ለደቡብ ትግራይ ማይጨው እና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት ሥልጠና በመሰጠት ላይ ነው፡፡

ታኅሣሥ 5/2004 ዓ.ም

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ሥልጠናው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ትግራይ ማይጨውና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት እንዲሁም በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በዋናው ማእከል ምክክር የተዘጋጀው ነው፡፡

ከታኅሣሥ 2 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ትግራይ ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና አዳራሽ በማይጨው ከተማ ከ 11 ወረዳዎች ለተወጣጡ 150 ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አስታወቁ፡፡ ከታኅሣሥ 2 እስከ 6 ቀን 2004 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ሥልጠና የተገኙት የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት፣ የአብነት መምህራን፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች መሆናቸውን ብፁዕነታቸው ገልጠዋል፡፡

ሥልጠናው በተሳካ መልኩ እንዲከናወን ሀገረ ስብከቱ የቅድሚያ ዝግጅት ማድረጉን ያስታወቁት ብፁዕነታቸው “ከአዲስ አበባ ተነሥታችሁ በማታውቁት መንገድ አስፋልቱን መሪ አድርጋችሁ ወደ ማይጨው ሀገረ ስብከት የመጣችሁ ልጆቻችን እንኳን ደኅና መጣችሁ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባልና አካል የሆነ ማኅበር ነው፤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን በቂ ግንዛቤ የሌላቸው ወገኖቻችን የተለያየ አሉባልታ ሊያስወሩ ይችላሉ፣ እናንተ ግን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተከናወነ ያለውን ሤራ ለማስቆም እንደምትሮጡ ምስክሮቹ እኛ ነን፡፡ ቅን አገልግሎታችሁን ስለተገነዘብን ሓላፊነቱን ወስደን ይህን ሥልጠና በጋራ አዘጋጅተናል፡፡ የጤፍ ዘር ለመልቀም አልመቸው ያለ ዝንጀሮ ከዳር ላይ ቆሞ ‘ጤፍን የዘራ ገበሬ ገበሬ አይባልም’ አለ እንደሚባለው ማኅበረ ቅዱሳንም ሤራችንን ያውቅብናል ብለው የሚሠጉና የሚፈሩ ተሐድሶ መናፍቃን በኑፋቄ ትምህርታቸው ብዙዎችን ለማሰናከል የሚያደርጉትን የጥፋት ሥምሪት ከነላኪዎቻቸው ስለምታውቁባቸው ላትስማሟቸው ትችላላችሁ፡፡ እውነተኛ ዓላማ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጸሎት፣ በሃሳብና በቅን ምክራቸው እንደማይለዩዋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ጉባኤያችንን ይባርክልን” ሲሉ አባታዊ ቃለ ምዕዳናቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት አባ ዘካርያስ ሕሉፍ ባስተላለፉት መልእክት «ካህናት የተሰጣችሁን አደራ በትክክል እንድትወጡና ዘመኑን በመዋጀት እንድታስተምሩ አሳስባለሁ፡፡ ይህ ሥልጠና የመመካከሪያ መርሐ ግብር በመሆኑ በንቃትና በትጋት ሥልጠናውን እንድትከታተሉ አደራዬ ጥብቅ ነው፡፡ መርሐ ግብሩን አመቻችቶ መምህራንን ከአዲስ አበባ በመላክ፣ መጻሕፍት፣ ደብተር፣ እስክሪቢቶ፣ የሠልጣኞችን የምሳ ወጪ እና የውሎ አበል በመሸፈን ማኅበረ ቅዱሳን ስላበረከተው መንፈሳዊ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ» ብለዋል፡፡

ታኅሣሥ 2 ቀን የተጀመረው ሥልጠና በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ፣ የነገረ ሃይማኖት መግቢያ፣ አእማደ ምሥጢራት፣ ነገረ ድኅነት፣ ነገረ ቅዱሳን እና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሰጡ ተገልጧል፡፡

ሥልጠናው በተጀመረበት ዕለት ስለ ተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ በስፋትና በጥልቀት ተዳስሷል፡፡ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያከናወኑት ሴራ ምን ያህል ከባድና አሳዛኝ እንደ ሆነ የተደረሰበት የጽሑፍ፣ የምስልና የድምጽ መረጃ ለካህናቱ ቀርቧል፡፡ ሠልጣኝ ካህናቱም መናፍቃን መልካቸውን እየቀያየሩ ሃይማኖታችንን ለማስነቀፍ የእኛን ቀሚስ ለብሰው፣ አስኬማችንን ደፍተው፣ መነኮሳትና ባሕታውያን እንዲሁም አጥማቂዎች መስለው በወርሐ ጾም በየሥጋ ቤቱ እየገቡ ሆን ብለው ሥጋ እየበሉ በአከባቢያችን የታዩ ተሐድሶ መናፍቃን ነበሩ ሲሉ ካህናቱ በዓይናቸው ያዩዋቸውንና በተግባር የገጠሟቸውን የተለያዩ ክሥተቶች በተጨባጭ መረጃ በቁጭት ተናግረዋል፡፡

በተሰጠው መረጃ የመናፍቃኑ ተልእኮ ለቤተ ክርስቲያን ፈተና መሆኑን በጥልቀት እንደ ተገነዘቡ የገለጡት ካህናቱ ክህነታዊ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተማር አደራቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው ሥልጠና የፊታችን ዓርብ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡