01 katelo

የማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ቃጠሎ ደረሰበት

ነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

01 kateloበማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቃጠሎ እንደደረሰበት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ፍስሐ ገለጹ፡፡

መረጃው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ኃይሉ በማምረቻ ክፍሉ ተከስቶ የነበረውን ቃጠሎ በአካባቢው ሕዝብና በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ወረዳ የእሳት አደጋ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ክፍል አባላት ርብርብ ወደ ሌሎች ክፍሎች ሳይዛመት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቃጠሎው 12 የልብስ ስፌት ማሽኖች፤ 2 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ካውያዎች፤ 1 መዘምዘሚያ ማሽን፤ 1 ቁልፍ መትከያ ማሽን፤ በዝግጅት ላይ የነበሩና ያልተጠናቀቁ፤ ለስፌት የሚያገለግሉ የግሪክ ጨርቆች፤ የካህናት፤ የዘማርያንና የሰባኪያን አልባሳት፤ ለአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተዘጋጁ አልባሳት፤ የግሪክ ጣቃ ጨርቆች፤ የማምረቻ ክፍሉ በሮች፤ መስኮቶችና ኮርኒስን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ ግምታቸውንም ለጊዜው ማወቅ እንዳልተቻለ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

02kateloበዕለቱ ቀኑን ሙሉ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ምንም ዓይነት ሥራ አገልጋዮቹ እንዳለከናወኑ የገለጹት ዳይሬክተሩ ቃጠሎው የተከሰተው አገልጋዮቹ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የአደጋው መንስኤ እሰካሁን አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ አደጋው የተከሰተበት ምክንያት ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ በማካሔድ ላይ ስለሚገኝ ምርመራው እንደተተናቀቀ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

ወደፊት ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ኃይሉ ከኢንሹራንሽ ጋር በተያያዘም ወደፊት የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡ በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ላደረጉ አካላት ለአራዳ ክፍለ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ ለአካባቢው ምእመናንና ፖሊስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በንዋያተ ቅዱሳት ማምረቻ ውስጥ የአልባሳት፤ የመባ /ዕጣን፤ ጧፍ፤ ዘቢብ/ ዝግጅት፤ የተማሪዎች አልባሳት፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉና በእንጨት የሚዘጋጁ ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራዎች ይሉ፡፡