የተራራው ምስጢር/ማቴ 17፡1-9/

ዲያቆን ታደለ ፈንታው


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልጶስ ቂሣርያ መነ ይብልዎ ሰብእ ለወልደ እጓለ እመሕያው የሰው ልጅን ማን እንደሆነ ይሉታል ? የሚል ጥያቄን ለደቀ መዛሙርቱ አቀረበላቸው ፡፡ አንዳንዶች ከነቢያት አንዱ ነህ አሉት ፡፡ በሥምም እየጠቀሱ መጥምቁ ዮሐንስ : ኤልያስ : ኤርምያስ ነህ በማለት ግምታቸውን አስቀመጡ፡፡ ደቀመዛሙርቱ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተነገረ ገና በእምነት አልጠነከሩም ነበርና ግምታቸው የተዘበራረቀ ነበረ፡፡

 

ከሐዋርያት አንዱ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ የእርሱ ተራ በደረሰ ጊዜ የሰጠው ምስክርነት ግን ድንቅ የሆነ ምስክርነት ነበር፡፡ «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ»/ማቴ 16፡13/ የሚል፡፡ የዮና ልጅ ስምዖን በዚህ ምስክርነቱ ብፁዕ ነህ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን እንዲህ አይነቱን ምስክርነት ሥጋና ደም አልገለጸልህም በሰማይ ያለው አባቴ እንጂ አለ ፡፡ በዘመናችን ብዙዎች የሥጋና ደም ሀሳብን ይዘው አምጻኤ አለማትነቱ፤ ከሃሊነቱ፤ ጌትነቱ፤ ተአምራቱ፤ መግቦቱ፤ ዓይን ነሥቶ ዓይን ለሌለው ዓይን ሰጥቶ መመገቡ አልታያቸው ብሎ አማላጅ ነህ ይሉታል፡፡ ያለባሕርይው ባሕርይ ሰጥተው በየመንደሩ፤ በየዳሱ አለ ብለው ይጠሩታል፤ እርሱ ግን «እነሆ ክርስቶስ በመንደር ወይም በእልፍኝ ውስጥ አለ ቢሏችሁ አትመኑ» አለ ፡፡ ከራሳቸው ልቡና አንቅተው ስለጌታችን የተሳሳተ መረዳት ያላቸው ሰውንም የሚያሳስቱ የሥጋና ደም ኃሳባቸውን ቀላቅለው ንፁህ የሆነውን የወንጌል ቃል የሚበርዙ ወገኖች ብፁዓን ናችሁ አልተባሉም ፡፡

 

ይህ ምስክርነት በተሰጠ ማለትም «በቂሣርያ የሰውን ልጅ ማን ይሉታል»ባላቸው በሰባተኛው ቀን ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ለብቻቸው ይዞአቸው ወደረጅምና ከፍ ወደአለ ተራራ ወጣ ፡፡ በከፍታው ላይ ያለ ልዑል እግዚአብሔር ረጅምና ከፍ ያለ ነገርን ይወዳል ፡፡ ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እግዚአብሔርን የተመለከተው በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ነበር»ጌታችን ሰው ሆኖ ሥጋን ሲዋኻድም ከፍጥረታት ሁሉ ከፍ ያለውን አማናዊ ዙፋን እርሱም የእመቤታችንን ማኅጸን ነበረ የመረጠው፡፡ ይኸንን ሁኔታ ሊቁ አባ ሕርያቆስ እንዲህ ብሎ በማድነቅ ይጠይቃል፡፡ «ድንግል ሆይ ሰባት የእሳት መጋረጃ ከሆድሽ በስተየት በኩል ተጋረደ በስተቀኝ ነውን? በስተግራ ነውን ? ታናሽ ሙሽራ ስትሆኝ፡፡ ለአባታችን ያዕቆብም የገለጸለት መሰላል ከምድር ከፍ ያለ መሰላል ነበረ፡፡ ምሳሌነቱን ከፍጥረታት ሁሉ ከፍ ላለች ለእመቤታችን ነው፡፡ የጌታችን ከፍ ያለ ነገር መዉደድ ምሳሌው ልዑለ ባሕርይ ነኝ ሲል ነው፡፡

 

ለምን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ተገለጠ ?


በመጀመሪያ ተራራ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው ፡፡ ተራራን በብዙ ድካም እንዲወጡት መንግሥተ ሰማያትንም በብዙ መከራ ያገኟታል ፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጥ እስመ በብዙህ ጻዕር ወበጻማ ኃለወነ ንባኣ መንግሥተ እግዚአብሔር በብዙ ጭንቅ መከራ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንገባ ዘንድ አለን በማለት አስረድቷል ፡፡ ተራራውን ሐዋያርት በሲኖዶስ ታቦር ብለው ጠርተውታል፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር «የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ ፡፡ ከገናናው ክብር በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው እርሱን ስሙት የሚል ያ ድምጽ በመጣለት ጊዜ ከእግዚአብሔር አብ ክብርንና ምስጋናን ተቀብሎአልና ፤ እኛም በቅዱሱ ተራራ ከእርሱ ጋር ሳለን ይህ ድምጽ ከሰማይ ሲወርድ ሰማን/1ኛ ጴጥ1፤16/ ብሏል ፡፡

 

ጌታችን ምስጢረ መለኮቱን በታቦር ያደረገው በሌላ ተራራ ያላደረገው አስቀድሞ ታቦር ትንቢት የተነገረበት ተራራ በመሆኑ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት «ታቦር ወአርሞንዔም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ» ብሎ ተናግሯል፡፡ የጌታችን ሰው መሆን የነቢያት ትንቢት ፍጻሜ ማግኘቱን ማሳያ ነው፡፡

 

አሥራ ሁለቱንም ደቀ መዛሙርት የመረጣቸው ጌታችን ነው ፡፡ በመጀመሪያ ሙሴን ለመስፍንነት አሮንን ለክህነት የመረጠበት ግብር እንዳልታወቀ ከደቀመዛሙርቱ ሦስቱን የመረጠበትን ምክንያት የሚያውቀው እርሱ ብቻ ነው ፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ግን ሦስቱን ወደ ተራራ ይዞአቸው ስምንቱን ከእግረ ተራራ ጥሎአቸው የሄደበት ምክንያት ስለነበራቸው ነው፡፡ የመጀመሪያው ከሌሎቹ የሚበልጡበት ምክንያት ነበራቸውና፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይወደው ነበርና ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ተብሎ በብዙ ቦታ ተገልጧል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ አንተ የምትጠጣውን ጽዋ እኛም እንጠጣለን ብሏል/ማቴ20፤22/፡፡እንደገናም ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ መስክሮ ሥለነበረ ምስክርነቱ በእርሱ ብቻ የሚቀር ሳይሆን እግዚአብሔር አብም በደመና ሆኖ የሰጠው ምስክርነት «በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጀ እርሱ ነው እርሱን ስሙት» በማለት የተናገረው ከቅዱስ ጴጥሮስ ምስክርነት ጋር ያለው ድንቅ ስምምነት ይገለጥ ዘንድ ነው፡፡ በዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ምስክርነት ሥጋና ደም ያልገለጠለት መሆኑ በተረዳ ነገር ታውቋል ፡፡ እንደገናም ቅዱስ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞአቸው ወደተራራ የወጣበት ምክንያት የዘብዴዎስ ልጆች እናት /እናታቸው/ ማርያም ባውፍልያ ጌታችን መንግሥቱ ከዚህ ዓለም መስሎአት ልጆቿን አስከትላ እየማለደች ሰገደችለት ፡፡ እንዲህም የሚል ልመናን ስለልጆችዋ አቀረበች፡፡

 

ወትቤሎ ረቢ ሊተ ከመ ይንበሩ እሉ ደቂቅየ አሐዱ በየማንከ ወአሐዱ በጸጋምከ በመንግሥትከ፡፡

በነገሥህ ጊዜ እኒህ ልጆቸ አንዱ በቀኘህ አንዱ በግራህ እንዲቀመጡ አድርግልኝ፡፡

ወአውሥአ እግዚእ ኢየሱስ ወይቤላ ኢተአምሩ ዘትስእሉ የምትለምኑትን አታውቁም አለ፡፡


ጌታችን መንግሥቱ ሰማያዊት እንጂ ምድራዊት አለመሆኑን ይገልጥላቸው ዘንድ ይዞአቸው ወደተራራ ወጣ፡፡ ስምንቱን ከእግረ ደብር ትቷቸው የወጣበት ምክንያት በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ ክብሩንና መንግሥቱን እንዳያይ ይሁዳ ትንቢት ተነግሮበታልና ለይቶም እንዳይተወው ከምሥጢረ መንግሥቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት ብሎ ምክንያት እንዳያገኝ ስምንቱን ጥሎአቸው ወጣ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሕዝቡን ያስተዳድሩ ዘንድ ሰባ ሰዎችን መርጦ ወደ ቅዱሱ ተራራ እንዲያቀርባቸውና ከመንፈሱ ወስዶ በሽማግሌዎቹ ላይ እንዲያፈስባቸውና ሙሴን እንዲያግዙት አዘዘው ፡፡ ከእያንዳንዱ ነገድ ስድስት ሰዎችን መረጠ ከአስራሁለቱ ነገድ የተመረጡት ሰባ ሁለት ሰዎች ሆኑ፤ እንደ እግዚአብሔር ቃል ሰባዎቹን ሰዎች ይዞ የቀሩትን ሁለቱን ኤልዳድንና ሞዳድን ከእግረ ደብር ትቷቸው ወደ ተራራው ወጣ፡፡ በደብረ ሲና ለሰባው ሊቃናት የተገለጠው ምስጢር ከተራራው ሥር ለነበሩ ሁለቱ ሰዎችም ተገልጧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በርእሰ ደብር ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የተገለጠው ምስጢር በእግረ ደብር ላሉ ለስምንቱም ተገልጧል ፡፡

 

ሙሴና ኤልያስ


ሙሴና ኤልያስ በቅዱሱ ተራራ ከጌታችን ጋር የተነጋገሩ ነቢያት ነበሩ ፡፡ በቅዱሱ ተራራ በተከበበ ብርሃን ውስጥ ሆነው ስማቸውን የጠቀስናቸውን ነቢያትን እንመለከታለን ፡፡ እነዚህ ፆም የሚያስገኘውን ጥቅም ያሳዩ ናቸው አርባ አርባ ቀናትን ጾመዋል ፡፡ በቅዱሱም ተራራ ከተገኙት ቅዱሳን መካከል ናቸው ፡፡ እነዚህ ለመገኘታቸው ምክንያት ነበራቸው ፡፡ ጌታችን አስቀድሞ እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃለው እምእለ ይቀዉሙ ዝየ እለ ኢይጥዕምዎ ለሞት እስከ ይሬእይዎ ለመንግሥተ እግዚአብሔር ከዚህ ቁመው ካሉት የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ የማይሞቱ አሉ ብሎ ተናግሮ ነበርና ነቢዩ ኤልያስን፥ ሙሴ እባክህ ክብርህን አሳየኝ ብሎ ለምኖ ነበርና ፊቴን ማየት አይቻልህም ነገር ግን ክብሬን በዓለቱ ላይ እተውልሃለሁ ብሎ ተናግሮት ስለነበረ እግዚአብሔር የተናገረው ቃል ከሞት በኋላ እንኳን ተፈጻሚነቱ የማያጠያይቅ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ሙሴም በቅዱሱ ተራራ ላይ ተገኘ፡፡ እንደገናም ጌታችን ስለማንነቱ ሲጠየቅ ሙሴ ነህ ኤልያስ ነህ ብለውት ስለነበረ እርሱ አምላከ ሙሴና አምላከ ኤልያስ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ከነቢያት ሁለቱ ተገኙ፡፡ እንደገናም ሙሴ የሕጋውያን ኤልያስ የደናግል ምሳሌ ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጠሩት ሁለቱም ወገኖች ናቸውና ፡፡

 

ስለምን ግርማ መለኮቱን ገለጠ ?


ጸሐፍት ፈሪሳውያን የሕጉ ባለቤት ሠራዔ ሕግ እርሱ መሆኑን ባለመገንዘባቸው በተደጋጋሚ ሕጉን ጥሷል በማለት ይከሱት ነበረ ፡፡አይሁድ ይህ ሰው ከእግዚአብሔር አይደለም ፤ ከእርሱስ ቢሆን ሰንበትን አይሽርም ነበር ብለዋልና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደወጣ የሰንበትም ጌታዋ መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ክብሩን መግለጥ ነበረበት፡፡ እንደገናም ቃሌን የሚጠብቅ ቢኖር ለዘላለም ሞትን አይቀምስም በማለት ሲያስተምራቸው በውኑ አንተ ከሞተው ከአባታችን ከአብርሐም ትበልጣለህን ? በማለት ጠየቁት ፡፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ ብሎአቸው ነበርና ክብሩን መግለጥ ነበረበት ፡፡ በሕይወት ካሉት ኤልያስን ከሞቱት ሙሴን የማምጣቱ ምስጢር በሞትና በሕይወት ላይ ስልጣን ያለኝ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ኤልያስን ከብሔረ ሕያውያን ማምጣቱ የሰማይና የምድር ገዢ እኔ ነኝ ሲል ነው፡፡ እንደገናም በሐዋርያቱ የተሰጠውን ምስክርነት በባሕርይ አባቱ በአብ ለማስመስከር ነው፡፡ አስቀድሞ «የሁለት ወገኖች ምስክርነት እውነት እንደሆነ ተጽፏል ስለእራሴ የምመሰክር እኔ ነኝ አብ ስለእኔ ይመሰክራል /ዮሐ.8፥17/ ብሎአቸው ነበርና ነው ፡፡

 

በቅዱሱ ተራራ ላይ


ከሐዋርያት ሦስቱ ከነቢያት ሁለቱ በተገኙበት ልብሱ እሳት ክዳኑ እሳት የሆነ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊታቸው ተለወጠ፡፡ አካሉ ሙሉ ብርሃን ሆነ፡፡ ጽጌያት ከአዕጹቃቸው እንዲፈነዱ፥ፊቱም እንደ ፀሐይ ብሩህ ሆነ፡፡ ልብሱም እንደበረድ ነጭ ሆነ፤ ክብሩን ግርማውን ጌትነቱን ገለጠ፡፡ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ተሰሙ፡፡ ከደመናውም ውስጥ «ዝንቱ ውእቱ ወልድ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ልመለክበት የወደድሁት ለተዋሕዶ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፡፡ ወሎቱ ስምዕዎ እርሱን ስሙት የሚል አስፈሪ ድምጽ መጣ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው አለው አንተ የአምላክነት ሥራህን እየሠራህ ብንራብ እያበላኸን፣ ብንታመም እየፈወስከን፣ ብንሞት እያነሣኸን፤ ሙሴ የወትሮ ሥራውን እየሠራ፣ ደመና እየጋረደ፣ መና እያወረደ፣ ባሕር እየከፈለ፣ ጠላት እየገደለ፡፡ ኤልያስ የወትሮ ሥራውን እየሠራ፣ ሰማይ እየለጎመ፣ እሳትን እያዘነመ፣ ዝናም እያቆመ፣ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፡፡ ወእመሰ ትፈቅድ ንግበር በዝየ ሠለስተ ማኅደረ ከዚህ ሦስት አዳራሽ እንሥራ፤ አሐደ ለከ አንዱን ለአንተ፤ ወአሐደ ለሙሴ አንዱን ለሙሴ፤ ወአሐደ ለኤልያስ አንዱን ለኤልያስ አለ፡፡ ይህንን ገና እየተናገረ እንዳለ ብሩህ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፡፡ አብ የሠጠው ምስክርነት ተሰማ፡፡ እመቤታችን በገሊላ ቃና እርሱን ስሙት /ዮሐ. 2፡5/ በማለት ስለ ልጅዋ የሰጠቸው ምስክርነት ይኸው ነበረ፡፡ የተዓምረ ማርያም ደራሲ የእመቤታችን ሀሳብ እንደ እግዚአብሔር ሀሳብ ነው የሚለው መንፈስ ቅዱስ የሚያናግረውን እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ ሀሳብና ምስክርነት ነው ፡፡

 

ከዚህ ትምህርት የምንማረው ምንድር ነው ?


አስተምህሮአችን መሠረቱን በነቢያትና ሐዋርያት ላይ ያደረገ መሆኑን በቅዱሱ ተራራ ላይ የተገኙት ነቢያትና ሐዋርያት ምስክሮች ናቸው፡፡ እኛም በነቢያትና ሐዋያርት መሠረት ላይ ታንጻችኋል ተባለልን፡፡ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት የታመነ ምስክርነት አግኘተናል፡፡ አስቀድሞ ሐዋርያው «በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ/ዮሐ1፡1/ በማለት የሰጠንን ምስክርነት እንደገናም ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ ላይ አደረ በማለት ያመጣውን ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት በዚህ ዓለም ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደውን አምላክ ወልደ አምላክ በማመን የወንጌል ጋሻን ደፍተን የእምነት ወንጌልን ተጫምተን በማመን እንበረታለን እንጂ ባለማመን ምክንያት አንጠፋም፡፡ ክርስቲያኖች ምስጢረ መለኮቱን የገለጠበትን ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ የሆነውን የደብረ ታቦርን በዐል የምናከብረው በዚህ መንፈስ ነው ፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ለትውልድ ካስተላለፈችው ታላላቅ መንፈሳውያት እሴቶች መካከል በጌታችን  በእመቤታችንና በቅዱሳኑ ሥም በዓላትን ማክበር ነው ፡፡ ከእነዚህም በዓላት መካከል አንዱ የደብረ ታቦር በዐል ነው፡፡ በዓሉም በተለየ መልኩ ይከበራል፤ ዳቦ በመድፋት፤ ጠላ በመጥመቅ፤ በተለይም የአብነት ተማሪዎች ከሕዝቡ በመለመን ስሙን ይጠራሉ፡፡ ይህ ልንጠብቀው የሚገባን መንፈሳዊ እሴታችን ነው፡፡ ጌታችን የቅዱሳኑን መታሠቢያ በተመለከተ ሲናገር በደቀ መዝሙር ሥም ቀዝቃዛ ዉኃ ብቻ ያጠጣ ዋጋው አይጠፋበትም እንዳለ /ማቴ.10፥42/ በባለቤቱ ሥም የሚደረገውማ እንደምን አብዝቶ ዋጋ አያሰጥ፡፡ ለሚወዱኝ እስከሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ /ዘጸ.21፥6/ ስላለ በዓሉን በማክበር የበረከቱ ተሳታፊ መሆን ይገባል::

ወስብሃት ለእግዚአብሔር
Normal 0 false false false EN-US X-NONE X-NONE MicrosoftInternetExplorer4

Normal 0 false false false EN-US X-NONE X-NONE MicrosoftInternetExplorer4