ንጉሥ ሰሎሞን ወልደ ዳዊት

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፳፫ ቀን በዛሬው ዕለት ንጉሥ ሰሎሞን፣ አባ ኖብ፣ ቅዱስ መርቆሬዎስ፣ ቅዱስ ቶማስ፣ ቅዱስ ፊልጶስና ሌሎችም ቅዱሳን ይታወሳሉ፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በመጽሐፈ ስንክሳር የተመዘገበዉን የንጉሥ ሰሎሞንን ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ንጉሥ ዳዊት ሕግ ተላልፎ ከኦርዮ ሚስት ከቤርሳቤህ ጋር ኀጢአት በሠራ ጊዜ ባሏን በማስገደሉ፤ ከእርሷ ጋርም በደል በመፈጸሙ እግዚአብሔር ነቢዩን ልኮ ከገሠፀው በኋላ ንስሐ ገብቶ መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ እግዚአብሔርም ንስሐዉን ተቀብሎ ኀጢአቱን ይቅር አለው፡፡ በኋላም በእግዚአብሔር ፈቃድ ቤርሳቤህን ሚስቱ አደረጋትና ሰሎሞንን ወለዱ፡፡ ሰሎሞን ሲያድግም በዙፋኑ እንደሚተካው ንጉሥ ዳዊት ለቤርሳቤህ ቃል ገባላት፡፡

ሰሎሞን ፲፪ ዓመት በሞላው ጊዜም አዶንያስ በዳዊት ምትክ ለመንገሥ ዐስቦ በሮጌል ምድር ምንጭ አጠገብ ኤልቲ ዘዘኤልቲ በሚባል ቦታ ላሞችን፣ በጎችንና ፍየሎችን አርዶ የሠራዊት አለቆችን፤ የንጉሥ አሽከሮችንና ካህኑ አብያታርንም ጠርቶ ግብዣ አደረገ፡፡ እነርሱም *አዶንያስ ሺሕ ዓመት ያንግሥህ* እያሉ አወደሱት፡፡

ዳዊትም የአዶንያስን ሥራ ከቤርሳቤህና ከነቢዩ ከናታን በሰማ ጊዜ የዮዳሄን ልጅ ብንያስንና ካህኑ ሳዶቅን፣ ነቢዩ ናታንንም፣ ግራዝማችና ቀኛዝማቹን ኹሉ አስጠርቶ ሰሎሞንን በራሱ በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን እንዲያወርዱትና በዚያም ነቢዩ ናታንና ካህኑ ሳዶቅም ቀብተው እንዲያነግሡት፤ ሰሎሞንም በአባቱ ፈንታ በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ አዘዘ፡፡

ካህኑ ሳዶቅም እንደታዘዘው ሰሎሞንን የንግሥና ቅባትን ቀባው፡፡ ቀርነ መለከቱንም ነፉ፤ ሕዝቡም ኹሉ ሰሎሞንን *ሺሕ ዓመት ያንግሥህ* እያሉ ተከትለዉት ወጡ፡፡ ከበሮም መቱ፤ ታላቅ ደስታም አደረጉ፡፡ ከድምፃቸውም የተነሣ ምድሪቱ ተናወጠች፡፡ ሰሎሞንም በመንግሥት ዙፋን ተቀመጠ፡፡ የንጉሡ አሽከሮችም *እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ይልቅ መልካም ያድርገው፤ ዙፋኑንም ከዙፋንህ ይልቅ ከፍ ከፍ ያድርገው* እያሉ ዳዊትን አመሰገኑት፡፡ ዳዊትም *ዐይኖቼ እያዩ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ለእኔ ለባሪያው ዛሬ የሰጠ የእስራኤል ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን* አለ፡፡

የሚሞትበት ጊዜ በደረሰ ጊዜም ልጁ ሰሎሞንን *እኔ ሰው ኹሉ በሚሔድበት በሞት ጐዳና እሔዳለሁ፡፡ አንተ ግን ጽና፤ ብልህ ሰውም ኹን፡፡ በሕጉ ጸንተህ ትኖር ዘንድ በሙሴ ሕግ የተጻፈዉን የፈጣሪህ የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ጠብቅ* ብሎ አዘዘው፡፡

ከዳዊት ዕረፍትም በኋላ ሰሎሞን በገባዖን ምድር መሥዋዕትን በሠዋ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጾ *እሰጥህ ዘንድ ልብህ ያሰበዉን ለምነኝ* አለው፡፡ ሰሎሞንም *እኔ ባሪያህ መግቢያዬንና መውጫዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝና ለዚህ ለብዙ ወገንህ በእውነት እፈርድ፤ ክፉዉን ከበጎዉ ለይቼ ዐውቅ ዘንድ ዕውቀትን ስጠኝ* ብሎ ለመነው፡፡

እግዚአብሔርም *ብዙ ዘመንንና ባለጠግነትን፤ የጠላቶችህንም ጥፋት አለመንኸኝምና፡፡ ነገር ግን ፍርድ መስማትን ታውቅ ዘንድ ለምነሃልና እንሆ እንዳልህ አደረግሁልህ፡፡ እነሆ ከአንተ አስቀድሞ እንዳልነበረ፤ ከአንተም በኋላ እንዳንተ ያለ እንዳይነሣ አድርጌ ብልህና አስተዋይ ልቡናን፤ ያለመንኸኝን ባለጠግነትንና ክብርንም በዘመንህ ኹሉ ሰጠሁህ* አለው፡፡

ሰሎሞንም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እውነተኛ ሕልም እንዳለመ ዐወቀ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶም በጽዮን በእግዚአብሔር ታቦተ ሕግ አንጻር ባለው መሠዊያ ፊት ቆሞ የሰላም መሥዋዕትን አቀረበ፡፡ ለሰዎቹና ለእሱም ታላቅ ግብዣ አደረገ፡፡

በዚያን ጊዜም ሁለት አመንዝራ ሴቶች ወደ እርሱ መጥተው በአንድ ቤት እንደሚኖሩና በሦስት ቀን ልዩነት ልጆችን እንደ ወለዱ፤ አንደኛዋ ሴትም ልጇን በሌሊት ተጭናው በሞተባት ጊዜ ያልመተዉን የሌላኛዋን ልጅ ወስዳ የሞተዉን ልጅ እንዳስታቀፈቻት በማብራራት የሞተው ልጅ ያንቺ ነው፤ ደኅናው ልጅ የኔ ነው የሚል ክሳቸዉን ለንጉሡ አሰሙ፡፡

ንጉሡም የሁለቱንም ንግግር ካደመጠ በኋላ *ደኅነኛዉን ልጅ በሰይፍ ቈርጣችሁ እኵል አካፍሏቸው* ብሎ አዘዘ፡፡

ያልሞተው ልጅ እናትም *ልጁን አትግደሉት፡፡ ደኅናዉን ለእርሷ ስጧት ስትል፤ ሁለተኛዋ ሴት ግን ቈርጣችሁ አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርሷም አይሁን* አለች፡፡

ንጉሡም *ልጁን አትግደሉት* ላለችው ሴት ደኅነኛዉን ሕፃን ስጧት፤ እርሷ እናቱ ናትና ብሎ ፈረደ፡፡

እስራኤልም ኹሉ ቅን ፍርድ ይፈርድ ዘንድ የእግዚአብሔር ጥበቡ በእርሱ ላይ እንዳለ አይተዋልና ንጉሡን ፈሩት፡፡

ከዚህ በኋላ እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በ፬፻፹ኛው፤ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በ፬ኛው ዓመት፣ በ፪ኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ጀምሮ በ፲፩ኛው ዘመነ መንግሥቱ፣ በ፰ኛው ወር ሠርቶ በ፯ ዓመታት ውስጥ ፈጸመው፡፡ የራሱን ቤትም በ፲፫ ዓመት ሠርቶ ጨረሰ፡፡

ሰሎሞን ቤተ መቅደሱንና የራሱን ቤት ከፈጸመ በኋላ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ የእስራኤልን ሽማግሎች፣ የነገድና የአባቶቻቸዉን ቤት አለቆች ኹሉ በ፯ኛው ወር (በጥቅምት) በኢየሩሳሌም ሰበሰባቸው፡፡ ካህናቱም ታቦቷን፣ የምስክሩን ድንኳንና ንዋያተ ቅድሳቱን ኹሉ ተሸክመው ንጉሡና ሕዝቡም በታቦቷ ፊት ሥፍር ቍጥር የሌላቸዉን በጎችንና ላሞችን እየሠዉ ታቦቷን ከኪሩቤል ክንፎች በታች በቤቱ ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አገቧት፡፡

ከዚህ በኋላ ካህናቱ ከቤተ መቅደስ በወጡ ጊዜ የእግዚአብሔር ብርሃን ቤተ መቅደሱን ሞላው፡፡ ካህናቱም ሥራቸዉን መሥራትና ከብርሃኑ ፊቱ መቆም ተሳናቸው፡፡ ያንጊዜም ሰሎሞን *እግዚአብሔር በደመና ውስጥ እኖራለሁ ብሏል፤ እኔም ለዘለዓለም የምትኖርበት ማደሪያህ ቤተ መቅደሱን በእውነት ሠራሁልህ* አለ፡፡ ከዚያም ፊቱን ወደ መሠዊያው መልሶ፣ እጆቹን ዘርግቶ፣ በጕልበቱ ተንበርክኮ ሰገደና ወደ እግዚአብሔር ጸሎት አደረሰ፤ ሕዝቡንም ኹሉ መረቃቸው፡፡

ጸሎቱን ከፈጸመ በኋላም ከመሠዊያው ፊት ተነሥቶ ቆመና *ለወገኖቹ ለእስራኤል ዕረፍትን የሰጠ እግዚአብሔር ይመስገን* እያለ በታላቅ ቃል የእስራኤልን ማኅበር መረቃቸው፡፡ ከዚያም ንጉሡና ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርበው ቅዳሴ ቤቱን አከበሩ፡፡ ሰሎሞን ስለ ሰላም ለእግዚአብሔር የሠዋቸው በጎችም ፳፪ ሺሕ ነበሩ፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጾ *የለመንኸኝን ልመናህንና ጸሎትህን ሰማሁ፤ እንደ ልመናህም ኹሉ አደረግሁልህ፡፡ ስሜ በዚያ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖር ዘንድ የሠራኸዉን ቤተ መቅደስ አከበርሁት፡፡ ልቡናዬም፣ ዐይኖቼም በዘመኑ ኹሉ በዚያ ጸንተው ይኖራሉ* አለው፡፡

እግዚአብሔር ብዙ ጥበብና ጸጋን የሰጠው ይህ ታላቅ ንጉሥ ለዐርባ ዓመት እስራኤልን በቅንነት አስተዳድሯል፡፡ ከንግሥናው በተጨማሪም ለነፍስም ለሥጋም የሚጠቅሙ፣ ትንቢትንና ትምህርትን የያዙ የጥበብና የመዝሙር መጻሕፍትንም ጽፏል፤ እነዚህም፡- መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን፣ መጽሐፈ መክብብ፣ መጽሐፈ ምሳሌ፣ መጽሐፈ ተግሣፅና መጽሐፈ ጥበብ ናቸው፡፡

ንጉሥ ሰሎሞን ከመንገሡ በፊት ፲፪፤ ከንግሥናው በኋላ ፵፤ በድምሩ ፶፪ ዓመታት በሕይወተ ሥጋ ከኖረ በኋላ በዛሬው ዕለት ሰኔ ፳፫ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፏል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን፡፡ የአባቶቻችን በረከት ይደርብን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፫ ቀን፡፡