አባታችን ሆይ(የመጨረሻው ክፍል)

 ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
አቤቱ ወደፈተና አታግባን÷ ከክፉ አድነን እንጂ÷ መንግሥት ያንተ ናትና÷ ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን።
ግንቦት 19/2003 ዓ.ም.

ጌታችን በዚህ ቃል የእኛን ደካማነት በማሳወቅና መታበያችንን በማጥፋት ፣ ፈተናዎች በእኛ ላይ ከመሠልጠናቸው በፊት  በትሕትና በመገኘት ልናርቃቸው እንደምንችል በግልጽ አስተማረን ፡፡ በዚህ ምክንያት ድላችን እጅግ ታላቅ ይሆናል ፡፡ ሰይጣን ከፊት ይልቅ በታላቅ ፍርሃት ውስጥ ይወድቃል ፡፡ እንዲህ ስል ለጸሎት በእግዚአብሔር ፊት ስንቀርብ በማስተዋል ልንሆን ይገባናል ሲል ነው  ፡፡ ልቡናችንን ሰብስበን መጸለይ ከተሣነን ግን ዝም ማለትን በመምረጥ የፈተናው ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ በትዕግሥት ልንጠባበቀው ይገባናል ፡፡  እንዲህ ካደረግን ከከንቱ ውዳሴና ከትዕቢት ነጻ እንደወጣን ማስተዋል ይቻለናል ፡፡

በዚህ ቦታ ሰይጣንን “ክፉ” እንዳለው እናስተውላለን ፡፡ በዚህም ያለ ዕረፍት እኛን ለመጣል በሚፋጠነው ሰይጣን ላይ ጦርነትን ልንከፍት እንዲገባን አሳሰበን ፡፡ ነገር ግን ሰይጣን ክፉ ሲባል ከፍጥረቱ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ነበር ማለቱ ግን አይደለም ፡፡ በተፈጥሮ ክፉ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት የለም “ብርሃን ከሌለ ጨለማ እንደሚሆን ደግ ሥራ ከሌለ ክፉ ሥራ ይነግሳልና፡፡ ነገር ግን  እኛው ነን ክፋትን  በፈቃዳችን ከተፈጥሮአችን ጋር የምንደባልቀው ፡፡ ስለዚህም እኛን በኃጢአት ስላሰናከለን ቅድመ ጠላታችን ተባለ ፡፡ እንዲሁም ያለ አንዳች ምክንያት እኛ ላይ ጦርነትን በመክፈቱ ጠላታችን ተሰኝቶአል ፡፡ ስለዚህም “ ከፈተና አድነን” ብለን እንድንጸልይ ሳይሆን “ከክፉ አድነን አንጂ” ብለን እንድንጸልይ አዘዘን ፡፡ እንዲህም ሲል በወዳጆቻችን ክፉ ሥራ ደስ ባንሰኝም ፤ በእነርሱ እጅ ማንኛውንም በደል ብንቀበል ፤ ለክፋታቸው  ምክንያት እርሱ ነውና  እነርሱን ጠላት ከማድረግ ተቆጥበን  ጠላትነታችንን በሰይጣን ላይ ሊሆን ይገባል ፡፡

ወደ ፈተና እንዳንገባ ጠላታችን ማን እንደሆነ ለይቶ በመጠቆም ፣ በእርሱ ተግባር እንድናዝን በማድረግ ፣ ባለማስተዋል የምንፈጽማቸውን ክፉ ተግባራትን ከእኛ ቆርጦ በመጣል ፣ እንዲሁም መንፈሳችንን በማነቃቃትና በማትጋት የጽድቅ ዕቃ ጦርን የሚያስታጥቀን ንጉሥ ማን እንደሆነ በማስታወስ እንዲሁም እርሱ ከሁሉ በላይ ኃያል እንደሆነ በማመልከት “መንግሥት የአንተ ናትና ኃይል ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን” እንድንል አዘዘን ፡፡

እናም በእርሱ ታምነን ያዘዘንንም ወደ ተግባር መልሰን ለመፈጸም እንትጋ ፡፡ እርሱ ንጉሣችን ከሆነ ማንንም ልንፈራ አይገባንም ፡፡ ጌትነቱን ማንም ሊቃወምና ሊያጠፋ የሚችለው የለም ፡፡ አርሱ  “መንግሥት የአንተ ናትና” ሲለን እኛን የሚዋጋውን ለጊዜው ፣ እግዚአብሔርን የሚቋቋም የሚመስለውን ሰይጣንን ለእኛ እንዲገዛ አሳልፎ እንደሚሰጠን ሲያመላክተን ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እርሱ ከእግዚአብሔር ባሪያዎች አንዱ ነው ፤ ምንም እንኳ ከተዋረዱትና ለመተላለፋችን ምክንያት ከሆኑት ወገን ቢሆንም ፡፡ እርሱ ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፈቃድ ካላገኘ በቀር በእግዚአብሔር ባሮች ላይ የማደር መብቱ የለውም ፡፡ ስለምን  እኔ “ በባሮቹ ላይ” ለምን እላለሁ ፣ በእሪያዎች ላይ ስንኳ በማደር እነርሱን አስቻኩሎና አጣድፎ ለማጥፋት ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፈቃድን መቀበል የግድ አለበት (ማቴ.7፥31) በእንስሳት መንጋ ላይ ከላይ ያለው እርሱ ካልፈቀደለት በቀር ከቶ ሊያድር አይቻለውም ፡፡

“ኃይል” አለ ፡፡ ስለዚህም ድክመቶችህ እጅግ ብዙ ቢሆኑም ያለሥጋት በድፍረት ለመቆም እንድትችል ሁሉን በቀላሉ መፈጸም  የሚቻለው እርሱ በአንተ ላይ መንገሡን አሳወቀህ ፡፡ በአንተም ሥራውን መከወን ለእርሱ አይሳነውም  ፡፡

“ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ አሜን”  በዚህ ወደ አንተ ከቀረቡ መከራዎች ሁሉ ነጻ ሊያወጣህ እንደሚችል ብቻ አልገለጸልህም ፡፡ ነገር ግን አንተን ማክበርና ማላቅ እንደሚቻለው አሳወቀህ ፡፡ የእርሱ ኃይል እጅግ ታላቅ እንደመሆኑ መጠን እንዲሁ ክብሩም እንዲሁ በቃላት ሊገለጽ የማይችል እጅግ ታላቅ ነው ፡፡ ለእርሱ የሆኑ ጸጋዎች ሁሉ ወሰን አልባና ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡  እርሱ ኃይሉ ታላቅ ክብሩም በቃላት ሊነገር የማይችል ፣ ወሰን አልባዎች እንዲሁም ፍጻሜ የሌላቸው ናቸው ፡፡ ድል አድራጊው እርሱ የእርሱ የሆኑትን እንዴት ባለ ክብር እንደሚያከብራቸውና ፍጹም በሆነ በራስ መተማመን እንዲሞሉ እንደሚያደርጋቸው ታስተውላለህን ?

ስለዚህም አስቀድሜ  ለማብራራትም እንደሞከርኩት በእርሱ ዘንድ  የተጠላውንና የማይወደደውን ቂምና ጥላቻን ከልባችን አስወግደን  ከንቱዎች ከሆኑት ከእነዚህ  ክፉ ጠባያት ርቀን በሁሉ ዘንድ መልካም የሆነውን መፈጸም እንዲገባን አበክሮ ሲያሳስበን ፣ እንዴት መጸለይ እንዳለብን ካስተማረን በኋላ በድጋሚ መልካም የሆነው ምግባር ምን እንደሆነ ያስታውሳል ፡፡ ስለዚህም ይህን ብንፈጽም በእኛ ላይ የሚመጣብንን ቅጣትና በብድራት የምንቀበለውን በመጠቆም ሰሚዎቹ ቃሉን አክብረው መታዘዝ እንዲሻላቸው ማሳሳቡን እንመለከታለን ፡፡

“ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ” ካለ በኋላ “የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና ፣ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ አባታችሁም ይቅር አይላችሁም” (ማቴ.6፥14) አለን ፡፡

በዚህም ኃይለ ቃል “ሰማይ”ና “አባት” የሚለውን ቃል በድጋሜ መጠቀሙን እናስተውላለን ፡፡ ይህም ሰሚዎቹ ትሕትናን ገንዘባቸው እንዲያደርጉ ለመርዳት ነው ፡፡ በዚህ ቃል አስቀድመው እንደ አውሬ ክፉ ምግባር ይመላለስ የነበረው ሕዝብ እርሱን የመሰለ አባት ማግኘቱንና ከተራና ከተናቀ ምድራዊ አስተሳሰብ አውጥቶ በሰማያት መኖሪያውን እንዳደረገለት ሊያሳየው እንዲህ አለው ፡፡ ይህን ሲፈጽምልን በጸጋው እንዳው በከንቱ ሳይሆን እኛም የእርሱ ልጆች እንባል ዘንድ የእኛም ሥራ እንደሚያስፈልግ ሲያስታውሰን አይደለምን ?  እግዚአብሔርን ለመምሰል የበደሉንንና በእኛ ላይ ክፋት የፈጸሙትን ይቅር ከማለት በቀር የበለጠ ነገር የለም ፡፡ እርሱም አስቀድሞ “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል” በማለት በእርግጥ ስለዚህ አስተምሮናል ፡፡

ይህም እንዲሆን ፈቃዱ እንደሆነ ሊያሳየን በእያንዳንዱ ኃይለ ቃል ላይ  “አባታችን ሆይ” “ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” “በደላችንን ይቅር በለን” “ ወደፈተና አታግባን” “ከክፉ አድነን እንጂ” በማለት የጋራ ጸሎት እንድንጸልይ ማዘዙን እናስተውላለን ፡፡ በወንድሞቻችን ላይ እንዳንቆጣና በእነርሱ ላይ በጠብ ከመነሣሣት እንድንቆጠብ ሲል  በእያንዳንዱ የጸሎታችን ክፍል ላይ እነዚህን የብዙ ቁጥር ግሶችን እንድንጠቀም አዞናል ፡፡

ከዚህ ሁሉ ማሳሰቢያ በኋላ የበደሏቸውን ይቅር ከማለት እንቢ ብለው እግዚአብሔር ተበቅሎ እንዲያጠፋላቸው የሚለምኑት በእጥፍ ሕጉን በመተላለፋቸው እንዴት የባሰ ቅጣት አይጠብቃቸው ይሆን !  እርሱ እግዚአብሔር ሁሉን እንዲህ አስማምቶ መፍጠሩ አንዱን ከአንዱ እንዳይለያይ በመሻቱ አይደለምን ? ለመልካም ነገር ሁሉ ፍቅር መሠረት ነው ፡፡ እርሱ ፍቅርን የሚያፈርሱ ነገሮችን ሁሉ ከእያቅጣጫው እንዲወገዱ ያደርጋቸዋል ፡፡ ሁላችንንም ወደ አንድ በማምጣት ፍቅርን እንደሲሚንቶ በመጠቀም እርስ በእርሳችን እንድንያያዝ ነው የፈጠረን ፡፡ አባትም ይሁን እናት ጓደኛም ይሁን ሌላ እንደ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር እኛን የሚወደን የለም ፡፡ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሁሉ እርሱ እግዚአብሔር  በየቀኑ ለእኛ የሚያደርገውን መግቦትና የእርሱን ሥርዓት ወዳድነት አሳይቶናል ፡፡ ነገር ግን ስለ ሕመሞቻችሁና ስለኀዘኖቻችሁ እንዲሁም በሕይወታችሁ ዘመን ስለገጠሟችሁ መከራዎች የምትነግሩኝ ከሆነ በየቀኑ እናንተ እርሱን ምን ያህል ጊዜ በክፉ ሥራችሁ እንደምታሳዝኑት ልብ በሉ ፡፡ ከዚህ በኋላ በደረሰባችሁ መከራ ሁሉ መገረምና መደነቃችሁን ታቆማላችሁ ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ስለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምክንያት በእኛ ላይ ስለመጣው ከፉ ነገር ሁሉ ልብ የማንል ከሆነ ግራ መጋባት ውስጥ ልንገባ እንችላለን ፡፡ በቀን ውስጥ ብቻ የምንፈጽማቸውን በደሎች በጥንቃቄ ብንመረምራቸው ስለመተላለፋችን እንዴት ያለ ታላቅ ቅጣት ሊታዘዝብን እንዲገባ መገንዘብ እንችላለን ፡፡              

ስለዚህም በቀን ውስጥ የፈጸምናቸውን በደሎች አንዱ ለአንዱ በመናዘዝ ፣ በደላችንን በማሰብ  የበደሉንን ይቅር ልንል ይገባናል ፡፡ በእርግጥ እያንዳንዳችን ምን በደል እንደበደልን ማወቅ ባንችልም ፣ በደሎቻችን እጅግ የበዙ መሆናቸውን መገንዘብ እችላለሁ ፡፡ ከእነዚህ ከፈጸምናቸው በደሎች መካከል ከእኛ መካከል አንዱ  የሚያውቃቸው ቢሆን እንኳን ከእነዚህ መካከል አንዱን መምረጥ ይሳነዋል ፡፡ ለምሳሌ ፡- ከእኛ በጸሎቱ ቸልተኞች አይደለንምን ? ከእኛ መካከል በትዕቢት ተሞልቶና ከንቱ ውዳሴን ሽቶ የሚጸልይ የለምን ?  ወንድሙን በክፉ የማይናገረው፣ ክፉውን የማይመኝ ፣ ወገኑን በንቀት ዐይን የማይመለከተው ፣ልብን የሚያቆስል ግፍን ቢፈጽምበት እንኳን የወንድሙን መተላለፍ ይቅር የሚል አለን ?

ነገር ግን እኛ በቤተክርስቲያን ለአጭር ጊዜ በቆየንባት ሰዓት ውስጥ እጅግ ታላቅ ክፋትን እንፈጽማለን ፡፡ ከቤተክርስቲያን ወጥተን ወደ ቤት ስንመለስ ምን ያህል የከፉ በደሎችን እንፈጽም ይሆን ? በወደቡዋ (በቤተክርስቲያን) ታላቅ የሆነ ወጀብ ካለ ወደ ኃጢአት መተላለፊያው ባሕር ስናመራ ማለትም ወደ ገበያ ሥፍራ ወሬዎች ፣ወደ የቤቶቻችን ስንመለስ በሥጋ ምቾቶቻችን ተስበን የከፉ ኃጢአቶቻችን እንዴት አንፈጽም ይሆን ?

ነገር ግን እግዚአብሔር ከእነዚህ ሁሉ መተላለፎቻችን እንድንድን ያለምንም ድካም አጭርና ቀላል መንገድን ሠርቶልናል ፡፡ የበደለንን ይቅር ማለት ምን ዐይነት ድካም አለው ?  ይቅር ለማለት ምንም ዐይነት ድካም የለውም ፤ ነገር ግን እርስ በእርሳችን በጠላትነት ተፋጠን እንገኛለን ፡፡ በውስጣችን ከተቀጣጠለው ቁጣ ለመዳንና መጽናናትን ለማግኘት ፈቃዳችን ብቻ በቂ ነው ፡፡ ይቅርታ ለማድረግ ባሕር ማቋረጥ ፣ ረጅም መንገድ መጓዝ ፣ ወይም ተራራን መቧጠጥ ወይም ብዙ ገንዘብ ማጥፋት ወይም ሥጋችንን ማጎሳቆል አያስፈልገንም ፤ ነገር ግን ፈቃደኛ መሆን ብቻ በቂ ነው ፡፡ እንዲህ ከሆነ ኃጢአታችን ሁሉ አንድ ሳይቀር ይወገድልናል ፡፡

ነገር ግን እርሱን ወንድምህን ይቅር ማለት ትተህ እርሱ እግዚአብሔር ያጠፋልህ ዘንድ የምትለማመን ከሆነ ፣ ምን ዐይነት የመዳን ተስፋ ሊኖርህ ይችላል? አስቀድመህ ከእግዚአብሔር ጋር በፈቃድ አልተስማማህም ፤ ከዚህ አልፈህ የጠላትህን ጥፋት በመጠየቅህ ምክንያት እግዚአብሔርን  ታስቆጣለህን ? እርሱን ትለማመነው ዘንድ የኀዘን ማቅን ደርበሃል ፤ ነገር ግን የአውሬ ጩኸት ወደ እርሱ እየጮኽ በኃጥእ ላይ የሚመዘዙትን የጥፋት ፍላጻዎችን በራስ ላይ ታመጣለህን? ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለጸሎት ሥርዓት ባስተማረበት ወቅት ከበቀል ነጽተን ጸሎታችንን ማቅረብ እንዲገባን “… በስፍራ ሁሉ አለቁጣና አለክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሡ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ ፡፡” ብሎ አስተምሮናል ፡፡ (1ኛ ጢሞ.2፥20) አንተ ምሕረትን ለራስህ የምትሻ ከሆነ ከቁጣ መቆጠብ ብቻውን ለአንተ በቂ አይደለም ፤ ነገር ግን ለዚህ ነገርም እጅግ አስተዋይ ልትሆን ይጠበቅብሃል ፡፡ አንተ በራስ ፈቃድ ራስህ ላይ የጥፋት ሰይፍን የምትመዝ መሆንህን ከተረዳህ ለአንተ መሐሪ ከመሆንህና የክፋት መርዝ የሆነውን ቁጣ ከሰውነት ከማስወገድ የበለጠ ለአንተ ምን የሚቀልህ ነገር አለ?

•    ነገር ግን ይቅር ባለማለትህ በአንተ ላይ ሊመጣ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ያላስተዋልክ እንደሆነ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ አንድ ወቅት በሰዎች መካከል ጠብ ይነሣና እርስ በእርሳቸው ክፉኛ ይነቃቀፋሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድ ሰው ከአንተ ምሕረትን ያገኝ ዘንድ ከእግርህ ሥር ወድቆ ይለማመንሃል፡፡ ነገር ግን የእርሱ ጠላት የሆነው መጥቶ አንተን እየተለማመነህ ያለውን ሰው ከወደቀበት መደብደብ ቢጀምር አንተ ከበደለህ ሰው ይልቅ አንተን የሚለማመንህን በሚመታው ሰው ላይ ይበልጥ አትቆጣምን? እንዲሁ የጠላቱን ጥፋት የሚለምን ሰው እግዚአብሔርን እንዲህ እንዲያስቆጣው ተረዳ ፡፡ አንተም እግዚአብሔርን ስለመተላለፍህ እየተለማመጥከው ሳለ ድንገት ልመናህን ከመሃል አቋርጠህ በቃልህ ጅራፍ ጠላትህን ልትገርፈው ብትጀምርና እግዚአብሔር ለአንተ የሠራልህን ሕግ ብታቃልል ፣ አንተን የበደሉህን ሰዎች ሁሉ በደል ትተህ ከቁጣ እንድትርቅ ያዘዘህን አምላክህን እርሱ ከአዘዘህ ትዕዛዛት ወጥቶ በተቃራኒው በአንተ ላይ ቁጣው እንደሚነድ አታደርገውምን? እግዚአብሔር አንተን ተበቅሎ ለማጥፋት የገዛ ኃጢአትህ በቂው ነው፡፡  ነገር ግን  በዚህ ተግባርህ ይህን እንዲፈጽምብህ እርሱን ታነሣሣዋለህን? ምንድን ነው? እርሱ ለአንተ የሰጠውን ትዕዛዝ ይዘነጋዋልን? እርሱ ሁሉን የሚያውቅ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ ሕግጋቶቹ ሁሉ በፍጹም ጥንቃቄ ይፈጸሙ ዘንድ የሚሻ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከአንተ እንደሚጠብቀው አድርገህ ሕግጋቶቹን ከመፈጸም ርቀህ እንደፈቃድህ በጥላቻና ሕግጋቶቹን  የምትጥሳቸው ከሆነ እጅግ የከፋ ቅጣት እንደሚጠብቅህ በአርግጥ እወቅ፡፡ አጥብቆ ትጠብቀው ዘንድ ያዘዘህን ትእዛዝ ካቃለልክ በኋላ ከእርሱ ዘንድ ምን በጎነትን አገኛለሁ ብለህ ትጠብቃለህ?

ከዚህም አልፈው እጅግ ቆሻሻ ወደ ሆነው ወደዚህ ምግባር የሚመለሱ ግን አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ለጠላቶቻቸው ጥፋትን የሚለምኑ ብቻ አይደሉም፤ የገዛ ልጆቻቸውን በመርገም የገዛ ሥጋቸውን የሚያጠፉ ወይም ከእርሱ የሚመገቡ ናቸው፡፡ በጥርሶቼ የልጄን ሥጋ መች በላሁ ብለህ አትንገረኝ፡፡ ይህንን በእርግጥ አድርገኸዋል፡፡ ከእግዚአብሔር ቁጣ ወጥቶ በልጅህ ላይ እንዲወድቅና ለዘለዓለማዊ ቅጣት ተላልፎ እንዲሰጥ እንዲሁም ከነቤተሰቡ ተነቃለቅሎ እንዲጠፋ ከመለመን የበለጠ ምን አስከፊ የሆነ ጸሎት አለ?

ለምን እንዲህ ይሆናል ፡፡ከዚህስ የከፋ ጭካኔ ምን አለ ? እንዲህ በክፋት ተጨማልቀህ በልቡናህ ውስጥ ይህን ክፉ መርዝ አስቀምጠህ እንዴት ከቅዱስ ሥጋው ልትቀበል ትቀርባለህ ? የጌታንስ ደም እንዴት ትቀበላለህ ? አንተ “ ሥጋውን በሰይፍ ከፋፍለህ ቤቱንም ገልብጠህ አጥፋው ፣ ያለውን ሁሉ እንዳልነበር አድርገህ አጥፋቸው” የምትል ፣ እልፍ ጊዜ ሞትን እንዲሞት የምትለማመን አንተ ሰው ሆይ ፣ አንተ ከነፍሰ ገዳዮች ፈጽሞ የምትለይ አይደለህም? ወይም ሰዎችን እንደሚመገብ እንደክፉ አውሬ ነህ ፡፡

ስለዚህ ከዚህ ክፉ ሕመምና እብደት ራሳችንን እንጠብቅ ፡፡ እርሱ እንዳዘዘን እኛን ለሚያሳዝኑን ርኅራኄን በማሳየት “የሰማዩ አባታችንን”  እንምሰለው ፡፡ የገዛ ኃጢአታችንን በማሰብ ከዚህ ክፋት እንመለስ ፡፡ በቤታችንም  ከቤታችንም  ውጭ በገበያ ቦታ ፣ በቤተክርስቲያን የምፈንጽመውን ኃጢአት በጥንቃቄ በመመርመር ከዚህ ክፋት እንራቅ ፡፡

ለዚህ ትእዛዝ ተገቢውን ትኩረት ካለመስጠት የተነሣ ካልሆነ በቀር ለከፋ ቅጣት የሚዳርገን ሌላ ትእዛዝ የለም ፡፡ ነቢያት ሲዘምሩ ፣ ሐዋርያት በመንፈሳዊ ቅኔ ሲቀኙ ፣ እግዚአብሔርም ሲያስተምር  እኛ ግን በዓለም ተጣብቀን እንባክናለን፡፡ ራሳችንን በምድራዊ ነገሮች አሳውረናል ፡፡ በተዋንያን መድረክ ላይ የሚነበበውን የንጉሥ ደብዳቤ ለመስማት በጸጥታ እንድንቆም የእግዚአብሔርን ሕግ በጸጥታ ለመስማት አንተጋም ፡፡  በዚያ የንጉሡ ደብዳቤ ሲነበብ አማካሪዎች፣ ገዢዎች የመንግሥት ልዑካኑና ሕዝቡ ሁሉ ቃሉን ለመስማት  ይቆማል ፡፡ በዚያ ጸጥታ ውስጥ አንድ ሰው ቢንቀሳቀስና ጩኸት ቢያሰማ ንጉሡን እንዳቃለሉ ተቆጥሮበት ከባድ ቅጣትን ይቀበላል ፡፡  በዚህ ግን ሰማያዊ ደብዳቤ በተነበበ ጊዜ በሁሉ አቅጣጫ ታላቅ የሆነ ሁከት ይቀሰቀሳል ፡፡ ነገር ግን ደብዳቤውን የላከው ንጉሥ ከዚህኛው ምድራዊ ንጉሥ እጅግ የሚልቅ ነበር ፡፡ ታዳሚዎቹም የተከበሩ ናቸው ፡፡ ሰዎች ብቻ አይደሉም የሚገኙበት መላእክት ፣ ሊቃነ መላእክት የሰማይ ሠራዊቶች ሁሉ ይገኙበታል ፡፡ አኛም በምድር ያለነው ምስጋናን እናቀርብ ዘንድ ከጉባኤው ታድመናል ፡፡ “ሥራዎቹ ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” ተብሎ እንደተጻፈ ፡፡ አዎን እርሱ ለእኛ የፈጸማቸው ሥራዎቹ ከቃላት ፣ እኛ ከምናስበውና ከምንረዳው በላይ ናቸው ፡፡

ይህን ጉዳይ ነቢያት ሁል ጊዜ የሚያውጁት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው በተለያየ መንገድ ይህን የእግዚአብሔርን ድል አድራጊነት ለእኛ ጽፈውልናል፡፡ ንጉሥ ዳዊት “ወደ ላይ ዓረግህ ፣ ምርኮን ማረክህ ስጦታህን ለሰዎች ሰጠህ”(መዝ.67፥18) እንዲሁም  “እግዚአብሔር ነው በሰልፍ ኃያል”(መዝ.23፥8)  ሌላውም ነቢይ “የኃይለኛውን ምርኮ ይበዘብዛል” ብሎአል ፡፡ የተማረኩትን ሊያስለቅቅ፣ ለእውራን ብርሃንን ሊሰጥ÷ ለሃንካሳን ምርኩዝ ሊሆናቸው ነው ጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣቱ ፡፡

 ሌላው ደግሞ በሞት ላይ ያገኘነውን ድል አሰምቶ በመናገር እንዲህ ይላል “ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሞት ሆይ ድል መንሣትህ የታለ? (ኢሳ.25፥8) በሌላ ቦታ ደግሞ ሰላምን ስለሚሰጠን ስለምሥራቹ ቃል  ሲመሰክር “ሰይፋቸውንም ማረሻ ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ”(ኢሳ.4፥4) ሲል ፤ ሌላኛው ነቢይ ደግሞ  ኢየሩሳሌምን እየተጣራ  “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበለሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ አነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፡፡ ትሑትም ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ፡፡” ብሎ አስተምሮአል፡፡ ( ዘካ.9፥9) ሌላኛውም ነቢይ “እናንተ የምትፈልጉት ጌታ ይመጣል ::  በዚያች ቀን በእርሱ ፊት ማን ይቆማል? በእርሱ ከእስራቶቻችሁ በመፈታታችሁ  እንደ ጥጃ ትዘላላችሁ፡፡” በዚህ ነገር የተደነቀው ሌላ ነቢይም “እርሱ የእኛ ጌታ ነው ከእርሱ ጋር የሚስተካከል ጌታ ፈጽሞ  የለም” ብሎአል ፡፡

ነገር ግን እነዚህንና ከእነዚህም ከጠቀስናቸው በላይ የተነገረለትን የእርሱን ቃል ለመስማት በመንቀጥቀጥ በጸጥታ መቆም ሲገባን ፣ እኛ በምድር እንዳለን ሳንረዳ አሁንም ራሳችንን በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዳለን በመቁጠር እንጮኸለን ፣ እናወካን፣ ሰላማዊ የሆነውን ጉባኤያችንን ሁል ጊዜ ምንም በማይጠቅሙ ንግግሮች ስንረብሸው እንገኛለን ፡፡

ስለዚህ በትንሹም ፣ በትልቁም ጉዳይ ፤ በመስማትም ፣ በመሥራትም በውጭም ይሁን ፣ በቤታችን እንዲሁም በቤተክርስቲያን እጅግ ቸልተኞች ሆነናል ፡፡ እነዚህ ክፋቶቻችንን እንደያዝን የጠላቶቻችንን ነፍስ በመለመን ከባድ ኃጢአትን በራሳችን ላይ እንጨምራለን ፡፡  ከዚህ ኃጢአታችን ጋር የሚስተካከል ምን ኃጢአት አለ? በዚህ ባልተገባ ጸሎታችን ምክንያት ለእኛ ስለመዳን የሚቀርልን ምን ተስፋ አለን?

 ከእኛ የማይጠበቅ ሥራን እየሠራን በእኛ ላይ በደረሰው ውድቀትና ሕመም ልንደነቅ ይገባናልን ?  ልንደነቅ የሚገባን እነዚህ በእኛ ላይ ባይመጡብን ነው ፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሮአዊ ከሆነው ባሕርያችን መንጭቶ ነው ፡፡ ለሁለተኛው በደላችን ግን ምንም ምክንያት የምናቀርብለት አይደልም ፡፡ ለፍጥረት ሁሉ ፀሐይን በሚያወጣውና ዝናብን በሚሰጠው እንዲሁም ሌሎችንም በጎ ሥጦታዎችን በሚሰጠን በእግዚአብሔር ላይ በጠላትነት መነሣትና እርሱን በቁጣ ተሞልቶ መናገር ፣ ምንም ምክንያት ልናቀርብለት የማንችልበት በደላችን ነው ፡፡ ከቆረቡና እጅግ ታላቅ የሆነውን ጸጋ ተቀብለው ካበቁ በኋላ ፣ ከአውሬ ይልቅ ከፍተው ፣ እርስ በእርሳቸው በጠላትነት ተፋጥጠው የሚኖሩና ጎረቤቶቻቸውን  በምላሳቸው እያቆሰሉና አፋችን በእነርሱ ደም እያራሱ በቁጥር እጅግ የከፋ ቅጣት ለራሳቸው የሚያከማቹ አሉ ፡፡

ስለዚህም ይህን መተላለፋችንን አስበን ይህን ክፉ መርዝ ከውስጣችን አስወግደን ልንጥለው ይገባናል ፡፡ አንዳችን በአንዳችን ላይ ያለንን ጠላትነት እናቁም ፡፡ ለእኛ እንደምንጸልይ አድርገን ለሰው ልጅ ሁሉ ጸሎትን እናድርግ ፡፡ እንደአጋንንት ጨካኞች ከመሆን ይልቅ እንደ ቅዱሳን መላእክት ርኅሩኀን እንሁን :: ምንም ዐይነት ጥቃት በእኛ ላይ እንዳይደርስ የራሳችንን ኃጢአትና የጌታ ትእዛዝን በመፈጸማችን የምናገኘውን ብድራት አስበን ፣ ከቁጣ ይልቅ የዋህነትን ገንዘባችን እናድርግ ፡፡ ከዚህች ምድር በምናልፍበት ጊዜ እኛ ለወንድማችን እንዳደረግንለት ጌታችን ለእኛም እንዲያደርግልን  ምንም የማይጠቅመንን ጠብን በትዕግሥት በማሳለፍ ጥለናት በምንሄዳት በዚህች ዓለም ሰላማውያን ሆነን እንመላለስ ፡፡ በሚመጣው ዓለም የምንቀበለው ቅጣት የሚያስፈራን ከሆነ ሕይወታችንን በጠብ ያልተሞላ ቀላልና ሰላማዊ እናድርገው ፡፡ ወደ እርሱም የምንገባበትን የምሕረትን በር እንክፈተው ፡፡ ከኃጢአት ለመራቅ አቅሙ ያነሰን ቢሆን እንኳ እኛን የበደሉንን ይቅር በማለት በጥበብ እንመላለስ ፡፡ ይህን ማድረግ የሚያስጨንቅ ወይንም የሚከብድ አይደለም ፡፡ ጠላቶች ላደረጉን ቸርነትን በማድረግ ለራሳችንን ታላቅ የሆነውን ምሕረት ከአምላክ ዘንድ እናከማች ፡፡

በዚህ ዓለም በሁሉ ዘንድ ተወዳጆች እንድንሆን እንዲሁም እግዚአብሔር እኛን ወዳጆቹ በማድርግ ፣ የክብሩን አክሊል እንዲያቀዳጀን ለሚመጣውም ዓለም የተገባን ሆነን እንድንገኝ እግዚአብሔር ይርዳን ፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ፍቅር ባለው በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእርሱ ክብር ምስጋና ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን ፡፡