ቅዱስ ጳውሎስ(ለሕፃናት)

ግንቦት 23 2003 ዓ.

በእመቤት ፈለገ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ዛሬ ስለ አንድ ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያ ታሪክ እንነግራችኋለን በደንብ ተከታተሉን፡፡
 
በድሮ ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማ የሚኖር ክርስቲያኖችን የሚጠላና በእነርሱ ላይ ክፉ ሥራ የሚሠራ ሳውል የሚባል ሰው ነበረ፡፡ ደማስቆ ወደምትባል ከተማም ክርስቲያኖችን ሊገድል ጉዞ ጀመረ፡፡
 
ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው ብርሃን በዙሪያው አንጸባረቀበት እርሱም በምድር ላይ ወደቀ በዚያን ጊዜ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምጽ ሰማ፡፡ ሳውልም “አቤቱ አንተ ማን ነህ?” አለው፡፡ እርሱም “አንተ የምታሳድደኛ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡” አለው ፡፡ልጆች ሳውል የሚያሳድደው ክርስቲያኖችን ሆኖ ሳለ ጌታችን ለምን እኔን ታሳድደኛለህ ብሎ ጠየቀው? ምክንያቱ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቤተ ክርስቲያንን እና ክርስቲያኖችን መጥላት ወይም በእነርሱ ላይ ክፉ ነገር ማድረግ ማለት በአምላካችን ላይ ክፉ ነገር ማድረግ ማለት ስለሆነ ነው፡፡
 

ሳውል ከወደቀበት ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ነገር ማየት አልቻለም ስለዚህ ሰዎች እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት “ሦስት ቀንም ዐይኑ ማየት አልቻለም፤ አልተመገበም፡፡ በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀመዝሙር ነበር፤ ጌታችንም ለሐናንያ ተገልጦ ሳውል የሚባል ሰው ይሁዳ በሚባል ሰው ቤት እየጸለየ ነው አግኘው አለው፡፡ ሐናንያም እጅግ በጣም ፈራ፡፡ ለጌታችንም “ይህ ሰው በክርስቲያኖች ላይ ምን ያህል ክፉ ነገር እንዳደረገ ሰምቻለሁ፡፡ ወደዚህም የመጣው ይህን ሊያደርግ ነው” አለው፡፡ ጌታችንም እንዲህ አለው “ሂድ ይህ ሰው ከዛሬ ጀምሮ ማንንም ክርስቲያን አይጎዳም ይልቁንም ሰዎችን የሚያስተምር ትልቅ አባት ይሆናል” አለው፡፡ ሐናንያም ወደተባለው ቤት ገባ፤ በሳውል ላይም እጁን ጭኖ “ወንድሜ ሳውል ሆይ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ኢየሱስ ክርስቶስ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው፡፡ ሳውልም ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ ምግብም በላ፡፡
 
ጌታችን ሳውል እንዲድን ብዙ ነገር አዘጋጀለት ሐናንያን ላከለት ደግሞም ማየት እንዲችል አደረገው፡፡ የሠራውን ሁሉ ይቅር ብሎት ክርስቲያን አደረገው፡፡ በኋላም ሳውል ትልቅ ሐዋርያ ሆኖ ቅዱስ ጳውሎስ ተባለ፡፡ 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ብፁዕ አቡነ በርናባስ፣ የካቲት 12 2003 ዓ.ም

የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ከባሕር ዳር ማዕከል

ግንቦት23፣ 2003ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ በርናባስ ግንቦት 20 ከምሽቱ 3.00 ማረፋቸው ይታወሳል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርናባስ፣ የካቲት 12 2003 ዓ.ምየብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም የተፈጸመ ሲሆን በሥርዓቱ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣  ብፁዕ አቡነ አረጋዊ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ  ብፁዕ አቡነ ሄኖክ፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜና የክልሉ ባለ ሥልጣናት፣ ከአዲስ አበባ የመጡ የደብር አስተዳዳሪዎች፣ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ የመጻሕፍት ትርጓሜ መምህር የሆኑት መምህር ደጉ ዓለም ካሣ፣  የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ ጸሐፊ አቶ ዘላለም አጥናፉ እንዲሁም ሌሎች በርካታ እንግዶችና ምዕመናን ተገኝተዋል፡፡

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ በብፁዕነታቸው ጥረት የተመሠረተውና ሀገረ ስብከቱ የሚገኘው የቤዛ ብዙኃን አጸደ ሕፃናት ተማሪዎች፣ በማኅበረ ቅዱሳን የአቡነ ጎርጎርዮስ አጸደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም የማኅበረ ቅዱሳን ባሕር ዳር ማዕከል የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢና ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የአበባ ጉንጉን በመያዝ አስከሬናቸውን አጀበዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ከቀኑ 6.00 ላይ የሀገረ ስብኩቱ መንበር በሆነው በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም ተፈጽሟል፡፡

 

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት

ለአባ የትናንቱ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ግንቦት 23፣2003ዓ.ም

ያለ ማወቅ ጽልመት ሀገሩን ሲወርሰው ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት

ማን ነበር ትውልዱን በወንጌል ያረሰው?

አባ ተክለ ሃይማኖት አባ የትናንቱ

ትዝ አለኝ ተጋድሎው ውል አለኝ ሕይወቱ

በቆላ በደጋ የተንከራተትኸው

የሃይማኖትን ተክል ዞረህ የተከልኸው

የኢትዮጵያ ፀሐይ አባ ተክለ አብ

እስቲ መለስ ብዬ ሥራህን ላስብ

በቀንና በሌሊት ከላይ ታች ዞረህ

ሕዝቡን አዳረስከው አስተምረህ መክረህ

ስንት ነበር አባ ‹የጉዞ አበልህ›?

ያረፍህበት ስፍራ የተዘጋጀልህ

የት ነበር መኝታው ጎን ማሳረፊያህ?

ንገረኝ እባክህ ማን ነበር የሸኘህ?

እሳት አባቴ ሆይ እኔ አመድ ልጅህ

በዘመኔ ቋንቋ እስኪ ልጠይቅህ?

/ምንጭ፦ ሐመር መጽሔት ግንቦት 2003 ዓ.ም እትም/ 

Abune Bernabas.jpg

የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርባናስ አረፉ

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
ግንቦት 21/2003 ዓ.ም.
Abune Bernabas.jpgከሃያ ዓመታት በላይ ቤተ ክርስቲያንን በጵጵስና በቅንነት ያገለገሉት የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ በርናባስ አረፉ፡፡

ርክበ ካህናትን ተከትሎ የሚደረገውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ለመካፈል ወደ አዲስ አበባ መጥተው በነበሩበት ወቅት ታመው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ የምልዐተ ጉባኤውን የመጨረሻውን ቀን ማለትም የማክሰኞ ዕለት ስብስባ አልተካፈሉም፡፡ በዚህም ሁኔታ አርብ ግንቦት 19 ቀን 2003 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተነስተው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ጋር ደብረ ማርቆስ ገብተው ያደሩ ሲሆን ወደ ሀገረ ስብከታቸው መቀመጫ ባሕር ዳር  ቅዳሜ 8፡00 ሰዓት ገብተው በመዋል ማታ 1፡30 ላይ እንዳረፉ ታውቋል፡፡

እረፍታቸው ከተሠማ በኋላ በዛሬው ዕለት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር በሀገረ ስብከቱ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የብፁዕነታቸው መኖሪያ ቤት ሀዘንተኛውን አጽናንተዋል፡፡
 
የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ.ም በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም  የሚፈፀም  ሲሆን  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ምዕመናን በሚገኙበት ይፈጸማል፡፡

ብፁዕ አቡነ በርባናስ የተወለዱት በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ወረዳ ልዩ ስሙ ፉቢ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በ1911 ዓ.ም. ሲሆን፥ በ1983 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ አንብሮተ እድ ጵጵስና ተሹመው በተለያዩ ኃላፊነቶች እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል፡፡

“ሕፃናት ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” ሉቃ.18÷16 (ለሕጻናት)

በአዜብ ገብሩ

ግንቦት 20፣ 2003ዓ.ም

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? በዛሬው ጽሑፋችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕፃናትን ምን ያህል እንደሚወድ የሚያስረዳ ጽሑፍ ይዘን ቀርበናል÷ በደንብ አንብቡት እሺ፡፡

በአንድ ወቅት ጌታችን ለምለም የሆነ ሣር ባለበት ቦታ ላይ ብዙ ሰዎች በዙሪያው ከበውት ቆመው ያስተምራቸው ነበር፡፡ ሰዎቹም የእርሱን ጣፋጭ የሆኑ ቃላት ለማዳመጥ ከተለያየ ቦታ የተሰበሰቡ ነበሩ፡፡ ሁልጊዜ ከጌታ የማይለዩት ዐስራ ሁለቱ ሐዋርያትም በዚያ ነበሩ፡፡ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጌታ በሄደበት ቦታ ሁሉ ይሄዳሉ፤ ከእርሱ ጋር ይጸልያሉ፤ እርሱንም ያገለግሉታል /ይታዘዙለታል/፡፡ ታዲያ ልጆች ጌታችን ቁጭ ብሎ የተሰበሰቡትን ሕዝብ እያስተማረ ሳለ ልክ እንደ እናንተ ሕፃን የሆነ ልጅ ወደ ጌታችን እየሮጠ መጣ፡፡ እንዲህም አለው “ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት እፈልጋለሁ አለ፡፡” ከዚያም ዘወር ሲል እንደ ፀሐይ የሚያበራውን የጌታችንን ፊት አየ፤ ጣፋጭ የሆነውንም የጌታችንን ድምጽ ሰማ፡፡ ጌታችንም የሕፃኑን እጅ ይዞ “ከእኔ ጋራ ና” አለው፡፡ ወደ ሐዋርያትም ዘወር ብሎ እንዲህ አላቸው፡፡ “በመንገድ ሳለን ስለምን ትከራከሩ ነበር?” እነርሱም ዝም አሉ፡፡ ምክንያቱም በመንገድ ሳሉ ከእኛ መካከል ከሁላችን የሚበልጥ ትልቅ ማነው? እያሉ ይከራከሩ ስለነበር ነው፡፡ ጌታችን ለጥቂት ጊዜ ዝም ብሎ ከቆየ በኋላ ሕፃኑን “ወደ እኔ ና” አለው ሕፃኑም ወደ ጌታችን ተጠጋ፡፡ ጌታችንም ሕፃኑን አንስቶ አቀፈው፡፡ ለሐዋርያቱም እንዲህ አላቸው “ከእናንተ መካከል ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁላችሁ ይበልጣል፡፡” ሐዋርያትም ጌታችንን በትኩረት ይሰሙት ነበር፡፡ የሚናገረውንም ቃል ለመረዳት ይሞክሩ ነበር፡፡ ሕፃኑ ልጅ ግን ጌታችንን የተናገረውን እንዲያስረዳው ጠየቀው ጌታችንም “ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው÷ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነርሱ ላሉት ናትና አለ፡፡”

ልጆች ጌታችን እንዴት እንደሚወዳችሁ አያችሁ? እናንተም ትወዱታላችሁ አይደል አዎ በጸሎታችሁ ወቅት ጌታን እንደምትወዱት ልትነግሩት ይገባል፡፡ እርሱ የሚወደውንም መልካም ሥራ ልትሠሩ ይገባል፡፡ ልትነግሩት ይገባል፡፡ ከጓደኞቻችሁ ጋር ሳትጣሉ በፍቅር ልትኖሩም ይገባል፡፡ ይህን ካደረጋችሁ ጌታችን እጅግ በጣም ይወዳችኋል፡፡ ሁሌም ከእናንተም ጋር ይሆናል ማለት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሐዊረ ሕይወት መንፈሣዊ ጉዞ ቁጥር 2

ሐዊረ ሕይወት ቁጥር 2 መንፈሣዊ ጉዞ

ሐዊረ ሕይወት መንፈሣዊ ጉዞ ቁጥር 2

   

አባታችን ሆይ(የመጨረሻው ክፍል)

 ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
አቤቱ ወደፈተና አታግባን÷ ከክፉ አድነን እንጂ÷ መንግሥት ያንተ ናትና÷ ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን።
ግንቦት 19/2003 ዓ.ም.

ጌታችን በዚህ ቃል የእኛን ደካማነት በማሳወቅና መታበያችንን በማጥፋት ፣ ፈተናዎች በእኛ ላይ ከመሠልጠናቸው በፊት  በትሕትና በመገኘት ልናርቃቸው እንደምንችል በግልጽ አስተማረን ፡፡ በዚህ ምክንያት ድላችን እጅግ ታላቅ ይሆናል ፡፡ ሰይጣን ከፊት ይልቅ በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ይወድቃል ፡፡ እንዲህ ስል ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ በማስተዋል ልንሆን ይገባናል ሲል ነው  ፡፡ ልቡናችንን ሰብስበን መጸለይ ከተሣነን ግን ዝም ማለትን በመምረጥ የፈተናው ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ በትዕግሥት ልንጠባበቀው ይገባናል ፡፡  እንዲህ ካደረግን ከከንቱ ውዳሴና ከትዕቢት ነጻ እንደወጣን ማስተዋል ይቻለናል ፡፡

በዚህ ቦታ ሰይጣንን “ክፉ” እንዳለው እናስተውላለን ፡፡ በዚህም ያለ ዕረፍት እኛን ለመጣል በሚፋጠነው ሰይጣን ላይ ጦርነትን ልንከፍት እንዲገባን አሳሰበን ፡፡ ነገር ግን ሰይጣን ክፉ ሲባል ከፍጥረቱ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ነበር ማለቱ ግን አይደለም ፡፡ በተፈጥሮ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት የለም “ብርሃን ከሌለ ጨለማ እንደሚሆን ደግ ሥራ ከሌለ ክፉ ሥራ ይነግሳልና፡፡ ነገር ግን  እኛው ነን ክፋትን  በፈቃዳችን ከተፈጥሮአችን ጋር የምንደባልቀው ፡፡ ስለዚህም እኛን በኃጢአት ስላሰናከለን ቅድመ ጠላታችን ተባለ ፡፡ እንዲሁም ያለ አንዳች ምክንያት እኛ ላይ ጦርነትን በመክፈቱ ጠላታችን ተሰኝቶአል ፡፡ ስለዚህም “ ከፈተና አድነን” ብለን እንድንጸልይ ሳይሆን “ከክፉ አድነን አንጂ” ብለን እንድንጸልይ አዘዘን ፡፡ እንዲህም ሲል በወዳጆቻችን ክፉ ሥራ ደስ ባንሰኝም ፤ በእነርሱ እጅ ማንኛውንም በደል ብንቀበል ፤ ለክፋታቸው  ምክንያት እርሱ ነውና  እነርሱን ጠላት ከማድረግ ተቆጥበን  ጠላትነታችንን በሰይጣን ላይ ሊሆን ይገባል ፡፡

ወደ ፈተና እንዳንገባ ጠላታችን ማን እንደሆነ ለይቶ በመጠቆም ፣ በእርሱ ተግባር እንድናዝን በማድረግ ፣ ባለማስተዋል የምንፈጽማቸውን ክፉ ተግባራትን ከእኛ ቆርጦ በመጣል ፣ እንዲሁም መንፈሳችንን በማነቃቃትና በማትጋት የጽድቅ ዕቃ ጦርን የሚያስታጥቀን ንጉሥ ማን እንደሆነ በማስታወስ እንዲሁም እርሱ ከሁሉ በላይ ኃያል እንደሆነ በማመልከት “መንግሥት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን” እንድንል አዘዘን ፡፡

እናም በእርሱ ታምነን ያዘዘንንም ወደ ተግባር መልሰን ለመፈጸም እንትጋ ፡፡ እርሱ ንጉሣችን ከሆነ ማንንም ልንፈራ አይገባንም ፡፡ ጌትነቱን ማንም ሊቃወምና ሊያጠፋ የሚችለው የለም ፡፡ አርሱ  “መንግሥት የአንተ ናትና” ሲለን እኛን የሚዋጋውን ለጊዜው ፣ እግዚአብሔርን የሚቋቋም የሚመስለውን ሰይጣንን ለእኛ እንዲገዛ አሳልፎ እንደሚሰጠን ሲያመላክተን ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እርሱ ከእግዚአብሔር ባሪያዎች አንዱ ነው ፤ ምንም እንኳ ከተዋረዱትና ለመተላለፋችን ምክንያት ከሆኑት ወገን ቢሆንም ፡፡ እርሱ ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈቃድ ካላገኘ በቀር በእግዚአብሔር ባሮች ላይ የማደር መብቱ የለውም ፡፡ ስለምን  እኔ “ በባሮቹ ላይ” ለምን እላለሁ ፣ በእሪያዎች ላይ ስንኳ በማደር እነርሱን አስቻኩሎና አጣድፎ ለማጥፋት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድን መቀበል የግድ አለበት (ማቴ.7፥31) በእንስሳት መንጋ ላይ ከላይ ያለው እርሱ ካልፈቀደለት በቀር ከቶ ሊያድር አይቻለውም ፡፡

“ኃይል” አለ ፡፡ ስለዚህም ድክመቶችህ እጅግ ብዙ ቢሆኑም ያለሥጋት በድፍረት ለመቆም እንድትችል ሁሉን በቀላሉ መፈጸም  የሚቻለው እርሱ በአንተ ላይ መንገሡን አሳወቀህ ፡፡ በአንተም ሥራውን መከወን ለእርሱ አይሳነውም  ፡፡

“ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን”  በዚህ ወደ አንተ ከቀረቡ መከራዎች ሁሉ ነጻ ሊያወጣህ እንደሚችል ብቻ አልገለጸልህም ፡፡ ነገር ግን አንተን ማክበርና ማላቅ እንደሚቻለው አሳወቀህ ፡፡ የእርሱ ኃይል እጅግ ታላቅ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ ክብሩም እንዲሁ በቃላት ሊገለጽ የማይችል እጅግ ታላቅ ነው ፡፡ ለእርሱ የሆኑ ጸጋዎች ሁሉ ወሰን አልባና ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡  እርሱ ኃይሉ ታላቅ ክብሩም በቃላት ሊነገር የማይችል ፣ ወሰን አልባዎች እንዲሁም ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡ ድል አድራጊው እርሱ የእርሱ የሆኑትን እንዴት ባለ ክብር እንደሚያከብራቸውና ፍጹም በሆነ በራስ መተማመን እንዲሞሉ እንደሚያደርጋቸው ታስተውላለህን ?

ስለዚህም አስቀድሜ  ለማብራራትም እንደሞከርኩት በእርሱ ዘንድ  የተጠላውንና የማይወደደውን ቂምና ጥላቻን ከልባችን አስወግደን  ከንቱዎች ከሆኑት ከእነዚህ  ክፉ ጠባያት ርቀን በሁሉ ዘንድ መልካም የሆነውን መፈጸም እንዲገባን አበክሮ ሲያሳስበን ፣ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ካስተማረን በኋላ በድጋሚ መልካም የሆነው ምግባር ምን እንደሆነ ያስታውሳል ፡፡ ስለዚህም ይህን ብንፈጽም በእኛ ላይ የሚመጣብንን ቅጣትና በብድራት የምንቀበለውን በመጠቆም ሰሚዎቹ ቃሉን አክብረው መታዘዝ እንዲሻላቸው ማሳሳቡን እንመለከታለን ፡፡

“ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ” ካለ በኋላ “የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ፣ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ይቅር አይላችሁም” (ማቴ.6፥14) አለን ፡፡

በዚህም ኃይለ ቃል “ሰማይ”ና “አባት” የሚለውን ቃል በድጋሜ መጠቀሙን እናስተውላለን ፡፡ ይህም ሰሚዎቹ ትሕትናን ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ለመርዳት ነው ፡፡ በዚህ ቃል አስቀድመው እንደ አውሬ ክፉ ምግባር ይመላለስ የነበረው ሕዝብ እርሱን የመሰለ አባት ማግኘቱንና ከተራና ከተናቀ ምድራዊ አስተሳሰብ አውጥቶ በሰማያት መኖሪያውን እንዳደረገለት ሊያሳየው እንዲህ አለው ፡፡ ይህን ሲፈጽምልን በጸጋው እንዳው በከንቱ ሳይሆን እኛም የእርሱ ልጆች እንባል ዘንድ የእኛም ሥራ እንደሚያስፈልግ ሲያስታውሰን አይደለምን ?  እግዚአብሔርን ለመምሰል የበደሉንንና በእኛ ላይ ክፋት የፈጸሙትን ይቅር ከማለት በቀር የበለጠ ነገር የለም ፡፡ እርሱም አስቀድሞ “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል” በማለት በእርግጥ ስለዚህ አስተምሮናል ፡፡

ይህም እንዲሆን ፈቃዱ እንደሆነ ሊያሳየን በእያንዳንዱ ኃይለ ቃል ላይ  “አባታችን ሆይ” “ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” “በደላችንን ይቅር በለን” “ ወደፈተና አታግባን” “ከክፉ አድነን እንጂ” በማለት የጋራ ጸሎት እንድንጸልይ ማዘዙን እናስተውላለን ፡፡ በወንድሞቻችን ላይ እንዳንቆጣና በእነርሱ ላይ በጠብ ከመነሣሣት እንድንቆጠብ ሲል  በእያንዳንዱ የጸሎታችን ክፍል ላይ እነዚህን የብዙ ቁጥር ግሶችን እንድንጠቀም አዞናል ፡፡

ከዚህ ሁሉ ማሳሰቢያ በኋላ የበደሏቸውን ይቅር ከማለት እንቢ ብለው እግዚአብሔር ተበቅሎ እንዲያጠፋላቸው የሚለምኑት በእጥፍ ሕጉን በመተላለፋቸው እንዴት የባሰ ቅጣት አይጠብቃቸው ይሆን !  እርሱ እግዚአብሔር ሁሉን እንዲህ አስማምቶ መፍጠሩ አንዱን ከአንዱ እንዳይለያይ በመሻቱ አይደለምን ? ለመልካም ነገር ሁሉ ፍቅር መሠረት ነው ፡፡ እርሱ ፍቅርን የሚያፈርሱ ነገሮችን ሁሉ ከእያቅጣጫው እንዲወገዱ ያደርጋቸዋል ፡፡ ሁላችንንም ወደ አንድ በማምጣት ፍቅርን እንደሲሚንቶ በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንያያዝ ነው የፈጠረን ፡፡ አባትም ይሁን እናት ጓደኛም ይሁን ሌላ እንደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እኛን የሚወደን የለም ፡፡ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሁሉ እርሱ እግዚአብሔር  በየቀኑ ለእኛ የሚያደርገውን መግቦትና የእርሱን ሥርዓት ወዳድነት አሳይቶናል ፡፡ ነገር ግን ስለ ሕመሞቻችሁና ስለኀዘኖቻችሁ እንዲሁም በሕይወታችሁ ዘመን ስለገጠሟችሁ መከራዎች የምትነግሩኝ ከሆነ በየቀኑ እናንተ እርሱን ምን ያህል ጊዜ በክፉ ሥራችሁ እንደምታሳዝኑት ልብ በሉ ፡፡ ከዚህ በኋላ በደረሰባችሁ መከራ ሁሉ መገረምና መደነቃችሁን ታቆማላችሁ ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ስለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምክንያት በእኛ ላይ ስለመጣው ከፉ ነገር ሁሉ ልብ የማንል ከሆነ ግራ መጋባት ውስጥ ልንገባ እንችላለን ፡፡ በቀን ውስጥ ብቻ የምንፈጽማቸውን በደሎች በጥንቃቄ ብንመረምራቸው ስለመተላለፋችን እንዴት ያለ ታላቅ ቅጣት ሊታዘዝብን እንዲገባ መገንዘብ እንችላለን ፡፡              

ስለዚህም በቀን ውስጥ የፈጸምናቸውን በደሎች አንዱ ለአንዱ በመናዘዝ ፣ በደላችንን በማሰብ  የበደሉንን ይቅር ልንል ይገባናል ፡፡ በእርግጥ እያንዳንዳችን ምን በደል እንደበደልን ማወቅ ባንችልም ፣ በደሎቻችን እጅግ የበዙ መሆናቸውን መገንዘብ እችላለሁ ፡፡ ከእነዚህ ከፈጸምናቸው በደሎች መካከል ከእኛ መካከል አንዱ  የሚያውቃቸው ቢሆን እንኳን ከእነዚህ መካከል አንዱን መምረጥ ይሳነዋል ፡፡ ለምሳሌ ፡- ከእኛ በጸሎቱ ቸልተኞች አይደለንምን ? ከእኛ መካከል በትዕቢት ተሞልቶና ከንቱ ውዳሴን ሽቶ የሚጸልይ የለምን ?  ወንድሙን በክፉ የማይናገረው፣ ክፉውን የማይመኝ ፣ ወገኑን በንቀት ዐይን የማይመለከተው ፣ልብን የሚያቆስል ግፍን ቢፈጽምበት እንኳን የወንድሙን መተላለፍ ይቅር የሚል አለን ?

ነገር ግን እኛ በቤተክርስቲያን ለአጭር ጊዜ በቆየንባት ሰዓት ውስጥ እጅግ ታላቅ ክፋትን እንፈጽማለን ፡፡ ከቤተክርስቲያን ወጥተን ወደ ቤት ስንመለስ ምን ያህል የከፉ በደሎችን እንፈጽም ይሆን ? በወደቡዋ (በቤተክርስቲያን) ታላቅ የሆነ ወጀብ ካለ ወደ ኃጢአት መተላለፊያው ባሕር ስናመራ ማለትም ወደ ገበያ ሥፍራ ወሬዎች ፣ወደ የቤቶቻችን ስንመለስ በሥጋ ምቾቶቻችን ተስበን የከፉ ኃጢአቶቻችን እንዴት አንፈጽም ይሆን ?

ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነዚህ ሁሉ መተላለፎቻችን እንድንድን ያለምንም ድካም አጭርና ቀላል መንገድን ሠርቶልናል ፡፡ የበደለንን ይቅር ማለት ምን ዐይነት ድካም አለው ?  ይቅር ለማለት ምንም ዐይነት ድካም የለውም ፤ ነገር ግን እርስ በእርሳችን በጠላትነት ተፋጠን እንገኛለን ፡፡ በውስጣችን ከተቀጣጠለው ቁጣ ለመዳንና መጽናናትን ለማግኘት ፈቃዳችን ብቻ በቂ ነው ፡፡ ይቅርታ ለማድረግ ባሕር ማቋረጥ ፣ ረጅም መንገድ መጓዝ ፣ ወይም ተራራን መቧጠጥ ወይም ብዙ ገንዘብ ማጥፋት ወይም ሥጋችንን ማጎሳቆል አያስፈልገንም ፤ ነገር ግን ፈቃደኛ መሆን ብቻ በቂ ነው ፡፡ እንዲህ ከሆነ ኃጢአታችን ሁሉ አንድ ሳይቀር ይወገድልናል ፡፡

ነገር ግን እርሱን ወንድምህን ይቅር ማለት ትተህ እርሱ እግዚአብሔር ያጠፋልህ ዘንድ የምትለማመን ከሆነ ፣ ምን ዐይነት የመዳን ተስፋ ሊኖርህ ይችላል? አስቀድመህ ከእግዚአብሔር ጋር በፈቃድ አልተስማማህም ፤ ከዚህ አልፈህ የጠላትህን ጥፋት በመጠየቅህ ምክንያት እግዚአብሔርን  ታስቆጣለህን ? እርሱን ትለማመነው ዘንድ የኀዘን ማቅን ደርበሃል ፤ ነገር ግን የአውሬ ጩኸት ወደ እርሱ እየጮኽ በኃጥእ ላይ የሚመዘዙትን የጥፋት ፍላጻዎችን በራስ ላይ ታመጣለህን? ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለጸሎት ሥርዓት ባስተማረበት ወቅት ከበቀል ነጽተን ጸሎታችንን ማቅረብ እንዲገባን “… በስፍራ ሁሉ አለቁጣና አለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ ፡፡” ብሎ አስተምሮናል ፡፡ (1ኛ ጢሞ.2፥20) አንተ ምሕረትን ለራስህ የምትሻ ከሆነ ከቁጣ መቆጠብ ብቻውን ለአንተ በቂ አይደለም ፤ ነገር ግን ለዚህ ነገርም እጅግ አስተዋይ ልትሆን ይጠበቅብሃል ፡፡ አንተ በራስ ፈቃድ ራስህ ላይ የጥፋት ሰይፍን የምትመዝ መሆንህን ከተረዳህ ለአንተ መሐሪ ከመሆንህና የክፋት መርዝ የሆነውን ቁጣ ከሰውነት ከማስወገድ የበለጠ ለአንተ ምን የሚቀልህ ነገር አለ?

•    ነገር ግን ይቅር ባለማለትህ በአንተ ላይ ሊመጣ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ያላስተዋልክ እንደሆነ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ አንድ ወቅት በሰዎች መካከል ጠብ ይነሣና እርስ በእርሳቸው ክፉኛ ይነቃቀፋሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ሰው ከአንተ ምሕረትን ያገኝ ዘንድ ከእግርህ ሥር ወድቆ ይለማመንሃል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጠላት የሆነው መጥቶ አንተን እየተለማመነህ ያለውን ሰው ከወደቀበት መደብደብ ቢጀምር አንተ ከበደለህ ሰው ይልቅ አንተን የሚለማመንህን በሚመታው ሰው ላይ ይበልጥ አትቆጣምን? እንዲሁ የጠላቱን ጥፋት የሚለምን ሰው እግዚአብሔርን እንዲህ እንዲያስቆጣው ተረዳ ፡፡ አንተም እግዚአብሔርን ስለመተላለፍህ እየተለማመጥከው ሳለ ድንገት ልመናህን ከመሃል አቋርጠህ በቃልህ ጅራፍ ጠላትህን ልትገርፈው ብትጀምርና እግዚአብሔር ለአንተ የሠራልህን ሕግ ብታቃልል ፣ አንተን የበደሉህን ሰዎች ሁሉ በደል ትተህ ከቁጣ እንድትርቅ ያዘዘህን አምላክህን እርሱ ከአዘዘህ ትዕዛዛት ወጥቶ በተቃራኒው በአንተ ላይ ቁጣው እንደሚነድ አታደርገውምን? እግዚአብሔር አንተን ተበቅሎ ለማጥፋት የገዛ ኃጢአትህ በቂው ነው፡፡  ነገር ግን  በዚህ ተግባርህ ይህን እንዲፈጽምብህ እርሱን ታነሣሣዋለህን? ምንድን ነው? እርሱ ለአንተ የሰጠውን ትዕዛዝ ይዘነጋዋልን? እርሱ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ ሕግጋቶቹ ሁሉ በፍጹም ጥንቃቄ ይፈጸሙ ዘንድ የሚሻ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከአንተ እንደሚጠብቀው አድርገህ ሕግጋቶቹን ከመፈጸም ርቀህ እንደፈቃድህ በጥላቻና ሕግጋቶቹን  የምትጥሳቸው ከሆነ እጅግ የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቅህ በአርግጥ እወቅ፡፡ አጥብቆ ትጠብቀው ዘንድ ያዘዘህን ትእዛዝ ካቃለልክ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ምን በጎነትን አገኛለሁ ብለህ ትጠብቃለህ?

ከዚህም አልፈው እጅግ ቆሻሻ ወደ ሆነው ወደዚህ ምግባር የሚመለሱ ግን አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ለጠላቶቻቸው ጥፋትን የሚለምኑ ብቻ አይደሉም፤ የገዛ ልጆቻቸውን በመርገም የገዛ ሥጋቸውን የሚያጠፉ ወይም ከእርሱ የሚመገቡ ናቸው፡፡ በጥርሶቼ የልጄን ሥጋ መች በላሁ ብለህ አትንገረኝ፡፡ ይህንን በእርግጥ አድርገኸዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ቁጣ ወጥቶ በልጅህ ላይ እንዲወድቅና ለዘለዓለማዊ ቅጣት ተላልፎ እንዲሰጥ እንዲሁም ከነቤተሰቡ ተነቃለቅሎ እንዲጠፋ ከመለመን የበለጠ ምን አስከፊ የሆነ ጸሎት አለ?

ለምን እንዲህ ይሆናል ፡፡ከዚህስ የከፋ ጭካኔ ምን አለ ? እንዲህ በክፋት ተጨማልቀህ በልቡናህ ውስጥ ይህን ክፉ መርዝ አስቀምጠህ እንዴት ከቅዱስ ሥጋው ልትቀበል ትቀርባለህ ? የጌታንስ ደም እንዴት ትቀበላለህ ? አንተ “ ሥጋውን በሰይፍ ከፋፍለህ ቤቱንም ገልብጠህ አጥፋው ፣ ያለውን ሁሉ እንዳልነበር አድርገህ አጥፋቸው” የምትል ፣ እልፍ ጊዜ ሞትን እንዲሞት የምትለማመን አንተ ሰው ሆይ ፣ አንተ ከነፍሰ ገዳዮች ፈጽሞ የምትለይ አይደለህም? ወይም ሰዎችን እንደሚመገብ እንደክፉ አውሬ ነህ ፡፡

ስለዚህ ከዚህ ክፉ ሕመምና እብደት ራሳችንን እንጠብቅ ፡፡ እርሱ እንዳዘዘን እኛን ለሚያሳዝኑን ርኅራኄን በማሳየት “የሰማዩ አባታችንን”  እንምሰለው ፡፡ የገዛ ኃጢአታችንን በማሰብ ከዚህ ክፋት እንመለስ ፡፡ በቤታችንም  ከቤታችንም  ውጭ በገበያ ቦታ ፣ በቤተክርስቲያን የምፈንጽመውን ኃጢአት በጥንቃቄ በመመርመር ከዚህ ክፋት እንራቅ ፡፡

ለዚህ ትእዛዝ ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት የተነሣ ካልሆነ በቀር ለከፋ ቅጣት የሚዳርገን ሌላ ትእዛዝ የለም ፡፡ ነቢያት ሲዘምሩ ፣ ሐዋርያት በመንፈሳዊ ቅኔ ሲቀኙ ፣ እግዚአብሔርም ሲያስተምር  እኛ ግን በዓለም ተጣብቀን እንባክናለን፡፡ ራሳችንን በምድራዊ ነገሮች አሳውረናል ፡፡ በተዋንያን መድረክ ላይ የሚነበበውን የንጉሥ ደብዳቤ ለመስማት በጸጥታ እንድንቆም የእግዚአብሔርን ሕግ በጸጥታ ለመስማት አንተጋም ፡፡  በዚያ የንጉሡ ደብዳቤ ሲነበብ አማካሪዎች፣ ገዢዎች የመንግሥት ልዑካኑና ሕዝቡ ሁሉ ቃሉን ለመስማት  ይቆማል ፡፡ በዚያ ጸጥታ ውስጥ አንድ ሰው ቢንቀሳቀስና ጩኸት ቢያሰማ ንጉሡን እንዳቃለሉ ተቆጥሮበት ከባድ ቅጣትን ይቀበላል ፡፡  በዚህ ግን ሰማያዊ ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ በሁሉ አቅጣጫ ታላቅ የሆነ ሁከት ይቀሰቀሳል ፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን የላከው ንጉሥ ከዚህኛው ምድራዊ ንጉሥ እጅግ የሚልቅ ነበር ፡፡ ታዳሚዎቹም የተከበሩ ናቸው ፡፡ ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚገኙበት መላእክት ፣ ሊቃነ መላእክት የሰማይ ሠራዊቶች ሁሉ ይገኙበታል ፡፡ አኛም በምድር ያለነው ምስጋናን እናቀርብ ዘንድ ከጉባኤው ታድመናል ፡፡ “ሥራዎቹ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” ተብሎ እንደተጻፈ ፡፡ አዎን እርሱ ለእኛ የፈጸማቸው ሥራዎቹ ከቃላት ፣ እኛ ከምናስበውና ከምንረዳው በላይ ናቸው ፡፡

ይህን ጉዳይ ነቢያት ሁል ጊዜ የሚያውጁት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው በተለያየ መንገድ ይህን የእግዚአብሔርን ድል አድራጊነት ለእኛ ጽፈውልናል፡፡ ንጉሥ ዳዊት “ወደ ላይ ዓረግህ ፣ ምርኮን ማረክህ ስጦታህን ለሰዎች ሰጠህ”(መዝ.67፥18) እንዲሁም  “እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኃያል”(መዝ.23፥8)  ሌላውም ነቢይ “የኃይለኛውን ምርኮ ይበዘብዛል” ብሎአል ፡፡ የተማረኩትን ሊያስለቅቅ፣ ለእውራን ብርሃንን ሊሰጥ÷ ለሃንካሳን ምርኩዝ ሊሆናቸው ነው ጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣቱ ፡፡

 ሌላው ደግሞ በሞት ላይ ያገኘነውን ድል አሰምቶ በመናገር እንዲህ ይላል “ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሞት ሆይ ድል መንሣትህ የታለ? (ኢሳ.25፥8) በሌላ ቦታ ደግሞ ሰላምን ስለሚሰጠን ስለምሥራቹ ቃል  ሲመሰክር “ሰይፋቸውንም ማረሻ ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ”(ኢሳ.4፥4) ሲል ፤ ሌላኛው ነቢይ ደግሞ  ኢየሩሳሌምን እየተጣራ  “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ አነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፡፡ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ፡፡” ብሎ አስተምሮአል፡፡ ( ዘካ.9፥9) ሌላኛውም ነቢይ “እናንተ የምትፈልጉት ጌታ ይመጣል ::  በዚያች ቀን በእርሱ ፊት ማን ይቆማል? በእርሱ ከእስራቶቻችሁ በመፈታታችሁ  እንደ ጥጃ ትዘላላችሁ፡፡” በዚህ ነገር የተደነቀው ሌላ ነቢይም “እርሱ የእኛ ጌታ ነው ከእርሱ ጋር የሚስተካከል ጌታ ፈጽሞ  የለም” ብሎአል ፡፡

ነገር ግን እነዚህንና ከእነዚህም ከጠቀስናቸው በላይ የተነገረለትን የእርሱን ቃል ለመስማት በመንቀጥቀጥ በጸጥታ መቆም ሲገባን ፣ እኛ በምድር እንዳለን ሳንረዳ አሁንም ራሳችንን በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዳለን በመቁጠር እንጮኸለን ፣ እናወካን፣ ሰላማዊ የሆነውን ጉባኤያችንን ሁል ጊዜ ምንም በማይጠቅሙ ንግግሮች ስንረብሸው እንገኛለን ፡፡

ስለዚህ በትንሹም ፣ በትልቁም ጉዳይ ፤ በመስማትም ፣ በመሥራትም በውጭም ይሁን ፣ በቤታችን እንዲሁም በቤተክርስቲያን እጅግ ቸልተኞች ሆነናል ፡፡ እነዚህ ክፋቶቻችንን እንደያዝን የጠላቶቻችንን ነፍስ በመለመን ከባድ ኃጢአትን በራሳችን ላይ እንጨምራለን ፡፡  ከዚህ ኃጢአታችን ጋር የሚስተካከል ምን ኃጢአት አለ? በዚህ ባልተገባ ጸሎታችን ምክንያት ለእኛ ስለመዳን የሚቀርልን ምን ተስፋ አለን?

 ከእኛ የማይጠበቅ ሥራን እየሠራን በእኛ ላይ በደረሰው ውድቀትና ሕመም ልንደነቅ ይገባናልን ?  ልንደነቅ የሚገባን እነዚህ በእኛ ላይ ባይመጡብን ነው ፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሮአዊ ከሆነው ባሕርያችን መንጭቶ ነው ፡፡ ለሁለተኛው በደላችን ግን ምንም ምክንያት የምናቀርብለት አይደልም ፡፡ ለፍጥረት ሁሉ ፀሐይን በሚያወጣውና ዝናብን በሚሰጠው እንዲሁም ሌሎችንም በጎ ሥጦታዎችን በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ በጠላትነት መነሣትና እርሱን በቁጣ ተሞልቶ መናገር ፣ ምንም ምክንያት ልናቀርብለት የማንችልበት በደላችን ነው ፡፡ ከቆረቡና እጅግ ታላቅ የሆነውን ጸጋ ተቀብለው ካበቁ በኋላ ፣ ከአውሬ ይልቅ ከፍተው ፣ እርስ በእርሳቸው በጠላትነት ተፋጥጠው የሚኖሩና ጎረቤቶቻቸውን  በምላሳቸው እያቆሰሉና አፋችን በእነርሱ ደም እያራሱ በቁጥር እጅግ የከፋ ቅጣት ለራሳቸው የሚያከማቹ አሉ ፡፡

ስለዚህም ይህን መተላለፋችንን አስበን ይህን ክፉ መርዝ ከውስጣችን አስወግደን ልንጥለው ይገባናል ፡፡ አንዳችን በአንዳችን ላይ ያለንን ጠላትነት እናቁም ፡፡ ለእኛ እንደምንጸልይ አድርገን ለሰው ልጅ ሁሉ ጸሎትን እናድርግ ፡፡ እንደአጋንንት ጨካኞች ከመሆን ይልቅ እንደ ቅዱሳን መላእክት ርኅሩኀን እንሁን :: ምንም ዐይነት ጥቃት በእኛ ላይ እንዳይደርስ የራሳችንን ኃጢአትና የጌታ ትእዛዝን በመፈጸማችን የምናገኘውን ብድራት አስበን ፣ ከቁጣ ይልቅ የዋህነትን ገንዘባችን እናድርግ ፡፡ ከዚህች ምድር በምናልፍበት ጊዜ እኛ ለወንድማችን እንዳደረግንለት ጌታችን ለእኛም እንዲያደርግልን  ምንም የማይጠቅመንን ጠብን በትዕግሥት በማሳለፍ ጥለናት በምንሄዳት በዚህች ዓለም ሰላማውያን ሆነን እንመላለስ ፡፡ በሚመጣው ዓለም የምንቀበለው ቅጣት የሚያስፈራን ከሆነ ሕይወታችንን በጠብ ያልተሞላ ቀላልና ሰላማዊ እናድርገው ፡፡ ወደ እርሱም የምንገባበትን የምሕረትን በር እንክፈተው ፡፡ ከኃጢአት ለመራቅ አቅሙ ያነሰን ቢሆን እንኳ እኛን የበደሉንን ይቅር በማለት በጥበብ እንመላለስ ፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስጨንቅ ወይንም የሚከብድ አይደለም ፡፡ ጠላቶች ላደረጉን ቸርነትን በማድረግ ለራሳችንን ታላቅ የሆነውን ምሕረት ከአምላክ ዘንድ እናከማች ፡፡

በዚህ ዓለም በሁሉ ዘንድ ተወዳጆች እንድንሆን እንዲሁም እግዚአብሔር እኛን ወዳጆቹ በማድርግ ፣ የክብሩን አክሊል እንዲያቀዳጀን ለሚመጣውም ዓለም የተገባን ሆነን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ፍቅር ባለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእርሱ ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን ፡፡               

        

     

 

ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም (ክፍል አራት)

በዲ/ን ዮሐንስ ልሳነወርቅ

ከክፍል ሦስት የቀጠለ

  7. የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (The interpretation of Scripture)

(ግንቦት 19/2003 ዓ.ም)

ለቅዱስ ኤፍሬም ስለ እግዚአብሔር የሰው ልጅ እውቀት ቀዳሚ ምንጩ በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ራሱ  ስለ ራሱ እንዲባል  የፈቀደውን ነው። የእግዚአብሔር ስሞችና በቅዱስ መጽሐፍ ያሉ የተለያዩ ዓይነቶችና ምሳሌዎች በእግዚአብሔርና በሰውነት መካከል መገናኛ ነጥብን ይፈጥራሉ፤እግዚአብሔር በፈጣሪ ትሕትናው የሰው ልጅ ሊረዳው ወደ ሚችለው ደረጃ ራሱን ዝቅ አደረገ። በሰው ልጅ በኩል በእግዚአብሔር የተሰጠውን ራሱን ወደማወቅ ወደሚወስደው መንገድ የመቅረብ ዕድል ለመጠቀም ከተፈለገ ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው፤በመጀመሪያ ደረጃ ቀድመን እንደተማርነው በመጽሐፍ ቅዱስ ፈጽሞ ለእግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ስሞችንና ስእላዊ አገላለጾችን ጥሬ ትርጉም በመውሰድ ያልተገባን ስህተት  ልንፈጽም አይገባም፤በሁለተኛ ደረጃም የአንባቢው ዝንባሌ የመቀበልና ቀናነት መሆን አለበት። ቅዱስ መጽሐፍን በተሳሳተ ዝንባሌ ወይም በራሱ ግንዛቤ የሚቀርብ ከሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ምንም ዓይነት እውቀት ለማግኘት ይሳነዋል ብቻ ሳይሆን ወደ ኃጢአትም ሊገባ ይችላል።

ቅዱስ መጽሐፍ አፍአዊ(ውጫዊ) እና ውሳጣዊ(ውስጣዊ) ትርጉሞች አሉት ሊባል ይችላል ፤ አፍአዊው እኛ ታሪካዊ እውነታ እያልን የምንጠራውን ይመለከታል፤ውሳጣዊው መንፈሳዊ እውነታን ይመለከታል። በሥግው ክርስቶስ ልክ ሰውነትም ፈጣሪነትም እንዳሉ ሁለቱም እንዲሁ በአንድነት ይኖራሉ። ፡ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሔር ሁለት ሥጋዌዎች ፡መጀመሪያ ስሙን በሰው ቋንቋ በቅዱሳት መጻሕፍት ሲያስቀምጥ ቀጥሎም ሥጋን ሲዋሐድ የሚያስተውለው ትይዩነት ቅዱስ መጽሐፍን በመረዳቱ ላይና በትርጓሜውም ላይ እምነት እንደሚያስፈልግ የሚያይበትን ጠቃሚ የብርሃን ፍንጣቂ ይልካል። ከእምነት ውጭ የናዝሬቱ ኢየሱስ ታሪካዊ ምልክት ብቻ ሆኖ ይቀራል፤ ሰውነቱ ለሚያየው ሁሉ የሚታየው ነው።የክርስቶስ ፈጣሪነት የሚስተዋለው ተመልካቹ በውሳጣዊ የእምነት ዓይን ሲያይ ብቻ ነው። ለቅዱስ መጽሐፍም እንዲሁ፡ውሳጣዊ የእምነት ዓይን በሌለበት የሚታየው ሁሉ አባቶች ፊደል ብለው የሚጠሩት ውጫዊው፣ታሪካዊው የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ነው።

ይህ  ትምህርታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቅነት ነው፤ያ የትምህርት መስክ ባለፈው ክፍለ ዘመን እንደ ማደጉ ፣ስለዚህ ይህ ታሪካዊ እይታ በጣም ትኩረት የሚሰጥበት ትርጉም ሆኗል።ለቅዱስ ኤፍሬም ግና ይህ እይታ በቂ አይደለም ፤ታሪካዊ እውነታን ብቻ የሚመለከት እንደመሆኑ ፣የእምነት ዓይን ብቻ ከታሪካዊው ሰው ኢየሱስ  ወደ ሥግው ክርስቶስ መሄድ እንደሚችል ሁሉ በቅዱስ መጽሐፍም ውሳጣዊ ትርጉሙን ለመመርመር ወደ ውስጥ መዝለቅ የሚችለው የእምነት ዐይን ብቻ ነው።

ቅዱሳት መጻሕፍቱ እንደመስታወት ተቀምጠዋል

ዓይኑ ብሩህ የሆነዉም በዚያ ውስጥ የእውነትን ምስል ያያል።(Faith 67:8)

እንደ መንፈሳዊ ትምህርት አዋቂነቱ ቅዱስ ኤፍሬም በቀዳሚነት አግባብነት ባለው አመለካከትና በዚህ ውሳጣዊው የእምነት ዓይን ብቻ ሊታይ የሚችል ውሳጣዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መመልከትን ይወዳል ። እንዲያዉም ቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እግዚአብሔር የሚሉትን ውጫዊ ዓረፍተ ነገሮችን ከመመልከት ማቆምና ጥሬ ትርጉማቸውን መውሰድ ሁለቱም እኩል አደገኞች እንደሆኑ በአጽንኦት ይገልጻል፤ ስለ እግዚአብሔር ማንነት ወደ ተሳሳተ አረዳድ ስለሚወስድ፤በተመሳሳይ ጊዜም በአጠቃላይ በትሕትና በሰው ቋንቋ እንዲነገር  ለፈቀደ ለራሱ ለእግዚአብሔር የምሥጋና አልባ ንግግር ምልክትና  ስለ እግዚአብሔር ትሕትና በአግባቡ አለመረዳት ነው።

አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ኃይል ለመግለጽ በተቀመጡ በስእላዊ አገላለጾች ላይ ብቻ

አትኩሮቱን የሚያደርግ ከሆነ

እግዚአብሔር ለራሱ ለሰው ልጅ  ጥቅም ራሱን በሰወረባቸው

በእነዚያ ስእላዊ አገላለጾች አማካይነት

ያንን ኃይል በማይገባ መልኩ ይወክለዋል፤አይረዳዉምም

እንዲሁም ለዚያ ክብር አይገባም

ምንም እንኳ ከእርሱ ጋር የጋራ ነገር ባይኖረውም

ማንነቱን ወደ ሰው ልጅ ደረጃ ያወረደ

ሰውነትን ወደ ራሱ መውደድ ያመጣ ዘንድ

 እርሱ ራሱን በሰው ልጅ መውደድ ውስጥ ሰወረ(Paradise 11:6)

ቅዱስ ኤፍሬም በቅዱሳት መጻሕፍት ውጫዊ ትርጉም ላይ ምንም ፍላጎት እንደሌለው ወይም ምንም ጥቅም እንደማይገኝበት አድርጎ እንደሚረዳ ልናስብ አይገባም። ይኽ ውጫዊው ትርጓሜ የክርስቶስ ሰውነት ያህል አገልግሎት አለው።የመጽሐፍ ቅዱስ ውጫዊው ታሪካዊ ትርጉምና ውስጣዊው መንፈሳዊ ትርጉም እጅግ እንደተሳሰሩና እንደ ተያያዙ በሰው ልጅ ውስጥ እንደ ሥጋና ነፍስ፣በክርስቶስ ውስጥም እንደ ሰውነትና ፈጣሪነት ናቸው።ለቅዱስ ኤፍሬም ጠቃሚ የሆነው የእነዚህ ሁሉ ጥንዶችን ግንኙነትና መስተጋብር መረዳት ነው። በየትኛዉም መንገድ ዙሪያ ቢሆንም የአንዱን ጥቅም በመካድ በሌላኛው ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ አደገኛና የተሳሳተ ነው።ስለዚህ ከአይሁድ ጋር የነበረው የቅዱስ ኤፍሬም ጥል ፡አይሁድ እነደ እርሱ አባባል በክርስቶስ ወደ ማመን ይመራቸው የነበረውን ወደ ውስጥ ጠልቀው ማየትን መቃወማቸው፡የኢየሱስ ሰውነትን ብቻ ማየታቸው እንዲሁም የቅዱሳት መጻሕፍት ውጫዊ ትርጓሜ ብቻ ማየታቸው ነው።

አይሁድ ህጉን ማጥናትንና ምክንያት መፈለግን

ባለመቻላቸው አፍረዋል

ይልቁን ከቃላቱ ድምጾች ራሳቸውን ካለ  ምንም መረዳት ውስጥ በመዝጋት

የትእዛዛቱን ትርጉም ቀላቀሉ

እውነተኛዉንና ትክክለኛውን

የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጓሜ ሊያዩበት

የሚችሉበትን አስተሳሰብ ለማግኘት

አልደከሙምና (Heresies 50:4)

ቅዱስ ኤፍሬም በውጫዊ ታሪካዊና ውስጣዊ መንፈሳዊ የቅዱሳት መጻሕፍት እይታዎች መካከል መሠረታዊ ልዩነት እንዳለ በውል የተረዳ ነው። የመጀመሪያው(ታሪካዊው) በፍጥረት ክልል ውስጥ ያለው ውሱን ነው፤ትርጓሜዎች ቢያንስ በክልስ ሀሳብ ደረጃ ሊወሰኑና ጠቅላይ ሊሆኑ ይችላሉ። በሌላ በኩል መንፈሳዊ ትርጓሜ በተለዩ ህጎች ውስጥ የሚሠራ ነው፤እንዲሁም በዋናነት ሰፊ ነው፤ሊሆኑ የሚችሉ ትርጉሞችም ውሱን አይደሉም። እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ያስቀመጣቸው ስሞች በተፈጥሮና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሁሉም ስፍራ የሚገኙት ምሳሌዎችና ዓይነቶች ለእውነት እንደ መስኮቶች ወይም ትናንሽ ቀዳዳዎች ናቸው። እንዲያዉም በመጀመሪያ ደረጃ በእነዚህ ትናንሽ ቀዳዳዎች ለማየት መሠረታዊው ቅድመ ሁኔታ የእምነት ዓይን ነው፤ አንዴ ከመጀመሪያ መኖሩ ከተረጋገጠ ግና ይኽ የእምነት ዓይን ከተለያዩ ሰዎች ጋር በተለያዩ መንገዶች ይሠራል፤ወይም እንዲያዉም በአንድ ሰው ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ግና በተለያዩ ጊዜያት ይሠራል። ውሳጣዊ ዓይኑ የጠፋበት ሰው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት አይችልም፤ ውስጣዊ ዐይኑ የሚያበራና ግልጽ የሆነ ግና ትልቅን ጉዳይ ያስተውላል። "ማንኛዉም ሰው ከትህትናው መጠን ጋር በተያያዘ መልኩ ከሁሉም የበለጠውን  እርሱን (እግዚአብሔርን) ይረዳል።”(Nativity 4:200)  

የእምነት ዓይን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በትኩረት ይመለከት ዘንድ እንዲህ ዓይነቱ  የእውነት ወይም መንፈሳዊ እውነታ ትልቅ ሀብት ቢሆንም  ማንም ግለ ሰብእ ሁሉንም ነገር የመረዳት ችሎታ የለዉም።ስለዚህም ውሳጣዊው ዓይን ይሆናሉ ብሎ የሚያስተውላቸው ትርጓሜዎች ወሰን የለሽ ናቸው።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አንድ ትርጉም ብቻ ቢኖር ኖሮ የመጀመሪያው ተርጓሚ ትርጉሙን ያገኘው ነበር፤ሌሎች አድማጮችም የመፈለግን ድካምና የማግኘትን ደስታ ባልተጋሩ ነበር። ይልቁን እያንዳንዷ የጌታችን ቃል የራሷ መልክ አላት፤እያንዳንዷ መልክም የራሷ አካል አላት፤ እያንዳንዷም አካል የራሷ መለያ አላት።እያንዳንዱም ሰው እንደየዓቅሙ ይረዳል ፤በተሰጠው መጠንም ይተረጉማል። (Commentary on the Diatessaron 7:22)

አንዱ ትርጉም ትክክል ሌላው ስህተት  የሚሆንበት አይደለም(ሁልጊዜ በታሪካዊ እይታ ሊሆን እንደሚችለው) ይልቁን ለአንድ ግለሰብ በተወሰነ ጊዜ ትርጉም ያለው እስከሆነ ድረስ የተገባ ትርጓሜ ነው።ስህተት የሚፈጠረው አንድ ሰው የራሱ መንፈሳዊ ትርጓሜ ብቻ ትክክል እንደሆነ ሲናገርና የአንድ ምንባብ ውጫዊና ውስጣዊ ትርጓሜዎች አይገናኙም ብሎ ሲያስብ ብቻ ነው።ይኽ በዋናነት ያ ጉዳይ አይደለም ሁለቱም የትርጓሜ ዓይነቶች ፡ታሪካዊው በአፍአዊው ስሜትና መንፈሳዊው በውሳጣዊው ስሜት በማተኮሩ በሁለት ፈጽሞ በተለያዩ የእውነታ አገላለጽ ወይም እውነታ ዙሪያ ያጠነጥናሉ፤ እንዲሁም አንደኛው እውነታ ሌላኛውን አያጠፋዉም ፤ሁለቱም አገላለጾች በአንድነት ጎን ለጎን በጋራ ሊኖሩ ይችላሉ።

ግልጽ ለሆኑ ምክንያቶች ቅዱስ ኤፍሬም ስለ ታሪካዊ ትርጓሜ የሚያትተው አልፎ አልፎ ብቻ ነው፤በዚህ ደረጃ ሲናገርም እሱ ሊለው የሚገባው እጅግ አርኪ አይደለም፤እጅግ በጣም ውስብስብ በሆኑት፣ባለፈው ዘመን ባደጉት የታሪካዊ ትርጓሜ ስልቶች ሲመዘን። ግን የእርሱ ዋና ጉዳይ ውስጣዊ፣መንፈሳዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በሆነበት ቦታ ሁሉ(ይኽም የእርሱ የሁል ጊዜ ጉዳይ ነው) በዚያ የእርሱ ምልከታዎች አሁንም ቢሆን ጥልቅ እይታ ያላቸው በመሆኑ አስተዋይ ዘመናዊ አንባቢዎችን መማረክ ይችላሉ።

በዚህ ክፍል የቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ምንነትና ትርጉም የመሰለኝን እየለየሁ ነው፤እንዲሁም እርሱ ራሱ በቀጥታ እንዲናገር ሊፈቀድለት አሁን ጊዜው ነው።

በዚህ ምንባብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥቅዱስ ኤፍሬም  ስለ ውሳጣዊ ትርጓሜዎች መብዛት ለክርስቶስ በመናገር ይጀምራል።

በአንተ(እግዚአብሔር) አንድ  አባባል ውስጥ የሚፈለገውን ስፋት ሁሉ መረዳት የሚችል ማን ነው? ከእርሱ ከምንወስደው በራቀ መልኩ ከእርሱ ብዙ እንተዋለንና ፤የተጠሙ ሰዎች ከምንጭ እንደሚጠጡት ። የእርሱ (እግዚአብሔር) እይታዎች ከእርሱ ከሚማሩት እይታዎች እጅግ የበዙ ናቸውና።እግዚአብሔር እያንዳንዱ ከቃሉ የሚማር እርሱ የፈለገውን አቅጣጫ እንዲያይ በሚያስችል መልኩ ቃሉን በብዙ ውበቶች ገልጾአል።እንዲሁም እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በእርሱ በየትኛዉም አቅጣጫ ላይ በመመሰጥ ባዕለጸጋ እንሆን ዘንድ በቃሉ ውስጥ ሁሉንንም የስጦታ ዓይነቶችን ሰውሮአል።የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ዛፍ ነውና በሁሉም አቅጣጫ ላንተ የተባረኩ ፍሬዎችን የሚሰጥ ፤እርሱ በምድረ በዳ እንደተሰነጠቀው ዐለት ነው ፤በሁሉም አቅጣጫ ለእያንዳንዱ መንፈሳዊ መጠጥ የሆነው።እነርሱ የመንፈስን መብል በሉ፤የመንፈስንም መጠጥ ጠጡ።

ማንኛዉም መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከት ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ሀብቶች ሁሉ ያገኘውን አንዱን ብቸኛ ያለ አድርጎ ሊወስድ አይገባውም፤ይልቁንም እርሱ ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ከብዙ ሀብቶች መካከል ያገኘውን አንዱን ብቻ መፈለግ እንደቻለ ሊያስተውል ይገባል።

እንዲሁም አንባቢው እርሱን ሀብታም ስላደረገው መጽሐፍ ቅዱስ  ምሥጢር ያለቀበት ደሀ አድርጎ ሊያስብ አይገባም።ይልቁንም አንባቢው ተጨማሪዎችን ማግኘት ካልቻለ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥልቀት ያመሥግን።እርካታ ስላገኘህ ተደሰት ፤የሆነ ነገር ስለቀረብህ አትዘን።የተጠማ ሰው ስለጠጣ ያመሠግናል፤ምንጩን በመጠጣት ሊያደርቀው አለመቻሉን በማረጋገጡ አያዝንም።ምንጩ ያንተን ጥማት ይቁረጥ ያንተ ጥማት ምንጩን  አያድርቅ!ምንጩ ሳይቀንስ ጥማትህ ቢቆረጥ በተጠማህ ጊዜ እንደገና ትጠጣለህ፤ነገር ግን አንዴ ከረካህ በኋላ ምንጩ ደርቆ ቢሆን ኖሮ በምንጩ ላይ ያገኘኸው ድል ያንተን ጉዳት ባረጋገጠ ነበር።ስለወሰድከው ምስጋናን ስጥ እንዲሁም በዝቶ ስለተረፈው አታጉረምርም።አንተ ለራስህ የወሰድከው የራስህ ድርሻ ነው፤የተረፈው አሁንም ያንተ ውርስ ሊሆን ይችላል።( Commentary on the Diatessaron 1:18-19)

ይቆየን

 

የተዛባ አመለካከት አገልግሎታችንን አያደናቅፈውም

ግንቦት 16፣2003ዓ.ም

 
በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለመደገፍና ለማጠናከር የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አያሌ ፈተናዎችን እያሳለፈ 19 ዓመታት ተጉዟል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በዓመታት ጉዞው ባከናወናቸው መልካም ተግባራት ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶችን ጨምሮ እጅግ በርካታ ወዳጆችን እንዳፈራ ሁሉ ጥቂት በተቃራኒው የቆሙ ስሙን በየጊዜው በክፉ የሚያነሱ ቡድኖችም ተነሥተውበታል፡፡

ወዳጆቹ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆች ናቸውና በአገልግሎቱ ተማርከው በሚሠራቸው መልካም ሥራዎች ተስበው ቤተ ክርስቲያን ያለባትን የአገልግሎት ክፍተት ለመሙላት በጋራ ከማኅበሩ ጋር በመሥራት ሲተባበሩ፤ በአንጻሩ ጠላቶቹ ደግሞ የተለያዩ አጋጣሚዎችን እያስታከኩ ማኅበሩን ለመወንጀል እየተጣጣሩ ይገኛሉ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ወዳጆች አፈራ? ጠላቶችስ ለምን ተነሡበት?

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ፈቅዶ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ወጣቶችን በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማደራጀት ከመደበኛው ትምህርታቸው ጎን ለጎን በየአካባቢው ወደሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሔደው መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ፤ በተጨማሪም ወጣቱ ሀገሩንና ሕዝቦቿን አክባሪ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ እንዲሆን በማስቻሉ ብዙ ወዳጆችን አግኝቷል፡፡

ከዚህም ሌላ የመናፍቃኑንና ቤተ ክርስቲያኒቱን እናድሳለን ብለው የተነሡትን የመናፍቃኑ ተላላኪ ቡድኖችን ሴራና የአክራሪ እስልምናውን እንቅስቃሴ በመረጃ አስደግፎ በማጋለጡ፣ ከክፉ ትምህርታቸው መመለስ ያልፈለጉ የተሐድሶ ቡድን አባላት ከቤተ ክርስቲያን እንዲወጡ ስለተወሰነባቸው እና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች እየተከታተለ ለዕድገቷና ለብልጽግናዋ በመሥራቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ወዳጆችን አፍርቷል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው የተሰለፉት ወገኖች ደግሞ ወጣቱን እንደጠፍ ከብት ወደ ማያውቀው የመናፍቃን አዳራሽ የመንዳት ልምዳቸው በመቋረጡና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመግባት የሚያደርጉት ሥርዓቷን የማፋለስ እንቅስቃሴ፤ እንዲሁም አገልጋዮቿንና ምእመናኖቿን የማስኮብለሉ አካሔድ ማኅበሩ በክትትል በተለያዩ መረጃዎች ስለገለጠባቸው ማኅበረ ቅዱሳንን በጠላትነት በማየት ማኅበሩ እንዲፈርስ የማይቧጥጡት ዳገት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

እነዚህ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች ለጥቂት ጊዜ ጋብ ብለው የነበሩ ቢሆንም አሁን ባገኙት አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንጀራዋን እየበሉ የሚኖሩ ወዳጆቻቸውን በማጠናከርና በማስፋፋት በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ከወዳጆቻቸው ተመድቦላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት ለማዛባትና በጎቿን ለመበታተን ሌት ከቀን እየሠሩ ነው፡፡

ይኼ ዕቅዳቸው የሚሳካው እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዓት መጠበቅ የሚቆረቆሩ ማኅበራትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አጀንዳ በማድረግና እንዲበተኑ ክፉ ሥራ በመሥራት ነው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ይሔንን ከንቱ ቅዠታቸውን እውን ለማድረግም በቤተ ክርቲያኒቱ የተለያየ ሓላፊነት ላይ የሚገኙትን የዓላማቸው አስፈጻሚዎች ሁሉ እየተጠቀሙ እንደሚገኙም ይታወቃል፡፡

ከዚህም ሌላ ድብቅ ዓላማቸው እንዲሳካ ተላላኪዎቻቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚሆን ነገር ግን ስውር ዓላማ ያለው ማኅበር እንዲመሠርቱና ከዚህ በፊት ከንቱ ተግባራቸው ታውቆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታግደው የነበሩ ማኅበራት ሁሉ ከሞቱበት እንዲቀሰቀሱ እየሠሩም እያደረጉም ይገኛሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያን ስም ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያቋቋሟቸውና የሚያቋቁሟቸው፣ ማኅበራትንም ሕጋዊ ዕውቅና ለማሰጠት እንዲያመቻቸው ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከኔ ሌላ ሌሎች አያስፈልጉም የሚል አቋም ያለው ማኅበር እንደሆነ ያስወራሉ፡፡

በእርግጥ ማኅበረ ቅዱሳን በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ደንብ ተከትለው በሚቋቋሙት ማኅበራት ላይ የማኅበሩ ጠላቶች ከሚያወሩትና ከሚያስወሩት አሉባልታ የተለየ አቋም አለው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርቲያን የሁለት ሺሕ ዓመታት ታሪክ ያላት ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ትሁን እንጂ መንበሯ ከሊቀ ጵጵስና ደረጃ ወደ ፕትርክና ለማሳደግ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ መራራ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ በዚህ ማለፏ ደግሞ ሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት የደረሱበት ዘመናዊ የአደረጃጀት ደረጃ ላይ ለመድረስ አልቻለችም፡፡ ልጆቿንም ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ ለመምራት ሳትችል ስለቆየች እነዚህን ክፍተቶች የሚሞሉ አንድ አይደለም በርካታ ማኅበራት እንደሚያስፈልጓት ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ነገር ግን እኩያኑ እንደሚሉት ሳይሆን እነዚህ ማኅበራት ሲቋቋሙ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዕድገትና የአገልግሎት ሥምረት የሚንቀሳቀሱ ተልእኮአቸውና ዓላማቸው ተለይቶ የሚታወቅ፣ መንፈሳዊ ተግባርን ብቻ የሚፈጽሙ፣ የሚናበቡና በስልት ለአንድ ውጤት የሚተጉ ሊሆኑ ይገባቸዋል የሚል ጽኑ አቋም አለው፡፡

ይሔንን አቋሙን ደግሞ በርካቶች የሚደግፉት እንደሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ያምናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የመናፍቃኑ ተላላኪዎች በቤተ ክርስቲያን ስም ያቋቋሟቸው ማኅበራት ከዚህ በፊት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥለውት የሔዱት ጠባሳ የሚታወቅ ስለሆነ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራት ላይ ግልጽ አቋም አለው፡፡ ከዚህም ሌላ እነዚህ የውስጥ ዐርበኞች ይኽ ስውር ዓላማቸው ያልታወቀባቸው ይመስል ማኅበሩን ለመወንጀል የማይለጥፉለት ታፔላ፣ የማይለፍፉት ወሬ የለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ የቤተክርስቲያን ጠላቶች ስለማኅበሩ የሚያወሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ እና ሁሉም የሚገነዘበው ግልጽ እውነታ መሆኑን ባለማወቃቸው እናዝናለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ምንም ስውር ዓላማ የለውም፤ ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ የጸዳና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው መተዳደሪያ ደንብና መመሪያን ሳያዛንፍ እየሠራ ያለ፤ በተሰጠውም መተዳደሪያ ደንብና ሓላፊነት መሠረት ከአባላቱና ከበጎ አድራጊ ምእመናን የሰበሰበውን ገንዘብ ገቢና ወጪ እያሰላ በውስጥ ኦዲተሮችም እያስመረመረ በመሥራት ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ማኅበር እንጂ በወሬ የሚኖር አይደለም፡፡ ይሔንን አሠራሩንም ቀርቦ ማየት ይቻላል፡፡ አባላቱም በገንዘባቸው፣ በዕውቀታቸው በጉልበታቸውና በመላ ሕይወታቸው ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግሉ እንጂ እንደ መናፍቃኑ ተላላኪዎች ለሆዳቸው ያደሩ፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነባቸው እዚህም እዚያም ደሞዝ የሚቀበሉ አይደሉም፡፡

ማንኛውም አካል እንዲያውቅልን የምንፈልገው ሐቅ ማኅበረ ቅዱሳን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰጠው ሓላፊነትና አባላቱም ለገቡለት ቃል ኪዳን ሃይማኖታቸው የሚፈቅደውን መስዋዕትነት ለቤተ ክርስቲያን ልዕልናና ክብር ለመክፈል የተዘጋጁ እንጂ በተዛባ አመለካከት ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉ አለመሆናቸውን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱ የሚታይ አሠራሩም ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህም የመናፍቃኑ ተላላኪዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላ ከአገልግሎታችን አንዲት ጋት ወደ ኋላ እንደማይመልሰን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡ ርእይና ተልእኮአችንን ለማሳካት ዛሬም ነገም እንሠራለን፤ ትናንትን ያሻገረን እግዚአብሔር ዛሬንም ያሳልፈናልና፡፡