Jesus.JPG

ዐቢይ ጾም፤ ወደ ትንሣኤ የሚደረግ ጉዞ

 

በዲ/ን ዘላለም ቻላቸው

 

አንድ ሰው ለጉዞ ሲነሣ ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት፡፡ በዐቢይ ጾምም እንዲሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ዐቢይ Jesus.JPGጾም መንፈሳዊ ጉዞ ነው፤ መድረሻውም ትንሣኤ ነው፡፡ ለእውነተኛው መገለጥ ለፋሲካ መሟላት የሚደረግ ዝግጅት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም አስፈላጊ የሆነና ስለ ክርስትና እምነታችንና ሕይወታችን በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር ስለሚገልጥልን ይህን በዐቢይ ጾም እና በትንሣኤ መካከል ያለውን ግንኙነት ለመረዳት በመሞከር መጀመር አለብን፡፡

 

የትንሣኤ በዓል ከበዓላት አንዱ ከመሆን እና የአንድ ያለፈ ክስተት መታሰቢያ ከመሆን በላይ ሊታሰብ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ጊዜም ብቻ እንኳን ቢሆን የትንሣኤን በዓል በሚገባው መልኩ አክብሮ በዚያም ከቀን ይልቅ በሚያበራው ሌሊት የተሳተፈና ያንን ልዩ ደስታ የቀመሰ ማንም ሰው ያውቀዋል፡፡ ያ ደስታ ግን ስለ ምንድን ነው? በትንሣኤ በዓል ዕለት እንደምናደርገው «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሀጺባ በደመ ክርስቶስ»፤ «ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ»፣ «ዛሬ ሁሉም ነገር፣ ሰማይም፣ ምድርም፣ ከምድር በታች ያሉ ነገሮችም በብርሃን ተሞሉ» እያልን መዘመር የምንችለው ለምንድነው? «የሞት መሞት፤ የሲኦል መበዝበዝ፣ የአዲስና የዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ…» እያልን ማክበር የምንችለው እንዴት ነው?

 

ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልሱ ይህ ነው፡፡ ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ከመቃብር ወጥቶ ያበራው አዲስ ሕይወት በክርስቶስ ለምናምን ለሁላችንም ተሰጥቶናል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ «በሞቱም እንመስለው ዘንድ ከእርሱ ጋር በጥምቀት ተቀበርን፤ እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን» /ሮሜ.6:4/ እንዳለው ይህ አዲስ ሕይወት እና ብርሃን ለእኛ የተሰጠን በጥምቀታችን ዕለት ነው፡፡

 

ስለዚህ የትንሣኤን በዓል ስናከብር፣ የክርስቶስን ትንሣኤ በእኛ ላይ እንደ ተደረገ እና አሁንም እንደሚደረግ አድርገን እናከብራለን፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዳችን የዚያን የአዲስ ሕይወት ስጦታ እና ያንን የምንቀበልበት እና በእርሱም የምንኖርበትን ኃይል ተቀብለናል፡፡ ይህ ስጦታ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር ሁሉ ስለ ሞትም ጭምር ያለንን አመለካከት የሚቀይር ነው፡፡ በደስታ «ሞት የለም» ብለን በእርግጠኝነትም መናገር እንድንችል የሚያደርገን ነው፡፡

 

ኦ! ሞት ግን አሁንም አለ፤ በእርግጠኝነት እንጋፈጠዋለን፤ አንድ ቀንም መጥቶ ይወስደናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በራሱ ሞት፣ የሞትን ባሕርይ /ምንነት/ እንደቀየረው ይህ ሙሉ እምነታችን ነው፤ ሞትን ወደ ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ፣ ማለፊያ፣ ፋሲካ አድርጎታል፤ ከአሳዛኝ ነገሮች ሁሉ የበለጠ አሳዛኝ የነበ ረውን ሞት ወደ ፍጹም ድልነት ቀይሮታል፡፡ «ሞትን በሞቱ ደምስሶ» የትንሣኤው ተካፋዮች አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው «ክርስቶስ ተነሥቷል፣ ሕይወትም ሆኗል፤ ማንም በመቃብር አይቀርም» የምንለው፡፡

 

ቁጥር በሌላቸው በቅዱሳኖቿ የተረጋገጠውና ግልጽ የተደረገው የቤተክርስቲያን እምነት ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እምነት በእኛ ውስጥ ሁልጊዜ አለመኖሩ [ይህንን ሁል ጊዜ አለማሰባችን]፤ እንዲሁም እንደ ስጦታ የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት ሁልጊዜ መጣላችንና መካዳችን እንዲሁም ክርስቶስ ከሞት እንዳልተነሣ ሆነን የመኖራችን ነገር እና ያ ልዩ ክስተት ለእኛ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑ የዕለት ተዕለት ተሞክሮአችን አይደለምን?

ይህ ሁሉ የሆነው በድካማችን ምክንያት ነው፡፡ ማለትም ጌታ «አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ፈልጉ» ባለን ጊዜ በወሰነልን ደረጃ «በእምነት፣ በተስፋ እና በፍቅር» መኖር ለእኛ የማይቻለን በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በቀላሉ እንረሳዋለን፤ ምክንያቱም ሁልጊዜም በተለያዩ ሥራዎች የተጠመድን እና በዕለት ተዕለት ተግባሮቻችን የተዋጥን ነን፤ ስለ ምንረሳም እንወድቃለን፤ በጥምቀት የተቀበልነውን አዲስ ሕይወት እና ብርሃንም እንጠራለን፡፡

 

በዚህ በመርሳት፣ በመውደቅ እና ኃጢአት በመሥራት በኩልም ሕይወታችን በድጋሜ «አሮጌ» ይሆናል፤ ጥቅም /ረብ/ የሌለው፤ ጨለማ እና ትርጉም አልባ፤ ትርጉም የሌለው ጉዞ፤ ትርጉም ወደሌለው ፍጻሜ ይሆናል፡፡

ሞትን እንኳን ሳይቀር ረስተነው ከቆየን በኋላ በድንገት «ደስታ በሞላበት ሕይወታችን» መሐል አስፈሪ፣ ሊያመልጡት የማይችሉት እና አስጨናቂ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፡፡

በየጊዜው ኃጢአታችንን ልንናዘዝ እንችላለን፤ ነገር ግን ሕይወታችንን ከዚያ ክርስቶስ ለእኛ ከገለጠውና ከሰጠው ከአዲሱ ሕይወት ጋር ማዛመድና ሕይወታችንን በዚያ ላይ መመሥረት እናቆማለን፡፡ ትልቁና እውነተኛው ኃጢአት፣ የኃጢአቶች ሁሉ ኃጢአት፣ የስም ብቻ የሆነው ክርስትናችን በጣም አሳዛኝ ገጽታ ይህ ነው፡፡ የሕይወታችንን ትርጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ላይ አለመመሥረት፡፡

 

ይህንን ልብ ካልን፣ የትንሣኤ በዓል ምን እንደሆነና ዐቢይ ጾም ለምን ከእርሱ በፊት እንዲኖር እንዳስፈለገ እንረዳለን፡፡

በዐቢይ ጾም በቤተክርስቲያን የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ዓላማም በቀላሉ የምንጥለውንና የምንወስደውን የዚያን የአዲስ ሕይወት ርእይ እና ጣዕም በውስጣችን እንድናድሰው ለመርዳት እና ተጸጽተን ወደ እርሱ እንድንመለስ ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም የማናውቀውን ነገር እንዴት ልንወድና ልንፈልግ እንችላለን? አይተነው እና አጣጥመነው የማናውቀውን ነገር እንዴት በሕይወታችን ካሉ ነገሮች ሁሉ በላይ ልናደርገው እንችላለን? በአጭሩ ስለ እርሱ ምንም አሳብ የሌለንን መንግሥት እንዴት ልንፈልግ እንችላለን? አንችልም፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያን በእነዚህ ሥርዓተ አምልኮዎች ይህን እንድናደርግ ትረዳናለች፡፡

 

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ወዳለው ሕይወት መግቢያችን፤ ከዚያም ጋር ያለን ኅብረት መሠረት በቤተክርስቲያን ያለው አምልኮ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን «ጆሮ ያልሰማውን፣ ዓይንም ያላየውን በሰው ልብም ያልታሰበውን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱት ያዘጋጀውን» ከዚያ ነገር ጥቂቱን ለእኛ የም ትገልጥልን በአምልኮ ሕይወቷ አማካኝነት /through her liturgical life/ ነው፡፡ በዚያ በአምልኮ ሕይወት መሐል ላይ ደግሞ፣ እንደ  ጠቅላላው የአምልኮ ሥርዓት ልብ እና ከፍታ፣ እንዲሁም ጨረሮቿ ሁሉም ቦታ እንደሚደርሰው ፀሐይ ሆኖ የትንሣኤ በዓል ይቆማል፡፡

የትንሣኤ በዓል በየዓመቱ ወደ ክርስቶስ መንግሥት ግርማ እና ውበት ለማሳየት የሚከፈት በር ነው፡፡ የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን በስውር ቢሆንም ፍጥረትን ሁሉ የሞላው፣ «ሞት የለም!» የሚለው የዚያ ድል ክብር መገለጫ ነው፡፡

 

አጠቃላይ የቤተክርስቲያን የአምልኮ ሕይወት ዓመታዊው የአምልኮ መርኀ ግብር /liturgical year/ የተደራጀው በትንሣኤ ዙሪያ ነው፤ ማለትም በዓመቱ በተከታታይ የሚመጡት ወቅቶች እና በዓላት ወደ ፋሲካ፣ ወደ ፍጻሜው የሚደረጉ ጉዞዎች ይሆናሉ፡፡ ፋሲካ ፍጻሜ ብቻ ሳይሆን ጅማሬም ነው፤ «አሮጌ» የሆነው ነገር ሁሉ ፍጻሜ እና የአዲስ ሕይወት መጀመሪያ፤ ከዚህ ዓለም በክርስቶስ ወደ ተገለጠው መንግሥት መሸጋገሪያ ነው፡፡

 

ይሁን እንጂ የኃጢአት እና የማይረቡ ነገሮች መንገድ የሆነው «አሮጌው» ሕይወት ግን በቀላሉ የሚሸነፍ እና የሚቀየር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊፈጽመው የማይችለውን ነገር የወንጌል ሕግ ትጠብቅበታለች፡፡ ከአቅማችን እና ከምንችለው እጅግ በጣም በሚበልጥ ርእይ፣ ግብ እና የሕይወት መንገድ እንፈተናለን ምክንያቱም ሐዋርያት እንኳን ሳይቀሩ የጌታን ትምህርት ሲሰሙ ተስፋ በመቁረጥ «ይህ እንዴት ይቻላል?» ብለው ጠይቀውታል፡፡ በእርግጥም በየዕለቱ በሚያስፈልጉን ነገሮች በመጨነቅ፣ ቀላል ነገሮችን፣ ዋስትናን እና ደስታን በመፈለግ የተሞላን የማይረባ የሕይወት እሳቤ ትቶ «ሰማያዊ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ» የተባለለትንና ከፍጽምና በቀር ሌላ ምንም ግቡ ያልሆነውን የሕይወት እሳቤ መያዝ ቀላል አይደለም፡፡

 

ዓለም በመገናኛ ብዙኃኖቿ በሙሉ «ተደሰቱ፣ ቀለል አድርጋችሁ እዩት /take it easy/፣ ሰፊውን መንገድ ተከተሉ» ትለናለች፡፡ ክርስቶስ ደግሞ በወንጌል «ጠባቡን መንገድ ምረጡ፣ ተዋጉና መከራን ተቀበሉ፤ ይህ ወደ እውነተኛው ደስታ የሚያደርስ ብቸኛው መንገድ ነውና» ይለናል፡፡ ቤተክርስቲያን ካልረዳችን ካልደገፈችን እንዴት ያንን አስጨናቂ ምርጫ መምረጥ እንችላልን? እንዴትስ መጸጸት /ንስሐ መግባት/ እና በየዓመቱ በትንሣኤ በዓል ዕለት ወደሚሰጠው የከበረ ቃል ኪዳን መመለስ እንችላለን? የዐቢይ ጾም አስፈላጊነቱ እዚህ ላይ ነው ይህ በቤተ ክርስቲያን የተዘጋጀልን ዕርዳታ፣ የትንሣኤ በዓልን የመብላት የመጠጣት እና የመዝናናት ፈቃድ የሚገኝበት ዕለት ነው ብለን ሳይሆን፣ በውስጣችን ያለው የአሮጌው መጨረሻ እና የእኛ ወደ አዲሱ መግቢያ አድርገን እንድንቀበለው የሚያስችለን የንስሐ ትምህርት ቤት ነው፡፡

 

በጥንታዊቷ ቤተክርስቲያን የዐቢይ ጾም ዋና ዓላማ ንኡሰ ክርስቲያንን ማለትም አዳዲስ አማንያንን በዚያን ጊዜ በትንሣኤ ዕለት ለሚፈጸመው ጥምቀት ማዘጋጀት ነበር፡፡ ነገር ግን /ክርስትና ከተስፋፋና/ የሚጠመቁ ሰዎች ቁጥር ከቀነሰ በኋላም ግን ቢሆን የዐቢይ ጾም መሠረታዊ ትርጉም በዚያው ጸንቷል፡፡ ስለዚህም ትንሣኤ በየዓመቱ ወደ ጥምቀታችን መመለሻ ሲሆን ዐቢይ ጾም ደግሞ ለመመለስ መዘጋጃችን ነው፤ በክርስቶስ ወደሆነው አዲስ ሕይወት ለመተላለፍ የምናደርገው ትጋትና ጥረታችን ነው፡፡

 

ዐቢይ ጾም ጉዞ ነው፤ መንፈሳዊ ጉዞ ነው፡፡ ገና ስንጀምረው፣ በዐቢይ ጾም ብሩህ ሐዘን /bright sadness/ ውስጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ስንራመድ ከር. . . ቀት ፍጻሜውን /መጨረሻውን/ እናያለን፡፡ ይህም የትንሣኤ በዓል ደስታ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ክብር መግባት ነው፡፡ የዐቢይ ጾምን ሐዘን ብሩህ የሚያደርገውና በወቅቱ የምናደርገውን ጥረት «መንፈሳዊ ምንጭ» የሚያደርገውም ይህ የትንሣኤ በዓል ቅምሻ የሆነው ብሩህ ርእይ ነው፡፡

ሌሊቱ ጨለማ እና ረጅም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን በመንገዱ ሁሉ ምስጢራዊ የሆነ ብሩህ ወገግታ በአድማሱ ላይ ያንፀባርቃል፡፡«ሰውን ወዳጅ /መፍቀሬ ሰብእ/ ሆይ! አቤቱ ተስፋ ያደረግነውን ነገር አታስቀርብን» አሜን፡፡

 

ምንጭ፡- [The Lent, Father Alexander Schemaman, St. vladmir’s Seminary Press,].

ሐመር መጋቢት 2002