“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን”

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

 “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይዕዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሠላም፤ ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ዲያብሎስን አሰረው፤ አዳምን ነጻ አወጣው፡፡ ሰላም! ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ኾነ፡፡”

ይህ ኃይለ ቃል የትንሣኤው የምሥራች ለምእመናን የሚታወቅበት ኃይለ ቃል ነው፡፡ የሚቀድስ ካህን፣ ሰባኪ በዘመነ ትንሣኤ ከስብከቱ አስቀድሞ በዚህ ኃይለ ቃል የክርስቶስን መነሣት ያውጃል፡፡ የሚቀድሰው ካህንም በኪዳን ጊዜ ሕዝቡን ከመባረኩ አስቀድሞ ይህንኑ ቃል ይናገራል ሰላምታ የሚቀባበሉ ምእመናንም ሰላምታ ከመስጠት አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን! አደረሳችሁ!

የክርስቶስ ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ከጥንት በነቢያት የተነገረ፤ በኋላም እርሱ ክርስቶስ ከመሞቱ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረው፤ ደግሞም በመነሣት የገለጠው፤ ሐዋርያትም በግልጥ ለዓለም የመሰከሩት ምሥጢር ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በትንቢተ ነቢያት

  • “እኔ ተኛሁ፤ አንቀላፋሁም፡፡ እግዚአብሔር አስነሥቶኛልና ተነሣሁ፤” (መዝ. ፫፥፭)፡፡
  • “እግዚአብሔር ይላል፤ ‹አሁን እነሣለሁ፤ መድኀኒት አደርጋለሁ፤ በእርሱም እገልጣለሁ፤›” (መዝ. ፲፩፥፭)፡፡
  • “እግዚአብሔር ይነሣል፤ ጠላቶቹም ይበተናሉ፡፡ … እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፡፡ ጠላቶቹንም በኋላው መታ፤” (መዝ. ፸፯፥፷፭)፡፡

ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ የክርስቶስን ከሙታን መነሣት አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ እርሱን መሰል ነቢያት ክርስቶስ እንደሚሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ ገልጸዋል፡፡ ምሳሌ ተመስሏል፤ ትንቢትም ተነግሯል፡፡ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ አደረ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ እንደሚነሣ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ወልድ ተናግሯል (ዮና. ፪፥፩፤ ማቴ. ፲፪፥፵)፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕም “ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፡፡ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፡፡ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን፤” በማለት የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን፤ ሕይወታችን መኾኑን ገልጾ ተናግሯል (ሆሴ. ፮፥፪)፡፡ በተጨማሪም “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል (መቃብር) ሆይ፥ ድል መንሳትህ ወዴት አለ?” ብሎ ሞት እና መቃብር ሥልጣናቸው በክርስቶስ እንደ ተሻረ፤ በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ትንሣኤ እንደ ተገለጸ ነግሮናል (ሆሴ. ፲፫፥፲፬)፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት ፵፱፥፱ ላይ “ልጄ ሆይ፥ ከመሰማሪያህ (ከመቃብር) ወጣህ፡፡ እንደ አንበሳ ተኛህ፤ አንቀላፋህም፡፡ እንደ አንበሳ ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም፤” የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል “የሚቀሰቅስህ የለም” የሚለው ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አስነሽ ሳይሻ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታችንም በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ እንዲህ በማለት አስተምሯል፤ “እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፍቃዴ እሰጣታለሁ፡፡ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤” (ዮሐ. ፲፥፲፯)፡፡ ይህ የሚያስረዳን ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ኾኖ በፈቃዱ እንደ ሞተና በሥልጣኑ እንደ ተነሣ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በሐዲስ ኪዳን

አራቱም ወንጌላውያን እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው የክርስቶስን ትንሣኤ በወንጌል ጽፈውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ ፳፰፥፩-፲፮ “በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዷልና፡፡ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ” ይላል፡፡ በዕለተ ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማየት መላእክት እንደዚሁም ቅዱሳት አንስት ተገኝተዋል፡፡ ሲወለድ የመወለዱን ዜና ለእረኞች የተናገሩ መላእክት በትንሣኤው ዕለትም ዜና ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት ለማብሠር ከመቃብሩ ተገኝተው የትንሣኤው ምስክሮች ኾነዋል፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜም መቃብር ጠባቂዎቹ ከመለኮቱ ግርማ የተነሣ ታውከዋል፤ እንደ በድንም ኾነዋል፡፡ “ወእምግርማሁ ተሀውኩ ወኮኑ ከመ አብድንት እለ የዐቅቡ መቃብረ፤ እርሱን ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ፤ እንደ በድንም ኾኑ፤” እንዳለ ቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፳፰፥፬)፡፡ መልአኩ “እናንተስ አትፍሩ! የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፡፡ ነገር ግን ኑና የተቀበረበትን ቦታ እዩ፤ ፈጥናችሁም ሒዱ፡፡ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤” ብሎ የትንሣኤውን የምሥራች ለሴቶች መግለጡንም ማቴዎስ በወንጌሉ ጽፎአል፡፡

ቅዱስ ማርቆስም በምዕራፍ ፲፮፥፩-፲፮ ትንሣኤውን አስመልክቶ ከቅዱስ ማቴዎስ ጋር የሚመሳሰል መልእክት ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም እንደዚሁ በምዕራፍ ፳፬፥፩-፳፬ የክርስቶስን ዜና ትንሣኤ ጽፎልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በአጻጻፍ ስልቱ ከሦስቱ ወንገላውያን ረቀቅ ያለ ቢኾንም ትንሣኤውን በመመስከር ከሦስቱ ወንጌላውያን ጋር ተባብሯል፡፡ በወንጌሉ ምዕራፍ ፳ ከቍጥር ፩ ጀምሮ ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ወደ መቃብሩ ገስግሰው በመሔድ ትንሣኤውን ለማየት እንደ በቁ፤ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራቹን እንደ ተናገሩ ዘግቦልናል፡፡

ከሦስቱ ወንጌላውያን በተለየ መልኩ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በዝግ ደጅ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሉበት እንደ ገባ፤ ትንሣኤውን እንደ ገለጠላቸው፤ “ሰላም ለእናንተ ይኹን!” ብሎ የሰላም አምላክ ነውና ከሐዘናቸው እንዳጽናናቸው፤ ፍርሃታቸውንም እንዳራቀላቸው፤ “አይዞአችሁ! አትፍሩ! እኔ ነኝ፤ እጄን፣ እግሬን እዩ፤” በማለት ፍጹም ፍቅሩን እንደ አሳያቸው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ገልጾልናል፡፡

ትንሣኤው ምትሐት አለመኾኑን ይገልጥላቸውም ዘንድም “ደቂቅየ ቦኑ ብክሙ ዘንበልዕ፤ ልጆቼ፥ ጥቂት የሚበላ አላችሁን?” በማለት ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ጠይቋቸዋል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በሕቱም መቃብር የተፈጸመ፤ አምላካዊ ኀይሉ የገለጠበት ትንሣኤ ነው፡፡ የተነሣውም “መግነዝ ፍቱልኝ፤ መቃብር ክፈቱልኝ፤” ሳይል ነው፡፡

ጌታ ባረገ በስምንት ዓመት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስም ሐዋርያትን መስሎ እንዲህ ሲል ትንሣኤውን መስክሮአል፤ “ስለ ኃጢአታችን የተሰቀለውን፤ ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ባስነሣው ስለምናምን ስለ እኛም ነው እንጂ፤” (ሮሜ. ፬፥፳፬)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ የጌታችን ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን መኾኑን ይነግረናል፡፡

ትንሣኤው ለእኛ ሕይወት መኾኑን ሲነግረን ደግሞ “እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን፤” በማለት አስተምሮናል (ሮሜ. ፮፥፬)፡፡ ይህም ጌታችን በሞቱ ሞትን እንደ ሻረ፤ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን እንዳበሠረ፤ እርሱ የትንሣኤያችን በኵር እንደ ኾነ፤ እኛም በሞቱ ብንመስለው የትንሣኤው ተካፋዮች እንደምንኾን ያሳየናል፡፡

ጌታችን በሚከተሉት አምስት ነገሮች በኵራችን መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፤

፩ኛ በጥንት፣ ገና ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቈጠር በመኖርና እኛን ፈጥሮ በማስገኘት በኵራችን ነው፡፡

፪ኛ በተቀድሶ (በመመስገን) በኵራችን ነው፡፡ ቅዱሳን የጸጋ ምስጋና የሚመሰገኑት እርሱን በኵር አድርገው ነውና፡፡

፫ኛ በትንሣኤው በኵራችን ነው፡፡ እርሱን በኵር አድርገን እንነሣለንና፡፡ “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ዂሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል፡፡ በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል፤ በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ኾነ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡

፬ኛ በዕርገቱ በኵራችን ነው፡፡ ቅዱሳን ዐረጉ መባሉ እርሱን በኵር አድርገው ነውና፡፡ “ዐርገ ከመ ያሌቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሓን፤ የንጹሓን ጻድቃንን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ አረገ” እንዲል (ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ)፡፡

፭ኛ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ምርኮን ማርኮ ገነት መንግሥተ ሰማያት በመግባት በኵራችን ነው፡፡

ስለዚህ በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር የእኛም ትንሣኤያችን መኾኑን ዐውቀን ተረድተን ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን መልካም ሥራ በመሥራት መኾን አለበት፡፡ እኛ ትንሣኤ ልቡና ሳንነሣ በየዓመቱ ትንሣኤውን ብናከብር ፈሪሳውያንን ወይም “ትንሣኤ ሙታን የለም፤ ፈርሰን፣ በስብሰን እንቀራለን” ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያንን መምሰል ይኾናል፡፡

ትንሣኤውን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመክረናል፤ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን ዐስቡ፤ በምድር ያለውንም አይደለም፡፡ እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና፡፡ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ፤” (ቈላ. ፫፥፩-፬)፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤያችን ነው ብለን ለምናምን ዂሉ ከምድራዊ ዐሳብ ነጻ ኾነን ተስፋ የምናደርገው ትንሣኤ እንዳለን በማሰብ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከትንሣኤም በኋላ የዘለዓለም ሞት መኖሩን ሳንዘነጋ በዓሉን ማክበር እንደሚገባን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡

ላይኛውን (ሰማያዊዉን መንግሥት) ለማያስቡ፤ መልካም ሥራ ለማይሠሩ ሰዎች ትንሣኤ ምን እንደሚመስል መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፤ “በመቃብር ያሉ ዂሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ስለዚህ አታድንቁ፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ፤” (ዮሐ. ፭፥፳፰)፡፡

ምእመናን፣ የትንሣኤያቸውን በኵር ክርስቶስን አብነት አድርገው፣ ቃሉን ሰምተው፣ ሕጉን ጠብቀው፣ ትእዛዙን አክብረው፣ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተው የትንሣኤን ዕለት ቢያከብሩ፤ ሥጋውን በልተው፣ ደሙን ጠጥተው፣ በንስሐ ተሸልመው፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ (ባልንጀራን በመውደድ) ጸንተው ቢኖሩ ላይኛውን ማሰብ ትንሣኤውን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ እንደዚህ ካደረጉ የትንሣኤውን ትርጕም ዐውቀዋል፡፡

ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግሥቱን እንድንወርስ ስሙን እንድንቀድስ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል ይኹንልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡