “ይበል ካህን፣ ይበል ሕዝብ…” የሚሉት ትእዛዛትም ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ በዚህም ሥርዓተ ቅዳሴ የካህናት ብቻ ሳይሆን የምእመናንና የካህናት የአንድነት ምስጢር መሆኑን እንረደለን፡፡

ይህንን የአንድነት ምስጢር ለማጽናት በፍትሐ ነገሥቱ ስለቅዳሴ በተነገረበት ክፍል “ምእመናን ሳይሰበሰቡ ቅዳሴ የሚጀምር አይኑር” የሚለው መልእክት እዚህ ላይ ልብ ይሏል፡፡

በዘመናችን የሚታየው የቅዳሴን ለካህናትና ለተወሰኑ ሰዎች መተው፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና የሕይወት ልምድ እንግዳ የሆነ ስርዋጽ ነው፡፡ አንዳንዶች ሥርዓተ ቅዳሴ በዋነኝነት የካህናት ሥራ እንደሆነ እና እነርሱ ግን ቢኖሩም እንኳን አዳማጭ፣ አዳማቂ እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከውስጧ ከሚሰሟት ሕመሞች አንዱ ነው፡፡ አንዳንዴ ለሚታየው በሥርዓተ ቅዳሴ በንቃት አለመከታተል፣ ከዚህም የተነሣ የመንፈሳዊ ሕይወት መድከም፣ አንዱ ምክንያት መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

የመሰባሰባችን ምስጢር

የምእመናን አንድነት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፡፡ እያንዳንዱ ምእመን ደግሞ የክርስቶስ ብልት ነው /1ቆሮ.12፥27/፡፡ እንግዲህ በምእመናን መሰባሰብ፣ ከምድራዊ አስተዳደራዊ ተቋም በተለየ የላቀች ቅድስት የሆነች የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን የአንድነቷ የቅድስናዋ ታላቅ መዓርግ /ፍጻሜ/ ይሆናል፡፡

“የቤተ ክርስቲያን ፍፁምነት” ማለትም ቅድስት የሆነች የቤተ ክርስቲያን በሰማያዊ ገጽታዋ መገለጥ ማለት ነው፡፡ የምእመናን ስብሰብ እንደማንኛውም ምድራዊ ስብስብ የሺህዎች “ድምር” ማለት ሳይሆን የክርስቶስ ሰማያዊ አካል /በስሙ በማመን ብልቶቹ የሆኑ ምእመናን ኅብረት/ መገለጥ ነውና፡፡

ብዙ የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊ ትውፊቶች የማይቀበሉ አዳዲስ የሥነ መለኮት አስተምህሮዎች ብቅ ብቅ ባሉበት በዘመናችን ይህን ጠንቅቀን ማወቅ ይገባናል፡፡ እነዚህ ምድራውያን አስተምህሮዎች ለአምልኮ ሥርዓት ግድ የሌላቸው፣ ቢኖራቸው እንኳ አንዱን የቅዳሴ ክፍል ከሌላው የሚያበላልጡ፣ አንዱን በጣም አስፈላጊ አንዱን ደግሞ ብዙም የማያስፈልግ አያደረጉ መመደብ የሚቀናቸው ናቸው፡፡ ስለቅዳሴ ብንጠይቃቸው ሕብስቱና ወይኑ የሚለወጥበትን ጊዜ አጉልተው ሌላውን አሳንሰው የሚናገሩ ናቸው፡፡ ሕብስቱና ወይኑ የመለወጡን ነገርም ቢሆን በኦርቶደክሳዊና ሰማያዊ መንገድ ሳይሆን በሳይንሳዊና ምድራዊ መንገድ ለማረጋገጥና ለመተንተን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እነዚህ አስተምህሮዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው፡፡

ይህን ሰማያዊ ምስጢር የምታውቅ ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የአንድ ምእመን ከቅዳሴ መቅረት በጣም ያስጨንቃት ነበር፡�The Eucharist, pp21/

የቤተ ክርስቲያን ቅድስና ይህ ነው፤ የክርስቶስ አካል መሆኗ፡፡ እያንዳንዳችን ምንም ያህል ኀጢአተኞች ልንሆን እንችላለን፤ ነንም፡፡ የምእመናን አንድነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግነ ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡ ይህም ከእኛ የመጣ ቅድስና ሳይሆን አካሉ በሆነች በቤተ ክርስቲየን “ራሷ” ሆኖ በመካከላችን ካለው ክርስቶስ የተገኘ ነው፡፡ ከኀጢአት የማንጠራ /የማንርቅ/ ጎስቋሎች ብንሆንም በመሰባሰባችን “የምትመሠረት” ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ግን በእውነት ንጽሕት ናት፤ የሕመሟ መድኀኒት፣ የቅድስናዋ ምንጭ በመካከሏ ነውና፡፡ በምእመናን መሰባሰብ “የተገነባች” ቤተ ክርስቲያን “ቅዱስ ሕዝብ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተመረጠ ዘር….” መባል ይገባታል፤ የመረጣት ከኀጢአት ባርነት አውጥቶ ያከበራት የቅድስናዋ አክሊል በመካለሏ ነውና /1ጴጥ.2፥9/፡፡ ለዚህ ነው በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ምእመናን “ቅዱሳን” ይባሉ የነበሩት፤ በመሰባሰብ ይኖሩ ነበረና /ፊልሞ.1፥7/፡፡

ይህ መሰባሰብ የቅድስና መዓዛ ነው፡፡ ይህ ሰማያዊ ደስታ ነበረ መራራውን መከራ በደስታ እንዲቀበሉት ያስቻላቸው፡፡ ይህ የቅድስና ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ደስታ ነበር፡፡ በአስቸጋሪው ዓለም ክርስትናን በቆራጥነት እንዲሰብኩ ያስቻላቸው ታላቅ አንድነት ከዚህ የመነጨው ፍቅረ ቢጽና ፍቅረ እግዚአብሔር ነው፡፡ “ፍፃሜ ማኅበርሃ ለቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክርስቲያን የማኅበሯ ፍጻሜ” ይህ ነውና፡፡

የምእመናን መሰባሰብ የክርስቶስን አካል እንደሚገልጥ፣ ቅዳሴውን የሚመራው ካህን ራስ የተባለ የክርስቶስን ክህነት ይገልጣል፡፡ /ኤፌ.5፥23፣1ቆሮ.11፥3/ በጸጋ በተሰጠው ሥልጣነ ክህነት ውስጥ ሆኖ /እያገለገለ// የክርስቶስን የባህርይ /ዘላለማዊ/ ክህነት ይመሰክራል፡፡ ካህኑ የሚለብሰው የክህነት ልብስ፣ ክርስቶስ በውስጧ ያደረው የቤተ ክርስቲያን መገለጫ ነው፡፡ ለዚህ ነው በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ምእመናን ሳይሰበሰቡ ልብሰ ተክህኖ መልበስ የተከለከለው፡፡ /መጽሐፈ ቅዳሴ/ በካህኑ ራስ ላይ ያለው አክሊል እንደ መልከ ጸዴቅ ሥርዓት ያለውን ዘለዓለማዊውን የክርስቶስ ክህነት ይመሰክራል፡፡ /ዕብ.7፥20-22፣ መዝ.109፥4፣ ዕብ.7፥1/ እንግዲህ የጌታችን ዘለዓለማዊ ክህነት በዘለዓለማዊና ሰማያዊ መቅደሱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን /በምእመናን መካከል/ በዚህ መልኩ ይገለጣል፤ ቅዱስ ጳዉሎስ “እርሱ ግን የማይለወጥ ክህነት አለው” እንዳለ /ዕብ.7፥25/፡፡ ስለዚህ መሰባሰባችን ክርስቶስን በመካከላችን አድርገን ነው፡፡ ስለዚህ በቅዳሴ መሰባሰባችን በመካከላችን ካለው ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በእውነት ታላቅ ነው፡፡

በመጨረሻ፣ እግዚአብሔር በማያሳየው ምድር በደስታ ይኖር ዘንድ አብርሃም ወገኖቹንና የአባቱን ቤት እንዲተው ከታዘዘ ወደ እግዚአብሔር መገለጫ፣ ወደ ጽዮን ተራራ ስንወጣ፤ የበኩራትን ማኅበር ልንመሠርት ስንሰባሰብ እንዴት ዓለማዊ ጣጣችንን አንተው? እስራኤል በሲና ተራራ በሚያስፈራ ሁኔታ የተገለጠውን እግዚአብሔርን ለመስማት ሦስት ቀን ከተዘጋጁ፤ ልብሳቸውን ካጠቡ፤ በሚያስደንቅ የመሥዋዕትነት ፍቅሩ ስለኛ የተሰቀለውን አምላካችንን ለማየት ብቻ ሳይሆን ለመብላት ለመጠጣት ስንሰባሰብ ምን ያህል መዘጋጀት፣ ልብሳችን ብቻ ሳይሆን ሥጋውንና ደሙን ሰውነታችንን ምን ያህል በንስሐ ማጠብ ይገባን ይሆን? /ዘፍ.12፥1፣ ዕብ.12፥22-24፣ ዘፀ.19፥14-15/ ሕፃኑ ሳሙኤል በቤተ መቅደስ ለሚጠራው ቃል በንቃት መልስ ከሰጠ፤ በእውነተኛ ቤተ መቅደሱ የተሰበሰብን እኛ በቅዳሴ ሰዓት በልዩ ልዩ መንገድ ለሚሰማው የእግዚአብሔር ድምፅ ምን ያህል በትጋትና በንቃት መልስ መስጠት ይኖርብን ይሆን? /1ኛ. ሰሙ.3፥1-14/ በእውነት እግዚአብሔር ከዚህ ሰማያዊ ጉባኤ አይለየን፡፡ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር 17ኛ ዓመት ቁጥር 6 ኅዳር/ታኅሣሥ 2002

 

Gedamat Awude Tinat04

ልዩ ዐውደ ጥናት

Gedamat Awude Tinat04

ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌላውም አድርግ

ሰዎች በኑሮአቸው ሁልጊዜ እንዲፈጽሟቸው በቅዱስ መፅሐፍ ከተቀመጡ መንፈሳዊ ተግባራት ውስጥ፡

  • የተራበን ማብላት፣
  • የተጠማን ማጠጠት፣
  • የታረዘን ማልበስ
  • በአጠቃላይ ለሰዎች ሁሉ በጎ ነገርን ማድረግ ናቸው፡፡

ይህን የተቀደሰ ነባር መንፈሳዊ ተግባር አጠናክሮ ለመቀጠል እና የተቸገሩ ወገኖቻችን ለመርዳት፣ “ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌላውም አድርግ” በሚል ርእስ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችን ማኅበራዊ ህይወት ለመደገፍ እና ራሳቸውን ችለው ህይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችል ሲፖዚየም ተዘጋጅቷል፡፡
በሲንፖዚየሙ ላይ

  • በማኅበራዊ ዘርፍ ከፍተኛ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ተሞክሮ ይቀርባል፡፡
  • በሁለት ልብሶች መርሐ ግብር ድጋፍ የተደረገላቸው አካላትን አስመልክቶ በፊልም የተደገፈ መረጃ ይቀርባል፡፡
  • በማኅበራዊ ዘርፍ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት ልምዳቸውን ያካፍላሉ፡፡

አዘጋጅ፡-በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
ቦታ፡- በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ
ቀን፡- ታህሣሥ 22 ቀን 2004 ዓ.ም
ስዓት፡-7፡30-11፡00
ስልክ 011 1 55 36 25

ደጉ ሰው (ለሕፃናት)

ታኅሣሥ 6/2004 ዓ.ም

በእኅተ ፍሬስብሐት

በአንድ ወቅት አንድ ሰው ከሚኖርበት ከተማ ተነሥቶ ለንግድ ወደ ሌላ ሀገር ጉዞ ጀመረ በጉዞው ወቅትም ሌቦች ከሚኖርበት ዋሻ አጠገብ ደረሰ፡፡ ሌቦቹም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ከዋሻው ወጥተው ደበደቡት፡፡ የያዘውን ገንዘብ በሙሉ ቀሙት፡፡ ልብሱንም ገፈው በዚያው ጥለውት ሄዱ፡፡ የተጎዳው ሰው መንቀሳቀስ ስላቃተው በዚያ ቆየ፡፡ እየመሸ ሲሄድ አንድ ሰው በዚያ ሲያልፍ አየ፡፡ መንገደኛውን ሲያየው “እርዳኝ! እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ መንገደኛው ግን ምንም ሳይረዳው ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሌላ መንገደኛ መጣ፡፡ የተጎዳው ሰው አሁንም “እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ መንገደኛው ግን አሁንም ምንም ሳይረዳው ጉዞውን ቀጠለ የተጎዳው ሰው የሚረዳው ሰው አጥቶ ሲያዝን ሳለ ሌላ መንገደኛ መጣ፡፡ መንገደኛው የተጎዳውን ሰው ሲያይ በጣም አዘነ፡፡ ከፈረሱ ላይ ወርዶ ወደ ሰውየው ሄደ፡፡ ከዚያም በቁስሉ ላይ መድኀኒት አደረገለት እና እንዳያመው በጥንቃቄ ይዞ በፈረሱ ላይ ጫነው፡፡ ከዚያም በአካባቢው ወዳለ ቤት ወሰደው፡፡ ለቤቱ ባለቤትም እሱ እስከሚመለስ በሽተኛውን እንዲንከባከቡለት አደራ ብሎ ሰጣቸው፡፡ ለሚንከባከቡትም ገንዘብ ከፈላቸው እና ሔደ፡፡

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ሁላችሁም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ ለሁሉም ሰውም መልካም ነገርን አድርጉ፡፡”

Mariam1

በአታ ለማርያም

ታኅሣሥ 3/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

Mariam1ሰይጣን በእባብ አካል ተሰውሮ ሔዋንን፤ በእርሱዋም አዳምን በማሳት በእነርሱ ላይ ሞት እንዲሠለጥንባቸው ስላደረገ “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደረጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትነድፋለህ” በማለት የፍቅር አምላክ እግዚአብሔር ፈረደበት፡፡ “በአንተ” የተባለው ሰይጣን ሲሆን፣ “በሴቲቱ” የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት (ገላ.4፡4)፣ “በዘርህ” ሲል የዲያብሎስ የግብር ልጆችን ሲሆን(ዮሐ.8፡49)፣ “በዘርዋ” የተባለው ክርስቶስ ነው(ገላ.3፡16)፡፡ ትርጉሙ እንዲህ አንደሆነም ወንጌላዊው ዮሐንስ “ዘንዶው በሴቲቱ ላይ ተቆጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የጠበቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ”አለን፡፡(ራእ.12፡17) እባብ የተባለው ሰይጣን ስለመሆኑም “ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ”(ራእ.12፡9) ብሎ ጻፈልን፡፡

አዳም በዚህ ፍርድ ቃል ምክንያት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ምን እንደሆነ ተረዳ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክ በሔዋንና በእርሱ ላይ የፈረደው ፍርድ እነርሱን ከማዳን አንጻር የርኅራኄ ፍርድ እንደሆነ፤ እርሱና ሔዋን በክፉ ምርጫቸው ምክንያት ያጎሳቆሉትን ተፈጥሮአቸውን ወደ ቀደሞው ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ንጽሕት ዘር ከሆነች ታናሽ ብላቴና እንደሚወለድና በመስቀሉ ሞት በእነርሱ ላይ የተላለፈውን የሞት ፍርድ እንደሚሽረው፣ አዳምና ሔዋን የተመኙትን የአምላክነት ስፍራ በክርስቶስ በኩል እንደሚያገኙት እንዲሁም በእርሱ የማዳን ሥራ የመለኮቱ ተካፋዮች እንዲሆኑ አስተዋለ፡፡  ይህም እውን እንደሚሆንም “አዳም ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” በሚለው አምላካዊ ቃሉ አረጋገጠ፡፡ ስለዚህም ለመሰናከሉ ምክንያት የሆነችው ሴት ለትንሣኤውም ምክንያት እንደሆነች ተረዳ፡፡ በዚህም ምክንያት አስቀድሞ ከሥጋዬ ሥጋ ከአጥንቴ አጥንት የተገኘሽ ክፋዬ ነሽ ሲል “ሴት” ብሎ የሰየማትን ሚስቱን “ሔዋን” ብሎ ስም አወጣላት፡፡ ትርጓሜውም የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው፡፡ እንዲያ ባይሆንና አባታችን አዳም ይህንን የእግዚአብሔርን አሳብ ባይረዳ ኖሮ እንዴት በሰው ዘር ላይ ሞት እንዲሠለጥን ምክንያት ለሆነችው ሚስቱ ሔዋን የሚል ስምን ያወጣላት ነበር? ነገር ግን በእርሱዋ ሰብእና ውስጥ እርሱንና ወገኖቹን ከሞት ፍርድ ነጻ የሚያወጣቸውንና ወደ ቀደመው ክብራቸው የሚመልሳቸውን ጌታ በሥጋ የምትወልድ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት የሆነች ንጽሕት ዘር እንዳለች ከእግዚአብሔር የፍርድ ቃል አስተዋለ፡፡

አዳም ይህን ሲረዳ ክፋዩ ለሆነች ሚስቱ ያለው ፍቅርና አክብሮት ከፊት ይልቅ ጨመረ፡፡ ከእርሱም በኋላ ለሚነሡ ወገኖቹም ለመዳናቸውና ለመክበራቸው ምክንያት ከሴት ወገን የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም እንደሆነ አስተውለው ወንዶች ለእናቶቻቸውና ለእኅቶቻቸው እንዲሁም ለሴት ልጆቻቸው ተገቢውን አክብሮትና ፍቅር እንዲያሳዩ ለማሳሰብ ሲልም ሚስቱን ሔዋን ብሎ መሰየሙንም መረዳት እንችላለን፡፡ እንዲህም ስለሆነ ነቢዩ ኢያሳይያስ “ዐይኖችን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሟቸዋል”(ኢሳ.60፡4)ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ራሱዋን የጌታ ቤተክርስቲያን በማድረግ፤ ቤተክርስቲያን በልጁዋ ክቡር ደም ተዋጅታ እንድትመሠረት ምክንያት ሆናለች፡፡ ስለዚህም አባታችን አዳም እንዳደረገው ነቢዩም እንደተናገረው ለእርሱዋ ያለንን ፍቅርና አክብሮት በጾታ ለሚመስሎአት እናቶቻችን፤ እኅቶቻችን፣ እንዲሁም ሴቶች ልጆቻችን በማሳየት እንገልጠዋለን፡፡

ከአዳም በኋላ የተነሡ ቅዱሳን አበው በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በእነርሱ ላይ የሠለጠነባቸው ሞት የሚወገድላቸውና ወደ ገነት የሚገቡት እግዚአብሔር አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድ እንደሆነ ከአዳም አባታቸው ተምረው ነበር፡፡ ስለዚህም ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ተካፋይ ለመሆን እሾኽና አሜካላ በምታበቅለውና ሰይጣን በሠለጠነባት በዚህ ምድር የመዳን ተስፋቸው የሆነችውን የቅድስት ድንግል ማርያምን መወለድ በተስፋ እየተጠባበቁ ቅዱስ ጳውሎስ “ማቅ፣ ምንጠፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣ ተጠሙም፣ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ዱር ለዱርና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ”(ዕብ.11፡33-38) በጽድቅ ተጉ፡፡ ጌታችንም እንደተስፋ ቃሉ ከንጽሕት ቅድስት እናቱ ተወልዶ በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በመቅረብ ወደ ገነት አፈለሳቸው፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ ጌታችንን መድኀኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እስክትወልድ ድረስ የተስፋ ቃሉ እንዳልተፈጸመ ለማስዳት ሲል ጨምሮ “እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል አላገኙም፡፡ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ አግዚአብሔር ስለ እኛ የምትበልጠውን አስቀድሞ በይኖአልና፡፡” ማለቱ(ዕብ.11፡39-40)

አባቶቻችን ከሐዋርያት በትውፊት አግኝተው እንደጻፉልን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልክ እንደ ይስሐቅ፣ ነቢዩ ሳሙኤል እና መጥምቁ ዮሐንስ፣ መካን ከነበሩ ወላጆች የተገኘች ናት፡፡ እናቱዋ ሐና በአባቱዋ በኩል ከአሮን ቤት ስትሆን በእናቷ በኩል ከይሁዳ ወገን ነበረች፡፡ አባቱዋ ኢያቄም ግን ከይሁዳ ወገን ነበር፡፡ እነዚህ ወላጆች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ነገር ግን ልክ እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ እስከ እርጅናቸው ድረስ ልጅ አልወለዱም ነበር፡፡ በአይሁድ ዘንድ መካንነት የእርግማን ምልክት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበር ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔር አምላክ ልጅ በመስጠት ይህን ስድብ ያርቅላቸው ዘንድ በቅድስናና በንጽሕና በመጽናት ምጽዋትንም በማብዛት በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡ ጸሎታቸውንና ምጽዋታቸውን እግዚአብሔር ስለተቀበለላቸው አምላክን በሥጋ በመውለድ ለዓለም መድኅን የሆነቸውን ቅድስት ድንግል ማርያምን በእርጅና ዘመናቸው ግንቦት አንድ ቀን ወለዷት፡፡ ማርያም ማለት የእግዚብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሐናም እግዚአብሔር አምላክ ስድቤን ከእኔ አርቆልኛልና ከእግዚአብሔር እንዳገኘዋት ለእግዚአብሔር መልሼ እሰጣታለሁ ብላ የተሳለቸውን ስለት አሰበች፡፡ ሦስት ዓመት ሲሞላትም ስለቷን ትፈጽም ዘንድ ከኢያቄም ጋር ልጇን ቅድስት ድንግል ማርያም ይዛ ወደ ቤተመቅደስ አመራች፡፡ በጊዜው ሊቀ ካህናት የነበረው ካህኑ ዘካርያስም ሕዝቡን ሰብስቦ በታላቅ ደስታ ተቀበላቸው፡፡ ነገር ግን ካህኑን ዘካርያስን የምግብናዋ ነገር አሳስቦት ነበረና ሲጨነቅ ሳለ ነቢዩ ኤልያስን ይመግበው ዘንድ መልአኩን የላከ እግዚአብሔር አምላክ(1ነገሥ.19፡6) እናቱ የምትሆነውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይመግባት ዘንድ ሊቀ መላእክትን ቅዱስ ፋኑኤልን አዘዘላት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም የምግቡዋ ነገር እንደተያዘለት ሲረዳ በቤተ መቅደስ ውስጥ እንድታድግ አደረጋት፡፡ ይህ እለት በሁሉም ኦሬንታልና የሐዋርያት የሥልጣን ተዋረድ(Apostolic succession) በተቀበሉ የሚታወቅና የሚከበር ክብረ በዓል ሲሆን  በአታ ለማርያም ወይም የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ መግባት በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህም “ልጄ ሆይ ስሚ፣ ጆሮሽንም አዘንቢዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ፤ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና፡፡”(መዝ.44፡10) የሚለው ቃል መፈጸሙን እናስተውላለን፡፡

የጌታን መወለድ በተስፋ ሲጠባበቁ ለነበሩ ቅዱሳን አበው ይህች ቀን እጅግ ታላቅ እለት ነበረች፤ ምክንያቱም የመዳናቸው ቀን  መቃረቧን የምታበሥር ቀን ነበረችና፡፡ ለእኛም ለክርስቲያኖች ይህች ቀን ታላቅ የሆነ በረከት ያላት ናት፡፡ ሙሴ የመገናኛ ድንኳኗንና በውስጡ ያሉትን ነዋያተ ቅዱሳት የጥጃና የፍየሎች ደምን ከውኃ ጋር በመቀላቅል በቀይ የበግ ጠጉርና በሂሶጵ በመንከር ረጭቶ ቀድሶአት ነበር፡፡(ዘጸ.24፡7-8፤ዕብ.9፡18-22) ንጉሥ ሰሎሞንም እርሱ ያሠራውን ቤተመቅደስ እርሱና ሕዝቡ ባቀረቡት የእንስሳት መሥዋዕት ቀደሷት ነበር፡፡(1ነገሥ.8፡23) እነዚህ ሥርዐታት ግን ክርስቶስ በደሙ ለሚዋጃት ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነበሩ፡፡

በዚህች ቀን ቅድስት እናታችን ራሱዋን የጌታ ቤተ መቅደስ በማድረግ የብሉዩዋ ቤተመቅደስ ክርስቶስ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ልትተካ መቃረቡዋን ለማብሠር ወደ ቤተ መቅደስ ያመራችበት ቀን ነው፡፡ ጌታችንም ከእርሱዋ የነሳውን ሥጋና ነፍስ በተዋሕዶ የራሱ ቤተመቅደስ በማድረግና እኛንም በጥምቀት የአካሉ ሕዋሳት እንድንሆን በማብቃት ሥጋችንን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ስለዚህም እኛ ክርስቲያኖች የቅድስት ድንግል ማርያምን ወደ ቤተመቅደስ መግባት ባሰብን ቁጥር እግዚአብሔር ቃል ከእርሱዋ በሥጋ በመወለዱ ያገኘነውን ድኅነትና ብዙ ጸጋዎችን እናስባለን፡፡ አሁን እኛ ክርስቲያኖች በጥምቀት ከእርሱዋ የተወለደውን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለብሰነዋል፤ (ገላ.3፡27) ከእርሱዋ በነሣው ተፈጥሮ በኩል ሞትን በመስቀሉ ገድሎ ሲያስወግደው፣ እኛም በጥምቀት ከእርሱ ሞት ጋር በመተባበራችን ሞትን ድል የምንነሣበትን ኃይልን ታጥቀናል፡፡ በጥምቀት ያገኘነውን ጸጋ ሠርተንበትና አብዝተነው ብንገኝ ከትንሣኤው ተካፋዮች መሆንን እናገኛለን፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመልን እግዚአብሔር ቃል ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለዱ ምክንያት ነው፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያም ብሉይን ከአዲስ ያገኛኘች መንፈሳዊት ድልድይ ናት፡፡ በብሉይ ያሉት ቅዱሳን በሐዲስ ኪዳን ካለነው ጋር አንድ ማኅበር የፈጠሩትና ከቅዱሳን መላእክትም ጋር እርቅ የወረደው ከእርሱዋ በነሳው ሰውነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህስ ወዲህ እናንተ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም”(ኤፌ.2፡19) ብሎ አስተማረ፡፡ ራሷን የጌታ ቤተ መቅደስ በማድረግ እኛንም በልጁዋ በኩል የመንፈሱ ቤተ መቅደስ እንድንሆን ምክንያት ሆናልናለችና የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ መግባት ለእኛ ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አለው፤ ስለዚህም ይህቺን እለት በታላቅ ድምቀት እናከብራታለን፡፡

 

እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም
ረድኤትና በረከት ያሳትፈን
ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ለደቡብ ትግራይ ማይጨው እና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ታኅሣሥ 5/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ሥልጠናው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ትግራይ ማይጨውና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት እንዲሁም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በዋናው ማእከል ምክክር የተዘጋጀው ነው፡፡

ከታኅሣሥ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ትግራይ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና አዳራሽ በማይጨው ከተማ ከ 11 ወረዳዎች ለተወጣጡ 150 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አስታወቁ፡፡ ከታኅሣሥ 2 እስከ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ሥልጠና የተገኙት የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ብፁዕነታቸው ገልጠዋል፡፡

ሥልጠናው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ሀገረ ስብከቱ የቅድሚያ ዝግጅት ማድረጉን ያስታወቁት ብፁዕነታቸው “ከአዲስ አበባ ተነሥታችሁ በማታውቁት መንገድ አስፋልቱን መሪ አድርጋችሁ ወደ ማይጨው ሀገረ ስብከት የመጣችሁ ልጆቻችን እንኳን ደኅና መጣችሁ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባልና አካል የሆነ ማኅበር ነው፤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ወገኖቻችን የተለያየ አሉባልታ ሊያስወሩ ይችላሉ፣ እናንተ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተከናወነ ያለውን ሤራ ለማስቆም እንደምትሮጡ ምስክሮቹ እኛ ነን፡፡ ቅን አገልግሎታችሁን ስለተገነዘብን ሓላፊነቱን ወስደን ይህን ሥልጠና በጋራ አዘጋጅተናል፡፡ የጤፍ ዘር ለመልቀም አልመቸው ያለ ዝንጀሮ ከዳር ላይ ቆሞ ‘ጤፍን የዘራ ገበሬ ገበሬ አይባልም’ አለ እንደሚባለው ማኅበረ ቅዱሳንም ሤራችንን ያውቅብናል ብለው የሚሠጉና የሚፈሩ ተሐድሶ መናፍቃን በኑፋቄ ትምህርታቸው ብዙዎችን ለማሰናከል የሚያደርጉትን የጥፋት ሥምሪት ከነላኪዎቻቸው ስለምታውቁባቸው ላትስማሟቸው ትችላላችሁ፡፡ እውነተኛ ዓላማ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጸሎት፣ በሃሳብና በቅን ምክራቸው እንደማይለዩዋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጉባኤያችንን ይባርክልን” ሲሉ አባታዊ ቃለ ምዕዳናቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ዘካርያስ ሕሉፍ ባስተላለፉት መልእክት «ካህናት የተሰጣችሁን አደራ በትክክል እንድትወጡና ዘመኑን በመዋጀት እንድታስተምሩ አሳስባለሁ፡፡ ይህ ሥልጠና የመመካከሪያ መርሐ ግብር በመሆኑ በንቃትና በትጋት ሥልጠናውን እንድትከታተሉ አደራዬ ጥብቅ ነው፡፡ መርሐ ግብሩን አመቻችቶ መምህራንን ከአዲስ አበባ በመላክ፣ መጻሕፍት፣ ደብተር፣ እስክሪቢቶ፣ የሠልጣኞችን የምሳ ወጪ እና የውሎ አበል በመሸፈን ማኅበረ ቅዱሳን ስላበረከተው መንፈሳዊ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ» ብለዋል፡፡

ታኅሣሥ 2 ቀን የተጀመረው ሥልጠና በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ፣ የነገረ ሃይማኖት መግቢያ፣ አእማደ ምሥጢራት፣ ነገረ ድኅነት፣ ነገረ ቅዱሳን እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሰጡ ተገልጧል፡፡

ሥልጠናው በተጀመረበት ዕለት ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በስፋትና በጥልቀት ተዳስሷል፡፡ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያከናወኑት ሴራ ምን ያህል ከባድና አሳዛኝ እንደ ሆነ የተደረሰበት የጽሑፍ፣ የምስልና የድምጽ መረጃ ለካህናቱ ቀርቧል፡፡ ሠልጣኝ ካህናቱም መናፍቃን መልካቸውን እየቀያየሩ ሃይማኖታችንን ለማስነቀፍ የእኛን ቀሚስ ለብሰው፣ አስኬማችንን ደፍተው፣ መነኮሳትና ባሕታውያን እንዲሁም አጥማቂዎች መስለው በወርሐ ጾም በየሥጋ ቤቱ እየገቡ ሆን ብለው ሥጋ እየበሉ በአከባቢያችን የታዩ ተሐድሶ መናፍቃን ነበሩ ሲሉ ካህናቱ በዓይናቸው ያዩዋቸውንና በተግባር የገጠሟቸውን የተለያዩ ክሥተቶች በተጨባጭ መረጃ በቁጭት ተናግረዋል፡፡

በተሰጠው መረጃ የመናፍቃኑ ተልእኮ ለቤተ ክርስቲያን ፈተና መሆኑን በጥልቀት እንደ ተገነዘቡ የገለጡት ካህናቱ ክህነታዊ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተማር አደራቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው ሥልጠና የፊታችን ዓርብ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

የሎጥ ዘመን በዚች ቅድስት ሀገርና ሕዝብ ላይ አይደገምም!!!

ዘመኑ የሎጥ ዘመን ሆኖአል፡፡ በዚያ ዘመን የተነሡ የሰዶምና የገሞራ ሕዝቦች እግዚአብሔርን እያወቁ “እናይ ዘንድ ሥራውን ያፋጥን፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ምክር ይምጣ”(ኢሳ.5፡19)በማለት እግዚአብሔርን በመገዳደር ወንዱ ከወንዱ ጋር ሴቷም ከሴቷ ጋር በመዳራታቸው ምክንያት እግዚአብሔር ተቆጥቶ ከሰማይ እሳትና ዲንን በማውረድ ፈጽሞ ያጠፋቸው ሕዝቦች ናቸው፡፡(ዘፍ.18፡16-32፤19)እነርሱን ያጠፉአቸው ዘንድ የተላኩም መላእክት የእግዚአብሔር ቁጣ በእነዚህ ላይ ምን ያህል  እንደነደደ ሲገልጡ “እኛ ይህቺን ስፍራ እናጠፋታለንና ጩኸታቸውም (ተግዳሮታቸውም)  በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋት ዘንድ እግዚአብሔር ልኮናል”(ዘፍ.19፡13)  ብለዋል፡፡ በዚህ ዘመንም እንደ ምዕራባውያኑ የእግዚአብሔርን ሕልውና ሽምጥጥ አድርገው የካዱ ወገኖች በሀገራችን ውስጥ ተነሥተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች ይህን ጸያፍ የሆነ ድርጊታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ በገንዘብ ፍቅር በሰከሩ ግብረ ገብ በሌላቸው ባለ ሀብቶች የሚደገፉ ናቸው ፡፡ ነገር ግን ማንም እንዳይስት ይጠንቀቅ፡፡  እነዚህ ወገኖች ለገንዘብ በማጎብደድ በዚህ ደሃ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ባሕሉና ሃይማኖቱ ፈጽሞ የማይፈቅደውን ከተፈጥሮ ሥርዐት የወጣውን ግብረ ሰዶማዊነትን ለገዛ ጥቅማቸው ሲሉ እንዲስፋፋ እየደከሙ ይገኛሉ፡፡

 

የምድሪቱም ሳይንቲስቶች በእነርሱ ላይ ሠልጥኖ የሚገዛቸውን የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈጸም ሲሉ ግብረ ሶዶማዊነትን ተፈጥሮአዊ ነው በማለት ሕዝቡን ያወናብዳሉ፤ ለእነርሱም ከለላ ይሰጣሉ፡፡ የእነዚህ የሰይጣን የግብር ልጆች ቃልን የሚሰማና የሚቀበል ወገን እግዚአብሔር “በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚመልስ ሰው ርጉም ይሁን”(ኤር.17፡5) እንዳለ የተረገመ ነው፡፡  ለመሆኑ ስለነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለእነዚህ ደፋሮች “እውነትን በዓመፃቸው ለሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ስለእግዚአብሔር ሊታወቅ የሚችለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና፡፡ የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርንነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ”፡፡ (ሮሜ.1፡18-21)በማለት የመሰከረባቸው ሲሆኑ “ጥበበኞች ነን ሲሉ የደነቆሩ ሰውንና ገንዘብን ወደ ማምለክ የመጡ በግብራቸው አራዊቶችን የመሰሉ እንዲሁም በድፍረት ይህን ጸያፍ ተግባር ተለማምደው ከዚህ ክፉ ልማዳቸው  መውጣት የተሳናቸው ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህና አጫፋሪዎቻቸው እግዚአብሔር ከመንጋው የተለዩ ይሆኑ ዘንድ በክፉ ምግባራቸው የገለጣቸውና እንደ ምርጫቸው ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ የሰጣቸው ወገኖች ናቸው፡፡ ልዩ መለያቸውም ወንዱ ከወንዱ ጋር ሴቷም ከሴቷ ጋር መዳራታቸውና ዓመፃ ሁሉ ግፍን መመኘትንና ክፋት የሞላባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡(ሮሜ.1፡26)

 

እነዚህ ወገኖች ግብረ ሶዶማዊነት ተፈጥሮአችን ነውና ልንከለክል አይገባንም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በእውን ተፈጥሮአቸው ከእኛ ተፈጥሮ የተለየ ነውን?ተፈጥሮአቸውስ ከሆነማ እንደ ሕጋዊው (ወንድና ሴት) ጋብቻ ድንበር ዘመን ባሕል ሳያግደው በሀገሩና ሕዝቡ ሁሉ ዘንድ በተፈጸመ ነበር፤ ተቃውሞም ባልገጠመው ነበር፡፡ ለአፈጻጸሙም የገንዘብ፣ የልዩ ልዩ ምክንያቶች ከለላና የሰልፍ ሆታ ባላስፈለገው ነበር፡፡ ይህ የሚያስረዳው ፍጹም ከተፈጥሮ የወጣ ክፉ ምግባር መሆኑን ነው፡፡ስለዚህም የዚህ ነውረኛ ድርጊት አቀንቃኞች ተፈጥሮአዊ አይደለምና ምክንያትንና ጥግ ፈለጉለት፡፡ ለዚህም በሰብአዊ ሕሊና የሚደረገውን ዓለማቀፋዊ ልግስናን (ዕርዳታን) እንደ መደራደሪያ (እንደማባበያ) ተጠቀሙበት፡፡ አቤት ክፋት፡፡

 

እነዚህ ወገኖች ተፈጥሮአችን ከእናንተ ጋር አንድ ነው የሚሉ ከሆኑ ተፈጥሮአዊ ጠባያቸውን ጠብቀው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሊኖሩ ይገባቸው ነበር፡፡ በጥቂቶች ላይ ብቻ የሚታይ ነው ከተባለስ በሰዶምና ገሞራ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይህ አስነዋሪ ተግባር ስለምን ታየ? (ዘፍ.18፡20፤19፡4) ተፈጥሮአዊ ከሆነስ እንዴት እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ እሳትንና ዲንን አዝንቦ ፈጽሞ አጠፋቸው? የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ እነርሱ አሳብ ከሆነ ከመጀመሪያው ስለምን ወንድ ብቻ ወይም ሴት ብቻ አድርጎ ሰዎችን አልፈጠራቸውም? ስለምንስ ሰዎችን ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው? ለዚህ የመከራከሪያ አሳብ የሚሰጡት አንዳች መልስ የላቸውም፡፡ ይልቁኑ ቅዱስ ጴጥሮስ “ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነው”(2ጴጥ.2፡19) እንዲል የእግዚአብሔርን ሕልውና በመካዳቸውና ለሰይጣን ፈቃድ በመገዛታቸው ለዚህ ነውረኛ ድርጊት ተላልፈው የተሰጡ የጥፋት ልጆች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖችና አጫፋሪዎቻቸው ተፈጥሮአዊ የሆነውን ሕግ ሽረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሲቃወሙ ትንሽ እንኳ እፍረት አይሰማቸውም፡፡ ይህ ነገ በራሳቸው ልጆቻቸው ላይ እንደሚፈጸም ዞር ብለው ማሰብ ተስኖአቸዋል፡፡ ነገር ግን በሕዝቡ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ እንዲነድ ታውረው ይህን አጸያፊና ነውረኛ ተግባርን ለማስፋፋት ሲሉ የኑሮው ውድነት ባስጨነቀው ምስኪን ሕዝብ ላይ ሌላ መከራ ሊጭኑበት ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ ይህን ምስኪን ሕዝብ ለእነዚህ ግብረ ሰዶማውያን አካሉን እንዲገብር ሲሉ ይህን አስነዋሪ ድርጊት በመዲናችን በአዲስ አበባ ያስተዋውቃሉ፡፡ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ጥቂት ባለሀብቶችም ለእነርሱ ከለላና ጥብቃ በማድረግ ክፉ ተግባራቸውን እንዲፈጽሙ ለምቾቶቻቸው ይጠነቃቃሉ፡፡ ይህ በእውነት እጅግ አጸያፊና በዚህ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ፈጽሞ ያልታየና ያልተሰማ ታላቅ አዋራጅና አጸያፊ ተግባር ነው፡፡ የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮም ይህን ድርጊት እጅግ ፈጽሞ ይቃወማል፡፡

 

ስለዚህም እንደነዚህ ካሉ ወገኖች ጋር በምንም ነገር የሚተባበር ክርስቲያን ቢኖር  እንደ ሎጥ ሚስት በራሱ ላይ ጥፋትን የሚያመጣና ሐዋርያት ያስተማሩንን ትምህርት የሚቃወም የወንጌል ጠላት ነው፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን ካስተማረችው ትምህርት ውጪ ተፈጥሮአዊ ሕግን የሚጻረር ይህን እኩይ ተግባርን የሚፈጽም፣ የሚያበረታታ፣ የሚያስተምር ክርስቲያን ሁሉ ከክርስቶስ ኅብረት የተለየና የተወገዘ ነው፡፡ (ሮሜ.2፡26፣32፤2ቆሮ.11፡16፤ገላ.1፡9)

 

አምላከ ነዳያን ይህቺን ሀገር ከእነዚህ ከጠገቡ ክፉ አውሬዎች እኩይ ተግባር ይጠብቃት፤ ከዚህ ከነውራቸው የሚጸጸቱበትን ልቡና ይመልስላቸው፡፡ የሚረዱአቸውንም ሐሳባቸውን ወደ በጎ ይመልስ ለዘለዓለም አሜን!!