የዘመነ ጰራቅሊጦስ ምንባባት

ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፱ .

በዓለ ጰራቅሊጦስ ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የተሰጠበት፤ ብዙ ሺሕ ምእመናን የሥላሴን ልጅነት ያኙበት ዕለት በመኾኑ ‹የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን› ተብሎ ይጠራል፡፡ በዓሉ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን፣ በያዝነው ዓመትም ግንቦት ፳፯ ቀን ይዘከራል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ሰንበት (ከኀምሳኛው ቀን) ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰንበት ያለው ጊዜም (ስምንቱ ቀናት) ‹ዘመነ ጰራቅሊጦስ› ወይም ‹ሰሙነ ጰራቅሊጦስ› ይባላል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ስለ መውረዱና በምእመናን ላይ ስለ ማደሩ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ሰሙን በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር፣ የሚሰጠውም ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ መውረድ የሚመለከት ነው፡፡

በበዓለ ጰራቅሊስ ዕለት ‹ይትፌሣሕ› የሚለው የትንሣኤ መዝሙር በቤተ ክርስቲያን ይዘመራል፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችም በትንሣኤ ዕለት የተነበቡት ናቸው፡፡ ምንባባቱ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ፣ በማረጉና መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት በመላኩ፤ እንደዚሁም ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍስሶ የሰውን ልጅ ከዘለዓለም ሞት በማዳኑ የሰው ዘር ብቻ ሳይኾን የሰማይ መላእክት፣ የምድር ፍጥረታት ሳይቀሩ ሐሤት እንደሚያደርጉ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም በመንጻቷ የጌታችንን ትንሣኤ በደስታ እንደምታከብር የሚያስረዳ መልእክት አላቸው፡፡

ከበዓለ ጰራቅሊጦስ በኋላ ባሉት ሰንበታት (እሑዶች) የሚዘመሩ መዝሙራትም ትንሣኤን፣ ዕርገትን፣ የመንፈስ ቅዱስን መውረድ የሚያስረዱ ሲኾኑ፣ ምሥጢራቸውም ከሙታን ተለይቶ ለተነሣው፣ አዳምና ልጆቹን ከዲያብሎስ ተገዢነት እና ከሲኦል ባርነት ላወጣቸው ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ ያስተምራል፡፡ ከኀምሳኛው ቀን (ከበዓለ ጰራቅሊጦስ) ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ (በስምንተኛው ቀን) የሚዘመረው መዝሙር፡- ‹‹ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኵሉ በሐውርት …›› የሚል ሲኾን፣ ትርጕሙም መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ መውረዱንና በእርሱ ኃይል በዓለሙ ዅሉ ቋንቋዎች መናገራቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡

በዚህ ዕለት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፡- ኤፌ.፬፥፩-፲፯፤ ፩ኛዮሐ.፪፥፩-፲፰፤ ሐዋ.፪፥፩-፲፰፤ መዝ.፷፯፥፲፰ (ምስባክ)፤ ዮሐ.፲፬፥፩-፳፪ ሲኾኑ፣ የምንባባቱ ፍሬ ሐሳብም የሚከተለው ነው፤

የጳውሎስ መልእክት፡- እያንዳንዳችን መንፈስ ቅዱስ በገለጸልን መጠን የየራሳችን ልዩ ልዩ ጸጋ እንዳለን፤ የዮሐንስ መልእክት፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘለዓለም ሕያው እንደ ኾነ፤ የሐዋርያት ሥራ፡- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ እንደ ወረደና በዓለሙ ዅሉ ቋንቋዎች መናገር እንደቻሉ፤ መዝሙረ ዳዊት (ምስባኩ)፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልዩ ልዩ ጸጋን እንደሚሰጥ፤ የዮሐንስ ወንጌል፡- እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን እንደ ወላጅ አልባ እንደማይተወን ያስረዳሉ፡፡ ቅዳሴው ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን፣ ይህም ምሥጢረ ሥላሴን፣ የጌታችንን ሰው መኾን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና መንፈስ ቅዱስን መላኩን ይናገራል፡፡

ቅድስት በኾነች በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በዅላችን ላይ ይደር፤ እጽፍ ድርብም ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡