ጰራቅሊጦስ (ለሕፃናት)

ሰኔ 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ

 

  • እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት/ መዝ 118፥24/

ይህች ታላቅ ዕለት  ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት ሴቶች የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡    እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ  በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡

አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኀይልን ከላይ ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ ልጆችዬ መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡

ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም  ሁኔታ ተከትሎ  ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡

በዓለ ሃምሳ የሚባለውን የአይሁድን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሀገራት የመጡ በጊዜው  የነበሩ ቁጥራቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ  ሰዎች የሐዋርያቱን ታላቅ የዝማሬና የእልልታ ድምፅ ሰሙ፡፡ ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል አንዱ የሆነው  ቅዱስ ጴጥሮስ የተሰበሰቡት ሁሉም እንዲሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፡፡ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቶ ከክፉ ሥራ ተመለሱ፣ ኀጢአትን አታድርጉ፣ በቅድስና ኑሩ፣ ወደ እኔም ተመለሱ ቢላችሁ፤ እናንተ ግን ምንም በደል ሳይኖርበት ገረፋችሁት፣ አንገላታችሁት፣ በመስቀል ላይም ሰቀላችሁት፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሔር ነውና ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ እርሱ ግን አሁንም ይቅር ባይ ነውና ከኀጢአታችሁ ተመለሱ ንስሐም ግቡ ፡፡” በማለት አስተማራቸው፡፡

የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያት በፊት የሚያውቁት አንድ ቋንቋ ብቻ ነበረ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ሰባ ሁለት ቋንቋን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ለሁሉም በየቋንቋቸው አስተማሯቸው፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር ከተመለከቱት ብዙዎች እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ወደ ሐዋርያትም ቀርበው “አባቶቻችን እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁና ምከሩን፡፡ እንደ እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆንና በቅድስና እንድንኖር ምን እናድርግ?”በማለት ጠየቁ፡ በዚያች ቀን ቁጥራቸው  ሦስት ሺ ያህል ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው  ክርስቲያን ለመሆን ቀረቡ፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፡፡ “እነሆ ሁላችሁም ንስሐ ግቡ፡፡ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምናችሁ ተጠመቁ፡፡” አላቸው በዚያው ዕለትም ሦስት ሺ ሰዎች ወደ ሐዋርያት በመቅረብ ኀጢአታቸውን ተናገሩ፤ ሐዋርያትም እግዚአብሔር ይፍታችሁ እያሉ ልጅነትን የሚያሰጣቸውን ጥምቀት አጠመቁዋቸው፡፡

ከዚያ ቀን ጀምሮም በየዓመቱ ይህችን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የምትባለውን በዓለ ጰራቅሊጦስን ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና ምሥጋና እናከብራታለን፡፡ እናንተም ልጆችዬ እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ተገኝታችሁ ቅዳሴ በማስቀደስ፣ መዝሙር በመዘመር እና በመጸለይ ይህችን ታላቅ በዓል ልታከብሯት ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን  አሜን፡፡