አርዮስ እና መንፈቀ አርዮሳውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያደረሱት ችግር – ክፍል አንድ

በቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል

ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በመጀመሪያው አራት መቶ ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን በብዙ አቅጣጫ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውባት እጅግ ስትሠቃይ ቆይታለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሱት ችግሮችም ከሁለት አቅጣጫዎች የመጡ ነበሩ፤ አንደኛው ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያው ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሡ ችግሮች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያው አብዛኛውን ጊዜ ችግር የተነሣው ከአሕዛብ ነገሥታት ሲሆን፣

፩ኛ/ የሮም መንግሥት ገዢዎችና በክፍላተ ሀገሩ የነበሩት የእነርሱ ወኪሎች እነሱ ያመልኩአቸው የነበሩትን ጣዖታት ክርስቲያኖች ስለማይቀበሉና ጨርሰውም ስለሚያወግዙ፤

፪ኛ/ አሕዛብ ያደርጉት እንደነበረው ክርስቲያኖች ለሮም ነገሥታት የአምልኮ ክብር ስለማይሰጡ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይና በክርስቲያኖች ላይ በየጊዜው ስደት ታውጆ ክርስቲያኖች ሲሠቃዩ ኖረዋል፡፡

፫ኛ/ የጣዖታት ካህናትና የጣዖታት ምስል ሠራተኞች በክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ምክንያት የጣዖት አምልኮ እጅግ ስለቀነሰና በአንዳንድ ቦታዎችም አምልኮ ጣዖት ጨርሶ ስለቀረ ኑሮአቸው በመቃወሱ፣ ከአሕዛብ ነገሥታት ጋር በመወገን በክርስቲያኖች ላይ ልዩ ልዩ ችግሮች ይፈጥሩ ነበር፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ ከውስጥ የተነሡ ችግሮችም እጅግ የበዙና የከፉም ነበሩ፡፡ ከመጀመሪያ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ መለያየትና መከፋፈል ስለታየ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ክፍሎች ትከፋፈል ይሆናል ተብሎ ተፈርቶ ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት ላይ እንደተጠቀሰው ከአይሁድ ወገን ወደ ክርስትና በገቡትና ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና በገቡት ክርስቲያኖች መካከል የታዩት ብዙ ልዩነ ቶች ነበሩ፡፡ ይህ ችግር በ፶፩ ዓ.ም በተደረገው በሐዋርያት ጉባኤ በተሰጠው ውሳኔ መፍትሔ አግኝቶ በመጠኑም ቢሆን ችግሩ ተወግዶ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ በሁለተኛውና በሦስተኛው መቶ ዓመት ላይ ተነሥተው የነበሩት ዶኬቲኮች፣ ግኖስቲኮችና የሰባልዮስና የጳውሎስ ሳምሳጢ ተከታዮች የነበሩ መናፍቃን ተነሥተው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ የከፋ ብጥብጥ ተነሥቶ ነበር፡፡

ይህም ችግር በየክፍላተ ሀገሩ በተጠሩ ሲኖዶሶች (ጉባኤዎች) የቤተ በክርስቲያን አንድነት ተጠብቆ ቆይቷል፡፡ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለምሥጢረ ሥላሴ ዶግማ (ትምህርት) በቤተ ክርስቲያን መምህራን መካከል ብዙ ልዩነቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ የእነጳውሎስ ሳምሳጢና የእነሰባልዮስ የኑፋቄ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያን አህጉራዊ ጉባኤያት (ሲኖዶሶች) ተወግዘው በዚህ ምክንያት የተነሣው ውዝግብ ጥቂት ረገብ ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከግማሽ ምእት ዓመት በኋላ በአርዮስ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ምክንያት ማለት አርዮስ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ብሎ በመነሣቱ ቤተ ክርስቲያን ለብዙ ዓመታት ስትታወክና ስትበጠበጥ ቆይታለች፡፡

፩. የአርዮስ የክሕደት (የኑፋቄ) ትምህርት

አርዮስ ከሦስተኛው ምእት ዓመት አጋማሽ በኋላ በ፪፻፷ ዓ.ም አካባቢ በሰሜን አፍሪካ በሊብያ ነው የተወለደው፡፡ ስሙ እንደሚያመለክተው የትውልድ ዘሩ (የዘር ሐረጉ) የሚዘዘው ከግሪክ ሲሆን፣ የተገኘውም ከክርስቲያን ቤተሰብ ነበር፡፡ በትውልድ ሀገሩ መሠረታዊ ትምህርቱን ከአጠናቀቀ በኋላ እስክንድርያ በሚገኘው ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከፍተኛ ትምህርት ተምሯል፡፡ አርዮስ በእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ወደመካከለኛው ምሥራቅ ሔዶ በአንጾኪያ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብቶ ከፍተኛ የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርትና የነገረ መለኮት ትምህርት ተምሯል፡፡ መምህሩም የታወቀው ሉቅያኖስ ነበር፡፡ ከእስክንድርያ ትምህርት ቤት ይልቅ የአንጾኪያ ትምህርት ቤት ለአርዮስ የክህደት ትምህርት ቅርበት እንደነበረው ብዙ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡

አርዮስ አብዛኛውን የኑፋቄ ትምህርቱን ያገኘው ከሉቅያኖስና ከአንጾኪያ ትምህርት ቤት ነው፡፡ በአንጾኪያ የሚፈልገውን ትምህርት ከጨረሰ በኋላ ወደ እስክንድርያ ተመልሶ ኑሮውን በዚያው አደረገ፡፡ አርዮስ እጅግ ብልህና ዐዋቂ ሰው በመሆኑ ብዙ ሰዎች ያደንቁት ነበር፡፡ አንደበተ ርቱዕም ስለነበረ ተናግሮ ሕዝብን በቀላሉ ማሳመን እንደሚችል ይነገርለታል፡፡ በዚያ በነበረው ዕውቀትና ታላቅ የንግግር ችሎታ የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ዲቁና ሾመው፡፡ የእስክንድርያ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ከከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ሌላ የግሪክ ፍልስፍናን በተለይም የፕላቶንን ፍልስፍና ያስተምሩ ስለነበር፣ አርዮስም ፍልስፍናን በተለይም ሐዲስ ፕላቶኒዝም (Neo-Platonism) የተባለውን ፍልስፍና በሚገባ ተምሯል፡፡

በዚህም የእስክንድርያውን ከፍተኛ ትምህርት ቤት ታላቅ መምህር የነበረውን የአርጌንስን (Origen) የተዘበራረቀ የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት ተከትሎ መጓዝ ጀመረ፡፡ አርጌንስ በምሥጢረ ሥላሴ ትምህርቱ አብን ከወልድ፣ ወልድን ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ በማዕረግና በዕድሜ ያበላልጥ ነበር፡፡ አርጌኒስ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በማበላለጥ አብ ከወልድ እንደሚበልጥ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ከወልድ እንደሚያንስ ያስተምር ነበር፡፡ ስለዚህ የአርዮስ የክህደት ትምህርቱ ዋናው መሠረት አርጌኒስ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ምንም እንኳን አርጌኒስ ስለቅድስት ሥላሴ ቢያስተምርም፣ አርዮስ አጥብቆ የተናገረውና የኑፋቄ ትምህርቱን ያስተማረው ስለአብ እና ስለወልድ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የአርዮስ የክሕደት ትምህርት የሚከተለው ነው፤

፩. አብ ብቻ ዘለዓለማዊ (ዘአልቦ ጥንት ወኢተፍጻሜት) ነው፡፡ ወልድ ግን ዘለዓለማዊ አይደለም፡፡ ነገር ግን እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበር ለማለት ‹‹ሀሎ አመ ኢሀሎ›› (እርሱ ያልነበረበት ጊዜ ነበር) እያለ ያስተምር ጀመር፡፡ ስለዚህ አብ አባት ተብሎ የተጠራውና እንደ አባት የታወቀው ከዘመናት በኋላ እንጂ ከዘመናት በፊት አብ ተብሎ አይጠራም አለ፡፡ ይህንን ያለው ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ብሎ ያልነበረበት ጊዜ ነበረ ለማለት ነበር፡፡

፪. የአርዮስ ዋናው የክሕደት ትምህርቱ ‹‹ወልድ ፍጡር ነው›› (ሎቱ ስብሐት) ማለትም ‹‹ወልድ ከመፈጠሩ በፊት አልነበረም፤›› የሚል ነው፡፡ ‹‹አብወልድን ከምንም ፈጠረና የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን አደረገውለወልድ ጥበብ፣ ቃል የሚባሉ የኃይላት ስሞች አሉት›› እያለ ያስተምር ነበር፡፡ ለክሕደቱ መሠረት የሆነውና ሁልጊዜ ይጠቅሰው የነበረውም፡- ‹‹ትቤ ጥበብ ፈጠረኒ መቅድመ ሉ ተግባሩጥበብ ከፍጥረቱ ሁሉ አስቀድሞ እኔን ፈጠረኝ አለች፤›› ተብሎ በመጽሐፈ ምሳሌ ፰፥፳፪ ላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል ነበር፡፡ በአርዮስ አስተሳሰብ ጥበብ የተባለ ወልድ ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ መጀመሪያ ወልድን ፈጠረ፡፡  ከዚያ በኋላ ወልድ ዓለምንና በውስጡ ያሉትን ሁሉ ፈጠረ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ያለ ወልድ ምንም የተፈጠረ ፍጥረት የለም ብሎ ያስተምርም ነበር፡፡

፫. ከዚህም ሌላ አርዮስ ወልድን ከአብ ሲያሳንስ ‹‹ወልድ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ አይደለም›› ይል ነበር፡፡ በሌላ በኩል ግን ወልድን ከሌሎች ከፍጡራን እጅግ ያስበልጠዋል፡፡ ወልድም በጸጋ የአብ ልጅ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እንደዚሁም ወልድ በምድር ሕይወቱ ታላቅ ትሕትናንና ተጋድሎን በማሳየቱ በባሕርይ ሳይሆን በጸጋ የአምላክነትን ክብር እንዳገኘ አርዮስ በአጽንዖት ይናገር ነበር፡፡

፬. በአርዮስ አመለካከት ወልድ በባሕርዩ ፍጹም ስላልሆነ የአብን መለኮታዊ ባሕርይ ለማየትም ለማወቅም አይችልም ይል ነበር፡፡

፭. አርዮስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ‹‹ወልድ ለአብ የመጀመሪያ ፍጥረቱ እንደሆነ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ለወልድ የመጀመሪያ ፍጥረቱ ነው›› ይል ነበር፡፡

ይህን የአርዮስን ክሕደት የሰማው የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ (ፓትርያርክ) ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አርዮስን አስጠርቶ የሚያስተምረው ትምህርት ሁሉ የተሳሳተ መሆኑን ገልጾለት ከስሕተቱ ተመልሶና ተጸጽቶ ከቅዱሳን አበው ሲተላለፍ በመጣው በኦርቶዶክስ እምነት እንዲጸና መከረው፡፡ አርዮስ ግን ከአባቱ ከተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ የተሰጠውን ምክር ወደ ጎን በመተው የክሕደት ትምህርቱን በሰፊው ማስተማር ቀጠለ፡፡ ይህንን የተመለከተ ያ ደግ አባት አርዮስን አውግዞ ከዲቁና ማዕረጉ ሻረው፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚለው፣ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አርዮስን ያወገዘው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራእይ ተገልጦለት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡

በአንድ ሌሊት በራእይ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወጣት አምሳል እንደ ፀሓይ የሚያበራ ረጅም ነጭ ልብስ (ቀሚስ) ለብሶ ለቅዱስ ጴጥሮስ ይታየዋል፡፡ ልብሱ ለሁለት የተቀደደ ሆኖ ቢያየው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ደንግጦ ጌታን ‹‹መኑ ሰጠጣ ለልብስከልብስህን ማን ቀደደብህ?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ጌታም ‹‹አርዮስ ልብሴን ቀደደብኝ›› ብሎ መለሰለት፡፡ ይኸውም በአባቶች ትርጕም ‹‹አርዮስ ከባሕርይ አባቴ ከአብ ለየኝ (አሳነሰኝ)›› ማለት ነው፡፡ ጌታም አርዮስን ከእንግዲህ ወዲያ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዳይቀበለው አዝዞት ተሰወረ፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ራእዩን ያየው በዲዮቅልጥያኖስ ስደት ጊዜ ተይዞ ለመገደል በእስር ቤት በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ አርዮስም ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚገደል አውቆ ከውግዘቱ ሳይፈታው እንዳይሞት ከውግዘቱ እንዲፈታው አማላጆች ይልክበታል፡፡ ተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ግን አርዮስን ‹‹በሰማይና በምድር የተወገዘ ይሁን!›› በማለት ውግዘቱን አጸናበት፡፡ በዚያኑ ቀን ተማሪዎቹን አርኬላዎስን እና እለእስክንድሮስን አስጠርቶ ያየውን ራእይ በመግለጥ አርዮስን እንዳይቀበሉትና ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዳይኖራቸው አዘዛቸው፡፡

ይቆየን