erope teklala 2006 01

የአውሮፓ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤ ተደረገ

 ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም.

በአውሮፓ ማእከል ሚድያና ቴክኖሎጂ ክፍል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከሐምሌ 11 እስከ 14 ቀን 2006 ዓ.ም. በኢጣልያ ዋና ማእከል ሮሜ ማእከል አካሄደ፡፡

erope teklala 2006 01በምእራብ አውሮፓ ልዩ ልዩ ሀገራት የሚገኙ ከሰማንያ በላይ አባላት፤ ከዋናው ማእከልና ከአሜሪካ ማእከል የተላኩ ልዑካን በተሳተፉበት ጉባኤ የማእከሉን የ2006 ዓ.ም. የአገልግሎት ሪፖርት ሰምቷል፤ የቀጣዩንም ዓመት ዕቅድና በጀት አጽድቋል፡፡ በተጨማሪም የማኅበሩ አገልግሎት በአኀጉሩ በሚፋጠንበት ዙሪያና በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በጉባኤው ላይ በሀገር ቤት እየተቸገሩ የሚገኙ ቅዱሳት መካናትንና አብነት ት/ቤቶችን ስለ መርዳት፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው ያሉ ኢትዮጵያውያን ሊደረግላቸው ስለሚገባው መንፈሳዊ እርዳታ እና አውሮፓ ያለው የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሚፋጠንበት ሁኔታ ላይ የማኅበሩ አባላት ሊኖራቸው ስለሚገባቸው ድርሻ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙባቸዋል፡፡ የጉባኤው ታዳሚዎች በቀረቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ የውሳኔ ሐሳቦችንም አሳልፈዋል፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረትም የአገልግሎት ዘመኑን የፈጸመውን የማእከሉን ሥራ አስፈጻሚ በአዲስ ተክቷል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ እንደተገለጠው የዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ በእጅጉ የተሳካ እና በማእከሉ የጠቅላላ ጉባኤ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ የተገኘበት ሲሆን ዝግጅቱም በአግባቡ የተከናወነ እንደ ነበር የማእከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን ሰሎሞን አስረስ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሰብሳቢው ገለጻ «ጉባኤው የማእከሉን አገልግሎት በሚያጠናክሩና አባላት በያሉበት ኾነው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ሊያደርጉት ስለሚገባው ተግባራዊ ሱታፌ እንዲወያዩ በማሰብ የተተለመ ነበር፡፡ አባለት በቀረቡላቸው የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት በማድረግ ያሳለለፏቸው ውሳኔዎች ተግባራዊ እንዲኾኑ ክትትል ይደረጋል» ብለዋል፡፡

በጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ በታቀደው መሠረት የጉባኤው ታዲሚዎች ሰኞ ሐምሌ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በጋራ የጥንታዊቷን የሮሜ ከተማ ጎብኝተዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በውጪው ዓለም አራት ማእከላትና ዐሥር ግንኙነት ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፤ የአውሮፓ ማእከል ከአራቱ ማእከላት አንዱ ነው፡፡ ቀጣዩ 15ኛ የማእከሉ ጉባኤ በፊንላንድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ እንዲከናወን ተወስኗል፡፡