አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እና የኬልቄዶን ጉባኤ – ካለፈው የቀጠለ

በቀሲስ ዶ/ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል

ጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.

… ቀጥሎ በ2ኛው የኤፌሶን ጉባኤ የተወገዘው የዶሪሌኡም ኤጲስቀጶስ አውሳብዮስ ተነሥቶ ዲዮስቆሮስ እሱንና የቊስጥንጥንያውን ፍላብያኖስን ‹‹ምንም የሃይማኖት ጕድለት ሳይገኝብን ያለ አግባብ አውግዞናል ጥቃትም አድርሶብናል፡፡ በተጨማሪም አውጣኪን ከግዝቱ በመፍታት የኦርቶዶክስ እምነትን አበላሽቷል፤›› በማለት ክስ አቀረበ፡፡ ይህ ተመሳሳይ ክስ በሮሙ ፖፕ ተወካዮችም ቀርቧል፡፡ በመሠረቱ ይህ ክስ እውነት እንኳ ቢሆን የሚመለከተው ሲኖዶሱን እንጂ የሲኖዶሱን ሊቀ መንበር ዲዮስቆሮስን አልነበረም፡፡ ከዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው የሮሙ ፖፕ ተወካዮችም ሆኑ ከሳሹ አውሳብዮስ በአጠቃላይ የኬልቄዶን ጉባኤም ቢሆን ዲዮስቆሮስን በእምነት ክህደት አልከሰሱትም፡፡ ሆኖም መናፍቅ ነው ተብሎ የታሰበውን አውጣኪን የ449 ዓ.ም. ሲኖዶስ ነጻ አድርጎ ከውግዘቱ ስለፈታው ብቻ ዲዮስቆሮስን የአውጣኪን የኑፋቄ ትምህርት ተቀብሏል ብለው በጭፍኑ ደምድመዋል፡፡ አውጣኪ ግን በፊት ያስተምር የነበረውን የኑፋቄ ትምህርት ትቶ በቃልም በጽሑፍም ኦርቶዶክሳዊ የእምነት መግለጫ በማቅረቡ በዚህ መሠረት ነው 2ኛው የኤፌሶን (የ449) ሲኖዶስ ነጻ ያደረገው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ አውጣኪ ያቀረበው የእምነት መግለጫ የሚገኝበት የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ እንዲነበብ ጠየቀ፡፡

የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ የመጀመሪያው ክፍል ከተነበበ በኋላ ጉባኤውን የጠራው ንጉሡ ዳግማዊ ቴዎዶስዮስ መሆኑና አውጣኪንም ነጻ ያደረጉት በጉባኤው የነበሩት ጳጳሳት በሙሉ ተስማምተው በፊርማቸው ያጸደቁት መሆኑ ተነበበ፡፡ በ449 ዓ.ም. በ2ኛው የኤፌሶን ሲኖዶስ ላይ የነበሩት ጳጳሳት ግን የ449 ሲኖዶስን ውሳኔ ፈጽሞ እንደማያውቁት የፈረሙትም በወታደሮች ተገደው በባዶ ወረቀት ላይ መሆኑን አጥብቀው ተናገሩ:: የግብጽ ጳጳሳት ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ‹‹የክርስቶስ ወታደር የዚህን ዓለም ባለሥልጣን ፈጽሞ አይፈራም፡፡ እሳት አንድዱ አንድ ሰማዕት እንዴት እንደሚሞት እናሳያችሁ!›› ብለው በጉባኤው ፊት ተናገሩ፡፡ ባዶ ወረቀት ላይ ነው የፈረምነው ካሉት አንዱ የኤፌሶኑ ኤጲስ ቆጶስ እስጢፋኖስ ነበር፡፡ ይህ ሰው አውጣኪ ነጻ እንዲደረግ ተነሥተው ከተናገሩት ሰዎች ሁለተኛው ነበር፡፡ አውሳብዮስና ፍላብያኖስም እንዲወገዙ ከተናገሩት 5ኛው ተናጋሪ እሱ ነበር፡፡  የሲኖዶሱ ጸሓፊ በ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ላይ የአውጣኪን የሃይማኖት መግለጫ ሲያነብ አንዳንድ አባቶች ይህን መግለጫ እንዳላዩትና ፊርማቸውም አስመስሎ የተፈረመ ነው በማለት ካዱ፡፡

ከዚህ በኋላ በጉባኤው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ እምነቱን እንዲገልጽ ተጠይቆ ሁለቱ ባሕርያት (የመለኮትና የሥጋ) ያለ መቀላቀልና ያለ ትድምርት፣ ያለ መለወጥና ያለ መለያየት በአንድ አካል እንደተዋሐዱ በሚገባ አስረዳ፡፡ እንዲሁም በቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት መሠረት ‹‹አአምን በአሐዱ ባሕርይ (ህላዌ) ዘቃለ እግዚአብሔር ሥግው፤›› ብሎ አስረዳ፡፡ ጉባኤውም በዚህ በዲዮስቆሮስ እምነት ላይ ምንም እንከን፣ ምንም ስሕተት አላገኘም፡፡ ጉባኤው በሌላ መንገድ ‹‹አውጣኪ በጽሑፍ ካቀረበው የተለየ በቃል ቢናገር ምን ትፈርድ ነበር?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ‹‹አውጣኪ የጻፈውን ትቶ ሌላ የክህደት ነገር ቢናገር፣ እሱን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በእሳትም እንዲቃጠል እፈርድበት ነበር፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በእንደዚህ ያለ ነጐድጓዳዊ አነጋገር ሁሉን ግልጥልጥ አድርጎ በተናገረ ጊዜ፣ ኬልቄዶናውያን ጸጥ አሉ፡፡ ዲዮስቆሮስን በመቃወም የተናገሩ የምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ግን ንግግሩ ልባቸውን ነክቶት ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን!›› በማለት ጮኹ፡፡

የመንግሥቱ ዳኞች በባዶ ወረቀት ላይ ነው የፈረምነው ስላሉት እንደገና ሲጠይቋቸው ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ መለሱ፡፡ እንደገና ፍላብያኖስን ዲዮስቆሮስ ነው ያስገደለው ስላሉት ቢጠየቁ አሁንም ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ መለሱ፡፡ በዚህ ሁኔታ እነዚህ ጳጳሳት 1ኛ/ በሐሰት በባዶ ወረቀት ላይ ፈርመናል በማለታቸውና፣ 2ኛ/ ፍላብያኖስንና አውሳብዮስን ያለ አግባብ በማውገዛቸው ይቅርታ ጠየቁ፡፡ የመንግሥቱ ዳኞች ፍላብያኖስ ኦርቶዶክስ መሆኑን አጥብቀው በጠየቁ ጊዜ፣ የሮሙ ተወካዮችና አብዛኞቹ አባላት በ449 ሲኖዶስ ጊዜ የነበሩትም ጭምር ፍላብያኖስ ኦርቶዶክስ እንደነበረ ተናገሩ፤ ‹‹ታዲያ ለምን ተወገዘ?›› ሲሉ ዳኞቹ ጠየቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ዲዮስቆሮስ ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ከሥጋዌ በኋላ ሁለት ባሕርያት እንዳለው አጥብቆ ይናገር ነበር፤›› ብሎ ተናገረ፡፡ የዚህም እውነት እንዲወጣ ብሎ የ449 ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ቀርቦ እንዲነበብ አበክሮ ጠየቀ፡፡ ለዚህ ምንም መልስ አልተሰጠውም፡፡

ሁሉም ዳኞቹም ጭምር ቃለ ጉባኤው እንዳይነበብ ስለፈለጉ ጸጥ አሉ፡፡ ሁሉም ዝም ቢሉም ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ንግግሩን በመቀጠል ፍላብያኖስ ‹‹ክርስቶስ ከሥጋዌ በኋላ ሁለት ባሕርያት አለው፤›› እያለ እንደሚናገር መልሶ መላልሶ አስረዳ፡፡ የቀድሞ አባቶች ግን ለምሳሌ አትናቴዎስ፣ ጎርጎርዮስና ቄርሎስ ‹‹አሐዱ ባሕርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው›› እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ‹‹ሁለት ባሕርያት›› ፈጽሞ እንደማይሉ በመጻሕፍቶቻቸው ሁሉ ለማንበብ እንደሚቻል አስረዳ፡፡ የቀረቡትን ማስረጃዎች ሁሉ ከቁም ነገር ሳያስገቡ ጉባኤውም በሚገባ ሳይወያይበት ዳኞቹ በጭፍን ፍላብያኖስና አውሳብዮስ ያላግባብ ነው የተወገዙት በማለት ውሳኔ አሳለፉ፡፡ በተጨማሪም አውጣኪ ቀርቦ ሳይጠየቅ ለ449 ጉባኤ ያቀረበውንም የሃይማኖት መግለጫ ሳይመለከቱ፣ በጭፍን በ449 ሲኖዶስ ላይ ያለ አግባብ ነው ነጻ ሆኖ ከግዝቱ የተፈታው ብለው ዳኞቹ፣ የፖፑ ተወካዮችና ሌሎቹ የጉባኤው አባላት ወሰኑ፡፡ ይህ በግልጥ የሚያመለክተው የኬልቄዶን ጉባኤ የተጠራው ዲዮስቆሮስንና አውጣኪን ለማውገዝና ፍላብያኖስንና አውሳብዮስን ነጻ ለማድረግ መሆኑን ነው፡፡

ከላይ ለቀረቡት ጥብቅ ማስረጃዎች ምንም መልስ ሳይሰጡ የመንግሥቱ ዳኞችና የሮሙ ፖፕ እንደራሴዎች የፖፑን የዶግማ ደብዳቤ (Tomos) አስተያየቱን እንዲገልጥ ለፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ሰጡት፡፡ ዲዮስቆሮስም ለጥቂት ጊዜ ከአነበበው በኋላ፣ ደብዳቤው ኦርቶዶክሳዊ ሳይሆን ንስጥሮሳዊ መሆኑን ገልጦ ደብዳቤውንና ደራሲውን ያለ አንዳች ማመንታት አወገዘ፡፡ ከተሰበሰቡት ጳጳሳት ብዙዎቹ ስለ ልዮን ደብዳቤ (Tomos) የዲዮስቆሮስን አስተያየትና ስሜት ተጋርተዋል፡፡ ነገር ግን አስተያታቸውን በይፋ ለመግለጥ ድፍረት አልነበራቸውም፡፡ ሌሎች ደግሞ ስለዚሁ ደብዳቤ ታላቅ ጥርጣሬና መደናበር እንዳደረባቸው በፊታቸው ላይ ይነበብ ነበር፡፡ ይህን የአባላቱን ሁኔታ የተመለ ከቱት ዳኞች በደብዳቤው ውስጥ የሚያውክና የሚያስቸግር ነገር እንዳለ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አንዳንድ ጳጳሳት ምንም ችግር አለመኖሩን ገልጠው፣ ሆኖም አንዳንድ የላቲን ቃላትንና አባባሎችን በደንብ ለመመርመር ጊዜ ለማግኘት ስብሰባው ለአምስት ቀናት እንዲበተን ጠየቁ፡፡ ጥያቄአቸውም ወዲያውኑ ተቀባይነት አግኝቶ ስብሰባው ተበተነ፡፡

ነገር ግን ከሦስት ቀናት በኋላ ጳጳሳቱ የመንግሥቱ ዳኞች በሌሉበት ለነሱም ሳይነግሩ ይፋዊ ስብሰባቸውን በፖፑ እንደራሴ ፓስካሲኑስ (Paschasinus) ሊቀ መንበርነት ቀጠሉ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የግብጽ ጳጳሳትና ሌሎች ብዙ ጳጳሳት አልተገኙም፡፡ ስብሰባውን እንደጀመሩ የፖፑ እንደራሴና የስብሰባው ሊቀ መንበር ‹‹የፖፑ ደብዳቤ መከበር አለበት፡፡ ሁሉም ደብዳቤውን መቀበል አለባቸው፡፡ ይህን ደብዳቤ የሚቃወም ተከሶ በጉባኤው ፊት መቅረብ አለበት፤›› ሲል አወጀ፡፡ ወዲያውኑ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ስብሰባው እንዲመጣ ወደ ማረፊያ ቦታው ሦስት ጳጳሳትና አንድ ዲያቆን ተላኩ፡፡ በዚያን ጊዜ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ከቤት እንዳይወጣ ንግሥት ብርክልያ ባዘዘቻቸው ወታደሮች ይጠበቅ ነበር፡፡ መልእክተኞቹም ዲዮስቆሮስን ወደ ጉባኤው እንዲመጣ በጠየቁት ጊዜ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ‹‹ጉባኤው የተበተነው ለአምስት ቀናት ሲሆን አሁን ገና ሦስት ቀናት ነው ያለፉት፡፡  አሁን እንዴት ለመሰብሰብ እንችላለን? ለመሆኑ የመንግሥቱ ተወካዮች ዳኞች ተነግሯቸዋል?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ አልተሰጠውም፡፡ ለሁለተኛው ጥያቄ ግን ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ምእመናን አያስፈልጉም፤›› ሲሉ መለሱለት፡፡

ቀጥሎ ከቤት ወጥቶ ወደ ስብሰባው ለመሄድ ይፈቅዱለት እንደሆነ ወታደሮቹን ማስፈቀዳቸውን መልእክተኞቹን ጠየቀ፡፡ እነርሱም በበኩላቸው ‹‹እኛ የተላክነው አንተን እንድንጠራ ነው እንጂ ወታደሮችን እንድንጠይቅ እይደለም፤›› ሲሉ መለሱና ተመልሰው ሄዱ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ሌሎች መልእክተኞች ለዲዮስቆሮስ ሌላ ጥሪ አቀረቡ፡፡ እሱም የመንግሥት ተወካዮች ዳኞች ከሌሉ እንደማይ መጣ ነግሯቸው ተመለሱ፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው በሲኖዶስ ሕግ መሠረት አንድ ሰው ሦስት ጊዜ ተጠርቶ ካልመጣ እንደሚወገዝ ስለሚያውቁ በዚሁ መሠረት ዲዮስቆሮስን በሌለበት ለማውገዝና የፖፕ ልዮንን የዶግማ ደብዳቤ (Tome of Leo) ሁሉም እንዲቀበሉት ለማድረግ ነበር፡፡ ይህም የታቀደው በፖፑ ወኪሎች ነበር፡፡ በዚህ መካከል ሌሎች ከሳሾች ቀርበው በፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ላይ የተለያዩ እምነትን የማይመለከቱ የሐሰት ክሶችን እንዲያቀርቡ ተደረገ፡፡ በመጨረሻም ዲዮስቆሮስ ወደ ጉባኤው እንዲመጣ ለሦስተኛ ጊዜ መልእክተኞች ላኩበት፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የኬልቄዶን ጉባኤ ሤራ በደንብ ስለገባው የሃይማኖት መልእክቱን ቀደም አድርጎ ያስተላለፈ መሆኑን ገልጾ በሕመም ምክንያት ወደ ጉባኤው ለመሄድ አለመቻሉን ስለገለጠላቸው መልእክተኞቹ ተመልሰው ሄዱ፡፡ የፖፑ ተወካዮችና አንዳንድ የእነርሱ ደጋፊዎች ዲዮስቆሮስን ለማውገዝ ይህንኑ ነበር የፈለጉት፡፡

የቅዱስ ዲዮስቆሮስ በኬልቄዶናውያን መወገዝ

የሮሙ ፖፕ ልዮን፣ የሮም የምሥራቁ ክፍል ንጉሠ ነገሥት የመርቅያንና የንግሥቲቱ የብርክልያ ታላቅ ተጽእኖ የነበረበት ይህ የኬልቄዶን ጉባኤ መጀመ ሪያም የተሰበሰበው ዲዮስቆሮስን ለማው ገዝና ከሥልጣኑ ለማውረድ ስለነበረ፣ እሱን ለማውገዝ ብዙ ምክንያቶች ይፈልጉ ነበር፡፡ በሃይማኖት በኩል ምንም ስሕተት ስላላገኙበት የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና አፍርሷል በማለት እሱን ወንጀለኛ ለማድረግ አስበው ሕጉን የሚያስከብሩት የመንግሥት ዳኞች ለአምስት ቀናት ጉባኤውን በበተኑበት ጊዜ ከግማሽ ያነሱ አባላት ተሰብስበው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሦስት ጊዜ ደጋግመው ጥሪ እንዲደርሰው አደረጉ፡፡ ዲዮስቆሮስም ከላይ እንደተገለጸው ሕግ አስከባሪዎቹ ዳኞችና ሌሎች ከእርሱ ጋር የተከሰሱት በሌሉበት ለመገኘት ስላልፈለገ በጉባኤው ላይ አልተገኘም፡፡ ይህን ምክንያት አድርገው ‹ሲያሻኝ ጭስ ወጋኝ› እንደሚሉት ቀኖና አፍርሷል በማለት የተሰበሰቡት በአንድ ድምፅ አወገዙት፡፡

ሲያወግዙትም ሦስት ምክንያቶች ዘርዝረዋል፤ 1ኛ/ በመናፍቅነት የተከሰሰውንና የተወገዘውን አውጣኪን ነጻ አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት መልሶታል፡፡ ከዚህ ላይ አውጣኪ በጽሑፍ ያቀረ በውንና በቃልም ያረጋገጠውን ኦርቶዶክሳዊ የሃይማኖት መግለጫ ሊመለከ ቱት አልፈለጉም፡፡ 2ኛ/ የሮሙ ፖፕ ልዮን የላከውን የሃይማኖት መግለጫ ደብዳቤ (The Tome of Leo) ባለመ ቀበል ደብዳቤውንም ፖፕ ልዮንንም አውግዟል የሚል ነው፡፡ 3ኛ/ በጉባኤው ላይ እንዲገኝ ሦስት ጊዜ ተጠርቶ አልተገኘም የሚል ነበር፡፡

ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ከተወገዘና ከሥልጣን እንዲወርድ ከተወሰነበት በኋላ ንግሥት ብርክልያ በግል አስጠርታ ሐሳቡን ለውጦ በልዮን ጦማር (Tome of Leo) ላይ እንዲስማማና እንዲፈርም ትእዛዝ አዘል ምክር ሰጥታው ነበር ይባላል፡፡ እሱ ግን መንፈሰ ጠንካራ ስለነበር የንግሥቲቱን ትእዛዝና ምክር አልተቀበለም፡፡ በዚህ ተናዳ ንግሥቲቱ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን በወታደሮች በሚያሰቅቅ ሁኔታ አስደበደበችው፡፡ በዚህም ድብደባ ጥርሶቹ ወላልቀው ጽሕሙም ተነጫጭቶ ነበር፡፡ እሱም የተነጨ ጽሕሙንና የወለቁትን ጥርሶች በአንድ ላይ ቋጥሮ ‹‹ይህ የሃይማኖት ፍሬ ነው፤›› የሚል ጽፎበት ለግብጽ ምእመናን ልኮላቸዋል ይባላል፡፡

የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ግዞት መላክ

እጅግ የሚገርመው የኬልቄዶን ጉባኤ ስብሰባውን ሳይፈጽም የጉባኤውም ዘገባ ገና ሳይደርሰው የቊስጥ ንጥንያ ንጉሠ ነገሥት መርቅያን የጉባኤውን ውሳኔዎች ሁሉ የሚያጸድቅ ጽሑፍ ለጉባኤው ላከ፡፡ እንዲሁም ንጉሡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጋግራ (ጋንግራ) ወደሚባል ደሴት እንዲጋዝ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደተጋዘበት ወደ ደሴተ ጋግራ በሄደ ጊዜ በፈቃዳቸው ሁለት ጳጳሳትና ሁለት ዲያቆናት ተከትለዉት ሄደው ነበር፡፡ ሦስተኛው ጻድቅ የነበረ መቃርዮስ የተባለ የኤድኮ ጳጳስ አብሮት ለመሄድ በመንገድ ላይ ሳለ ‹‹ቅዱስ ማርቆስ ደሙን ባፈሰሰበት ከተማ የሰማዕትነት አክሊል ስለሚጠብቅህ ቶሎ ብለህ ሂድ እንዳያመልጥህ፤›› ብሎ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ስለነገረው ወዲያውኑ ወደ ግብጽ ሄደ፡፡ ንጉሠ ነገሥት መርቅያን ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስን ወደ ግዞት እንዲላክ ከአደረገ በኋላ የጉባኤው ውሳኔ በመንግሥት መጽደ ቁን በመግለጽ ለእስክንድርያና ለመላዋ የግብጽ ሕዝብና ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን መልእክት ላከ፡፡ ወዲያውኑም በዲዮስቆሮስ ምትክ ፕሮቴሪዮስ የሚባል ኤጲስ ቆጶስ በቊስጥ ንጥንያ ሹሞ ወደ እስክንድርያ በብዙ ወታደሮች ታጅቦ እንዲሄድ አደረገ፡፡ ወታደሮቹም ለአዲሱ ፓትርያርክ የማይታዘዙትንና የማይገዙትን ከባድ ቅጣት እንዲቀጡ በጥብቅ ታዝዘው ነበር፡፡

የግብጽ ክርስቲያኖች ግን ለዲዮስቆሮስ ታማኝነታቸውን በመግለጥ ንጉሡ ለላከው ፓትርያርክ አንገዛም አሉ፡፡ የግብጽ ጳጳሳትም አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ለፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ ታማኝነታቸውን በአንድ ድምፅ ገልጠው፣ ፖፕ ልዮንንና የልዮንን ጦማር (The Tome of Leo I) እንዲሁም የኬልቄዶንን ጉባኤን ጉባዔ ከለባት ብለው በመጥራት አወገዙት፡፡ ፓትርያርክ አንዲሆን የተላከባቸውንም ፕሮቴሪዮስን አወገዙ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ መርቅያንም ይህን እንደሰማ አጸፋውን ለመመለስ ጳጳሳቱ በሙሉ በኬልቄዶን ጉባኤ ውሳኔና በልዮን ጦማር ላይ እንዲ ፈርሙ በግብጽ ለነበሩት የጦር ሹማም ንቱና መኰንኖቹ ትእዛዝ አስተላለፈ፡፡ መኰንኖቹም በትእዛዙ መሠረት ጽሑፎቹን ለማስፈረም ወደየጳጳሳቱ ሲሄዱ መጀመሪያ የተገኘው ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ወደ ግዞት ሊከተለው ሲል ‹‹ወደ እስክን ድርያ ሂድ፤ በዚያ የሰማዕትነት አክሊል ይጠብቅሃል፤›› ያለው የኤድኮ ጳጳስ አባ መቃርዮስ ነበር፡፡ ወታደሮቹ ጽሑፎቹን አልፈርምም በማለቱ ከዚያው ደብድበው ገድለውታል፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነታቸው በመጽናታቸውና የኬልቄዶንን ጉባኤ ባለመቀበላቸው ሠላሳ ሺሕ (30,000) የሚሆኑ ካህናትና ምእመናን ተገድለዋል፡፡ ከጥቂት የሰበካ አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር አብዛኞቹ የአብያተ ክርስቲያናት ሕንጻዎች የኬልቄዶንን ጉባኤ ለሚደግፉ ጥቂት ክርስቲያኖች በንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ እንዲሰጣቸው ተደረገ፡፡

ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ አምስት ዓመት በግዞት ግፍና ሥቃይ እየተቀበለ ከቆየ በኋላ በ456 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡ መላው የግብጽ ካህናትና ምእመናን የአባታቸውን ማረፍ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ሐዘን ተሰማቸው፡፡ ወዲያውኑ ካህናቱና ሕዝበ ክርስቲያኑ ተሰብስበው የዲዮስቆሮስ ዋና ጸሓፊ የነበረውን ጢሞቴዎስ የተባለውን አባት በአንድ ድምፅ መርጠው በዲዮስቆሮስ ፋንታ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ተብሎ የእስክን ድርያ 26ኛው ፓትርያርክ ሆኖ እንዲሾም አደረጉ፡፡ ይህ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ የንጉሠ ነገሥቱ የመርቅያን ዋና እንደራሴ አገረ ገዥው በእስክንድርያ አልነበረም፡፡ ገዥው ሲመለስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን አዲስ ፓትርያርክ መርጠው መሾማቸውን በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደ፡፡ አገረገ ዥውም ግብጻውያን ፓትርያርክ የመምረጥ መብት እንዳልነ በራቸው ነገራቸው፡፡ ለማናቸውም እርሱ እስከሚመለስ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው በማለት ምርጫውን እንደማይቀበለው በግልጥ ነገራቸው፡፡ ለእነሱ የተሾመላቸ ውንና መንግሥትም የሚቀበለውን ፕሮቴሪዮስን የግድ መቀበልና ለእርሱ መታዘዝ እንዳለባቸው ነግሮአቸው ሌላ ፓትርያርክ መምረጥ በመንግሥት ላይ እንደማመፅ የሚያስቆጥርና ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ነው በማለት አስጠነቀቃቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የእስክንድርያ ፓትርያርክ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ጳጳሳቱን በሙሉ ጠርተው ሲኖዶስ አደረጉና የኬልቄዶንን ጉባኤና የጉባኤውን ደጋፊዎች እንደገና አወገዟ ቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ዲዮኒስዮስ የሚባል አንድ የመንግሥት ወታደራዊ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከቊስጥንጥንያ ተልኮ መጣ፡፡ የመጣውም የግብጽ ክርስቲያኖች በሙሉ መንግሥት የሾመውን ፕሮቴሪ ዮስን እንዲቀበሉ ለማድረግ ነበር፡፡ ለእርሱም የማይታዘዙትን ከባድ ቅጣት እንዲቀጣቸው ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር የመጣው፡፡ ይህ ባለሥልጣን በመጣ ጊዜ ፓትርያርክ ዳግማዊ ጢሞቴዎስ ከእስክንድርያ ወጥተው የተለያዩ ሀገረ ስብከቶችን በመጐብኘት ላይ ነበሩ፡፡ ፓትርያርኩ በተመለሱ ጊዜ መንበረ ሊቀ ጵጵስናቸው ውጭውም ውስጡም በመንግሥት ቊልፍ ተቈልፎ አገኙት፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ እጅግ ተናደው መንግሥት ወደሾመው ፓትርያርክ ወደ ፕሮቴሪዮስ ሄደው በንጉሡ የተሾመውን ፓትርያርክ ከተደበቀበት አውጥተው ገደሉት፡፡ ይህ ዓመፅ መንግሥትን ስላሳሰበ በሕዝብ ላይ አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ አልተፈለገም፡፡ ሆኖም ንጉሥ መርቅያን ግብጻውያን የመረጡት ፓትርያርክ ጢሞቴዎስና ወንድሙ ተይዘው ዲዮስቆሮስ ታስሮበት በነበረበት በደሴተ ጋግራ እንዲጋዙ አደረገ፡፡ ይህንም ያደረገው የሕዝቡን መንፈስ ለመስበርና ተስፋ ለማስቈረጥ ነበር፡፡ የሕዝቡ መንፈስ ግን ፈጽሞ አልተለወጠም፡፡

የቊስጥንጥንያ መንግሥት ደጋግሞ ፓትርያርክ ቢልክም ግብጻውያን ግን መንግሥት የሚልካቸውን ፈጽሞ አይቀበሉም ነበር፡፡ እስከ ኬልቄዶን ጉባኤ ድረስ በግብጽ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በቅዳሴና በሌሎች የጸሎት አገልግሎት ጊዜ በግሪክኛ ቋንቋ ነበር የሚጠቀሙት፡፡ ከዚህ በኋላ ግን በቅብጥ ቋንቋ መጠቀም ጀመሩ፡፡ ከ451 ዓ.ም. ጀምሮ ማለት ከኬልቄዶን ጉባዔ በኋላ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፈለች፡፡ በአንድ በኩል የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሙሉ ድጋፍ የነበራቸው እኛ መለካውያን ብለን የምንጠራቸው የምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች የሆኑ ሁሉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የምሥራቅ ወይም የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ማለት የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

የፖፕ ልዮን ቀዳማዊ የሃይማኖት መግለጫ ጦማር

የልዮን የሃይማኖት መግለጫ ጦማር (ደብዳቤ) (The Tome of Leo) የሚከተሉት ነጥቦች ነበሩት፡-

1ኛ/በክርስቶስ ውስጥ የመለኮት ባሕርይና የትስብእት ባሕርይ በአንድ አካል አንድ ሆኑ፤ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መለወጥ፡፡

2ኛ/ እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል፡፡ ይህም ማለት መለኮት የመለኮትን ሥራ ይሠራል፤ ትስብእትም የትስብእትን ሥራ ይሠራል፡፡ 

3ኛ/ ‹‹ከመዋሐድ በፊት ሁለት ነበሩ፤ ከተዋሐዱ በኋላ ግን አንድ ባሕርይ ነው ማለት ሞኝነት ነው፤›› የሚል ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡

ከልዮን ጦማር ውስጥ ከዚህ በላይ የገለጥናቸው አንድ አካል ከማለቱ በስተቀር የንስጥሮስን ትምህርት ነው የሚገልጡት፡፡ ሁለቱ ባሕርያት አንድ ሆኑ ሲሉ እንደ ኀዳሪና ማኅደር፣ ጽምረትን እንጂ ተዋሕዶን አይገልጡም፡፡ ተዋሕዶ ግን እንደ ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ባሕርይ የግብር ክልሉን ጠብቆ ይኖራል›› የሚለው በተዋሕዶ የቃል ገንዘብ ለሥጋ፣ የሥጋ ገንዘብ ለቃል መሆኑንና መገናዘቡን መወራረሱንም የሚጻረር ነው፤ ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ይላል ‹‹እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፡፡›› ይህም ማለት ‹‹የቃል ገንዘብ ለሥጋ ሆነ፤ የሥጋም ገንዘብ ለቃል ሆነ፤›› ማለት ነው፡፡  ይህ ፍጹም ተዋሕዶን የሚያመለክት ነው፡፡  ስለዚህ ነው ሥግው ቃል በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው የምንለው፡፡

የልዮንን ጦማርና የኬልቄዶንን ጉባኤ ውሳኔ በመከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ‹‹ክርስቶስ ሁለት ባሕርያት አንድ አካል አለው›› ይላሉ፡፡ በአገላለጽም ሁለቱ ባሕርያት የተዋሐዱት ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለያየትና ያለ መለወጥ ነው ይላሉ፡፡ አንድ ባሕርይ ለማለት የፈሩት ወደ አውጣኪ ትምህርት ይወስደናል ብለው በመፍራት ነው፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሁለቱ ባሕርያት (የሥጋና የመለኮት) ተዋሐዱ ስንል ‹‹ወረሰዮ አሐደ ምስለ መለኮቱ ዘእንበለ ቱስሕት ወኢትድምርት፣ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ›› (ያለ መቀላቀልና ያለ መጨመር፣ ያለ መለየትና ያለ መለወጥ ከመለኮቱ ጋር አንድ አደረገው፤) እንላለን፡፡  አባቶቻችን ያስተማሯት ርትዕት ሃይማኖታችንም ይህች ናት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ

የተወደዳችሁ የማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ተከታታዮች፣ ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል መቅረቡንና በታኅሣሥ ወር ፳፻፱ ዓ.ም በታተመው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፰ ሐመር መጽሔት፣ ከገጽ ፰ – ፲፭ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡