የሆሳዕና እሁድ

በዲ/ን በረከት አዝመራው
 
«አንች የጽዮን ልጅ አትፍሪ፤ እነሆ ንጉሥሽ በእህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ይመጣል» ተብሎ እንደተጻፈ ኢየሱስ የአህያ ውርንጫ አግኝቶ በእርሱ ተቀመጠ ዮሐ.12፥15፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመምጣቱ አስቀድሞ 1400 ዓመታት በፊት እግዚአብሔር በአብርሃም የእምነት ቃል ኪዳን ሕዝቡ ያደረጋቸውን እስራኤላውያንን በጽኑ  ክንድ ከባርነት ቀንበር አውጠቶ ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን አምድ እየመራ በመገናኛዋ ድንኳን ውስጥ አድሮ እርሱ ንጉሣቸው ሆኖ እነርሱ ደግሞ ህዝቡ ሆነው በምድረ በዳ መራቸው፤ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከነዓንም አገባቸው፡፡ እስራኤል ግን ምድራዊ ንጉሥ በመፈለግ ንጉሣቸው እግዚአብሔርን በመተዋቸው እግዚአብሔርን በደሉ፤ በምድር ላይ ያለች የመንግሥቱ ማሳያ ሊሆኑ የመረጣቸው ሕዝቡ ምድራዊ ንጉሥ ፈልገዋልና፡፡ መልከ መልካምና ያማረ የሆነው ሳኦል እስራኤል የመረጡት ምድራዊ ንጉሥ ውጫዊ ክብር ብቻ ያለው መሆኑን አስመስከረ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ዓለም ያልሆነች በቁሳዊው ኅብር ያላጌጠች፣ የትህትናና የፍቅር የምሥጋና የሆነች መንግሥቱን ሊያመለክት ሲወድ ከወንድሞቹ ሁሉ ያነሰውንና በገና ደርደሪውን የእሴይን ልጅ ዳዊትን መረጠ፡፡ የዳዊት መንግሥት ብታልፍም « ከሆድህ ፍሬ በዙፋንህ ላይ አስቀምጣለሁ» ያለውን ቃልኪዳን ግን አላጠፋም ፡፡ ስለዚህም በአምላክነቱ ለዘላለም የነገሥታት ንጉሥ የሆነ ወልድ ከዳዊት ዘር ሰው ሲሆን የዳዊት ተስፋ ተፈጸመ፤ በመለኮታዊ ስልጣኑ በእግዚአብሔር እሪና ያለው ወልደ እግዚአብሔር የዳዊት ልጅ ሆኗልና፡፡ ስለዚህም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ሲያበስራት «ካንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤ እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፡፡ እርሱም በያዕቆብ ወገን ላይ ለዘላለም ይነግሳል» በማለት የትንቢቱን ፍፃሜ አበሰረ፡፡ /ሉቃ.1/

  ንጉሥነ ክርስቶስ

ጌታችን ሲወለድ ስብዓሰገል «የተወለደው የእስራኤል ንጉሥ ወዴት ነው» በማለት ንጉሥነቱን ገልጠዋል፡፡ /ሉቃ. 2፥2/ ነገር ግን በምድራዊ ክብር ያጌጠ ሳይሆን በከብቶች ግርግም የተኛ፣ በእረኞችና በከብቶች የተከበበ ትሁት ንጉሥ ነው፡፡ መንግሥቱ ከዚህ ዓለም ያልሆነች ሰማያዊት ነችና መላእክት በዝማሬ አመሰገኑት፡፡ ጌታ ንጉሥ ያልሆነበት አንድ ጊዜም  ባይኖርም ይህች መንግሥቱ በምድራዊ ክብር ሳይሆን በትህትና በፍቅር ያጌጠች ሰማያዊት ስለሆነች በሃሳባቸው ምድራውያን የሆኑ ሰዎች ሊያውቋት አልቻሉም፡፡ ስለዚሀ የቀጠራት ሰዓት ስትደርሰ ሰማያዊትና መንፈሳዊት መንግሥቱን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ በትህትና ገለጣት፡፡

«ሆሳዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የእስራኤል ንጉሥ የተባረከ ነው፡፡» ዮሐ.12፥13   

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአልዓዛር ቤት በቢታኒያ የመጨረሻውን ራት ከበላ በኋላ ሐዋርያቱን ልኮ የአህያ ውርንጫ አስመጥቶ በርሷ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም  የሚከተሉት ነገሮች ተገልጠዋል፡ ፣

1.    መንግሥቱ የትህትና እና የፈቃድ መሆኗን

አህያ ከእንሰሳት ሁሉ የማታስፈራ ናት፡፡ ጌታም እንደ ነገሥታቱ ስርዓት በከበረ ሰረገላና በፈረስ ሳይሆን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ መንግሥቱ የትህትና መሆኗንና ሁሉም ሰው ተገዶ እና ፈርቶ ሳይሆን በፈቃዱ የሚገባባት መሆኗን ለማሳየት ነው፤ በአህያ ሰውን አባሮ መያዝ እንኳ አይቻልምና፡፡ ይህም በአጋጣሚ እንደ አንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ የሆነ ሳይሆን ነቢያት በትንቢት የተናገሩትና በእግዚአብሔር የድህነት ጉዞ የታሰበ ነው፡፡ ነቢዩ ዘካርያርስ ስለዚህ ሲናገር «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንች የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዬ፤ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም  ሆኖ በአህያም በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንች ይመጣል» በማለት ገልጦታል፡፡ ዘካ.9፥9፡፡

2.    የመገለጡ አላማ ለድህነት እንጅ ለክብር አለመሆኑ

 
እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል ከማክበራቸው ከአምስት ቀን በፊት በዚህ ዕለት ለፋሲካ የሚሆኑት ጠቦቶችን ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ይገቡ ነበር፡፡ /ዘጸ.12፥1- 36/ ጌታችንም በዚህ ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም መውጣቱ የመንግስቱን ምሥጢር በመስቀልና በመስዋዕትነት ፍቅር የሚገልጽ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ከላይ በተጠቀሰው የዘካርያስ ትንቢት ላይ « እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው» የሚለው፡፡ ጌታችን ንጉሥ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ለመመስገን አስቦ ሳይሆን ይቀበሉት ዘንድ አለምን ለማዳን የመጣው ንጉሥ እርሱ መሆኑን በአደባባይ ለማወጅ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ምሥጋናን  ከህፃናት የተቀበለው፤ ሕፃናት ሁሉን ይቀበላሉና፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አትገቡም በማለት የተናገረው፡፡ / ሉቃ. 18፥17 / የመዳን ተስፋ የተነገረላቸው እስራኤላውያን ባልተቀበሉት ጊዜ ግን የመጣበት ዓላማ ይህ ስለነበር  ስለነርሱ አለቀሰ፡፡ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፤ እንዲህም አለ «ለሰላምሸ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ እንኳ ብታወቂ አሁን ግን ከአይንሽ ተሰውሯል» ሉቃ. 19.41፡፡ የመምጣቱ ዓላማ ለዓለም ሰላምን የሚሰጥ /እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቅ/ አዳኝ ንጉሥ፣ የፋሲካ በግ መሆኑን ለማወጅ ነበርና ባልተቀበሉት ጊዜ አለቀሰላቸው፡፡ «ሆሳዕና» ማለት ግን «አሁን አድን» ማለት ስለሆነ አዳኝነቱ መቀበል ነበር፡፡ ንጉሥነቱን በአዳኝነቱ መግለጡም መንግሥቱ የፍቅር መሆኑንና ዙፋኑም መስቀል መሆኑን ለመግለጥ ነው፤ በጉ «የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ» ነውና፡፡ ራዕይ.19፥13- 16

  የሆሳዕና አከባበር በቅድስት ቤተክርስቲያናችን

ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሆሳዕና በታላቅ ክብር ታከብራለች፡፡ አከባበሯም እንደ አይሁድ እሁድ ሆሳዕና በእግዚአብሔር ስም የመጣች የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፣ ሆሳዕና በአርያም ካሉ በኋላ አርብ « ይሰቀል ይሰቀል» በማለት ሳይሆን እስከ መጨረሻው ድረስ ከእርሱ ጋር መሆንን በሚያሳይ አስደሳችና መንፈሳውያን ስርዓቶቿ ነው፡፡ እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዑደት

በቤተከርስቲያትን ሥርዓት መሰረት የሆሳዕና ጠዋት ቅዳሴ ከመገባቱ በፊት ዑደት ይደረጋል፡፡ ዑደቱም ከቤተመቅደስ ተጀምሮ በየአራት በሮች እየቆመ ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከተዞረ በኋላ በመጨረሻ ካህናቱና ዲያቆናቱ ወደ ቤተመቅደሱ ሲመለሱ ያልቃል፡፡ ዑደቱንም ዲያቆናት መስቀልና ስዕል /የእመቤታችን/ ይዘው፣ ካህኑ ማዕጠንት እያጠኑ ይመሩታል፡፡

 
ይህ ዑደት የቤተክርስቲያን ዘላለማዊው ጉዞዋ ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ጉዞ ከእግዚአብሔር ይጀምራል፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔር ጅማሬ እንጅ የሰው አይደለምና፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ዑደት ከመሰዊያው ይጀምራል፤ መስዊያው ሰማያዊ ነውና፡፡ የዚህ የቤተክርስቲያን ጉዞ መሪ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር መርቶ ያደረሰ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለዚህ ካህኑ ዕጣን እያጠነ ይመራል፡፡ ይህ ጉዞ መከራ ያለበት መንገዱ ጠባብ ይሁን  እንጅ በደስታ የተሞላ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑ መስቀል ሲይዝ ሕዝቡ ደግሞ ይዘምራሉ፡፡ ደስታና መስቀልን በአንድ ላይ ለመግለጥ ነው፡፡ የዚህ ጉዞ ፍጹም አርአያ ደግሞ እመቤታችን ናት ሁለቱንም ታሳያለችና፡፡ በአንድ በኩለ «ኅዘን በልቧ ያለፈ» ሲሆን በሌላ በኩል « ተአብዮ ነፍስዬ ለእግዚአብሔር ወትተሐሰይ መንፈስየ» ብላ ዘምራለችና፡፡ ዑደቱ በምዕራብ በር በኩል /በዋናው በር/ መጀመሩ እና በእያንዳንዱ በር መቆማችን የዘላለም ደጆች መከፈታቸውንና ሰማያውያንም የጉዞአችን /የማኅብራችን/ ተካፋዮች መሆናቸውን ያጠይቃል፡፡ በመጨረሻም ዑደቱ በካህናቱ ወደቤተ መቅደሱ መግባት መጠናቀቁ የክርስትና ጉዟችን ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም በመኖር መፈጸሙን ያሳያል ፡፡ በዚህ ጉዞዋ ቤተክርስቲያናችን እስከ መጨረሻው ከክርስቶስ የሚጸና ዘላለማው ጉዞዋን ትናገራለች፡፡

  ቅዳሴ

ከዑደት በኋላ ቅዳሴ ይቀጥላል፡፡ በቅዳሴም የክርስቶስን ሥጋና ደም እንቀበላለን በዚህም እስከሞት ድረስ የሚዘልቅ አንድነታችን እንገልጣለን፡፡ ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ «ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሌ ይፈጸማል፡፡ ለአህዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና ይዘብቱበትማል፣ ያንገላቱትማል፣ ይተፉበታል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል በሦስተኛውም ቀን ይነሳል፡፡» እንዳለ የኢየሩሳሌም ጉዞው ወደሞት የተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ስለዚህ በሥጋወደሙ ከእርሱ ጋር የሆንን ምእመናንንም ከእርሱ ጋር ወደ ሙት እንሄዳለን፡፡   

ፍትሐት

ከቅዳሴ በኋላ ፍትሃት ይደረጋል፤ ይህም ለህዝቡ ሁሉ ነው፡፡ አንዳንዶች ይህ ፍትሃት ምናልባት በዚህ ሰሞን የሚሞቱ ካሉ በሚል የሚደረግ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ፍትሃት ለሁሉም ክርስቲያን ጭምር ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የጌታን ሞትና ትንሳኤ ማሰብ ሳይሆን አብረነው ሞቱን ትንሳኤውን እንካፈላለንና፡፡ ሰውነታችን በጸሎትና በስግደት ለዓለማዊ ፈቃዳችን ሁሉ ገድለን በእርሱ ትንሳኤ ትንሳኤ ልቦናን እንነሳለንና፡፡ ይህም ለመነኮሳት እንደሚደረግ ፍትሃት ያለ ነው፡፡ መነኮሳት ሲመነኩሱ ለዚህ ዓለም የሞቱ መሆናቸውንና የክርስቶስን መስቀል መሸከማቸውን ለማጠየቅ የሙታን ጸሎት እንደሚደረግላቸው ምእመናንንም የጌታን መስቀል በመሸከምና መከራውን በመካፈል ለዓለም ለመሞት በመወሰን ቤተክርስቲያን የሙታን ጸሎት ታደርግላቸዋለች፡፡ በዚህም ጌታችንን አብረን ወደ ሞቱ እንከተለዋለን፡፡

  ወስብሐት ለእግዚአብሔር