እናቴ ሆይ እሳቱን አትፍሪ፤ እግዚአብሔር ያድነናል፡፡

ሐምሌ ፲፰ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

007

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደ ተመዘገበው ሐምሌ ፲፱ ቀን ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ በሰማዕትነት መከራ የተቀበሉበትና ስማቸውን የሚጠራ፣ ዝክራቸውንም የሚዘክሩ ምእመናን ይቅርታን፣ ምሕረትን እንደሚያገኙ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ኪዳን የተቀበሉበት ዕለት ነው፡፡ እንደዚሁም እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እነዚህን ቅዱሳን መርዳቱ የሚነገረው በዚሁ ዕለት ነው፡፡ የሰማዕታቱ ቅዱስ ቂርቆስና የኢየሉጣ ታሪክም በአጭሩ የሚከተለው ነው፤

 

አንጌቤን በሚባል አገር በክርስትና ሃይማኖት ጸንታ የምትኖርና እግዚአብሔርን የምትፈራ ቅድስት ኢየሉጣ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ልጇን ቅዱስ ቂርቆስንም በሃይማኖትና በምግባር አሳድጋዋለች፡፡ የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራት ከሮም ወደ ጠርሴስ ከልጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡

 

የንጉሡ ወታደሮችም ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን እግዚአብሔርን እንዲክዱ፤ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቢያፈስራሯቸውም ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልኾኑም፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ ጨውና ሰናፍጭ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

 

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች በቸነከራቸው ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡

 

እንደገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ባደረገ ጊዜም መኰንኑ በተአምራቱ በመቈጣቱ ምላሱን ቢያስቈርጠውም ጌታችን ምላሱን አድኖለታል፡፡

 

ዳግመኛም በፈላ የጋን ውሃ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ፤ አናንያ፣ ዓዛርያና ሚሳኤልን ከእሳት ነበልባል ያዳናቸው እግዚአብሔር እኛንም ከዚህ የፈላ ውሃ ያድነናል” እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ያ ውሃም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ ከተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜም ቅዱስ ገብርኤል በሕይወት አድኗቸዋል፡፡

 

በአጠቃላይ ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ “ሞት ቢኾን፣ ሕይወትም ቢኾን፣ መላእክትም ቢኾኑ፣ ግዛትም ቢኾን፣ ያለውም ቢኾን፣ የሚመጣውም ቢኾን፣ ኃይላትም ቢኾኑ፣ ከፍታም ቢኾን፣ ዝቅታም ቢኾን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢኾን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ፤” /ሮሜ.፰፥፴፰-፴፱/ ሲል ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡

 

በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡

 

በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይኾኑ ብዙ ምእመናንም ተጠቅመዋል፡፡ ለዚህም ስሙ በሚጠራባቸው ገዳማትና አድባራት የሚያደርጋቸው ድንቅ ድንቅ ተአምራት ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህም ቅዱሳን መላእክት በእግዚአብሔር ስም መከራ የሚቀበሉ ምእመናንን እንደሚጠብቁና ከልዩ ልዩ ደዌ እንደሚፈውሱ የሚያስረዳ ታሪክ ነው፡፡

 

እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ “እናቴ ሆይ አትፍሪ” እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ኹሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል “አይዞህ! አይዞሽ! አትፍራ! አትፍሪ” በመባባል እስከ ሞት ድረስ በመታመን በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ በትዕግሥት ለማሳለፍ ቈርጠን መነሣት ይኖርብናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይኾን ለኹላችንም የተሰጠ የጋራ የድኅነት በር ነውና፡፡

 

ከዚሁ ኹሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን “በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን” እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ /መዝ.፴፬፥፯/፡፡

 

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በቅዱስ ገብርኤል፣ በቅድስት ኢየሉጣና በቅዱስ ቂርቆስ ጸሎትና ምልጃ ይጠብቀን፡፡ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡