ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ

ርእሰ ዐውደ ዓመት

ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ

የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት መስከረም አንድ ቀን ይከበራል፡፡ ስያሜው ቅዱስ ዮሐንስ በመባል ሲታወቅ ከመስከረም አንድ እስከ ስምንት ድረስ ያሉት ዕለታትንም ያካትታል፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው መዝሙር ክብረ ቅዱስ ዮሐንስንና ርእሰ ዐውደ ዓመትን የሚያወሳ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ያስተማረውን ትምህርትና ገድሉን የሚያመለክት ስብከት ይሰበካል፤ ትምህርቱም ይሰጣል፡፡ አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ስም የተሰየመበት ምክንያት፡-

፩. የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል መነሻ በመሆኑ

ቅዱስ ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹እነሆ÷ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤ ጥርጊያውንም አስተካክሉ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ የአዋጅ ነጋሪ ድምጽ፤ ዮሐንስም በምድረ በዳ ያጠምቅ ነበር፤ ኃጢአትንም ለማስተስረይ የንስሓ ጥምቀትን ይሰብክ ነበር፡፡ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፤ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ሁሉንም ያጠምቃቸው ነበር»  (ማር.፩፥፪-፭) ብሎ ጽፎልናል፡፡ የካህኑ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነስቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ›› እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት በምድረ በዳ እያስተማረና የንስሓ ጥምቀት እያጠመቀ በዘመነ ወንጌል መጀመሪያ ምዕራፍ ተገኝቷል፡፡ እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በነቢያት መጨረሻ በሐዋርያት መጀመሪያ ተገኝቶ ዘመነ ሐዲስን እንደሰበከና ከዘመነ ብሉይ ወደ ዘመነ ሐዲስ መሸጋገሪያ ጊዜ ላይ ስለነበረ ያለፈውን ዘመን የምንሸጋገርበት የዘመን መለወጫ ቀን የቅዱስ ዮሐንስ መታሰቢያ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

፪. መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ ነውና

በቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ላይ ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዱአቸው ወገን ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም›› (ማቴ.፲፩፥፲፩) ብሎ ጌታችን ስለ ዮሐንስ በተነገረለት መሠረት የጻድቃን የሰማዕታት ርእስ እንደመሆኑ አዲስ ዓመትም የበዓላት ሁሉ በኩር ርእስ ነውና በስሙ ተጠርቷል፡፡ እንደዚሁም ጌታ ባረገ በ፻፹ ዘመን በእስክንድርያ ፲፪ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የተሾመው ቅዱስ ድሜጥሮስ  ባሕረ ሐሳብን ሲደርስ ከዮሐንስ ጀምሮ ደርሶታል፤ ሲጨርስም ለኢየሩሳሌም፣ ለሮም፣ ለኤፌሶንና ለአንጾኪያ ሊቃነ ጳጳሳት ልኳል፡፡ በእስክንድርያ /ግብጽ/ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በዓላት የሚከበሩትና አጽዋማት የሚገቡት ከመስከረም አንድ ተነስቶ በመቁጠር ነው፡፡  በቤተ ክርስቲያናችን የበዓላቱና የአጽዋማቱ መደብ የሚታወቅበትና የዘመናቱ ሂደት ተቀምሮ የሚታወጅበት መስከረም አንድ በመሆኑ ርእሰ ዐውደ ዓመት ይባላል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም የዘመን መለወጫን አዲስ ዓመት በዓል አስመልክቶ እንደነገረን ‹‹ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፤›› የዓመት በዓል ራስ ዮሐንስ መጥቅዕና አበቅቴን የምትወልድ ነህ›› እየተባለ ይዘመርለታል፡፡