የኢትዮጵያውያን ይዞታ በሆነው በዴርሱልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱአምላክ አሜን!

ሁላችሁም እንደምታውቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም ካሏት ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዱና ዋናው በዴርሱልጣን የሚገኘው የመድኀኔዓለም፣ የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማት ናቸው፡፡ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያውያንበምድረ እስራኤል የነበራቸው ርስት ከሦስት ሽህ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ መገኛዋን ከዓባይ ምንጭ ጋር በማያያዝ ያለምንም ማሳሳት ከአርባ ጊዜ በላይ የተመዘገበች፤ በታሪክ፣ በእምነትና በማኅበራዊ ትሥሥር ከእስራኤል ጋር የጸና ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡
ከንግሥተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጉብኝት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ያለማቋረጥ በየዓመቱ በዓለ ፋሲካን ለማክበር፣ ዓመታዊ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ በርስት የተሰጣቸውን ይዞታ ለማስከበርና በንግድ ሥራዎች ይጓዙ እንደነበር በታሪክም በቅዱሳት መጻሕፍትም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡
ለዚህም በሐዲስ ኪዳን ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ምክንያት የሆነውና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 40 የተጻፈው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትሥሥርን ከማጠናከር ባሻገር በዴርሱልጣን እና በብዙ መካናት ቋሚ ይዞታን በማቋቋም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን መሥርተዋል፣ መንበረ ጵጵስናም አቋቁመዋል፡፡ ይህም ድርጊት ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የሕዝቦቿ ምልክትና መመኪያ እድትሆን አድርጓታል፡፡
ይሁን እንጅ ነባሩን ታሪካዊ እውነት ለመሻርና በማይገባ ሁኔታ ግብፃውያን በሌላቸው መብትና ሕጋዊ ባልሆነ የፈጠራ መረጃ ኢትዮጵያን ከኢየሩሳሌም የዴርሱልጣን ገዳም ባለቤትነቷን ለማሳጣት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሳይቀር መስዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ገዳማቸውን ጠብቀው እስከ አሁን ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ይዞታ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት በተጨማሪ ኢየሩሳሌምን ይገዙ በነበሩ መሪዎች የግብርና የመንግሥት አዋጅ መዛግብት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጉዘው ታሪክ በጻፉ ምሁራን፣ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻ እና በዓለም አቀፍ መዛግብት ሳይቀር የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡
ለምሳሌ ያህልም እንደነ አባ ጀሮም ያሉ የላቲን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደነ ከሊፋ ዑመርና ሳላሐዲን ባሉ ገዥዎች፣ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ ይዞታ ባላቸው በአርመንና በሶርያ ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በግሪክና በራሽያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት የተመሰከረ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ግብፃውያን በሚፈጥሩት ግፍና ኢሰብዓዊ ድርጊት በይዞታችን ያለውን ገዳም ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ አንኳ ሳንችል በመቅረታችን እየፈራረሰ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱ ስታሰማ በነበረው ተደጋጋሚ አቤቱታና የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ሕጋዊ የመብት ጥያቄ መሠረት የእስራኤል መንግሥት ገዳሙን ለማደስ ቃል በመግባቱ እና በዚሁ መሠረት መንግሥት ቃሉን በመጠበቅ በቅርቡ ጉዳት ከደረሰበት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተመቅደስ እድሳቱ በመጀመሩ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ በቅድስት ቤተክርስቲያን እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም በመግለጽ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡
የተጀመረው እድሳት በዴርሱልጣን የሚገኙ እና እጅግ በአስከፊ ጉዳት ላይ ያሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ይዞታዎች በማዳረስ ገዳሙ ጥንታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚደረግልን እናምናለን፡፡
አሁን እየተደረገ ያለውን ጥገና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል መንግሥት ምስጋናችሁን እንድታቀርቡልን የግብጽ ቤተክርስቲያንን መሠረት የለሽ ክስና ሁከት በመቃወም ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደ ፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚየ ግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ ማስረጃ መሠረት የሌለው የባለቤትንት ጥያቄ በማንሣት እየፈጠሩት ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያቆሙ፣
ዴርሱልጣን የኢትዮጵያ ገዳም ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ የነበረና ወደፊትም የኢትዮጵያ ሆኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፣ የኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በሁሉም ዘመን በቋሚነት ለመገኝታቸው ምስክር ስለሆነ ከዚህ የተሳሳተ ትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
በመጨረሻም የተጀመረው የእድሳት ሥራ ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የኢትዮጵያ የዴርሱልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠገኑልን፣
በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የሰው ልጅ ቅርስ ጥበቃ ለሚያሳስባቸው በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥሪያችንን እያስተላለፍን እድሳቱ ያለምንም እንቅፋትና ሁከት ከፍጻሜ እንዲደርስ ጸሎታችንና ምኞታችን መሆኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት
ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፡ ኢትዮጵያ