ወርኃ ክረምት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት (ዘመነ ክረምት)

ሐምሌ 4 ቀን 2004 ዓ.ም.

መብዐ ሥላሴ (ከጎላ ሚካኤል)

“ክረምት” የሚለው ቃል ከርመ፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርሃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ማለት ነው፡፡(ጥዑመ ልሳን ካሳ ያሬድና ዜማው 1981 ዓ.ም ገጽ 53)

 

በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

 

ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች፡፡ ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው  የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት፣ ወቅት ነው፡፡በመሆኑም በሃገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

 

ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወፆሩ ዘርኦሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡  በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.125)

 

እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሪ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቢ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡ “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡” (ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ፤ ብርድና ሙቀቱ፤ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

 

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡ አራት ወቅቶች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ምሳሌ ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ ምንባባትን በማዘጋጀት፣ ከሕብረተሰቡ ሥራና አኗኗር ጋር በማያያዝ እንዲሁም ከወቅታዊው አየር ጠባይ ጋር በማስማማት እያንዳንዳቸውን በ91 ቀን ከ15 ኬክሮስ (አንድ አራተኛ) በመክፈል ለወቅቶቹም ሥያሜ፣ ምሳሌ፣ ትርጉሙንና ምሥጢሩን በማዘጋጀት ትገለገልባቸዋለች፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን የከፈለችባቸው ወቅቶች፡-

  1. ዘመነ መጸው (መከር) ከመስከረም 26 ቀን እስከ ታኅሣሥ 25
  2. ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ከታኅሣሥ 26 ቀን እስከ መጋቢት 25
  3. ዘመነ ጸደይ (በልግ) ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25
  4. ዘመነ ክረምት ሰኔ 26ቀን እስከ መስከረም 25 ናቸው፡፡

 

ወቅቶችን እንዲህ በመከፋፈል በወቅቱ ከሚታየው የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲመረምሩ ለንስሐ እንዲበቁ አጥብቃ ታስተምራለች፡፡ ያለንበት ወቅትም ክረምት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት የሚሰጠውን ትምህርት በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

 

ወርኃ ክረምት ከላይ በጥቂቱ እንደተመለከትነው በሦስት ንዑሳን ክፍላት ይከፈላሉ፡፡ እነኚህም፡-

1.    መነሻ ክረምት፡- የዝግጅት ወቅት

ሀ. ከበአተ ክረምት እስከ ሐምሌ ቂርቆስ(ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 19) ያለው ወቅት ነው፡፡  በዚህ ወቅት ዝናምና ደመና ምድርን የሚያለመልሙበት፣ ዘር የሚዘራበት ፣ የተዘራው የሚበቅልበት በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርዕን ደመናን ዝናምን የሚያዘክሩ  ምንባባት ይነበባሉ፣ መዝሙራትም ይዘመራሉ፡፡

 

ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ድምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌስሁ ነድያን፣ ይጸግቡ ርሁባን፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረሀብተኞችም ይጠግባሉ፡፡” በማለት በድጓው የዘመረው ይገኝበታል፡፡

 

ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፡፡ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እምሕያው፡፡ ማለትም፡- ሰማዮችን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃልና፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም” በማለት የዘመረው ይሰበካል፡፡

 

በምንባበት በኩል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከት ታገኛለች፤ እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው፡፡” በማለት ያስተማረው ትምህርት ይነበባል፡፡(ዕብ.6፥7-8)

 

ለ. ከሐምሌ ቂርቆስ እስከ ማኅበር (ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 29) መባርቅት የሚባርቁበት በባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ምድር ጠል የምትጠግብበት ወቅት ነው፡፡ “ደመናት ድምፁን ሰጡ፣ ፍላጾችህም ወጡ የነጎድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበር፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ” ሲል ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ይሰበካል፡፡(መዝ.76፥18) ደመኖች ታይተው ባርቀው የነጎድጓድ ድምፅ እንዲሰማ ጌታችን ከዓለም ጠርቶ አስተምሮ ወንጌለ መንግሥት ተናግረው በኃጢአት ጨለማ የተያዘውን ዓለም በትምህርታቸው እንዲያበሩ የተላኩ የ72ቱ አርድዕት ዝክረ ነገር ይታወሳል፡፡(ሉቃ.10፥17-25)

 

መዝሙሩ፡- “ምድርኒ ርዕየቶ ወአኰተቶ ባህርኒ ሰገደት ሎቱ፤ ምድር አየችው አመሰገነችውም ባሕርም ሰገደችለት” /ድጓ/

“እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ በሰማይም በምድርም በባህርም በጥልቅም ቦታ ሁሉ”/መዝ.134፥6-7/

“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልፅግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፣ በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳቱንም ከመዛግብቱ ያወጣል ” (መዝ.64፥9) በማለት እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑንና የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

ወንጌል፡- መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች (ማቴ.13፥47)

ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፤ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው፡፡(ማቴ.14፥26-27)

2.    ማዕከለ ክረምት

ሀ. ከማኅበር እስከ አብርሃም (ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 29)

ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ነው፡፡ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር ትጀምራለች፡፡ “ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” እንዲሉ በክረምት ዝናሙን ተደብቀው የነበሩ አእዋፍ ከበአታቸው ይወጣሉ፤ ጥበበኛው ሰሎሞን አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማ ጊዜ ደረሰ፤ የቀረርቶውም ቃል በምድራችን ተሰማ (መኃ.2፥12) ሲል እነደተናገረው የአእዋፍ የምስጋና ድምፅ ይሰማል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም “የሁሉም ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፣ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፣ አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” እያለች እንደ ቅዱስ ዳዊት ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘለዓለም የሆነውን የሰማይ አምላክ ታመስግናለች(መዝ.144፥15-20፣ መዝ 135፥25-26)

 

ለ. ዕጉለ ቋዓት፥ ደስያት

ይህ ክፍለ ክረምት ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ ያሉት 17 ዕለታት የሚጠሩበት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ክረምት ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ሲሆን ወቅቱም ዕጓለ ቋዓት ደስያት ዐይነ ኩሉ ይባላል፡፡ ዕጓለ ቋዓት የሚለው ቃል ቁራን ሲያመለክት፣ ቁራ ሲወለድ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወለዳል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሻሉ፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እየደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ “ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘብዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? ” (ኢዮ.38፥41) ተብሎ እንደ ተገለጠው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር ግን በክንፍ የሚበሩ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅርሔ ለተመላው አምላክነቱ ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ዕጓለ ቋዓት በማለት ታስታውሰዋለች፡፡

 

ደስያት ማለት በውኃ የተከበቡ ቦታዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጥቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ ያዩ በውስጥ በውጭ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ በደሴት (በቤተ ክርስቲያን) የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

 

በዚህ ወቅት፡- ክፍለ ክረምቱ እንደተገባደደ፥ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዞች ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችን አሞራዎች ድምፃቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡

 

በተጨማሪም ከነሐሴ 27-29 ያለው ጊዜን “ሞተ አበው” በመባል ይታወቃል፡፡ ከ22ቱ አርዕስተ አበው የአብርሃም ይስሐቅና ያዕቆብ ቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ ቅዱስ መጽሐፋችንም “አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሰዋ ወጣ፤ እግዚአብሔር ቤዛ አድርጎ ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ አወረደለት” በማለት የአብርሃምን ታዛዥነት የይስሐቅን ቤዛነት ያወሳል፡፡ የተቀበሉትም ቃል ኪዳን “ወተዘከረ ሣህሎ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም ወመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እም ሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍስ ርኅብት” በማለት ይዘመራል፡፡

 

3.    ፀዓተ ክረምት (ዘመን መለወጫ)

ሀ. ከአብርሃም እስከ ዮሐንስ

ይህ ወቅት የዓመቱ መንገደኛ ነው፣ በሐምሌና በነሐሴ ደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ ፍንትው ብላ መውጫዋ የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ ጎህ ጽባህ፣ መዓልተ ነግህ፣ ብርሃን ተብሎ የጠራል፡፡ የክረምቱ ጭፍን ጨለማ ሊያከትም ብርሃን ሊበራ የተቃረበበት መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ይበሰራል፡፡ በሊቀ መልእክት ቅዱስ ሩፋኤል እጅ የጦቢያን ዓይን እንዳበራ ፤ የምእመናን ዓይነ ልቡና እግዚአብሔር እንዲያበራ ይጸለያል፡፡

 

ከዚሁ ጋር የክረምቱ ደመና ዝናብና ቅዝቃዜ ውርጭ ጭቃው ከብዶባቸው የዘመን መለወጫን፣ የፀሐይ መውጫን ቀን በጉጉት ለሚጠባበቁ ምእመናን ልጆቿ ቅድስት ቤተ ከርስቲያን፡- “ነፍሳችሁን ተመልከቱ፥ ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ” ስትል ለበለጠ መንፈሳዊ ትጋት ታነቃቃቸዋለች፡፡ ክረምት ሲያልፍ የሰማዩ ዝናም የምድሩ ጭቃ ሊቀር እንሆ ሁሉ በዚህች ዓለም መከራ ተናዝዘው ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስቶስ በክብር የሚገለጥበት ዓለም የምታልፍበት ዕለት ባላሰቧት ጊዜ እንደምትመጣ እንዲገነዘቡ ነገረ ምጽአቱን እንዲያሰቡ “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ!” እያለች በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንዲያብቡ “እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል… አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል” (መዝ.49፥2-3) እያለች ትመሰክራለች፡፡

 

ለ. ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ (መስከረም 8)

ዘመን መለወጫ አዲስ ተስፋ በምእመናን ልብ የሚለመለምበት ጊዜ ነው፡፡ የተተነበየው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ተፈጸመ፤ ከዘመነ ፍዳ ወደ ዘመነ ምሕረት የምትሸጋገሩበት ጊዜ ደረሰ፤ እያለ ያወጀው የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ዜና ሕይወት ይነገራል፡፡ “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ፣ እውነት ከምድር በቀለች” (መዝ.88፥10-11) በማለት ስለ እውነት ሊመሰክር የወጣውን የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወት በማውሳት ቤተ ክርስቲያን ልጇቿ እንደርሱ እውነተኞች እንዲሆኑ አርአያነቱን እንዲከተሉ ለእውነት እንዲተጉ ታስተምራለች፡፡ ሰማዩ፣ ውኃው የሚጠራበት ወቅት በመሆኑ በሥነ ፍጥረት በማመለከት ልጆቿን ከብልየት እንዲታደሱ፣ በመንፈስ እንዲጎለምሱ፣ከርኩሰት ከጣኦት አምልኮ፣ከቂም በቀል እንዲጠሩ እንዲነፁ “የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እያለች በሐዋርያው ቃል ታስተምረናለች፡፡(1ኛ ጴጥ.4፥3) ከዚሁ ጋር፡-በርኩሰት የተመላውን ሕይወታችንን ካለፈው ዘመን ጋር አሳልፈን የምድር አበቦች በጊዜው እነደሚያብቡ እኛም በምግባር በሃይማኖት እንድናብብ ትመክረናለች፡፡

 

ሐ. ከዘካርያስ እስከ ማግስተ ሕንፀት

ይህ ንዑስ ወቅት ዘመነ ፍሬ በመባል ይታወቃል፡፡ ከመስከረም 9 እስከ 16 ያሉትን ዕለታት በተለይ በሰኔና በሐምሌ የተዘራው ዘር ለፍሬ መብቃቱን የሚያስብበትና እንደ ቅዱስ ዳዊት “ምድር ፍሬዋን ሰጠች እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል”(መዝ.66፥6) ተብሎ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሳምንት ነው፡፡ ፍሬውም ከቁር ከበረዶና ከትል ተርፎ ለጎተራ እንዲበቃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴዋ “በእንተ ፍሬ ምድር ናስተበቊእ ከመ እግዚአብሔር ይሁብ ፍሬሃ ለምድር፣ ለዘርና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለምድር ፍሬ እንማልዳለን” በማለት አምላኳን ትማጸናለች፡፡

 

ልጇቿ ምእመናንም “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ. 24፥20) ሲል መድኃኔዓለም እንዳስተመረው የሃይማኖት ፍሬ ምግባርን፣ ቱሩፋትን ሳይሠሩ በልምላሜ (በሃይማኖት) ብቻ ሳሉ እንዳይጠሩ ለንስሐ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ በማስተማር ነገረ ምጽአቱን በማዘከር “ድልዋኒክሙ ንበሩ፣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ” በማለት ታስተምራለች፡፡

 

ስለዚህ ይህ ክፍለ ክረምት የዕለተ ምጽአት ምሳሌ ነው፡፡ ወቅቱ የአዝመራ ወቅት ነው፡፡ፍሬ መለያ እንደሆነ ሁሉ የሰው ሥጋ ከተቀበረና ትቢያ ከሆነ በኋላ ተነስቶ በዕለተ ምጽአት በጽድቅና በኃጢአት ይለያልና፡፡(ማቴ.25፥32)

 

መ. ከመስከረም እስከ ፍጻሜ ክረምት(መስከረም 25)

ዘመነ መስቀል ከመስከረም 17 እስከ 25 ያሉት ዘጠኝ ቀናት የሚጠሩበት ሌላው መጠሪያቸው ነው፡፡ ይህ ክፍለ ክረምት ነገረ መስቀሉ የሚነገርበት ነው፡፡ በቅናት ተነሳስተው አይሁድ የቀበሩት የጌታችን መስቀል በንግሥት እሌኒ ጥረትና በፈቃደ እግዚአብሔር ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ተቆፍሮ የወጣበት መታሰቢያ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ መስቀልን ክብር የሚመለከት ትምህርት ይሰጣል፤ ክቡር ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክት ሰጠሃቸው” (መዝ.59፥4) በማለት የተናገረው ይሰበካል፡፡ ጊዜው የክርስቶስና የመስቀል ጠላቶች ያፈሩበት የመስቀሉ ብርሃን ለዓለም ያበራበት በመሆኑ የመስቀሉ እንቅፋት ተወግዷልና ምእመናን በዚህ ይደሰታሉ(ቆላ.2፥14-15) በቅዱስ መስቀሉ ተቀጥቅጦ ኃይሉን ያጣው ዲያብሎስን በትእምርተ መስቀል ከእነርሱ ያርቁታል፡፡ በቅዱስ መስቀል የተደረገላቸውን የእግዚአብሔር ቸርነት እያስታወሱ በአደባባይ በዝማሬ መንፈሳዊ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡

 

እንግዲህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ውስጥ ላለነው ራሳችንን ከጊዜው ጋር እንድናነጻጽር ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት አዘጋጅታ ልጆቿን ለሰማያዊ መንግሥት ዝግጁ እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ ተፈጥሮን አይተን አገናዝበን የምንማር፣ ለንስሐ የተዘጋጀን ስንቶቻችን ነን? “ቁም! የእግዚአብሔርን ተአምራት አስብም!” እንዳለ (ኢዮ.37፥14) ያለንበትን ሕይወት አስበን ለንስሐ እንበቃ ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት አይለየን፤