06temeraki

የታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም መንፈሳዊ ት/ቤት ያሠለጠናቸውን ደቀመዛሙርት አስመረቀ

ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

06temerakiየዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ያሠለጠናቸውን ደቀመዛሙርት ሐምሌ 25 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ አስመረቀ፡፡

27 ደቀመዛሙርት በአብነት ትምህርት በዲፕሎማ የተመረቁ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ በብሉይ ኪዳን 5፤ በሐዲስ ኪዳን 8፤ በድጓ 1፤ በቅኔ 1፤ በቅዳሴ 11፤ በአቋቋም 1 የተመረቁ ናቸው፡፡ 10 በመደበኛ /በአዳሪነት/፤ ቀሪዎቹ 17 ደቀመዛሙርት ደግሞ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡ ከአብነት ትምህርት በተጨማሪ በሥነ መለኮት ትምህርት ቅዳሜ እና እሁድ ትምህርታቸውን የተከታተሉ 38 ደቀመዛሙርትም በሠርተፊኬት ተመርቀዋል፡፡

02temerakiበጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በተከናወነው የምረቃ መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የገዳሙ የበላይ ሓላፊዎች፤ የገዳሙ ሊቃውንት እና ደቀመዛሙርቱ በተገኙበት ቅዱስነታቸው በዲፕሎማ እና በሠርተፊኬት ለተመረቁ ደቀመዛሙርት የምሥክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ለተመራቂ ደቀመዛሙርት የምሥክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት አባታዊ መመሪያ “ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊት፤ ታሪካዊት እንደመሆኗ መጠን ሀገራችን ሰፊ፤ ሕዝባችንም ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ በተማራችሁት ትምህርት መሠረት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ያለውን የትምህርት ጥም የምትቀርፉ ባለአደራዎች ናችሁ፡፡ አደራዋን ጠብቃችሁ የጎደለውን አሟልታችሁ፤ የጠፉትን መልሳችሁ፤ ያሉትንም አጽንታችሁ ቸግሩን እንድታስወግዱ ያስፈልጋል€ ብለዋል፡፡

የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም የመምህራንና ቀሳውስት ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በ1925 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፤ 82 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በእነዚህ ዓመታትም በርካታ ደቀመዛሙርትን አፍርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 300 ደቀመዛሙርት ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ልብስና ቀለብ እየተሰጣቸው በመደበኛነት/አዳሪነት/ በመማር ላይ ያሉ 70 ደቀመዛሙርት ብቻ ናቸው፡፡ ከ70ዎቹ መደበኛ ደቀመዛሙርት መካከልም ሦስቱ መነኮሳይያት እናቶች እንደሆኑ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተገልጿል፡፡

05temerakiበዚሁ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ ገዳሙን በታማኝነት እና በቅንነት ለ50 ዓመታት ያገለገሉት የእድሜ ባለጸጋው አባት መጋቤ ሀብታት አባ እስጢፋኖስ ወልደ ኢየሱስ ከገዳሙ የተበረከተላቸውን ካባና የምሥክር ወረቀት ከቅዱስ ፓትርያርኩ እጅ ተቀብለዋል፡፡