ኪዳነ ምሕረት

%e1%8a%aa%e1%8b%b3%e1%8a%95

በዲያቆን ኃይለ ኢየሱስ ቢያ

የካቲት ፲፭ ቀን ፳፻፱ .

‹‹ኪዳን›› የሚለው ቃል ‹‹ተካየደ – ተዋዋለ፤ ቃል ኪዳን ተጋባ፤ ተማማለ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ኪዳን፣ ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው /ዘዳ.፳፱፥፩፤ ኤር.፴፩፥፴፩-፴፫፤ መዝ.፹፰፥፫/፡፡ በሌላ በኩል ኪዳን የጸሎት ስም ሲኾን፣ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት ኪዳን ይባላል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳን (ውል፣ ስምምነት) የተቀበለችበት ዕለት (የክብረ በዓል ስም) ደግሞ ኪዳነ ምሕረት ይባላል፡፡

በየዓመቱ የካቲት ፲፮ ቀን የምናከብረው ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ኾና ‹‹ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማኅፀንየ ዘጾረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዬ ሥጋ፣ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው ስለመኾንህ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ስለቻለችህ ማኅፀኔ፤ ከአንተ ጋር ከአገር ወደ አገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ›› እያለች ስትጸልይ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ ወደእርሷ መጥቶ ‹‹ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይኹን! እንዳደርግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?›› አላት፡፡ እመቤታችንም በስሟ የሚማጸኑትንና መታሰቢያዋን የሚያደርጉትን፣ ለችግረኛ የሚራሩትን፣ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጹትን፤ ዕጣን ዘይትና መብአ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን፤ ለእመቤታችንና ለሃይማኖታቸው ካላቸው ፍቅር የተነሣ ልጆቻቸውን በስሟ የሰየሙትን ዅሉ እንዲምርላትና ከሞተ ነፍስ እንዲያድንላት ጠየቀችው፡፡

ጌታችንም ‹‹ይህን ዅሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው፤ በራሴ፣ በአባቴ እና በመንፈስ ቅዱስ ማልኩልሽ›› ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው ‹‹… ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል፤ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት፡፡ አንተ ‹መታሰቢያሽን ያደረገ፣ ስምሽንም የጠራ፣ የዘለዓለም ድኅነትን ይድናል› ብለሃታልና …፤›› በማለት የሚማጸነው፡፡

በተአምረ ማርያም መጽሐፍ እንደተመዘገበው በዚህ ዕለት የሚታሰቡ ሁለት ተአምራት አሉ፤ ከእነዚህም አንደኛው የስምዖን ታሪክ ነው፡፡ ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት ከቤቱ ገብቶ ‹‹ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ ሌላ ምግብ አልበላም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ሲያወጣና ሲያወርድ ቆየና ‹‹አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለው›› በማለት፣ ‹‹የእግዚአብሔርን እንግዳ›› ላለማሳዘን ሲል ልጁን አርዶ አቀረበለት፡፡ እንግዳ መሰሉ ሰይጣንም ሥጋውን ቅመስልኝ ብሎ ግድ አለው፡፡ ስምዖንም (በላዔ ሰብእ) አርዶ ያዘጋጀውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ሰይጣን ስላደረበት (ስለተዋሐደው) ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ቤተሰቦቹን፣ ጎረቤቶቹንና መንገደኛውን ዅሉ ይበላ ጀመር፡፡ በአጠቃላይ ፸፰ ሰዎችን ከበላ በኋላ አንድ በቍስል የተመታ ሰው አገኘና ሊበላው ሲል ‹‹ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ በሥላሴ፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ለመነው፤ እርሱም ዝም አለው፡፡

በመጨረሻም ‹‹በድንግል ማርያም ስም›› አለው፡፡ ስምዖን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜም ወደ ልቡናው ተመልሶ ‹‹እስኪ ቃሉን ድገመው›› አለው፤ በሽተኛውም መልሶ ‹‹ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ›› ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ ‹‹ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ›› ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፤ ውኃው ጕሮሮውን እንኳን ሳያርስለት ‹‹ጨረስህብኝ›› ብሎ ነጥቆት ሔደ፡፡ በሌላ ቦታም አንድ ገበሬ አግኝቶ ሊበላ ሲል ገበሬው ‹‹በላዔ ሰብ የምትባል አንተ ነህ?›› ባለው ጊዜ ‹‹ለካስ አመሌን ሰው ዅሉ አውቆብኛል›› ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን ‹‹ልጄ በማይታበል ቃልህ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ ጌታችንም ‹‹ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ፣ ፈጣሪውን የካደ ሰው ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?›› ብላ ስምዖንን (በላዔ ሰብእን) አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

ሁለተኛው ተአምር ደግሞ ከብሮ ከኖረ በኋላ ለድህነት በተጋለጠ አንድ ምእመን ላይ የተደረገ ነው፤ ከክርስቲያን ወገን የኾነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ‹‹ከብሬ በኖርኹበት አገር ተዋርጄ አልኖርም›› ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ከአገሩ ወጥቶ ሲሔድ ሰይጣን ያዘነ ሰው መስሎ ደንጊያውን በምትሐት ወርቅ አስመስሎ ‹‹ሥላሴን፣ ጻድቃንን፣ ሰማዕታትንን፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን ወርቅ እሰጥሃለሁ›› አለው፡፡ ዅሉንም ካደለትና ወርቁን ተቀብሎ ዞር ሲል ‹‹ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያምየአምላክ እናት አይደለችም› ብለህ ካድልኝ›› አለው፡፡ ሰወየውም ‹‹እርሷንስ አልክድም›› ስላው በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት የሟቹን ነፍስ ሊወስዱ ሲሉ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ፡፡ እመቤታችንም ጌታችንን ‹‹ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ?›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ከልብኑ ይትመሐር እምየ፤ እናቴ፣ ውሻ ይማራልን?›› አላት፡፡ እመቤታችንም፡- ‹‹‹ስምሽን የጠራውን፣ መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ› ያልኸው ቃል ይታበላልን?›› አለችው፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ምሬልሻለሁ›› አላት፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ›› ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከላይ በተአምራቱ እንደተመለከትነው አንዱ ለእመቤታችን የሰጠው የአማላጅነት ኪዳን ነው፡፡ ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማድረግ፣ ማስማር (ይቅርታ ማሰጠት) ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ዅሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን›› እያሉ ለሚለምኗት ዅሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የምንከተል ምእመናን ዅሉ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ እንደመኾኗ ከዅሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ኾነ በሰው ዘንድ ባለሟልነትን ማግኘት ወይም ቅርብ መኾን ደግሞ አንድን ጉዳይ በቀላሉ ለማስፈጸም ይጠቅማል፡፡ ለምሳሌ፡-

  • መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመኾኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ኾኗል /ሉቃ. ፩፥፲፱-፳፮/፡፡
  • አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመኾኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች /መጽሐፈ አስቴር ፫፥፲/፡፡
  • ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመኾኑ ‹‹ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን እኔን ከጻፍከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ?›› በማለት ለእስራኤላውያን ምሕረትን አሰጥቷል /ዘፀ.፴፪፥፲፬/፡፡

ስለዚህ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትም እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር፡- ‹‹ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እምአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም፤ ለሕዝብሽ፣ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ፤ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ዅሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትኾኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ዘንድ ሥልጣን አግኝተሻል›› በማለት አመስግኗታል /አንቀጸ ብርሃን/፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰታቸው፡- ‹‹ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤ የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት፣ መርገም (ኀጢአት) ባጠፋን ነበር›› ብለዋል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡‹‹ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ፡፡ መዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ፡፡ ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ፡፡ ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ፤›› ሲሉ ይማጸኗታል /ቅዳሴ ማርያም ቍ.፻፷፭-፻፸፩/፡፡

ስለዚህም ዘወትር በሥርዓተ ቅደሴአችን፡- ‹‹ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ዅል ጊዜ ድንግል የምትኾኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊልን፡፡ በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ፤ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡ በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን ዘንድ በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፡፡ በእውነት ንግሥት የምትኾኚ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ፤›› በማለት እመቤታችንን እንማጸናታለን፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ፤ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፤›› በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት፣ ጻድቃን፣ ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባ፣ እንደሚገባ ተናግሯል /መዝ.፹፰፥፫/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማን ነው?›› በማለት እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚጠራ፣ እንደሚያከብር፣ እንደሚቀድስና ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል /ሮሜ.፰፥፴፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው፤›› /መዝ.፹፮፥፫/ በማለት እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላካችን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ዅሉ ልዩ ነው፡፡ ይህም እንደምን ነው ቢሉ፡-

  • ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመኾኗ፤
  • አምላክ ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለዱ፤
  • ከመለለዷ በፊት፣ በወለደች ጊዜ፣ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመኾኗ፤
  • በሁለቱም ወገን (በአሳብም በገቢርም) ድንግል በመኾኗ፤
  • አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይኾን የእናትነት በመኾኑ፤
  • ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ ስለመረጣት ነው፡፡

ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን፣ እንደበላዔ ሰብእ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን፣ ንስሐ ገብተን፣ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን፣ የስሙ ቀዳሽ፣ የመንግሥቱ ወራሽ ለመኾን ያብቃን፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳዒነት አይለየን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት፡-

  • መጽሐፈ ስንክሳር
  • መዝገበ ታሪክ
  • ተአምረ ማርያም
  • አማርኛ መዝገበ ቃላት
  • ክብረ ቅዱሳን