Picture3

ማኅበረ ቅዱሳን ሐዋርያዊ አገልግሎት በአርሲ ሀገረ ስብከት አካሔደ

ታኅሣሥ 20/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሐዋርየዊ Picture3አገልግሎት በአርሲ ሀገረ ስብከት ከኅዳር 29/2004 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 10/2004 ዓ.ም ለ11 ተከታታይ ቀናት በተለየዩ ወረዳዎች አካሔደ፡፡ 27 አባላት የተሳተፉበት ሐዋርያዊ አገልግሎት በተመረጡ 6 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በአሰላ ከተማ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያፈራቻቸው የማኅበረ ቅዱሳን ሰባኪያነ ወንጌል አማካይነት በአውደ ምሕረት ላይ ለምእመናን ሰፋ ያለ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡ በማኅበሩ መዝሙር ክፍል አባላት አማካይነት ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩትን የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቀ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡

በአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ማኅበረ ቅዱሳን በያዘው እቅድ መሠረት የሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎት እንዲካሔድ በመፍቀድና በመከታተል እንዲሁም አባታዊ ምክራቸውንና ቡራኬ በመለገስ፤ በጸሎት በማገዝ አገልግሎቱ የተሳካ እንዲሆን አባታዊ ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በ6ቱ ወረዳዎች ማለትም በአሳሳ ደብረ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል፤ በሳጉሬ ደብረ ገነት ልደታ ለማርያም፣ በበቆጂ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ በኢተያ ቅዱስ በዓለወልድ፤ በሁሩታ ደብረ መዊዕ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በአሰላ ደብረ መድኃኒት መድኀኔዓለም እና በዴራ ደብረ መድኀኒት መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያናት በእያንዳንዳቸው ለ2 ቀናት /በበቆጂ አንድ ቀን ብቻ/ የቆየ የወንጌል ትምህርትና ያሬዳዊ ዝማሬ ቀርቧል፡፡ አገልግሎቱም ምዕመናን በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲቆሙ ከተለያዩ ኢ አማኒያን የኑፋቄ ትምህርት እንዲጠበቁ፤ ከእነሱም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትሻውን አገልግሎት እንዲያበረክቱ ፤ንስሐ ገብተው የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለው የመንግሥቱ ወራሾች ይሆኑ ዘንድ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ላይ ያተኮረ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም በሳጉሬ ቅድስት ሥላሴ፣ በአሰላ ደብረ ምጽላል ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በቅድስት ሥላሴ /ቤተ ሥላሴ/ ቤተ ክርስቲያናት ቅዳሜና እሑድ ከቅዳሴ በኋላ በማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ መምህራን ለምእመናን ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

በአገልግሎት ዙሪያ ያነጋገርናቸው ምእመናን በሰጡት አስተያየት እምነታቸውን ለማወቅና ለመረዳት እንዲሁም ከመናፍቃን Picture2የኑፋቄ ትምህርት ይጠበቁ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና መሠረት ያደረገ ትምህርት በቀጣይነት እንዲሰጥ፤ እንዳይቋረጥባቸው ተማጽነዋል፡፡ “በሕፃንነቴ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እሰማቸው የነበሩ መዝሙራትን እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ እባካችሁ እኛንም ልጆቻችንም ከዳንኪራ ባልተናነሰ በስመ መዝሙር ከሚቀርቡና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ካልጠበቁ ጩኸቶች ታደጉን፡፡” ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ ውዥንብር ውስጥ ይከታቸው የነበረው የያሬዳዊ ዜማ አቀራረብ የማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ክፍል ያቀረበውን ከተመለከቱ በኋላ ትክክለኛውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት የጠበቁትን ለመለየት እንደረዳቸውና ማኅበረ ቅዱሳን እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ “የማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን በሚዘምሩበት ወቅት በተለይ ሴቶች እኅቶቻችን ሲዘመሩ የሙሴ እኅት ማርያም እስራኤላውያን ባህረ ኤርትራን በተሻገሩበት ወቅት ከበሮ ይዛ እግዚአብሔርን ያመሰገኘችበት ዝማሬ አስታወሰኝ፡፡ ሰናይ እገሪሆሙ ለእለ ይእዜኑ ሰናየ ዜና /ኢሳ.52 እንዲል የምሥራች የሚናገሩ ሰዎች እግሮች አመጣጥ መልካም ነው፡፡ መልካም ዜና የሚናገሩ ናቸውና፡፡”በማለት በአገልግሎቱ በመደሰት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡በተጨማሪም ከየማዕከላቱ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በሐገረ ስብከቱ 27 ወረዳዎች ውስጥ 500 ቤተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በሁሉም ወረዳዎች በመንቀሳቀስ 15 የወረዳ ማእከላት 11 የግንኙነት ጣቢያዎችና 1 ልዩ ማእከል በማቋቋም ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የተካሔደው ሐዋርያዊ የአገልግሎት መርሐ ግብር ኅዳር 29/2004 ተጀመሮ በ6 ወረዳዎችና በአሰላ ከተማ አከናውኖ ታኅሣሥ 10/2004 ዓ.ም በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰ ሲሆን በአጠቃላይ ከ20000 በላይ ምእመናን በመርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት ተከታትለዋል፡፡