ዘመነ አስተምሕሮ (አስተምህሮ) ካለፈው የቀጠለ

ኅዳር ቀን ፳፻፱ .

፬. መጻጕዕ

ከኅዳር ፳፯ እስከ ታኅሣሥ ፫ ያሉትን ሰባት ቀናት የሚያጠቃልለው አራተኛው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ‹‹መጻጕዕ›› ይባላል፡፡ የቃሉ ፍቺ በደዌ ዳኛ፣ በአልጋ ቍራኛ የተያዘ በሽተኛ ማለት ሲኾን ዕለቱ ‹‹መጻጕዕ›› ተብሎ መሰየሙም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውር ኾኖ የተወለደውን ጐበዝ ዓይን ያበራበትን ዕለት ለማስታዎስ ነው፡፡ የዕለቱ (እሑድ) መዝሙር ‹‹ይቤሉ እስራኤል ኢርኢነ ወኢሰማዕነ ዘዕውሩ ተወልደ ወተከሥተ አዕይንቲሁ በሰንበት ….፤ ዕውር ኾኖ ተወልዶ ዓይኖቹ በሰንበት የበሩለትን ሰው እስራኤል ‹አላየንም፤ አልሰማንም› አሉ ….›› የሚለው የእስራኤላውያንን በክርስቶስ ተአምር አለማመን የሚገልጸው የቅዱስ ያሬድ ትምህርት ነው፡፡

ምስባኩም ‹‹ደቂቀ ዕጓለ እመሕያው እስከ ማእዜኑ ታከብዱ ልበክሙ ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተሐሱ ሐሰተ አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ፤ እናንት የሰው ልጆች፣ እስከ መቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ? ከንቱ ነገርን ለምን ትወዳላችሁ? ሐሰትንም ለምን ትሻላችሁ? እግዚአብሔር በጻድቁ እንደ ተገለጠ ዕወቁ፤›› የሚለው እግዚአብሔር ለጻድቃኑ በሚያደርገው ድንቅ ሥራ ማመን እንደሚገባ የሚያስረዳው የዳዊት መዝሙር ነው /መዝ.፬፥፪-፫/፡፡ ወንጌሉ ደግሞ ዮሐ.፱፥፩ እስከ መጨረሻው ሲኾን ቅዳሴውም ቅዳሴ እግዚእ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት መድኀኒታችን የዕውሩን ዓይን ከማብራቱ ባሻገር ሕሙማነ ሥጋን በተአምራቱ፤ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርቱ ስለ ማዳኑ የሚያወሳ ቃለ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡

በዓቢይ ጾሙ መጻጉዕ መዝሙሩ፡- ‹‹አምላኩሰ ለአዳም››፤ ምስባኩ፡- ‹‹እግዚአብሔር ይረድኦ ወስተ አራተ ሕማሙ ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ዅሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡ እኔስ ‹አቤቱ ይቅር በለኝ፤ አንተን በድያለሁና ለነፍሴ አስተስርይላት› አልሁ›› /መዝ.፵፥፫-፬/፤ ወንጌሉ፡- ዮሐንስ ፭፥፩-፳፭፤ ቅዳሴው ተመሳሳይ (እግዚእ) ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የሚቀርበው ትምህርት ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ከአልጋው ጋር ተጣብቆ የኖረው በሽተኛ በክርስቶስ ኃይል ከደዌው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ መሔዱንና የክርስቶስን ገባሬ ተአምርነት የሚመለከት ነው፡፡

፭. ደብረ ዘይት

አምስተኛውና የመጨረሻው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ‹‹ደብረ ዘይት›› በመባል የሚታወቅ ሲኾን የሚያጠቃልለውም ከታኅሣሥ ፬ – ፮ ያሉትን ሦስት ቀናት ነው፡፡ በዕለቱ (እሑድ) ‹‹ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ለእለ በሰማይ ወለእለ በምድር …፤ እግዚአብሔር በሰማይም በምድርም ለሚኖሩ ፍጡራን ሰንበትን ለዕረፍት ሠራ (ፈጠረ) ….፤›› የሚለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይዘመራል፡፡ ‹‹ለነዳያኒሃኒ አጸግቦሙ እክለ ወለካህናቲሃኒ አለብሶሙ ሕይወተ ወጻድቃኒሃኒ ትፍሥሕተ ይትፌሥሑ፤ ባልቴቶቿን እጅግ እባርካቸዋለሁ፤ ድሆቿንም እኽልን አጠግባቸዋለሁ፡፡ ካህናቷንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለሁ፡፡ ጻድቃኖቿም እጅግ ደስ ይላቸዋል፤›› የሚለው የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ይሰበካል /መዝ.፻፴፩፥፲፭-፲፮/፡፡ የዕለቱ ወንጌል ሉቃስ ፲፪፥፴፪-፵፩ ሲኾን ቅዳሴው ደግሞ ቅዳሴ አትናቴዎስ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ሰንበት የዕረፍት ዕለት መኾኗን ከሚያስገነዝቡ ትምህርቶች በተጨማሪ የደጋግ አባቶችን መንፈሳዊ ታሪክ፣ የወረሱትን ሰማያዊ ሕይወትና ያገኙትን ዘለዓለማዊ ሐሤት መሠረት በማድረግ እኛ ምእመናንም እንደ አባቶቻችን ለመንግሥተ ሰማያት በሚያበቃ ክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን መኖር እንደሚገባን የሚያተጋ ቃለ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡

በዓቢይ ጾሙ ደብረ ዘይት መዝሙሩ፡- ‹‹እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት››፤ ምስባኩ፡- ‹‹እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ ወአምላክነሂ ኢያረምም እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፤ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡ አምላካችንም ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነዳል፡፡›› መዝ.፵፱፥፫/፤ ወንጌሉ፡- ማቴዎስ ፳፬፥፩-፴፮፤ ቅዳሴ፡- ተመሳሳይ (አትናቴዎስ) ነው፡፡ በሳምንቱ ጌታችን የምጽአቱን ነገር ለደቀ መዛሙርቱ በደብረ ዘይት ማስተማሩን፣ ዳግም ለፍርድ ሲመጣም ለዅሉም እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን የሚከፍለው መኾኑን የሚገልጹ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱት አራቱ የዘመነ አስተምሕሮ ሰንበታት (ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕና ደብረ ዘይት) ስያሜአቸው ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር ተመሳሳይ ቢኾንም የሚዘመሩት መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበኩ ምስባካትና የሚነበቡ ምንባባት እንደዚሁም የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ ትምህርቶቹ የተለያዩ ናቸው ስንል የሚነገረው ምሥጢርና ይዘት በወቅታዊ በዓላት ላይ የሚያተኵር መኾኑን ለመግለጽ ነው እንጂ በየትኛውም ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን የሚቀርበው ትምህርት አንዱ የእግዚአብሔር ቃል ብቻ ነው፡፡ ሳምንታቱን በዚህ መልክ የከፋፈለውም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ሲኾን ይህንንም ከመጽሐፈ ድጓው መመልከት ይቻላል /ድጓ ዘአስተምሕሮ/፡፡ የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ወቅቱ ሲደርስ የዓቢይ ጾም ሳምንታትን የተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እናሳውቃለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጮች፡-

  • መጽሐፈ ግጻዌ፡፡
  • ማኅቶተ ዘመን፣ መምህር በሙሉ አስፋው፤ ፳፻፩ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡፡
  • ጾምና ምጽዋት፣ ዲያቆን ቃኘው ወልዴ፤ ሐምሌ ፳፻፩ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡፡
  • ያሬድና ዜማው፣ ሊቀ ካህናት (ርእሰ ደብር) ጥዑመ ልሳን ካሣ፤ ፲፱፻፹፩ ዓ.ም፡፡
  • ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት፣ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ፡፡