ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ፤ ከላይ(ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤(ቅ/ያሬድ)

 

 

ዲያቆን አቢይ ሙሉቀን

በቦታ የማይወሰነው አምላክ ሥጋን በመዋሕዱ ወረደ፤ ተወለደ፤ ተሰደደ፤ ተራበ፤ ተጠማ፣ ተሰቀለ እየተባለ ይነገርለታል፡፡ የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም መጥቶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በመወሰን ተወለደ፤ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ዞሮ አስተማረ፤ በመስቀል ላይ መከራን ተቀበለ፤ ሞተ፤ተቀበረ፤ተነሣ፤ ዐረገ፡፡ ዘለዓለማዊ አምላክ በመሆኑም በሁለም ስፍራ ይኖራል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዐቢይ ጾም እግዚአብሔር ሊመሰገንበት የሚገባውን ምስጋና በጀመረበት ክፍሉ “ሃሌ ሃሌ ሉያ ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፤ ከላይ (ከሰማይ) የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤” ብሏል፡፡ ነገር ግን  አላወቁም፤ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ ነውና” በማለት ጾመ ድጓ በሚባለው ድርሰት ይገልጸዋል፡፡

በዚህ ክፍለ ንባብ ሊቁ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም ዓለምን አሳልፎ የሚኖር እንደ ሆነ፣ እንዲሁ ስለ ልዕልናው በሰማያት የምትኖር ይባላልና ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት አለ፡፡ እርሱ ራሱ ለደቀ መዛሙርቱ የጸሎት ሥርዓት ሲያስተምራቸው “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር…” ብላችሁ ጸልዩ ብሎ የእርሱ አባትነት ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳልሆነና ከምድራዊ አባት የተለየ እንደሆነ በማስረዳት “በሰማያት የምትኖር በሉኝ” አለ፡፡ ሊቁም ይህን መሠረት አድርጎ “ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት” አለን፡፡

ከሰማይ የወረደው ቅድመ ዓለም አብ ያለ እናት በማይመረመር ጥበቡ የወለደው ድኅረ ዓለም ድንግል ማርያም ያለ አባት በማይመረመር ጥበብ የወለደችው ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነው፡፡ ሥጋዊ ልደት የሆነ እንደሆነ ከአባት ዘር ከእናት ደም ተከፍሎ ይወለዳል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ግን ከአብ ያለእናት፤ ከእናት ያለአባት ሲሆን  እንዲህ ነው ተብሎ አይመረመርም፡፡ በማይመረመር ልዩ ጥበብ ስለተወለደ ስለልዕልናው በሰማይ የምትኖር ይባላል፡፡ ዘበእንተ ዕበይከ ትትሜሰል በደመናት፤ ስለልዕልናህ በደመናት ትመሰላለህ እንዲል፤ ስለዚህ ከላይ ከሰማይ የወረደውን ማለት በልዕልና ያለውን የሚኖረውን አምላክ አይሁድ ሰቀሉት፡፡

የአይሁድን ግብዝነት የጌታን ሁሉን ቻይነትም ሲያስረዳን፤  “ምንም አላወቁም፤ የሰቀሉት በቃሉ የሚያድነውን የሁሉን ጌታ ነው” ይለናል፡፡ በማቴዎስም ወንጌል ፱፥፲፰ ታሪኩ ተመዝግቦ እንደምናገኘው የመቶ አለቃው ልጁ በታመመበት ጊዜ “እባክህ አድንልኝ” በማለት ተማጸነው፤ “እኔ መጥቼ አድንልኃለሁ” ብሎትም ነበር፡፡ የመቶ አለቃውም በበኩሉ ፍጹም እምነትን የተሞላ ስለነበር “ሁሉ ይቻልሃል፤ በቃልህ ብቻ ተናገር ልጄ ይድናል” ብሎ ስለሁሉን ቻይነቱ  በምሳሌ ተናገረ፡፡ ጌታም የመቶ አለቃውን እምነት አድንቆ እንደወደድክ ይደረግልህ አለው፤ ልጁም ተፈወሰ፡፡ ይህንም የሚያውቀው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እግዚአ ኵሉ ዘየሐዩ በቃሉ የሚያድን የሁሉ ጌታ” በማለት ገልጾታል፡፡

እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ መሰደዱን፣ መጠመቁን፣ በገዳመ ቆሮንቶስ መጾሙን በአጠቃላይ የነገረ ድኅነት ጉዞ ብላ ትገልጸዋለች፡፡ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ፵ መዓልት  ፵ ሌሊት ጾመ፡፡ የዐቢይ ጾም ሳምንት መግቢያ የሆነውን የመጀመሪያውን ሳምንት “ዘወረደ፤ ከሰማይ የወረደው አምላክ” በማለት ታስበዋለች፡፡

በዚህም ሳምንት ከሰማየ ሰማያት መውረዱን፣ ከድንግል ማርያም መወለዱን፣ ለዓለም ቤዛ ሲል መከራ መቀበሉን የምናስብበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ጾመ ሕርቃል በመባልም ይታወቃል፡፡ ጾመ ሕርቃል የተባለበትም ምክንያት ጌታችን የጾመው ፵ መዓልት ፵ ሌሊት ሲሆን እኛ ግን ፶፭  ቀናት እንጾማለን ፡፡  ይህም የሆነበት ምክንያት ጌታ ከጾመው ፵ ቀን በተጨማሪ ቅዳሜና እሁድ ለብቻው ተቆጥሮ አንድ ሳምንት፡፡ በመጨረሻ ያለው አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመሆኑ በመጀመሪያ ያለው አንድ ሳምንት ደግሞ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ሐዋርያት፡- ጌታ ፵  መዓልት ፵  ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ ነው የጾመው፤ እኛ ደግሞ እሑድና ቅዳሜ አንጾምም በማለት በመጀመሪያ ያለውን አንድ ሳምንት ጨምረው ጹመውታል፡፡

ሌላው በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፲፭ እንደምናገኘው በ፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም ፎቃ፣ በሮም ደግሞ ሕርቃል የሚባሉ ነገሥታት ነበሩ፡፡ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ፎቃ ጨካኝና ለክርስቲያኖች የማይራራ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ፤ ለሮሙ ንጉሥ “እባክህ ከእንዲህ ካለው ጨካኝ ንጉሥ አድነን፤ እኛ ላንተ እንገዛለን” በማለት ይልኩበታል፡፡ እርሱም ለጊዜው ቸል ብሏቸው ቆይቶ ነበር፡፡ከዕለታት አንድ ቀን “ግዙራን ይነሥእዋ ለመንግሥትከ፤ ክርስቲያኖች መንግሥትህን ይወርሷታል” የሚል ራእይ አይቶ፤ ይህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ ነው በማለት እንደገና የላካችሁብኝን ነገር አልረሳሁትም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያት ነፍስ ያጠፋ ዕድሜ ዘመኑን ይጹም ብለዋልና፤ ያን ብፈራ ነው እንጂ አላቸው፡፡ እነሱም የአንድ ሰው ዕድሜ ፸ ፹ ነው፤ እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን ብለውት ጠላታቸውን አጥፍቶላቸዋል፡፡ እነሱም ተከፋፍለው አንድ ሳምንት ጹመውታል፡፡

ስለዚህም በንጉሡ በሕርቃል ምክንያት ስለተጾመ ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ታሪክ ያላወቁት አንድ ጊዜ ብቻ ጾሙ፡፡ ታሪክ ያወቁት ደግሞ ቀድሞም ሐዋርያት ጹመውታል በማለት መጾም ቀጥለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህን መሠረት አድርጋ ከጌታ ጾም መግቢያ ላይ እንዲጾም ሥርዓት ሠርታለች፤ በመሆኑም ምእመናን ከጾሙ በረከት ያገኙ ዘንድ እንዲጾሙ ታስተምራለች፡፡ በዘመኑ ክርስቲያኖች ከጨካኙ ግዛት የዳኑበት ነው፡፡ ዛሬም ምእመናን ከጨካኙ ዲያብሎስ ፈተና፣ መከራና የጭካኔ አገዛዝ ነጻ የሚወጡበት ነውና ሊጾሙት ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማየ ሰማያት መውረድ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድና ወደዚህ ዓለም መምጣት የሚታሰብበት ስለሆነ “ዘወረደ” ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “እስመ ጾም ትፌውስ ቁስለ ነፍስ ወታጸምም ኵሎ ዘሥጋ ፍትወታተ፤ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች፤ የሥጋን ፍላጎትንም ታስታግሳለች፡፡” ጾመን፤ ጸልየን፤ የሚታገለንን የሥጋ ፍላጎት ለማስታገሥ፣ ነፍሳችንን ለማዳን፣  ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት፣ የኃጢአት ስርየት ለማግኘት ይህን ጾም በመጾም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እናገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር