ወርኀ ጳጕሜን አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት

ጳጕሜን ፬ ቀን ፳፻፰ .

የኢትዮጵያን የዘመን አቈጣጠር ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ‹ጳጕሜን› የምትባል 13ኛ ወር ስላለችን ነው፡፡ የቤት ኪራይና የወር ደመወዝ የማንከፍልባትና የማንቀበልባት፤ መብራትና ውኃ ግን ከነሐሴ ወር ጋር ጨምረው የሚያስከፍሉባት፤ ሲሻት አምስት፣ ሲያስፈልጋት ስድስት፣ ስትፈልግ ደግሞ ሰባት የምትኾን ወር ናት፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ የኢትዮጵያ ወሮች መካከል ወርኀ ጳጕሜን በብዙ መንገድ የተለየች ናት፡፡

በአንድ በኩል በጣም ትንሿ ወር ናት፡፡ ሲቀጥልም ወርኃዊ በዓላት የማይውሉባት ወር ናት፡፡ ደግሞም ከሌሎች ወሮች በተለየ የቀኖቿ መጠን የሚቀያየሩ ብቸኛ ወር ናት፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ወሮች በተለየም ስሟ ኢትዮጵያዊ ያልኾነ ወር ናት፡፡ በሁለት ዘመናት መካከል እንደ መሸጋገሪያ የምትታይ ወርም ናት፡፡

‹ጳጕሜ› ማለት በግሪክ ቋንቋ ‹ጭማሪ› ማለት ሲኾን ዓመቱ በሠላሳ ቀናት ሲከፈል የሚተርፉት ዕለታት ተሰባስበው የሚያስገኟት ተጨማሪ ወር ናት፡፡ ወይም በየዕለቱ በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር መካከል የሚፈጠሩት ልዩነቶች ተሰባስበው የተከማቹባት ወር ትባላለች፡፡

ዓመቱ በዐውደ ፀሐይ ሲለካ 365 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ሲኾን፣ በጨረቃ ሲለካ ደግሞ 354 ቀናት ከ22 ኬክሮስ፣ ከ1 ካልዒት፣ ከ36 ሣልሲት፣ ከ52 ራብዒት፣ ከ48 ኀምሲት ነው፡፡ በሁለቱ አቈጣጠር መካከል (በፀሐይና በጨረቃ) በዓመት ውስጥ ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ7 ኬክሮስ ይኾናል፡፡

በዘመን አቈጣጠራችን ውስጥ ከዕለት በታች የምንቈጥርባቸው ስድስት መለኪያዎች አሉ፡፡ እነዚህም ኬክሮስ፣ ካልዒት፣ ሣልሲት፣ ራብዒት፣ ኀምሲትና ሳድሲት ናቸው፡፡ 60 ሳድሲት 1 ኀምሲት፣ 60 ኀምሲት 1 ራብዒት፣ 60 ራብዒት 1 ሣልሲት፣ 60 ሣልሲት 1 ካልዒት፣ 60 ካልዒት ደግሞ 1 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ 60 ኬክሮስ ደግሞ 1 ዕለት፤ 1 ኬክሮስ 24 ደቂቃ ነው፡፡ ወርኀ ጳጕሜንን ለማግኘት የሚረዳንም የየዕለቱን ልዩነታቸውን መመልከቱ ነው፡፡

በየዕለቱ በጨረቃና በፀሐይ መካከል 1 ኬክሮስ ከ52 ካልዒት ከ31 ሣልሲት ይኾናል፡፡ ይህም ማለት 5 ሰዓት ከ48 ደቂቃ ከ46 ካልዒት (ሴኮንድ?) ነው፤ ይህ ልዩነት በአንድ ወር ምን ያህል እንደሚደርስ ለማወቅ በ30 ብናበዛው 30 ኬክሮስ ከ1560 ካልዒት፣ ከ930 ሣልሲት ይኾናል፡፡ የዓመቱን ለማግኘት ደግሞ በ12 ብናበዛው 360 ኬክሮስ ከ18720 ካልዒት፣ ከ11160 ሣልሲት ይመጣል፡፡

ቀደም ብለን 60 ኬክሮስ አንድ ዕለት ይኾናል ባልነው መሠረት 360 ኬክሮስ ለ60 ሲካፈል 6 ዕለታትን ይሰጠናል፡፡ 18720 ካልዒትን በስድሳ በማካፈል 312 ኬክሮስን እናገኛለን፡፡ ያም ማለት ትርፉን 12 ኬክሮስ ትተን 300ውን ኬክሮስ ለ60 በማካፈል 5 ዕለት እናገኛለን ማለት  ነው፡፡ ይኼም 5 ዕለት ከ12 ኬክሮስ ይኾናል፡፡ 11160 ሣልሲትን ለ60 ብናካፍለው 186 ካልዒት ወይም ደግሞ 3 ኬክሮስና 6 ካልዒት ይኾናል ማለት ነው፡፡

ከላይ ኬክሮስን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነው 6 ዕለት ሕጸጽ ይባላል፡፡ ፀሐይና ጨረቃን እኩል መስከረም አንድ ላይ ዓመቱን ብናስጀምራቸው ፀሐይ የወሯ መጠን ምንጊዜም 30 ሲሆን ጨረቃ ግን በአንደኛው ወር 29 በሌላኛው ወር ደግሞ 30 ስለምትኾን ዓመቱ እኩል አያልቅም፤ የጨረቃ ዓመት የሚያልቀው ነሐሴ 24 ቀን ነው፡፡ ይህም ማለት ጨረቃ በሁለት ወር አንድ ጕድለት ታመጣለች ማለት ነው፡፡

ይህንን ነው ሊቃውንቱ ሕጸጽ (ጕድለት) ያሉት፡፡ በዚህም መሠረት ከላይ ኬክሮሱን በዓመቱ ቀናት አባዝተን ያገኘነውን 6 ዕለት ለጨረቃ ሕጸጽ ስንሰጠው የመስከረም /ጥቅምት 1፣ የጥቅምት /ኅዳር 2፣ የጥር /የካቲት 3፣ የመጋቢት /ሚያዝያ 4፣ የግንቦት /ሰኔ 5፣ የሐምሌ /ነሐሴ 6 ኾነው ተካፍለው ያልቃሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በጨረቃና በፀሐይ ዑደት መካከል በዓመት ያለው ልዩነት 11 ቀናት ከ15 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት ይኾናል፡፡ ስድስቱን ዕለታት ጨረቃ ለምታጋድልበት ሕጸጽ ብንሰጠው ቀሪ 5 ዕለት ይኖረናል፡፡ ወርኀ ጳጕሜን ማለት እነዚህ 5 ቀናት ናቸው፡፡

አሁን የዐሥራ አንዱን ዕለታት ከፈጸምን ሽርፍራፊዎቹን (15 ኬክሮስና 6 ካልዒት) እንመልከት፤
ከላይ እንደ ተመለከትነው በፀሐይና ጨረቃ ዓመታት መካከል የተፈጠሩትን 11 ቀናት ስድስቱ ለሕጸጽ ማሟያ ሲገቡ የቀሩት 5 ዕለታት ናቸው ጳጕሜን የምትባለውን ወር ያስገኟት፡፡

በጎርጎርዮሳውያኑ አቈጣጠር እነዚህ 5ቱ ዕለታት በጃንዋሪ፣ ማርች፣ ሜይ፣ ጁላይና ኦገስት ላይ ስለ ተጨመሩ ወሮቹ 31 ሊኾኑ ችለዋል፡፡ ይህንን የከፈለው በ46 ቅልክ የነበረው ዩልየስ ቄሣር ነው፡፡ ለአራቱ ወሮች 30 ቀን፣ ለአንዱ 28/29 (በየአራት ዓመቱ)፣ ለቀሩት ሰባት ወሮች ደግሞ 31 ቀን ሰጥቷቸዋል፤ ለአምስቱ ወሮች 31 ያደረጋቸው ከጳጕሜን ወስዶ ሲኾን ለሁለቱ ወሮች አንዳንድ ቀን የጨመረላቸው ደግሞ ከፌቡርዋሪ 2 ቀናት ወስዶ ወሩን 28 በማድረግ ነው፡፡

ከእንግዲህ የሚተርፉት ከላይ የየዕለቱን ልዩነት በዓመት ስናባዛ የቀሩት 15 ኬክሮስና 6 ካልዒት ናቸው፡፡ ሁለቱን ከላይ ያየናቸውን ስንደምራቸው (12 ኬክሮስ + 3 ኬክሮስ ከ6 ካልዒት) 15 ኬክሮስ ከ 6 ካልዒት ይመጣሉ፡፡ 1 ዕለት 60 ኬክሮስ በመኾኑ 1 ዕለትን (60 ኬክሮስን) ለማግኘት ከላይ ያገኘነውን 15 ኬክሮስ በ4 ማባዛት ይኖርብናል፡፡

በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን የምትኾነውም እነዚህ በየዓመቱ የተሰባሰቡ 15 ኬክሮሶች አንድ ላይ መጥተው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንድ ዕለት ስለሚኾኑ ነው፡፡ እርሷም ሠግር (leap year) ትባላለች፡፡ ጎርጎርዮሳውያኑ ይህቺን ሠግር በፌቡርዋሪ ወር ላይ ጨምረው ወሩን በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ 29 ቀን ያደርጉታል፡፡

15ቱ ኬክሮስ በአራት ዓመት ተደምረው አንድ ዕለት መጡና በአራት ዓመት አንድ ጳጕሜን ስድስት ቀን እንድትኾን አድርገዋታል፡፡ የቀረችው 6 ካልዒትስ የት ትግባ? ከተባለ ካልዒት አንዲት ዕለት ትኾን ዘንድ 3600 ካልዒት ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን ያህል ካልዒት ለማግኘት 600 ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ ለዚህ ነው ጳጕሜን በየስድስት መቶ ዓመታት ሰባት የምትኾነው፡፡

ጳጕሜን 5 ቀን በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዘንድ ‹ዕለተ ምርያ› ወይም ‹የተመረጠች ቀን› ትባላለች፡፡ ሊቃውንቱ የጌታችንን ልደት ሲያሰሉባት የቆየችው ዕለት በመኾኗ ነው ይህንን ስያሜ ያገኘችው፡፡ የጌታችንን ልደት ቀን የምትወስነው የጳጕሜን 5ኛዋ ቀን ናት፡፡ በዓለ ልደት የሚውለውም ጳጕሜን 5 በዋለበት ቀን ነው፡፡

ለምሳሌ ዘንድሮ (በ2008 ዓ.ም) ጳጕሜን 5 ቀን ቅዳሜ ነው የምትውለው፤ ስለዚህም በ2009 ዓ.ም በዓለ ልደት የሚውለው ቅዳሜ ነው ማለት ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ጳጕሜን 6 ቀን ስትኾን ልደት በ28 የሚከበረው በዓለ ልደት ጳጕሜን 5 ቀንን (ዕለተ ምርያን) ስለማይለቅ ነው፡፡

በዘመነ ዮሐንስ ግን ስድስተኛዋ የጳጕሜን ቀን በዓለ ልደትን በአንድ ቀን ዝቅ ብሎ እንዲከበር ስለምታደርገው ልደትን ታኅሣሥ 28 ቀን እናከብራለን፡፡ ታድያ ምነው ጥምቀት፣ ግዝረትና ሌሎችም በዓላት አይለወጡም? ቢሉ ሊቃውንቱ የሚሰጡት ምላሽ ‹‹ትውልድ ሱባዔ እየቈጠረ በተስፋ የጠበቃት ዕለተ ልደትን ስለ ኾነ ነው፤ ሌሎቹ በዓላትም የመጡት በልደቱ ምክንያት ነው›› የሚል ነው፡፡

በጎርጎርዮሳውያንም ቢኾን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዓለ ልደት ዝቅ ብሎ ይከበራል፡፡ የእነርሱ የማይታወቀው ጭማሪዋ ፌብርዋሪ ላይ ስለ ኾነች ነው፡፡ ያ ደግሞ አዲሱን ዓመት ካከበሩ በኋላ ስለሚመጣ ነው፡፡ የእኛ ግን የምትወድቀው ጳጕሜን መጨረሻ ላይ በመኾኗና ከአዲስ ዓመት በፊት ስለምትጨመር ቍጥሯ ጐልቶ ይታወቃል፡፡

እንግዲህ ጳጕሜን የምትባለው አስገራሚዋና ትንሿ ወራችን እንዲህ በስሌት የተሞላች፣ በሦስት ዓመታት አምስት ቀን ኾና ቆይታ በአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ስድስት፣ በየስድስት መቶ ዓመት ደግሞ ሰባት ቀን የምትኾን ወር ናት፡፡ እንደዚሁም ታላላቆቹ ወሮች ምንም ሳይፈጥሩ የልደትን ቀን የምትወስን፣ የዓመቱን ሠግር የምታመጣ፣ ታሪከኛ ወር ናት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡- የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገጽ፣ ፳፻፮ ዓ.ም (ከመጠነኛ ማስተካከያ ጋር)፡፡