በደማቸው እንዳንጠየቅ ሥጋት አለን

በስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የምናስተውለው ችግር በሕዝቦች መካከል ያለው የቋንቋ ልዩነትና በነዚህ ቋንቋዎች ሠልጥነው የተዘጋጁ ልኡካን ማነስ ነበር፡፡ ይህ ችግር ብዙ ማኅበረሰቦችን ከስብከተ ወንጌል ተለይተው እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህም ሌላ ሕዝቡ በተለያዩ የእምነት ድርጅቶች እንዲወሰድና ከበረት እንዲወጣም ሆኗል፡፡

 

አሁን አሁን በመጠኑም ቢሆን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ሰባክያን፣ መዘምራን፣ ማኅበራት ወዘተ ምእመናን በሚያውቁትና በሚረዱት ቋንቋቸው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንዲያገኙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

መዝሙሮች፣ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍት ወዘተ ወደ ልዩ ልዩ የሀገራችን ቋንቋዎች በመተርጐም ላይ ናቸው፡፡ ከዚህም አለፍ ብሎ በየቋንቋው ትምህርት የሚሰጡ፣ መዝሙር የሚያዘጋጁ፣ የሚቀድሱና የሚናዝዙ ካህናትም እየተገኙ ነው፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ በሰንበት ት/ቤቶች፣ በሰባክያን፣ በመዘምራን፣ በማኅበራት፣ በዲያቆናትና በካህናት የሚደረገው ጥረት በየአካባቢው ያለውን ሕዝብ ከመናፍቃን ቅሰጣ ታድጐ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያውቅ እያደረገው መሆኑን በየጊዜው የሚሰሙት ዜናዎች ያስረዳሉ፡፡

በበቂ ሁኔታም ባይሆን ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን ችግር ለመቅረፍና አገልግሎቱን ለማስፋፋት መዝሙራቱን፣ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍቱን በየቋንቋው ከመተርጐም እና ከማዘጋጀት ባለፈ በአካባቢያቸው /በአፍ መፍቻ/ ቋንቋቸው ትምህርተ ወንጌልን የሚያስተምሩና በመቅደስ አገልግሎት የሚሳተፉ ወገኖች ከየአህጉረ ስብከቱ በየደረጃው ካሉ የቤተክርስቲያን ሓላፊዎች ጋር በመተባበር በርቀት ከጠረፋማ እና ገጠራማ አካባቢዎች ሠልጣኞችን በማስመጣት እያስተማረ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 15 ቀን 2002 ዓ. ም. ድረስ ከጋምቤላ ሀገረ ስብከት ከሰባት የገጠር ወረዳዎች ለተውጣጡ አሥራ ስድስት ተተኪ ሰባክያን የሰጠውን ሥልጠና መጥቀስ ይቻላል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ስብከተ ወንጌል ካልተስፋፋባቸው የሀገሪቱ ገጠራማ እና ጠረፋማ የወረዳ ከተሞች የተተኪ ሰባክያን ሥልጠና ሲሰጥ ይሄኛው ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን፤ እስከ አሁን ከየሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ጋር በመነጋገር ከ96 የሀገሪቱ ጠረፋማ ወረዳዎች ለተውጣጡ ከሁለት መቶ በላይ ተተኪ መምህራን መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት ተምረው በቋንቋቸው ሕዝቡን እንዲያስተምሩ አሠልጥኖ አሰማርቷል፡፡

የሥልጠናውን ውጤት ለመዳሰስ እንደተሞከረው የተተኪ ሰባክያን ሥልጠና የወሰዱት ሰባክያን የአካባቢያቸውን ሕዝብ ከባዕድ አምልኮ በመመለስ፣ አስተምሮ በማስጠመቅ፣ አብያተ ክርስቲያናት በመትከልና የሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማደራጀት እና በማቋቅም ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ዓይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

በመጠኑም ቢሆን ይህ ውጤት የተገኘው ለሥራው የየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት ድጋፍ፣ ከአጥቢያ ጀምሮ ሥልጠናውን ለመውሰድ የሚመጡትን ሠልጣኞች ከሚገኙበት ገጠራማና   ጠረፋማ ስብከተ ወንጌል ካልተዳረሰባቸው ወረዳዎች በመመልመል የየወረዳው ቤተ ክህነት ሓላፊዎች ቀናና የጋራ ትብብር ስለታከለበት ነው፡፡ ይህ ታላቅ ሥራ የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልእኮ የሆነውን የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት የሚያስፋፋ በመሆኑ በየአካባቢው የሚሠሩትን መልካም ሥራዎች ብቻ በየራሳቸው እያዩ ከማመስገን ባሻገር አገልግሎቱ የሚስፋፋበትንና የሚጠነክርበትን ሥራ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ መጠቆም እንወዳለን፡፡

በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመናፈቅ እየተጠባበቁ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ወገኖች ፈጽሞ በመናፍቃኑ ትምህርት ተጠራርገው ከመወሰዳቸው በፊት በቋንቋቸው በማስተማርም ሆነ በቋንቋቸው የሚያስተምሩ ሰዎችን ከየአካባቢያቸው በማሠልጠን ወንጌልን እንዲያስተምሯቸው ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህን ወገኖች ወደተፈለገው የአገልግሎት ደረጃ ለማድረስ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጡ ሥልጠናዎች እነሱን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ የአመላመል ሒደቱ፣ የትምህርት አሰጣጡ፣ የትምህርት መርጃ መሣሪያ አቅርቦቱ፣ ሥልጠናው የሚሰጥበት ማዕከላዊ ቦታ በዋናነት ሊታሰብበት የሚገባው ቁም ነገር መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደካህናት ማሠልጠኛዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት፣ የመቀሌ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ከሚገቡት ተማሪዎች መካከል በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሊያስተምሩ ለሚችሉት እና በርቀት ለሚገኙት አካባቢዎች የተለየ ትኩረትና ቦታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም የሥልጠናና የትምህርት ሒደቱን የሚከታተል የትምህርት ክፍል /ዲ¬ርትመንት/ ማቋቋም ይቻላል፡፡

እነዚህን ደቀ መዛሙርት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ሥራ ለመሥራት በሚችሉበት መንገድ አሠልጥኖ ማሠማራቱ በሀገሪቱ የሚገኙትን ልዩ ልዩ ሕዝቦች በቀላሉ ለማስተማርና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ያላቸውን የእናትነትና የልጅነት አንድነት ለማጠናከር ይረዳል፡፡ በየቦታው የሚደረገውን የትርጉምና የድርሰት ሥራ፤ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚሰጠውን   ሥልጠናና ትምህርትም ሥርዓት በማስያዝ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ በደስታና ለቤተ ክርስቲያን በመቅናት የተጀመረው በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የማስተማር፣ የመዘመር፣ የማሠልጠን፣ የተለያዩ ጽሑፎችን የመድረስና የመተርጐም ሥራ ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶ ፍሬ ሊያፈራ በሚችልበት መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛና ቀጥተኛ ትምህርት በመናፈቅ    የሚጠብቁንን ሕዝቦች በኃጢአትና በክህደት ተጠልፈው በዲያብሎስ እጅ ወድቀው በሥጋም በነፍስም በመጐዳታቸው ምክንያት በደማቸው እንዳንጠየቅ እንሠጋለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር